የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ በኢትዮጵያ

በሀገራችን ኢትዮጵያ የተሸከርካሪ አደጋ በእጅጉን እየበዛ እና ከፍተኛ የሆነ የሞትና የንብረት ጉዳት እያስከተለ ይገኛል፡፡ የበርካቶች ህይወት አጥፍቷል፣ አካል አጉድሏል እንዲሁም ንብረት አውድሟል። ሁልግዜ በየማለዳው በራዲዮ የምንሰማቸው የትራፊክ ዘገባዎችም እጅግ ዘግናኝ እና ሁላችንንም የሚያስደነግጥ፣ የህሊና እረፍት የሚነሳ እና ወቶ የመግባት ዋስትናችንን ጥርጣሬ ውስጥ የሚከት ወደመሆን ደርሶል፡፡ ችግሩ እጅግ አሳሳቢ እና አስከፊ የሚያደርገው ደግሞ ጉዳት አደራሾቹ በአደጋው ተጋላጭ ለሆኑት ግለሰቦች እርዳታ ከመስጠት ወይም እርዳታ እንዲያገኙ እና ህይወታቸው እዲተርፍ ከማድረግ ይልቅ ጉዳቱን አድርሰው የሚሰወሩ መሆናቸው ነው፡፡

በተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አንድም ጉዳት አድራሹ ባለመታወቁ በሌላ በኩል ደግሞ ጉዳቱን አድራሹ ቢታወቅም ጉዳቱን ያደረሰው ተሽከርካሪ የመድን ሽፋን የሌለው በመሆኑ ተጎጂዎቹን ለባሰ ስቃይ እና እንግልት የሚዳርጋቸው ጉዳይ ነው፡፡

ከእንዲህ ያለን ችግር ለማቃለል የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን አስገዳጅ በሆነ መልኩ በሕግ ተደንግጎ መኖር እጂጉን ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡  በመሆኑም በሀገራችን ለዚህ ችግር መፍትሔ ሊሆን የሚችል ሕግ ወጥቶ በሥራ ላይ ውሎ ይገኛል፡፡ የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ  ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2002 በአሁኑ ሰዓት በሥራ ላይ የሚገኝ ሕግ ነው፡፡ የሕጉን ይዘት ከዚህ ቀጥሎ ባለው ጽሑፍ በዝርዘር እንመለከተዋለን፡፡

1.    የመድን ምንነት

ስለ የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ  ወገን መድን ከማውራታችን በፊት መድን ወይም ኢንሹራንስ ምን ማለት ነው? የሚለውን ጥያቄ መልስ ሰጥቶ ማለፍ ተገቢ ነው፡፡ በዚሁ መሠረት መድን ወይም ኢንሹራንስ ከተለያየ አቅጣጫ በማየት ትርጉም ሊሰጠው እንደሚችል የዘርፉ ሙሁራን ይገልፃሉ፡፡

ከግለሰቦች  መነሻ ነጥብ ተነስቶ የሚሰጠው ትርጉም የመጀመሪያው ሲሆን እሱም “Firstly, from the point view of an individual it may be defined as a risk transfer mechanism or an economic device whereby a person, called the insured/assured transfers a risk of a possible financial loss resulting from unforeseeable events affecting property, life or body to a person called the insurer for consideration.” ይህም በቀላል አማርኛ ስንተረጉመው “ አንድ ሰው በንብረቱ፣ በህይወቱ ወይም በአካሉ ላይ ባልተጠበቀ ሁኔታ ሊያጋጥም በሚችል አደጋ ምክንያት የሚደርስ በገንዘብ የሚለካ ጉዳትን ለኢንሹራንስ ድርጅት ማስተላለፊያ መንገድ ነው፡፡”

ሁለተኛው መነሻ ነጥብ ከኢንሹራንስ ሰጪው ድርጅት በመነሳት ሲሆን “Secondly, from the point of view of the insurer, insurance may be defined as a mechanism through which a risk is distributed among the group of persons who are exposed to the same type of risk, i.e., persons who bear the risk of suffering a financial loss as a result of events affecting property, life or body” ይህም በቀላል አማርኛ ስንተረጉመው “ኢንሹራንስ ሰጪው በአደጋ ምክንያት የሚያጋጥምን ኪሳራ በተመሳሳይ አይነት አደጋ ተጋላጭ ለሆኑ ሰዎች የሚያከፋፍልበት መንገድ ወይም ዘዴ ነው፡፡”

