Font size: +
29 minutes reading time (5772 words)

ፍቺ ከፍርድ ቤት ውጭ - የሰበር ሰሚ ችሎት እና የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔዎች አጭር ዳሰሳ

ለዚህ ጽሑፍ መነሻ የሆነው ጸሐፊው በሥራ ምክንያት በሚያያቸው መዝገቦች ስር ሲገጥሙት የነበሩ ክርክሮች እንዲሁም በተለያዩ አጋጣሚዎች ከሥራ ባልደረቦቹ ጋር ጋብቻ ከፍርድ ቤት ውሳኔ ውጭ በሁኔታዎች ስለሚፈርስበት አግባብ ያደረጋቸው ውይይቶች ሲሆኑ በዋነኛነት ግን የቅርብ ምክንያቱ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ የሰጠው ውሳኔ ነው። በፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ሥር እንደተመለከተው ጋብቻ የሚፈርስባቸው ብቸኛ ሦስት ምክንያቶች ሞት ወይም የመጥፋት ውሳኔ፤ ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች አንዱ በመጣሱ ምክንያት ጋብቻው እንዲፈርስ ሲወሰን እንዲሁም ፍቺ መሆናቸው የተመለከተ ሲሆን በአንቀጽ 117 ሥር እንደተመለከተው ደግሞ ጋብቻን በፍቺ ለማፍረስ ሥልጣን የተሰጠው ለፍርድ ቤቶች ብቻ ነው። 

ፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመ.ቁ. 14290 መጋቢት 25 ቀን 1999 ዓ.ም (ያልታተመ)፤ በቅጽ 5 በመ.ቁ. 31891 ሚያዚያ 14 ቀን 2000 ዓ.ም. እንዲሁም በቅጽ 19 በመ.ቁ. 102662 የካቲት 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በሰጣቸው ውሳኔዎች ጋብቻ በፍርድ ቤት ውሳኔ ያልፈረሰ ቢሆንም የተጋቢዎቹ ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ መኖር (በዚህም ጊዜ ሌላ ትዳር መፈጸም) ጋብቻውን በሁኔታ ፈራሽ እንደሚያደርገው ወስኗል። በዚህ የፍርድ ቤቱ አቋም ሕጋዊነት እና ምክንያታዊነት ላይ በብዛት የሚነሱ ክርክሮች ቢኖሩም ጉዳዩ ዋነኛ መነጋገሪያ የሆነው ግን የፌደሬሽን ምክር ቤት በአመልካች ወ/ሮ ቀለሟ ተፈራ እና በተጠሪ አቶ ፍሰሃ ደምሴ መካከል በነበረው ክርክር ላይ በሰጠው ውሳኔ ነው።

በእነዚህ የሰበር ችሎቱ ውሳኔዎች መነሻነት ያቀረቡት የፍቺ አቤቱታ ጋብቻው በሁኔታዎች ፈራሽ በመሆኑ የሚሰጥ የፍቺ ውሳኔ የለም በሚል የተወሰነባቸው እና በመጨረሻም ለፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ያቀረቡት አቤቱታ አያስቀርብም በሚል ውድቅ የተደረገባቸው ወ/ሮ ቀለሟ ተፈራ ውሳኔው ከሕገ-መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ነው በሚል ትርጉም እንዲሰጣቸው ቅሬታቸውን ለፌደሬሽን ምክር ቤት አቅርበዋል። ምክር ቤቱም የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ በጉዳዩ ላይ የውሳኔ ሃሳብ እንዲያቀርብለት ካደረገ በኋላ ምክር ቤቱ መስከረም 27 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጠው ውሳኔ የሰበር ችሎቱን ውሳኔ ሽሮታል። ምንም እንኳን ውሳኔው በግለሰቧ አቤቱታ አቅራቢነት ታይቶ ጉዳዩ ለሰበር ችሎት አያስቀርብም በሚል የተሰጠውን ውሳኔ በቀጥታ የሚመለከት ቢሆንም ምክር ቤቱ ውድቅ ያደረገው የውሳኔው ዋና ጉዳይ የሆነውን ጋብቻ በሁኔታዎች ስለሚፈርስበት አግባብ በመሆኑ ሶስቱም የሰበር ችሎት ውሳኔዎች የተሻሩ ሲሆን ይህ የምክር ቤቱ ውሳኔ በአዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 11 እና 56 መሠረት በሀገሪቱ ያሉትን ማናቸውንም አካላት ፍርድ ቤቶችንም ጨምሮ የሚያስገድድ ነው።

በዚህ ጽሁፍ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ መነሻ ምክንያት እንዲሁም የሕግና የአመክንዬ መሠረት በአንድ በኩል እንዲሁም የምክር ቤቱ ውሳኔ ምክንያታዊነት እና ሕጋዊነት በሌላ በኩል በዝርዝር ለማየት ጥረት ተደርጓል። በመጨረሻም የሰበር ውሳኔዎቹ እና የምክር ቤቱ ውሳኔ አስገዳጅነት ያልተቀየረ በመሆኑ ተግባራዊ መፍትሄ ሊሆኑ የሚችሉ አማራጮች ተዳስሰዋል። የጽሁፍ አጭር ሃሳብ የሰበር ችሎቱ የሰጣቸው ውሳኔዎች ከፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ ውጭ በመሆናቸው እንዲሁም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የሰጠውም ውሳኔ በሌለው ስልጣን የተሰጠ በመሆኑ ሁለቱም የየራሳቸው ጉድለት አለባቸው የሚል ነው። በመጨረሻም በዚህ ጽሁፍ ሕጉን በማሻሻል ሊሰጥ የሚችለው መፍትሄ እንዲሁም ሕጉን ከማሻሻል በመለስ ያሉ ተግባራዊ መፍትሄዎች ለመጠቆም ጥረት ተደርጓል።


1. ጋብቻ በሁኔታዎች ስለ መፍረስ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ መነሻ ምክንያት


በፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጋብቻ ከፍርድ ውሳኔ ውጭ በሁኔታዎች ሊፈርስ እንደሚችል በቅድሚያ ተነስቶ የነበረው በመ.ቁ. 14290 መጋቢት 25 ቀን 1999 ዓ.ም. በተሰጠ ውሳኔ ነው። በመዝገቡ አመልካች የሟች አቶ በየነ መረጬ ሚስት መሆናቸውን ገልጸው ሲከራከሩ ተጠሪዎች በበኩላቸው አመልካች ሚስት አለመሆናቸውን እና ሚስት ናቸው ቢባል እንኳን ከሟች ጋር ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የቆዩ እና ሌላ ባል አግብተው ልጅ የወለዱ በመሆናቸው ግንኙነታቸው ተቋርጧል በማለት እንደተከራከሩ መዝገቡ ያስረዳል። የግራቀኙ ክርክር ይህ ሲሆን በመዝገቡ የነበረው አካራካሪ ጉዳይ አመልካቿ የሟች ሚስት ናቸው ወይስ አይደሉም እንዲሁም ናቸው ቢባል ግንኙነታቸው ከሟች ህይወት ማለፍ በፊት ተቋርጦ ነበር ወይስ አልነበረም የሚል ነው።


ለዚህ አከራካሪ ጉዳይ መልስ ለመስጠት ሁለት ነጥቦችን ማጣራት ተገቢ ሲሆን እነሱም የፍሬ ነገር እና የሕግ ጉዳዮች ናቸው። የፍሬ ነገር ጉዳዩ በሟች እና አመልካች መካከል የነበረው የጋብቻ ግንኙነት ሟች ከማረፋቸው በፊት ተቋርጦ ነበር ወይስ አልነበረም የሚል ሲሆን የሕግ ጉዳዩ ደግሞ ግንኙነታቸው ተቋርጧል ቢባል ሕጉ ጋብቻን ለማፍረስ ምክንያት አድርጎ በአንቀጽ 75 ስር ካስቀመጣቸው ሶስት ምክንያቶች ውስጥ በየትኛው አግባብ ጋብቻው እንዲፈርስ ሊወሰን ይገባል የሚል ይሆናል። የፍሬ ነገሩ ጉዳይ አላስፈላጊ ነው ወይም ቅድሚያ የሕጉ መነሻ ሳይታወቅ ፍሬ ነገሩን ማጣራት ተገቢ ነው አይደለም የሚለው ክርክር እንደተጠበ ሆኖ በጉዳዩ ላይ ምሉዕ ውሳኔ ለመስጠት እና ለበታች ፍርድ ቤቶች በአስገዳጅነት ስልጣኑ ብቻ ሳይሆን በምክንያታዊነቱም አስገዳጅ ውሳኔ ከመስጠት አንጻር ሁለቱም ጉዳዮች መነሳት እና መመለስ ያለባቸው ናቸው።


በመ.ቁ. 14290 ስር የሰበር ችሎቱ በዝርዝር የተመለከተው የፍሬ ጉዳዩን ብቻ ነው በሚያስብል ደረጃ ሐተታው ግንኙነታቸው ሟች ከማረፋቸው በፊት ተቋርጦ ነበር አልነበረም የሚለውን በማጣራት ላይ ትኩረቱን ያደረገ ነው። የሰበር ችሎቱ በውሳኔ በአብዛኛው የተነተነው ግንኙነቱ መቼ ተቋረጠ እና ይህ ጉዳይ በምን ማስረጃ ተረጋገጠ የሚለው የፍሬ ነገር ክርክር ላይ ትችት በማድረግ ነው። እዚህ ላይ በዋነኛነት የሰበር ሰሚ ችሎቱ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 80-3-ሀ፣ በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 454/97 ስር መሠረታዊ የሕግ ስህተቶችን ለመመልከት ስልጣን የተሰጠው ሲሆን ችሎቱ የፍሬ ጉዳይ ክርክሮችን አከራክሮ ለመወሰን ስልጣን በሕጉም አልተሰጠውም። ከሕጉም ባለፈ ምንም እንኳን የዚህ ጽሁፍ ዓላማ ባይሆንም በዳበረው የሕግ ፍልስፍና እና የዳበረ የሕግ ስርአት ባላቸው ሃገራትም የሰበር ችሎቶች በፍሬ ጉዳዮች መነሻነት የሚቀርብላቸውን ቅሬታ ለመመልከት ሥልጣን የላቸውም። ከዚህ በመነሳት ችሎቱ ግንኙነቱ መቼ እና እንዴት ተቋረጠ ለሚለው ጉዳይ የሰጠው ሐተታ ከስልጣኑ ውጭ እንደሆነ ግልጽ ነው።


