ዶ/ር ትዝታ በፌዴራል ከፍተኛው ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ጉዳዩዋን ለመከታተል በችሎት ታድማለች፡፡ በሥር ፍርድ ቤት በቤቷ ላይ ያለአግባብ ፍርድ ተሰጥቷል ብላ ስላመነች የተማረ ጠበቃ የይግባኝ አቤቱታ ጽፎላት ጉዳይዋን በራሷ ትከታተላለች፡፡ እንደ እርሷ አስተሳሰብ ጉዳይዋን ከእርሷ ይልቅ የሚረዳው የለም በሚል ከዳኛ ፊት ቀርባ ለማስረዳት ጓጉታለች፡፡ በዛሬው ቀጠሮ ይህ ሐሳቧ እንደሚሳካላት በውጭ የሚያማክራት ጠበቃ ነግሯታል፡፡
መዝገቡ ለዛሬ በቀጠሮ ያደረው ቀደም ሲል ረዳት ዳኛ ፊት ቀርባ ስለጉዳዩ ካሳሰበች በኋላ የይግባኝ አቤቱታውን ለመስማት በሚል ነው፡፡ ችሎት ተቀምጣ የምትሰማው የዳኛው ድምፅ ‹‹አያስቀርብም ብለናል!›› ‹‹አያስቀርብም›› የሚሉ አጭርና መርዶ ነጋሪ ቃላት ናቸው፡፡ የእሷ ጉዳይ ገና ያልተሰማ በመሆኑ እንዲህ ያለውን ፍርድ ዛሬ እንደማትሰማው አምናለች፡፡ የሕግ አማካሪዋም ልቧን አጽንቶላታል፡፡ ተራዬ እስኪደርስ በሥር ፍርድ ቤት ተፈጸመ የተባለውን ስህተት ለማስረዳት ከማስታወሻዬ ላይ ነጥቦቹን ተራ በተራ በወፍ በረር ልቃን ብላ ጀምራለች፡፡ ከተመሰጠችበት ንባብ ያናጠባት በዳኛው የተጠራው ስሟ ነበር፡፡
‹‹ዶ/ር ትዝታ በረደድ›› ብለው ዳኛው ሲጠሩ ከመቅጽበት ከዳኛው ፊት ተገተረች፡፡ ዳኛው ማንነቷን ካረጋገጡ በኋላ ‹‹ይግባኙ አያስቀርብም ብለናል፤›› ሲሏት በደንብ አልሰማቻቸውም፡፡ ‹‹እህ እህ ምን አሉ?›› ብላ ስትጠይቅ ‹‹አያስቀርብም ተዘግቷል፣ ጨርሰናል፤›› አሏት፡፡ ‹‹ይግባኜ አልተሰማም፣ ረዳቱ ነው ያናገረኝ፣ እርስዎን ዛሬ ማየቴ ነው… ለውሳኔ አልተቀጠረም… መዝገቡ የሌላ እንዳይሆን …›› ብዙ ለማለት ብታስብም ባህላዊው የፍርድ ቤት ፍርኃት አላስችላት አለ፡፡ ከእሷ በፊት የተስተናገዱት አቀርቅረው እንደወጡ እሷም በቁሟ አቀረቀረች፡፡ ከዳኛው ፊት እንደቆመች ዳኛው ሌላ ባለጉዳይ ማስተናገድ ቀጠሉ፡፡
በዚህ መነሻ ነበር ከችሎት ስትወጣ ጨዋታ የጀመርነው፡፡ ‹‹አያስቀርብም›› ማለት ምንድነው? በምን ምክንያት ነው? የማያስቀርበውስ እንዴት ነው? ዳኛው ይግባኜን አይሰሙም እንዴ? የሚሉትንና እኔ መልስ ልሰጣት የማልችላቸውን ጥያቄዎች ያዥጎደጎደችው፡፡ ሕጉ የሚለውን፣ ዳኛው ሊፈጽሙት ይገባ የነበረውን ሥርዓት ብነግራት ይባሱኑ ትበሳጫለች በማለት በቀልድ ነገሯን ለማጣጣል ጥረት አደረግኩ፡፡
እናንተ ሐኪሞችስ በማይነበብ ጽሑፍ ለበሽታህ መድኃኒቱ ይሄ ነው ብላችሁ ብጣቂ ወረቀት ትሰጡ የለም እንዴ? አልኳት፡፡ ዶ/ር ትዝታም መለሰች ‹‹እንዴ እኛ እኮ ደማችሁን ለክተን፣ ሙቀታችሁን አይተን፣ የሚሰማችሁን በዝርዝር ሰምተን፣ ደምና ሰገራ፣ ኤክስሬይና ራጅ ተመልክተን ነው፤ ከጻፍነውም በኋላ የመድሃኒት ባለሙያ የማይነበበውን አንብቦ ተገቢውን መድሃኒት ይሰጣችኋል አለች›› በልቤ ‹‹ልክ ነሽ›› አልኩ፡፡ እንዲያውም የመደመጥ መብት በሐኪሞች የተሻለ ይተገበራል፡፡ በእኛ አገር ሐኪሞች ከዳኞች ይልቅ ደንበኛቸውን ይሰማሉ፣ ጊዜ ይሰጣሉ፣ ሰፊ ምርመራም ያከናውናሉ አልኩ፡፡ እርሷንም እንድትጽናና ነግሬያት የነጋሪት ጋዜጣ ወደ መግዣው ሱቅ በመሔድ ከእሷና ከሐሳቧ ሸሸሁ፡፡
የ‹‹ያስቀርባል - አያስቀርብም›› ነገር ግን የሕግ ዕውቀቱ የሌላቸውን ቀርቶ ለሕግ ባለሙያዎችም በአግባቡ የሚገባ ወይም የተረዳ አይመስለኝም፡፡ ፀሐፊው በፍርድ ቤቶች አካባቢ ከገጠሙት ጉዳዮችና በችሎት ከሚያስተውለው ተግባር አንፃር ‘አያስቀርብም እንቆቅልሽ፣ ያስቀርባል ሎተሪ’ እየሆነ መምጣቱን አስተውሏል፡፡ የ‹‹አያስቀርብም›› ልማድ በሰበር ችሎት ሳይቀር የሚስተዋል ቢሆንም፣ በዚህ ጽሑፍ በከፍተኛ ፍርድ ቤቶች የታዘብኩትን አጠር አድርጌ ለመቃኘት እሞክራለሁ፡፡ ተሞክሮው በጎ የተሠራውን፣ ጊዜ ወስዶ መዝገብ መርምሮ በምክንያት ወይም ያለምክንያት አያስቀርብም የሚሉትን ተሞክሮዎች ስለማይመለከት የአሠራር ክፍተት ባለባቸው ላይ ማተኮሩ ተገቢ ሳይሆን አይቀርም፡፡ አያስቀርብም በሕጉ ያለውን ቦታ፣ ከዳኛው የሚጠበቀውን ሥርዓት፣ በተግባር የሚታዩ ክፍተቶችን፣ የክፍተቶቹን አንድምታ በመቃኘት የሚስተካከልበትን መፍትሔ ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡
ስለ ይግባኝ መብትነት