የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥብቃ በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ

የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎች የአንድ ሀገር ባህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ ልማትን በማፍጠን ረገድ ትልቅ ሚና የሚጫወቱ መሣሪያዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የዚህ ሥራ ፈጣሪዎች የሚበረታቱበትንና አዳዲስ ፈጠራዎችን የሚያበረክቱበት ምቹ ሁኔታ መፍጠር እጅጉን አስፈላጊ ነው፡፡

የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች በሕግ እውቅና መስጠትና ጥበቃ ማድረግ አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበራታቱ እና የሚጠበቅባቸውን በህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እድገት በኅብረተሰቡ ውስጥ እንዲያመጡ እንዲሁም የፈጠራው ባለቤቶች ከሥራቸው እንዲጠቀሙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 91(3) ላይ መንግሥት አቅም በፈቀደ መጠን ኪነ ጥበብን፣ ሳይንስና ቴክኖሎጂን የማስፋፋት ግዴታ እንዳለበት ይደነግጋል፡፡ በዚሁ መሠረት  መንግሥትም የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ለማክበርና ለማስከበር ይረዳው ዘንድ አዋጅ ቁጥር 410/1996 በማውጣት ሥራ ላይ አውሎ በመተግበር ላይ ይገኛል፡፡ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ሁል ጊዜ እያደጉ እና እየተለዋወጡ የሚሄዱ በመሆናቸው በአዋጅ ቁጥር 410/1996 ላይ የተወሰነ ማሻሻያና ጭማሪ በማስፈለጉ ይህ አዋጅ በአዋጅ ቁጥር 872/2007 ማሻሻያ አድርጎ በሥራ ላይ አውሏል፡፡ ይህም መሆኑ ከአለም እና ከተለዋዋጭ ሁኔታዎች ጋር ለመራመድ ያስችላል፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብት ጽንሰ ሀሳብ

የቅጅ መብት ማለት የኪነ-ጥበብ፣ ዕደ-ጥበብ፣ የሥነ-ጽሑፍና የሳይንስ መስክ የፈጠራ ሥራዎች ባለቤቶች በፈጠራ ሥራዎቻቸው ላይ የሚኖራቸው የአእምሯዊ ንብርት መብት ነው፡፡ ይህ መብት የኢኮኖሚና የሞራል መብቶችን የሚያካትት ነው፡፡

ኢኮኖሚያዊ መብት የፈጠራ ሥራውን የማባዛት፤ የመከወን፤ ብሮድካስት የማድረግ፤ ወደ ሌሎች ሥራዎች የመለወጥና ሌሎች ብቸኛ መብቶችን የሚያካትት ሲሆን የሞራል መብት ደግሞ የፈጠራ ሥራው ደራሲ (የሥራው አመንጪ) የመባል፣ ሥራዎቹ እንዳይዛቡ የማድረግና መሰል መብቶችን የሚያካትት ነው፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ዓላማ የፈጠራ ባለሞያዎች የፈጠራ ሥራዎቻቸውን ለማከናወን ያፈሰሱትን እውቀት፣ ጊዜና ኃብት እንዲያካክሱና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ሆነው ለተጨማሪ የፈጠራ ሥራ እንዲነሳሱ ለማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች መጠበቅ ቀጣይ የፈጠራ ሥራን ለማበረታታትና ኢንቨስትመንት እንዲበረታታ አቅም ለመፍጠር የሚያግዝ ነው፡፡

በጥቅሉ ኮፒራይት የፈጠራ ባለመብቶችን የሞራል መብት በማስጠበቅና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ በማድረግ ቀጣይነት ያለው የፈጠራ ሥርዓት ለመፍጠር የሚያስችል እና በህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እድገት በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲያመጡ  ማድረግ ነው፡፡

መብቱ በኢትዮጵያ ያለው ታሪካዊ ዳራ

አገራችን ኢትዮጵያ በተለያዩ የኪነ ህንፃ፣ ቅርፃ ቅርፅ፣ ሥነ-ስዕል፣ ሥነ-ጽሑፍ እና የኪነ-ጥበብ ያላቸው ህዝቦች ባለቤት እንደሆነች በዘርፉ የተሰማሩ ባለሞያዎች እና ጥናቶቻቸው ያረጋግጡልናል፡፡ ነገር ግን ለብዙ ዓመታት የዚህ ዘርፈ የፈጠራ ባለመብቶች መብቶቻቸው ተከብሮላተው ከፈጠራቸው ተጠቃሚ አልነበሩም፡፡ በኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ለመጀመሪያ ጊዜ የተካተተው በ1952 ዓ.ም በወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ውስጥ የተወሰኑ መብቶችን በማካተት ነው፡፡ ይህም ማለት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ በሕግ ማዕቀፍ ተካቶ ሥራ ላይ የዋለው በቅርብ ዓመታት ነው፡፡ 

በአሁኑ ሰዓት የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን በተመለከተ ጥበቃ የሚያደርግላቸው በ1996 ዓ.ም የወጣው አዋጅ ቁጥር 410/1996 እና ይህንን አዋጅ ለማሻሻል የወጣው አዋጅ ቁጥር 872/2007 ናቸው፡፡ አዋጅ ቁጥር 872/2007 በአዋጅ ቁጥር 410/1996 ውስጥ የተካተቱ የተወሰኑ አንቀፆች ላይ ማሻሻያ ያደረገ እና አዲስ መብቶችን ያካተተ ነው፡፡ በመሆኑም አዲሱ አዋጅ ነባሩን አዋጅ ቁጥር 410/1996 ሙሉ ለሙሉ የሻረ አይደለም፡፡ በተሻሻለው አዋጅ የተካተቱትን አዳዲስ ነጥቦች ዝቅ ብለን በሌላ ክፍል የምንመለከተው ይሆናል፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብት ትርጎሜ

በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 2(8) ላይ “የቅጅ መብት ማለት ከአንድ ሥራ የሚመነጭ የኢኮኖሚ መብት ሲሆን አግባብነት ባለው ጊዜ የሞራል መብቶችን ይጨምራል” በማለት ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ከትርጉሙ እንደምንረዳው የቅጅ መብት የሥራው አመንጪ የሆነው ሰው ከሥራው የሚያገኘው ኢኮኖሚያዊ እና የሞራል መብት ነው፡፡ እነኚህ የሥራው አመንጪ መብቶች በአንቀጽ 7 እና 8 ላይ ተገልፆ ይገኛሉ፡፡ የሥራው አመንጪ የራሱን አእምሮ ውጤት የሆነውን የፈጠራ ሥራ ማለት የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነ ጥበብ፣ ዕደ-ጥበብ እና የሳይንሳዊ መስኮች በተለይም መጽሐፍ፣ ቡክሌት፣ በመጽሔት ወይም በጋዜጣ ላይ የሚገኝ መጣጥፍ፣ የኮምፒዩትር ፕሮግራም፣ ንግግር፣ ሌክቸር፣ የሀይማኖት ስብከት፣ ድራማ፣ ድራማዊ ሙዚቃ ሥራ፣ የመድረክ ውዝዋዜ፣ የኦዲዮ ቪዥዋል ሥራ፣ የኪነ ህንፃ ሥራ፣ የስዕል የቅብ፣ የቅርፃ ቅርጽ ሥራ፣ የፎቶ ግራፍ ሥራ፣ ስዕላዊ መግለጫ፣ ካርታ ፕላን እና የመሳሰሉት ሥራዎች ላይ ኢኮኖሚያዊ እና የሞራል መብትን ያገኛል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 2 (14) ላይ “ተዛማጅ መብት ማለት ከዋኝ፣ የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲውሰር፣ የብሮድካስቲንግ ድርጅት በሥራው ላይ ያለው መብት ነው” በማለት ትርጉም ሰጥቶታል፡፡ የተዛማጅ መብቶች ባለቤት በሥራው ላይ የሁለተኛ ደረጃ መብት ነው ያላቸው፡፡ በሥራው ላይ የመጀመሪያ ደረጃ መብት ያለው የሥራው አመንጪው ነው፡፡

ጥበቃ ለማግኘት የሚስፈልጉ መመዘኛዎች፣ የብቸኝነት ተፈፃሚነት ወሰን

ጥበቃ ለማግኘት የሚያስፈልጉ መመዘኛዎች

አንድ የሥነ-ጽሑፍ፣ ኪነ-ጥበብ ወይም በሳይንሳዊ መስክ ፈጠራ የሆነ ሥራ የሥራው አንጪው የአዕምሮ ውጤት እስከሆነ ድረስ የሥራው ዓላማና ጥራት ደረጃ ግምት ውስጥ ሳይገባ ወጥ (ኦርጅናል ) ከሆነ እና የተቀረጸ ወይም ግዙፍነት ካገኘ ሥራው በመውጣቱ ብቻ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ጥበቃ እንዲያገኝ በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 6(1) ላይ ተገልፆል፡፡ በመሆኑም የሥራው አመንጪ ለሥራው ጥበቃ ለማግኘት ሥራው 1ኛ ወጥ (ኦርጅናል) መሆን ያለበት መሆኑ እና 2ኛ ሥራው ግዙፋዊነት ያገኘ መሆን እንዳለበት እንደ ቅድመ ሁኔታ ተቀምጧል፡፡

1ኛ. ወጥ (ኦርጅናል) መሆን

የሥራ አመንጪው የሥራው ሥራ ከሌሎች ሥራዎች ላይ ያልተቀዳ መሆን እንዳለበት የሚገልጽ ሀሳብ ነው፡፡ ይህም ማለት ሥራው በሥራው አመንጪው ሰው የአእምሮ ውጤት መሆን አለበት የሚለውን ጽንሰ ሃሳብ ያያዘ ነው፡፡

2ኛ. ግዙፋዊነት (የተቀረፀ) መሆን

አንድ ሥነ-ጽሑፍ፣ የኪነ-ጥበብ ወይም በሳይንሳዊ ሥራ የሥራ አመንጪው የአእምሮው ውጤት የሆነ ወጥነት ያለው ሆኖ በጉዙፍ በሆነ ነገር ላይ መስፈር አለበት፡፡ ይህም ማለት የአእምሮ ውጤት የሆነው ሥራው በሃሳብ ደረጃ የቀረ ሳይሆን አንድ ግዙፍ በሆነ እቃ ላይ የሰፈረ መሆን አለበት፡፡ ለምሳሌ ያክል አንድ የመጸሐፍ ደራሲ የጽሑፉን ሀሳብ በአእምሮ ስለያዘ የቅጅ መብቱ አይጠበቅለትም፡፡ ይልቁንም ይህን የአእምሮ ውጤቱ የሆነውን ድረሰት በወረቀት ላይ ሲያሰፍረው ነው ጥበቃ የሚያገኘው ፡፡ በአዋጅ ቁጥር 410/1996 በአንቀጽ 2(1) ላይ መቅረጽ ወይም ግዝፈት እንዲያገኝ ማድረግ ማለት አንድ ሥራ፣ ምስል ድምጽ ወይም የአንደኛቸው አምሳያ ምትክ ለዚሁ ተብሎ በተዘጋጀ መሳያ አማካኝት እንዲታይ፣ እንዲባዛ፣ ወይም እንዲሰራጭ ማድረግ ማላት እንደሆነ ይገልፃል፡፡