በሌላ በኩል የሰበር ችሎቱ በመ.ቁ 102662 (በቅጽ 19 የታተመ) በሰጠው ውሳኔ በመዝገቡ አመልካች የነበሩት ግለሰብ ግንኙነቱ አልተቋረጠም በሚል ያቀረቡትን የፍሬ ጉዳይ ክርክር ለመመልከት ስልጣን የለኝም በሚል ውድቅ አድርጎታል። በመ.ቁ. 14290 ስር ስለ ፍሬ ጉዳዩ ትኩረት ያደረገው ችሎት በዚህኛው መዝገብ አቋሙን ቀይሮ ስልጣን የለኝም ማለቱ የችሎቱ አቋም አገላለጽ እርስ በእርሱ የሚጣረስ እንደሆነ ያሳያል። ምክንያቱም የሰበር ሰሚ ችሎት የፍሬ ነገር ክርክሮችን ለመመልከት ከጅምሩም ቢሆን ሥልጣን የሌለው በመሆኑና ከዚህ ባለፈ ፍሬ ነገሩን ለመመርመር በምን አግባብ እንደተፈለገ ባለመገለጹ ነው።


ከፍሬ ነገሩ ሐተታ በላይ አከራካሪው ጉዳይ ሕጉ ጋብቻን ለማፍረስ ምክንያት አድርጎ በአንቀጽ 75 ስር ካስቀመጣቸው ሶስት መንገዶች ውስጥ በየትኛው አግባብ ጋብቻው ሊፈርስ ይገባል የሚለው ነው። ነገር ግን በሚገርም ሁኔታ ችሎቱ በዚህ ላይ የሰጣቸው ትንተናዎች በጣም ጥቂት ከመሆናቸውም በላይ ጥያቄ እንጂ የሕግ ትችት አይታይባቸውም። በውሳኔው በዚህ ላይ ለተነሳው ጉዳይ ችሎቱ “ግንኙነቱ በሕጋዊ መንገድ መቋረጡ እስካልተረጋገጠ ድረስ ግንኙነቱ ተቋርጧል ማለት አይቻልም የሚል ጥያቄ መነሳቱ አይቀርም” … “በእውነታ ደረጃ ተለያዩ እንጂ በሕጋዊ መንገድ ስላልተለያዩ ግንኙነቱ ሕጋዊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል ለማለትም አስቸጋሪ ይሆናል" እንዲሁም” 1ኛ መልስ ሰጭ ከሟች አቶ በየነ መረጭ ጋር ተለያይተው በነበረበት ጊዜ ሌላ ትዳር መስርተው የመኖራቸው ዕውነታ ከአቶ በየነ መረጭ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በሕጋዊ መንገድ ተቋርጦ ነበር ለሚለው የጎላ ግምት በቂ መነሻ ሆኖ አግኝተነዋል” የሚሉ እና መሰል አገላለጾችን ሲጠቀም ይታያል። (ሰረዝ የተጨመረ)


በመሠረቱ ጋብቻ በሕጋዊ መንገድ ተቋርጧል ሊባል የሚችለው በሕግ አግባብ ለተቋቋመ ፍርድ ቤት ጋብቻ ይፍረስልኝ የሚል አቤቱታ ቀርቦ በአንቀጽ 75 ስር ከተመለከቱት ምክንያቶች ውስጥ ጋብቻው እንዲፈርስ ውሳኔ ሲያገኝ ወይም ከተጋቢዎቹ አንዱ ሕይወቱ በማለፉ ወይም መጥፋቱ በፍርድ ቤት ሲታወጅ ብቻ ነው። ጋብቻው የሚፈርሰው በሕጋዊ መንገድ ነው ማለት በሕጉ በግልጽ በተመለከተው መንገድ ወይም አግባብ ብቻ ነው ማለት ስለመሆኑ ለችሎቱ ማስረዳት ለቀባሪው ማርዳት ይሆናል። ችሎቱ በአንድ በኩል በእውነታ መለያየት በሕግ መለያየትን እንደማያስከትል በግልጽ ያመለከተ ሲሆን በእውነታው ዓለም የሚከናወኑ ተግባራት ሕጋዊ ለመባል ሕጉ ባስቀመጠው መንገድ እና ቅደም ተከተል መፈጸም እንደሚኖርባቸው መግለፁ ትክክል ነው። ነገር ግን ችሎቱ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 80-3-ሀ፣በአዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 10 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 454/97 ሥር ከተሰጠው ስልጣን ውጭ ማስረጃን በመመዘን በደረሰበት ድምዳሜ በሟች እና አመልካቿ መካከል የነበረው የጋብቻ ግንኙነት ሟች ከማረፋቸው በፊት በነበሩት 13 ዓመታት ጀምሮ እንደተቋረጠ አረጋግጧል። በዚህም ፍሬ ነገር በመነሳት በሕጉ ስር ለ13 ዓመታትም ሆነ ከዚህ በላይ ግንኙነት ማቋረጥ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ጋብቻን በሁኔታዎች ለማፍረስ እንደሚያበቃ ለመወሰን መነሻ የሆነው ሕግ ወይም የሕግ ፍልስፍና ሳያነሳ ግንኙነቱ በህጋዊ መንገድ ተቋርጧል ለማለት "1ኛ መልስ ሰጭ ከሟች አቶ በየነ መረጭ ጋር ተለያይተው በነበረበት ጊዜ ሌላ ትዳር መስርተው የመኖራቸው ዕውነታ ከአቶ በየነ መረጬ ጋር የነበራቸው ግንኙነት በሕጋዊ መንገድ ተቋርጦ ነበር ለሚለው የጎላ ግምት በቂ መነሻ ሆኖ አግኝተነዋል"ሲል አትቷል። (ሰረዝ የተጨመረ)


ከዚህ በላይ አስገራሚው ነገር ችሎቱ ግንኙነት በሕጋዊ መንገድ የሚቋረጥበት ሁኔታ የሕግ ወይም የፍሬ ነገር ግምትም እንደሆነ ለመጥቀስ ጥረት ማድረጉ ነው። ጋብቻ ከሶስቱ መንገዶች ውጭ የሚፈረስ ስለመሆኑ በየትኛውም የሕጉ ክፍል በራሱ ወይም የሕግ ወይም የፍሬ ነገር ግምት ነው ተብሎ ያልተመለከተ ሲሆን ከዚህ በፊት ችሎቱ በጉዳዩ ላይ የሰጣቸው ውሳኔዎች አለመኖራቸው እየታወቀ ይህን ያህል ክብደት ለያዘ ጉዳይ አንድም ዐረፍተ-ነገር ትንተና ሳይሰጡ ማለፍ ትክክል አይደለም። ቀጥለውም በተወሰኑት ሁለት መዝገቦች ስር ችሎቱይህንን ውሳኔ ጠቅሶ ከማለፍ ውጭ በጉዳዩ ላይ ዘርዘር ያለ ትንታኔ አልተሰጠበትም።


2. የሰበር ችሎቱ ውሳኔዎች አመክንዮ


የሰበር ችሎቱ ውሳኔዎችን ምክንያት ከማየታችን በፊት የውሳኔው ጭብጥ ላይ የተወሰነ ማብራሪያ መስጠቱ ተገቢ ነው። ጸሀፊው ያነጋገራቸው አንዳንድ የሕግ ባለሙያዎች የሰበር ችሎቱ ውሳኔ የሚያጠነጥነው ፍቺ መቼ ተፈጽሟል በሚለው የማስረጃ ጉዳይ ላይ እንደሆነ እና ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ፍቺ ይፈጸማል የሚል አለመሆኑን ሃሳባቸውን ገልጸዋል። ነገር ግን በሁለት ምክንያቶች ጉዳዩ የማስረጃ ጉዳይ አለመሆኑን መገንዘብ ይቻላል። አንደኛው ሕጉ በየትኛውም ቦታ ተለያይቶ መኖር ፍቺ እንደተፈጸመ ያስቆጥራል ባለማለቱ ወይም ተለያይቶ መኖር ጋብቻ ከሚፈርስባቸው መንገዶች ውስጥ ባለማስቀመጡ ጉዳዩ የሕግ ድጋፍ የሌለው በመሆኑ ነው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ለፍቺ የፍርድ ቤት ውሳኔ አስፈላጊ እና አስገዳጅ በመሆኑ ተጋቢዎቹ ፍርድ ቤት አለመምጣታቸው ከተረጋገጠ መቼ ተለያይተዋል የሚለው ክርክር ፋይዳ ቢስ በመሆኑ ነው። ከዚህም ባለፈ ጸሀፊው ያነጋገራቸው የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ዳኛ የሰበር ችሎቱ የሰጣቸው እነዚህ ውሳኔዎች ትርጉም ወይም ሃሳብ ከማስረጃ ወይም ፍቺ ከተፈጸመበት ጊዜ አንጻር የተያያዘ ሳይሆን ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ በመኖር ስለሚፈጸም ፍቺ መሆኑን ገልጸዋል።


ከፍ ሲል እንደተመለከተው የፍቺ ውሳኔ ለመስጠት ሥልጣን የተሰጠው ለፍርድ ቤቶች ብቻ ነው። እዚህ ላይ በግልጽ ሊታይ የሚገባው የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቀድሞ ከነበረው የፍትሐ ብሔር ሕግ እንዲሁም ባህላዊ ደንቦች አንጻር በጉዳዩ ላይ ለየት ያለ አቋም መያዙ እምብዛም ለባህል ሥርዓቶች ቅድሚያ የሰጠ እንዳልሆነ አከራካሪ አይደለም። እንዲያውም አንዳንድ ጻሀፊያን በፍቅር፣መተሳሰብ፣ መቻቻል እንዲሁም በታላላቆች ጥረት ሊፈቱ የሚችሉ አብዛኛዎቹ ጋብቻ ነክ ክርክሮች ወደ ፍርድ ቤቶች እንዲመጡ በማድረጉ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ተጋቢዎቹን ለበለጠ ጠብ የሚጋብዝ፣ ለሶስተኛ ወገኖች ጣልቃ ገብነት የሚዳርግ፣ የተጋቢዎቹን ምስጢር የሚያወጣ እንዲሁም ለወደፊቱ መስማማትን የማይታሰብ የሚያደርግ እንደሆነ በአጽንኦት ይከራከራሉ። ነገር ግን መታወቅ ያለበት ጉዳይ እነዚህ ሐሳቦች የሚነሱት የቤተሰብ ሕጉ በወቅቱ ከነበረው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ሲታይ የባህል እና የልማድ ሁኔታዎችን ከግምት አለማስገባቱ ያለውን ችግር እና ውጤቱን ከመተቸት አንጻር ሲሆን አንዴ ሕጉ ሥራ ላይ ከዋለ ፍርድ ቤቶች ይህንን ሕግ መተርጎም እና ሥራ ላይ ማዋል ኃላፊነታቸው በመሆኑ ክርክሮቹ የንድፈሃሳብ ብቻ ይሆናሉ ማለት ነው።


