ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ (Provisional Interim measure) እና የፍርድ ቤት ሥልጣን

ይህ ጽሑፍ በግልግል ወይም በእርቅ የሚታዩ ጉዳዮችን ተከትሎ የሚሰጡ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃዎች ወይም ትዕዛዝ ያላቸዉን የሕግ ማዕቀፍ እና ተግባራዊ አፈጻጸም የሚዳስስ ነዉ፡፡

በሕጉ ዘርፍ በአብዛኛዉ  ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ (Provisional Interim measure) ሀሳብ ከግልግል ዳኝነት ሂደቶች ጋር ተያይዞ የሚነሳ  እንደሆነ ብዙ ድርሳኖች  ያወሳሉ፡፡ የብላክስ ሎዉ መዝገብ ቃላትም  ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝን ከዓለም ዓቀፍ የግልግል አሰራር ጋር በማገናኘት ትርጉም የሚሰጠዉ ሲሆን የግልግል ፍርድ ቤት  የሙግቱን ዉጤት ሊጎዳ የሚችልን ያልተገባ ተግባር ለመከላከል ከፍርድ በፊት የሚሰጠዉ ትዕዛዝ እንደሆነና በብሔራዊ ሕጎች ከሚሰጠዉ ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ (temporary injunction) ጋር አቻ እንደሆነ ይገልፀዋል፡፡ 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም አቀፍ የንግድ ሕግ ኮሚሽን (UNCITRAL) ባዘጋጀዉ አለም አቀፍ የንግድ ግልግልና እርቅ ሞዴል ሕግም ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ አንድ የግልግል እና እርቅ አሰራሮች ሊያካትቱት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ ኮሚሽኑ ባዘጋጀዉ ሞዴል ሕግ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ በተለያዬ ምክንያቶች ሊሰጡ እንደሚችሉ ተመላክቷል፡፡ እነሱም የሙግቱን ዉጤት የሚጠብቀዉን  ነገር ነባራዊ ሁኔታ ባለበት ለመጠበቅ ወይም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ፣ የክርክሩን ሂደት ወይም ዉጤት ላይ ጉዳት ሊያደርስ የሚችል ተግባር እንዳይፈጸም ወይም እንዲቆም ለማድረግ፣ ዉሳኔዉን ማስፈፀሚያ ወይም የግልግሉን ወጪ ሊሸፍን የሚያስችል ንብረት ለማስከበር እንዲሁም ለክርክሩ አወሳሰን ወሳኝነት ያላቸዉን ማስረጃዎች ጠብቆ ለማቆየት ሊሰጥ እንደሚችል ይገልፃል፡፡

በተመሳሳይ በእኛ ሀገር ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ ወይም ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ወይም በግልግል ጉባዔ ሊሰጥ እንደሚችል ያለዉ የሕግ ማዕቀፍ ያሳያል፡፡ ከመደበኛ የፍርድ ቤት ክርክር ጋር በተገናኘ ፍርድ ቤቶች የተለያዩ ጊዜያዊ ትዕዛዞችን ሊሰጡ የሚችሉ ሲሆን እነዚህ ትዕዛዞች ጊዜያዊ መፍትሔዎች (provisional remedies) ተብለዉ የሚታወቁት ናቸዉ፡፡ ጊዜያዊ የሚል ስያሜ የተሰጣቸዉ ብቻቸዉን ፀንተዉ ሊኖሩ የማይችሉ ከዋናዉ ክርክር ጋር ተያያዥነት ያላቸዉ በመሆናቸዉ ነዉ፡፡ በፍትሐ ብሔር ሥነ-ሥርዓት ሕጉ እንደ ጊዜያዊ መፍትሔዎች ከተቀመጡት ዉስጥ  በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 151 ንብረት ማስከበር (attachment before judgment) ፣ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 154  ለጊዜዉ የሚሰጥ የማገድ ትዕዛዝ (temporary injunction) እንዲሁም በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 160 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሰረት ከፍርድ በፊት የሚሰጡ ሌሎች ጊዜያዊ ትዕዛዝ (interlocutory orders) ተጠቃሽ ናቸዉ፡፡

ከግልግል እና ዕርቅ አሰራር ጋር በተገናኘ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ ወይም ትዕዛዝ የሚሰጡበት ሁኔታ በግልግል የዳኝነት እና የዕርቅ አሰራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ተመላክቷል፡፡ ይህ አዋጅ በንግድ እና ኢንቨስትመንት ዘርፍ የሚሳተፉ አካሎች አለመግባባታቸዉን ከፍርድ ቤት ዉጪ በሆነ መንገድ ባነሰ ወጪ፣ በአጭር ጊዜ እና ለጉዳዩ ቅርብ በሆነ ባለሙያ በሚሳተፍበት አማራጭ የሙግት መፍቻ እንዲፈቱ ማስቻልን እንደ ዓላማ በማድረግ የተዘጋጀ ነዉ፡፡ አዋጁ ሲወጣ ቀደም ሲል ከነበረዉ የሕግ ማዕቀፍ ሽፋን ያልተሰጣቸዉ የነበሩ የግልግል እና የዕርቅ አሰራሮችን እና ሀሳቦችን አካቶ ይዟል፡፡ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ የሚወሰድበትን ወይም የሚሰጥበት ስርዓትም  በአዋጁ ከተካተቱ ጉዳዮች ዉስጥ አንዱ ነዉ፡፡

ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ ወይም  ትዕዛዝ ለምን ይሰጣል?

