Font size: +
10 minutes reading time (2031 words)

በሠራተኛ ቅጥር ሂደት ስለሚፈፀም የኋላ ታሪክ ፍተሻ፣ አስፈላጊነት እና ሕጋዊነት

መግቢያ

በዚህ የውድድር ዘመን አሰሪዎች ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት ወይም ምርት በጥራት እና በፍጥነት ለደንበኞቻቸው ማቅረብ ይገባቸዋል። ከዚህም ባለፈ አንዳንድ ሙያዎች በባህሪያቸው በአደራና እምነት ላይ የተመሰረቱ (positions of trust) ስለሆነ ሰራተኛው ለዚህ የሥራ መደብ የተገባ መሆን ይገባዋል።  በመሆኑም አሰሪዎች መልካም ስማቸውን ጠብቀው የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ እና በሰለጠነ የሰው ሃይል ተቋማቸውን ያጠናክራሉ። ሆኖም ግን የሰው ሃይል ቅጥር በሚፈፅሙበት ወቅት ከግለሰብ የግል ባህሪ እና በዲጅታል ቴክኖሎች መሳሪያዎች ሀሰተኛ ሰነድ ለማዘጋጀት ከመቼው ጊዜ በላይ ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ ረቂቅ፣ በቀላሉ የሚገኝና ተግባር ላይ የሚውል በመሆኑ የቅጥር መስፈርቱን የማያሟላ እና ለስራው ትክክለኛና ተገቢ ያልሆነው ስራተኛ እንዲቀጥሩ በማድረግ ከገበያ ተወዳዳሪነት የሚያስወጣ የስጋት ተጋላጭነታቸውን አሳድጎታል።

በአደጉ ሃገራት ይህን ችግር ለመፍታት በቅጥር ሂደት ወቅት የሥራ ቅጥር አመልካቹን የኋላ ታሪክ ህግን በተከተለ መልኩ በሦስተኛ ወገን መርማሪዎች ወይም አሰሪዎቹ በራሳቸው በማጣራት ትክክለኛ የትምህርት ማስረጃ፣ የሥራ ልምድ፣   የስነ ልቦና እና የአካል ብቃት ያለውን በመቅጠር መልካም ስማቸውን እና የኢንዱስትሪ ሰላማቸውን በማረጋገጥ የገበያ ተወዳዳሪነታቸውን ያረጋግጣሉ። 

በሃገራችንም በቅጥር ወቅት የኋላ ታሪክን የመፈተሽ ተግባር ከላይ የተመለከቱትን የስጋት ተጋላጭነቶችን ታሳቢ ባደረገ መልኩ በአግባቡ ምርመራ ሲደረግ አይስተዋልም። በመንግስት መስሪያ ቤት ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሰራተኞችን የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል። የዚህ ፅሁፍ ፀሃፊ በተሳተፈበት የመንግስት ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ ማጣራት ተግባር በሃሰት በተዘጋጀ የትምህርት ማስረጃ ወይም አግባብነት ባለው ባለስልጣን እውቅና ባልተሰጣቸው ኮሌጆች ተምረው የተቀጠሩ ሰራተኞች ሊገኙ ችለዋል።  በዚህም የመንግስት ሃብት ተገቢነት በሌላቸው ሰራተኞች ከመባከኑም ባለፈ ደረጃውን ያልጠበቀ አገልግሎት ለሕብረተሰቡ በመስጠት የመልካም አስተዳደር እጦት እና ለብልሹ አሰራር መስፋፋት እንደ አንድ ገፊ ምክንያት ሊጠቀስ እንደሚችል ይታመናል። በማጣራት ሂደቱ ሰራተኞቹ የተማሩበት ኮሌጆች እና ዪንቨርስቲዎች የፍተሻውን ህጋዊነት ከግላዊነት መብት(Privacy right) ጥበቃ አኳያ  መረጃዎቹን ሊሰጡ የሚችሉት ተመራቂ የቀድሞ ተመሪዎቻቸው ፍቃዳቸውን የሰጡበት ህጋዊ ሰነድ ወይም የፍርድ ቤት ማዘዣ ካልቀረበ መረጃውን አሳልፈው እንደማይሰጡ ክልከላ ሲያደርጉ ተስተውለዋል። 