በተያዘው ጉዳይ የሰበር ችሎቱ ጋብቻ ከተፈጸመ በኋላ ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ መኖር እና በዚህ ጊዜ ውስጥ ሌላ ጋብቻ መስርቶ መኖር ፍርድ ቤት መቅረብ ሳያስፈልግ ጋብቻውን ለማፍረስ በቂ እንደሆነ ለመጀመሪያ ጊዜ ውሳኔ የሰጠው በመ.ቁ. 14290 ነው። ከዚህ በኋላ የተወሰኑት መዝገቦች በአብዛኛው በሃተታቸው "በተመሳሳይ ጉዳይ ላይ ችሎቱ ውሳኔ የሰጠበት በመሆኑ" የሚል አገላለጽን በመጠቀም የሚወሰኑ በመሆናቸው ለአስተማሪነትም ሆነ ለትችት የሚበቁ አይደሉም። በመሆኑም በጸሀፊው እምነት አብዛኛው የጉዳይ ትንተና ማተኮር ያለበት በመ.ቁ. 14290 ላይ ነው።

 
በዚህ መዝገብ የሰበር ችሎቱ በሕጋዊ መንገድ መፋታት እና በእውነታ መፋታት የሚሉ ሁለት ነጥቦችን በማንሳት የመዝገቡ ፍሬ ነገር የትኛውን እንደሚያረጋግጥ ለማሳየት ሞክሯል። በመሠረቱ በእውነታ መፋታት (de facto divorce) የሚለው ጉዳይ ለሀገራችን የሕግ ሥርዓት ይበልጡንም ለፍርድ ቤቶች አዲስ ጽንሰ ሃሳብ በመሆኑ ችሎቱ በተወሰነ ደረጃ ማብራሪያ መሰጠት ሲገባው ይህንን ሳያደርግ መቅረቱ በጸሀፊው እምነት ውሳኔውን ለመረዳት አዳጋች ያደርገዋል። በመዝገቡ የተሳተፉ ተከራካሪዎች እንዲሁም በጠበቃ የሚወከሉት ተሟጋቾች እንደተጠበቁ ሆነው አብዛኛው የቤተሰብ ችሎት ተከራካሪዎች ስለሕግ እና የሕግ ጽንሰሃሳቦች ያላቸው እውቀት እጅጉን ዝቅተኛ በሆነበት ሁኔታ እንዲህ መደረጉ የችግሩን አሳሳቢነት የበለጠ ያጎላዋል። ችሎቱ የሁለቱን ልዩነት እና የሕግ መነሻ በግልጽ ሳያስቀምጥ ለነዚህ ሁለት ዓይነት ፍቺዎች መሠረት የሚሆኑትን ጉዳዮች ያስቀምጣል።


በእውነታ መፋታት (de facto divorce) በሕግ ፊት ከመፋታት (de jure divorce) በተለየ ምን እንደሆነ አቶ ፊሊጶስ አይናለም ሲተረጉሙ በተግባር ወይም በእውነታ የተፋቱ ነገር ግን በሕግ እይታ ያልተፋቱ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህም ሕግ ጋብቻ በፍቺ እንዲቋረጥ ያስቀመጠው መስፈርት እና አሰራር ሳይከበር በተጋቢዎቹ ፍላጎት ብቻ ተለያይተው የሚኖሩበት ሁኔታ ነው።


የሰበር ችሎቱ ተጋቢዎቹ ከአቅም በላይ የሆነ ምክንያት ካልከለከላቸው በስተቀር ለረጅም ዓመት ተለያይተው ከኖሩ፣ በዚህም ጊዜ ሌላ ትዳር መስርተው መኖር ከጀመሩ እና ምንም ዓይነት ግንኙነት ካልነበራቸው ፍርድ ቤት ቀርበው ፍቺ ማስወሰን ሳይጠበቅባቸው ጋብቻው ቀሪ ይሆናል በሚል ምክንያቱን አስቀምጧል።በዚህ ላይ የመጀመሪያው እና ዋናው ችግር የትኛው የሕግ ወይም የአመክንዮ መሠረት ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ጋብቻን ማፍረስ እንደሚደግፍ አለመገለጹ ነው።የሰበር ችሎት እንደማንኛውም ፍርድ ቤት ውሳኔውን መሠረት ማድረግ ያለበት በሕግ፣ በማስረጃ እና በምክንያት ብቻ ነው። ውሳኔ በምን የሕግ አግባብ እንደተወሰነ መግለጽ እንዳለበት በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕግ የተመለከተ ሲሆን ይህ አስገዳጅ ድንጋጌ ተፈጻሚ መሆን ያለበት በአንድ ተከራካሪ ላይ ውጤት ፈጥሮ ከሚያልፈው ውሳኔ (declarative judgements) ጀምሮ በሀገሪቱ ሁሉም ፍርድ ቤቶች አስገዳጅነት እስካለው የሰበር ችሎት ውሳኔ ይጨምራል። በሁሉም ፍርድ ቤት ላይ አስገዳጅነት ያለው ውሳኔ ደግሞ አስገዳጅነቱን ከሕግ ብቻ ሳይሆን ከምክንያታዊነትም ማግኘት ግድ የሚለው ሲሆን ምክንያት የሌላቸው ውሳኔዎች የተከራካሪን መብት የሚያጣብቡ እንዲሁም የሰበርን አስፈላጊነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ይሆናሉ። በሌላም በኩል ምክንያት አለመጥቀስ የሥር ፍርድ ቤቶች የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ችላ በማለት ውሳኔ እንዲሰጡ እና ይህም ተመሳሳይ ጉዳዮች ወደ ሰበር ችሎቱ በገፍ እንዲመጡም ምክንያት ይሆናል።


ሁለተኛው ችግር የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 75 ሥር በግልጽ ካስቀመጣቸው ሶስቱ የጋብቻ መፍረሻ መንገዶች ውጭ ሌላ መንገድ ማበጀቱ ነው። በዚህ ድንጋጌ ሥር ሶስት ጋብቻ የሚፈርስባቸው መንገዶች የተመለከቱ ሲሆን እነዚህም ሞት ወይም የመጥፋት ውሳኔ፣ ጋብቻ ለመፈጸም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች አንዱ በመጣሱ ምክንያት ጋብቻው እንዲፈርስ መወሰን እንዲሁም ፍቺ ናቸው። ድንጋጌው ከሶስቱ መንገዶች ውጭ ጋብቻ እንደሚፈርስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ ያስቀመጠው ነገር የለም። ይህ ከሆነ ደግሞ ከእነዚህ መንገዶች ውጭ ሕግ አውጭው ጋብቻ እንዲፈርስ ፍላጎት የለውም ማለት ነው። በጸሀፊው እምነት ሕጉ ግልጽ ሆኖ እያለ ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ በመኖር ፍቺ እንዲፈጸም ማድረግ ለፍርድ ቤቶች ከተሰጠው ሕግ የመተርጎም ሥልጣን በመውጣት ሕግ የማውጣት ስልጣንን እንደመያዝ ሊቆጠር ይችላል። ይሄ ደግሞ በሕገ-መንግሥቱ ከተመለከተው የሥልጣን ክፍፍል ድንጋጌ ጋር የሚጣረስ ነው።


የሰበር ችሎቱ በሰ.መ.ቁ. 102662 ማብራሪያ ሲሰጥ የሚከተለውን አገላለጽ ተጠቅሟል።


…. ጋብቻው ተቋርጧል ወይንስ አልተቋረጠም የሚለውን ለመወሰን በአመልካች እና ተጠሪ መካከል በጋብቻ ውስጥ የሚጠበቁ ግዴታዎች በአግባቡ ሲተገበሩ ያልነበሩ እና እነዚህን ግዴታዎች ለመወጣት በአመልካች በኩል ያጋጠመው ሁኔታ በሕጉ የተጣሉባቸውን ግዴታቸውን ለመወጣት የማያስችል የነበረ መሆኑ ባልተረጋገጠበት …….


የዚህ አገላለፅ ጭብጥ ተጋቢዎቹ በጋብቻ ውስጥ በተሻሻለው የፌደራል ቤተሰብ ሕግ መሰረት ሊወጧቸው የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎች ከአቅማቸው በላይ በሆነ ምክንያት ካልሆነ በስተቀር መወጣት ካልቻሉ ጋብቻው ፈራሽ ይሆናል እንደማለት ነው። በመሠረቱ በቤተሰብ ሕግ ተጋቢዎቹ በጋብቻ ውስጥ እንዲወጡ የሚጠበቅባቸው ግዴታዎች ብዛት ያላቸው ሲሆኑ ሕጉ የጋብቻ ውጤቶች በሚል ያስቀመጣቸውን ግዴታዎች መነሻ በማድረግ በግላዊ ግንኙነታቸው እና የንብረት ግንኙነትን የሚመለከቱ ግዴታዎች ናቸው። በእነዚህ ሁለት ዓይነት ግዴታዎች መሠረትም በጋብቻ ውስጥ ግላዊ ግንኙነትን መሠረት ያደረጉ ግዴታዎች እንዲሁም ንብረትን በተመለከተ የሚጠበቁ ግዴታዎች በሚል ከፍሎ ለማየት ያስችላሉ። የሰበር ችሎቱ ተጋቢዎቹ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ ባለመወጣት ሲል የትኛውን ግዴታን አለመወጣት ጋብቻውን ለማፍረስ በቂ እንደሚሆን በግልጽ አላስቀመጠም። ለምሳሌ በተሻሻለው የፌደራል ቤተሰብ ሕግ በአንቀጽ 49 ስር ተጋቢዎቹ የመከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ ግዴታ፣ በአንቀጽ 50 ስር ቤተሰቡን የመምራት፣ በአንቀጽ 53 ስር አብሮ የመኖር፣ በአንቀጽ 54 ስር የመኖሪያ ስፍራቸውን የመወሰን እንዲሁም በአንቀጽ 56 ስር እንደተመለከተው የመተማመን ግዴታ አለባቸው። የጋብቻ በተጋቢዎቹ ግላዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት ተጋቢዎቹ እነዚህ ግዴታዎችን እንዲወጡ ከሆነ የትኛውን ግዴታ ሳይወጡ ሲቀሩ ነው ጋብቻውን ለማፍረስ በቂ ምክንያት የሚሆነው? ለረጅም ዓመታት ሳይተማመኑ ትዳራቸውን የሚመሩ ተጋቢዎች ጋብቻቸው በሁኔታዎች ፈርሷል? ተጋቢዎቹ ሳይተጋገዙ በሚስት ብርታት ብቻ ትዳሩ ቢቀጥል ጋብቻው እንደፈረሰ ይቆጠራል? የሚሉ እና መሰል ጥያቄዎች ከውሳኔው አንድምታ አንጻር አከራካሪ ጉዳዮች ናቸው።


