መግቢያ
የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ከመጣበት /ከተወለደበት/ እለት አንስቶ እስከ ሕይወቱ ፍፃሜ ድረስ በዚች ምድር ላይ የሚኖረው ለተወሰነ ጊዜ ነው፡፡ የሰው ልጅ በዚች ምድር ላይ ዘላለማዊ አይደለም፡፡ ለያንዳንዱ ሰው በፈጣሪው የተጠው የምድር ቆይታ ጊዜ አለው፡፡ ይህ የምድር ላይ ቆይታው በአይቀሪው ሞት ይጠናቀቃል፡፡ የሰው ልጅ ወደዚች ምድር ከተቀላቀለበት እለት አንስቶ እስከ እለተ ሞቱ ድረስ የሕግ መብት አለው፡፡
በዚች ምድር ላይ በቆይታው ጊዜው የሰው ልጅ የተለያዩ መብቶች እና ግዴታወች አሉ፡፡ ለምሳሌ ያህል ንብረት የማፍራት መብት የሚጠቀስ ነው፡፡ በእለት ተእለት ኑሮው የተለያዩ ሥራዎችን እየሠራ የራሱን ብሎም የቤተሰቡን ጉርስ ለመሸፈን ጥረት ያደርጋል፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ የራሱ የሆነ ጥሪት ማፍራቱ አይቀሬ ነው፡፡ ይህን ጥሪት በምድር ላይ እስካለ ብቻ ነው የሚጠቀምበት፡፡ ሕይወቱ ካለፈች በኋላ ይህን ያፈራውን ንብረት በሕይወት ያሉ የሱ የቅርብ ሰዎች ናቸው የሚጠቀሙበት፡፡ እነዚህ በሕይወት ያሉ የሟችን ንብረት ሕይወቱ ካለፈ እለት በኋላ የሚጠቀሙበት በውርስ በመውረስ ነው፡፡ ውርስ የአንድ የሞተን ሰው ኃብትና ንብረት እንዲሁም ሊተላለፉ የሚችሉ መብትና ግዴታዎች ለአንድ ወይም ከአንድ በላይ ለሆኑ በሕይወት ላሉ ሰዎች የሚላለፋበት ሕጋዊ ሰርዓት ነው፡፡ ይህ ሰርዓት ደግሞ ሊያስከትል የሚችለው ሕጋዊ ውጤት ስለሚኖረው ራሱን የቻለ ሕግ ሊኖረው ይገባል፡፡
የሟችን ንብረት የሚወርሱት እንማንናቸው፣ ወራሽነትን የሚያሳጡ ነገሮች ምንድን ናቸው፣ ንብረቱ እንዴት ይከፋፈላል፣ ሟች ኑዛዜ ከተወ ኑዛዜው ሕጋዊ ውጤት እንዲኖረው ምን ምን መሟላት አለበት እና የመሳሰሉትን ነገሮች የሚመራው የሕግ ክፍል የወርስ ሕግ ይባላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ የሃገራችን የውርስ መሠረታዊ ጉዳዩች እንቃኛለን፡፡