Font size: +
31 minutes reading time (6109 words)
Featured

የጋብቻ እና ፍቺ ሕጋዊ ውጤቶች ከተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንፃር

የሰው ልጆች በዚህ ምድር ላይ መኖር የጀመሩትና ማህበራዊ መስተጋብር እንድ ህብረተሰብ ክፍል ብሎም እንደ ሀገር መኖር የጀመሩበት ጊዜ እና ቦታ ላይ የታሪክ ሊቃውንት በእርግጥ ይሄ ጊዜና ቦታ ባይሉንም ረጅም ዘመናትን እንዳስቆጠሩ ይገልፃሉ፡፡ የአንድ ሀገር ወይም ማህበረሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ይህ የሕብረተሰብ መሠረት የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረተው በተለያየ መልኩ ቢሆንም ዋናው ግን የህብረተሰቡ አካል የሆኑት ሰዎ (ወንድ እና ሴት) በሚፈጸሙት ጋብቻ ነው፡፡ ቤተሰብ የህበረተሰቡ ዋና መሶሶ በመሆኑ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ቦታና ከበሬታ የሚሰጠው የህብረተሰቡ መሠረት የሆነ ተቋም እንደ ተቋም ከመቋቋሙ አንስቶ እስከ መጨረሻው ጊዜው ድረስ በሕግና እና ስርዓት መመራት ይኖርበታል፡፡ የቤተሰብ መመስርቻ የሆነው ጋብቻ በህብረተሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ኖሮት እንዲዘልቅ ህብረተሰቡ ባወጣው ሕግ መሠረት መመሥረት ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም በቆይታው ጊዜ የሚፈጠሩትን ግንኝነቶችና ውጤቶች እንዲሁም በሕግ መሠረት ከለላ ሊኖራቸው ይገባል፡፡ ለምሳሌ ያህል የልጅ አስተዳደግና አስተዳደር፣ በትዳር ውስጥ ስለሚፈጠሩ ንብረቶች፣ ከትዳር በፊት የነበሩ ንብረቶች፣ በባልና ሚስት መሀል ስለሚኖረው ግለሰባዊ ግንኙነቶች፣ በዚህ ትዳር ውስጥ ሆኖ ማድረግ ስለተከለከሉ ነገሮች እና ወዘተ የመሳሰሉት በሕግ መሠረት መደንገግ ይኖርባቸዋል፡፡

ሰዎች በተለያዩ ምክንያቶች ይህን የህብረተሰብ ምሰሶ የሆነውን ትዳር (ቤተሰብ) ሊያፈርሱት ይችላሉ፡፡ ይህ በሕግ መሠረት የተቋቋመው ተቋም በሕግ መሠረት ሕጋዊ በሆነ መልኩ ነው መፍረስ ያለበት፡፡ ፍቺ በሕጉ መሠረት በመፈጸም ትዳር ሲፈርስ የራሱ የሆነ ሕጋዊ ውጤት ይኖረዋል፡፡ የልጆች ቀለብ በትዳር ውስጥ የፈሩ ንብረቶች አከፋፈል ወዘተ በሕግ መሠረት መሆን ይኖርበታል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ውስጥም የጋብቻና ፍቺ ሕጋዊ ውጤቶቻቸው ከቀለብ መስጠት፣ ንብረት ግንኙነት (Pecuniary effect) እና ግላዊ የተጋቢዎቹ ግንኙነት (personal effect) ላይ በማተኮር በአሁኑ ሰዓት በፌዴራል መንግስት ደረጃ የወጣውን የተሻሻለውን የቤተሰብ ሕግ ዙሪያ ያለውን የሕግ ማዕቀፍ እና አተገገባበሩ ላይ ትኩረት በማድረግ የሚዳሰስ ይሆናል፡፡

 

ስለ ጋብቻ (ቤተሰብ) አመሠራረት

ሀ. የጋብቻ ምንነት

አሁን ስራ ላይ ባለው የፌዴራል የተሻሻው የቤተሰብ ሕግ ውስጥ ጋብቻ የሚለውን ቃል ትርጉም በቀጥታ አልተሰጠም፡፡ ነገር ግን ከሕጉ የተለያዩ ድንጋዎች የቃሉ ትርጉም ማግኘት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሀገሮች ግን ለቃሉ በቤተሰብ ህጎቻቸው ትርጉም ለመስጠት ይሞክራሉ ለምሳሌ የኢንዶኒዥያ የቤተሰብ ሕግ “ጋብቻ በአንድ ወንድና በአንድ ሴት መካከል መንፈሳዊና ቁሳዊ ጥምረት በመፍጠር በፈጣሪ ፈቃድ ዘላቂና ደስተኛ ቤተሰብ ለመመስረት የሚደረግ ጥምረት ነው” በማለት ትርጉም ይሰጣል፡፡ ነገር ግን ይህ ትርጉም ጋብቻ የሚለውን ቃል በምዕሉነት እየተረጎመ አይደለም፡፡ ለአብነት ለመግለጽ ያክል ተጋቢዎቹ በስምምነት የጋራ ቁሳዊ ጥምረት ሳይፈጥሩ በየግላቸው የግል ንብረቶችን እያስተዳደሩ በጋብቻ ተሳስረው መኖር ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ጋብቻ ለሚለው ቃል ሁሉን በአንድ የሚያስማማ ትርጉም ማስቀመጥ አይቻልም፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ህጋችን ውስጥ በዋነኝነት በሶስት አይነት የጋብቻ ማስፈፃሚያ ስርዓቶች እውቅና ሰጥቷል፡፡ እነዚህም፡-

1.       በክብር መዝገብ ሹም ፊት የሚፈጸም ጋብቻ፣

2.       በሀይማኖት ስርዓት መሠረት የሚፈጸም ጋብቻ እና

3.       በባህል ስርዓት መሠረት የሚፈጸም ጋብቻ ናቸው፡፡ (በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 1 - 4)፡፡

በውጭ ሀገር የተፈጸመ ጋብቻ በዛ ሀገር ጋብቻ አፈፃፀም ሕግ መሠረት የተፈጸም ከሆነ እና የዚህን ሀገር (ኢትጵያ) ህዝብ ሞራል እስቃልተቃረነ ድረስ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት ከላይ በተገለጸው ሶስት አይነት ስርዓቶች ከተፈጸሙ ጋብቻዎች ጋር እኩል እውቅናና ተቀባይነት አለው፡፡

ለ. ጋብቻን ለመፈጸም በቅድሚያ መሞላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች

ከላይ በተጠቀሱት 3 ስርዓቶች ጋብቻ ቢፈጸምም ሶስቱም ዓይነት የጋብቻ መፈጸሚ ስርዓቶች በቅድሚያ ሊያሟሏቸው የሚገባ ቅድመ ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎ መሰረታዊ የሆኑ ናቸው፡፡

1.      ፈቃደኝነት (Consent)

የሚጸና ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነፃና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ እንደሆነ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 6 ላይ ተገልፆል፡፡ በኢፌዲሪ ህገ መንግስት አንቀጽ 34(2) ላይ “ጋብቻ በተጋቢዎቹ ነፃና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ ይመሰረታል ይላል፡፡ ስለዚህ በየትኛውም አይነት ጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት ጋብቻ ቢፈጸምም የተጋቢዎቹ ነፃ እና ሙሉ ፈቃደኝነት አስፈላጊ ነው፡፡

2.      እድሜ

ጋብቻ ራሱን የቻለ ኃላፊነት የሚያስከትል በመሆኑ ወደ ጋብቻው የሚቀላቀሉት ተጋቢዎች ይህን ኃላፊነት መቀበል የሚችሉ መሆን አለበት፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከጤና አንጻርም ወደ ጋብቻ የሚገቡ ሰዎች እድሜያቸው ብቁ መሆን አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ተጋቢቹ ለጋብቻው ፈቃዳቸውን በነፃ መስጠት መቻል አለባቸው፡፡ በዚህ በተሻሻለው ቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7(1) ላይ ወንዱም ሆነ ሴቷ አስራ ስምንት አመት ሳይሞላቸው ጋብቻ መፈጸም እንደማይችሉ ይገልፀል፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ ይህ እድሜ ሳይሞላ በፍትህ ሚኒስቴሩ ከመደበኛ እድሜ ሁለት ዓመት ያልበለጠ ጊዜ በመቀነስ እንዲጋቡ ሊፈቅድ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው ከባድ ምክኛት ሲያጋጥም ብቻ ነው፡፡

3.      ዝምድና

ከህብረተሰቡ ሞራልና ከጤና ምክኛት የተነሳ ተጋቢዎች የቅርብ ዘመድ (የስጋም ሆነ የጋብቻ ዘመድ) መሆን እንደሌለባቸው እሙን ነው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 8 እና 9 ላይ ክልከላው በግልጽ የተቀመጠ ነው፡፡

4.      በጋብቻ ላይ ጋብቻ

የፀና ጋብቻ ያለው አንድ ሰው ይህ ጋብቻ ጸንቶ እያለ ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማይችል (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 11) ክልከላ ተጥሎበታል፡፡

5.      በብቸኝት ለመኖር የተወሰነ ጊዜ

ይሄኛው ክልከላ ወይም ቅድመ ሁኔታ ከላይ ካሉት አራት ቅድመ ሁኔታዎች ለየት ባለ መልኩ በሴቶች ላይ ብቻ የተጣለ ነው፡፡ አንዴት ሴት አስቀድሞ የነበራት ጋብቻ ከቀረ በኋላ አንድ መቶ ሰማኒያ ቀን ካላለፈ በቀር ሌላ ጋብቻ መፈጸም እንደማትችል ክልከላ ተጥሎባታል፡፡ ነገር ግን ይህ አንድ መቶ ሰማኒያ ቀን ሳይደርስ የወለደች እንደሆን ወይም ጋብቻ የምትፈጽመው ከቀድሞ ባሏጋር ከሆነ ወይም ዕርጉዝ አለመሆኗ በህክምና ከተረጋገጠ ወይም ይህን ጊዜ እንዳትጠብቅ በፍ/ቤት የተወሰነ እንደሆነ ይህን ጊዜ ሳትጠብቅ ጋብቻ ልትፈጽም እንደምትችል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 16 (2) ላይ ተቀምጧል፡፡ ይህ ክልከላ በመሰረታዊነት የተቀመጠው የህፃናትን መብት ለመጠበቅ ነው፡፡ ህፃናት ወላጆቻቸውን የማወቅና ከወላጆቻቸው እንክብካቤ የማግኘት መብት እንዳላቸው በህገ መንግስታችንና አለማቀፍ ስምምነቶች ላይ የተቀመጡ እና የተረጋገጠ መብታቸው ነው፡፡ በመሆኑም ይህን ክልከላ በማድረግ የሕፃናትን መብት ለማስከበር የወላጆቻቸውን ማንነት ላይ አከራካሪ ሁኔታ እንዳይፈጠር ነው፡፡

ሐ. ጋብቻ እንዳይፈጸም ስለመቃወም

ጋብቻ የቤተሰብ መመስረቻ መሰረታዊው እና ዋናው መንገድ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ቤተሰብ ደግሞ የህብረተሰብና የሀገር መሠረት እና መሰሶ ነው፡፡ ይህ የህብረተሰብ እና የሀገር መሰሶ የሆነው ጋብቻ የተጋቢዎቹ ብቻ ሳይሆን የህብረተሰቡ እና የሀገርም ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህም የህብረተሰብ እና የመንግስት ጥበቃና እንክብካቤ የሚያስፈልገው ተቋም ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ጋብቻው ከመፈጸሙ በፊት መሞላት ያለበት ቅድመ ሁኔታ ወይም ክልከላዎች የተቀመጡት፡፡