በሀገራችንም ሕግ ላይም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 654(1) ላይ “የኢንሹራስ ውል ፖሊሲ ማለት ኢንሹራንስ ሰጪ የሚባለው በአንድ ወይም በብዙ የተመደበውን የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕርምየም) ተቀብሎ በውሉ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ ኢንሹራንስ ለገባው ሰው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ነው፡፡” በማለት ትርጉሙን አስቀምጧል፡፡

በአጠቃላይ ከላይ የተገለፁትን ትረጉሞች መሠረት በማድረግ የምንረዳው መድን ወይም ኢንሹራንስ ማለት አንድ ሰው ባለተጠበቀ አደጋ  ህጋዊ  የፍታብሔራዊ ተጠያቂነትን፣  በንብረቱ፣ በህይወቱ ወይም በአካሉ ላይ ለደረሰው ጉዳት አስቀድሞ ከኢንሹራንስ ድርጅት ጋር በገባው ስምምነት መሠረት የሚከፈለው የካሳ ክፍያ ስምምነት ማለት ነው፡፡ ይህም ማለት የኢንሹራንስ ድርጅቱ አስቀድሞ በተስማማው መሠረት የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕርምየም) በመስብሰብ አደጋው በደረሰ ጊዜ ጉዳቱ ለደረሰበት ሰው ካሳ የሚከፍልበት እና ከጉዳቱ እንዲቋቋም የሚያደርግ መንገድ ነው፡፡

እዚህ ጋር በደንብ ልንረዳው እና ልንገነዘበው የሚገባው ጉዳይ መድን ወይም ኢንሹራንስ በጭራሽ ህጋዊ የፍታብሔራዊ ተጠያቂነትን፣  የንብረት ጉዳትን፣ ሞትን ወይም የአካል ጉዳትን የሚያስቀር ሳይሆን በዚህ ምክንያት የደረሰ ጉዳትን ለመካስ በካሳ መልከ ክፍያ መስጠትን የሚያመላክት መሆኑን ነው፡፡

2.   የመድን አስፈላጊነት

መድን ወይም ኢንሹራንስ እጅግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ ከነዚህ ጠቀሜታዎቹ ውስጥ አንደኛው በአንድ ሰው ላይ የሚደርስን የፍታብሔራዊ ተጠያቂነትን፣ የንብረት ጉዳትን፣ ሞትን ወይም የአካል ጉዳትን መሠረት የሚደርስን የኢኮኖሚያዊ ኪሳራን በካሳ መልክ የኢንሹራንስ ድርጅቱ ስለሚከፍለው በተቻለ መጠን ያ ሰው ጉዳቱ ሳይደርስ ወደነበረበት የኢኮኖሚያዊ አቅሙ መመለስ ማስቻሉ ነው፡፡ ይህ በመሆኑም ጉዳት አድራሹ ወይም ጉዳት የደረሰበት ሰው የከፋ ኪሳራና አዘቅጥ ውስጥ እዳይገቡ የሚያደርግ እና ማህበረሰቡም ከጉዳቱ በላይ በጉዳቱ ምክንያት ለሚከሰት ኢኮኖሚያዊ ቀውስ እንዳይከሰትት ያደርጋል፡፡

በሁለተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው የመድን ጠቀሜታው የመድን ድርጅቶቹ ጉዳትን በተመጣጠነ ሁኔታ ማከፋፈላቸው ነው፡፡ ይህም ማለት የኢንሹራንስ ድርጅቶቹ ተመሳሳይ የጉዳት ስጋት ካለባቸው ሰዎች  ተመጣጣኝ የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕርምየም) በመሰብሰብ ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሳ ይከፍላሉ፡፡ ይህን በማድረግ የሚደርሰውን ጉዳት ያከፋፍላሉ፡፡

በሦስተኛነት ሊጠቀስ የሚችለው የመድን ጠቀሜታ ደግሞ ለህብረተሰቡ ብሎም ለሀገር ቁጠባን የሚያሳድግ እና ኢንቨስትመንትን የሚደግፍ መሆኑ ነው፡፡  የኢንሹራንስ ድርጅቶቹ ከኢሹራንስ ገቢዎች በቋሚነት የሚሰበስቡት ክፍያ (ፕርምየም) ለሰዎች በቁጠባ መልክ የሚቀመጥላቸው ነው፡፡ ይህም ቁጠባን የሚያበረታታና የሚያሳድግ ነው፡፡ ቁጠባ ባደገ ቁጥር ደግሞ ለኢንቨስትመንት መሠረት ይሆናል፡፡

