መግቢያ
በሀገራችን ኢትዮጵያ የተሸከርካሪ አደጋ በእጅጉን እየበዛ እና ከፍተኛ የሆነ የሞትና የንብረት ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡ የበርካቶች ህይወት አጥፍቷል፣ አካል አጉድሏል እንዲሁም ንብረት አውድሟል። ሁልግዜ በየማለዳው በራዲዮ የምንሰማቸው የትራፊክ ዘገባዎችም እጅግ ዘግናኝ እና ሁላችንንም የሚያስደነግጥ፣ የህሊና እረፍት የሚነሳ እና ወቶ የመግባት ዋስትናችንን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ወደመሆን ደርሶል፡፡ ችግሩ እጅግ አሳሳቢ እና አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ ጉዳት አደራሾቹ በአደጋው ተጋላጭ ለሆኑት ግለሰቦች እርዳታ ከመስጠት ወይም እርዳታ እንዲያገኙ እና ህይወታቸው እዲተርፍ ከማድረግ ይልቅ ጉዳቱን አድርሰው የሚሰወሩ መሆናቸው ነው፡፡
በተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አንድም ጉዳት አድራሹ ባለመታወቁ በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳቱን አድራሹ ቢታወቅም ጉዳቱን ያደረሰው ተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የሌለው በመሆኑ ተጎጂዎቹን ለባሰ ስቃይ እና እንግልት የሚዳርጋቸው ጉዳይ ነው፡፡
ከእንዲህ ያለን ችግር ለማቃለል የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አስገዳጅ በሆነ መልኩ በሕግ ተደንግጎ መኖር እጂጉን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡ በመሆኑም በሀገራችን ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችል ሕግ ወጥቶ በሥራ ላይ ውሎ ይገኛል፡፡ የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2002 በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ የሚገኝ ሕግ ነው፡፡ የሕጉን ይዘት ከዚህ ቀጥሎ ባለው ጽሑፍ በዝርዘር እንመለከተዋለን፡፡