በአንድም ሆነ በሌላ ምክኛት እነዚህ የተቀመጡ ቅድመ ሁኔተዎች ሳይሞሉ ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል፡፡ ለምሳሌ፡- በሕግ ከደነገገው እድሜ በታች ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል ወይም በቤተዘመዶች መካከል ጋብቻ ተፈጽሞ ሊገኝ ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ ቅድመሁኔታውን አሟልቶ ያልተፈጸመ ጋብቻ ካለ ወይም ሊደረግ እቅድ ካለ ይህን እንዳይፈጽም ወይም ሕጋዊ እርምት እንዲወሰድ ኃላፊነት ለመንግስትና ለህብረተሰቡ የተሰጠ አደራ ነው፡፡ ይህም ማለት በዓቃቤ ሕግ በኩል እና በተጋቢዎቹ ዘመዶችና በሌሎች በጉዳዩ ያገባናል በሚሉ የህጻናትና ሴቶች መብት አስከባሪ ድርጅቶች እና በመሳሰሉ ድርጅትቶች በኩል የሚከናውኑ ይሆናል፡፡

ጋብቻው እንዳይፈጸም መቃወምን ወይም እንዲፈርስ ጥያቄ ማቅረብን የሚችሉት ወገኖችን ማንነት የሚወስነው ለተቃውሞው መሠረት የሆነው ጉዳይ ማለትም ያለተሞላው ቅድመ ሁኔታ ይወስነዋላ ማለት ነው ፡፡ለምሳሌ የመቃወሚያወ መሠረት በጋብቻ ላይ ጋብቻ ከሆነ ይህን ቀድሞ የጸና ጋብቻ ያለው/ያላት ባለትዳር ወይም ዐ/ሕግ ይሆናል ማለት ነው፡፡

ይህ ጋብቻ ተፈጽሞ ከሆነ እንዲፈርስ የሚቀርበው አቤቱታ ለፍ/ቤት ነው፡፡ (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75(ለ) )፡፡ ነገር ግን ሊፈጸም የታቀደው ጋብቻ እንዳይፈጸም የሚቀረብ አቤቱታ ከሆነ የሚቀርበው ጋብቻውን ለሚያስፈጽመው ባለስልጣን ነው፡፡ ይህም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 19 ላይ ተገልፆ ይገኛል፡፡ ይህ መቃወሚያ በጽሑፍ መቅረብ ያለበት እና እጅግ ቢዘገይ ጋብቻው ሊፈጸምበት ከታቀደው ቀን ቀጠሮ 15 ቀን በፊት መሆን ይኖርበታል፡፡ ይህ ተቃውሞ የቀረበለት ተቋምም በሕግ በተቀመጠው 5 ቀን ውስጥ ውሳኔ መስጠት አለበት፡፡ ውሳኔው ተቃውሞውን ውድቅ ያደረገ  እንደሆነ ውሳኔው የመጨረሻ ነው፡፡ ነገር ግን ውሳኔው ተቃውሞውን በመቀበል ጋብቻውን እንዳይፈጽም የወሰነ እንደሆነ ጋብቻው እንዳይፈጸም ማድረግ ያለበት እና ይህንኑ ውሳኔ ወዲያው ለተጋቢዎች ማሳወቅ ይኖርበታል፡፡ በዚህ ውሳኔ ላይ ተገቢዎቹ ይግባኛቸው ለፍ/ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡

መ. ስለ ጋብቻ ምዝገባ 

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት በየትኛውም የጋብቻ ማስፈፃሚያ ስርዓቶች የተፈጸመ ጋብቻ መመዝገብ እንዳለበት ያስገድዳል፡፡ የጋብቻ መፈጸሚያ ስርዓቱ የተለያየ ቢሆንም የምዝገባ ስርዓቱ ግን አንድ ብቻ ነው፡፡ ይህን የጋብቻ መመዝገብ ሀላፊነት የተሰጠው ለክብር መዝገብ ሹም ጽ/ቤት ነው፡፡ ነገር ግን ይህ ጽ/ቤት እስኪቋቋም ድረስ የከተማ አስተዳደር መዘጋጃ ቤቶች ይህን ስራ ያከናውናሉ፡፡ በአሁኑ ሰዓት በአዋጅ ቁጥር 760/2004 ወሳኝ ኩነቶች ማለትም ልደት፣ ሞት፣ ጋብቻ፣ ፍቺ የመሳሰሉት እንዲመዘገቡ ተደንግጎል፡፡በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 278/2005 ደግሞ የወሳኝ ኩነቶች ጽ/ቤት ተቋቁሞ ስራውችን ለመስራት ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡

ጋብቻ በሕጉ የተመለከቱትን ውጠቶች ማስከተል የሚጀምረው ከተመዘገበበት ጊዜ ጀምሮ ሳይሆን ጋብቻው ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ ከዚህ መረዳት የሚቻለው የጋብቻ ምዝገባ አስፈላጊነት ጋብቻውን ሕጋዊነት እና የሚጸና ነው አይደለም ብሎ ለመወሰን ሣይሆን ለማስረጃነትና ለሌላ ተዛማጅ ጉዳዮች ነው፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 41896 በአመልካች ወ/ሮ ታደለች ዋለልኘ እና ተጠሪዎች እነ ወ/ሮ አዲስ አለሙ መካከል በነበረው ክርክር የስር ፍ/ቤት ጋብቻ እንዳለ የሚቆጠረው ጋብቻው በክብር መዝገብ ሹም ፊት ቀርቦ ከተመገበበት ቀን ጀምሮ ነው በማላት የሰጡትን ውሳኔ መሰረታዊ የሕግ ስተት አለው በማለት በመሻር በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 28/3/ መሠረት ጋብቻው ሕጋዊ ውጤት የሚጀምረው ጋብቻው ከተፈጸመበት ቀን ጀምሮ ነው በማለት ወስኖል፡፡

 

 ሠ/ የጋብቻ ቅድመ ሁኔታ አለመሟላት የሚስከትለው ውጤት

ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ጋብቻ ከመፈፀሙ በፊት መምላት ያለባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ዘርዝረናል፡፡ነገር ግን እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሟሉ ጋብቻው ቢፈፀም የፍታብሄር እና የወንጀል ሕጋዊ ውጤቶች አሉት፡፡ይህ ፅሁፍ የሚያተኩረው በፍታብሄራዊ ውጤቶቹ ላይ ነው፡፡እነኚ ቅድመ ሁኔታዎች ሣይሟሉ ጋብቻ ከተፈፀመ ጋብቻው እንዲፈርስ አቤቱታ የሚቀርበው ለፍ/ቤት ነው፡፡አቤቱታውም የሚቀርበው እንደየጉዳዮቹ በተለያዩ አካላት ነው፡፡በጉዳዩ ላይ የሚያገባቸው አካላት (interested party) ለፍ/ቤት በሚያቀርቡት አቤቱታ ነው የትዳሩ እጣ ፈንታ የሚወሰነው፡፡ ነገር ግን እዚጋ መታወቅ ያለበት ጉዳይ አቤቱታው ላይ ፍ/ቤቱ ጋብቻው ይፍረስ የሚል ውሳኔ እስካልሰጠ ድረስ እንዲፈርስ አቤቱታ የቀረበበት ትዳር እንደማንኛውም ሕጋዊ ትዳር ተቀባይነትና ሕጋዊ ውጤት እንዳለው ነው የሚቀጥለው (valid unless and until invalidated)፡፡

 

የጋብቻ ውጤት

በዚህ ፅሁፍ መግበያ እና በክፍል አንድ ላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው ጋብቻ ሕጋዊ ድርጊት ነው፡፡ሕጋዊ ድርጊት ደግሞ ሁልጊዜም ሕጋዊ ውጤትን ያስከትላል፡፡ስለሆነም ጋብቻም ሕጋዊ ድርጊት እንደመሆኑ መጠን ሕጋዊ ውጤት የሚኖረው ስለመሆኑ የታወቀ ነው፡፡እነዚህም ሕጋዊ ውጤቶች በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት (personale effect)ወይም በተጋቢዎቹ የንብረት ግንኙነት (pecunary effect)የሚኖራቸው ናቸው፡፡

በየትኛውም የጋብቻ አፈፃፀም ስርዓት ጋብቻው ቢፈፀምም የሶስቱም አይነት ጋብቻ ውጤት አንድ አይነት ነው፡፡(በተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ40)

ተጋቢዎች ትዳራቸው ያስከተለውን ግላዊ ግንኙነት ውጤቶች ወይም የንብረት ግንኙነት ውጤቶችን በተወሰነ መልኩ በውል እንዲመራ ሊያደርጉት ይችላሉ፡፡ ይህም ማለት አንዳንዱ የጋብቻ ውጤቶች በውል ሊቀሩ ወይም ሊሻሻሉ የሚችሉ ናቸው ማለት ነው ፡፡ ነገር ግን ሌሎች ለውል ሊቀሩ ወይም ሊሻሻሉ የማይችሉ አስገዳጅ ውጤቶችም አሉዋቸው፡፡ ይህም በተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 42(3) ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡

1.      የጋብቻ ውል

ከላይ እንደተገለጸው የተወሰኑ የጋብቻ ውጤቶች በውል ሊቀር ወይም ሊሻሻል ይችላል፡፡ ይህ ውል የጋብቻ ውል ተብሎ ይጠራል፡፡ ከተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 42(1) እና (2) እንደምንረዳው የጋብቻ ውል ተገቢዎቹ የንብረት ግንኙነታቸውን እና አልፎ አልፎም ግላዊ ግንኙነታቸውን አስመልክተው የሚፈራረሙት ውል ነው፡፡

ይህ የጋብቻ ውል 1ኛ አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎችን ሊቃረን አይገባውም፡፡ ይህ ሆኖ ከተገኘ ውሉ ፈራሽ ነው፡፡ 2ኛ ይህ ውል መፈጸም ያለበት ጋብቻው ከመፈጠፀሙ በፊት ወይም ጋብቻው በሚፈጸምበት ዕለት ነው፡፡ 3ኛ ይህ ውል በጽሑፍ ሆኖ አራት ምስክሮች ሁለቱ ከባል ወገን ሁለቱ ደግሞ ከሚስት ወገን መሆን አለበት፡፡ 4ኛ የውሉ ቅጅ በፍ/ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ዘንድ ሊቀመጥ ይገባል፡፡ 5ኛ ይህ ውል በሌሎች ሶስትኛ ወገኖች ግዴታ የሚያስከትል ስምምነቶችን ማድረግ አይቻሉም፡፡ እንዲሁም ተጋቢዎቹ የጋብቻ ውሉንም በጥቅሉ በአንድ ሀይማበኖት ወይም ባህል ወይም ሀገር ሕግ በመጥቀስ ብቻ ተስማምተናል ማለት አይቻሉም፡፡ 6ኛ ተጋቢዎች የጋብቻ ውላቸውን ለማሻሻል ወይም በጋብቻ ውስጥ እያሉ አዲስ ውል ቢፈራረሙ እንዲህ ዓይነቱን ማሻሻልያ ወይም አዲሱን ውል ፍ/ቤት ቀረቦ መጽደቅና ተቀባይነት ማግኘት አለበት፡፡

