Font size: +
9 minutes reading time (1875 words)

ስለባልና ሚስት የጋራ እና የግል ንብረቶች በተመለከተ የፌዴራሉን የቤተሰብ ሕግና የተመረጡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎችን መሰረት በማድረግ የቀረበ

በፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ አዋጅ ቁጥር 213/1992 ከአንቀጽ 2 እስከ 4 በተጠቀሱት ድንጋጌዎች  ጋብቻ በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣ በኃይማኖት እና በባሕል ሥርዓት መሠረት ሊፈጸም ይችላል፡፡ ከእነዚህ የጋብቻ መፈጸሚያ ስርዓቶች ውስጥ በአንደኛው ስነ-ስርዓት ጋብቻ የተፈጸመ እንደሆነ በጥንዶቹ መካከል በሕግ እውቅና የተሰጠው የትዳር ግንኙነት ተመስርቷል ይባላል፡፡ ጥንዶቹ ከዚህ በላይ ከተጠቀሱት የጋብቻ መፈጸሚያ መንገዶች ውስጥ በአንዱ ጋብቻ ቢፈጽሙ የጋብቻ ውጤትን መሠረት በማድረግ በሕግ የጋራ እና የግል ንብረቶቻቸው ላይ የሚኖረው ውጤት ተመሳሳይ ነው፡፡  

በዚህ ጽሑፍ ጋብቻ በተጋቢዎቹ የግልና የጋራ ንብረት ላይ ስለሚኖረው ውጤት እንዲሁም በጋብቻ ውስጥ የተፈራ ንብረት የግል ወይም የጋራ ሊባል ሲለሚችልበት የሕግ አግባብ፤ በተጋቢዎቹ መካከል የሚደረግ የስጦታ ውል ህጋዊ ውጤቱና የአደራረግ ስነ ስርዓቱ፣በትዳር ውስጥ የወጣ ወጪ ለትዳር ጥቅም ዋለ ሊባል ስለሚችልባቸውና የማይቻልባቸው ሁኔታዎች ከፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ እንዲሁም ከሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ውሳኔዎች አንጻር በተመረጡ የንብረት አይነቶች በመከፋፈል ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡

የግል ወይም የጋራ ንብረት ለማለት መሠረቱ

ጋብቻ በተጋቢዎች መካከል በንብረት በኩል የሚኖረው ውጤት በጋብቻ ውል አማካኝነት ሊወሰን ይችላል፡፡ የጋብቻ ውል በፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 42 መሠረት ተጋቢዎቹ ጋብቻው ንብረታቸውን በተመለከተ ስለሚያስከትለው ውጤት ጋብቻውን ከመፈጸማቸው በፊት ወይም እጅግ ቢዘገይ ጋብቻውን በሚፈጽሙበት እለት በውል መወሰን ይችላሉ፡፡ በአንቀጽ 43(1)(2) መሠረት በሕግ የተከለከለ ሰው የጋብቻ ውል ለመዋዋል የሕግ ችሎታ ያለው ሲሆን ይህም ውል እርሱ እራሱ ሊፈጽመውና በፍርድ ቤት ሊጸድቅ ይገባል፡፡ የጋብቻ ውል በጽሑፍ መደረግና በአራት ምስክሮች (ሁለት በባል ወገን ሁለት በሚስት ወገን ) ሆነው ሊፈርሙበት ይገባል፡፡ ጥንዶቹ ከዚህ በላይ በተገለጸው አኳሀን ጋብቻ በንብረት ረገድ የሚኖረውን ውጤት መወሰን የሚችሉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ውል ሳያደርጉ የተጋቡ እንዲሁም የፈጸሙት ውል በሕግ ፊት የማይጸና በሆነ ጊዜ ጋብቻው በንብረት በኩል የሚኖረው ውጤት የሚገዛው በቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎችና በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር ችሎት በሚሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜዎች ይሆናል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ ከዚህ በታች ባለው ክፍል የጋብቻ ውል በሌለ ጊዜ ወይም ኖሮም በሕግ ፊት የማይጸና በሚሆንበት ጊዜ የተጋቢዎቹ ንብረት የግል ወይም የጋራ ስለሚባልበት የሕግ አግባብ ዳሰሳ አደርግለሁ፡፡

