አዲስ ለተወለደ ህፃን ልጅ ስም የማውጣት መብት፤ የእናት ወይስ የአባት? - የሕግ ባለሙያዎች ወግ

ከሰሞኑ በአንድ ጠበቆች፣ ዳኞች፣ ዓቃቢያነ ሕግች፣ የሕግ ምሁራን እና የሴቶች መብት አቀንቃኞች የተገኙበት የሴቶች እኩልነት እና ሰብዓዊ መብቶች በሚል ርእስ የተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ ተገኝቼ ሳለሁ፤ አንዲት ተሳታፊ ጠበቂት ሃሳቧን ስታጋራ ለህፃን ስያሜ የመስጠት መብት የወላጆች የጋራ መብት ነው ብላ በደፈናው ተናግራ ስትጨርስ የውይይቱ መሪ ይህን ሀሳብ በሕግ የተደነገገ መብት ነው ብላ ስትደግም ከተሳታፊዎች ጉርምምታ ሲበዛ ለምን አላጠራውም በሚል፤ ይህንን ንግግሯን የሚደግፍ የሕግ ማዕቀፍ ካለ በሚል ጥያቄ አቅርቤላት ነበር፡፡ አወያዪዋም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እና ሕገ-መንግሥቱ ይደነግጋል በማለት ምላሽ ስትሰጥ፤ በዚህ ነጥብ ላይ የጦፈ ክርክር ይነሳል፡፡

በአንድ ወገን ይህንን ስያሜ የመስጠት ቅድሚያ መብት የሚደነግገው የፍትሐብሔር ሕጉ ነው እንዲሁም በቤተሰብ ሕጉ በግልፅ የተደነገገ አንቀጽ የለም በሚል ሲቃወሙ፤ በሌላ ፀንፍ አወያዩዋን ጨምሮ ሌሎች ተሳታፊዎች ደግሞ የሴቶች እኩልነት በሕገ-መንግሥቱ ስለተደነገገ እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ስር ቤተሰብን በጋራ የማስተዳደር ኃላፊነት በጋራ መሆን አለበት በሚለው አንቀጽ ስር ይወድቃል በማለት ተከራከሩ፡፡ በመጨረሻም ከስምምነት መድረስ ሲያቅተን ጭብጥ ቀይረን ውይይቱን ቀጠልን፤ ነገር ግን እንደ አንድ የሕግ ባለሙያ ጉዳዩን የበለጠ ልመረምር ይገባል ብዬ ይህንን ዕልባት ያላገኘ ነጥብ ወደ ማውቃቸው የሕግ ምሁራን ወስጄ ሀሳባቸውን ስጠይቅ እዚህም ሁለት ጎራ የያዘ ምላሽ አገኘሁ፡፡ በዚህም የተነሳ ይህንን ነጥብ የበለጠ ለማጥራት ከሕግ ማዕቀፎቹ፣ ከመሰረታዊ የሕግ ፍልስፍና መርሆች እና ከፆታ እኩልነት አንጻር ለመመርመር ወደድኩ፡፡ ምንም እንኳ በውይይቱ አንዱን ጎራ ይዤ ስከራከር የነበረ ቢሆንም ለዚህ ፅሁፍ አላማ ሲባል ገለልተኛ ሆኜ የሁለቱንም ገራ ክርክር አካትቼ እንደሚከተለው አቀርባለሁ፡፡  

በመሰረቱ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ከመምጣቱ በፊት ቤተሰብን በሚመለከት ገዥ ድንጋጌዎችን በስሩ አቅፎ የነበረው የፍትሐብሔር ሕጉ ነበር፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉም በንጉሱ ዘመን እንደመውጣቱ ወንድን ከሴት ከፍ ያደረጉ ሕግጋትን በውስጡ አቅፎ ይዟል፡፡ ለምሳሌ በቤተሰብ አምዱ አባት የቤተሰብ ራስ መሆኑን እንዲሁም ቤተሰቡ የት እና በምን ሁኔታ መኖር እንዳለበት የመወሰን መብት የመሳሰሉት አቅፎ ይዟል፡፡