በመሆኑም በዚህ ፅሁፍ በቅጠር ወቅት የኋላ ታሪክ ፍተሻ አስፈላጊነት፣ በሃገራችን ተግባሩን የሚፈቅድ ወይም የሚከለክል ህግ ስለመኖሩ፣ የህግ ወሰን ወይም ቅድመ ሁኔታ ከኖረ ይህንኑ አክብሮ የኋላ ታሪክ ፍተሻ ስለሚደረግበት ሁኔታ አግባብነት ካላቸው የሃገራችን ህጎችን አንፃር እንመለከታለን። 

"እመን ግን አረጋግጥ"

በስራ ቅጥር ሂደት የሚፈፀም የኋላ ታሪክ ፍተሻ (background screening) (ከዚህ በኋላ "ፍተሻ" ወይም "ምርመራ" እየተባለ የሚገለፀው) አሰሪ የሥራ ውል ከመፈፀሙ በፊት የሥራ ውድድር መስፈርቱን አሟልቶ ለቅጥር ብቁ የሆነውን አመልካች ወይም እጩ ሰራተኛ የትምህርት የስራ ልምድ ከወንጀል ነፃ ማስረጃ እና ሌሎች አስፈላጊ ማስረጃዎችን ትክክለኝነት በራሱ ወይም በሶስተኛ ወገን የሚፈትሽበት አሰራር ነው። ከላይ በመግቢያው ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ከአንዳንድ ስራዎች ተፈጥሮ አስገዳጅነት፣ የሰራተኛው የግል ባህሪና ጤንነት እና ከዲጅታል ቴክኖሎጂ የኪሳራ ስጋትት አጋላጭነት አንፃር አሰሪዎች በመተማመን ላይ የተመሰረተ የሰራተኛ የቅጥር ሁኔታን ለማቆም ተገደዋል። 

ውቧ ቀስተ ደመና ያለ ካፊያ ዝናብ አትወጣም እንዲሉ የዲጅታል ቴክኖሎጂ በሚያስደምም ሁኔታ ለሰው ልጅ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታን ያስገኘ ቢሆንም በተቃራኒው ለእኩይ ተግባር መዋሉ አልቀረም። ለእኩይ ተግባር በመዋል ረገድ ሃሰተኛ የትምህርት ማስረጃ፣ የሥራ ልምድ እና የመልካም ስነ ምግባርና የሥራ አፈፃፀም የምስክር ወረቀቶችን ፍፁም ለመለየት በሚያስቸግር መልኩ (deepfake)  ለማዘጋጀት ጥቅም ላይ እያዋለ ይገኛል። ማህበራዊ ሚድያዎችም የሰራተኛን ምርታማነት በሚቀንስ ሁኔታ ጊዜን እና ትኩረትን ከስራ ላይ በመስረቅ በአሰሪዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ ይገኛሉ። ከግለሰብ ባህሪ የሚመነጭ የስራ ከባቢ  አምባጓሮን እና ምርታማነት የመቀነስ  ስጋትን ቀድሞ ለመከላከል የቀደመ የወንጀል ጥፋተኝነት እና የዕፅ ወይም የአልኮል ወይም የማህበራዊ ሚድያ ሱሰኝነት በቅጥር ወቅት እንዲያጣሩ ተገደዋል። ለዚህም ነው፣ የግል የምርመራ ተቋማት የዘመኑ ቴክኖሎጂ ረቂቅነት እና በቀላሉ ተደርሽ ሆኖ ለእኩይ ተግባር እየዋለ መሆኑን ተረድተው ለደንበኞቻቸው "እመን ግን አረጋግጥ" የሚል ምክር በመለገስ ቅድመ መከላከል ላይ ያተኮረ የሰራተኛ ቅጥር ፓሊሲ እንዲከተሉ የሚያደርጉት። ከዚህ አንፃር በሌሎች ሃገሮች አሰሪዎች የሰራተኛ ቅጥር ውል ከመፈፀማቸው በፊት የአመልካቹን የኋላ ታሪክ በተመለከተ ትኩረት አድርገው የሚመረምሩዋቸውን ጉዳዩች እና አስፈላጊነት ለማየት እንሞክራለን። 