ቀደም ሲል እንደተገለፀዉ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ በመደበኛ ፍርድ ቤት ከሚሰጡ ጊዜያዊ የመፍትሔ ትዕዛዝ ጋር አቻ ትርጉም ያለዉ ሲሆን ከሚሰጥበት ዓላማ አንፃርም ተቀራራቢነት ያለዉ ነዉ፡፡ በአዋጁ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የሚሰጡበት ሁኔታዎች እንደ ማሳያ የተመላከቱ ሲሆን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም አቀፍ የንግድ ሕግ ኮሚሽን በሞዴል ሕጉ ከጠቀሳቸዉ ምክንያቶች ጋር ተመሳሳይነት ያላቸዉ ናቸዉ፡፡ በአዋጁ በአንቀፅ 20(2) ስርም ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የሚሰጠዉ አስፈላጊ የሆኑ ማስረጃዎችን ለመጠበቅ፣ የክርክሩ አካል የሆኑ ዕቃዎች እንዲጠበቁ ለማድረግ፣ የግልግል ዉሳኔ ሊያርፍባቸዉ የሚችሉ ሐብቶችና ፈንዶች እንዲጠበቁ ማድረግ፣ ለግልግል ምክንያት የሆነዉ ጉዳይ እስኪወሰን የነበረዉ ሁኔታ እንዲቀጥል ወይም ወደ ነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ እንደሆነ ተመላክቷል፡፡

 

ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ በማን ይሰጣል?

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአለም አቀፍ የንግድ ሕግ ኮሚሽን (UNCITRAL) ባዘጋጀዉ አለም አቀፍ የንግድ ግልግልና እርቅ ሞዴል ሕግ ሆነ የብዙ ሀገሮች ልምድ የሚያሳየዉ የግልግል ጉባዔ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የመስጠት ሥልጣን እንዳላቸዉ ነዉ፡፡ በአብዛኛዉ ሀገሮችም ይህ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ግልግል እና ዕርቅ ከመጀመሩ በፊት ወይም በሂደት ላይ እያለ በፍርድ ቤት ይሰጣል፡፡ ይሁንና ፍርድ ቤቶች የግልግል እና የዕርቅ ሂደት የተሳካና ዉጤታማ እንዲሆን ድጋፍ  መስጠት እንዳለባቸዉ በብዙሀኑ ተቀባይነት ያለዉ አሰራር ቢሆንም መቼ እና እንዴት የሚለዉ ጥያቄ የሚያስነሳ ጉዳይ ነዉ፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ፍርድ ቤቶች በግልግል የተሰጠዉ ጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲፈፀም ድጋፍ በማድረግ ብቻ እንዲወሰኑ ሲያደርጉ  አንዳንዶች ደግሞ የፍርድ ቤቶችን ሚና ድጋፍ በማደረግ ብቻ ሳይወሰኑ በግልግል በሚታይ ጉዳይ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጡ በሚያስችል ደረጃ የሕግ ማዕቀፋቸዉን የሚቀርፁበት ሁኔታ አለ፡፡ በተለይም የዳበረ እና ያደገ የአማራጭ የሙግት መፍቻ ወይም የግልግል ሥርዓት ባልተገነባባቸዉ ሀገሮች ፍርድ ቤቶች የግልግል ሂደት ከመጀመሩ በፊት ሆነ በግልግል ሂደት ላይ እያለ መጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጡ የሚደረግበት ሁኔታ ይስተዋላል፡፡ በተመሳሳይ አዋጅ ቁጥር 1237/2013  ጊዜያዊ መጠባበቂያ እርምጃ የሚወሰድበትን መንገድ አስቀምጧል፡፡  በአዋጁ አንቀፅ 20 እና ተከታይ ድንጋጌዎች የግልግል ጉባዔዉ የመጠባባቂያ ትዕዛዞችን ለመስጠት ሥልጣን እንዳለዉ የተመላከተ ሲሆን  ተዋዋዮች በግልግል ጉባዔዉ ሳይገደቡ ፍርድ ቤት የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸዉ ማመልከትም ይችላሉ፡፡ ለፍርድ ቤት የመጠባበቂያ ትዕዛዙ እንዲሰጥ ሊጠየቅ የሚችለዉ ግልግሉ ከመጀመሩ በፊት ወይም ግልግል ሂደቱ ተጀምሮ ባለበት ሁኔታ እንደሆነ በአንቀፅ 9 እና 27 በግልፅ ተመላክቷል፡፡ በተመሳሳይ በአንቀፅ 55(3) እና 70(2)  መሰረት  በእርቅ እየታዬ በሚገኝ ጉዳይ ላይም ተዋዋይ ወገኖች የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥላቸዉ ፍርድ ቤትን መጠየቅ ይችላሉ፡፡

ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እና አከራካሪዉ የፍርድ ቤት ሥልጣን

በመደበኛዉ የፍርድ ቤት ክርክር  የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰ/መቁ 191402 በሰጠዉና በቅጽ 25 ላይ በሰፈረዉ  የሕግ ትርጉም ዋናዉ የክርክር ጉዳይ እስኪጀመር ድረስ ጊዜያዊ እግድ ሊሰጥ እንደሚችል ያመላከተ ቢሆንም በጊዜያዊነት የሚሰጡ መፍትሔዎች (provisional remedies) እንደ ንብረት ማስከበር፣ ንብረት ማሳገድ እና ሌሎች ከፍርድ በፊት የሚሰጡ ትዕዛዞች በአብዛኛዉ ዋናዉን ክርክር መጀመር ተከትሎ ይሰጡ የነበር ለመሆኑ የፍርድ ቤቶች ልምድ ያሳያል፡፡ ይህ ልምድ የመጣዉ የሥነ-ሥርዓት ሕጉ ጊዜያዊ ትዕዛዝ የሚሰጡበት ሂደት የዋናዉን ክርክር  መጀመር ተከትሎ  የሚሰጥ በሚመስል መልኩ በማስቀመጡ ሲሆን በሰበር ደረጃም ከዋናዉ ክርክር ተነጥሎ ብቻዉን ሊቀርብ እንደሚችል ትርጉም የተሰጠዉ ሕጉ በግልፅ በማስቀመጡ ሳይሆን ትዕዛዙ ከሚሰጥበት ዓላማ አንፃር ታይቶና ተብራርቶ ነዉ፡፡ አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ካካተታቸዉ አዲስ ጉዳዮች አንዱ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ አቤቱታ ራሱን ችሎ ሊጠይቅ የሚችል ዳኝነት መሆኑን በግልፅ ማስቀመጡ ነዉ፡፡ በግልግል ወይም በዕርቅ የሚታዩ ጉዳዮች ከፍርድ ቤት ዉጪ የሚታዩ እንደመሆናቸዉ  ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ እንዲወሰድ የሚቀርበዉ ጥያቄ ፍርድ ቤት የሚቀርበዉ ከዋናዉ ጉዳይ ተነጥሎ በመሆኑ የጊዜያዊ ትዕዛዝ አቀራረብ ላይ አዲስ የሆነ ለዉጥ ማምጣት ችሏል፡፡ ይህ ጊዜያዊ ትዕዛዝ ከዋናዉ ክርክር ተነጥሎ ሊቀርብ የሚችል ከሆነ በመደበኛዉ ክርክርም ይሁን በግልግል በሚታዩ ጉዳዮች  ዳኝነቱ የሚጠየቀዉ  የሥረ-ነገር ሥልጣንን ተከትሎ መሆን አለመሆኑ ጥያቄ የሚያስነሳ ነዉ፡፡ ከፍ ሲል በተጠቀሰዉ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት  የሕግ ትርጉም ጊዜያዊ የእግድ ትዕዛዝ ዋናዉ ክርክር እስኪቀርብ ሊጠየቅ እንደሚችል ከሚገልፅ ዉጪ  ለየትኛዉ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ምላሽ አይሰጥም፡፡ ለምሳሌ ከገንዘብ መጠኑ አንፃር በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሥረ-ነገር ሥልጣን ስር ሊወድቅ የሚችልን ክርክር ጊዜያዊ እግድ ጥያቄ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ማስተናገድ ይቻላል ወይስ አይቻልም የሚለዉን የሚመልስ አይሆንም፡፡ በተመሳሳይ አዋጅ ቁጥር 1237/2013  የተቀረፀዉ ጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዝን ከዋናዉ ጉዳይ ተነጥሎ ብቻዉን እንደ አንድ ዳኝነት ሊቀርብ በሚችል ሁኔታ እንደመሆኑ አቤቱታዉ ለየትኛዉ ፍርድ ቤት ይቀርባል የሚለዉ ጥያቄ ምላሽ የሚያስፈልገዉ ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘም አቤቱታዉ የፍርድ ቤቶችን የሥረ-ነገር ሥልጣን ተከትሎ የሚቀርብ ነዉ ወይስ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ብቻ የሚታይ ነዉ የሚለዉ አከራካሪ ሆኖ ያደረ ጉዳይ ሆኗል፡፡

ይህ ክርክርም በአተገባበርም የታዬ ሲሆን ሕጉ በሁለት ዓይነት መንገድ እንዲተገበር ምክንያት ሆኗል፡፡ የዚህ ጽሁፍ ዓላማም ያለዉን የተለያዬ አተገባበር ከሕጉ አንጻር መቃኘት ግንዛቤ መፍጠር በመሆኑ ሕጉ እንዴት በተለያዬ መንገድ እየተተገበረ እንዳለ ሁለቱን አሰራሮች በአጭሩ ማየት  ያስፈልጋል፡፡  

የመጀመሪያዉ ዕይታና አተገባበር፡ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የፍርድ ቤቶችን የሥረ-ነገር ሥልጣን ሳይከተል እንደማንኛዉም የእግድ ትዕዛዝ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሊሰጥ ይገባል የሚለዉ ነዉ፡፡ ይህን አቋም የሚያራምዱትም ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥበት የተጠየቀበት ጉዳይ ከገንዘቡ መጠን አንፃር ከፍርድ ቤቱ ሥልጣን በላይ ቢሆን እንኳን የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዙን ለመስጠት ሥልጣን እንዳለዉ ይገልፃሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ ሥልጣን አለዉ ብለዉ ከሚጠቅሷቸዉ ምክንያቶች ዉስጥ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ  ግምት እንደሌለዉ ክርክር የሚቆጠር መሆኑንና ፍርድ ቤቱ ከስልጣኑ በላይ ያሉ ጉዳዮች የሚታዩበትን የግልግል ጉባዔ እንዲሚያቋቁመዉ ሁሉ በገንዘብ ደረጃ ከስልጣኑ በላይ በሆነ ጉዳይ መጠባበቂያ ትዕዛዝ ሊሰጥ የማይችልበት ምክንያት የሌለ መሆኑን በመጥቀስ ነዉ፡፡ በተመሳሳይ በሌሎች ክርክሮች ለምሳሌ የዉርስ ንብረት ማጣራት ክርክር፣የባልና ሚስት ክርክር፣ የማኅበር መፍረስ ክርክር በሚደረግበት ወቅት ፍርድ ቤቱ የሚሰጣቸዉ የእግድ ትዕዛዞች በገንዘብ መጠናቸዉ እየታየ ሳይሆን የእግድ አቤቱታ ግምት በሌላቸዉ ክርክሮች የሚስተናገድ ስለሆነ በተመሳሳይ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ሲሰጥም የፍርድ ቤቱን ሥልጣን ለመወሰን የገንዘብ መጠናቸዉ ታሳቢ ሊደረግ አይገባም፡፡ መጠባበቂያ ትዕዛዝ እግድን ጨምሮ የሚሰጡት ለጊዜዉ በመሆኑ እንደ ዉሳኔ ዘላቂ የሆነ መብት እና ግዴታን የማይፈጥሩ ስለሆነ የገንዘብ መጠናቸዉ የፍርድ ቤት ሥረ-ነገር ሥልጣንን ለመወሰን ግምት ዉስጥ ሊገባ አይገባም የሚሉ መከራከሪያዎች ይቀርባሉ፡፡

