Font size: +
6 minutes reading time (1213 words)

ጠበቃ በጋብቻ ፍቺ ሂደት ስለሚኖረው የሙያ ወሰን እና የሰበር ተቃርኖ

ጋብቻ በሁሉም ባህሎችና ሃይማኖቶች ትልቅ ክብር እና ልዩ ቦታ የሚሰጠው የሃገር ምሶሶ የሆነ የቤተሰብ ተቋም የሚፈጥ ሕጋዊ ኩነት ነው፡፡ በመሆኑም ፀንቶ እንዲቆይ በመንግስት እና በህብረተሰቡ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ መንግስት ጋብቻ ሲመሰረት፣ በጋብቻ ውስጥ እና ሲፈርስ ግንኙነቱ የሚመራበትን ሥነ ስርዓት በህግ በመደንገግ ጥበቃ ያደርጋል፡፡ ጋብቻ በፍች እንዲፈርስ ጥያቄ በሚቀርብበት ወቅት ፍርድ ቤት ጋብቻው ፀንቶ እንዲቆይ ለማስቻል ሊከተላቸው እና ሊፈፀማቸው የሚገቡ የጥበቃ ሥነ-ሥርዓት በቤተሰብ ህግ ተደንግጓል፡፡ (አንቀፅ 76 - 82 ይመለከቷል)። 

ይህ ድንጋጌ ፍርድ ቤቱ ሊከተለው ወይም ላይከተለው የሚችለው ፍቅድ ስልጣን ሳይሆን ህግ አውጭው የሕብረተሰብ የተፈጥሮ መነሻ የሆነው ቤተሰብ በቀላሉ በፍች እንዳይፈርስና ፀንቶ እንዲቆይ ለማድረግ የተከተለው የፓሊሲ አቅጣጫ ነው።

ሆኖም ግን የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 150408 (ቅፅ 23 ይመለከቷል) ጋብቻ በፍች በሚፈርስበት ወቅት ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው ተብሎ በቤተሰብ ህጉ የተደነገውን የፓሊሲ አቅጣጫ መከተል ሳያስፈልግ ከተጋቢዎች አንዱ ጋብቻው በፍች ጥያቄ እንዲፈርስለት አግባብ ባለው ህግ መሰረት ውክልና በመስጠት በወኪሉ ወይም በጠበቃ አማካኝነት የፍች ጥያቄ ፍርድ ቤት በማቅረብ ጋብቻ ማፍረስ ይችላል የሚል አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል።

በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የጋብቻ ፍች በውክልና ለመፈፀም እንደሚቻል የሰጠው ውሳኔ የቤተሰብ ህጉ ጋብቻ ፀንቶ እንዲቆይ ለማድረግ በፍች ጥያቄ ወቅት ከተከተለው የፓሊስ አቅጣጫ አንፃር አግባብነቱን፣ ለውሳኔው መሰረት ያደረገውን የህግ ትርጉም ትንተና ዘዴ አሳማኝነትና ቅቡልነት እንዲሁም ቤተሰብ ተቋም ላይ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ እናጠይቃለም።