የግል ንብረት 

በፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 57 መሠረት ባልና ሚስት ጋብቻ በሚፈጽሙበት ጊዜ በየግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ በየግላቸው ያገኟቸው ንብረቶች የግል ንብረቶቻቸው ሆነው ይቆጠራሉ፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው ጋብቻ በሚፈጽምበት ጊዜ በግል የነበረው ንብረት ከጋብቻ በኋላም የግል ሆኖ እንደሚቀጥልና ጋብቻ ከፈጸመ በኋላ በውርስ ወይም በስጦታ የሚያገኘው ንብረቶች በጋብቻ ውስጥ የግል ሆነው እንደሚቀጥሉ በመርህ ደረጃ ተደንግጓል፡፡ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 58(1) መሠረት ባልና ሚስቱ ከተጋቡ በኋላ አንዱ የግል ሀብቱ በሆነ ንብረት ለውጥ ያገኘው ወይም በግል ገንዘቡ የገዛቸው ወይም የግል ንብረቱን ሽጦ የሚያገኘው ገንዘብ የግል ይባልልኝ ብሎ ለፍርድ ቤት ጥያቄ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ ያጸደቀው እንደሆነ የግል ሀብቱ ይሆናል፡፡ የባልና ሚስት የጋራ ሀብትን በተመለከተ በአንቀጽ 62(1) ስር የተደነገገ ሲሆን በዚህም ድንጋጌ መሠረት ባልና ሚስቱ ከግል ጥረታቸውና ከግል ወይም ከጋራ ንብረታቸው የሚያገኟቸው ገቢዎች ሁሉ የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ፡፡ በቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 62(2) እንደተጠቀሰው ከዚህ በላይ በአንቀጽ 58(2) መሠረት የአንደኛው ተጋቢ የግል ሀብት ነው ካልተባለ በስተቀር ባልና ሚስት ከተጋቡ በኋላ በግብይት የሚያገኙት ንብረት ሁሉ የጋራ ሀብታቸው ይሆናል፡፡ እንዲሁም በአንቀጽ 62(3) በስጦታው ውል ወይም በኑዛዜው ቃል በሌላ አኳሀን ካልተመለከተ በስተቀር በስጦታ ወይም በኑዛዜ ለተጋቢዎቹ የተሰጧቸው ንብረቶች ሁሉ የጋራ ሀብቶች ይሆናሉ፡፡

የቤተሰብ ህጉ ያስቀመጣቸውን ድርጋጌዎች በዚህ ረገድ ካየን  በጋብቻ ውስጥ የተፈሩ ንብረቶች የጋራ ናቸው ወይስ የግል? በሚለው ነጥብ ላይ የተለያዩ ንብረቶችን በመጥቀስ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገቦቹ ከሰጣቸው አስገዳጅ ውሳኔዎች ጋር በማጣቀስ በሚከተለው መልኩ ዳሰሳ አደርጋለሁ፡፡

ቤትና ይዞታን በተመለከተ

ባልና ሚስት በትዳር ውስጥ ሲኖሩ ከሚያፈሯቸው ንብረቶች መካከል ቤትና ይዞታ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል፡፡ እነዚህ ንብረቶች ይዞታው ከጋግብቻ በፊት ተፈርቶ ቤቱ ደግሞ በጋብቻ ውስጥ የሚሰራት እድል ሰፊ ነው፡፡ ከዚህም ባሻገር በይዞታው ላይ ከጋብቻ በፊት ቀድሞ የነበረ ቤት ይኖርና ጥንዶቹ ከተጋቡ በኋላ በቤቱ ላይ እድሳት የሚያደርጉበት እንዲሁም ተጨማሪ ክፍሎችን አስፋፍተው የሚሰሩበት እድልም ሰፊ ነው፡፡ በእነዚህ ሁኔታዎች ጥንዶች ሲኖሩ ቆይተው ትዳራቸው በፍቺ አልያም በሞት በሚፈርስበት ጊዜ ይዞታው ላይ ያለው ንብረት የጋራ ወይም የግል ሊባል ይገባል የሚል ክርክር በፍርድ ቤቶች ዘንድ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡

ይዞታው ከጋብቻ በፊት በምሪት የተገኘ ሆኖ ቤቱ ግን በጋብቻ ውስጥ በጋራ የተሰራ በሆነ ጊዜ  

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 14479 በቅጽ 4፣ በመ/ቁ 26130 በቅጽ 6 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ “ ቤት የተሰራበት ቦታ አንደኛው ወገን ጋብቻ ከመፈጸሙ በፊት በመንግስት ተመርቶ ያገኘው ሲሆንና በዚሁ ቦታ ላይ ባልና ሚስቱ በጋብቻ ውስጥ ቤት ቢሰሩ ቤቱ በጋብቻ ውስጥ ስለተሰራ የጋራ ሀብት ነው ይዞታው ግን ከጋብቻ በፊት ስለተመራ የግል ነው ሊባል አይገባል በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ለውሳኔውም መሠረት ያደረገው በህገ መንግስቱ አንቀጽ 40(3) መሠረት ግለሰቦች በመሬት ላይ የይዞታ መብት እንጂ የባለቤትነት መብት ስለማይኖራቸው፣ቤቱ እና ቤቱ የተሰራበት ቦታ ለየብቻ ለያይቶ በመመልከት ቤቱ የጋራ ነው ቦታው ግን የግል ነው ሊባል ስለማይገባ በማለት ቤቱም ሆነ ይዞታው የጋራ ሀብት ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ 

የአንደኛው ተጋቢ የግል የሆነ ቤትን በጋብቻ ውስጥ ባልና ሚስቱ እድሳት ካከናወኑ

ባልና ሚስት ከመጋባታቸው በፊት የአንደኛው ተጋቢ የነበረውን የግል ቤት በጋብቻ ውስጥ አድሰው ሰርተው ከሆነ የተደረገው እድሳት በቤቱ ላይ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ በመሆኑ የጋራ ንብረት ሊባል ይገባል በሚልና የተደረገው እድሳት መሰረታዊ ለውጥ የማያመጣ በመሆኑ ቤቱ የግል ሊባል ይገባል የሚል ክርክር ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 31833 በቅጽ 6 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ የተደረገው እድሳት መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ነው ወይስ አይደለም? የሚለውን አከራካሪ ጭብጥ ለመፍታት የቤትና የግንባታ እውቀት ያለው ልዩ አዋቂ በፍ/ብ/ሥ/ሥ/ሕ/ቁ 136 መሠረት ፍርድ ቤቶች  መድበው በማስጠናት አዋቂው በሚሰጠው ሙያዊ ምላሽ መሠረት በቤቱ እድሳት የተደረገው ለውጥ መሰረታዊ ከሆነ ቤቱን የጋራ በማለት መወሰን፣ የተደረገው የዕድሳት ለውጥ መሰረታዊ ካልሆነ ቤቱን የግል ብሎ መወሰን ይገባል ሲል ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ በሰ/መ/ቁ 45207 በቅጽ 11 በተሰጠው የሕግ ትርጓሜ በቤቱ ላይ የተደረገው መሰረታዊ ለውጥ የማያመጣ እድሳት ከሆነና ጋብቻው ከፈረሰ አንደኛው ተጋቢ የሚኖረው መብት ለእድሳት ከወጣው ወጪ ግማሹን መካፈል ነው እንጂ ቤቱን አይመለከተው፡፡

ከጋብቻ በፊት አንደኛው ተጋቢ ተበድሮ ቤት ቢሰራ እና ብድሩ በጋብቻ ጊዜ ከጋራ ሀብት ( ደመወዝ) ቢከፈል ቤቱ የጋራ? ወይስ የግል ሊባል ይገባል?