ሁለተኛዉ ዕይታና አተገባበር፡ የጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዝ አሰጣጥ የፍርድ ቤቶችን የሥረ-ነገር ሥልጣንን ይከተላል የሚለዉ ነዉ፡፡ የዚህ ክርክር አዉድ ፍርድ ቤቶች የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ሊሰጡ የሚችሉት ጉዳዩን ለመመልከት በተፈቀደላቸዉ የገንዘብ መጠን ልክ ወይም የሥረ-ነገር ሥልጣን ልክ  እንደሆነ የሚገለፅ ነዉ፡፡ የሚቀርበዉ ዋና ምክንያትም የግልግል ዳኝነት እና  የዕርቅ አሰራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዝ አሰጣጥና አፈፃፀምን በተመለከተ የፍርድ ቤቶችን የሥረ-ነገር ሥልጣን ሊከተል በሚችል መልኩ የተዘጋጄ መሆኑን በመግለፅ ነዉ፡፡

የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅም በግልግል ወይም በእርቅ የሚታዩ ጉዳዮች ጋር በተገናኙ የሚጠየቁ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የሚቀርቡበትንና የሚሰጡበትን አግባብ ለጉዳዩ በልዩ ሁኔታ ከተዘጋጀዉ ከግልግል የዳኝነት እና የዕርቅ አሰራር ሥርዓት አዋጅ ቁጥር 1237/2013 አንፃር መታየት እንዳለባቸዉ ያምናል፡፡ በጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ አሰጣጥ ጋር በተገናኘ በፍርድ ቤቶች በአተገባበር ረገድ እየታዬ ያለዉ ልዩነት ዋና መነሻ የሆነዉ አዋጁ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የሚቀርብ አቤቱታ ለየትኛዉ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ በግልፅ አለማስቀመጡ ነዉ፡፡ የአዋጁ አንቀጽ 9 እና 27 የግልግል ሂደት ከመጀመሩ በፊት ሆነ ከተጀመረ በኋላ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ በፍርድ ቤት ቀርቦ ሊሰጥ እንደሚችል ቢያስቀምጥም ለየትኛዉ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ያስቀመጠዉ ነገር የለም፡፡ የስልጣኑን ጉዳይ አከራካሪ የሚያደርገዉም ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ አፈፃፀም እንዲሁም በዕርቅ በሚታይ ጉዳይ ላይ የሚሰጥ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የፍርድ ቤት  የሥረ-ነገር ሥልጣንን እንዲከተል ተደርጎ መቀመጡ ነዉ፡፡ ይህም በዕርቅ በሚታይ ጉዳይ ላይ ጊዜያዊ ትዕዛዝ ሲሰጥ እና የግልግል ጉባዔ ትዕዛዝ አፈፃፀም የፍርድ ቤት ሥልጣንን ከተከተለ በግልግል በሚታይ ጉዳይ የሚሰጥ ትዕዛዝስ እንዴት የሥረ-ነገር ሥልጣንን አይከትልም? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ የአዋጁንም ሙሉ ይዘት ስንመረምር የምናገኘዉ ዉጤት በግልግል ወይም በእርቅ የሚታዩ ጉዳዮች ጋር በተገናኘ የሚሰጡ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ የፍርድ ቤት ሥረ-ነገር ሥልጣንን እንደሚከተል ነዉ፡፡ የሕግ አዉጪዉ ዓላማም ተመሳሳይ እንደሆነ ለማሳየት የሚከተሉትን ነጥቦች ትኩረት ሰጥቶ ማየት ያስፈልጋል፡፡

1ኛ. በዕርቅ እየታዩ ባሉ ጉዳዮች በግልግል እንደሚታዩ ጉዳዮች ሁሉ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ ወይም ትዕዛዝ እንደሚሰጥ በአዋጁ ተመላክቷል፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 55(3) በዕርቅ እየታዬ ባለ ጉዳይ ተዋዋይ ወገኖች ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ እንዲሰጥ ጥያቄ ሊያቀርቡ የሚችሉት ጉዳዩን ለመመልከት ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ ይገልፃል፡፡ በተመሳሳይ በዕርቅ እየታዬ  ባለ ጉዳይ አስታራቂዉ በዉል በተመለከተዉ ጊዜ ዉስጥ ወይም ጊዜዉ ያልተወሰነ ከሆነ  በስድስት ወር ዉስጥ ተግባሩን እንዲፈፀም የሚጠበቅበት ሲሆን በዚህ ጊዜ ዉስጥ ተዋዋይ ወገኖች ጉዳዩን ወደ ግልግል ወይም ወደ ፍርድ ቤት መዉሰድ እንደማይችሉ፣ ጉዳት እንዳይደርስባቸዉ የመጠባበቂያ  እርምጃ እንዲወሰድ መጠየቅ እንደሚችሉና ጥያቄዉም የሚቀርበዉ  ነገሩን ለመመልከት የሥረ-ነገር ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት ለመሆኑ በአንቀጽ 70(2) ተደንግጓል፡፡ ይህ አዋጅ የግልግል እና እርቅ አሰራርን ለመወሰን የወጣ አዋጅ እንደመሆኑ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝን በተመለከተ ለሁለቱ ጉዳዮች የተለያዬ አሰራር ሊያስቀምጥ የሚችልበት ምንም ዓይነት ገፊ ምክንያት የለም፡፡ በዕርቅ ጉዳይ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ አቤቱታ ጉዳዩን ለመመልከት የሥረ-ነገር ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት መቅረብ እንዳለበት እያስቀመጠ የግልግል ጉዳይ ላይ የሚወሰድ እርምጃ የፍርድ ቤት ሥረ-ነገር ሥልጣን እንዳይከተል ሊደረግ የሚችልበት ምንም የስነ-አመክንዮ ሁኔታ አይኖርም፡፡