በዓለም አቀፍ ተሞክሮ እንደሚያሳየንም ሆነ በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 5 ላይ እንደተገለፀው ማንኛውም ሀሳብ፣ የአሰራር ሂደት፣ ሲስተም፣ የአሰራር ዘዴ፣ ፅንሰ ሀሳብ፣ ቀመር፣ ለአጠቃላይ ሥራ የሚያገለግል የቁጥር ሰንጠረዥና ቅፅ፣ መርህ፣ በአንድ ሥራ ውስጥ የተተነተነ ወይም የተብራርም ሆነ ያለተብራራ ግኝት ወይም ዳታ፣ የሕግ ባህሪ ያላቸው ማንኛቸውም ይፋ የሆኑ የሕግ እና የአስተዳደር ሰነዶችና ይፋ የሆኑ ትርጎሜያቸው በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ሕግ ጥበቃ አይደረግላቸውም፡፡ 

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የተፈፃሚነት ወሰን

በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው ተሞክሮ የሚያሳየው የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የሕግ ጥበቃ ሲሰጥ የጥበቃው መሠረት ከሥራው አመንጪ ዜግነት ወይም ቆሚ የመኖሪያ አድራሻ ጋር በተያያዘ ወይም ሥራው ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመበት ቦታ ወይም ህትመት የማፈልግ ከሆነ ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘበት ቦታ ጋር በተያያዘ መልኩ ነው፡፡

በአገራችንም በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 3 ላይ የሕግ ጥበቃው የተፈፃሚነት ወሰኑን አስቀምጦ እናገኘዋለን፡፡ በአንቀጽ 3(1)(ሀ) ላይ የሥራው አመንጪው ዜግነቱ ኢትዮጵያዊ ከሆነ ወይም ቋሚ መኖሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሆነ ሥራው ያለ ቅድመ ሁኔታ ወዲያው የሕግ ይበቃ ይደረግለታል፡፡ ሥራው የሚታተም ከሆነ እና በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ የታተመ ከሆነ ወይም በታተመ በ30 ቀን ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ከሆነ የሥራው አመንጪው ኢትዮጵያዊ ሆነ አልሆነ ወይም ቋሚ መኖሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ ሆነ አልሆነ ሥራው ወዲያው የሕግ ጥበቃ ያገኛል፡፡

የኦዲዮቪዥዋል ሥራን በተመለከተ የፕሮዲውሰሩ ዋና መስሪያ ቤት ወይም ቋሚ መኖሪያው ኢትዮጵያ ውስጥ ከሆነ ሥራው በኢትዮጵያ ውስጥ ጥበቃ ያገኛል፡፡ እንዲሁም በኢትዮጵያ ውስጥ የተገነባ የኪነ ህንፃ ሥራ ወይም የቆመ ህንፃ ወይም ሌላ ስትራክቸር ውስጥ የተካተተ የኪነ ህንፃ ሥራ ጥበቃ እንደሚያገኝ በአንቀጽ 3(1)(ሐ) ና (መ) ላይ ተገልፆል፡፡

በአዋጁ አንቀጽ 3(2) እንደተገለፀው ኢትዮጵያ በፈረመቻቸው አለም አቀፍ ስምምነቶች ወይም ኮንቬንሽኖች መሠረት ጥበቃ ያገኙ ሥራዎች በአገራችንም ጥበቃ ይደረግላቸዋል፡፡

የሥራ አመንጪው በሥራው ላይ ያለው መብት

በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 40 እና 41 ላይ ማንኛውም ዜጋ በንብረቱ ላይ ሙሉ መብት እዳለው እና በፈለገው የሥራ መስክ ተሰማርቶ መኖር እንደሚችል ደንግጎል፡፡ በማንኛነውም ሥራ ላይ የተሰማራ ሰው ከሥራው ኢኮኖሚያዊና የሞራል መብት እንደሚያገኝ እሙን ነው፡፡ በሥነ ጽሑፍ፣ የኪነጥበብ ወይም በሳይንሳዊ ፈጠራ ሥራ ላይ የተሰማራ ማንኛውም ሰው እነዚህ መብቶች እንደሚያኝ በአዋጀ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 7 እና 8 ላይ ተገልፆ ይገኛል፡፡

 ሀ/  ኢኮኖሚያዊ መብት

የሥራ አመንጪው ኢኮኖሚያዊ መብት ማለት ከፈጠራ ሥራው የሚያኘው በገንዘብ ሊለካ የሚችል መብት ማለት ነው፡፡ ይህ መብቱም በአዋጁ አንቀጽ 7 ላይ እንደተገለፀው ሥራውን የማባዛት፣ የመተርጐም፣ የማመሳሰል፣ የማቀናበር ወይም ወደ ሌላ አይነት መቀየር፣ በሽያጭ ወይም በኪራይ ኦርጅናል ሥራን ወይም ቅጂውን የማከፋፈል፣ ኦርጂናል ሥራን ወይም ቅጂውን ለህዝብ የማሳየት፣ በይፋ የመከወን፣ ብሮድካስት ማድረግ እና በሌላ መልክ ማሥራጨትን የመሳሰሉት መብቶች ያሉት መሆኑን ይገልፃል፡፡ እነዚህ መብቶች የሥራ አመንጪውን በኢኮኖሚያዊ ጥቅም እንዲያገኝ የሚያደርጉት ናቸው፡፡