3.   የመድን አይነቶች

መድን  ወይም  ኢንሹራንስ  የፍታብሔራዊ  ተጠያቂነትን፣  የንብረት ጉዳትን፣ ሞትን ወይም የአካል ጉዳትን  እና  ሌሎችንም ጉዳዮችን  ዋስትና  የሚሰጥ መሆኑን ከላይ አይተናል፡፡ ወድን  ወይም ኢንሹራንስን  የዘርፉ  ሙሁራን  በተለያዩ መልኩ ይከፋፍሎቸዋል፡፡ በዋናነትም

      1ኛ. የህይወት መድን 

      2ኛ. የንብረት መድን እና

      3ኛ. የፍታብሔራዊ ተጠያቂነት መድን ናቸው፡፡

ነገር ግን ከዚህም በላይ ዝርዘር በማድረግ የሚከፋፍሉም ምሁራን አሉ፡፡ ይህም 1ኛ. የጤና መድን 2ኛ. የተሽከርካሪ መድን 3ኛ. የህይወት መድን 4ኛ. የእሳት ቃጠሎመድን 5ኛ. የጉዞ መድን 6ኛ. የመኖሪያ ቤት መድን  7ኛ. የሥራ አጥነት መድን የትራንስፖርት መድን 8ኛ. የተሸከርካሪ አደጋ መድን 9ኛ. የህጋዊ ሃላፊነት መድን እና የመሳሰሉት እያሉ ይከፋፍሎቸዋል፡፡

በሀገራችንም የተለያዩ የመድን አይነቶች በመድን /ኢንሹራንስ/ ድርጅቶች ይሰጣሉ፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ በጥልቀት የምንመለከተው ስለ የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ነው፡፡

4.  የተሽከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና

የተሸከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና ዋስትና በተገባለት ተሽከርካሪ ላይ በድንገተኛ ለሚደርስ ግጭት ወይም መገልበጥ ወይም በእሳት፣ ከውጭ በደረሰ ፍንዳታ፣ በውስጣዊ አካል መቀጣጠል፣ በመብረቅ፣ በሌብነት ወይም በሌብነት ሙከራ ምክንያት ለሚደርስ ጉዳት ወይም ጥፋት የካሣ ክፍያ ይፈፅማል፡፡

ነገር ግን በተፈጥሮ ክስተቶችን ምክንያት ማለትም የጎርፍ መጥለቅለቅ፣ የአውሎ ንፋስ የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ፣ የመሬት መንቀጥቀጥና በመሳሰሉት ሳቢያ በተሽከርካሪው ላይ ለደረሰ ጉዳት ወይም ጥፋት ቢደርስ አይሸፈንም፡፡

የተሽከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና ውል ላይ በሚደረግ ተጨማሪ ስምምነት መሠረት በአደጋው ጉዳት ለሚደርስባቸው ተሣፋሪዎች፣ በሽፍታ ወገን ሆን ተብሎ በተሽከርካሪው ላይ በሚደርስ ጉዳት፣ ከሀገር ድንበር ወሰኖች ውጭ በሚደረግ ጉዞ የሚደርሱ ጉዳቶችን የመድን ሽፋን እንዲያገኙ ማድረግ ይቻላል፡

የተሽከርካሪ ጠቅላላ ዋስትና ውል በተሽከርካሪው ላይ ለሚደርስ ጉዳት ወይም ጥፋት በተጨማሪ የሦስተኛ ወገን ኃላፊነትን በተመለከተ በአዋጅ ቁጥር 799/2002 በተደነገገው መሠረት

1.     በሰው ላይ ለሚደርስ የአካል ጉዳት ወይም፣ ሞት እና

2.    በንብረት ላይ ለሚደርስ ውድመት ካሳ ይከፍላል፡፡

5.   የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ  ወገን መድን ሕግ በኢትዮጵያ

በአሁኑ ሰዓት ሥራ ላይ ያለው የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ በ2002 ዓ.ም በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት የወጠው አዋጅ ቁጥር 799/2002 ነው፡፡ ይህ ሕግ የመጣው በመስረታዊነት በአራት ምክንያቶች ነው፡፡ እነሱም

   1ኛ. በተሸከርካሪ ምክንያት እየደረሰ ያለው አደጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ በጣም እየጨመረ በመምጣቱ፣