የቤተሰብ ጥበቃ፡ ጠቅላላ

በኢፌድሪ ሕገ-መንግሥት በአንቀፅ 34(3) ቤተሰብ የሕብረተሰቡ የተፈጥሮአዊ መነሻ እንደሆነ እና ከመንግሥትና ከህብረተሰብ ጥበቃ የማግኘት መብት እንዳለው ይደነግጋል።  የዚህ ጥበቃ ዋናው ምክንያት ትዳሩ ሰላማዊና ጤናማ በሆነ መልኩ ቀጥሎ  የህብረተሰቡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ  ነው፡፡ መንግስት አስተዳደራዊና ሥነ ሥርዓታዊ በሆነ መልኩ ለቤተሰብ ጥበቃ ያደርጋል። አስተዳደራዊ ጥበቃ መሰረት የሚያደርገው መንግስት ከጋብቻ በፊትና በኋላ ቤተሰብ ፀንቶ እንዲቆይ የሚያስችሉ የምክር አገልግሎት፣ ትምህርትና ስልጠና  በመስጠት፣ በመስኩ የተሰማሩትን በመደገፍና እውቅና በመስጠት ይሆናል። ይህ ተግባርና ሃላፊነት በአዋጅ ቁጥር 1263/2014 በአንቀጽ 36 ለሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ተሰጥቶታል፡፡ እንዲሁም የቤተሰብ ችሎት በማቋቋም፣ የዳኞች አሿሿም እና ችሎት አመራር ልምድና ብቃትን መሰረት ያደረገ እንዲሆን የሚያደርግ የፍርድ ቤት አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ይሆናል። ሥነ ሥርዓታዊ ጥበቃ ሕግን መሰረት ያደረገ ሲሆን ጋብቻ ሲፈፀም፣ በጋብቻ ውስጥ እና ሲፈርስ ግንኙነቱ የሚመራበትን ሥነ ስርዓት በመደንገግ ቤተሰብ ፀንቶ እንዲቆይ ጥበቃ ይደረጋል። የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የወጣበት ዋና ዓላማ ለቤተሰብ ጥበቃ ለመስጠት እንደሆነ በመግቢያው ላይ ተገልፁዋል፡፡ ይህ ፅሁፍ ትኩረት የሚያደርገው አጠቃላይ የጥበቃ አይነቶች ላይ ሳይሆን የቤተሰብ ሕጉ ጋብቻ በፍች በሚፈርስበት ወቅት ከሚከተለው የጥበቃ የፓሊሲ አቅጣጫ አንፃር ሰበር ሰሚ ችሎቱ ፍች በውክልና መፈፀም እንደሚቻል የሰጠውን አስገዳጅ ውሳኔ አግባብነት ካላቸው የቤተሰብ ህጉ ድንጋጌዎች አንፃር ለመመርመር በመሆኑ በሚቀጥሉት ክፍሎች በዚኁ ላይ ብቻ ትኩረት እናደርጋለን፡፡