አንድ የሥራ አመንጪ በሥራው ላይ ያለውን ኢኮኖሚያዊ መብት ለሌላ ሰው በውል አሳልፎ መስጠት ይችላል፡፡ የአንድ ወጥ የሥነ-ጥበብ ሥራ ወይም የአንድ ደራሲ ወይም የዜማ ደራሲ ኦርጅናል ጽሑፍ በሥራው አመንጪ ከተላለፈ በኋላ ከሚደረገው ድጋሪሚ ሽያጭ ዋጋ ላይ የሥራ አመንጪው ወይም ወራሹ የተወሰነ ድርሻ ማግኘትን መብት እንደለው በአዋጅ አንቀጽ 7/3/ ላይ ተገልፆል፡፡

 ለ/ የሞራል መብት

ይህ መብት በገንዘብ የማይተመን መብት ነው፡፡ ይህም የሥራው አመንጪ ለሰራው ሥራ ተገቢው እውቅና እንዲሰጠው የሚያደርግ መብት ነው፡፡ በአዋጅ አንቀጽ 8 ላይ እንደተገለፀው የሥራው አመንጪው የኢኮኖሚ መብት ባለቤት ቢሆንም ባይሆንም ወቅትዊ ሁኔታን በብሮሪድካስት አማካኝነት ለመዘገብ ባጋጣሚ ወይም በድንገት ከተካተተ ውጪ የሥራ ለአመንጪቱ እንዲታወቅ የመጠየቅ፣ ሳይታወቅ የመቆየት ወይም የብዕር ስም የመጠቀም፣ ክብሩንና መልካም ስሙን የሚያጎድፍ የሥራ መባዛት፣ መቆራረጥ ወይም በሌላ መልክ መቀየርን የመቃወም እና ሥራውን የማሳተም መብቶቹ የሞራል መብቱ ናቸው፡፡በሌላ አገላለፅ የሞራል መብት የፈጠራ ሥራው ባለቤት ደራሲ (የሥራው አመንጪ) የመባል፣ ሥራዎቹ እንይዛቡ የማድረግና መሰል መብቶችን የሚያካትት ነው፡፡

እነዚህ የተዘረዘሩት መብቶች በሕግ መሠረት ለወሳሾች ወይም ለስጦታ ተቀባዮች ካልሆነ በቀር የሥራ አመንጪው በህይወት እያለ ወደ ሶስተኛ ሰው ሊተላለፉ አይችሉም፡፡ የሞራል መብት ከኢኮኖሚያዊ መብት በተቃራኒ መልኩ ወደ ሶስተኛ ወገን በውል ሊተላለፍ አይችሉም፡፡

የኢኮኖሚያዊና የሞራል መብቶች ፀንተው የሚቆዩበት ጊዜ

ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች የሚገኙ የኢኮኖሚያዊ መብቶች የቆይታ ጊዚያቸውን በተመለከተ በሕጉ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ አለው፡፡ የህም በአዋጁ አንቀጽ 20 ላይ እንደተገለፀው የኢኮኖሚያዊ መብቶች የሥራ አመንጪው በህይወት በሚቆይበት ዘመንና ከሞተ በሆላ ለወራሾቹ እስከ 50 (ሃምሳ) ዓመት ፀንቶ እንደሚቆዩ ተገልፆል፡፡

በተመሳሳይ መልኩ የሞራል መብቶችም የሥራ አመንጪው በህይወት እስካለ ድረስ እና ከሞተ በኃላ የኢኮኖሚያዊ መብቶቹ ፀንተው ለሚቆዩበት ጊዜ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በአዋጁ አንቀጽ 8(4) ተገልፆል፡፡

የሥራ አመንጪው ኢኮኖሚያዊ መብቱን የማይጠቀምበት ሁኔታዎች

አንድ የሥነ ጽሑፍ፣ የኪነጥበብ ወይም ሳይንሳዊ ፈጠራ ባለቤት ከላይ በተገለፀው መልኩ የኢኮኖሚያዊ መብቶች እንዳሉት ተመልክተናል፡፡ ነገር ግን እነዚህን የኢኮኖሚያዊ መብቶች የሥራው አመንጪ ወይም ወራሾቹ ወይም የቅጂ መብት ባለቤት የሆኑ ሰዎች የማይጠቀሙበት ሁኔታ አለ፡፡ ይህ ማለት በነዚህ ሁኔታዎች ኢኮኖሚያዊ መብቶቼ ተጥሰዋል በማለት ጥያቄ የማያቀርብባቸው ወይም እዳይደረጉ ብሎ መከልከል የማይችልባቸው ናቸው፡፡ በአዋጅ ቁጥር 410/1996 ከአንቀጽ 9 እስከ 19 ድረስ በተቀመጡት ሁኔታዎች ያለ ሥራ አመንጪው ወይም ወራሾቹ ወይም የቅጂ ባለመብቱ ፍቃድ ውጭ የኢኮኖሚያዊ መብቶች ሌሎች ሰዎች ሊጠቀሙበት ይችላሉ፡፡ እነዚህም፡-

         1ኛ አንድ ቅጂ ለግል ጥቅም ለማዋል ማባዛት፣

         2ኛ ከአንድ ከታተመ ሥራ ጥቅስ መውሰድ፣

          3ኛ ለማስተማሪያነት ወይም ለማብራሪያ የሚውል የታተመ ሥራ ወይም የድምፅ ሪከርዲንግ ማባዛት፣

          4ኛ ለትርፍ ባልተቋቋመ ቤተ-መፃህፍት፣ ቤተ-መዛግብት ወይም መሰል ተቋማት የሚያደርጉት ማባዛት፣

          5ኛ ለህዝብ መረጃ አገልግሎት ዓላማ ማባዛት፣ ብሮድካስት ማድረግና ማሰራጨት፣

          6ኛ የኮምፒተር ፕሮግራሙ ለታለመለት ዓላማና አገልግሎት እዲውል ነጠላ ቅጅ ማድረግ ወይም ማሻሻል፣

          7ኛ ለግል አገልግሎት ዓላማ ወደ አገር ውስት መስገባት፣

          8ኛ በግል በቤተሰብ ወይም በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ ያለ ክፍያ የሚደረግ ክወና እና