  • የትምህርት ማስረጃ

የትምህርት ማስረጃ የአንድን ተቀጣሪ በሙያው መስክ ያለውን ዕውቀት እና ክህሎት የሚመዘንበትና ተገቢነቱ የሚረጋገጥበት ነው። ዘመኑ ከደረሰበት የዲጅታል ቴክኖሎጅ እድገት አንፃር የትምህርት እና ሌሎች ማስረጃዎች ፍፁም በተመሳሰለ መልኩ ሰዉ ሰራሽ የአስተውሎት ቴክኖሎጁን ( AI generated deepfake text and images) በመጠቀም በቀላሉ ላሊዘጋጁ ይችላሉ። እንዲሁም የትምህርት ጥራትና ብቃት ማረጋገጫ ተቋም ፍቃድ ባልሰጣቸው የትምህርት ተቋማት ተምረው ወይም አስፈላጊውን የምዘና ፈተና ሳያልፉ ሃሰተኛ ማስረጃ ይዘው ለቅጥር የመቅረብ ሁኔታ ይታያል። 

በመሆኑም በሙያው ሳይማር ወይም ሳይሰለጥን በተለያየ መልኩ የሃሰት የትምህርት ማስረጃ በማዘጋጀት መንግስትና በግል ተቋማት በመቀጠር ያልተገባ ጥቅም በማግኘት ሃብት ከማባከናቸው ባለፈ ከሙያው ሊገኝ የሚገባውን ደረጃውን የጠበቀ ጥራት ያለው አገልግሎት ወይም ምርት ባለ መስጠት እና መልካም ስምና ዝና እንዲያጡ ያደርጋል። ከዚህም በተጨማሪ ቀጣሪ ተቋማቱ ተገቢውን የትምህርት ማስረጃ ባልያዘ ሰራተኛ ምርትና አገልግሎት በመስጠታቸው የህግ ተጠያቂነት ሊያስከትልባቸው ይችላል።  

በመሆኑም የተቀጣሪዎችን የትምህርት ማስረጃ በማረጋገጥ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ቀድሞ ማስወገድ ይገባል። 

  • የሥራ ልምድ

ብዙውን ጊዜ ከመቀጠር ፍላጎትና ጉጉት የተነሳ ስራ ቅጥር አመልካቾች የቀደመ የሥራ ልምድን በተመለከተ የተጋነነ ወይም የተሳሳተ መረጃ እንደሚሰጡ ጥናቶች ያመለክታሉ። አሰሪዎቹም ይህን ስለሚያውቁ ትክክለኛ የስራ ልምድ ያለው ስለመሆኑ ማረጋገጥ እንዳለባቸው ያምናሉ። ይህ የማረጋገጥ ተግባር የሰራተኛውን ልምድ ብቻ ሳይሆን ስለ ታማኝነቱ፣ ስብዕናውን እና ተረጋግቶ ለረዥም ጊዜ ከአሰሪው ጋር የመዝለቅ ባህሪውን ለማወቅ ይጠቅማል። በመሆኑም ተቀጣሪው ያቀረበው የስራ ልምድ ከተረጋገጠው ጋር ልዩነት ወይም አለመጣጣም ካለ ስለዚሁ ጉዳይ ለመጠየቅ እድል ይሰጣል፣ ወደፊት ሊኖራቸው የሚችለውን መተማመን ላይ የተመሰረተ ግንኙነት አስቀድሞ በማወቅ መረጃ ላይ የተመሰረት መሰረተ የቅጥር ውሳኔ ለማሳለፍ ይረዳል።  የስራ ልምድን ማረጋገጥ አመልካቹ ስራ የጀመረበትን እና ያቆመበትን ቀን፣ የስራ ተግባርና ሃላፊነት፣ ደሞዝና ጥቅማጥቅም፣ እና ሥራውን ያቋረጠበትን ወይም ለመልቀቅ ያቀረበውን ምክንያት ለማወቅ ያስችላል። 