አንደኛው ተጋቢ ከጋብቻ በፊት ተበድሮ በብድሩ ገንዘብ ቤት ቢሰራ እና ብድሩን በጋብቻ ጊዜ ከጋራ ሀብት( ደመወዝ) ቢከፍል ይህ ቤት የባልና ሚስቱ የጋራ ሀብት ሊባል ይገባል ወይስ አይገባም? በሚሉ ጭብጦች ላይ ክርክር ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 35376 ቅጽ 5 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ ቤቱ ከጋብቻ በፊት የተሰራ ሆኖ እዳው ከጋራ ንብረት (ደመወዝ) በጋብቻ ውስጥ በመከፈሉ ቤቱ የጋራ ሊባል አይገባም በማለት ቤቱን ከጋብቻ በፊት የሰራው ተጋቢ ወስዶ በጋብቻ ውስጥ ከደመወዙ ላይ የከፈለው እዳ ግማሹን አንደኛው ተጋቢ የሚወስድ ይሆናል ሲል ወስኗል፡፡  

በውርስ በተገኘ ንብረት ምትክ በካሳ መልክ ከመንግስት በተሰጠ ገንዘብ የተሰራ ቤትን በተመለከተ

አንደኛው ተጋቢ በውርስ የሚያገኛቸው ንብረቶች በመንግስት ለልማት ይፈለጋሉ ተብለው በመወረሳቸው ምክንያት በዚሁ ምትክ ባገኘው የካሳ ገንዘብ ቤት ቢሰራ ይህ ቤት የባልና ሚስቱ የግል ነው ወይስ የጋራ? በሚል ክርክር ሲነሳ ይስተዋላል፡፡ ይህን መሠረት በማድረግ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መ/ቁ 203715(ያልታተመ) ላይ በሰጠው ትርጓሜ የካሳ ገንዘብ ተቀብሎ ቤት የሠራው ተጋቢ ቤቱን የሠራው በካሳ ገንዘቡ መሆኑን በመጥቀስ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 58 መሠረት የግል ሀብት እንዲባልለት ለፍርድ ቤት አቤቱታ አቅርቦ ፍርድ ቤቱ የግል ሀብት መሆኑን ሊያጸድቅለት ይገባል በማለት ይህ ባልሆነበት ሁኔታ በካሳ ብር ብቻ ቤቱ በመሰራቱ የግል ሀብት ሊባል የሚችልበት የሕግ አግባብ የለም ሲል ወስኗል፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ የካሳው ገንዘብ በባንክ የተቀመጠ ከሆነ ግን በሰ/መ/ቁ 65708 ቅጽ 13 ላይ በተሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት ገንዘቡ የካሳ ተቀባዩ ተጋቢ የግል ሀብት ተደርጎ ይቆጠራል፡፡

የስጦታ ውል በባልና ሚስት መካከል የሚደረግበት የሕግ አግባብ

በፌዴራሉ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 73 መሠረት ባልና ሚስት ተጋብተው በሚኖሩበት ጊዜ በመካከላቸው የሚያደርጓቸው ውሎች ፍርድ ቤት ቀርቦ ካልጸደቀ በስተቀረ ውጤት አይኖረውም በማለት ተደንግጓል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 209994 ( የልታተመ) በሰጠው የሕግ ትርጓሜ የስጦታ ውሉ በሰነዶች ምዝገባ ማረጋገጫ ጽ/ቤት ዘንድ ቀርቦ መደረጉ በቤተሰብ ህጉ በአንቀጽ 73 ላይ የተቀመጠውን አስገዳጅ ድንጋጌ ሊተካ ስለማይችል ከባልና ሚስት ግንኙነት ልዩ ባህሪ አንጻር ጉዳዩ ታይቶ ስጦታው በፍርድ ቤት ካልጸደቀ በስተቀር ሊጸና አይገባም ሲል ወስኗል፡፡ ስለዚህ ሰበር በሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት ባልና ሚስቱ የሚያደርጓቸው የሥጦታ ውሎች በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ዘንድ ቀርበው ያደረጉት ቢሆንም እንኳ በፍርድ ቤት አቅርበው ካላጸደቁት የሚጸና ስጦታ ውል ሊሆን አይችልም ማለት ነው፡፡