እነዚህ ከላይ የሰፈሩት ስድስቱ ነጥቦች የጋብቻ ውል በተጋቢዎች ሲፈጸሙ መሞላት ያለባቸው ቅድመ ሁኔታዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች ካልተሞሉ የጋብቻ ውል ፈራሽ ይሆናል ወይም ውሉ እንዳልተደረገ ቆጠራል፡፡ ነገር ግን በ4ኛ ደረጃ ላይ የተገለጸው የውሉ ቅጅ በፍ/ቤት ወይም በክብር መዝገብ ሹም ጋር ሊቀመጥ ይገባል የሚለው ላይ ሁለት የተለያዩ ሀሳቦች አሉ፡፡ አንደኛው ሃሳብ ይህ ውል በተጠቀሱት ተቋማት ዘንድ እንዲቀመጥ ሕጉ በገልጽ የደነገገ ስለሆነ ይህ ተደርጎ ባይገኝ  ውሉ ሕጋዊ ውጤት አይኖረውም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው ሀሳብ ደግሞ ይህ ውል በተጠቀሱት ተቋማት ዘንድ እንዲቀመጥ ያስፈለገበት ምክኛት ለጥንቃቄና ለሶስተኛ ወገኞች ጥቅም ተብሎ በመሆኑ ሦስተኛ ወገኖች ላይ ውጤት እንዳይኖረው በማድረግ በተገቢዎቹ ላይ ግን ሕጋዊ ውጤቱ እንዳለ እንዲቀጥል ማድረግ ይገባል የሚል ነው፡፡በዚህ ነጥብ ላይ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ አቋም የሁለተኛው ሀሳብ ነው፡፡ ምክንያቱም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 45 ላይ የውሉ ሰነድ ስለሚቀመጥበት ቦታ ሲገለጽ የሚቀመጥበትን ቦታ ከመግለጽ ውጭ ይህ ሆኖ ባይገኝ የውሉን ውጤት ሳይገልጽ ነው ያለፈው፡፡ ነገር ግን ስለ ውሉ ፎርም እና ውሉን ለመዋዋል ስላለው የነጻነት ወሰን በአንቀጽ 44 እና 46 ላይ ሲገለጽ በሕጉ አባባል መሠረት ውሉ በጽሁፍ ካልሆነ እና ተጋቢዎች በውላቸው ውስጥ ለሌላ ሶስተኛ ወገኖች ላይ ግዴታ የሚያስከትል ስምምነት ቢፈጽሙ ውሉ ውጤት አይኖረውም በማለት ይገልጻሉ፡፡ በአንቀጽ 45 ላይ ግን ይህን አላደረገም፡፡ውሉ በተጠቀሱት ተቋማት ዘንድ መቀመጣቸው ግዴታ ማድረግ ቢፈልግ ኖሮ ሕጉ በግልጽ እንደ ሌሎች ሁሉ በግልጽ ያስቀምጥ ነበር፡፡በመሆኑም የሁለተኛው ሀሳብ ሚዛን የሚደፋ ነው፡፡

በሕጉ እምነት ተጋቢዎች የጋብቻቸውን ውጤት በውል ከወሰኑና የጋብቻ ውሉም አስገዳጅ የሕግ ድንጋጌዎችን ያልተቃረን ከሆነ የጋብቻ ውሉ የግልም ሆነ የንብረት ግንኙነታቸውን እንዲገዛ ይደረጋል፡፡ ነገር ግን በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ ተነስተን ስንመለከት አብዛኛውን ጊዜ ተጋቢዎች የጋብቻቸውን ውጤት በውል አይወስኑትም፡፡በጥቂት ሁኔታዎች እንኳን ውል ሲዋዋሉ ውሉ በሕጉ የሚፈለገውን መመዘኛ አሟልተው የሚፈጽሙት እጅግ በጣም ጥቂቶች ናቸው፡፡በመሆኑም ውሉ ውጤት አይኖረውም፡፡ እንደነዚህ ያለ ሁኔታ ሲፈጠር ደግሞ ይህን ክፍተት የመድፈን ሀላፊነት የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ነው፡፡በዚህም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ የተጋቢዎችን ግላዊ እና ንብረት ነክ ግንኙነቶች የጋብቻ ውል በሌለበት ወይም ውሉ በሕግ ፊት ውጤት አልባ በሆነ ጊዜ የሚመራበትን የሕግ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡

2.      ጋብቻ ግላዊ ግንኙነት ላይ ስለሚኖረው ውጤት

ጋብቻ ተጋቢዎቹ በማህበረሰቡ ውስጥ በፊት ከነበራቸው ማህበረሰባዊ ቦታ ማለትም ለአቅም አዳም እና ሄዋን ደርሰው ከነበሩበት ወንደላጤነት እና ሴተላጤነት ወደ ሌላኛው ማህበረሰባዊ ቦታ አባወራ እና እማወራ የሚቀየሩበት እና የማህበረሰብ መሠረት የሆነውን ቤተሰብ የሚመሰርቱበት ነው፡፡ ይህ የሚመሰረተው ጋብቻ ተገጋቢዎቹ በፊት ከነበራቸው ግላዊ ህይወት ወደ ጋራ የሆነ ህይወት የሚያዘዋውራቸው ነው፡፡ በዚህ የጋራ የሆነ ህይወት ውስጥ ግላዊ ግንኙነታቸው ዘላቂ እና የተረጋጋ እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ ይህም ባልና ሚስት እርስ በርሳቸው መከባበር፣ መተጋገዝና መደጋገፍ አለባው፡፡ ይህ የመተጋገዝ፣ የመከባበር እና የመረዳዳት ግዴታ በምንም ሁኔታ ተጋቢዎቹ ሊያስቀሩት የማይችሉት ግዴታቸው ነው፡፡ (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 49) ፡፡

ተጋቢዎቹ ቤታቸው በፍቅር የደረጃ፣ መከባበር፣ መተሳሰብ እና መተጋገዝ የሰፈነበት እንዲሆን ባል እና ሚስት ቤትን በማስተዳደር እኩል የሆነ ሚና ሊኖራቸው ይገባል፡፡ በኢፌዲሪ ሕግ መንግስት አንቀጽ 34(1) ላይ “ተጋቢዎች በጋብቻ አፈፃፀም፣ በጋብቻው ዘመንና በፍቺ ጊዜ እኩል መብት አላቸው” ይላል፡፡ ይህ የሀገራችን የሕግ ሁሉ የበላይ የሆነ ህገ መንግስት ባል እና ሚስት በትዳራቸው እኩል መብት እንዳላቸው ይገልፃል፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 50 ላይም ባል እና ሚስት በቤተሰብ አመራር፣ ልጆች አስተዳደር እና የቤተሰቡን ደህንነት ጥቅም በማስከበር ላይ እኩል መብት ያላቸው መሆኑን ይገልፃል፡፡  በመሆኑም ቀደም ባሉ ጊዜያት በሰፊው ይስተዋል የነበረው ሴቶችን በጋብቻ ውስጥ የበታች አድረጎ የሚወስድ አስተሳሰብ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በማያሻማ ሁኔታ እንዲወገድ ተደርጓል፡፡

ጋብቻ በተጋቢዎች ግላዊ ግንኙነት ላይ የሚፈጠረው ሌላኛው ውጤት አብሮ የመኖርን ግዴታ ነው፡፡ ተጋቢዎች በፊት ከነበራቸው ማህበራዊ ቦታ ከላጤነት ወደ ጋራ የሆነ ህይወት ሲዘዋወሩ ዋነኛው መገለጫው አብሮ መኖራቸው ነው፡፡ ቤተሰብ ተመሰረተ የሚባለውም ተጋቢዎቹ በጋራ መኖር ጀምረው ጤናማ የሆነ የሩካቤ ስጋ ግንኙነት በማድረግ ልጆች በማፍራት የማህበረሰቡን ቀጣይነት ሲያረጋግጡ ነው፡፡ ይህን አብሮ የመኖር እና ለጤንነታቸው አደገኛ እስካልሆነ ድረስ የሩካቤ ስጋ ግንኙነት መፈጸም ግዴታ በባል እና ሚስት ላይ የተጣለ ግዴታ ነው፡፡ ይህን የሚቃረን የማናቸውም ስምምነት ማድረግ አይችሉም፡፡ (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 53)፡፡ በጋራ የመኖር ግዴታቸውን ሲወጡ የጋራ መኖሪያ ቦታቸውን በጋራ ተጋቢዎቹ ይወስናሉ፡፡ በአንደኛው ተጋቢ ስምምነት ብቻ የመኖሪያ ቦታን መምረጥ አይቻልም፡፡

ከላይ እንደተገለጸው በትዳር ውስጥ ተጋቢዎች በጋራ የመኖሪያ ቦታቸውን መርጠው አብረው የመኖር ግዴታ አለባቸው፡፡ ነገር ግን ባልና ሚስት ለተወሰነ ወይም ላልተወሰነ ጊዜ ተለያይተው ለመኖር ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ ይህ የሚሆነው በተለያየ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ በስራ ምክኛት ባል አዲስ አበባ ቦሌ ሚስት ደግሞ ባሌ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡

3.      ጋብቻ በንብረት በኩል ስለሚኖረው ውጤት

ጋብቻ ከሚያስከትላቸው ሕጋዊ ውጤቶች አንደኛው በንብረት ወይም በሀብት ላይ የሚያስከትለው ውጤት ነው፡፡ ማንኛውም ሰው የፈለገው ስራ ላይ ተሰማርቶ ሀብትና ንብረት ማፍራት መብት እንዳለው በህገ መንግስታችን አንቀጽ 41(1)ና(2) ላይ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሰው የፍላጎቱ በሆነ ስራ ላይ ተሰማርቶ ሀብትና ንብረት ማፍራት ይችላል፡፡በዚሁ መሠረት አንድ ሰው ወደ ጋብቻ ከመግባቱ በፊት በላቡና በወዙ ሰርቶ ያገኘው ወይም በስጦታ ወይም በውርስ ያገኘው ሀብትና ንብረት ሊኖረው ይችላል፡፡ይህን ከትዳሩ በፊት ያገኘውን ሀብትና ንብረት ወደ ትዳር ሲገባ የግል ንብረቱ ሆነው ይቀጥላል፡፡በትዳሩ ውስጥ ከገባ በኋላም ለግሉ በስጦታም ወይም በውርስ ያገኘው ንብረት የግል ንብረት ሆኖ ይቀጥላል፡፡ነገር ግን ተጋቢዎች የግል ንብረታቸው የሆነውን የጋራ ንብረት ነው በማለት ሊስማሙ ይችላሉ፡፡