2ኛ. አዋጁ በግልግል ጉባዔ የሚሰጥ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ አፈፃፀም የፍርድ ቤቶችን ሥረ-ነገር ሥልጣንን ተከትሎ እንደሚቀርብ ባስቀመጠበት ሁኔታ  ለአፈፃፀም መነሻ የሚሆን ትዕዛዝ የፍርድ ቤቶችን የሥረ-ነገር ሥልጣን የማይከተልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ በአብዛኛዉ የግልግል ጉባዔ የሚቋቋመዉ በተዋዋይ ወገኖች ምርጫ በመሆኑና የሚሰጡትም ትዕዛዝ ያለፍርድ ቤት ድጋፍ ሊፈፀም የማይችልበት ሁኔታ ስለሚኖር አፈፃፀሙ ወደ ፍርድ ቤት የሚመጣበት ሁኔታ አለ፡፡ የትዕዛዙን አፈፃፀም አስመልክቶም የአዋጁ አንቀጽ 25(3) በግልግል ጉባዔ የተሰጠ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ አፈፃፀም ጥያቄ ሊቀርብ የሚችለዉ ጉዳዩ በግልግል ባይታይ ኖሮ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት፣ ትዕዛዙ በዉጪ ሀገር በሚገኝ የግልግል ዳኝነት የተሰጠ ከሆነ ጉዳዩን ለማየት ሥልጣን ላለዉ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሚሆን ይናገራል፡፡ ፍርድ ቤቶችም በግልግል ጉባዔ የተሰጠ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ አፈፃፀም ጥያቄ ዉድቅ ሊያደርጉ ከሚችልባቸዉ ምክንያቶች አንዱ የተጠየቀዉ ፍርድ ቤት አፈፃፀሙን ለመመልከት ሥልጣን ከሌዉ እንደሆነ በአንቀጽ 26(1)(መ) ተመላክቷል፡፡  በዉጪ ሀገር የሚገኝ ግልግል የተሰጠ ብይን ወይም ዉሳኔ የማስፈፀም የሥረ-ነገር ሥልጣን ያለዉ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እንደሆነ በፌደራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀጽ 5(1)(ለ) እና 11(2)(ሀ) በግልፅ የተመላከተ ነገር ነዉ፡፡ የግልግል እና የዕርቅ አሰራር አዋጁ የፌደራል ለፍተኛ ፍርድ ቤት በሕግ የተሰጠዉን የሥረ-ነገር ሥልጣን ሳይቀር ጠቅሶ አፈፃፀሙ ለከፍተኛ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል መግለፁ ሕግ አዉጪዉ ከጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዝ ጋር የሚሰጡ ትዕዛዞችና አፈፃፀማቸዉ ላይ የፍርድ ቤቶችን ሥረ-ነገር ሥልጣን አጽንዖት እንደሰጠበት የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡ ይህ የአዋጁ ድንጋጌ በግልግል ጉባዔ የሚሰጥን ትዕዛዝ አፈፃፀም የሚመለከት ቢሆንም አፈፃፀሙ የፍርድ ቤት ሥልጣንን እንዲከተል ያደረገበት ዋና ምክንያት የፍርድ ቤቶች የሥረ-ነገር ሥልጣን ለመለየት ከሚቀመጠዉ ከፍርድ ቤቶች ብቃት (competency) አንፃር በመቃኘት እንደሆነ ግልፅ ነዉ፡፡ በተመሳሳይ ከግልግል ጉባዔ ጎን ለጎን በፍርድ ቤት ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ እንዲሰጡ ሲጠይቅ የፍርድ ቤቶችን የሥረ-ነገር ሥልጣን የማይከተል ከሆነ አፈፃፀሙ የፍርድ ቤት ሥልጣንን ሊከተል ይገባል ካለበት መነሻ ሃሳብ ጋር የሚጋጭ ይሆናል፡፡  በምክንያታዊ መለኪያ ሲታይም ትዕዛዝ መስጠት እና የተሰጠን ትዕዛዝ ማስፈፀም እኩል ብቃትን (competency)የሚጠይቁ አይደሉም፡፡ የተሰጠን ትዕዛዝ ማስፈፀም ትዕዛዙ የሚለዉን ብቻ እንደ ትዕዛዙ ቃል ወደ ተግባር እንዲቀየር በማድረግ ብቻ የሚወሰን ነዉ፡፡ ለአፈፃፀም መነሻ የሆነዉን ትዕዛዝ መስጠት ግን የተጠየቀዉን አቤቱታ ከሥነ-ሥርዓታዊ እና ከመደበኛ ሕጎች አንፃር መመርመርን የሚጠየቅ በመሆኑ ትዕዛዝን ከማስፈጸም ከፍ ያለ ምርመራ የሚጠይቅ ነዉ፡፡ ከመደበኛ የፍርድ ቤት ክርክር ጋር በተገናኘም ለአፈፃፀም መነሻ የሆነዉን ፍርድ የሰጠዉ ፍርድ ቤት ዋና ጉዳዩን ለመመልከት ሥልጣን ለሌለዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔዉን እንዲያስፈፀም ሊያደርግ እንደሚችል ከፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 372(1)(መ) መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህ ጊዜ ዉሳኔዉን የሚያስፈፅመዉ ፍርድ ቤት ዉሳኔዉን ከሰጠዉ ፍርድ ቤት ጋር እኩል ሥልጣን እንዳለዉ እንደሚቆጠር  በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 374(1) ተመላክቷል፡፡ እነዚህ ድንጋጌዎች ፍርድ ቤቶች በሥረ-ነገር ደረጃ በሕግ የተሰጣቸዉን ቀጥታ ጉዳይ ሥልጣን ለሌለዉ ፍርድ ቤት ማስተላለፍ ባይችሉም ለአፈፃፀም ዓላማ ሲባል ዉሳኔያቸዉን ለማስፈፀም ጉዳዩን ለመመልከት ሥልጣን ለሌለዉ ፍርድ ቤት ማስተላለፍ እንደሚችሉ የሚያሳዩ ናቸዉ፡፡ ይህ ሁኔታ የተሰጠን ዉሳኔ ማስፈፀም ዉሳኔዉን በመጀመሪያ ደረጃ መርምሮ  ከመወሰን ጋር እኩል እንዳልሆነና ሥልጣን የሌለዉ ፍርድ ቤትም ሊሰራዉ እንደሚችል የሚያሳይ ነዉ፡፡ የግልግል ዳኝነት እና ዕርቅ አሰራር አዋጁ ጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲፈፀም ጥያቄ የሚቀርበዉ የፍርድ ቤቶችን ሥረ-ነገር ሥልጣን ተከትሎ መሆኑን ካስቀመጠ ትዕዛዙን ከማስፈፀም ከፍ ያለምርመራ የሚያስፈልገዉን ለአፈፃፀሙ መነሻ የሆነዉን ትዕዛዝ  ሲሰጥ የፍርድ ቤት ሥልጣን እንዳይከተል ያደርጋል ተብሎ የሚታሰብ አይሆንም፡፡  