ከመንግሥት ለውጥ ጋር ተያይዞ አሁን የምንጠቀምበት ሕገ-መንግሥት ዴሞክራሲን አስተዋውቆ የጾታ እኩልነትን ሲያውጅ፤ ከዚህ ጋር የማይሄዱ ሕጎች የቤተሰብ ሕጉን ጨምሮ ተሻሽለዋል፡፡ በዚህም አግባብ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ወንድ እና ሴት በትዳር ውስጥ አብረው ሲኖሩ በግላዊም ሆነ በንብረት ላይ እኩል መብት እንደሚኖራቸው ይደነግጋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ከትዳር መፍረስ በኋላም በልጆች አሳዳጊነት እና ንብረት ክፍፍል ላይ እኩል መብት አላቸው በማለት ያትታል፡፡ ይህ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በስራ ላይ ሲውል ከዚህ ቀደም እንጠቀምበት የነበረውን የፍትሐብሔር ሕጉ ውስጥ የነበረውን የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌውች በሙሉ ሽሯል፡፡

በሌላ በኩል ስለ አንድ ሰው ስያሜ እና ተያያዥ ጉዳዮች (Law of Person) የሚያስተዳድሩት ድንጋጌዎች በፍትሐብሔር ሕጉ ከአንቀጽ አንድ ጀምሮ ይገኛሉ፡፡ በዚሁ ሕግ አንቀጽ 34-35 መሰረት ለአንድ ህፃን ልጅ ስያሜ የመስጠት መብት ቅድሚያ ለአባት መሆኑን ያትታል፡፡ በተጨማሪም አባት ሳይኖር የአባት ቤተሰቦች፣ ከሌሉ እናት እና የእናት ቤተሰቦች እያለ ቅደም ተከተሉን ያስቀምጣል፤ በዚሁ ሕግ እናት ለልጁ በተለምዶ የቤት ስም የማውጣት መብት ተሰጥጧታል፡፡ ይህ ስለ ሰዎች ግላዊ ሁናቴ የሚደነግገው ሕግ ስለ ቤተዘመድ ስም ያስቀመጣቸው አንቀፆች ጥቅም ላይ ካለመዋላቸው የተነሳ ተሸረዋል፤ ከነኚህ ስለ ቤተዘመድ ከሚያትቱት አንቀፆች ውቺ ያሉት ድንጋጌዎች ግን በስራ ላይ የሚገኙ ገዢ ሕግጋት ናቸው፡፡

አሁን ለዚህ ፅሁፍ መነሻ ወደሆነው የክርክር ነጥብ ስመለስ፤ በመጀመሪያ ስያሜ የመስጠት መብት የጋራ መብት ነው ከሚሉት ወገኖች መከራከሪያ ጭብጦችን ልዘርዝር፤

የፆታ እኩልነት በህገ-መንግሥት አንቀጽ 7፣ 25፣ 35 መሰረት እና በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 50፣ 54፣ና 66(1) ስር በመቀመጡ፤ ይህንን ሚቃረኑ ሕጎች ውጤት አልባ ናቸው፡፡ ስለዚህም ስለ ስያሜ በሚደነግገው የፍትሐብሔር ሕግ ስር ለአባት ስያሜ የመስጠት ቅድሚያ የሚሰጠው አንቀጽ ውጤት አልባ ይሆናል፡፡

ለአንድ ሕፃን ልጅ ስያሜ የመስጠት ጉዳይን የሚመለከተው ሕግ የፍትሐብሔር ሕጉ ሳይሆን የቤተሰብ ሕጉ ነው፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ከልጅ ስያሜ ባለፈ እናትን እና አባት ስለሚያካትት የግል ሳይሆን የቤተሰብ ጉዳይ ስለሚሆን በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ስር ሊካተት ይገባል፡፡

የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ይህንን የስያሜ ጉዳይ በተመለከተ በቀጥታ የተቀመጠ አንቀጽ ባይኖረውም፤ ቤተሰብን በጋራ ስለማስተዳደር የሚያትተው አንቀጽ 50(2) እንደሚያዘው ‹ባልና ሚስት በማናቸውም ሁኔታ በጋራ ተባብረው የቤተሰባቸውን ጥቅም ማስከበርና ጥበቃ የማድረግ፤ በተጨማሪም ልጆቻቸው ኃላፊነት የሚሰማቸው ዜጎች እንዲሆኑ ለማስቻል በጥሩ ትምህርት እና እንክብካቤ ሊያሳድጉ ይገባል›፡፡ በመሆኑም እናትና አባት ለልጆቻቸው አሳዳጊና ተንከባካቢ ‹Guardian & Tutor› ስለሆኑ ይህ ሀላፊነታቸው ደግሞ በተዘዋዋሪ ‹Impliedly› ስያሜ መስጠትን ያካትታል፡፡ ስለዚህ አንቀጽ 50(2) በቀጥታ ባይገልፀውም ተለጥቶ ሲነበብ ስያሜ መስጠትንም የሚጨምር ይሆናል፡፡