   2ኛ. በተሸከርካሪ አደጋ ምክንያት የሚደርሰው የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሣራ ማህበራዊ ችግር እያሰከተለ ያለ በመሆኑ፣

  3ኛ. የተሸከርካሪ አደጋ ተጎጂዎች አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ስርዓት ማመቻቸት አስፈላጊ በመሆኑ እና

  4ኛ. የተሸከርካሪ ባለንብረቶች የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን  እዲኖራቸው ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡

5.1.            ሕጉ (አዋጁ) የሚመለከተው

ከብስክሌትና የአካል ጉዳተኞች ተሸከርካሪ (ዊልቼር) በስተቀር በመንገድ ላይ የሚሄድ በኤሌትሪክ ወይም በመካኒካል ሀይል የሚሰራ ባለሞተር ተሸከርካሪ፣ ግማሽ ተሳቢ ወይም ተሳቢ ላይ ሁሉ ሕጉ ተፈፃሚ እንደሚሆን  ከአዋጁ አንቀጽ 2(5) ላይ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህ ማለትም ከባጃጅ እንስቶ ቀላልና ከባድ ተሸከርካሪዎች ሁሉ ይህን የመድን የምስክር ወረቀት ሳይዙ መንቀሳቀስ አይችሉም። በአዋጁ አንቀጽ 3(1) ላይ እንደተገለፀው ማንኛውም ሰው ተሸከርካሪው በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው አደጋ የፀና የመድን ሽፋን ሳይኖው ተሸከርካሪውን  በመንገድ ላይ መንዳት፣ መጠቀም ወይም ሌላ ስው እንዲነዳ ወይም እንዲጠቀም ማድረግ ወይም መፍቀድ እደማችል ተደንግጎ እናገኛለን፡፡ ነገር ግን በልዩ ሁኔታ የትራንስፖርት ሚኑስትሩ የመድን ሽፋን ሳይኖራቸው በመንገድ ላይ ሊውሉ የሚችሉ ተሸከርካሪዎችን ሊወስን እደሚችል በዚሁ ሕግ ላይ ተቀምጦል፡፡

የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ምስክር ወረቀት ካልያዙ ሽፋኑ እንደሌላቸው ተቆጥሮ ተሽከርካሪዎቹ በፖሊስ ተይዘው ይቆያሉ። ተሽከርካሪው የመድህን ተለጣፊ ምልክት ከሌለው ወይም በወቅቱ የታደሰ ካልሆነ መድህን ለተሽከርካሪው የመግባት ግዴታ ያለበት ሰው አዋጁን እንደጣሰ ተቆጥሮ በሕግ እንደሚጠየቅ በአዋጁ አንቀጽ 13 ላይ ተደንግጎል።

ለተሸከራካሪው የሦስተኛ ወገን መድን የመግባት ግዴታ ያለበት የተሸከርካሪው ባለቤት፣ ተሸከርካሪው ላይ በኪራይ ወይም በውክልና መብት አግኝቶ የሚጠቀም ሰው ወይም ሌሎች እንዲጠቀሙበት መፍቀድ የሚችል ማንኛውም ሰው ነው፡፡

5.2.     የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የሚሸፍነው ጉዳት

የሚሸፈኑት የጉዳት አይነቶች ተሽከሪካሪው ለሚያደርሰው ግጭት፣ የእሳት ቃጠሎ ወይም ፍንዳታ፤ የተሸከርካሪው ጭነት፣ አካል ወይም መሳሪያ ወድቆ ለሚያደርሰው ጉዳት እና ከተሽከርካሪው እንቅስቃሴ  ጋር ተያይዞ የሚደርስ ማንኛውንም ጉዳትን ያካትታሉ። በአዋጁ አንቀጽ 4(2) ላይ በተገለፀው መሠረት በሀገራችን ያለው የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን ፖሊሲ መድን የተገባለት ተሸከርካሪ ለሚያደርሰው የሰው ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ኪሳራ መከፈል የሚገባውን ካሳና አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ወጪ የሚሸፍን ነው፡፡