          9ኛ አንድ የታተመ ሥራ ቅጅ ለህዝብ የተሸጠ ሲሆን ቅጅው በሽያጭ መልክ እደገና መሸጥ ናቸው፡፡   

ኢኮኖሚያዊ መብት የመጀመሪያ ባለመብትነት፣ ስለማስተላለፍና ፈቃድ ስለመስጠት

ኢኮኖሚያዊ መብት የመጀመሪያ ባለመብትነት፣

ሁልጊዜም ቢሆን የአንድ ሥራ አመንጪ ለሥራው የመጀመሪያው የኢኮኖሚያዊ መብቶች ባለቤት ነው፡፡ አንድ ሥራ በበርካታ የሥራ አመንጪዎች የተሰራ ከሆነ የሥራ አመንጪዎቹ በጋራ የመጀመሪያ የኢኮኖሚያዊ መብቶች ባለቤት ይሆናሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ሥራ የስብስብ ሥራ ሲሆን ወይም በተቀጠረ ወይም የአገልግሎት ክፍያ በተከፈለው ሰው የተሰራ ከሆነ የመጀመሪያ የኢኮኖሚያዊ መብቶች ባለቤት ሥራው እንዲሰራ ያመነጨው ሰው ወይም ቀጥሮ ያሰራው ሰው ይሆናል፡፡  ሥራው የኦዲዮቪዥዋል ሥራ ከሆነ ፕሮዲውሰሩ የመጀመሪያ የኢኮኖሚያዊ መብቶች ባለቤት ይሆናል፡፡

አንድ የፈጠራ ሥራ ተሰርቶ ሲወጣ ተቃራኒ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ ሥራው በስሙ የታተመ ሰው የሥራው አመንጪ ተደርጎ የሕግ ግምት እደሚወሰድ የአዋጁ አንቀጽ 22(1) ላይ ተገልፆል፡፡ በመሆኑም ሥራው የኔነው የሚል ሌላ ሰው ካለ የሱ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ አቅርቦ ይህን የሕግ ግምት ማፍረስ መቻል አለበት፡፡

የሥራው አመንጪ ባልታወቀት ጊዜ ስሙ በሥራው ላይ የተጠቀሰው አሳታሚ ተቃራኒ ማስረጃ እስካልቀረበ ድረስ የሥራው አመንጪ እንደወከለው ተቆጥሮ የኢኮኖሚያዊ እና የሞራል መብቶች ተጠቃሚ  ይሆናል፡፡

ኢኮኖሚያዊ መብት ስለማስተላለፍና ፈቃድ ስለመስጠት

በአዋጁ አንቀጽ 23 ላይ የሥራው አመንጪ ወይም የቅጅ መብት ባለመብቱ የኢኮኖሚያዊ መብቱን ሙሉ ለሙሉ ወይም በከፊል ማስተላለፍ ወይም ፈቃድ መስጠት እደሚችል አስቀምጧል፡፡ ይህን መብቱን የሚያስተላልፈው ወይም ፍቃድ የሚሰጠው በጽሑፍ በሆነ ውል እደሆነም ንኡስ ቁጥር 2 ይገልፃል፡፡ ይህም የሆነው የመብቱን ባለቤት የሆነውን ሰው በአግባቡ ጥበቃ ለማድረግ ታስቦ ነው፡፡ ይህ በጽሑፍ የተደረገ የመብት ማስተላለፍ ወይም ፍቃድ መስጠት ሁሉንም የኢኮኖሚያዊ መብቶች (በአዋጁ አንቀጽ 7 ላይ የተመለከቱትን) ወይም የተወሰኑ መብቶቹን ብቻ ሊሆን ይችላል፡፡ እነዚህ የተላለፉ ወይም በፍቃድ የተሰጡ መብቶች የቱ የቱ እደሆነ መገለፅ አለባቸው፡፡ ማንኛውም ኢኮኖሚያዊ መብት ማስተላለፍ ወይም በፍቃድ መስጠት በግልፅ ያልተመለከተን መብት መተላለፍን ወይም መፍቀድን እደማጨምር በእንቀፅ 22(3) ላይ ተገላፆል፡፡

የኢኮኖሚያዊ መብት የተላለፈለት ወይም ፍቃድ የተሰጠው ሰው መብት በስምምነቱ መስረት የሚወሰን ይሆናል፡፡ የዚህ መብት ወሰን በመብቱ መገልገል ወይም መጠቀም የተገደበ ነው፡፡ ይህ መብት ሥራው የታተመበትን ቁሳዊ ነገር የባለቤትት መብት አያጠቃልልም፡፡

የሥራው አመንጪ ወይም የቅጅ መብት ባለቤት የሆነው ሰው የኢኮኖሚያዊ መብቶቹን በስምምነት ሲያስተላልፍ ወይም ፍቃድ ሲሰጥ ለምንያክል ጊዜ እንደሚቆይ ሊስማሙ ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ይህን የቆይታ ጊዜ በጽሑፍ ስምምነታቸው ውስጥ ያላካተቱት ከሆነ ሕጉ ይህ መብት የሚቆጥበትን ጊዜ አስቀምጦል፡፡ መብትን ማስተላለፍ ለ10 ዓመታት ብቻ ወይም በፍቃድ መስጠት ከሆነ ደግሞ ለ5 ዓመታት ብቻ እንደሆነ በአዋጁ አንቀጽ 24 (3) ላይ ተገልፆል፡፡ ይህ መሆኑ በቆይታው ጊዜ ላይ የሚፈጠረውን አለመግባባት የሚያስቀር እና መብታቸውን የሚያስከብር ነው፡፡