ከላይ በተዘረዘሩት ምክንያቶች የተነሳ የፍትሐብሔር ሕጉ የስያሜ ድንጋጌዎች ከፆታዊ እኩልነት መብት ጋር ተፃራሪ ስለሆነ ሊሻር እነደሚገባው፣ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 50(2) በቀጥታ ባይገልፀውም ተለጥቶ ሲነበብ ስያሜ መስጠትንም የሚጨምር ስለሆነ እና ጉዳዩ ከሚያካትታቸው ሰዎች አንፃር ከግላዊ ባህሪ ይልቅ ቤተሰብን የሚመለከት ስለሆነ ስያሜ የመስጠት መብት በሁለቱም ተጋቢዎች የጋራ ስምምነት መሰረት የሚከናወን ይሆናል በሚል ተከራክረዋል፡፡

በሌላ በኩል የዚህ ሀሳብ ተቃራኒዎች በበኩላቸው የሚከተሉትን መከራከሪያ ነጥቦች በማስቀመጥ ስያሜ የመስጠት መብት በፍትሐብሔር ሕጉ ድንጋጌ መሰረት ቅድሚያ የአባት ነው በማለት ተከራክረዋል፤

በመጀመሪያ ጉዳዩ የአንድን ሰው ስያሜን የሚመለከት ስለሆነ የግል ጉዳይ ነው፡፡ ምክንያቱም ስም ለልጁ መጠሪያ እስከሆነ ድረስ የቤተሰብ ሕግ ገዢ ሊሆን አይችልም፡፡ በፍትሐብሔር ሕጉ በግልፅ ስለ ስያሜ የተደነገጉ ድንጋጌዎች እያሉ በተውሶ ከሌላ ሕግ መጠቀም ከሕግ ፍልስፍና አንፃር ተገቢ አይደለም፡፡

ሀገራችን የምትከተለው የሕግ ስርዓት ‹Civil Law Legal System› በመፅሀፍ የተደነገጉ ሕጎች ስለሚጠቀም አንቀፆች በግልፅ ለታለመላቸው አላማ ብቻ ነው ሊውሉ የሚገባው፡፡ በመሆኑም የህገ-መንግሥቱ የእኩልነት ድንጋጌዎች እና የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 50(2) በልኩ ሊተረጉመው ይገባል እንጂ የሕግ ስርዓታችን በማይፈቅድ መልኩ እነደ አውሮፓና አሜሪካ ሀገራት ሊለጠጥ አይገባም፡፡

በተያያዘም አንድ ሕግ አንድን ነገር በጋራ ይወሰን የሚል ከሆነ በስሩ ስምምነት ላይ መድረስ ካልተቻለ ምን ሊደረግ እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ ስለዚህ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 50(2) ስያሜን ይጨምራል ብንል እንኳ፤ አባት እና እናት መስማማት ካቃታቸው ምን ሊደረግ እነደሚገባ ሊያስቀምጥ ይገባ ነበር፡፡ በመሆኑም ከላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ የመፍትሄ ሀሳብ አለማስቀመጡ ስያሜን እንደማያካትት ገላጭ ማስረጃ ነው፡፡

የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሰረት በአንዳንድ ልዩ በሆኑ ሆኔታዎች እናት እና አባት በህይወት እያሉ የአሳዳጊነት መብት ለሌላ ሦስተኛ ወገን ተላልፎ ሊሰጥ የሚችልባቸው ሁኔታዎች አሉ፡፡ ስለዚህ በአሳዳጊነት ‹Guardian & Tutor› መብት ውስጥ ስያሜ መስጠት ከተካተተ ለሦስተኛ ወገኖች መብቱ ሊተላለፍ ሊሆን ነው ማለት ነው፡፡