ለትዳር ጥቅም የዋለ ገንዘብ

ጥንዶቹ በጋብቻ ውስጥ እያሉ በሽያጭም ሆነ በሌላ አግባብ የተገኘ ገንዘብ ለትዳር ጥቅም እንደዋለ የሕግ ግምት እንደሚወሰድ በቤተሰብ ህጉ ከአንቀጽ 85-93 ያሉ ድንጋጌዎች ያስገነዝቡናል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መ/ቁ 27697 በቅጽ 5 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ አንድ ንብረት የተሸጠው ትዳር ጸንቶ ባለ ጊዜ ከሆነ ገንዘቡ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ  85-93 ባሉ ድንጋጌዎች መሠረት ለትዳር ጥቅምት እንደዋለ የሕግ ግምት ስለሚወሰድ ገንዘቡ በከፊል ወይም በሙሉ የሚገኝና ለትዳር ጥቅምት አለመዋሉን የማስረዳት ሸክሙ ለትዳር ጥቅም አልዋለም የሚለው ተጋቢ ነው በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ በሰ/መ/ቁ 202105( ያልታተመ) ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ በጋብቻ ወቅት የወጣ ወጪ ለትዳር ጥቅም መዋሉ ግምት እንደሚወሰድበት የሕግ ግምት መኖሩ እንደተጠበቀ ሆኖ ባልና ሚስቱ በፍቺ ወቅትና ጸብ ውስጥ ባሉበት ጊዜ ገንዘብ ሲወጣ ለትዳር ጥቅም ውሏል ሊባል የሚችልበት የሕግ ምክንያት አይኖርም በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ ሰበር በተለያየ ጊዜ የሰጣቸውን የሕግ ትርጓሜዎች ስንመለከት አንድ ወጪ የወጣው በትዳር እና በሰላም እየኖሩ ከሆነ ወጪው ለትዳር ጥቅም እንደዋለ የሕግ ግምት ይወሰዳል፡፡ ወጪው ለትዳር ጥቅም ያልዋለ ከሆነ አልዋለም የሚለው ተጋቢ የማስረዳት ሸክም ይኖርበታል፡፡ በሌላ መልኩ ወጪው የወጣው ግራቀኙ ጸብ ላይ እና በፍቺ ሂደት ውስጥ በነበሩበት ወቅት የሆነ እንደሆነ ወጪው ለትዳር ጥቅም ወጥቷል ሊባል አይገባም ማለት ነው፡፡