በእርግጥ የሶስቱ የሰበር ችሎቱ ውሳኔዎች የተጋቢዎቹ ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ መኖር እና በዚህም ጊዜ ሌላ ጋብቻ መስርቶ መኖር በሁኔታ ጋብቻውን የሚያፈርስ እንደሆነ ያመላክታሉ። ይህም ማለት ተጋቢዎቹ አብረው እንዲኖሩ የሚገደዱበትን የአንቀጽ 53 ንዑስ አንቀጽ 1 ግዴታ ወደ ጎን በመተው በስምምነትም ሆነ ያለስምምነት ለረጅም ጊዜ ተለያይተው ሲኖሩ እና በዚህም ጊዜ ውስጥ ሌላ ጋብቻ መስርትው የሚገኙ ከሆነ የጋብቻ ግንኙነታቸውን ለመቋጨት በቂ ነው ማለት ነው። በመሠረቱ ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ የመኖሩ ሁኔታ ሊፈጠር የሚችለው ከሁለት መንገዶች በአንዱ ነው። አንደኛው በስምምነት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ያለስምምነት ነው። በስምምነት ተለያይቶ መኖርን በተመለከተ ተጋቢዎቹ በፍላጎታቸው ለተወሰነ ጊዜም ሆነ ላልተወሰነ ጊዜ ተለያይተው ለመኖር እንዲችሉ ሕጉ የፈቀደላቸው ሲሆን በመካከሉ ስምምነቱ እንዲቋረጥ ለመጠየቅም እንደሚቻል ተመልክቷል። ይህንን ግዴታ በተመለከተ ክርክር የተነሳ እንደሆነ ክርክሩ እልባት ሊያገኝ የሚችለው በጋብቻ ውስጥ ስላሉ አለመግባባቶች አፈታት በተመለከተው የሕጉ ክፍል ሥር በመሆኑ ብዙ አከራካሪ አይሆንም። ነገር ግን ለተወሰነ ጊዜ ተለያይቶ ለመኖር ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ተለያይቶ ለመኖር የተስማሙ ተጋቢዎች በዚያው ሳይገናኙ ቢቀሩ ውጤቱ ምን ሊሆን ይችላል የሚለው ግልጽ ባይሆንም ከሁለቱ አንዱ ግን ይህንን በፈለገ ወቅት ለማቋረጥ እንደሚቻል በአንቀጽ 55(2) ስር መመልከቱ በማንኛውም ወቅት ሊሰራበት የሚችል መብት በመሆኑ አቤቱታ ለፍርድ ቤት በቀረበ ወቅት ተለያይቶ የመኖር ስምምነቱን ለማቋረጥ ይቻላል።


አከራካሪ የሚሆነው እና በሕግ በግልጽ ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ያልተመለከተው ተጋቢዎቹ ያለስምምነት ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የሚኖሩበት እንዲሁም በስምምነት ተለያይተው ስምምነታቸውን ሁለቱም ሳያቋርጡ በዚያው የሚለያዩበት ሁኔታ ነው። ይህም ተጋቢዎቹ በጋብቻ ውስጥ ሲኖሩ ከቆዩ በኋላ ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ በራሳቸው ፍላጎት ተለያይተው መኖርን የሚመለከት ጉዳይ ነው። በመሠረቱ በቀደመው የቤተሰብ ሕግ ስር ተጋቢዎቹ አልፈልግሽም አልፈልግህም በሚል መለያየት እንደማይችሉ በግልጽ ተመልክቶ ይገኛል። የዚህም ድንጋጌ አንድምታ ተጋቢዎቹ ፍርድ ቤት እንደአግባብነቱም የቤተሰብ ሽምግልና ጉባዔ ሳይቀርቡ ጋብቻውን አልፈልግም በሚል ተለያይተው መኖር እንደማይችሉ መከልከል ነው። በመሆኑም በነባሩ የቤተሰብ ሕግ እንደዚህ ዓይነት ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ በመኖር ጋብቻ ይፈርሳል አይፈርስም የሚለው ጉዳይ በሕግ ምላሽ ያገኘ ነው።


የተሻሻለው የፌደራል የቤተሰብ ሕግ ግን ለዚህ ጉዳይ ቀጥተኛ ወይም በተዘዋዋሪ መንገድ ምላሽ አይሰጥም። እዚህ ጋር በፌደራሉ ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 105 ንዑስ ቁጥር 1 ሥር ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት አብረው የሚኖሩ ሰዎች ግንኙነታቸውን በፈለጉ ጊዜ እንዲያቋርጡ ፍቃድ ተሰጥቷቸዋል። ይህ ፍቃድ ጋብቻ ለፈጸሙ ሰዎች የተሰጠ መብት አለመሆኑን ሕጉ ስለጋብቻ በሚደነግጋቸው ክፍሎች ሥር አለማስቀመጡ አንዱ ማሳያ ነው። ሕጉ ግንኙነቱ ውስጥ ባሉ ሰዎች ፍቃድ ብቻ ያለተጨማሪ ሥርዓት በፈለጉ ጊዜ ግንኙነታቸው እንዲያቋርጡ ጋብቻ ሳይፈጽሙ እንደባልና ሚስት አብረው ለሚኖሩ ሰዎች ፍቃድ ሰጥቶ ጋብቻ ውስጥ ላሉ ሰዎች መከልከሉ ወይም በዝምታ ማለፉ የቀድሞውን የቤተሰብ ሕግ መንገድ በተዘዋዋሪ እንደተከተለ እንዲሁም በተሻሻለው የፌደራሉ ቤተሰብ ሕግ ሥር ሁኔታው ተቀባይነት እንደሌለው አመላካች ነው።


ይህ ትርጉም በቂ ካልሆነ ወይም አግባብነት የለውም ቢባል ሕጉ ግልጽ ባልሆነበት ሁኔታ ከሚቀርበው ክርክር አንጻር እየተመለከቱ ምላሽ መስጠት የፍርድ ቤቶች ኃላፊነት ነው። ይህም የፍርድ ቤቶች ተግባር በነጭ እና በጥቁር ቀለማት የተጻፈውን ሕግ ህይወት እንደመስጠት ያለ ተግባር መሆኑ ብዙ አከራካሪ አይደለም። በዚህ ጉዳይ ላይ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት በሁኔታ ጋብቻ ስለሚፈርስበት ሁኔታ ፍርድ ቤቶች ሲሰጧቸው የነበሩ ውሳኔዎች የተለያዩ አቋሞችን የሚከተሉ ነበሩ።


እንደሚታወቀው የሰበር ችሎቱ በሚሰጣቸው ውሳኔዎች እንዲያሳካ የሚፈለገው ዓላማ በተለያዩ የሀገሪቱ ፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ውሳኔዎች ወጥነት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው። ነገር ግን በተያዘው ጉዳይ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ከተሰጠም በኋላ የሚፈለገው ወጥ የሆነ የሕግ ትርጉም ብዙም የተገኘ አይመስልም። በአንድ በኩል አንዳንድ ችሎቶች የሰበር ውሳኔዎቹ ጋብቻው በፍቺ እንዲፈርስ አቤቱታ ሲቀርብ ተጋቢዎቹ ለረጅም ጊዜ ተለያይተው መኖራቸው ከተረጋገጠ ጋብቻው በሁኔታዎች ፈርሷል፤ በዚህም ምክንያት የሚሰጥ የፍቺ ውሳኔ የለም በማለት ውሳኔ ይሰጣሉ። በሌላ በኩል እንዲሁ ጋብቻው በሁኔታዎች ፈርሷል አልፈረሰም የሚለውን በማጣራት እና ጋብቻው በሁኔታዎቹ ፈርሷል የሚባልበት ጊዜ ተገልጾ ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ጋብቻው በፍቺ ፈርሷል በሚል ውሳኔ የሚሰጡ ችሎቶችም ይገኛሉ። በመሆኑም የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ራሱ በአግባቡ እየተፈጸመ አለመሆኑ ራሱን የቻለ ክፍተት እንደሆነ ለመመልከት ይቻላል። ነገር ግን በጸሀፊው እምነት ውሳኔ መስጠት የፍርድ ቤቶች ኃላፊነት በመሆኑ ተጋቢዎቹ ለረጅም ጊዜ መለያየት አለመለያየታቸውን በማጣራት የፍቺውን ቀን በአግባቡ በመለየት ውሳኔ መስጠት እንጂ የሚሰጥ የፍቺ ውሳኔ የለም ማለት ተገቢ አይመስልም።


በመሠረቱ ጋብቻ ለረጅም ጊዜ ተለያይቶ በመኖር እንዲፈርስ ወይም በፍርድ ቤት የፍቺ አቤቱታ በቀረበ ወቅት እንዲፈርስ ተከራካሪዎች የሚከራከሩት በአብዛኛው ወይም ሙሉ በሙሉ ለማለት በሚቻል መልኩ ከፍቺው ውሳኔ በኋላ ለሚነሳው የፍቺ ውጤት ክርክር ይበልጡንም ለንብረት ክርክር እንዲሁም አባትነትን ለማረጋገጥ መሆኑ አከራካሪ ጉዳይ አይደለም። ምክንያቱም ጋብቻው መቼ ፈረሰ የሚለው የጊዜ ጉዳይ ትርጉም ባለው ውጤት ማለትም በመብት ማግኘት አለማግኘት ላይ ካልተመሰረተ በቀር በራሱ ፋይዳ የማይኖረው በመሆኑ ነው። በመሆኑም ለሕጉ ክፍተት ምላሽ ሲሰጥ ጋብቻው መቼ ፈረሰ የሚለው ጭብጥ ከውጤቱም አንጻር መታየት ይኖርበታል።