አንድ ሕግ ከሚሻርባቸው መንገዶች መካከል በሌላ ሕግ መውጣት ምክንያት እና ጥቅም ላይ ባለመዋል(ባለመጠቀም) ይገኙበታል፡፡ በመሆኑም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በስራ ላይ ሲውል ሊሽር የሚገባው በፍትሐብሔር ሕጉ ስር የነበሩትን ስለ ቤተሰብ የሚደነግጉ አንቀፆች እንጂ ስለግል ሕግ ‹Law of Person› አንቀፆችን ሊሆን አይገባም፡፡ እንዲያውም ጥቅም ላይ ባለመዋላቸው የተነሳ ስለ የቤተዘመድ ስም ‹Family Name› የሚያትቱት አንቀፆች ተሻሩ እንጂ እንኳን ለልጁ ቅድሚያ ስም ማውጣት ይቅርና ሚስት ራሷ የአባቷን ስም እንድትቀይር ልትገደድ ትችል ነበር፡፡

በመሆኑም ስም የማውጣት መብት ለአባት ቅድሚያ መስጠቱ እኩልነትን አይፃረርም፡፡ ምክንያቱም የፆታ እኩልነት ማለት በሁሉም ረገድ እኩል ይሁኑ ማለት ሳይሆን እንደ ሁኔታው አንዱ ሌላው ላይ ጫና እንዳያሳድር ለመጠበቅ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ለሴቶች ከህገ-መንግሥቱ ጀምሮ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እና ሌሎች ሕጎች ቅድሚያና ልዩ ጥበቃ ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ ለልጅ ስያሜ ቅድሚያ የመስጠት መብት በፍትሐብሔር ሕጉ ስር እንደተቀመው የአባት ነው፡፡

ማጠቃለያ

በእውነቱ ከሆነ ከላይ የተጠቀሱት የሕግ ባለሙያዎች ክርክር እንዳለ ቢሆንም በተግባር ስም እኔ ላውጣ በሚል ወደ ፍ/ቤት ያመራ መዝገብ ወይም የሰበር ውሳኔ እስከአሁን ያለ አይመስለኝም(በግሌ አላጋጠመኝም)፡፡ በተጨማሪም የማህበረሰባችን የቤተሰብ አወቃቀር እና የቤተሰባዊነት መርህ እንደሚያሳየው አንድ ህፃን ልጅ ሲወለድ በብዛት ስም የሚያወጡት ከወላጆቹ ይልቅ ጓደኛ፣ ጎረቤት እና ዘመድ አዝማድ የመሳሰሉ ሰዎች በመሆናቸው ስያሜ ላይ ብዙም ግጭት አይስተዋልም፡፡ ቢያጋጥምም ልጅ ማግኘት ትልቅ የደስታ ምልክት ስለሆነ እዛው  በቤተሰቡ ውስጥ የይፈታል እንጂ ወደ ፍ/ቤት የመምጣት ዕድሉ ጠባብ ነው፡፡

ነገር ግን እንደሕግ ባለሙያ ወጥ የሆነ አካሄድ ሊኖር ስለሚገባ እና ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ቢመጣ እንኳ የተለያየ ውሳኔ እንዳይኖር በሚል ይህን ክርክር ለማሳወቅና ግልፅ ለማድረግ ታሳቢ ያደረገ ፅሁፍ ነው፡፡ በመሆኑም እንደ ገለልተኛ ባለሙያ ስመለከተው ሁለቱም ጎራዎች ተገቢ የሆነ የክርክር ነጥብ አላቸው፡፡ የመጀመሪያው ጎራ የፍትሐብሔሩ የስያሜ አንቀፆች ከፆታዊ እኩልነት ጋር መጋጨታቸው እውን ነው፤ በሌላኛው ጎራ ደግሞ በግልፅ ያልተሻረ ሕግ እያለ በሌላ ሕግ መገዛት ተገቢ አለመሆኑ እና አንድን አንቀጽ ከታለመለት አላማ ውጪ መለጠጥ ከመሰረታዊ የሕግ መርሆች አንፃር የሚፃረር መሆኑ እውነት ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኔ እይታ፤ ምንም እንኳ ሕጉ እኩልነት የሚያጠነጥን ባይሆንም በግልፅ እስካልተሻረ ድረስ በደፈናው መሸፋፈን የለብንም፡፡ ስለዚህ የትኛው ሀሳብ ሚዛን ይደፋል የሚለው ለአንባቢዎች፤

‹ፍርዱን ለናንተው ብያለሁ›

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የማዕድን ሥራዎች ፈቃድ የተሰጠው ሰው እና በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ንዑስ-ሥራ ...
የሽያጭ ውልን የተመለከቱ አንዳንድ ነጥቦች ከሰበር ውሳኔ ጋር ተገናዝቦ የቀረበ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 19 March 2024