ነገር ግን የመድን ገቢው ወይም ቤተሰብ (የትዳር ጓደኛ፣ ልጅ፣ አባት፣ እናት ወይም  የሚያስተዳድረው ማንኛውም ሰው) ላይ የሚደርስ ሞት፣ የአካል ጉዳትና የንብረት ጉዳት፣ በመድን ገቢው ተቀጥሮ የሚሰራ ሰው በሥራው ላይ እያለ በሚደርስ የግጭት አደጋ ወይም የሞት ወይም የአካል ጉዳት ወይም የንብረት ጉዳት፣ መድን በተገባለት ተሸከርካሪ ላይ የሚደርስ አደጋ፣ መድን በተገባለት ተሸከርካሪ ላይ በኪራይ ወይም በክፍያ በሚጎጎዝ ንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ሃላፊነት እና ከኢትዮጵያ ግዛት ክልል ውጪ የደረሰ የተሸከርካሪ አደጋ ተከትሎ የመጣ ሃላፊነትን የማይሸፍን መሆኑን እና ካሳ እደማይከፈለው ከአዋጁ አንቀጽ 7 እንረዳለን፡፡ በሌሎች ሕጎች ግን ጉዳት አድራሹን ወይም ተሽከርካሪው የመድህን ሽፋን ካለው መድህን የሰጠውን ኩባንያ ካሳ የመጠየቅ መብታቸው እንደ ተጠበቀ ነው።

5.3.           የካሳው መጠን

በሦስተኛ ወገን የተሸከርካሪ መድን  ፖሊሲ ለደረሰ ጉዳት የሚሸፍነው የካሳ መጠን በአዋጁ አንቀጽ 16 ላይ ተገልፆል፡፡ በዚሁ መሠረት በአንድ ሰው ላይ ለሚደርስ የሞት አደጋ ከብር 5 ሺህ እስከ ብር 40ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ፤ በአንድ ሰው ላይ ለሚደርስ ለአካል ጉዳት እስከ ብር 40 ሺህ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ እንዲሁም በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ወይም ኪሳራ ከብር 100 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ የሚከፈል ይሆናል፡፡

ነገር ግን ከዚህ በሕጉ ከተቀመጠው የገንዘብ መጠን በላይ ጉዳት የደረሰበት ሰው ጉዳት አድራሹን ወይም በሕግ ሃላፊነት ያለበትን ሰው በፍ/ቤት ተገቢነት ባለው ሌላ ሕግ መሠረት ከሶ ካሳ መጠየቅ ይችላል፡፡ በሦስተኛ ወገን የተሽከርካሪ የመድን ዋስትና የአሽከርካሪውን እድሜ፣ የአካል ወይም የአእምሮ ሁኔታ፤
የተሽከርካሪውን ሁኔታ፣ የፈረስ ጉልበት ወይም የሲሊንደር ችሎታ ወይም ዋጋ፤
የሚይዘው ሰው ብዛት፣ የጫነውን እቃ ክብደት፣ አካላዊ ባህሪ ወይም ልዩ መሳሪያ፣ ተሽከርካሪው አገልግሎት ላይ የሚውልበትን ጊዜ ወይም አካባቢ መሠረት በማድረግ ካሳ እንዳይከፈል አያደርግም። አንዲሁም እንደ ሌሎች የመድን ዋስትናዎች በመድን ውሉ በተስማማነው መሠረት አይደለም በሚል የመድን ኩባንያው ወይም ሌላ አካል ካሳው እንዳይከፈል መቃወም ወይም መከልከል አይችልም።

የመድን ፈንድ ኤጀንሲው ጉዳት አድራሹ ተሽከርካሪ ካልታወቀ ወይም የመድህን ሽፋን ከሌለው በተሽከርካሪው ለደረሰ የሞት ወይም የአካል ጉዳት ከላይ የጠቀስነውን የካሳ መጠን ይከፍላል። የአስቸኳይ ህክምና ወጪንም ይሸፍናል ::

5.4.      አስቸኳይ የህክምና እርዳታ

ማንኛውም ሰው መንገድ ላይ በተሸከርካሪ አደጋ ጉዳት ከደረሰበት በአደጋው ቦታ፣ ወደ ህክምና በሚጓጓዝበት ወቅትና በድንገተኛ ክፍል እስከ ብር 2 ሺህ አስቸኳይ የህክምና እርዳታ የማግኘት መብት አለው፡፡ ማንኛውም የጤና ተቋም ይህን አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ክፍያ ሳይጠይቅ የመስጠት ግዴታ አለበት። ክፍያውን አገልግሎቱን ከሰጠ በኋላ ከመድን ኩባንያው ወይም ከመድህን ፈንድ ኤጀንሲው  የሚጠይቅ መሆኑን በአዋጁ አንቀጽ 27(3) እና (4) ላይ ተገልፆል።

6.    የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ  ወገን መድን ሽፋን የሚሰጡ ተቋማት