ከንብረት ክርክር አንጻር ከታየ ፍቺው ሲወሰን ፍቺ ተፈጽሞበታል የተባለበት ጊዜ ለንብረት ክፍፍል አቤቱታ ለማቅረብ እንደመነሻ የሚያገለግል በመሆኑ ወሳኝነት ይኖረዋል። ይህም ማለት ፍቺ ተፈጽሞበታል ከተባለበት ጊዜ አንስቶ በ10 ዓመት ጊዜ ውስጥ የንብረት ክፍፍል አቤቱታ ካልቀረበ ጥያቄው በይርጋ እንደሚታገድ በሰበር ችሎቱ ተወስኗል። በመሆኑም ጋብቻው እንዲፈርስ ክስ ሲቀርብ ተጋቢዎቹ ከ10 ዓመታት በላይ ሳይገናኙ ተለያይተው መኖር ጀምረው ከሆነ ከፍቺው በኋላ ባል ወይም ሚስት የሚያቀርቡት የንብረት ክፍፍል ክስ በይርጋ ቀሪ የሚሆንበት እድል ይኖራል ማለት ነው። ነገር ግን የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ሙሉ በሙሉ የንብረት ክፍፍል ክስ የማቅረብ መብትን የሚከለክል በመሆኑ የይርጋ መቃወሚያ በማይነሳባቸው ክርክሮች ሥር ተጋቢው የጋራ ንብረት የመካፈል እድሉን የሚያሳጣ ይሆናል። ይህ አካሄድ በሰበር ችሎቱ ብቻ ሳይሆን ከፍ ሲል እንደተመለከተው ጋብቻው በሁኔታዎች የፈረሰ በመሆኑ የሚሰጥ የፍቺ ውሳኔ የለም በሚል ውሳኔ በሚሰጡ ችሎቶችም የሚከሰት ይሆናል ማለት ነው።


ሁለተኛው ውሳኔው ከውጤት አንጻር መታየት ካለበት ሊታይ የሚገባው አባትነትን የማረጋገጥ ክርክር ነው። እንደሚታወቀው በጋብቻ ውስጥ ለተወለደ ልጅ አባት ነው የሚባለው ባልየው ነው። ይህ በሕግ ግምት አባትነት የሚታወቅበት መንገድ ሲሆን ዳኝነቱን ያቀረበው ተከራካሪ ልጁ የተወለደው በጋብቻ ውስጥ መሆኑን እስካስረዳ ድረስ ባልየው ያለምንም ተጨማሪ መስፈርት የልጁ አባት ነው ተብሎ ፍርድ ይሰጣል። ከፍ ሲል ከተመለከቱት የሰበር ችሎቱ ውሳኔዎች አንጻር እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ጋብቻው በፍርድ ቤት ፈራሽ ሳይደረግ ተጋቢዎቹ ተለያይተው ሲኖሩ ሌላ ትዳር መስርተው የሚገኙ ከሆነ ነው። ይህ ሁኔታ ሲያጋጥም የመጀመሪያው ጋብቻ ባለመፍረሱ የጸና ሲሆን ባል በፊናው ሌላ ትዳር የመሠረተ፣ እንዲሁም ሚስት በፊናዋ ሌላ ትዳር የመሰረተች ከሆነ እስከሶስት የሚደረሱ ጋብቻዎች ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህ ሶስት ጋብቻዎች ጸንተው ባሉበት ጊዜ ልጅ ሲወለድ አባቱ ማን ነው የሚለውን ለመመለስ በሕጉ መሠረት ከአንድ በላይ ጋብቻ ያለ በመሆኑ ውሳኔውን አስቸጋሪ ያደርገዋል።


ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት በመዝገቦቹ ሥር የሰጣቸው ውሳኔዎች የሕግ መነሻቸው ያልተጠቀሰ እንዲሁም በፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ሥር ከተመለከተው የጋብቻ ማፍረሻ መንገዶች የወጣ በመሆኑ አግባብነት ያለው አይደለም። በመሆኑም ጋብቻ በሁኔታዎች ፈርሷል በሚል የሚሰጡ ውሳኔዎች ከሕጉም ሆነ ከምክንያታዊነት የወጡ በመሆናቸው የሚፈጥሯቸው ችግሮች ፈርጀ ብዙ ናቸው።


3. የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሕጋዊነት እና ምክንያታዊነት


በማንኛውም የሕግ ጉዳይ ላይ ክርክር ተደርጎ ውሳኔ ከመሰጠቱ በፊት ውሳኔ ሰጪው አካል ጉዳዩን ተመልክቶ ለመወሰን ሥልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለው ጭብጥ መታየት ይኖርበታል። በተያዘው ጉዳይም የፌደሬሽን ምክር ቤት በወ/ሮ ቀለሟ ክስ ላይ የሰጠውን የውሳኔ ይዘት ከመመልከታችን በፊት ምክር ቤቱ ውሳኔውን ለመስጠት የሚያስችለው ሥልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለውን መመልከት አስፈላጊ ነው። በመሆኑም ምክር ቤቱ የሰበር ችሎቱን ውሳኔ ውድቅ ማድረጉ ከተሰጠው ስልጣን አንጻር ሲመዘን በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለማስተላለፍ ስልጣን አለው ወይስ የለውም የሚለውን በአጭሩ መመልከት ያስፈልጋል።


በፌደራሉ ሕገ-መንግሥት ሥር እንደተመለከተው ሕገ-መንግሥታዊ ክርክሮችን ተመልክቶ ውሳኔ የመስጠት ሥልጣን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ነው። ምንም እንኳን የምክር ቤቱ ስልጣን አከራካሪ ባይሆንም ሕገ-መንግሥታዊ ክርክር ማለት ምን ማለት ነው የሚለው ነጥብ አጨቃጫቂ ሲሆን ይስተላል። በዚህ ጉዳይ ብዛት ያላቸው ሃሳቦች የሚነሱ ቢሆንም በዋነኛነት ግን ሁለት ሃሳቦች ተቀባይነት ያገኙ ይመስላሉ። አንደኛው ለምክር ቤቱ የተሰጠው ሥልጣን በሕገ--መንግሥቱ ሥር የሚነሳ ትርጉም ወይም ከሕገ-መንግሥቱ ውጭ ያሉ ሕጎች፤ውሳኔዎች እንዲሁም ሌሎች አሰራሮች ከሕገ-መንግሥቱ አንጻር ያላቸውን አካሄድ ወይም ተቃርኖ መርምሮ ውሳኔ ላይ መድረስ ነው የሚል መከራከሪያ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ ሁሉም ሕገ-መንግሥት ነክ ክርክሮችን በሙሉ ለመመልከት ሥልጣን ተሰጥቶታል የሚል ክርክርም ይነሳል። ነገር ግን አንደኛ በአንቀጽ 83(1) ሥር የተሰጠው ሥልጣን ሕገ-መንግሥትን የመተርጎም እንጂ የፍሬ ጉዳይ ክርክሮችን የማየት ባለመሆኑ፤ ሁለተኛ በአንቀጽ 84(2) ሥር የሕገመንገሥት ትርጉም ማለት የፌደራል ወይም የክልል ሕግ ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ይቃረናሉ ወይስ አይቃረኑም የሚል እንደሆነ ለመግለጽ መሞከሩ፤ ሶስተኛ በአንቀጽ 62(1) ሥር በተመለከተው አግባብ ምክር ቤቱ ስልጣኑ በሕገ-መንግሥት ትርጉም ላይ ብቻ የተወሰነ በመሆኑ እንዲሁም እያንዳንዱን በተዘዋዋሪ መንገድ የሕገ-መንግሥት ጉዳይ የሚመለከት ክርክርን ለመዳኘት ስልጣን አለው ማለት በአንቀጽ 79(1) ሥር የዳኝነት ስልጣን ለፍርድ ቤቶች ብቻ ተሰጥቷል የሚለውን ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ የመጀመሪያው የክርክር መስመር በአብዛኛው መልኩ ተቀባይነት አግኝቷል።


በጉዳዩ ላይ ሰፊ ጥናትና ምርምር ያደረጉት ዶ/ር አሰፋ ፍሰሃ ሕገ-መንግሥቱ ሲወጣ በዚህ ጉዳይ ላይ የነበረው መንፈስ ፍርድ ቤቶችን ከጉዳዩ ማግለል ሳይሆን የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚያወጣቸውን ሕጎች ሕገ-መንግሥታዊነት እንዳይመረምሩ መገደብ ብቻ እንደሆነ ይገልጻሉ። ይህም ማለት አንድ ሕግ ሕገ-መንግሥታዊ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ጭብጥ በፍርድ ቤቶች እንዲታይ የአርቃቂዎቹ ፍላጎት ባይሆንም ከዚህ ውጭ ያሉ ክርክሮችን ግን ከፍርድ ቤቶች መውሰድ ተፈጥሯዊ ከሆነው የፍርድ ቤቶች ሥልጣን ጋር የሚጋጭ በመሆኑ ተቀባይነት ያገኘ አይመስልም። በመሆኑም የፌደሬሽን ምክር ቤት ስልጣን የሕጎች ሕገ-መንግሥታዊነት ላይ እንጂ በሌሎች ጉዳዮች ላይ አለመሆኑን በዘርፉ ያሉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ።


ከዚህ ጋር በተያያዘ ጸሃፊው የፌደሬሽን ምክር ቤቶች ከሕገ-መንግሥት ትርጉም ባለፈ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ለመመርመር ወይም በይግባኝ ለመመልከት ሥልጣን ያላቸው ስለመሆኑ የሚዘረዝር ጽሁፍም ሆነ የሌሎች ሀገራት ልምዶችን ለማግኘት አልቻለም።


የፌደሬሽን ምክር ቤት የሰጣቸው ውሳኔዎች ላይ ዳሰሳ ያደረጉት አቶ ሙስጠፋ ናስር በበኩላቸው አብዛኛው ምክር ቤቱ ውሳኔ የሰጠባቸው ጉዳዮች በፍርድ ቤት ሊታዩ የሚገባቸው መሆኑን ጠቅሰው የሕገ-መንግሥት አጣሪ ጉባዔውም ሆነ ምክር ቤቱ ጥሰት ተፈጽሞባቸዋል በሚል የጠቀሷቸው የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎች ፍርድ ቤቶች ሕገ-መንግሥቱን የሚቃረን ውሳኔ ሰጥተዋል ለማለት ሩቅ መሆናቸውን ገልጸዋል።


በሌላ በኩል ምክር ቤቱን ለማጠናከር እና ሥልጣን እና ተግባሩን ለመዘርዘር የወጣው አዋጅ አንቀጽ 3 ሥር የምክር ቤቱን ስልጣን እና ተግባር ሲዘረዝር በንዑስ አንቀጽ 1 ሥር ሕገ-መንግሥቱን እንዲተረጉም ሥልጣን ተሰጥቶታል። ከዚህ ባለፈ ግን በዝርዝሩ ውስጥ በፍርድ ቤቶች ወይም በሌሎች አካላት የሚሰጡ ውሳኔዎችን በይግባኝ ተመልክቶ ለመወሰን ስልጣን አልተሰጠውም።