በፍች ወቅት የሕግ ጥበቃ የፓሊሲ አቅጣጫ

በጋብቻ ሕይወት ውስጥ በልዮ ልዮ ምክንያቶች የትዳር አጋሮች ጋብቻው እንዲቀጥል ማድረግ የሚሳናቸው ጊዜ ያጋጥማል፡፡ በዚህ ሁኔታ ደግሞ በህጋዊ መንገድ የተመሰረተው ጋብቻ ህጉን በጠበቀ አግባብ መፍረስ አለበት፡፡ በቤተሰብ ህጋችን ጋብቻ ከሚፈርስባቸው ምክንያቶች አንዱ በፍርድ ቤት የፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ ነው(አንቀጽ 83(ሐ) ይመለከቷል)፡፡ ባልና ሚስቱ ትዳራቸውን በፍቺ ማፍረስ የሚችሉት እንዲሁ በገዛ ፈቃዳቸ “በቃኸኝ በቃሺኝ” በማለት በመለያየት ለየብቻ በመኖር ሳይሆን የቤተሰብ ህጉ ያስቀመጠውን ስነ-ስርዓት በማክበር እና በመከተል ይሆናል፡፡ በቤተሰብ ህጋችን በአንቀጽ 76 መሰረት ጋብቻ በፍቺ ሊፈርስ የሚችለው ባልና ሚስቱ በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑና ይህንኑ ለፍርድ ቤት አቅርበው ውሳኔው ተቀባይነት ሲያገኝ ወይም ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱ ተጋቢዎች በአንድነት ጋብቻው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነው፡፡ የፍች ስምምነት ወይም ጥያቄ ከቀረበ በኋላ ፍርድ ቤቱ ጋብቻው ፀንቶ እንዲቆይ ለማድረግ መከተል ያለበትን ሥነ ሥርዓት ደንግጓል (አንቀፅ 76- 82 ይመለከቷል)። ፍርድ ቤቱ ጋብቻው በፍች እንዲፈርስ የፍች ስምምነት ወይም ጥያቄ ሲቀርብለት ባልና ሚስቱን በተናጠልም ሆነ በአንድነት በማነጋገር የፍችው ጥያቄ የሚቀርበትንና አለመግባባቱ በስምምነት ለመፍታት የሚችሉበትን ሁኔታ ለመፍጠር እንዲችሉ እንዲያግባባ የቤተሰብ ህጉ በአንቀጽ 78(1) እና 82(1) ይደነግጋል፡፡ ከዚህ ድንጋጌ የምንረዳው ዳኛው በፍቺ ጉዳይ ያለውን የአስታራቂነት ሚና ሲሆን ጋብቻው ፀንቶ እንዲቆይ ባልና ሚስቱ በመካከላቸው ያለው አለመግባባት እንዲፈቱ የማግባባት እና የመምከር ሃላፊነት እንደተሰጠው ነው፡፡ ሕግ አውጭው ጋብቻው በቀላሉ ሊታከሙ በሚችሉ አለመግባበቶች ምክንያት በፍች እንዳይፈርስ የሚያስችል የሕክምና ስልትን (Therapeutic Approach) እንደ ፓሊሲ አቅጣጫ ተከትሏል፡፡ ለዚህም የቤተሰብ ችሎት በማቋቋም፣ ልምድ ያለቸውን ዳኞች በመመደብ፣ ለዳኞች የአስታራቂነትና የማማከር ስልትና ዘዴዎች ስልጠና በመስጠት እና ሌሎች አስፈላጊ አስተዳደራዊ እርምጃዎችን በመውሰድ ጋብቻ ፀንቶ እንዲቆይ በማድረግ ለቤተሰብ ጥበቃ ይደረጋል፡፡

ፍርድ ቤቱ ይህን የአስታራቂነት ሕክምናውን የሚፈፅመው ደግሞ ባልና ሚስቱን በአንድነት ወይም በተናጠል በማነጋር ነው፡፡ ይህም ማለት  ባልና ሚስቱ በውክልና ሳይሆን ግዴታ በአካል መቅረብ ይገባቸዋል፡፡ ፍች በውክልና ይፈፀም ቢባል ህጉ የሚከተለውን የቤተሰብ ጥበቃ ፓሊሲ ማሳካት አይቻልም፡፡ ሕግ አውጭው ይህ ሃሳብ ቢኖርው ኖሮ ‹‹እንዳስፈላጊነቱ›› የሚል ቅፅል በማስገባት ለፍርድ ቤቱ ፍቅድ ስልጣን ይሰጠው ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ጋብቻ በልዩ ሁኔታ  ሲፈጠር በውክልና መፈፀም እንደሚቻል በግልፅ በቤተሰብ ሕጉ በአንቀጽ 12 እንደተደነገገው ፍችም በተመሳሳይ በልዩ ሁኔታ የሚፈጸምበትን ሁኔታ ይደነግግ ነበር፡፡ በመሰረቱ ፍች እና ጋብቻ ምስረታ ፍፁም የተለያዩ ሕጋዊ ተግባራት ሲሆኑ በእነዚህ ተግባራት ላይ ሕግ አውጭው ቤተሰብን ከመጠበቅ አንፃር የተለያየ ፓሊሲ ተከትሏል፡፡ በልዩ ሁኔታ ጋብቻ በውክልና እንዲፈፀም በማድረግ ቤተሰብ እንዲመሰረት እድል የፈጠረ ያበረታታ ሲሆን በፍች ወቅት ግን ቤተሰብ በተቻለ መጠን ፀንቶ እንዲቆይ የሚያስችል ሥነ-ስርዓት አበጅቷል፡፡ የባልና ሚስቱን በአካል መቅረብ አስገዳጅ ሁኔታ መሆኑን የሚያጣናክርልን የፍርድ ቤቱ የአስታራቂነት ሚና ውጤት ያላገኘ እንደሆነ ቀጣይ የሚከተላቸው ስነ-ስርዓታዊ ድንጋጌዎች ናቸው፡፡ ከፍርድ ቤት ውጭ ራሳቸው በሚመርጧቸው ሽማግሌዎች አማካይነት ጉዳያቸውን በዕርቅ እንዲጨርሱ ወይም በዕርቅ ለመጨረስ ያልተስማሙ እንደሆነ ከሶስት ወር የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ ለመወሰን የባልና ሚስቱ በአካል መገኘት አስፈላጊ እንደሆነ መረዳት እንችላለን፡፡ በአጠቃላይ ፍርድ ቤቱ ይህን ሃላፊነቱን ሊከተለው ወይም ላይከተለው የሚችለው ፍቅድ ስልጣን ሳይሆን ህግ አውጭው የሕብረተሰብ የተፈጥሮ መነሻ የሆነው ቤተሰብ በቀላሉ በፍች እንዳይፈርስና ፀንቶ እንዲቆይ ለማድረግ የተከተለው የፓሊሲ አቅጣጫ ነው።