በሀገራችን የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ብቻ የሚሰጡ ድርጅቶች የሉም፡፡ ይልቁንም ጠቅላላ የመድን ሽፋን የሚሰጡ ድርጅቶች ብቻ ናቸው ያሉት፡፡ ይህ በመሆኑም በአዋጁ አንቀጽ 4 ላይ ጠቅላላ የመድን ሥራ የሚሰሩ የመድን ኩባንያዋች የሦስተኛ ወገን የመድን ሽፋን የመስጠት ግዴታ ጥሎባቸዋል።

እነዚህ ኩባኒያዎች ከሰጡት ሽፋን የሚሰበስቡትን አረቦን በተቀመጠው ተመን መሠረት የተወሰነውን ለመድን ፈንድ ኤጀንሲ ገቢ ያደርጋሉ፡፡ አረቦን ተመን የመድን ፈንድ ኤጀንሲ በሚያቀርበው ጥናት መሠረት የሚወስነው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡

7.   ስለ መድን ፖሊሲ

በአዋጁ አንቀጽ 2(8) ላይ የመድን ፖሊሲ ማለት የመድን ገቢው ተሽከርካሪ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው የሞት አደጋ፣ የአካል ጉዳት ወይም የንብረት ኪሳራ ካሳ ለመክፈል እና አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት ክፍያን ለመፈፀም መድን ሰጪው ውለታ የሚገባበት ሰነድ ነው በማለት ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ በንግድ ሕጉ አንቀጽ 654(1) ላይ “የኢንሹራስ ውል ፖሊሲ ማለት ኢንሹራንስ ሰጪ የሚባለው በአንድ ወይም በብዙ የተመደበውን የኢንሹራንስ መግቢያ ዋጋ (ፕርምየም) ተቀብሎ በውሉ የተመለከተው አደጋ በደረሰ ጊዜ ኢንሹራንስ ለገባው ሰው የተወሰነ ገንዘብ ለመክፈል ግዴታ የሚገባበት ነው” ትርጉሙን አስቀምጧል፡፡ ይህ ማለት በሌላ ቋንቋ መድን ሰጪው ከመድን ገቢው ጋር የሚፈመው ውል ማለት ነው፡፡

የተሽከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ፖሊሲ ውስጥ በማንኛውም ሁኔታ የመድን ፖሊሲው ተጠያቂነትን አያስከትልም በሚል ወይም በፖሊሲው መሠረት ለካሳ ክፍያ ጥያቄ መነሻ የሚሆነው ክስተት ከደረሰ በኋላ የተወሰነ ድርጊት ከተፈፀመ ወይም ሳይፈፀም ከቀረ ኃላፊነት ቀሪ ይሆናል በሚል የተደረገ ከሆነ ይህ ፖሊሲ ወይም ውል በሕግ ፊት ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ (የአዋጁ አንቀጽ 6(1))፡፡ እንዲሁም በአዋጁ አንቀጽ 8 እንደተገለጸው ማንኛውም ሰው የተሽከርካሪ መድን ፖሊሲ ለማግኘት ሲል ፖሊሲውን ተፈፃሚነት ሊያስቀር የሚችል ሀሰተኛ መግለጫ መስጠት ወይም ፖሊሲውን ላይ ያለውን መብት ሊያስቀር የሚችል ማናቸውንም ድርጊት መፈፀም እደማይችል በመግለፅ ክልከላ አስቀምጧል፡፡

8.    ስለ መድን ምስክረ ወረቀት እና ፀንቶ የሚቆይበት ጊዜ

መድን ሰጪ ድርጅት ከመድን ገቢው ጋር የመድን ሽፋን ለመስጠት ከተስማሙ የመድን ፖሊሲውን (የመድን ስምምነት ውላቸውን) ለመድን ገቢው ይሰጠዋል፡፡ ከመድን ፖሊሲው በተጨማሪ በአዋጁ አንቀጽ 9(1) እና 12(1) ላይ እንደተገለፀው የመድን ፖሊሲውን በሚሰጥበት ጊዜ የመድን ምስክር ወረቀት እና የመድን ተለጣፊ ምልክት ለመድን ገቢው አብሮ መስጠት እዳለበት ሕጉ በመድን ድርጅቱ ላይ ግዴታ ጥሎበታል፡፡ የመድን ምስክር ወረቀት ማለት የተሽከርካሪው ባለንብረት ወይም ህጋዊ ግዴታ ያለበት ሰው ተሸከርካሪው በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው አደጋ በአዋጁ መሠረት መድን የገባለት መሆኑን የሚያረጋግጥ ሰነድ ነው፡፡