ተጋቢዎች ትዳር የሚፈጽሙ እስከ መጨረሻው አብሮ ለመኖር መሆኑ እሙን ነው፡፡ በዚህ በትዳር ባሉበት ጊዚያት በግል ንብረትነት ይዘዋቸው ያሉ ንብረቶችን መሸጥ መለወጥ አይቀሬ ጉዳይ ነው፡፡ እነዚህ የግል ንብረቶችና ሀብቶችን በመሸጥ ወይም በመለወጥ የሚገኘው አዲስ ንብረትና ሀብት  የግል ንብረት ይሆናል፡፡ ነገር ግን እነዚህ በግል ሀብት የተገዙ ወይም የተለወጡ ንብረቶች የግል ሀብትና ንብርት እንደሆኑ የግል ንብረቱ ባለቤት ለፍ/ቤት የግል ይባልልኝ በማለት ጥያቄ ማቅረብ እና ማፅደቅ አለበት፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 58(1)ና(2) ይህን ይገልፃሉ፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በአንቀጽ 62/2/ መሠረት የጋራ ንብረት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 37275 ላይ ነአመልካች ሻ/ባሻ ገዛኸኝ ድልነሳው እና ተጠሪ ወ/ሮ ተዋበች ደመቀ መካከል በነበረው ክርክር የአመልካች የግል ንብረት የነበረ ቤት በትዳር ባሉበት ጊዜ ሽጠው በተሸጠው ገንዘብ ሌላ አዲስ ቤት ገዝተዋላል ነገር ግን አመልካች አዲስ የገዙትን ቤት የግል ይባልልኝ በማለት ጥያቄ ለፍርድ ቤት ያላቀረቡ እና ያላጸደቁ በመሆነ የጋራ ንብረት ነው በማለት ወስኖል፡፡

ኑሮ በትዳር ውሰጥ የጋራ ቢሆንም ከላይ በተገለጸው መልኩ ተገቢያዎቹ የግል ንብረቶቻቸውን ይዘው በትዳር በመቀጠል ይችላሉ፡፡ በዚህ ጊዜ እነዚህ ንብረቶችም የሚተዳደሩት በግል የንብረቱ ባለቤት በሆነው ሰው ነው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 59 ላይ እያንዳንዱ ተገቢ የግል ሀብቱን እራሱን ለማስተዳደርና ገቢውንም ለመቀበል ይችላል፡፡ እንዲሁም የግል ሀብቱን ራሱ ሊያዝበት ነፃነት አለው በማለት ይገልፃል፡፡ ነገር ግን የግል ንብረቱ ባለቤት የሆነው አንደኛው ተገቢ የግል ንብረቱን በሙሉ ወይም በከፊል ሌላኛው ተጋቢ እንዲያስተዳድርለት እና እንዲያዝበት በጋብቻ ውላቸው ሊወሰን ይችላል፡፡ ይህ በሚሆንበት ጊዜ የግል ንብረቱ ባለቤት የሆነው ተጋቢ ሌላኛውን ተጋቢ ስለንብረቱ አስተዳደር ዓመታዊ የሂሳብ መግለጫ መጠየቅ ይችላል፡፡ ይህ ሲሆን ሌላኛው ተጋቢ ሲጠይቅ የይህንኑ የመስጠት ግዴታ አለበት (የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 60(2) )፡፡ እንዲሁም ከተጋቢዎቹ አንዱ የግል ንብረቱንና ሀብቱን በሙሉ ወይም በከፊል እንዲያስተዳድርለት ለሌላኛው ተጋቢ ውክልና መስጠት እንደሚችል በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 61 ላይ ተቀምጧል፡፡

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው በጋብቻ ውስጥ ተጋቢዎች የግል ንብረት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ይህን ንብረት በዋንኛነት የንብረቱ ባለቤት የሚያዝበትና የሚስተዳድረው መሆኑን እንዲሁም የግል ንብረቱ ባለቤት የሆነው አንደኛው ተጋቢ ሌላኛው ተጋቢ እንዲያስተዳድርለት በጋብቻ ውል ወይም በውክልና መስጠት እንደሚችል ተረድተናል፡፡(በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ከአንቀጽ57-61)

ተጋቢዎች በትዳር ከተሳሰሩበት እለት ጀምሮ ህይወታቸውን በጋራ ሲመሩ የጋራ ንብረት ማፍራታቸው አይቀሬ ነው፡፡በጋብቻ ውላቸው ተጋቢዎች ከትዳር በፊት የነበራቸውን የግል ንብረት የጋራ ንብረት ማድረግም ይችላሉ፡፡በጥቅሉ በትዳር ዘመናቸው ተጋቢዎች የግል ንብረትና ሀብት እንደሚኖራቸው ሁሉ የጋራ ንብረትና ሀብት ሊኖራቸው ይችላል፡፡ከተሻሻለው የቤተሰብ ህጋችን አንቀጽ 57 እና 58 ለመገንዘብ የምንችለው ነገር በትዳር ውስጥ የተፈሩ ሀብቶችና ንብረቶች ፣ ለተጋቢዎቹ በጥቅሉ በውርስ ወይም በስጦታ  የተሰጡአቸው ሀብትና ንብረቶች በተጨማሪም የግል ሀብትና ንብረት ተሸጦ ወይም ተለውጦ የተገኘ ንብረት ሆኖ የግል ንብረቱ ባለቤት በፍርድ ቤት ቀርቦ የግል ንብረት መሆኑን ያላጸደቃቸው ንብረቶችና ሀብቶች ሁሉ የጋራ ንብረት እንደሆኑ ይቆጠራል፡፡ከዚህ በተጨማሪ በአንቀጽ 62(1) ላይ ባልና ሚስት ከግል ጥረታቸውና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኟቸው ገቢዎች ሁሉ የጋራ ሀብቶቻቸው እንደሚሆኑ ይገልፃል፡፡የግል ንብረት የግል ቢሆንም ከንብረቱ የሚገኝ ገቢ ግን የጋራ ነው፡፡

የንብረት ባለቤትነት የሚገለጹባቸው መንገዶች የተለያዩ ናቸው፡፡ በሀገራቸን የማይንቀሳቀሱ ንብረቶች እንደ ቤቶችና መኪና የመሳሰሉት ባለቤትነታቸው የሚረጋገጠው በባለቤትነት የምስክር ወረቀት ነው፡፡ በጋብቻ ውስጥ የተጋቢዎች የጋራ ንብረት በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ ተመዝግቦ ሊገኝ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ አንደኛው ተጋቢ የግል ሀብቱ መሆኑን ካላስረዳ በስተቀር ማንኛውም ንብረት በአንደኛው ተጋቢ ስም ብቻ የተመዘገበ ቢሆንም እንኳን የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡(የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 63(1))

ባልና ሚስት በትዳር ዘመናቸው ወቅት የሚገኘውን ገቢ እያንዳንዳቸው በየራሳቸው ይቀበላሉ፡፡ገቢ ማለት በዚህ አነጋገር ደመወዝ ፣ ከግል ንብረት የሚመነጭ እንዲሁም ከጋራ ንብረት የሚመነጭ ማለት ነው፡፡ በግል የመነጨውን ገቢ የሚቀበለው የገቢው ምንጭ የሆነው ተጋቢ ነው፡፡ ነገር ግን ሌላኛው ተጋቢ ሲጠይቅ ገቢውን የተቀበለው ተጋቢ ያገኘውን የገቢ መጠን ማሳወቅ ግዴታ እንዳለበት በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 64(3) ላይ ተገልፃል፡፡ የገቢው ምንጭ አንደኛው ተጋቢ ቢሆንም የጋራ ሀብት ስለሆነ ሌላኛው ተጋቢ የማወቅ መብት ይኖረዋል ማለት ነው፡፡ተጋቢዎቹ ከፈለጉ በየግላቸው የሚገኙትን ገቢ የጋራ የባንክ ሂሳብ በመክፈትማስቀመጥ ይችላሉ፡፡እዚህ ጋር መታወቅ ያለበት በመርህ ደረጃ የገቢው አመንጪ ገቢውን ቢቀበልም በልዩ ሁኔታ (exceptionally) ግን ሌላኛው ተጋቢ ገቢውን ሊቀበል ይችላል፡፡ይህ የሚሆነው በሁለት መልኩ ነው፡፡አንደኛው የገቢው አመንጪ የሆነው ተጋቢ ለሌላኛው ተጋቢ  በውል ገቢውን እንዲቀበል ሲፈቅድለት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፍ/ቤት ትዕዛዝ ነው ፡፡ይህ በፍ/ቤት የሚሰጠው ትዕዛዝ ከባልና ከሚስት አንደኛው ስጠይቅ ነው፡፡በሌላ በኩል ደግሞ ገቢው በሙሉ ወይም በከፊል እንዲከበር በፍ/ቤት ሊታዘዝ ይችላል ፡፡ እዚህ ላይ ልብ ልንል የሚገባው ነገር በሌላ ህጎች መከበር የሌለባቸው ገቢዎችና ንብረቶች የማይከበሩ መሆኑን ነው፡፡ለምሳሌ የጡረታ አበል ሊከበር እንደማይቸል የጡረታና በሌሎች ህጎች የተመለከተ ነው፡፡እንዲሁም በፍታብሄር ስነስርዓት ሕጉም ውስጥ ሊከበሩ የማይችሉ የንብረት ዓይነቶችና የደመወዝ መጠን በአንቀፅ 404 ላይ ተገልፆል ይገኛል፡፡

በኢፌዲሪ ህገመንግስት አንቀፅ 34(1) ላይ ተጋቢዎች በትዳር ዘመናቸው በሁሉ ነገር ላይ እኩል መብት እንዳላቸው ይገልፃል፡፡ እንዲሁም በአንቀፅ 35(7) ላይ ሴቶች ንብረት በማስተዳደር ከወንዶች ጋር እኩል መብት አላቸው በማለት ደንግጎአል፡፡ እነኚህ የህገ መንግስቱ መርሆች በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 66(1)ላይ በማካተት ባልና ሚስቱ የጋራ ሀብታቸውን በጋራ ያስተዳድራሉ በማለት ገልጾታል፡፡ ስለዚህም በመርህ ደረጃ ባልና ሚስት የጋራ ንብረታቸውን በጋራ ያስተዳድራሉ፡፡ነገር ግን ባልና ሚስቱ በስምምነት የጋራ ንብረታቸውን አንዳቸው እንዲያስተዳድሩ ማድረግ ይችላሉ፡፡ይህም በውል ለአንደኛው ወገን እንዲያስተዳድር ሲሰጥ ነው፡፡ በተለያየ አጋጣሚ (ምክነያት) ከተጋቢዎች አንዱ ችሎታ ሲያጣ ወይም ንብረት የማስተዳደር መብቱ በፍ/ቤት ሊገፈፍ ይችላል፡፡ይህ በሚሆንበት ጊዜ ሌላኛው ተጋቢ ንብረቱን የማስተዳደር ተግባር ያከናውናል፡፡ በውልም ሆነ ንብረት የማስተዳደር መብቱ በመገፈፉ ወይም ችሎታ በማጣቱ አንደኛው ተጋቢ ንብረቱን በሚያስተዳድርበት ጊዜ ሌላኛው ንብረቱን የሚያስተዳድረው ተጋቢ የንብረቱን አስተዳደር በተመለከተ ለሌላኛው ተጋቢ መረጃ የመስጠት ግዴታ እንዳለበት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 67 ላይ ተቀምጧል፡፡