የሰበር ውሳኔ ተቃርኖ

የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 150408 (ቅፅ 23 ይመለከቷል) ጋብቻ በፍች በሚፈርስበት ወቅት ፍርድ ቤቱ ሊከተለው የሚገባው ተብሎ በቤተሰብ ህጉ የተደነገውን የፓሊሲ አቅጣጫ መከተል ሳያስፈልግ ከተጋቢዎች አንዱ ጋብቻው በፍች ጥያቄ እንዲፈርስለት አግባብ ባለው ህግ መሰረት ውክልና በመስጠት በወኪሉ ወይም በጠበቃ አማካኝነት የፍች ጥያቄ ፍርድ ቤት በማቅረብ ጋብቻ ማፍረስ ይችላል የሚል አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል። ችሎቱ ፍች በውክልና እንደሚቻል በምክንያትነት ያቀረበው የቤተሰብ ሕጉ በአንቀፅ 12 ጋብቻ ለመፈጸም በልዩ ሁኔታ በውክልና እንደሚቻል ህጉ እየፈቀደ የፍቺ ጥያቄ በውክልና ሊቀርብ አይችልም በማለት የሚቀርበው ክርክር ተቀባይነት የለውም የሚል ነው፡፡ ሁለቱን ሕጋዊ ተግባሮች አንድ አድርጎ በማመሳሰል፣ ሕጉ በልዩ ሁኔታ ጋብቻ በውክልና መመስረት ከተቻለ ፍች እንዲሁ በውክልና መፈፀም ይቻላል የሚል ትርጉም ሰጥቷል፡፡ ችሎቱ የማመሳሰል ትርጉም ላይ ትኩረት ከማድረግ በዘለለ በሁለቱ ሕጋዊ ተግባሮች መካከል ያለውን ልዩነት እና ሕግ አውጭው የተከተለውን የቤተሰብ ጥበቃ የፓሊሲ አቅጣጫ ለውሳኔው ግብአት አላደረገም፡፡ ጋብቻ ምስረታ እና ፍች ፍፁም የተለያዩ ሕጋዊ ተግባራት ሲሆኑ በእነዚህ ተግባራት ላይ ሕግ አውጭው ቤተሰብን ከመጠበቅ አንፃር የተለያየ ፓሊሲ ተከትሏል፡፡ በልዩ ሁኔታ ከባድ ሁኔታ ሲያጋጥም ጋብቻ በውክልና እንዲፈፀም በማድረግ ቤተሰብ እንደፈጠር እድል በመፍጠር ያበረታታ ሲሆን በፍች ወቅት ግን ቤተሰብ በተቻለ መጠን ፀንቶ እንዲቆይ የሚያስችል ሥነ-ስርዓት አበጅቷል፡፡ ሕግ አውጭው ጋብቻው በቀላሉ ሊታከሙ በሚችሉ አለመግባበቶች ምክንያት በፍች እንዳይፈርስ የሚያስችል የሕክምና ስልትን እንደ ፓሊሲ አቅጣጫ ተከትሏል፡፡ ፍርድ ቤቱ ይህን የአስታራቂነት ሕክምናውን የሚፈፅመው ደግሞ ባልና ሚስቱን በአንድነት ወይም በተናጠል በማነጋር ነው፡፡ ይህም የሚፈፀመው ባልና ሚስቱ በእንደራሴ ተወክለው ሳይሆን ግዴታ በአካል መቅረብ ነው፡፡ ሆኖም ግን ሰበር ሰሚ ችሎቱ ይህን ድንጋጌ በተቃረነ መልኩ የጋብቻ ፍቺ በውክልና መፈፀም እንደሚቻል አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመስጠት በፍች ጥያቄ ወቅት ቤተሰብን ለመጠበቅ ጋብቻው ፀንቶ እንዲቆይ ፍርድ ቤት ሊከተላቸው የሚገቡ በቤተሰብ ሕጉ የተደነገጉ ድንጋጌዎችን ተፈፃሚነት ቀሪ አድርጓል፡፡