3ኛ. የግልግል ጉባዔዉ ክርክሩን ሲመራ ድጋፍ የሚያስፈልገዉ ከሆነ የድጋፍ  ጥያቄዉ ሊቀርብ የሚችለዉ ጉዳዩ በግልግል ባይታይ ኑሮ ነገሩን ለማየት ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት መሆኑ ሌላዉ ማረጋገጫ ነዉ፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 37(1)  ጉባዔው በራሱ ወይም አንዱ ተከራካሪ ወገን የሚያቀርበዉን ጥያቄ መነሻ በማድረግ ማስረጃዎችን ለመቀበልና ሌሎች የጉባዔዉን ትዕዛዝ ለማስፈፀም ጉባዔ በራሱ ሥልጣን ሊፈጽማቸዉ የማይቻል ከሆነ ወይም መፈፀም ካልቻለ ጉዳዩን ለማየት የሥረ-ነገር ሥልጣን ባለዉ ፍርድ ቤት አማካኝነት ጥያቄዉ እንዲቀርበለት መጠየቅ እንደሚችል ተመላክቷል፡፡ ይህ ድንጋጌ መጠባበቂያ ትዕዛዝን  ጨምሮ ግልግል ጉባዔዉ ስራዉን በሚሰራበት ወቅት ክርክሩን ለመምራት አስፈላጊ የሆኑ በራሱ መፈፀም የማይቻለዉን ማንኛዉም ነገር ሊያከናዉን የሚችለዉ ጥያቄዉን ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት በማቅረብ እንደሆነ የሚያሳስብ ነዉ፡፡ ከዚህ ጋር በተገናኘ በአብዛኛዉ የግልግል ጉባዔ የፍርድ ቤቶችን የማኅተም አገልግሎት የሚጠይቁበትን ሁኔታ እንደ ምሳሌ ማንሳት ይቻላል፡፡ የግልግል ጉባዔ በአብዛኛዉ በተዋዋዮች የሚቋቋም በመሆኑ የሚሰጡት ትዕዛዝ እንደ መደበኛ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ተቀብሎ የመፈፀም ያለዉ ልምድ አናሳ በመሆኑ በፍርድ ቤት በኩል ትዕዛዝ እንዲተላለፍላቸዉ እና የማኅተም አገልግሎት እንዲሰጣቸዉ ሲጠይቁ ይስተዋላል፡፡ ይህ አገልግሎት ወይም ድጋፍ የተለዬ የፍርድ ቤቶችን የምርመራ እና የምዘና ደረጃ የሚጠይቅ ባይሆንም ሕጉ በግልጽ አቤቱታዉ ሊቀርብ የሚገባዉ ጉዳዩ በግልግል ባይታይ ኑሮ ነገሩን ለመመልከት ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ እንደዚህ ዓይነት የተለዬና ከፍ ያለ ምዘና እና ምርመራ ሂደቶችን የማይጠይቁ ድጋፎች ሥልጣን ባለዉ ፍርድ ቤት በኩል እንዲሰጥ ሕጉ እያስቀመጠ ለጊዜዉም ቢሆን መብት እና ግዴታ የመፍጠር፣ ንብረት ላይ የሚኖርን መብት የመገደብ  ዉጤት የሚኖራቸዉን ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝን ሥልጣን ለሌለዉ ፍርድ ቤት እንዲሰጡ የማድረግ ሕግ አዉጪዉ ዓላማ ይኖረዋል ተብሎ የሚታሰብ አይሆንም፡፡

4ኛ. አዋጁ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ጥያቄ የስረ-ነገር ሥልጣንን ሳይከተል በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚችል ታሳቢ ቢያድረግ ኖሮ በአዋጁ ቀጥታ ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ይቀርባሉ በማለት እንደገለፃቸዉ  ሌሎች ጉዳዮች በግልፅ ማስቀመጥ ይችል ነበር፡፡ ለምሳሌ በአዋጁ አንቀጽ 12(3)(ለ) ተዋዋዮች የግልግል ዳኛ ተስማምተዉ መምረጥ ባልቻሉ ጊዜ ገላጋይ ዳኛ እንዲሾም የሚቀርበዉ አቤቱታ ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ በግልፅ ተመላክቷል፡፡ ከይግባኝ ሥርዓት ዉጪ በአንቀጽ 15(4) በገላጋይ ዳኛ ላይ ተቃዉሞ ቀርቦ ጉባዔዉ የወሰነዉ ዉሳኔ ላይ ቅሬታ ያለዉ ወገን ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተቃዉሞዉን እንደሚያቀርብ ተመላክቷል፡፡ በአንቀጽ 46 መሰረትም ለግልግል ዳኝነት የሚያስፈልገዉ ወጪ ወይም የግልግል አገልግሎት ክፍያ ላይ በሚሰጠዉ ዉሳኔ ላይ ተቃዉሞ ሊቀርብ የሚችለዉ ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንደሆነ ተገልጿል፡፡ በተመሳሳይ  ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ የፍርድ ቤት ሥልጣንን ሳይከተል በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታይ ታሳቢ በማድረግ ሕጉ ተዘጋጅቶ ቢሆን ኑሮ   በግልፅ ለመጀመሪያ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ያስቀምጥ ነበር፡፡