  • የቀደመ ወንጀል ጥፋተኝነት ታሪክ

የአንድን ሰው ግለ ታሪክ ለማወቅ ስንነሳ መጀመሪያ ወደ አይምሮችን የሚመጣው የቀደመ የወንጀል ጥፋተኝነት እንዳለው ማጣራት ነው። የወንጀል ጥፋተኝነት ታሪክ ስለ ሰውየው ባህሪ ብዙ ነገር እንድንረዳ ያግዘናል። ይህም ተቀጣሪው ደንበኞች ላይ ስጋት ይፈጥራል ወይም  ምቹ ያልሆነ የስራ ከባቢ ይፈጥራል ወይስ አይፈጥርም የሚለውን ለመወሰን፣ ወንጀሉ ከስራው ባህሪ እና ከሙያው ጋር የተያያዘ መሆን አለመሆኑን ለማወቅ ለአሰሪው እድል ይሰጠዋል። ከዚህም በተጨማሪ በተለይም እምነት ላይ የተመሰረቱ የሥራ መደቦች(Trust positions) በትክክለኛና ተገቢነት ባላቸው ሰራተኞች እንዲያዙ እድል ይሰጣል። መምህራን፣ የሂሳብ ባለሙያዎች፣ ከፍተኛ የአስተዳደር ቦታዎች፣ የመንግስት ስራተኛ ወዘተረፈ በአደራ እና በእምነት የሥራ ግንኙነት ላይ የሚመሰረቱ የስራዎች ናቸው።  በመሆኑም እጩ ሰራተኛው የቀደመ የወንጀል ጥፋተኝነት ማረጋገጥ ተገቢ ይሆናል። በፌደራል እና ክልል ፓሊስ ተቋማት የወንጀል ሪከርድ ማጣራት ያስፈልጋል። 

  • ምስክርነትን ማረጋገጥ (Reference Check)

አንድ ዕቃ ከመግዛታችን በፊት ከዚህ ቀደም ገዝተው የተጠቀሙትን ስለጥንካሬው፣ ምቾቱና ጥራቱ እንጠይቃለን። በቅጥር ወቅትም አሰሪው ስለሰራተኛው ባህሪ፣ የስራ ትጋት፣ በቡድን የመስራት ብቃት፣ ለሙያው አበርክቶቱ፣ ስነ ምግባርና ሌሎች ጉዳዮች ምስክርነት ከሰጠው ባለሙያ ወይም ሃላፊ የማረጋጥ ይገባል። ይህ የማረጋገጥ ተግባር ከትምህርትና ከስራ ልምድ ይለያል። የምስክርነት ማረጋገጫ ትኩረት የሚያደርገው የሰራተኛውን የስራ አፈፃፀም እና አመለካከቱን ለመለየት ነው። ከስራ ቅጥር ማመልከቻው ከተመለከተው ምስክርነት ባለፈ ከቀድሞ ስራ ባልደረቦቹና ከሌሎች ሃላፊዎች ሊወሰድ ይችላል። 

  • የአልኮል ምርመራ Drug Screening

አካላዊ እና አይሞሮአዊ ጤንነቱ የተጠበቀ ሰራተኛ ለማንኛውም የስራ ዓይነት እና ሁኔታ አስፈላጊ ነው። ምርታማነት እና የአገርልግሎት ጥራት እንደሚጨምር እሙን ነው። ይህ ጤነኝነት ከሚረጋገጥባቸው መንገዶች አንዱ የዕፅ እና የአልኮል ምርመራ ነው። የተቀጣሪው ደም ውስጥ አደገኛ ዕፅ ወይም አልኮል ስለመኖሩ ማረጋገጫ ይሰጣል። ይህም ከሱስ በሚመነጭ የስራ አፈፃፀም ብቃት ማነስን፣ ከሰራተኛ ወይም ከደንበኛ ጋር የሚደረግ አምባጓሮን እና ጉዳትን ለመስቀረት ይረዳል። በተለይም የሥራ ባህሪው ይህን ቅድመ ሁኔታ እንዲያሟላ ሊጠይቅ ይችላል።  በአየር መንገድ እና በሹፍርና ቅጥር በአስገዳጅ ሁኔታ የአልኮል እና እፅ ምርመራ ሊደረግ ይገባል። 