በፍች ወቅት የጠበቃ ሚና

ሰበር ሰሚ ችሎቱ የጋብቻ ፍቺ በውክልና መፈፀም እንደሚቻል ፍችን የተመለከቱ ድንጋጌዎችን እና የፓሊሲ አቅጣጫ በተቃረነ መልኩ አስገዳጅ የሕግ ትርጉም እንደሰጠ ተመልክተናል፡፡ በዚህም መሰረት ጠበቃ ፍችን በማስገኘት ላይ ተመስርቶ የጥብቅና አገልግሎት መስጠት የሚችል ቢሆንም ተግባራዊ የሚሆን አይደለም፡፡ የመጀመሪያው በፍች ወቅት ፍርድ ቤት የጥበቃ ዓለማውን ለማሳካት የባልና ሚስቱ ሁለቱም ወይም አንዳቸው በጠበቃ ተወክለው ሳይሆን ግዴታ ፍርድ ቤት በአካል መገኘት አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ፍርድ ቤት የጋብቻ ፍቺን ጉዳይ በመደበኛ የክርክር ሥርዓት (adjudication) የሚመራው ሣይሆን ባልና ሚስቱን በማስማማት ጋብቻው ፀንቶ እንዲቆይ የአስታራቂነት ወይም የአስማሚነት ሚና ያለው ከመሆኑ አኳያ ጠበቃ በፍቺው ጉዳይ የሚያስረዳው የክርክር ጭብት አይኖርም፡፡ በመሆኑም አንድ ጠበቃ ፍቺን በተመለከተ ፍርድ ቤት የሚቀርብ የፍቺ ማመልከቻ ከማዘጋጀትና የምክር አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ አንዳቸውን በመወከል ፍርድ ቤት ፊት ቀርቦ ፍች እንዲወሰን ማድረግ አይችልም፡፡

በአጠቃላይ የሰበር ውሳኔው አስገዳጅ የሕግ ትርጉም በመሆኑ ወደፊት በቤተሰብ ችሎት አመራር፣ በጠበቃና ፍርድ ቤት ግንኙነት ላይ እንዲሁም በጠቅላላው በቤተሰብ እና በማህበረሰብ ላይ የሚፈጥረው አሉታዊ ተፅዕኖ ከፍተኛ ስለሚሆን ከአሁን አስፈላጊው እርመጃ መወሰድ ይገባዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ከውርስ ኃብት ክፍፍል ጋር የተያያዙ አንዳንድ ነጥቦች ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤ...
የከተማ መሬት ሕግ በአዲስ አበባ - ክፍል አንድ - የሚል የሕግ መጽሐፌን በማሳ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024