ስለመብቶች ተፈፃሚነት

በጊዜያዊነት ስለሚወሰዱ እርምጃዎች

በቅጅና ተዛማጅ መብቶችን በተመለከተ በቅጂ ምክንያት የሚፈጠርን የመብት ጥሰት ለመከላከል፣ ተፈፀመ የተባለን መብት ጥሰት የሚያስረዱ አግባብነት ያለውን ማስረጃ ለመጠበቅ፣ መዘግየቱ በባለመብቱ ላይ ሊተካ የማይችል ጉዳት ሊያደርስ የሚችል የሚያመላክት ነገር ካለ ፍርድ ቤት ፈጣንና ውጤታማ የጊዜያዊ አርምጃ ትዕዛዝ መስጠት ግዴታና ሃላፊነት አለበት፡፡ በአዋጁ አንቀጽ 33 ላይ እነዚህን ጊዜያዊ ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ባለመብቱ የመጠየቅ መብት እዳለው እና ፍ/ቤቶችም ይህን የማድረግ ግዴታ እዳለባቸው ደንግጎል፡፡  

የፍትሐብሄር  መፍትሔዎች

የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ጥሰትን በተመለከተ በባለመብቱ ላይ ለሚደርስ ማንኛውም የኢኮኖሚያዊና የሞራል መብት ጥሰት የፍትሐብሄር ክርክሮች አቅርበው መብታቸውን የማስከበር መብት አላቸው፡፡ ይህን የፍትሐብሄር መብት ክርክር አስመልክቶ የዳኝነት ስልጣን ያለው ፍርድ ቤት (በተሻሻለው አዋጅ መሠረት የአእምሮዊ ፅ/ቤት በሚቋቋመው ትሪቡናል ከውል ውጭ ያሉ ክርክሮችን ሳይጨምር) የመብቱ ባለቤት ያወጣውን ወጪ ጨምሮ ለደረሰበት ቁሳዊና ሞራላዊ ጉዳት በቂ ካሳ እዲከፈለው የማዘዝ፣ ጊዜያዊ እግድ መስጠት እና አስፈላጊ ሆኖ ያገኘውን ሌሎች ትዕዛዞችን መስጠት እዳለበት በእንቀፅ 34 ላይ ተገልፆል፡፡ 

የድንበር ላይ እርምጃዎቸ

የኢትዮጵያ የገቢዎችና የጉምሩክ ባለስልጣን የቅጅ ወይም ተዛማጅ መብቶች በለቤት በሚያቀርበው ማመልከቻ መሠረት አመልካቹ መብቱን የጣሱ ናቸው ብሎ ያመበባቸውን ዕቃዎች ወይም ባለስልጣኑ በራሱ አነሳሽነት የመብቱ ጥሰት ያስከትላሉ ብሎ ያመበባቸውን ዕቃዎች በቁጥጥር ስር በማድረግ ወደሃገር ውስጥ አንዳይገቡ ማድረግ እዳለበት በአዋጁ አንቀጽ 35 እና በማሻሻያ አዋጁ ላይ ተመልክቷል፡፡ 

የወንጀል ቅጣት

በአዋጅ ቁጥር 410/1996 እና ማሻሻያ አዋጅ 872/2007 ላይ የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን ሆነ ብሎም ሆነ በቸልተኝነት የጣሰ ሰው በወንጀል አንደሚቀጣ ይደነግጋሉ፡፡ በዚሁ መሠረት ጥበቃ ያገኙ መብቶችን ሆነ ብሎ የጣሰ ማንኛውም ሰው ከ5 አመት በማያንስ እና ከ10 አመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራት እና ከብር 25000 በማያንስ እና ከብር 50000 በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡ እነኚህኑ መብቶቸ በከፍተኛ ቸልተኝነት የጣሰ ማንኛውም ሰው ከ1 አመት በማያንስ እና ከ5 አመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራት እና ከብር 5000 በማያንስ እና ከብር 25000 በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡

ከዚህም የእሥራት እና የመቀጮ በተጨማሪ አግባብነት ባለው ጊዜ ወንጀሉን ለመፈፅም ያገለገሉ ዕቃዎች ወይም መሳሪያዎች እና መብት የጣሱ ዕቃዎችን መያዝ፣ መውረስ እና ማውደምን ትዕዛዝ ሊሰጥባቸው ይችላል፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የሚያስገኙ ሥራዎች ምዝገባ ጠቀሜታ