ተጋቢዎች በትዳር ተሳስረው የጋራ ንብረት አፍርተው ሲኖሩ ይህን የጋራ ንብረት በጋራ ማስተዳደር እንዳለባቸው ከላይ በተገለጸው መልኩ ለመረዳት ችለናል፡፡ እነዚህን የጋራ ንብረቶች ተጋቢዎቹ በጋራ በሚያስተዳድሩበት ወቅት ንብረቱን መሸጥ መለወጥ ያስፈልጋቸው ይሆናል፡፡ ይህ ጋራ ንብረት መሸጥ መለወጥ ከፈለጉ በሌላ የሕግ የተለየ ሁኔታ ካልተደነገገ በስተቀር የተጋቢዎቹ የጋራ ስምምነት አስፈላጊ ነው፡፡ በአንቀጽ 68 የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የጋራ ንብረትና ሀብት ወደሌላ ሶስተኛ ወገን በሽያጭ ሆነ በስጦታ የሚቀየረው በተጋቢዎቹ የጋራ ስምምነት ብቻ መሆኑን ይገልፃል፡፡ እዚህ ላይ በጋራ ንብረት የሆነውን አንደኛው ተጋቢ ሌላኛውን ተጋቢ ፈቃድ ወይም ስምምነት ሳያገኝ ብቻውን ለሌላ 3ኛ ወገን በሽያጭም ሆነ በሌላ መንገድ ቢያስተላልፍ ሌላኛው ተጋቢ ለፍርድ ቤት በሚያቀርበው ጥያቄ ግዴታው እንዲፈርስ መጠየቅ ይችላል፡፡ ይህ ግዴታ እንደፈረሰ የሚጠይቀው ተጋቢ ለፍ/ቤት ጥያቄውን የሚያቀርበው ግዴታው መገባቱን ካወቀበት ቀን ጀምሮ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወይም በሌላ በማንኛውም ሁኔታ በ2 አመት ጊዜ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይህ የተባለው ጊዜ ካለፈ ይህን ጥያቄ ማቅረብ እንደማይቻል በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 69(2) ላይ ተገልፆል፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 38126 በአመልካች ዲያቆን ኃ/ጊዮርጊስ ወንድም እና ተጠሪዎች እነ የሺ ተፈሪ መካከል በነበረው ክርክር የአሁኑ 2ኛ ተጠሪ ከ1ኛ ተጠሪ ባለቤት ከሆኑት የጋራ ንብረታቸው የሆነውን ቤት ለአሁኑ አመልካች በ01/03/1995 ዓ.ም ያለ 1ኛ ተጠሪ ፍቃድ ይሸጥለታል፡፡ 1ኛ ተጠሪም በስር ፍርድ ቤት ውሉ ያለ እሳቸው ፍቃድ የተፈጸመ በመሆኑ እነዲፈርስ በማለት በ09/08/1999 ዓ.ም ክስ ታቀርባለች፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰበር ችሎት የአሁን 1ኛ ተጠሪ የሆነችው ክስ ያቀረበችው በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 69/2/ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ማለትም ሽያጩን ካወቀችበት ጊዜ ጀምሮ በ6 ወር ጊዜ ውስጥ ወይም በማንኛውም ሁኔታ በ2 አመት ጊዜ ውስጥ ክሶን ያላቀረበች ስለሆነ (ክሶን ያቀረበችው ከ4 አመት በሆላ ነው) ውሉ እንዲፈርስ ክስ የማቅረያ ጊዜ አልፎል፡፡ ስለሆነም ውሉ አይፈርስም በማለት ውሳኔ ሰጥቶላ፡፡

የሰው ልጅ በዚህ ምድር ላይ ሲኖር እለት በለት ኑሮውን ለመደጎም ወጪዎችን ያወጣል፡፡ በትዳር ውስጥም ተጋቢዎ ትዳራቸውን ለማቃናትና ዘላቂነቱን ለማስቀጠል የተለያዩ ወጪዎች ማውጣታቸው የማይቀር ሀቅ ነው፡፡ በመሆኑም ተጋቢዎች የትዳራቸውን ወጪ ለመሸፈን እያንዳንዳቸው እንዳቅማቸውና ችሎታቸው አስተዋፅኦ የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ የህይወት መንገድ ሁልጊዜም አልጋ በአልጋ አይሆንም ውጣ ውረድ በህይወት ውስጥ ማጋጠሙ አይቀርም፡፡ በዚህ ጊዜ ወደ ብድር እና እዳ መገባት ሊያጋጥም ይችላል፡፡ በትዳር ውስጥም ተጋቢዎቹ ለግላቸው ወይም ለትዳራቸው ሲሉ እዳ ውስጥ ሊገቡ ይችላሉ፡፡ ይህ በሆነበት ጊዜ እዳውን ለመክፈል እዳው ለግል የተወሰደ ከሆነ ከባለእዳው ተጋቢ የግል ሀብት ይሸፈናል፡፡ ነገር ግን የግል ሀብቱ ይህን ለመሸፈን የማይችል ከሆነ ተጋቢዎች የመረዳዳትና የመተጋገዝ ግዴታ ስላለባቸው ይህ እዳ ከጋራ ሀብታቸው ይከፈላል፡፡ እዳው ግን ለትዳራቸው ጥቅም ከሆነ ከጋራ ሀብታቸው የሚከፈል ይሆናል፡፡ ነገር ግን የጋራ ሀብቱ በቂ ካልሆነ ከተጋቢወቹ የግል ሀብት ይከፈላል፡፡

4.      ጋብቻ ቀለብ ከመስጠት ጋር ስለሚኖረው ውጤት

በዚህ ጽሑፍ ክፍል እንደ ውስጥ ዝምድና (የስጋም ይሁን የጋብቻ) በጋብቻ ቅድመ ሁኔታነት የሚታይበትን መንገድና የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤት ተመልክተናል፡፡ የዚህ የዝምድና ሌላኛው ውጤት ደግሞ በዘመዳሞቹ መካከል የሚፈጠረው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ነው፡፡በዚህ ክፍል ትኩረት ሰጥተን የምንመለከተው የጋብቻ ዝምድና የሚያስከትለውን የቀለብ መስጠት ግዴታ ነው፡፡

ቀለብ የመስጠት ግዴታ በሕግ ሲቀመጥ አራት መሰረታዊ መርሆዎችን ከግምት አስገብቶ ነው፡፡

1ኛ/ ቀለብ የመስጠት ግዴታ የሚጣለው እንዲሁ የስጋ ወይም የጋብቻ ዘመድ ነው ለተባለ ሰው ሁሉ ሳይሆን ጠበብ ብሎ በጣም ቅርብ ለሆኑ ዘመዶች ብቻ ነው፡፡

2ኛ/ የግዴታው መጠን ለቀለብ ጠያቂው የእለት ተእለት ኑሮ መሰረታዊ የሆኑ ነገሮችን በማቅረብ ላይ እንጂ የቀለብ ጠያቂውን ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ለማሟላት የሚያስገድድ መሆን አይኖርበትም፡፡

 3ኛ/ ቀለብ የመስጠት ግዴታው በቀለብ ጠያቂው ላይ የጥገኝነት ስሜት በሚፈጥር መልኩ ሳይሆን ተቀጥሮ ወይም ስራ ፈጥሮ ራሱን ማስተዳደር የሚችልበት ሁኔታንና ስሜትን በሚፈጥር መልኩ መሆን አለበት፡፡  

4ኛ/ ቀለብ ጠያቂው ሠርቶ ለመኖር አቅም የሌለውና የተቸገረ መሆን አለበት

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 198 ላይ ቀላብ የመስጠት ግዴታ የተጣለበትን ሰውና ቀለብ ጠያቂው ማን እንደሚሆን አስቀምጧል፡፡ ይህም በቀጥታ ወላጆችና ተወላጆች ማለትም በአባትና ልጅ፣ በእናትና በልጅ እንዲሁም በአያትና ልጅ መካከል አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ በቀጥታ የጋብቻ ዘመዳሞች መካከል ማለትም በባልና ሚስት አባት ወይም እናት ወይም አያት ወይም ልጅ ወይም በሚስትና በባል አባት ወይም እናት ወይም አያት ወይም ልጅ መሃላ ያለ ግዴታው ነው፡፡ ይህ አይነቱ በቀጥታ ያለውን የዝምድና  መስመር የያዘው ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ወደ ጎን የሚቆጠር ዝምድና ላይ በወንድምና በወንድም ወይም በወንድምና እህት ወይም በእህትና እህት መካከል ግዴታ የተጣለ ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ባልና ሚስት የመረዳዳት የመተጋገዝና የመደጋገፍ ግዴታ እንዳለባቸው ከላይ አይተናል፡፡ በመሆኑም ይህን ግዴታቸው አንዱ ለአንዱ ቀለብ የመስጠት ግዴታን የሚያካትት መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

በሕጉ ላይ እንደተመለከተው ባል ለሚስት ወንድም ወይም እህት እንዲሁም ሚስት ለባል ወንድም ወይም እህት የቀጥታ የጋብቻ ዘመዶች ስላልሆኑ እነርሱን መርዳት ግዴታ እንደሌለባቸው ይገልፃል፡፡ ነገር ግን የባል ወይም የሚስት ወንድም ወይም የእህታቸውን የመርዳት ቀለብ የመስጠት ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህን ግዴታ ለመወጣት ደግሞ ከግል ሀብት ወይም ከጋራ ሀብት ወጪ ማድረግ ይችላሉ፡፡ በመሆኑም ዘሮ ዘሮ ለባልና ለሚስት እህት ወይም ወንድም ቀለብ የመስጠት ግዴታ ለባልና ሚስቱ የሕግ ግዴታ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡

የቀለብ ሰጭው ግዴታ እንደባለጉዳዮቹ (ቀለብ ሰጪውና ተቀባዮ) ሁኔታና እንደ አካባቢው ልማድ መሰረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት እንደሆነ በአንቀጽ 197 ላይ ተገልፆል፡፡ ይህም ማለት እንደ ቀለብ ሰጪውና ቀለብ ተቀባዩ አቅምና ፍላጎትን መሠረት ባደረገ መልኩ የሚከናወን ነው፡፡ እነዚህ መሰረታዊ ፍላጎቶች ምግብ፣ መኖሪያ፣ ልብስ፣ ጤናውን እንዲጠብቅ እና ትምህርት ናቸው፡፡ ስለሆነም የቀለብ ሰጭው አቅምና የቀለብ ተቀባዩን ፍላጎት መሠረት ባደረገ መልኩ ቀለብ የመስጠት ግዴታው ይፈፀማል ማለት ነው፡፡ ለምሳሌ የአንድ አቶ አበበ የተባለ ግለሰብ የሚስቱ አባት የራሳቸው መኖሪያ ያለቻው ነገር ግን የሚበሉትና የሚለብሱት ከቸገራቸው የአቶ አበበ ግዴታ ትምህርት እንደሚማሩ ወይም እንዲታከሙ ማድረግ ሳይሆን እንደ አቅሙ የሚመገቡትን ምግብና የሚለብሱትን ልብስ መስጠት ይሆናል፡፡

ቀለብ ጠያቂው ከቀለብ ሰጪው ጋር የቅርብ ዘመድ (በሕጉ በተቀመጠው መሠረት) መሆኑ ከተረጋገጠና ሰርቶ እራሱን ለማስተዳደር አቅም የሌለውና ችግር ላይ የወደቀ መሆኑ ሲረጋገጥ ብቻ ነው ቀለብ መጠየቅ የሚችለው፡፡ ይህም ማለት ቀለብ የመጠየቅ መብት ስራ በማግኘትና ባለማግኘት ላይ የተመሰረተ ሳይሆን የመስራት አቅም መኖር እና አለመኖር ላይ መሆኑን ከሕጉ መረዳት ይችላል፡፡ በመሆኑን መስራት አቅም እያለው ስራ ያላገኘ ሰው ቀለብ መጠየቅ አይችልም፡፡