ከዚህ አጠቃላይ የሥልጣን መሠረት ወደ ተያዘው ጉዳይ ስንመለስ የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጋብቻ በሁኔታዎች ሊፈርስ እንደሚችል ውሳኔ የሰጠው በተሻሻለው የፌደራሉ ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ስር ከተመለከተው ሶሰት የጋብቻ መፍረሻ መንገዶች ውጭ በመውጣት እንደሆነ ከፍ ሲል ተመልክቷል። ምክር ቤቱ በውሳኔው የሰበር ችሎቱን ውሳኔ ውድቅ ለማድረግ ያሰፈረው ምክንያት ውሳኔው ከሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 50(5)፤ አንቀጽ 55 እንዲሁም አንቀጽ 79(3) ጋር የሚቃረን ነው በማለት ነው። ነገር ግን ሰፊው የውሳኔው ትንተና እንደሚያሳየው ውሳኔው ውድቅ የተደረገው ከቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 75 ውጭ የፍቺ ምክንያት ችሎቱ ተጠቅሟል እንዲሁም ፍቺ በአንቀጽ 82 የፍርድ ቤት ሥልጣን ሆኖ እያለ የሚሰጥ የፍቺ ውሳኔ የለም መባሉ ስህተት ነው በሚል ነው።


የሰበር ሰሚው ችሎት ውሳኔ ጥሷቸዋል የተባሉትን የሕገ-መንግሥት ድንጋጌዎችን ስንመለከት በቅድሚያ የተጠቀሰው አንቀጽ 50 ንዑስ አንቀጽ 5 ነው። ነገር ግን ይህ ድንጋጌ ከጉዳዩ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት የሌለው እና የሚያትተውም ስለክልል ምክር ቤቶች የሕግ አውጭነት ሥልጣን በመሆኑ እዚህ ላይ መተቸቱ አላስፈላጊ ነው። ሁለተኛው የተነሳው አንቀጽ 55 ስለ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሕግ አውጪነት ሥልጣን ሲሆን በዚህ ድንጋጌ ሥር ሊተች የተፈለገው ጉዳይ የሰበር ችሎቱ ሕግን በመተርጎም ሰበብ በሕጉ ያልተመለከተ አዲስ ሕግ አውጥቷል የሚል ነው። በመሠረቱ በአንቀጽ 75 ጋብቻ የሚፈርስባቸውን ምክንያቶች ሶስት ብቻ ሲሆኑ የሰበር ችሎቱ ከነዚህ ውጭ አራተኛ የፍቺ መንገድ ያስቀመጠ ስለመሆኑ አጠያያቂ አይመስልም። ሕግ አውጭው ከነዚህ ምክንቶች ውጭ ጋብቻ ሊፈርስ የሚችልበት አማራጭ ባላስቀመጠበት ወይም ዝርዝሮቹን ክፍት አድርጎ ባልተወበት ሁኔታ አዲስ የፍቺ ምክንያት መጠቀም ሕጉን ከመተርጎም ሥልጣን ከፍ ያለ ነው። በሌላ በኩል ግን ሊነሳ የሚችለው ጉዳይ ሕጉ ሲወጣ ሊታሰቡ ያልቻሉ ጉዳዮች ሲነሱ ፍርድ ቤቶች ከነባራዊው ሁኔታ አንጻር እየተመለከቱ መፍትሄ ማበጀት ይኖርባቸዋል የሚል ክርክር ነው። ነገር ግን ለጊዜው የሰበር ችሎቱ ውሳኔ የሕግ ትርጉም ነው ወይስ በትርጉም ሰበብ የተከናወነ አዲስ ሕግ የማውጣት ተግባር የሚለው ራሱን የቻለ ሰፊ ጥናት የሚያስፈልገው ነው። ነገር ግን በጸሀፊው እምነት የፌደራሉ ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 እና 117 ሥር የፍቺ መንገዶች እና ፍቺን ለመወሰን ሥልጣን የተሰጠው አካል ግልጽ በመሆናቸውና ሕጉ ግልጽ በሆነበት ሁኔታ ደግሞ መተርጎም አስፈላጊ ባለመሆኑ የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔ የሕግ ትርጉም ነው ለማለት ያስቸግራል።


በመጨረሻም የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ይጥሰዋል የተባለው ድንጋጌ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 79(3) ነው። ይህ ድንጋጌ የሚያትተው ስለ ዳኞች ነጻነት እንደሆነ በግልጽ መረዳት ይቻላል። ይህም ማለት ዳኞች ከማንም ወገን ጣልቃ ገብነት በጸዳ መልኩ ሥራቸው ሕግን መሠረት ባደረገ መልኩ ብቻ ይሰራሉ ማለት ነው። ይህ ከንዑስ አንቀጽ 2 የሚለየው በዋነኛነት ንዑስ አንቀጽ 2 ስለ ተቋማዊ ነጻነት የሚደነግግ በመሆኑ እና ንዑስ አንቀጽ 3 ደግሞ ስለ ዳኞች ግላዊ ነጻነት (የውሳኔ ነጻነት) የሚደነግግ በመሆኑ ነው። ምክር ቤቱ ዳኞች "በሕግ ካልሆነ በሌላ ሁኔታ አይመሩም" የሚለውን አገላለጽ የተረዳው ሕግ አውጭው ካሰበው ዳኞች ከሌሎች አካላት ከሚመጣ ተጽዕኖ ውጭ ውሳኔ ይሰጣሉ በሚለው አንድምታ ሳይሆን ከሌላ አንጻር እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል።


የምክር ቤቱ ሥልጣን እና የሰጠው ውሳኔ መነሻዎች እነዚህ ከሆኑ ሊነሳ የሚገባው ጥያቄ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ እነዚህን የሕግ ድንጋጌዎች ይጥሳል ቢባል እንኳን ምክር ቤቱ በምን ሥልጣኑ ውሳኔውን ለመሻር ቻለ? የሚል ነው። በቅድሚያ ምክር ቤቱ በሕገ-መንግሥቱ ሥልጣን እንዲኖረው የታሰበው በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚወጡ ሕጎች ሕገ- መንግሥታዊነትን ለማጣራት በሚል ሲሆን በተያዘው ጉዳይ ግን ይህ ጭብጥ ባልሆነበት ሁኔታ ውሳኔውን ተመልክቶ ውሳኔ መስጠቱ ከሥልጣኑ ውጭ እንደወጣ የሚያመላክት ነው። በሰበር ችሎቱ ውሳኔዎች ሕገ-መንግሥቱን የሚመለከት ክርክር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ አልተነሳም። የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የጠቀሳቸው ዝርዝሮች የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች ያስነሳሉ ቢባል እንኳን ፍርድ ቤቶች እንዳይመለከቷቸው ባልተከለከሉበት ጭብጥ ላይ በመሆኑ ምክር ቤቱን የሚመለከት አይሆንም። በተዘዋዋሪ ሕገ-መንግሥቱን የሚመለከት ጉዳይ ነው ቢባል እንኳን በዳበረው የሕገ-መንግሥት ፍልስፍና (constitutional jurisprudence) ፍርድ ቤቶች ሕገ-መንግሥቱን የሚመለከት ጉዳይ ሙሉ በሙሉ ማየት አይችሉም የሚል ሕግ ባለመኖሩ እንዲሁም ከተከለከሉት ጭብጥ ውጭ ሌሎችን ለመመልከት የሚችሉ በመሆናቸው ለምክር ቤቱ ጣልቃ ገብነት በር ሊከፍቱ አይችሉም። የምክር ቤቱን ሥልጣን እና ተግባር ለመዘርዘር የወጣው አዋጅም ቢሆን ምክር ቤቱ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ ተመልክቶ ለመሻርም ሆነ ለማጽደቅ ሥልጣን አይሰጠውም። በመሆኑም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ የሰበር ችሎቱን ውሳኔ መርምሮ ውድቅ ለማድረግ በሕገ-መንግሥቱ፤ በመቋቋሚያ አዋጁ እንዲሁም በዳበረው የሕግ ፍልስፍና ሥልጣን ያልተሰጠው በመሆኑ በጉዳዩ ላይ የሰጠው ውሳኔ ከሥልጣን ውጭ (ultra-vires) ነው ሊባል ይችላል።


4. የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ ምክንያታዊነት


የፌደሬሽን ምክር ቤቱ በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ከመስጠቱ በፊት አስተያየት እንዲሰጥበት ለሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ እንዲሁም ከሕገ-መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የቀረበለትን የውሳኔ ሃሳብ ተመልክቷል። የቋሚ ኮሚቴው የውሳኔ ሃሳብ ምን እንደሆነ በውሳኔው ያልተገለጸ ቢሆንም ምክር ቤቱ ውሳኔውን ሲሰጥ የሕገ-መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔውን ያቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ከነምክንያቱ የተጠቀመ በመሆኑ የሁለቱንም ምክንያቶች በአንድነት መመልከት ያስፈልጋል።


በቅድሚያ ውሳኔው ሊሻር የቻለው በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 75 ስር ጋብቻ ከሚፈርስባቸው ምክንያቶች ውጭ ፍርድ ቤት ሌላ መመዘኛ እየፈለገ ጋብቻን ማፍረሱ ተገቢነት የለውም የሚል ነው። ምንም እንኳን ምክንያቱ የቀረበበት አገላለጽ ትክክለኛ እና ጨዋነትን የተላበሰ ባይሆንም ሊባል የተፈለገው ከሶስቱ የጋብቻ መፍረሻ ምክንያቶች ውጭ ፍርድ ቤቶች ሊያበጁ አይችሉም የሚል ነው። ከላይ በዝርዝር እንደተመለከተው የሰበር ችሎቱ ከሕጉ ውጭ በመውጣት የሰጠው ውሳኔ በመሆኑ አመክንዮው ትክክለኛ እና ህጋዊም ነው።


ሌላው የቀረበው ምክንያት ውሳኔው ተጋቢዎች በቸልተኝነት ጋብቻቸውን ከፍርድ ቤት እውቅና ውጭ በፍቺ መልክ እንዲያቋርጡ መንገድ የሚከፍት እንዲሁም ህገ-ወጥነትን ያበረታታል የሚል ነው። እዚህ ላይ የቤተሰብ ሕጉ ሲወጣ ጋብቻ በሶስት መንገዶች እንዲፈጸም እድል ተሰጥቶ ለምን በፍርድ ቤት ብቻ እንዲፈርስ ተደረገ የሚል ክርክር ይነሳል። ምን ያህሉ የኢትዮጵያ ኅብረተሰብ ነው በፍትሐ ብሔር ሕግና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት ብቻ ፍቺ ሲፈጽም የቆየው የሚል ጥያቄም ተነስቶ ነበር። እንዳውም በዚህ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት ዶ ዶ/ር ኤሊያስ ኑር በአንድ ወቅት የሚከተለውን ተናግረዋል።


"ለጋብቻ አፈጻጸም ሥርዓት ሶስት መንገዶች(በሮች) ተፈቅደውለት እያለ ለፍቺ ስርዓቱስ ለምንድነው አንድና አንድ መንገድ ማለትም በፍርድ ቤት ብቻ እንዲከናወን የሚደረገው?"