በሃገራችን የኋላ ታሪክ ፍተሻ ሕጋዊነት 

የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 የስራ ቅጥር በሚፈፀምበት ወቅት አሰሪው የስራ ቅጥር አመልካችን የኋላ ታሪክ ስለሚያጣራበት ሁኔታ አልደነገም። ሆኖም ግን ህግ አውጭው አዋጁን ለማውጣት ያስፈለገበትን ዓላማ ከኋላ ታሪክ ፍተሻ አስፈላጊነት ጋር ካመሳከርነው ተገቢነቱን እንረዳለን። አዋጁ መግቢያው ላይ ካስቀመጣቸው ዓላማዎች መካከል አሠሪና ሠራተኛ የጋራ ራዕይ ኖሯቸው የሥራ ግንኙነቶቻቸውን መሠረታዊ በሆኑና በህግ በተደነገጉ መብቶችና ግዴታዎች ላይ በመመስረት አስተማማኝ የኢንዱስትሪ ሰላም፤ የዘላቂ ምርታማነት እና የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም በመፍጠር ሀገራችን ለተያያዘችው ፈጣን የኢኮኖሚ ዕድገት የማስመዝገብ ብሔራዊ ግብ በትብብርና በጋራ እንዲሰሩ ማድረግ ሊያሳካው የሚፈልገው አንዱ ዓላማ እንደሆነ ይገልፃል። በመሆኑም አሰሪው የሰራ ቅጥር በሚፈፅምበት ወቅት የኌላ ታሪክ ፍተሻ ማከናውኑ በዋናነት ያልተገባ ሰራተኛ ቀጥሮ የኢንዱስትሪ ሰላሙን፣ ምርታማነትን እና የገበያ ተወዳዳሪነቱን እንዳያጣ አስቀድሞ ለመከላከል ስለሆነ የአዋጁን አላማ ያሳካል። በተጨማሪም ምርመራው የሚከናወነው የስራ አመልካቹ የሥራ መደቡ ላይ ለመቀጠር አስፈላጊ መስፈርቶቹን ስላማሟላቱ የሚያስረዱ የትምህርት፣ የስራ ልምድ እና ሌሎች ማስረጃዎችን በፍቃዱ ያቀረባቸውን መሰረት በማድረግ ስለሆነ በሁሉቱ መካከል ወደፊት ስለሚኖራቸው መተማመን የሚረገጥበት የመጀመሪያው አጋጣሚ በመሆኑ ሊበረታታ አመላካቹ የተሳሳተ መረጃ ካቀረበ ከቅጥሩ በፊት እምነት ሊጣልበት የማይገባ ስለመሆኑ ከወዲሁ ማረጋገጥ ያስችለዋል ። 

 