በጋብቻ የተዛመዱ ሰዎች ጋር የቀለብ መስጠት ግዴታው የሚቆረጥበት አጋጣሚ አለ፡፡ ይህም ጋብቻው በፍቺ ወይም የጋብቻ ቅድመ ሁኔታዎች ባለመሞላታው ጋብቻው ከፈረሰ ቀለብ የመስጠት ግዴታው ቀሪ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ጋብቻው የፈረሰው በሞት ምክኛያት ከሆነ ግዴታው ቀሪ አይሆንም ( የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 199)፡፡ ይህም የሆነበት ምክኛያት ጋብቻው የፈረሰው ከአቅም በላይ በሆነ ሀይል በመሆኑ እንጂ በተጋቢዎቹ ቤተዘመዶች መካከል ያለው ግንኙነት ጤናማ መሆኑን ስለሚያሳይ ነው፡፡ ሌላው ቀለብ የመስጠት ግዴታ ቀሪ የሚሆንበት ምክኛት ቀለብ ጠያቂው ቀለብ ሰጪው ወይም በቅርብ ዘመዶቹ ህይወት ወይም ንብረት ላይ የወንጀል ተግባር የፈጸመ ወይም ለመፈጸም ሙከራ ያደረገ እንደሆን ነው፡፡ ይህም የሆነበት ምክኛት ከፍትህ መርሆች አንዱ “ማንም ሰው ከራሱ ጥፋት አትራፊ (ተጠቃሚ) መሆን የለበትም” (No one can benefit from his own fault) የሚል በመሆኑ ነው፡፡

ቀለብ የመስጠት ግዴታ የተጣለበት ሰው ይህን ግዴታውን ባይወጣ ቀለብ ተቀባዩ ወደ ፍ/ቤት ጉዳዩን በማቅረብ ቀለብ ያልሰጠው ባለግዴታ ግዴታውን እንዲወጣ ማስወሰን ይቻላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቀለብ አለመስጠት የወንጀል ሃላፊነትም ያስከትላል፡፡

 

ስለጋብቻ መፍረስና ውጤቶች

 

የሀገር እና የህብረተሰብ ምሶሶ የሆነው ቤተሰብ በጋብቻ አማካኝነት የሚመሰረተው እስከ ተጋቢዎች እድሜ ፍፀሜ ድረስ አብሮ ለመኖር ነው፡፡ ነገር ግን በተለያዩ ምክንያቶች ይህ የተመሰረተው ጋብቻ ሊፈርስ ይችላል፡፡ በዚህ ጽሑፍ  ክፍል አንድ ላይ እንደተገለጸው ጋብቻ የሚፈጸመው በሕግ በተደነገገ ስርዓትን በመከተል ነው፡፡ ይህ ስርዓትን ተከትሎ በሕግ እውቅና አግኝቶ የተመሰረተ ጋብቻ ሲፈርስም ሕግን ተከትሎ መሆን አለበት፡፡ ጋብቻው የተፈጸመው በየትኛውም አይነት ስርዓት ቢሆንም የጋብቻው መፍረስና የሚያስከትለው ውጤት ግን አንድ ዓይነት ነው፡፡

በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75 ላይ ጋብቻ ስለሚፈርስባቸው ምክንያችን በመዘርዘር አስቀምጧል፡፡ እነኚህም፡-

1ኛ ከተጋቢዎቹ አንዱ ከዚህ ዓለም በሞት የተለየ ከሆነ፣

2ኛ ከተጋቢዎቹ አንዱ በፍ/ቤት ለመጥፍቱ ውሳኔ የተሰጠ እንደሆነ፤

3ኛ በሕጉ ጋብቻ ለመፈጸም እንደ ቅድመሁኔታ የተቀመጡት ነገሮች ሳይሞሉ ጋብቻው የተፈጸመ እንደሆነ እና ጋብቻው እንደፈረሰ ውሳኔ ሲሰጥ እና

4ኛ የጋብቻ ፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ ጋብቻው ይፈርሳል፡፡ ይህ ጽሑፍ ካሉት አራት የጋብቻ መፍረስ ምክኛቶች አንዱ በሆነው ፍቺ ላይ ትክረቱን ያደረጋል፡፡

 

ስለፍቺና ውጤቶች

ከላይ ለመግለጽ እንደተሞረው በሕጋዊ መንግድ ተመስርቶ የነበርውን ጋብቻ ለማፍረስ አንደኛው ምክኘኛት ፍቺ ነው፡፡ ጋብቻ በህብረተሰቡና በመንግስት ጥበቃ የሚደረግለት ተቋም ነው፡፡ የዚህ የጥበቃው ዋናው ምክኛት ትዳሩ ስላማዊና ጤናማ በሆነ መልኩ ቀጥሎ የህብረተሰቡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ነው፡፡ ነገር ግን ከተጋቢዎቹ አቅም በላይ በሆነ ወይም ሌላ ምክኛት ተጋቢዎቹ ትዳራቸው እንዳይቀጥል ማድረግ የሚሳናቸው ጊዜ ያጋጥማል፡፡ በንደዚህ አይነት ጊዜ ደግሞ በሕጋዊ መሠረት የተመሰረተው ጋብቻ ሕጉን በጠበቀ መሠረት በሰላም እንዲለያዩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ ጋብቻ በሁለት የተለያዩ ስርዓቶች የተፈጸመ ቢሆንም አንድ ጊዜ በሕግ አግባብ የተደረገ ፍቺ በቂና ሙሉ ሕጋዊ ውጤት የሚያስከትል ነው( የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 75/ሐ/ )፡፡ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 40781 ላይ በአመልካት አቶ ፍቅረስላሴ ካህሳይ እና በተጠሪ ወ/ሮ ሮማን ታደሰ መካከል በነበረው ክርክር ላይ የሚከተለውን ውሳንኔ ሰጥቶል፡፡ የክርክሩ ፍሬ ነገር የነበረው አመልካች እና ተጠሪ ጥር 16 ቀን 1984 ዓ.ም በባህላዊ ስርዓት ጋብቻ አዲስ አበባ ላይ ፈጽመዋል፡፡ እንዲሁም የካቲት 5ቀን 1985 ዓ.ም በአውስትራሊያ ሃገር የብሔራዊ ጋብቻ ፈጽመዋል፡፡ አመልካች እና ተጠሪ ጋባቻቸውን በአውስትራሊያ ማጅስትሬት ፍ/ቤት በፍቺ አፍርሰዋል፡፡ ተጠሪ ይህ ጋብቻ መፍረሱን ተቀብለው በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት የፍቺው ውጤት እንዲወሰንላቸው አቤቱታ አቅርቡ ከፍተኛ ፍ/ቤቱ በአውስትራሊያ ሃገር በፍቺ የፈረሰው ጋብቻ በዛው ሃገር የተደረገው እንጂ በአዲስ አበባ የተደረገው አይደለም በማለት ጋብቻ ሳይፈርስ የፍቺ ውጤት ሊወሰን አይችልም  በማለትአቤቱታወን ውድቅ አደረገ፡፡ ተጠሪም በአዲስ አበባ የተደረገው ጋብቻ በፍቺ ይፍረስልኝ በማለት ክስ አቀረቡ፡፡ አመልካች ግን ጋብቻው አንዴ አውስትራሊያ ሃገር በፍቺ ፈርሶል በማለት ክርክር አቀረበ ነገር ግን ፍ/ቤቱ የአመልካችን ክርክር ውድቅ በማድረግ በአዲስ አበባ የተደረገው ጋብቻ በዚህ ፍ/ቤት ውሳኔ በፍቺ ፈርሶል በማለት ውሳኔ ሰጠ፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱም ከላይ በተሰጠው ውሳኔ ላይ ለቀረበለት አቤቱታ ተከታዩን ውሳኔ ሰጥቶል፡፡ በሃገራችን ሕግ የተቀመጠ ሶስት አይነት የጋብቻ መፈጸሚያ ስርዓት አሉ፡፡ ከነዚህ ስርዓቶች በአንደኛው ተጋቢዎች ጋብቻ ከተፈጸሙ በድጋሚ እነዚሁ ተጋቢዎች ጋብቻው ጸንቶ እያለ ሌላ ጋብቻ ሊፈጸሙ የሚችሉበት የሕግ አግባብ በሃገራችን የለም፡፡ በድጋሚ ተደርጎ እንኮን ቢገኝ ጋብቻው ፀንቶ የሚቆየው የመጀመሪያው ጋብቻ ከተፈጸመበት ቀን አንስቶ ነው፡፡ ጋብቻ አንድ እንጂ ሁለት አይደለም፡፡ ጋብቻ ከሚፈርስባቸው ምክኛቶች አንዱ በፍቺ ውሳኔ ሲሰጥ መሆኑ ነተሻሻለው ብተሰብ ሕግ አንቀጽ 75/ሐ/ ያመለክታል፡፡ ጋብቻ አንድ እንደሆነ ሁሉ ጋብቻው በፍቺ ሊፈርስ የሚችለው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ተጠሪ እና አመልካች  በአዲስ አበባ እና በአውስትራልያ ጋብቻ የፈፀሙ ቢሁንም ግራ ቀኙ የትዳር ግንኙነታቸውን በፍቺ ማቆረጥ ስለፈለጉ በአውስትራልያ  ፍ/ቤት የፍቺ ውሳኔ አሰጥተዋላ፡፡ ይህን ፍቺ ሁለቱም ተቀብለው የየራሳቸውን ኑሮ መኖር ጀምረዋል፡፡ ግንኙነታቸው ከተቆረጠ ዳግሞ በአዲስ አበባ የተደረገው ጋብቻ ለሁለተኛ ጊዜ በፍቺ ሊፈርስ ይገባል የሚባልበት የሕግ ምክኛት አይኖርም፡፡ በመሆኑም ጋብቻው በፍቺ የፈረሰው የአውስትራልያ ፍ/ቤት የፍቺ ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ በመሆኑም ከፍተኛ ፍ/ቤት በድጋሚ የተሰጠው የፍቺ ውሳኔ ተገቢ አይደላም፡፡ ስለሆነም የፍቺው ውጤት የሚጀምረው በአውስትራሊያ ፍ/ቤት የፍቺ ውሳኔ ከተሰጠበት ቀን ጀምሮ ነው በማለት ወስኖል፡፡

 

ለዚህም የተሻሻለው የቤተሰብ ህጋችን ፍቺ እንዴት እንደሚካሄድ፣ በማን እንደሚካሄድ እና ውጤቶች በዝርዝር ያስቀመጠው፡፡ በዚህም መሠረት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ፍቺ በሁለት መንገዶች ሊከናወን እንደሚችል በአንቀጽ 76 ላይ ይገልፃል፡፡ ይህም 1ኛ ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት ሲወስኑና ይህንኑ ለፍ/ቤት አቅርበው ውሳኔያቸው ተቀባይነት ሲያገኝ፡፡ 2ኛ ከተጋቢዎቹ አንዱ ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ በፍ/ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ነው፡፡

ሀ/ በስምምነት ፍቺ ስለመፈጸም  

በስምምነት ፍቺ ማድረግ በተሻለው የቤተሰብ ሕግ ከተቀመጡበት ሁለት አይነት የፍቺ ማካሄጃ መንገድ አንዱ ነው፡፡ ባልና ሚስት በስምምነት ተፋትተው ወሳኔያቸውን ያጸድቅላቸው ዘንድ ለፍ/ቤት ማቅረብ ይችላሉ፡፡ ባልና ሚስቱ የፍቺውን ውጤትም አብረው ተስማምተው በተመሳሳይ መልኩ ከፍቺ ስምምነታቸው ጋር ለፍ/ቤት አቅርበው ማጽደቅ ይችላሉ፡፡ ለፍቺ ስምምነት ያደረሳቸውን ምክኛት ከፈለጉ ይገልጻሉ፡፡ ነገር ግን እንዲገልጹ አይገደዱም፡፡