የኮንዶሚኒየም ቤት  

የኮንዶሚኒየም ቤት  አስቀድሞ በሚደረግ የረጅም ጊዜ ቅድመ ቁጠባን መሠረት አድርጎ በተለያየ ጊዜ በሚወጣ እጣ ለባለእድለኛው የሚተላለፍ ቤት ነው፡፡ በእነዚህ ሂደቶች ውስጥ የቤት ባለቤት የሚሆነው ወገን ቁጠባውን ጋብቻ ከመመስረቱ በፊት አስቀድሞ ሲቆጥብ ቆይቶ እጣው በጋብቻ ውስጥ ሊወጣ ይችላል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ቁጠባውና እጣው ከጋብቻ በፊት ሆኖ የቤት ባለቤት የሚያደርገው የሽያጭ ውል በጋብቻ ውስጥ የሚፈረምበትና የቤቱ ቁልፍ ርክክብ የሚከናወንበት ሂደትም ይኖራል፡፡ በእነዚህ ሁሉ ክስተቶች በባልና ሚስቱ መሀል አለመግባባት በሚፈጠርበት ወቅት የኮንዶሚኒየም ቤቱ የጋራ ወይስ የግል ንብረታቸው የሚለው ጥያቄ አከራካሪ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ ከዚህ በታች የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰበር መዝገቦቹ የሰጠውን የሕግ ትርጓሜ መሠረት በማድረግ አጭር ዳሰሳ ለማድረግ እሞክራለሁ፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 74451 በቅጽ 14 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት የኮንዶሚኒየም ቤት የተገኘው በጋብቻ ጊዜ ከሆነ በአንደኛው ተጋቢ ስም የተገኘው የኮንዶሚኒየም ቤት ቅድመ ክፍያ በጋብቻ ወቅት ካፈሩት የጋራ ንብረት የተከፈለ ከሆነ፣ ቤቱን ለማሳመርና የቤቱን ፓርትሽን ለመስራት በጋብቻ ውስጥ ያፈሩትን ገንዘብ ከተጠቀሙ ቤቱ የባልና ሚስቱ የጋራ ሀብት እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም የኮንዶሚኒየም ቤቱ እና ያለበት እዳ እንደማንኛውም ንብረት የጋራ ስለሚሆን ከተስማሙ በስምምነት መስማማት ካልቻሉ ተሸጦ እዳው ተከፍሎ ቀሪውን ባልና ሚስቱ ሊካፈሉ ይገባል እንጂ አንደኛው ከፍሎ ያስቀር ማለት የተጋቢዎቹን የእኩልነት መብት የሚጥስ ነው፡፡

ሰበር በቅጽ 10 በመ/ቁ 51893 በሰጠው የሕግ ትርጓሜ መሠረት ለኮንዶሚኒየም ቤት አንደኛው ተጋቢ ከማግባቱ በፊት ተመዝግቦ እጣው በጋብቻ ጊዜ የወጣ ከሆነ እና የቤቱ ባለቤት የሚያደርጋቸው የሽያጭ ውል በጋብቻ ውስጥ እያሉ ከተፈጸመ የኮንዶሚኒየም ቤቱ በቤተሰብ ህጉ አንቀጽ 62(2) መሠረት በጋብቻ ጊዜ በግብይት የተገኘ ሊባል የሚችል ስለሆነ የጋራ ሀብት ነው፡፡

የንግድ ፈቃድ

ባልና ሚስቱ ጋብቻቸውን ከመፈጸማቸው በፊት አንደኛው ተጋቢ የንግድ ፈቃድ የተሰጠው ቢሆንና ይህን የንግድ ፈቃድ መሠረት በማድረግ በአነስተኛ እና በጥቃቅን ማህበራት በጋብቻ ውስጥ ቢደራጅ የንግድ ቤቱም በትዳር ውስጥ ከተሰጠው የንግድ ፈቃዱ ብቻ ከጋብቻ በፊት በመውጣቱ የንግድ ሱቁ ከጋብቻ በፊት ያፈራውት የግል ንብረቴ ነው ማለት አይቻልም ሲል የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 136872 በቅጽ 22 ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ከጋብቻ በፊት የንግድ ፈቃድ ወጥቶ የንግድ መስሪያ ሱቅ በጋብቻ ውስጥ የተገኘ ከሆነ ሱቁ የተጋቢዎቹ የጋራ ሀብት ነው፡፡