ይህ በመድን ሰጪ ድርጅቱ ለመድን ገቢው የሚሰጠው የመድን ምስክር ወረቀት

     1ኛ. የመድን ገቢውን ስምና አድራሻ፣

     2ኛ. መድን የተገባለትን ተሸከርካሪ ሠሌዳ፣ የሞተርና የሻንሲ ቁጥሮች፣

     3ኛ. የመድን ፖሊሲው የሚጀምርበትንና የሚያበቃበትን ጊዜ፣

     4ኛ. የመድንፖሊሲው የተሰጠባቸውን ሁኔታዎች፣

     5ኛ. በመድን ፖሊሲው ተጠቃሚ የሚሆኑትን ሰዎች ወይም ወገኖች፣ እና

     6ኛ. የመድን ሰጪውን ስምና አድራሻ መግለፅ አለበት፡፡

የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን አዋጅ አንቀጽ 9 መሠረት የተሰጠ የመድን ምስክር ወረቀት ከተሰጠበት ቀን አንስቶ ከአንድ ዓመት ላላነሰ ጊዜ የሚፀና ነው፡፡ የመድን ሽፋን ውሉ ሲቋረጥ ወይም የውል ዘመኑ ሲያልቅ መድን ገቢው የመድን ምስክር ወረቀቱንና የመድን ተለጣፊውን ወዲያውኑ ለመድን ሰጪው ድርጅት መመለስ አለበት፡፡

9.  ስለ መድን ፈንድ

የመድን ፈንድ ማለት ቋሚ የፋይናንስ ምንጭ ሆኖ በኢትዮጲያ ብሔራዊ ባንክ በሚከፈት ልዩ የባንክ ሂሳብ ውስጥ ተቀማጭ እንዲሆን በአዋጁ የተቋቋመ ነው፡፡ የፈንዱ የገንዘብ ምንጭ ከፈንዱ ተመን የሚሰበሰብ እና በሚኒስትሮች ምክር ቤት በሚወሰን ሌላ ተጨማሪ ገቢ ነው፡፡ ይህን ፈንድ የሚያስተዳድረው በሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 300/2006 የተቋቋመው የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ነው፡፡

የፈንዱ ዓላማ መድን ባልተገባለት ወይም ባልታወቀ  ተሽከርካሪ አደጋ ምክንያት፤

ጉዳት የደረሰበት ሰው አስቸኳይ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኝ ማድረግ፤

የአካል ጉዳት ለደረሰበት ሰው ካሳ እንዲከፈለው ማድረግ፣ እና

ለሞተ ሰው ቤተሰብ አባላት ካሳ እንዲከፈል ማድረግ ነው፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 20(2) ላይ እንደተገለጸው ኤጀንሲው ጉደት ለደረሰባች ሰዎች የሚከፍለው የካሳ ክፍያ ከላይ የተገፀውን የፈንዱን ዓላማ ለማሳካት በአቃጁ አንቀጽ 16 ላይ የተቀመጠውን መጠን ድረስ ብቻ እንደሆነ ያስቀምጣል፡፡ ይኸውም  በአንድ ሰው ላይ ለሚደርስ የሞት አደጋ ከብር 5 ሺህ እስከ ብር 40ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ፤ በአንድ ሰው ላይ ለሚደርስ ለአካል ጉዳት እስከ ብር 40 ሺህ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ እንዲሁም በንብረት ላይ ለሚደርስ ጉዳት ወይም ኪሳራ ከብር 100 ሺ ያልበለጠ የገንዘብ ካሳ የሚከፈል ይሆናል፡፡

የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ ጉዳት ለደረሰባቸው አካላት በሕጉ የተቀመጠውን የጉዳት ካሳ መጠን ከከፈለ በኃላ ይህን የከፈለውን ክፍያ ለጉዳቱ በሃላፊነት ተጠያቂ ከሆነው ሰው ላይ የማስመለስ መብት እንዳለው በአዋጁ አንቀጽ 20(3) ተደንግጎል፡፡

ስለ የመድን ፈንድ አስተዳደር ኤጀንሲ

ይህ እጀንሲ በሚኒስተሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 300/2006 የተቋቋመ መንግስታዊ ተቋም ነው፡፡ ኤጀንሲው በዋናነት የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ  ወገን መድን አዋጅ ቁጥር 799/2002 እና እሱን ተከትለው የወጡ መመሪያዎችንና ደንቦችን የማስፈፀም ግዴታ ተጥሎበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የፈንዱን አላማ እንዲያሳካ እና ፈንዱን እንዲያስተዳድር ሃላፊነት ተጥሎበታል፡፡