የቅጅ መብት ኢንዱስትሪ በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ባህላዊ እድገት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው፡፡  የኮፒራይት ኢንዱስትሪው ይህንን ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችለው ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሲሰጠውና በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ከሥራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ የሚበረታቱበትን ሁኔታ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የቅንጅትና ተዛማጅ መብት ጥበቃ አዋጅ መውጣት አንዱና ዋነኛው መገለጫ ነው፡፡ የአምሯዊ ንብርት ባለቤትነትን የማረጋገጥ ተግባር ከዘረፉ ውስብስብነት አንፃር የአዋጁ መውጣት ብቻውን የፈጠራ ባለሙያዎችን መብት ለማስከበር በቂ አይደለም፡፡ በመሆኑም በአዋጁ የተቀመጠውን ጥበቃ ለማስፈጸም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የሚያስገኙ ሥራዎች ምዝገባ ደንብ ማዘጋጀት ማጽደቅና ሥራ ላይ ማዋል አስፈላጊ ነው፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብት የሚያስገኙ ሥራዎች  በሕግ ጥበቃ ለማግኘት ግዙፍነት ማግኘትና ወጥ (ኦሪጂናል) መሆን በቂ ነው፡፡ ይህም ከኢንዱስትሪያዊ ንብረቶች የሚለዩበት ዋና ባህርይ ነው፡፡ በፈጠራ ሥራዎች ባለቤቶችም ዘንድ ሆነ በሕግ አስፈፃሚ አካል ምዝገባ ለቅጅና ተዛማጅ መብት ጥበቃ እንደ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠ አድርጎ የማየት አዝማሚያ ቢኖርም፤ ምዝገባ ለቅጅና ተዛማጅ መብቶች አስገዳጅ አይደለም፡፡ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ባለቤቶች ፍላጎት አነሳሽነት ምዝገባ ማድረግ ግን ይችላል፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብት የሚያስገኙ ሥራዎች በዓለም አቀፍ ስምምነቶች መሠረት የሚደረገው ጥበቃ አውቶማቲክ ነው፡፡ የቅጅና ተዛማጅ መብት የሚያስገኙ ሥራዎች ወጥና ግዙፍ እስከሆኑ ድረስ ያለምንም ቅመ ሁኔታ ጥበቃ እንደሚደረግላቸው በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 6(1) ተደንግጓል፡፡ ስለሆነም የቅጅና ተዛማጅ መብት የሚያስገኙ ሥራዎችን መመዝገብ ለምን ያስፈልጋል? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል፡፡

1ኛ. በሕግ አስፈፃሚ አካላት ዘንድ የትኞቹ ሥራዎች ኦርጅናል ናቸው፤ የትኞቹ የተቀዱ ናቸው የሚለውንና መሰል ከቅጅና ተዛማጅ መብት ጥሰት ጋር ተያይዞ በሚነሱ ክርክሮች ላይ መረጃ የማግኘት ችግሮች ሲከሰቱ ይስተዋላል፡፡ በዚህ ረገድ የቅጅና ተዛማጅ መብት የሚያስገኙ ሥራዎች ምዝገባ የመጀመሪያ ደረጃ ማስረጃ በመሆን ሊያገለግል ይችላል፡፡ በመሆኑም በሕጉ የተቀመጠው አውቶማቲክ ጥበቃ እንዳለ ሆኖ የፈጠራ ሥራ ባለቤቶች ሥራዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ አእምሯዊ ንብረት ጽ/ቤት በመውሰድ የፈቃደኝነት ምዝገባ ሊያከናውኑ ይችላሉ፡፡ ይህም ከላይ የተጠቀሰውን የማስረጃ ችግር ሊያቃልል ይችላል፡፡

2ኛ. በተጨማሪም የቅጅና ተዛማጅ መብት የሚስገኙ ሥራዎች ምዝገባ በኮፒራይት ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚያደረጉ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ሊያቀላጥፍና ሊያፋጥን ይችላል፡፡

3ኛ. በሌላም በኩል የቅጅና ተዛማጅ መብት ጥሰት በቅጅና ተዛማጅ መብት ጥበቃ አዋጅ መሠረት ከባድ ቅጣትን የሚያስከትል በመሆኑ እነዚህን ሥራዎች ወደ ተግባር ለመቀየር የሚደረግ የግብይት ሂደት ውስጥም የባለቤትነት ማረጋገጫ ጥያቄ በገዢዎች በኩል ሲነሳ ይታያል፡፡ በአብዛኛውም ገዢዎች እና አታሚዎች የባለቤትነት ማረጋገጫ ከሚመለከተው የመንግሥት መስሪያ ቤት ካላመጣችሁ ህትመትም ሆነ ሌሎች ተግባራን አናከናውንም በማለት የኮፒራይት ኢንዱስትሪው በፍጥነት እንዳያድግ በተወሰነ መልኩ መሰናክል ሆኗል፡፡ በዚህ ረገድ ይህ የፈቃደኝት ምዝገባ በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚከሰቱ ችግሮች ሊያቃልል ይችላል ተብሎ ይታመናል፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁ.410/1996 ላይ የተደረገ ማሻሻያ እና አዋጅ ቁጥር 872/2007 ማብራሪያ

በአገራችን ለሥነ-ጽሑፍ፣ ኪነ-ጥበብና ሳይንሳዊ መስክ ውጤት ለሆኑ የፈጠራ ሥራዎች ጥበቃ የሚያደርገው አዋጀ ቁ.410/1996 የባለመብቶችን ኢኮኖሚያዊና ሞራላዊ መብቶች ከዓገለም አቀፍ ስምምነቶች ጋር በተጣጣመ መልኩ የተቀረፀ በመሆኑ በአዋጁ ላይ የተካተቱት አግባብ ያላቸው ድንጋጌዎች፣ መሰረታዊ አሰተሳሰቦችንና ጉዳዩችን ያቀፋ ዓለም አቀፍ ይዘት ያላው ናቸው፡፡ በሌላ በኩል በአዋጁ ላይ መካተት የነበረባቸው ነገር ግን ያልተካተቱ ሃሳቦችን በመለየት እና በማካተት የቅጅና ተዛማጅ መብቶችን በተሟላ ሁኔታ ለማስጠበቅ እና ለማስተዳደር በሚያስችል መልኩ እንዲሻሻሉ እንዲሁም የዘርፋ እድገት የሚፈጥራቸውን አዳዲስ አሰራሮች በማካተት አዋጁን እንደገና በመፈተሽ ሊወስዱ የሚገባቸውን ማሻሻያዎች ተግባራዊ ማድረግ የዘርፋን እድገት ቀጣይነት ለማረጋገጥ በሚደረግ እንቅስቃሴ ውስጥ የሚኖረው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነው፡፡ በተጨማሪም የቅጅና ተዛማጅ መብት ባለቤቶች በተደራጅና በተጠናከረ አግባብ መብቶቻቸውን ማስተዳደር የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር አስፈላጊ በመሆኑ እና ሀገራችን የበርን (በዓለም አቀፍ ደረጃ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ላይ የተደረገ ስምምነት ነው) ስምምነትን ለመፈረም በዝግጅት ላይ የምትገኝ በመሆኑ በአዋጁ ላይ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ከስምምነቱ ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ለማድረግ አሁን በሥራ ላይ ያለውን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ  ቁጥር 410/1996 ማሻሻል አስፈላጊ እንደሆነ ታምኖበት አዋጁ ተሸሽሎ አዋጅ ቁጥር 872/2007 ፅድቆ በሥራ ላይ ውሏል፡፡