ባልና ሚስቱ ፍቺው ላይ እና ውጤቱ ላይ ተስማምተው እንደሚያጸድቅላቸው ፍ/ቤት ሲቀርቡ ፍ/ቤቱ በጋራም ሆነ በተናጥል ስለ ጥያቄያቸው ያነጋግራቸዋል፣ እንዲሁም የመፍታት ሀሳባቸውን እንዲለውጡ ይጠይቃቸዋል፡፡ ከዚህም አልፎ የበለጠ አስበውበትና በሰከነ አምሮ ተወያይተው እንደመጡ ለማስቻል እስከ ሶስት ወር የማሰላሰያ ጊዜ እንደነገሩ ሁኔታ ሊሰጣቸው እንደሚችል በአንቀጽ 76(2) ተገልፆል፡፡ ይህን የሶስት ወር ማሰላሰያ ጊዜ ፍ/ቤቱ የሚሰጠው እንደ ነገሩ ሁኔታ እያየ ነው፡፡

ፍ/ቤቶች ተጋቢዎቹ በስምምነት ተፋተው መጥተው ፍቺው እንዲጸድቅ ሲጠይቁ ይህን ፍቺ ከማጸደቃቸው በፊት ጋብቻ በዘፈቀደ እንዳይፈርስ እና ጸንቶ እንዲቆይ ለማድረግ ፍ/ቤቶች ሊያደርጓቸው የሚገቡ መርሃግብሮችን ሕጉ በአንቀጽ 78 እና 80 ላይ አስቀምጦታል፡፡ እነዚህም ተጋቢቹ የፍቺ ሀሳባቸውን እንዲለውጡ መጠየቅ፣ የማሰላሰያ ጊዜ እንደነገሩ ሁኔታ ሶስት ወር የማይበልጥ ጊዜ መስጠት፣ ፍቺው ትክክለኛ ፍላጎታቸው መሆኑን እና በነፃ ፍቃዳቸው የሰጡ መሆኑን ማረጋገጥ እና ስምምነቱ ከሕግና ሞራል ጋር የማይቃረን መሆኑን ማረጋገጥ ግዴታ አለባቸው፡፡

በስምምነት የመፍታት ጉዳይ ሲነሳ ውጤቱም አብሮ መታየት አለበት፡፡ ከጋብቻው የተወለዱ ልጆች፣ በጋብቻው ወቅት የተፈራ የጋራ ሀብትና ንብረት፣ ለትዳር ጥቅም የተገባ እዳና አከፋፈሉ እና የመሳሰሉ ጉዳዮቸ እንዴት እንደሚሆን ሊገለጽ ይገባል፡፡ ባልና ሚስቱ ስለፍቺው ውጤት ያደረጉት ስምምነት የልጃቸውን ደህንነትና ጥቅም በበቂ ሁኔታ የሚስጠብቅ ወይም የአንደኛውን ተጋቢ ጥቅም የሚጎዳ ሆኖ ካገኘው ፍ/ቤቱ የፍቺውን ስምምነት ብቻ በማጽደቅ የፍቺውን ውጤት በተመለከተ ጉድለቶቹን እንዲያስተካክሉ ወይም ተገቢ መስሎ የታየውን ውሳኔ ይሰጣል፡፡ ይህም የሚያሳየን በስምምነት ፍቺ ወስጥ የፍ/ቤት ሚና እንዳለ ነው፡፡

ለ/ የፍቺ ጥያቄ በመቅረቡ ምክንያት ስለሚፈጸም ፍቺ

ይህ አይነት ፍቺ አንደኛው ተጋቢ ብቻ ወይም  ሁለቱም ተጋቢዎች ፍቺ ፈልገው ጠይቀው ነግር ግን ስለፍቻቸው ሆነ ስለውጤቱ ያደረጉት ስምምነት የሌለበት ነው፡፡ ስለሆነም የፍ/ቤት ሚና በዚህ አይነት ፍቺ ስምምነት የማጽደቅ ሳይሆን በተጋቢዎቹና በሽማግሌዎቹ በመረዳት ቢቻል ትዳሩን ማቃናት ካልሆነ ግን ፍቺውን የሚያስከትለውን ውጤት መወሰን ይሆናል፡፡ በመሆኑም በስምምነት ከሚደረገው የፍቺ አይነት ይልቅ በዚኛው ላይ የፍ/ቤት ሚና ከፍ ያለ ነው፡፡

በአንቀጽ 82 ስር ፍ/ቤቱ ዘርዝርና ሰፋ ያሉ ሀላፊነቶች የተሰጡት ሲሆን ከፍ/ቤቱ ሌላ በተጋቢዎቹ የሚመረጡ አስታራቂ ሽማግሌዎች በጉዳዩ ላይ እንዲገቡበት የማድረግ እድል አለ፡፡ የአስተራቂ ሽማግሌዎቹን የስራ ክንውን ሪፖርቶች የመቀበልና ለሽማግሌዎቹ የስራ መመሪያ መስጠት የፍ/ቤቱ ኃላፊነት ስለመሆኑ አንቀጽ 119 እስከ አንቀጽ 122 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች ተመልክቶ ይገኛል፡፡ ፍ/ቤቱ ባልና ሚስቱን በተናጠልም ሆነ በአንድነት በማነጋገር የፍቺው ጥያቄያቸውን ትተው አለመግባባታቸውን በስምምነት እንዲቋጩት ያግባባል፡፡ ይህን ሞክሮ ያልተሳካለት እንደሆነ ባልና ሚስቱ ከፍ/ቤት ውጪ ራሳቸው በሚመርጡት ሽማግሌዎች አማካኝት ጉዳያቸውን በእርቅ እንዲጨርሱ ሊያደርግ ይችላል፡፡  ባልና ሚስቱ በመፋታት ቆርጠው በሽማግሌም አለመስማማታቸውን መፍታት ካልቻሉ ፍ/ቤቱ ከሶስት ወር ያልበለጠ የማሰላሰያ ጊዜ ሊሰጧቸው ይችላሉ፡፡

ፍ/ቤቱ ባልና ሚስቱ ለየብቻ ወይም በጋራ አናግሮአቸው ያልተስማሙበትን ነጥብ እንዲፈቱ ጠይቀዋቸው፣ በራሳቸው በመረጡት ሽማግሌዎች ጉዳያቸውን አሳይተው ስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋቸው እንዲሁም ከሶስት ወር ያልበለጠ የማሰላሰያ ጊዜ ሰጥተዋቸው በዚህ ሁሉ ጥርት ጥረቱ ፍሬ ካላፈራ የሽማግሌዎቹ የመጨረሻ ሪፖርት ከደረሰው ወይም የተሰጠው የማሰላሰያ ጊዜ ከአለቀበት ቀን ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል፡፡

በአንቀጽ 82(5) እና (6) ላይ ፍ/ቤቱ ስለሚሰጠው ጊዜያዊ ትዕዛዝ ይገልፃል፡፡ ፍ/ቤቱ አቤቱታው እንደቀረበ ወዲያው ባልና ሚስቱ ስለሚተዳደሩበትና ስለሚኖሩበት ሁኔታ፣ ስለልጆቻቸው አጠባበቅ ስለሚኖሩበት ስፍራና ስለአኗኗራቸው እንዲሁንም ስለንብረታቸው አስተዳደር ተገቢ መስሎ የታየውን ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡ ይህም የጋራ ንብረቱን የያዘው ሰው ንብረቱ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የልጆች አስተዳደግ እና አኗኗር ችግር እንዳይገጥመው እንዲሁም በጋራ የሚኖሩ ከሆነና ቅራኔያቸው ከፍ ያለ ከሆነ በጋራ መሆናቸው የባሰ ችግር እንዳይፈጠር ጠቀሜታ አለው፡፡ ፍ/ቤቱ በጋራ ከሚኖርበት አንዳቸው መውጣት ያለባቸው መሆኑን ካመነበት ተጋቢዎቹ ያላቸው ተጨባጭ ሁኔታ መሠረት በማድረግ የጋራ መኖሪያቸውን ለቆ መውጣት የበለጠ የሚጎዳው የትኛው መሆኑን በመመርመርና የልጃቸውን አጠባበቅና ጥቅም ግምት ውስጥ በማስገባት ሊወስን እንደሚገባ ሕጉ ይደነግጋል፡፡

ለረጅም ጊዜ መለያየት መፋታት ሊያመላክት ይችላል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ባልና ሚስት ሕጋዊ መንገድ የመሰረቱት ጋብቻ በሕጋዊ መንገድ ሳያፈርሱ በመለያየት የየግል ኑሯቸውን ለረዥም ጊዜ መኖር ይጀምራሉ፡፡ ይህ አይነቱ መለያየት የፍቺ አይነት ውጤት እንዳለው የፌደራሉ ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 20938 በአመልካች ወ/ሮ ሸዋዬ እና በተጠሪ ወ/ሮ ሳራ መካከል በነበረው ክርክር ‘‘በወ/ሮ ሳራና በአቶ ይልማ መሀል የነበረው ጋብቻ በሕጉ በተቀመጡ የጋብቻ ማፍረሻዎች ባይፈርስም በስር ፍ/ቤት ወ/ሮ ሳራ የሰጡት ቃል መፍረሱን የሚያሳይ ነው። ወ/ሮ ሳራና አቶ ይልማ በጋብቻው መቀጠል ባለመቻላቸው ተጣልተው ተለያይተው በየፊናቸው የየራሳቸውን ኑሮ ሲኖሩም ነበር። ለጋብቻው መፍረስ የሚያበቁ ምክንያቶች መኖራቸውንና አቶ ይልማም ወ/ሮ ሸዋዬን ማግባታቸውን ወ/ሮ ሳራ ያውቁት ነበር። ሆኖም ሁለቱም የየራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ስለነበር ወ/ሮ ሳራ አቶ ይልማ ወ/ሮ ሸዋዬን ማግባታቸውን ቢያውቁም ሟች በህይወት እያሉ ጋብቻውን ‘በጋብቻዬ ላይ የተፈፀመ ሕገወጥ ጋብቻ ነው’ ብለው አልተቃወሙትም። ሰለዚህ የስር ፍ/ቤቶች ይህን ባረጋገጡበት ሁኔታ ‘ወ/ሮ ሳራ ሟች እስከሞቱበት እለት ሚስት ነበሩ’ ብለው መወሰናቸው ትክክለኛውን የሕግ አተረጓጎም የተከተለ አይደለም። ፍቺ መፈፀሙን የሚያሳይ ማስረጃ አለመቅረቡ ብቻ አንድን ጋብቻ የፀናና ውጤት የሚያስከትል ነው ሊያስብለውም አይችልም። ባለመግባባት ተለያይተው ፍቺ ለመፈፀም የሚያስችል ምክንያት የነበራቸው ተጋቢዎች የየራሳቸውን ኑሮ በየበኩላቸው ጀምረው ከኖሩ በኋላ ባል ወይም ሚስት ናቸው ሊባሉ አይችሉም’’ በማለት ወስኖላ፡፡