የፌደራሉ የቤተሰብ ሕግ ሲወጣ ያለው ክፍተት እንደተጠበቀ ሆኖ የምክር ቤቱ ይኼኛው ምክንያት ጋብቻን በፍቺ ለማፍረስ ሥልጣን ተሰጥቷቸው እያለ ፍቺ አንወስንም የሚሉ ፍርድ ቤቶች ተጋቢዎቹ ግንኙነታቸውን በራሳቸው እንዲያቋርጡ በማድረግ ሕገ-ወጥነትን ያበረታታል የሚል ትችት ቀርቦበታል። ይህ ምክንያት ላይ ላዩን ሲታይ ትክክለኛ ይመስላል። ምክንያቱም ሕግ ከደነገገው መውጣት ሕገ-ወጥነት ስለሚሆን ነው። ነገር ግን ጠለቅ ብሎ ለተመለከተው ፍርድ ቤት እስካላፈረሰው ግንኙነቱ ቀጥሏል በሚል በዚያው የሚቀር ተጋቢ ነው ወይስ ፍርድ ቤት ጋብቻውን ባለማፍረሱ ንብረት የመጠየቅ መብቴ በይርጋ ቀሪ ይሆናል የሚል ተጋቢ ነው የፍቺ ጥያቄውን ወደ ፍርድ ቤት ለመውሰድ ጥረት የሚያደርገው የሚለውን ለተመለከተ ምላሹ በተቃራኒው እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም። በምክር ቤቱ ውሳኔ እንደተመለከተው የፍቺ ጥያቄ የሚቀርበው ንብረት ለመጠየቅ እንደሆነ የሚታወቅ በመሆኑ ፍርድ ቤት ባለመምጣቱ የሰበር ችሎቱ በሰጠው ውሳኔ አግባብ መብቱን የሚያጣ መሆኑን ስለሚረዳ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብን ያበረታታል። በመሆኑም ምንም እንኳን የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ከሕጉ ውጭ ቢሆንም ተጋቢዎች ንብረት የመካፈል መብታቸውን በይርጋ እንዳያጡ ጋብቻቸውን በወቅቱ ፍርድ ቤት ቀርበው እንዲያስፈርሱ የሚያደርግ እንጂ ምክር ቤቱ እንዳተተው ሕገ-ወጥነትን የሚያበረታታ አይሆንም።


በእርግጥ የምክር ቤቱ መሠረታዊ የሆነ ጥያቄ ሊነሳበት የሚችለው ተጋቢዎች ለየትኛውም ጊዜ ያህል ተለያይተው ቢኖሩ ፍቺ እንዲወሰን ለፍርድ ቤት አቤቱታቸውን ማቅረብ ይችላሉ? ማለትም ምን ያህል ዓመት ተለያይተው የኖሩ ተጋቢዎች ናቸው የፍቺ አቤቱታ ለማቅረብ የሚችሉት? 10 ዓመት? 20 ዓመት? 40 ዓመት? ወይስ ከተጋቢዎቹ አንዱ ህይወቱ እስካላለፈና በዚህም ጋብቻው በሞት እስካልፈረሰ ድረስ? አብዛኛዎቹ የፍትሐብሔር መብቶች በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ ክስ ቀርቦ ዳኝነት ካልተጠየቀባቸው መብቶቹን መነሻ በማድረግ በፍርድ ቤቶች ክስ ከማቅረብ በይርጋ ይታገዳሉ። ከዚህ አንጻር ምክር ቤቱ የሰጠው ውሳኔ ተጋቢዎች መብታቸውን በወቅቱ እንዳይጠይቁ በማድረግ ዳተኝነትን የሚያበረታታ መሆኑ ግልጽ ነው። ምክር ቤቱ የሰበር ችሎቱን ሕገ-ወጥነትን የሚያበረታታ ውሳኔ ሰጥቷል በሚል የሚወቅሰው በዚህ መልኩ ከፍ ያለ ማህበራዊ ቀውስ ሊያስከትል የሚችል ውሳኔ በመስጠት ነው። በዚህ ላይ ደግሞ ይህንን ዓይነት ማህበራዊ ቀውስ ሊያመጣ የሚችል ውሳኔ ለመስጠት ከሥልጣን ውጭ የተሄደበት ርቀት ምክር ቤቱ ቆም ብሎ ሊያስብበት እንደሚገባ አመላካች ነው።


ከዚህ ጋር በተያያዘ የምክር ቤቱ ውሳኔ ነባራዊውን የሀገሪቱን ሁኔታ ያገናዘበ አይመስልም። ለዚህም መነሻ የሚሆነው አብዛኛው የሀገሪቱ ዜጋ የሚኖረው መደበኛ ፍርድ ቤት ለማግኘት እድል በማይኖርበት አካባቢ ነው። ተጋቢዎች ጋብቻቸውን ለማፍረስ ወደ ፍርድ ቤት ለመምጣት እድሉ ካለመኖሩም ባለፈ እድል አላቸው ቢባል እንኳን ፍርድ ቤት በመምጣትም ሆነ ባለመምጣት ሊገኝ ወይም ሊታጣ የሚችለውን ውጤት ካለማወቅ መነሻነት ፍቺን ለማስወሰን ወደ ፍርድ ቤት የማምራት ተነሳሽነት በሚፈለገው ደረጃ እንዳልሆነ አጠያያቂ አይደለም።


በመጨረሻም ምክር ቤቱ የሰበር ችሎቱን ውሳኔ የተቸው ሕገ-መንግሥቱ ያረጋገጠውን የሴቶች እና ህጻናት መብትን አያስከብርም በማለት ነው። የዚህም መነሻ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 34 እና 35 ስር የተመለከተው ሴቶች በጋብቻ አፈጻጸም፣ በጋብቻ ዘመንና በፍቺ ወቅት ከወንዶች እኩል መብት አላቸው እንዲሁም በፍቺ ወቅት የልጆችን መብት የሚያስጠብቁ ሕጎች ይወጣሉ በሚል የተደነገገው የሕገ-መንግሥቱ ክፍል ነው። በመሠረቱ በመዝገቡ ለምክር ቤቱ ቅሬታቸውን ያቀረቡት አመልካች ሴት በመሆናቸው ጉዳዩን ከሴቶች መብት አንጻር መመልከቱ ውሳኔውን ሩቅ አዳሪ አያደርገውም። ምክንያቱም መተቸት ካለበት በውሳኔው መብታቸውን ሊያጡ ስለሚገባቸው ተጋቢዎች በሙሉ እንጂ ስለሴቶች ብቻ ባለመሆኑ ነው። በመዝገቡ ቅሬታ ያቀረቡት ተጠሪ ቢሆኑ ምክር ቤቱ ይህንን አመክንዮ ላይጠቀመው ነው? ወይስ ወንዶችም በፍቺ ወቅት ከሴቶች እኩል መብት አላቸው በሚለው ምክንያት ሊተካ ይችል ነበር? የሚለው ጥያቄ ከጾታ ልዩነት አንጻር ብቻ ታይቶ ሊታለፍ የሚገባው ጉዳይ አይመስልም። ከዚህ ይልቅ ምክር ቤቱ በጠቅላላ አገላለጽ የሰበር ችሎቱ ውሳኔ ተጋቢዎቹ ንብረት በማፍራት ረገድ ያላቸውን የእኩልነት መብት እንዲጣስ እድል ይፈጥራል በሚል ተችቶ ቢያልፍ የተሻለ ይመስል ነበር። እንዲሁም ሁሉንም ጉዳዮች ከሕገ-መንግሥቱ ጋር ለማገናኘት የተሄደበት መንገድ ረዘም ያለ ነው። እንደሚታወቀው ሕገ-መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ በመሆኑ መሠረታዊ ሰብዓአና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን የያዘ በመሆኑ እንዲሁም ዝርዝሩ በበታችአዋጆች፣ደንቦች እንዲሁም ሌሎች ሕጎች የሚደነገግ በመሆኑ በዝርዝር ሕጎች ላይ የሚነሱ ክርክሮች ሕገ-መንግሥታዊ ጽንሰ-ሀሳብ ወይም መነሻ ይኖራቸዋል። በዚህ አካሄድ በጸሀፊው እምነት የትኛውንም ክርክር እና ጉዳይ ሕገ-መንግሥታዊ ማድረግ ከባድ ባለመሆኑ ሕገ-መንግሥታዊ ክርክሮች መለየት እና በነዛም ላይ ትኩረት ሰጥቶ መወሰን ተገቢ እና ሕጋዊም ነው።


በአጠቃላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በውሳኔው ካነሳቸው አመክንዮዎች ሰበር ችሎቱ ከሕጉ ግልጽ ንባብ ውጭ መውጣቱን በተመለከተ ካነሳው ውጭ ሌሎቹ ውሳኔውን ለመሻር የሚያበቁ በቂ ምክንያቶች አይደሉም። ነገር ግን ምክር ቤቱ ውሳኔውን ለመስጠት ሥልጣን የሌለው ቢሆንም ይህ ታልፎ በፍሬ ጉዳዩ ላይ ከታየ ከተሻሻለው የፌደራል ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ውጭ አዲስ የፍቺ መንገድ መጠቀም በሚል የቀረበው ምክንያት ብቻውን ውሳኔውን ለመሻር በቂ እና ምክንያታዊ እንደሆነ ጸሀፊው ያምናል።


ማጠቃለያ እና የመፍትሄ ሃሳቦች


በዚህ አጭር ጽሁፍ ለመመልከት እንደተሞከረው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ጋብቻ በፍቺ እንዲፈርስ በፍርድ ቤት የተሰጠ ውሳኔ ባይኖርም ተጋቢዎቹ ለረጅም ጊዜ ተለያይተው በመኖራቸው እና በዚህም ወቅት ሌላ ትዳር መመስረታቸው ጋብቻውን በሁኔታዎች ለማፍረስ የሚያበቃ ምክንያት እንደሆነ የሰጠው ውሳኔ ጋብቻ እንዲፈርስባቸው ሕግ አውጭው ካስቀመጣቸው ሶስት መንገዶች ውጭ ነው። ምንም እንኳን ችሎቱ ውሳኔው ላይ ሊደረስ የቻለው ተጋቢዎቹ በእውነታው ለረጅም ጊዜ መለያየታቸው ግንኙነታቸው እንደተቋረጠ ያስረዳል በሚል የሕግ ሳይሆን የእውነታ መሠረት ላይ በመመርኮዝ ቢሆንም ይህ ውሳኔ በግልጽ ከሕግ ውጭ መሆኑን መረዳት ብዙ አዳጋች አይሆንም።