የፌደራል የመንግስት ሰራተኞች አዋጅ ቁጥር 1064/201 የሰራተኛ ቅጥር በሚፈፀምበት ወቅት በምልምላና መረጣ ሂደት አመልካቹ ሊያሟላ ስለሚገባው ቅድመ ሁኔታ ከመደንገግ ውጭ ስለ ኋላ ታሪክ ፍተሻ የሚለው ነገር የለም። ከአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ የሚለየው በመርህ ደረጃ በአመልካቾች መካከል በብሄረሰብ፣ በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣ በአካል ጉዳት፣ በኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ወይም በሌላም ሁኔታ በሥራ ፈላጊዎችም መካከል ልዩነት ማድረግ የሚከለከል ቢሆንም የመንግስት ሰራተኛ ለመሆን ብቁ የማያደርጉ ሁኔታዎችን በግልፅ አስቀምጧል፡፡ እነዚህም ቅጣቱ ከተፈጸመ፣ በይርጋ ከታገደ ወይም በይቅርታ ከተሠረዘ በኋላ አምስት ዓመት ያለፈው ካልሆነ በስተቀር የሙስና፣ የእምነት ማጉደል፣ የስርቆት፣ የማጭበርበር ወይም የአስገድዶ መድፈር ወንጀል ፈጽሞ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት የተፈረደበት ማንኛውም ሰው፣ ብቃት ማረጋገጫ ማስረጃ የሌለው ሰው፤ በዲስፕሊን ጉድለት ምክንያት ከሥራ የተሰናበተ ሰው ከሥራ ከተሰናበተበት ጊዜ ጀምሮ አምስት ዓመት ከመሙላቱ በፊት በመንግሥት ሠራተኛነት ሊቀጠር አይችልም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ማንኛውም አመልካች በመንግሥት ሥራ ተቀጥሮ ለማገልገል ብቁ መሆኑን ለማረጋገጥ ከኤች.አይ.ቪ./ኤድስ ምርመራ በስተቀር የጤንነት ማረጋገጫ የሕክምና ምርመራ እና ለቅጥር የማያበቁ ተብለው ከተጠቀሱት ወንጀሎች ነጻ መሆኑን የሚያረጋግጥ ከፖሊስ የተሰጠ ማስረጃ የማቅረብ ግዴታ አለበት፡፡(አንቀፅ 13 እና 14 ይመለከቷል) 

የጤና ማረጋገጫ የሕክምና ምርመራ የዕፅ እና የአልኮል ሱሰኝነትን ለማጣራት የሚደረግ ምርመራን ያካትታል ? የሚለው ጥያቄ አከራካሪ በመሆኑ ምላሽ ይሻል። አዋጁ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎች በምልመላና መረጣ ወቅት ያስቀመጠው የመንግስት ሥራ በፍፁም ታማኝነት እና የአገልግሎት ጥራት ደረጃ  መሰራት እንዳለበት ለማመልከት ነው። በመሆኑም ቅድመ ሁኔታዎቹ በሥራ አመልካቹ መሟላታቸውን በአግባቡ የኋላ ታሪኩን በመፈተሽ የቅጥር ውል መፈፀም ይበልጥ የአዋጁን አላማ ያሳካል። 

 

የግላዊነት መብት ጥበቃ (Privcy protection)

በቅጥር ወቅት የሚፈፀም የኋላ ታሪክ ፍተሻ የህገ መንግስት ጥበቃ ካለው የግላዊነት መብት(privacy right) ጋር የሚገናኝ በመሆኑ ህግን ባከበረ መልኩ መፈፀም ይገባዋል። የትምህርት ማስረጃ፣ የጤና ሁኔታ ምርመራ፣ የስራ ልምድ እና ሌሎች ሁኔታዎች በግላዊነት መብት ጥበቃ የሚደረግላቸው ናቸው። በመሆኑም ህግን መሰረት በማድረግ ወይም በግለሰቡ ፍቃድ ካልሆነ በስተቀር በማናቸውም ሁኔታ አይደፈሩም ።(ህገ-መንግስት አንቀፅ 26 እና ፍትህ ብሄር ህግ ስለ ሰዎች መብት የተመለከቱትን ድንጋጌዎች ይመለከቷል)።  በመሆኑም በሥራ ቅጥር ወቅት አመልካቹ ያቀረባቸውን ማስረጃዎች ትክክለኝነት ከሶስተኛ ወገኖች ቀርቦ ለማጣራት ፍቃዱን መስጠት ይገባዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ፀሃፊው የደቡብ ክልል አቃቤ ህግ ሆኖ በሚሰራበት ወቅት ክልል አቀፍ መንግስት ሰራተኞች የትምህርት ማስረጃ የማጣራት ግብረ ሃይል አባል ሆኖ የተሳተፈ ሲሆን ሰራተኞች በተማሩባቸው ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች በመሄድ የማጣራት ተግባር በሚፈፅምበት ወቅት የግላዊነት መብት ጥበቃን መሰረት በማድረግ አንዳንድ ዩንቨርስቲዎች መረጃ አሳልፈው ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ እንደቀረ ያስታውሳል። የዩንቨርስቲዎቹ የመከራከሪያ ሃሳብ ከቀድሞ ተመራቂዎቻችን ይህን የማጣራት ተግባር እንድትፈፅሙ ፍቃዳቸውን የገለፁበት ህጋዊ ውክልና ወይም በፍርድ ቤት የምርመራ ማዘዣ ሳትይዙ መረጃውን እንድንሰጥ አንገደድም፣ አሳልፈን ብንሰጥ ተያቂነት ያመጠብናል የሚል ነበር። በወቅቱ ይህ የመከራከሪያ ሃሳብ ትክክል እና ህጋዊ መሆኑን በመረዳት የሰራተኞቹን ውክልና ለመቀበል እጅግ አስቸጋሪ ሆኖ በመገኘቱ የፍርድ ቤት የምርመራት ትዕዛዝ ማዘዣ በማውጣት ችግሩን ልንፈታ ችለናል። 