ሐ/ የፍቺ ውጤቶች

ፍ/ቤቱ ፍቺውን ከወሰነ በኋላ የፍችውን ውጤት በተመለከተ ባልና ሚስቱ እዲስማሙ ይጠይቃቸው፡፡ እዚህ ላይ የምንረዳው ነገር ፍቺውን ፍ/ቤቱ ከወሰነ በኋላ የፍቺውን ውጤት ማለትም ስለልጆቻቸው፣ ስለጋራ ንብረታቸው እንዲሁም የገራ እዳወቻቸው በተመለከተ ተስማምተው እንደወሰኑ ፍ/ቤት በጠየቃቸው መሠረት ተስማምተው ሊወስኑ እንደሚችሉ ነው፡፡ ነገር ግን ባልና ሚስቱ የፍቺው ውጤት ላይ ያልተስማሙ ከሆነ ፍ/ቤቱ በራሱ ወይም በሽማግሌዎች ወይም ፍ/ቤቱ በሚሾሟቸው ባለሙዎች አማካኝነት ወይም አመቺ መስሎ በሚታየው በማንኛውም ዘዴ የፍችውን ውጤት ይወስናል፡፡

በዚህ ጽሑፍ ክፍል ሁለት ውስጥ ለመግለጽ እንደሞከረው ተጋቢዎች በጋብቻ ውላቸው ውስጥ የጋብቻው መፍረስ በንብረት በኩል የሚያስከትሉ ውጤቶችን አስቀድመው ሊወስኑ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን የጋብቻ ውሉ የሌለ እንደሆነ ወይም በሕግ ፊት የማይጸና ከሆነ ፍ/ቤቱ በሕግ በተቀመጠው መሠረት የፍቺውን ውጤት ይወስናል፡፡ በዚህም መሠረት በመጀመሪ ደረጃ የግል  ንብረት ክፍፍል ይካሄዳል፡፡ በተጋቢዎች እጅ ያሉ ንብረቶች ሁሉ የጋራ ንብረት እንደሆኑ ስለሚገመት እያንዳንዱ ተጋቢ ይህ ንብርት የግሌ ነው የሚለውን የማስረዳት ሸክም የሱ ወይም የሷ ይሆናል፡፡ የግል ንብረቱ መሆኑን ያስረዳው ተጋቢ የግል የሆነውን ንብረቱን ይወስዳል፡፡ ይህ የግል ንብረቱ የሆነው ነገር ከጋራ ንብረታቸው ጋር የተቀላቀለ ስለመሆኑ የተረጋገጠ  ከሆነ ከግል ንበረቱ ጋር ተመጣጣኝ  የሆነ ገንዘብ ወይም ንብረቱን ከጋራ ንብረታቸው ውስጥ ይወሰዳል፡፡ የየግል ንብረታቸውን ወስደው ከጨረሱ በሆላ የጋራ ንብርት ክፍፍል ከማድረጋቸው በፊት ዕዳዎችን መክፈል ይቀጥላል፡፡ በቅድሚያ ለትዳራቸው ያለባቸውን ዕዳ ከጋራ ንብረታቸው ይከፍላሉ ይህ የጋራ ሃብት እዳቸውን የማይቻል ከሆነ ከግል ንብረታቸው ይከፍላሉ፡፡ ነገር ግን አንዳዴ ንብረቱ የግል ነው የጋራ የሚለው ላያ ጭቅጭቅ ይነሳል ለምሳሌ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመዝገብ ቁጥር 46606 በአመልካች አቶ ገብረስላሴ አማረ እና ተጠሪ ወ/ሮ አብረኸት ተጫነ መካከል በነበረው የፍቺ ክርክር ላይ የሚከተለውን ውሳኔ ሰጥቶል፡፡ የአመልካች እና የተጠሪ ጋብቻ የፈረሰው መጋቢት 24 ቀን 2000 ዓ.ም ነው፡፡ አመልካች የኮንዶሚኒየም ቤቱን የተመዘገበው ተጠሪን ከማግባቱ በፊት ቢሆንም እጣ የወጣለት ከተጠሪ ጋር የፀና ጋብቻ በነበረነት  ወቅት ነው፡፡ ጋብቻው ፀንቶ እስካለ ድረስ ተጠሪን ከማግባቱ በፊት ስለተመዘገበ ብቻ ቤቱ  የግል ንብረቱ እንደማይሆን በተሻሻላው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 62/1/ ድንጋጌ መገንዘብ የሚቻል በመሆኑ አመልካች ያቀረቡት ክርክር የሕግ መሠረት የሌለው ነው፡፡ በመሆኑም የኮዶሚኒየም ቤቱ የጋራ ንብረት ነው፡፡ ጋብቻው ከፈረሰ በሆላ ሚከፈለው ክፍያ አመልካችና ተጠሪ በጋራ የመክፈል ግዴታ አለባቸው፡፡ በተመሳሳይ የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመዝገብ ቁጥር 51893 በአመልካች አቶ እንዳልካቸው ዘለቀ እና ተጠሪ ወ/ሮ ብሁዓለም መንግስቱ መካከል በነበረው ክርክር የኮዶሚኒየም ቤት ጋር በተያያዘ ከጋብቻ በፊት በአንደኛው ተጋቢ ምዝገባው የተካሄደው ቢሆንም የቤቱ ዕጣ የወጣው ብሎም የቤቱ ሽያጭ ውል የተደረገው በጋብቻ ጸንቶ በነበረበት ወቅት መሆኑ በተረጋገጠ ጊዜ ለቤቱ መገኘት ምክኛት የሆነው ተጋቢ ቤቱ የግል መሆን አለበት በሚል የሚቀርብ ክርክር ተቀባይነት  ሌለው ነው በማለት ወስኖል፡፡

 

ያለባቸውን እዳ ከፍለው ከጨረሱ በኋላ ወይ የጋራ ንብረት ክፍፍል ይሄዳሉ፡፡ በመረህ ደረጃ የጋራ ንብረታቸውን ባልና ሚስቱ እኩል ይከፋፈላሉ፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ በአንቀጽ 84 ላይ እንደተጠቀሰው ፍ/ቤቱ ለፍትህ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው በካሳ መልክ ለአንደኛው ተገቢ ከሌላኛው ተጋቢ ድርሻ ላይ ቀንሶ ለሌላኛው ሊሰጥ ይችላል፡፡ ይህን የጋራ ንብረቶቻቸውን ሲከፋፈሉ በመጀመሪያ በዓይነት በዓይንት እንዲካፈሉ ይደረጋል፡፡ ይህ ክፍፍል ሲደረግ ለእያንዳንዱ ተጋቢ ይበጥ ጠቃሚነት ያላቸውን ንብረቶች እንዲያገኙ ጥረት ይደረጋል፡፡ ይህ ሲሆን የእኩልነት መርሁን ለማስከበር ልዩነቱን በገንዘብ ሊካስ ይገባል፡፡

ልጆቻቸውን በተመለከተ በስምምነታቸው መሠረት የሚኖሩበት ቦታ እና ቀለባቸውን ይወስናሉ፡፡ ነገር ግን ካልተስማሙ ፍ/ቤቱ ለልጆቹ አመቺ የሆነውን እና መብታቸውን በሚያስከበ  

 

ማጠቃለያ

አንድ ህብረተሰብ እንደ ህብረተሰብ ቀጣይነት እንዲኖረው ይፈልጋል፡፡ ባህሉ፣ ቋንቋው፣ ስርዓቱ፣ ወጉ ወዘተ ተጠብቆለት እንዲቀጥል የሁሉም የህብረተሰብ ምኞትና ፍላጎት ነው፡፡ ይህ ህብረተሰብ ደግሞ ቀጣይነት እንዲኖረው ቤተሰብ መኖር አለበት፡፡ ምክንያቱም ቤተሰብ የህብረተሰብ ምሶሶ ነውና፡፡ በመሆኑም ለህብረተሰቡ ምሶሶ የሆነው ቤተሰብ በህብረተሰቡ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ይህም ጥበቃ የሚደረግልት ቤተሰብ ከመመስረቱ ጀምሮ ጋብቻ ከመፈጸሙ በፊት መሞላት ያለበት ቅድመ ሁኔታዎችን ወደ ጋብቻም ከተገባ በኋላ በተጋቢዎቹ መካከል የሚኖረውን ግላዊም ሆነ፣ ንብረት ነክ ግንኙነታቸውን፣ በህብረተሰቡ የሚጠበቅባቸውን ግዴታ የመሳሰሉትን ነገሮች በሕግ እና በስርዓት እንዲመሩ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በተሻሻለው የቤተሰብ ህጋችን ላይ እነዚህ ነገሮች በግልጽ እና በዝርዝር ተቀምጠዋል፡፡ ይህ ሕግ ጋብቻ ለመፈጸም የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎችን እና ክልከላዎችን፣ እነዚህ ክልከላዎች ወይም ቅድመ ሁኔታዎች ሳይሞሉ ጋብቻው ቢፈጸም የሚያስከትለውን ሕጋዊ ውጤታቸውን፣ ጋብቻ ሕጉን ተከትሎ ከተፈጸመ በኋላ በተጋቢዎቹ ስምምነት ግላዊ ግንኙነታውን እና ንብርት ነክ ጋንኙነታቸውን አስገዳጅ የሆኑ የሕግ ድንጋጌዎችን ሳይቃረኑ በጋብቻ ውላቸው መወሰን እንደሚችሉ፣ ይህ የጋብቻ ውል ከሌለ ሕጉ ጠቅላላ መሰረታዊ መርሆችን ያስቀመጠ ስለመሆኑ ተጋቢዎች ቀለብን ለቤተዘመድ ለሆኑ እና ለተቸገሩ መስጠት እንዳለባቸው እና የመሳሰለሉት ማስቀመጥ ችሏል፡፡ ሕጉ ይህን ሁሉ ያደረገው ተጋቢዎች በፍቅርና በሰላም እንዲኖሩና ወልደው ከብደው የህብረተሰቡን ቀጣይነት ለማረጋገጥ ነው፡፡

ሰዎች በዚች ምድር ላይ ሲኖሩ መጋጨታቸው ወይም በተለያየ ምክንያት የመሰረቱትን ጋብቻ ሊያፈርሱ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡ ሕጉ ጋብቻ የሚፈርስባቸውን ምክንያቶችና ውጤታቸውንም አስቀምጧል፡፡ ከነዚህ ምክንያቶች አንዱ ፍቺ ነው፡፡ ተጋቢዎች ሕጉን ጠብቀው እንደተጋቡ ሁሉ ፍቺ የግድ ሲሆን ደግሞ ሕጋዊ በሆነ ሁኔታ መፋታት እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡ ፍቺውን ተጋቢዎች በስምምነት ማድረግ እንደሚችሉ ወይም በአንዱ ወይም በሁለቱም ተጋቢዎች ጥያቄ እንደሚሆን ሕጉ አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪም የፍቺው ሕጋዊ ውጤት የእኩልነትን መርህ መሠረት አድርጎ መሆን እንዳለበትም ተገልፆአል፡፡ በመሆኖኑም በሕጋዊ መንገድ የተመሰረተው ጋብቻ በሕጋዊ መንገድ መፍረስ አለበት፡፡ ይህ ሕጋዊ ፍቺም ሕጋዊ ውጤት አለው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ፍርድ ቤት ቅጣት ማቅለያን ወይም ማክበጃን በሌላ ማቅለያ ወይም ማክበጃ ቀይሮ ማ...
ለተዋጣለት ወንጀል ምርመራ የሚጠቅሙ ቀዳሚ ነገሮች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024