ኤጀንሲው የበጀት ምንጩ ከመንግሥት የሚመደብለት በጀት ነው፡፡ እጄንሲውን በበላይንት የሚመራው የመድን ፈንድ ቦርድ ሆኖ በመንግሥት የሚሾም ዳይሬክተር እና እንዳስፈላጊነቱ ዋና ምክትል ዳይሬክተር እንዲሁም አስፈላጊ የሆኑ ሥራተኞች ያሉት ነው፡፡

በአዋጁ የተከለከሉና የሚያስቀጡ ተግባራት እና ቅጣታቸው

በአዋጁ አንቀጽ 30 ላይ እንደተገለፀው ማንኛውም ሰው የዚህን አዋጅ ወይም አዋጁን መሠረት አድርገው የወጡ ደንቦች ድንጋጌ ተላልፎ የተገኘ እንደሆነ በወንጀል ያስጠይቃል፡፡ በመሆኑም ማንኛውም ሰው በአዋጁ ወይም አዋጁን መሠረት አድርገው የወጡ ደንቦች መሠረት አድርግ የተባለውን ማድረግ ወይም አታድርግ የተባለውን አለማድረግ አለበት፡፡ ካልሆነ ግን ሕግ መተላለፍ ስለሆነ በወንጀል ይጠየቃል እንዲሁም ቅጣት ይጣልበታል፡፡ 

በአዋጁ የተጣሉ ክልከላዎች ፡-

1ኛ.  በአዋጁ አንቀጽ 3 ማንኛውም ስው ተሸከርካሪው የሦስተኛ ወገን መድን ሽፋን ሳይኖረው በመንገድ ላይ መንዳት፣ መጠቀም ወይም ሌላ ሰው እንዲነዳ ወይም እዲጠቀም ማድረግ ወይም መፍቀድ እይችልም፣

2ኛ. በአዋጁ አንቀጽ 13 የመድን ተለጣፊ ምልክት ሳይዙ ተሸከርካሪን በመንገድ ላይ መንዳት እና

3ኛ. በአዋጁ አንቀጽ 27(2) ማንኛውም የጤና ተቋም ይህን አስቸኳይ የህክምና እርዳታ ክፍያ ሳይጠይቅ የመስጠት ግዴታውን ካልተወጣ ናቸው፡፡

ከላይ ያነሳናቸውን የአዋጁን ግዴታዎች መጣስ ከብር 3ሺ- 5ሺ የገንዘብ መቀጮ ወይም እስከ አንድ አመት እስር እንደሚያስቀጣ በአዋጁ አንቀጽ 30 ላይ ተደንግጎል፡፡

ማጠቃለያ


በተሸከርካሪ አደጋ ምክንያት የሚደርሱ አደጋውች እጅግ እየበዙ እና ጉዳታቸውም እየከፋ ይገኛል፡፡ በተሸከርካሪ አደጋ ምክንያት በሚደረሱ ጉዳቶች ምክንያት ብዙወች ህይወታቸውን፣ አካላቸውን እና ንብረታቸውን አተዋል፣ እያጡም ይገኛሉ፡፡ ከዚህ የተነሳም ለከፋ የኢኮኖሚያዊ ችግር እየተጋለጡ ነው፡፡

 

ይህን የኢኮኖሚያዊ ችግር በተወሰነ መልኩ እንዲቋቋሙ እና አስቸኳይ የህክምና እርዳታ እዲያገኙ ለማስቻል የተሸከርካሪ አደጋ የሦስተኛ ወገን መድን ሕግ ወጥቶ ተግባራዊ መሆኑ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ለማንኛውም የተሽከርካሪ አደጋ እዳይደርስብን ወይም እንዳናደርስ እንጠቀቅ፡፡ አደጋ ከደረሰ ግን ከላይ በጠቀስናቸው መብቶች እንጠቀም፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሁለት ኢትዮጵያውያን ወግ: የቀድሞውና አዲሱ ኢትዮጵያዊነት በኢፌዴሪ ሕገ መንግ...
የቤተሰብ ሕጉ አንቀጽ 107/2/ ከሌሎች የቤተሰብ ሕጉ ድንጋጌዎች እና ከሕገ መ...
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 19 April 2024