በመሆኑም የትምህርት ማስረጃ፣ የጤና፣ የስራ ልምድ ፣ የመልካም ምግባርና የሥራ አፈፃፀም ምስክርነት እና ከወንጀል ነፃ መረጃ ከግላዊነት መብት ጋር እጅግ የተቆራኘ እና ሊከበር የሚገባ በመሆኑ መረጃው ከሚገኝበት ከሶስተኛ ወገን በቅርብ  ለማጣራት የሥራ አመልካቹን ፍቃድ መቀበል አስገዳጅ ቅድመ ሁኔታ ነው። የማጣራት ተግባሩ በአሰሪው ወይም አሰሪው በሚቀጥረው ይህንኑ ለመፈፀም ህጋዊ ፈቃድ ያለው አካል የአመልካቹን ፍቃድ በግልፅ መቀበል ይገባዋል። ከዚህ ጋር አግባብነት ያለው የፍቃድ አሰጣጥ ሂደት በፍትሃብሄር ህጋችን አንቀፅ 2032 መሰረት ውስን ውክልና በመስጠት ይሆናል። ይህ ውስን የውክልና ስልጣን ወካዩ መብቱ እንዳይጎዳ ስልጣኑን በማገደብ ለሚፈለገው አላማ ብቻ እንዲውል በመፍቀድ መብቱን እንዲጠብቅ ያስችለዋል። ከዚህም በተጨማሪ ይህ ውክልና በሰነድ አረጋገጭ ፊት ቀርቦ መረጋገጥና መመዝገብ አለበት። 

 

የግል ምርመራ ተቋማት አስፈላጊነት 

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የምርመራ ተግባሩ በአሰሪው ወይም ይህንኑ ተግባር ለመፈፀም ህጋዊ የሥራ ፈቃድ ባለው አካል መሆን ይገባዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ጉዳይ በሃገራችን የግል የምርመራ ተቋማት ስለሌሉ ተግባሩ የሚፈፀመው በአሰሪው ብቻ እንዲሆን ያስገድዳል። በሌሎች ሃገራት የኋላ ታሪክ የመመርመር ተግባር ፍቃድ ባላቸው የምርመራ ባለሙያዎች እውቀትና ክህሎት በመታገዝ የሚፈፀም ሲሆን ጥራት ያላው መረጃ እንዲያገኙ ያስችላል። በመሆኑም አሰሪዎች ትኩረታቸውን እና ጊዜያቸውን በተቋማቸው ስትራቴጂክ ጉዳዮች ላይ በማዋል ከቅጥር ጋር ተያይዞ ያለውን የኋላ ታሪክ ማጣራት ተግባር ለግል የምርመራ(Private investigation) ተቋማት ይሰጣሉ። የውጭ ሃገር ኢንቨስተሮች ወደ ሃገራችን ሲገቡ የሰራተኛ ቅጥር ሁኔታን በተመለከተ የተቋማቸው ባህል የሆነውን እና በሌሎች ሃገሮች የለመዱትን የኋላ ታሪክ ምርመራ በግል የምርመራ ተቋማት እንዲፈፅምላቸው ስለሚፈልጉ በዚህ ረገድ ክፍተት እንደሚገጥመን ማወቅ ይገባል። በመሆኑም የህግ እና የአስተዳድር ክፍተቶችን በማስተካከል የግል የምርመራ ተቋማት ወደ ሥራ የሚገቡበትን ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። 

