መግቢያ
የሰው ልጆች በዚህ ምድር ላይ መኖር የጀመሩትና ማህበራዊ መስተጋብር እንድ ህብረተሰብ ክፍል ብሎም እንደ ሀገር መኖር የጀመሩበት ጊዜ እና ቦታ ላይ የታሪክ ሊቃውንት በእርግጥ ይሄ ጊዜና ቦታ ባይሉንም ረጅም ዘመናትን እንዳስቆጠሩ ይገልፃሉ፡፡ የአንድ ሀገር ወይም ማህበረሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የሕብረተሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረተው በተለያየ መልኩ ቢሆንም ዋናው ግን የህብረተሰቡ አካል የሆኑት ሰዎ (ወንድ እና ሴት) በሚፈጸሙት ጋብቻ ነው፡፡ ቤተሰብ የህበረተሰቡ ዋና መሶሶ በመሆኑ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም እንደ ተቋም ከመቋቋሙ አንስቶ እስከ መጨረሻው ጊዜው ድረስ በሕግና እና ስርዓት መመራት ይኖርበታል፡፡ የቤተሰብ መመስርቻ የሆነው ጋብቻ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት እንዲዘልቅ ህብረተሰቡ ባወጣው ሕግ መሠረት መመሥረት ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም በቆይታው ጊዜ የሚፈጠሩትን ግንኝነቶችና ውጤቶች እንዲሁም በሕግ መሠረት ከለላ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል የልጅ አስተዳደግና አስተዳደር፣ በትዳር ውስጥ ስለሚፈጠሩ ንብረቶች፣ ከትዳር በፊት የነበሩ ንብረቶች፣ በባልና ሚስት መሀል ስለሚኖረው ግለሰባዊ ግንኙነቶች፣ በዚህ ትዳር ውስጥ ሆኖ ማድረግ ስለተከለከሉ ነገሮች እና ወዘተ የመሳሰሉት በሕግ መሠረት መደንገግ ይኖርባቸዋል፡፡
ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ይህን የህብረተሰብ ምሰሶ የሆነውን ትዳር (ቤተሰብ) ሊያፈርሱት ይችላሉ፡፡ ይህ በሕግ መሠረት የተቋቋመው ተቋም በሕግ መሠረት ሕጋዊ በሆነ መልኩ ነው መፍረስ ያለበት፡፡ ፍቺ በሕጉ መሠረት በመፈጸም ትዳር ሲፈርስ የራሱ የሆነ ሕጋዊ ውጤት ይኖረዋል፡፡ የልጆች ቀለብ በትዳር ውስጥ የፈሩ ንብረቶች አከፋፈል ወዘተ በሕግ መሠረት መሆን ይኖርበታል፡፡
በዚህ ጽሑፍ ውስጥም የጋብቻና ፍቺ ሕጋዊ ውጤቶቻቸው ከቀለብ መስጠት፣ ንብረት ግንኙነት (Pecuniary effect) እና ግላዊ የተጋቢዎቹ ግንኙነት (personal effect) ላይ በማተኮር በአሁኑ ሰዓት በፌዴራል መንግስት ደረጃ የወጣውን የተሻሻለውን የቤተሰብ ሕግ ዙሪያ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ እና አተገገባበሩ ላይ ትኩረት በማድረግ የሚዳሰስ ይሆናል፡፡