መደምደሚያ

ከዚህ በላይ በተጠቀሰው መሠረት ባልና ሚስቱ የጋብቻ ውል ካልፈጸሙ ወይም የፈጸሙት የጋብቻ ውል በሕግ ፊት የማይጸና በሆነ ጊዜ በትዳር ውስጥ የሚያፈሯቸው ንብረቶች የግል ወይም የጋራ ናቸው ለማለት የቤተሰብ ሕግ ድንጋጌዎችና የሠበር ውሳኔን መሠረት ያደርጋል፡፡ በትዳር ውስጥ የወጣ ወጪም ለትዳር ጥቅም የወጣ ነው የሚል የሕግ ግምት የሚወሰድበት ቢሆንም ጥዶቹ በፍቺ ወቅት እና በጸብ ውስጥ ሳሉ ያወጡት ወጪ ለትዳር ጥቅም ዋለ ሊባል አይገባም፡፡ የኮንዶሚኒየም ቤት እጣ ከጋብቻ በፊት ቢወጣም የቤት ባለቤት የሚያደርገው የሽያጭ ውል በጋብቻ ወስጥ ከተፈረመ ቤቱ የባልና ሚስቱ የጋራ ሀብት ነው፡፡ አንደኛው ተጋቢ ይዞታውን ከጋብቻ በፊት በምሪት ቢያገኘውና በጋብቻ ውስጥ ቤት ቢሰሩ ቤቱ የባልና ሚስቱ የጋራ ሀብት ነው፡፡  ባልና ሚስቱ የስጦታ ውል ካደረጉ የስጦታ ውሉ በሰነዶች ምዝገባ እና ማረጋገጫ ጽ/ቤት ቢደረግም በፍርድ ቤት ቀርቦ ካልጸደቀ በቀር ዋጋ አይኖረውም፡፡ በውርስ የተገኘ ቦታ ለልማት ተፈልጎ በምትኩ ከመንግስት ገንዘብ ቢሰጥና ገንዘቡ በባንክ ያለ ከሆነ የውርስ ተቀባዩ ተጋቢ የግል ሀብት ነው፡፡ ሆኖም ግን በዚህ ገንዘብ ቤት ቢገዛ የተገዛው ቤት በውርስ ሀብት ምትክ በተሰጠ ገንዘብ መሆኑን በመጥቀስ የግል ተብሎ ይጸድቅ ዘንድ ለፍርድ ቤት አቤቱታ ቀርቦ ካጸደቀ በስተቀር የግል ሊባል አይገባም፡፡ የአንዱ ተጋቢ የግል የነበረ ቤት በጋብቻ ውስጥ እድሳት ካደረጉ የተደረገው እድሳት መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ቤቱ የጋራ ሀብት ሊሆን ይገባል፡፡ እድሳቱ መሰረታዊ ለውጥ የማያመጣ ከሆነ ቤቱ ከጋብቻ በፊት ያፈራው ተጋቢ የግል ንብረት ይሆናል፡፡ 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የግልግል ስምምነት /Arbitration Agreement/ እና የፍርድ ቤቶች ሥል...
የወንጀል ምርመራና የፍርድ ቤቶች ሚና

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - ጋዜጠኛ ፍቅሩ በላይ ከ on Wednesday, 20 September 2023 18:24

ጋዜጠኛ ፍቅሩ በላይ ከቦንጋ ነው ስለ ህግ ግንዛቤው ስላካፈልከን እውቀት እያመሰገንኩ ጥያቄ አለኝ፣ ይሄውም ከሁለቱ ተጋቢዎች አንዱ ከጋብቻ በፊት(ቀደም ብሎ)በቤተሰብ ጉባኤ በሽማግሌ ተወስኖ የተሰጠው የውርስ ይዞታ ያለው ሆኖ ከጋብቻ በኋላ መኖሪያ ቤት ተገንብቷልና አይበለውና ፍቺ ብከሰት ቤቱና ይዞታው የጋራ ነው ወይስ የግል ይሆናል? የህግ አንቀፆችስ በዚህ ላይ ምን ይላሉ??

ጋዜጠኛ ፍቅሩ በላይ ከቦንጋ ነው ስለ ህግ ግንዛቤው ስላካፈልከን እውቀት እያመሰገንኩ ጥያቄ አለኝ፣ ይሄውም ከሁለቱ ተጋቢዎች አንዱ ከጋብቻ በፊት(ቀደም ብሎ)በቤተሰብ ጉባኤ በሽማግሌ ተወስኖ የተሰጠው የውርስ ይዞታ ያለው ሆኖ ከጋብቻ በኋላ መኖሪያ ቤት ተገንብቷልና አይበለውና ፍቺ ብከሰት ቤቱና ይዞታው የጋራ ነው ወይስ የግል ይሆናል? የህግ አንቀፆችስ በዚህ ላይ ምን ይላሉ??
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 14 December 2024