በሌላ በኩል የፌደሬሽን ምክር ቤቱ ፍርድ ቤቶች አንድን ሕግ በአግባቡ ተርጉመዋል ወይስ አልተረጎሙም ወይም ሕግን በአግባቡ ሥራ ላይ አውለዋል ወይስ አላዋሉም በሚል ለመዳኘት በሕገ-መንግሥቱም ሆነ በማቋቋሚያ አዋጁ ሥልጣን አልተሰጠውም። በመሆኑም በተያዘው ጉዳይ ጋብቻ ስለሚፈርስበት አግባብ የሰበር ችሎቱን ውሳኔ ተመልክቶ ውሳኔ የሰጠው ከሥልጣኑ ውጭ በመውጣት ነው። ይህ አካሄድ የሕግ መሠረት የሌለው፣ የፍርድ ቤቶችን ሥልጣን የሚጋፋ እና የዳኝነት ሥልጣን ለፍርድ ቤቶች ብቻ ተሰጥቷል የሚለውን የሕገ-መንግሥት ድንጋጌ የሚጥስ በመሆኑ ሊተችና ሊነቀፍ ይገባዋል። መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻርም ከታየ እጅግ ብዛት ያላቸው የሰበር ሰሚው ችሎት ውሳኔዎች ለምክር ቤቱ ለመቅረብ ወረፋ በመጠባበቅ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው ምክር ቤቱ ራሱን የቻለ የይግባኝ አካል ወደ መሆን ደረጃ የደረሰ በመሆኑ የምክር ቤቱ አካሄድ ለመደበኛ ፍርድ ቤቶች ህልውና እና ነጻነት ራሱን የቻለ ፈተና የሚጋርጥ ነው። ቀድሞውንም በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች አቅማቸውን እና የሕዝብ አመኔታቸውን ላጡት ፍርድ ቤቶች ምክር ቤቱ እየተከተለ ያለው መንገድ ጉዳቱ ከፍ ያለ ነው። በጸሀፊው እምነት በጉዳዩ ላይ የሕግ ባለሙያዎች፣ ዳኞች እንዲሁም የምክር ቤቱ ተወካዮች ባሉበት ሰፊ ክርክር እና ውይይት ተደርጎበት ምክር ቤቱ እየሄደበት ያለው መንገድ ፈር ካልተበጀለት በቀር ለፍርድ ቤቶች ሥልጣን ይልቁንም ህልውና አደገኛ መሆኑ ግልጽ ነው።


መፍትሄውን በተመለከተ በሁለት መንገድ፥ ማለትም ሕግ በማውጣት እና ሕግ ከማውጣት በመለስ ያሉ መፍትሄዎች በሚል መመልከት ይቻላል። የመጀመሪያውን በተመለከተ ጋብቻን በሁኔታዎች ማፍረስ ስለሚቻልበት መንገድ የሕግ ማሻሻያ በማድረግ መመለስ ይቻላል። ይህም ማለት ከሶስቱ የጋብቻ ማፍረሻ ምክንያቶች በተጨማሪ ጋብቻ በሁኔታ ስለሚፈርስበት አግባብ በግልጽ አማራጭ በማስቀመጥ ምላሽ ሊያገኝ ይችላል። ማሻሻያውም መቼ እና እንዴት ጋብቻ በሁኔታ እንደሚፈርስ እንዲሁም ስለ ማስረጃ አቀራረብ የሚመለከት ከሆነ አከራካሪውን ጉዳይ በመመለስ ረገድ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። በጸሀፊው እምነት ጋብቻን ለማፍረስ ለፍርድ ቤት ሥልጣን መሰጠቱ ተገቢ ሲሆን ከዚህ ውጭ ግን ተጋቢዎች በራሳቸው ፍላጎት ጋብቻቸውን ጥለው በሚሄዱበት ወቅት ሊፈጠር የሚችለውን ችግር መፍትሄ ለመስጠት ተጋቢዎቹ በእውነታው የተለያዩ እንደሆነ ንብረትንም ሆነ ሌሎች የፍቺ ውጤቶች በምን ያህል ጊዜ መጠየቅ እንዳለባቸው ግልጽ የይርጋ ድንጋጌ ማስቀመጥ ይቻላል። ለዚህም ይርጋ መነሻ ጊዜ ተደርጎ ሊወሰድ የሚገባው ጋብቻው በፍቺ እንዲፈርስ የተወሰነበት ጊዜ ሳይሆን ተጋቢዎቹ ተለያይተው መኖር የጀመሩበት ጊዜ መሆን ይኖርበታል። ምክንያቱም የይርጋ መነሻ የሚሆነው መብቱን መጠየቅ ከሚቻልበት ጊዜ ጀምሮ መሆን ያለበት በመሆኑ ነው።


በጉዳዩ ላይ የሕግ ማሻሻያ ከማውጣት በመለስ ያሉ መፍትሄዎችን በተመለከተ ቀዳሚው እና ዋነኛው ጉዳይ ስለ ሁኔታው ግንዛቤ በማስጨበጥ ችግሩ እንዳይፈጠር መከላከል ሊሆን ይገባዋል። ምክንያቱም ስለ ውሳኔዎቹ ከመነጋገር በላይ ከፍ ያለ ውጤት ሊያመጣ የሚችለው በሕጉ አግባብ ተጋቢዎች ፍቺያቸውን በፍርድ ቤት እንዲፈጽሙ ትምህርት መስጠት በመሆኑ ነው።


ፍርድ ቤቶች በጉዳዩ ላይ ሊከተሉ የሚገባውን አካሄድ በተመለከተ ምንም እንኳን የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ ከሥልጣኑ ውጭ የተሰጠ ቢሆንም በአዋጅ ቁጥር 251/93 አንቀጽ 56 መሠረት የመጨረሻ እና አስገዳጅ በመሆኑ ተፈጻሚ ሊደረግ ይገባል። ይህም ማለት ፍርድ ቤቶች ተጋቢዎች ለረጅም ጊዜ ተለያይተው እና ሌላ ጋብቻ መስርተውም ቢቀርቡ የፍቺ ጥያቄውን ተቀብሎ ፍቺ መወሰን ይኖርባቸዋል። ፍቺ ተፈጽሟል የሚባልበትም ጊዜ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ መሆን ይኖርበታል።


ለዚህ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው የፍቺ አቤቱታ በቀረበ ጊዜ ግራቀኙን በማከራከር እንዲሁም በቤተሰብ ሕጉ ሥር በተመለከተው አግባብ ግራቀኙ ለማቀራረብ ጥረት በማድረግ ውጤት ላይ ካልተደረሰ ውሳኔው ከተሰጠበት ጊዜ ጀምሮ ጋብቻው በፍቺ ፍርሷል በሚል ውሳኔ መስጠት ነው። በዚህ አግባብ በአንድ በኩል ፍርድ ቤት ብቻ ጋብቻን ለማፍረስ ስልጣን አለው የሚለውን የአንቀጽ 117 ድንጋጌ ማስጠበቅ ይቻላል። አንዲሁም ጋብቻ የሚፈርስባቸው ብቸኛ ምክንያቶች ናቸው ተብለው በአንቀጽ 75 ስር ከተመለከቱት ሶስት መንገዶች መውጣት ሳያስፈልግ መወሰን ይቻላል። ከውሳኔው በኋላ የንብረት ክርክር የተነሳ እንደሆነ ንብረቱ ተለያይተው በኖሩበት ወቅት የተፈራ መሆኑ ከተረጋገጠ በመርህ ደረጃ ንብረቱን ያፈራው ተጋቢ የግል ንብረት ነው ተብሎ መወሰን ያለበት ሲሆን ለንብረቱ መፈራት ተጋቢዎቹ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ አስተዋጽኦ ነበራቸው የሚል ክርክር የተነሳ ከሆነም ተጋቢዎቹ ለንብረቱ መፈራት በጋራ አስተዋጽኦ አድርገዋል ወይስ በአንደኛው ተጋቢ ጥረት ብቻ ንብረቱ ተፈርቷል የሚለውን በማጣራት የጋራ አስተዋጽኦ ከተገኘ ከግል ጥረቱ አንጻር ያለው ብልጫ መሰረታዊ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን በመለየት የንብረት ክርክሩን እልባት መስጠት ይቻላል።


እዚህ ላይ አስተዋጽኦ ሲባል ጠበብ ባለ መልኩ ብቻ በመረዳት ልክ በንግድ ማህበራት ሥር እንደሚጠበቀው ድርሻን በዓይነት፣በዕዳ፣በክህሎት ወይም በገንዘብ በመወጣት ብቻ ሳይወሰን ሰፋ ባለ እና አብዛኛውን የሀገሪቱ ሴት ባለትዳሮችን ከግምት ባስገባ መልኩ ንብረቱ በተፈራ ወቅት አብሮ በመኖር እና ትዳሩን በመምራት የትዳሩን እና የንብረቱን ህልውና በማስቀጠልም መልኩ ሊወሰድ ይገባል። በዚህ ዓይነት መንገድ በአንድ በኩል በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 75 ሥር የተመለከቱትን ዝግ የጋብቻ መፍረሻ መንገዶች መከተል እንዲሁም የፍቺ ውጤት የሆነውን የንብረት ክፍፍልም በአግባቡ ማስተናገድ ይቻላል። በሌላ በኩል አባትነትን ከማረጋገጥ ጋር ተያይዘው ለሚነሱ ክርክሮች የየክርክሩ ልዩ ሁኔታ ከማስረጃው አንጻር እየታየ ምላሽ ማግኘት የሚገባው መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ በመርህ ደረጃ ግን በፌደራሉ ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 148 መሠረት ውሳኔ መስጠት ይቻላል።

ይህ ጽሑፍ በግርጌ ማስታወሻ ብዙ ማጣቀሻዎችን እና ማብራሪያዎችን የያዘ ሲሆን ጽሑፉን እስከግርጌ ማስታወሻው ከዚህ ያውርዱ

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በይርጋ የማይታገዱ የውርስ ጉዳዮች እና ከኑዛዜ ጋር የተያያዙ ይርጋዎች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Monday, 24 June 2024