 

ማጠቃለያ 

የግል የንግድ ተቋማት አስተማማኝ የኢንዱስትሪ ሰላም፣ ዘላቂ ምርታማነት እና የገበያ ተወዳዳሪነት አቅም በመፍጠር ምርትና አገልግሎታቸውን በማቅረብ የንግድ ትርፍ የማግኘት ዋና አላማ አላቸው። የመንግስት መስሪያ ቤቶችም እንዲሁ በሕዝብ የተጣለባቸውን አደራ በማክበር ጥራትና ደረጃውን የጠበቀ አገልግሎት በመስጠት መልካም አስተዳደርና የህግ የበላይነት እንዲከበር ያደርጋሉ። ሁለቱም አሰሪዎች ይህን አላማቸውን ለማሳካት የሰው ሃብት አስተዳደራቸው ውጤታማ መሆን ይገባዋል። ሆኖም ግን ከአንዳንድ የሥራ ሙያዎች ተፈጥሮ፣ ከግለሰብ ባህሪ እና ከዲጅታል ቴክኖሎጂ በሚመነጭ የችግር ተጋላጭነት ምክንያት ውጤታማ የሰው ሃብት አስተዳደር እንዳይኖር በማድረግ የሚፈልጉትን ዓላም እንዳያሳኩ እያደረገ ይገኛል። ይህን ችግር ለመፍታት ሃገራት በስራ ቅጥር ወቅት የስራ አመልካችን የኋላ ታሪክ አግባብ ያላቸውን ህጎች አክብሮ በመመርመር ተገቢ የሆነውን ብቻ በመቅጠር  ላይ የተመሰረተ የሰው ሃብት አስተዳደር ሥርዓት ዘርግተዋል። በሃገራችን በግል ዘርፉ ብዙም ባይስተዋልም የመንግስት መስሪያ ቤቶች የሰራተኞቻቸውን የትምህርት ማስረጃ በማጣራት የሰው ሃብት አስተዳደራቸውን የማስተካከል ተግባር እየፈፀሙ ይገኛል። የዚህን ተግባር ህጋዊነት አግባብነት ካላቸው ህጎች አንፃር ስንመረምር በህግ በመፍቀድ ወይም በመከልከል ረገድ የተደነገገ ባይሆንም ህጎቹ ሊያሳካኩት ከሚፈልጉት ዓላማ አንፃር በቅጥር ወቅት የሥራ አመልካችን የኋላ ታሪክ ማጣራት ተገቢነት እንዳለው መረዳት እንችላለን። ሆኖም ግን የምርመራ ተግባሩ ከግላዊ መብት ጥበቃ አንፃር በስራ አመልካቹ ሙሉ ፍቃድ ላይ ተመስርቶ መፈፀም ይገባዋል። አሰሪው የምርመራ ተግባሩን መፈፀም የሚችል ቢሆንም ይበልጥ የምርመራ ሙያ እውቀት፣ ክህሎትና ዘዴዎች ባለቤት በሆነ የምርመራ ተቋማት የሚፈፀም ቢሆንም በኛ ሃገር የተለመደ አይደለም። ሃገራችን ወደ ኢንዱስትሪ መር ኢኮኖሚ የምታደርገውን ጉዞ የሚያግዝ በመሆኑ የህግና አስተዳደራዊ ክፍተቶችን በማስተካከል የግል የምረማራ ተቋማት ወደ ሥራ የሚገቡበት ሁኔታ ማመቻቸት ይገባል። 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ስለ ይዞታ እና የቀዳሚነት ግዥ ይገባኛል የማለት መብት
ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ (Provisional Interim measure) እና...
 

Comments 1

Abebe
Guest - Bonsa on Thursday, 27 June 2024 11:46

በእውነት ብዙ ነገር ተምረበታልው በርታ እውቀትክ ይጭመርልክ

በእውነት ብዙ ነገር ተምረበታልው በርታ እውቀትክ ይጭመርልክ
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024