5ኛ. በግልግል የሚታዩ ጉዳዮች በዉርስ ንብረት ማጣራት፣ፍቺ እና የማኅበር መፍረስ  ክርክር ጋር የተለያዩ መሆናቸዉ ሌላዉ መታየት ያለበት ጉዳይ ነዉ፡፡ አዋጅ ቁጥር 1237/2013 ተከትሎ የሚቀርቡ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ ጥያቄ የፍርድ ቤቶችን ሥረ-ነገር ሥልጣን ሳይከተል በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ሊሰጥ የሚችል መሆኑን ከሚነሰዉ መከራከሪያ አንዱ የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በገንዘብ መጠኑ ከስልጣኑ በላይ በሆኑ ጉዳይ ላይ እግድ የሚሰጡ መሆኑን በመግለጽ ነዉ፡፡ ለምሳሌነት ከሚጠቀሱት ዉስጥም የዉርስ ማጣራት፣ፍቺ እና የማኅበር መፍረስ ክርክርን ተከትሎ የሚነሱ ክርክሮች ጋር የሚሰጠዉን እግድ እና የማስከበር ትዕዛዝ ነዉ፡፡ ይሁን እንጅ እነዚህ በምሳሌነት የሚጠቀሱት ክርክሮች ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲታዩ የሚደረጉት በገንዘብ መጠናቸዉ ሳይሆን በጉዳዩ ካላቸዉ ልዩ ባሕሪ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ክርክሮች የገንዘብ መጠናቸዉ ግምት ዉስጥ ሳይገባ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚታዩ መሆናቸዉ በሕግ የተወሰነ እስከሆነ ድረስ ጊዜያዊ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የሚቀርበዉም አቤቱታ ሊቀርብ የሚገባዉና የሚሰጠዉ  በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት መሆኑ አከራካሪ አይሆንም፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም የዉርስ ንብረት ሲጣራ፣የባልና ሚስት ንብረት ክርክር ሲደረግና የማኅበር መፍረስ ጉዳይ ሲታይ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 151፣154 እና 160 እና ተከታይ ድንጋጌዎች ጊዜያዊ ትዕዛዝ የሚሰጠዉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ጊዜያዊ ትዕዛዝን የመስጠት ብቸኛ ሥልጣን ስላለዉ ሳይሆን ዋናዉ ጉዳይ የሚታይበት ፍርድ ቤት በመሆኑ እንደሆነ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች በግልግል የማይታዩና በግልግል ሊታዩ ከሚችሉ ነገሮች የተለዩ በመሆናቸዉ በግልግል ከሚታይ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የሚሰጠን ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ሥልጣን ለማስረዳት ሊቀርቡ የሚችሉ አይደሉም፡፡ በግልግል ዳኝነት እና ዕርቅ አሰራር አዋጁ አንቀጽ 3(1) መሰረትም በግልግል እና በዕርቅ የሚታዩት ንግድ ነክ ለሆኑ ጉዳዮች በመሆኑ  በግልግል ባይታዩ ኑሮ ፍርድ ቤት ሊቀርቡ የሚችሉት አንድም ከገንዘቡ መጠን ወይም ከጉዳዩ ዓይነት አንፃር ታይቶ ሥልጣን  በሚኖረዉ ፍርድ ቤት ነዉ፡፡  ይህ ሁኔታ ደግሞ ጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዙን መስጠትም ሥልጣን የሚኖረዉ ዋናዉን ጉዳይ  የመመልከት ሥልጣን የሚኖረዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ የሚያረጋግጥ ነዉ፡፡ ዋናዉን ጉዳይ ለመመልከት ሥልጣን የሌለዉ ፍርድ ቤት በተለዬ ሁኔታ ጉዳዩን እንዲመለከት በሕግ ተወስኖ እስካልተሰጠዉ ድረስ ጊዜያዊ መጠባበቂያ ትዕዛዙን ለመመልከትና ለመስጠት የሚችልበት አግባብ አይኖርም፡፡

እንደ መዉጫ!

ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ከዋናዉ ጉዳይ ተነጥሎ እንደ ዳኝነት ሊጠይቅ የሚችል መሆኑ የግልግል ዳኝነት እና ዕርቅ አሰራር አዋጅ ከዘረጋቸዉ አዲስ ሥርዓቶች አንዱ ነዉ፡፡ ይህ ትዕዛዝ የሚሰጠዉ የግልግል ጉባዔ ከመቋቋሙ በፊት ወይም በሂደት ላይ እያለ ሲሆን ተከራካሪዎች ጥያቄዉን ለፍርድ ቤት ወይም ለግልግል ጉባዔዉ ሊያቀርቡት ይችላሉ፡፡ ጥያቄዉም ለጊዜዉም ቢሆን መብት እና ግዴታን የመፍጠር ዉጤት ያለዉ፣ በንብረት አጠቃቀም ላይ ገደብ ሊጥል የሚችል፣ ትዕዛዙ ባለመሰጠቱም የግልግል ሂደቱን፣ዉጤቱን እና አፈፃፀሙ ላይ ወሳኝ ተፅዕኖ ያለዉ በመሆኑ እንደ ማንኛዉም ክርክር በጥንቃቄ መታየትን የሚጠይቅ ነዉ፡፡ አዋጁ  በግልግል በሚታይ ጉዳይ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ለፍርድ ቤት ጥያቄዉ ሲቀርብ ለየትኛዉ ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ወይም ጥያቄዉ የፍርድ ቤቶችን የሥረ-ነገር ሥልጣንን ተከትሎ ሊቀርብ እንደሚችል የሚለዉ ነገር  አለመኖሩ ወጥነት የሌለዉ አሰራር እንዳይኖር ምክንያት ሆኗል፡፡ አሻሚ የሆነዉ ጉዳይ ዘላቂ መፍትሔ ሊሰጠዉ የሚችለዉ ሕጉን በማሻሻልና ጥያቄዉ ለየትኛዉ ፍርድ ቤት ሊቀርብ እንደሚገባ በግልፅ  በማስቀመጥ ቢሆንም የሕግ ትርጓሜ መርህን በመከተል ወጥ የሆነ አሰራር እንዲኖር ማድረግ ደግሞ የፍርድ ቤት ድርሻ ነዉ፡፡ ተቀባይነት ካላቸዉ የሕግ አተረጓጉም መንገዶችም አንዱ ስነ-አመክዮዋዊ ትርጉሜ (Logical interpretation) የሚባለዉ ሲሆን አሻሚ የሆነዉን ጉዳይ ወይም ድንጋጌ ከጠቅላላ የሕጉን ድንጋጌዎች በአዉድነት በመጠቀም ከነሙሉ ይዘቱ አገናዝቦ በመመርመር አመክንዮዋዊ በሆነ መንገድ አንድ ግልፅ የሆነ ድምዳሜ ላይ የሚደረስበት ነዉ፡፡ ይህ ዓይነት የትርጓሜ ስልት አሻሚ የሆነዉን ድንጋጌ ትክክለኛ ፍቺ እንዲሁም የሕግ አዉጪዉን ትክክለኛ የሀሳብ ክፍል ለማግኘት ወሳኝነት ያለዉ እንደሆነ ይታመናል፡፡ በተመሳሳይም የግልግል እና የዕርቅ አሰራር አዋጁ በግልግል በሚታዩ ጉዳዮች ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ሊጠየቁ የሚችሉት የፍርድ ቤቶችን ሥረ-ነገር ሥልጣንን ተከትሎ መሆኑን አዋጁ በተመሳሳይ ጉዳይ ያስቀመጣቸዉን ድንጋጌዎች በማየት እና አሻሚ ከሆነዉ ጉዳይ ጋር ያላቸዉን ትስስር በመመርመር የሕግ አዉጪዉን ትክክለኛ ሀሳብ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ አዋጁ በዕርቅ እየታዬ ያለ ጉዳይ ላይ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ እርምጃ ወይም ትዕዛዝ እንዲሰጥ የሚቀርበዉ ጥያቄ ነገሩን ለመመልከት ሥልጣን ባለዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ አስቀምጧል፡፡ በግልግል ሂደት ጉባዔዉ የሚሰጠዉ ትዕዛዝ እዉቅና እንዲያገኝ እና እንዲፈፀም ጥያቄ የሚቀርበዉም ጉዳዩ በግልግል ባይታይ ኑሮ ነገሩን ለመመልከት ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ ተመላክቷል፡፡ ግልግል ጉባዔ ማስረጃ እንዲሰበሰብ ወይም በራሳቸዉ መፈፀም የማይችሉት ሁኔታ ሲፈጠር ድጋፍ እንዲደረግ ጥያቄ የሚቀርበዉም በተመሳሳይ የሥረ-ነገር ሥልጣንን ተከትሎ ጉዳዩን ለመመልከት ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት ነዉ፡፡ ይህ በሆነበት ሁኔታ በግልግል በሚታይ ጉዳይ ላይ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ ሲጠየቅ የሥረ-ነገር ሥልጣንን የሚከተል መሆኑ አለመገለፁ የብዕር ግድፈት (Slip of the pen) ነዉ ከሚያስብል በቀር ሙሉ ስልጣኑ ለፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተሰጥቷል ወደ ሚል ድምዳሜ የሚያደርስ አይሆንም፡፡  በሌላ በኩልም አዋጁ ጊዜያዊ መጠባበቂያ እርምጃ ወይም ትዕዛዝ እንዲሰጥ ከሚጠየቅ ጥያቄ ያነሰ ምርመራ የሚያስፈልጋቸዉን የአፈፃፀምና ድጋፍ ጥያቄ የፍርድ ቤቶችን ሥረ-ነገር ሥልጣንን ተከትሎ ሥልጣን ላለዉ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ግልፅ በሆነ ሁኔታ እያስቀመጠ በግልግል በሚታይ ጉዳይ ላይ የፍርድ ቤቶች ሥረ-ነገር ሥልጣን ግምት ዉስጥ አልገባም ብሎ ማሰብ ምክንያታዊ አይሆንም፡፡  በተመሳሳይ በዕርቅ በሚታይ ጉዳይ ላይ  ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ እንዲሰጥ የሚጠየቀዉ ነገሩን ለመመልከት ሥልጣን  ላለዉ ፍርድ ቤት እንደሆነ እስከተገለፀ ድረስ በግልግል በሚታዩ ጉዳዮች ላይም የሚቀርቡ ጊዜያዊ የመጠባበቂያ ትዕዛዝ ጥያቄ የፍርድ ቤቶችን ሥረ-ነገር ሥልጣን  ተከትለዉ ሊቀርቡ  ይገባል፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በሠራተኛ ቅጥር ሂደት ስለሚፈፀም የኋላ ታሪክ ፍተሻ፣ አስፈላጊነት እና ሕጋዊነት
የዋስትና መብት መከበር ላይ በፖሊስ የሚቀርብ የይግባኝ ጥያቄ ህጋዊ አንድምታው ...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 23 May 2024