በአዋጁ 410/1996 ላይ የተመላከቱ የሕግ ክፍተት ያለባቸው ድንጋጌዎች እና በአዋጅ 872/2007 የተሸሻሉ

1ኛ. አንቀጽ 6 (2)፡- ጥበቃ ለማግኘት የሚያስፈልጉ መመዘኛዎች

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጠበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 6(2) መረት የፎቶግራፍ ሥራዎች ጥበቃ ለማግኘት አንቀጽ 6(1) ላይ ከተጠቀሰው ወጥ መሆን እና ግዙፍነት የማግኘት መስፈርት በተጨማሪ ሥራው የአንድ ስብስብ አካል ወይም በመጽሀፍ ሲታተሙ ወይም የሥራ አመንጪዎች ወይም የወኪሉ ስምና አድራሻ ሲይዙ ጥበቃ የሚደረግላቸው ሲሆን ይህም በበርን ስምምነት አንቀጽ 5 /2/ ላይ አንድ ሥራ ያለምንም ፎርማሊቲ ጥበቃ ማግኘት እንደሚኖርበት ከተቀመጠው አንፃር ሲታይ ልዩነት የሚፈጥር በመሆኑ በአዋጁ ላይ የተቀመጠውን መስፈርት በማንሳት አዋጁን ማሻሻል እንደሚገባ ታምኖበት በአዋጅ ቁጥር 872/2007 ይህ ድንጋጌ ተሽሮል፡፡

2ኛ. አንቀጽ 9፡- ለግል አገልግሎት ሥራን ማባዛት

በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 9/1/ መሠረት የቅጅ መብት ባለቤት የታተመ ሥራን ለግል ፍጆታ አንድ ቅጅን ጥቅም ላይ ለማዋል ጥበቃ የሚደረግለትን ሥራ ማባዛት እንደሚችል ተቀምጧል፡፡ በዚህ መሠረት ማንኛውም ግለሰብ ጥበቃ የሚደረግለትን የታተመ ሥራ አንደ ኮፒ ለግል ዓላማው ማባዛት ይችላል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን አዋጁ ለግል ጥቅም የሚደረግ ማባዛት ተግባራዊ ከመደረጉ በፊት መሟላት ያለበትን ጉዳይ በግልፅ ባያስቀምጥ አዋጁን ሊያስፈፅመው ከተነሳበት ዓላማ አንፃር ማንኛውም ሰው ጥበቃ የሚደረግለትን ሥራ ለግል ፍጆታ ከማባዛቱ በፊት የቅጂው ኦርጂናል ሥራ በቅድሚያ ባለቤት ሊሆን ይገባል፡፡ ይህም የቅጂ መብት ባለቤቱ በአዋጁ የተሰጡትን የኢኮኖሚያዊ መብቶች ከማረጋገጥ አንፃር የሚኖረው ፋይዳ የላቀ እንደሆነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ በዚሁ መሠረት ጥበቃ የሚደረግለትን ሥራ ለግል ፍጀታ አንድ ቅጂ ለማባዛት በቅድሚያ የቅጂው ኦርጂናል ሥራ ሊኖር እንደሚገባ በማካተት በማሻሻያ በአዋጁ ቁጥር 872/2007 ላይ በማስቀመጥ ነባሩን ድንጋጌውን አሻሽሎታል፤፤ ይህም በድንጋጌው ላይ ግልፅነትን ከመፍጠር አኳያ የሚኖረው አስተዋጽኦ የላቀ ነው፡፡

3ኛ. አንቀጽ 20፡- የቅጅ መብት ኢኮኖሚያዊ መብቶች የሚቆዩበት ጊዜ

በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ አንቀጽ 20 መሠረት የኢኮኖሚ መብቶች የሥራ አመንጪው በህይወት በሚቆይበት ዘመን እና ከሞተ በኋላ ለወራሾቹ እስከ ሃምሳ አመት ፀንተው ይቆያሉ ይላል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በበርን ስምምነት መሠረት ኢኮኖሚ መብቶች ለሥራ አመንጪው ፀንተው የሚቆይቱ በህይወት እስካለ ጊዜ ድረስ ሲሆን ከሞተም በኋላ ለወራሾቹ እስከ ሃምሳ አመት ድረስ የሚቆዩ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ከበርን ስምምነት ጋር ተቃርኖን የሚፈጥር አይደለም፡፡

ነገር ግን በአዋጁ መሠረት የሥራ አመንጭው ከሞተ በኋላ የጥበቃ ግዜው መቆጠር የሚጀምረው የሥራ አመንጪው ከሞተበት አመት ጀምሮ በመሆኑ እና በበርን ስምምነት ደግሞ የጥበቃ ግዜው ተግባራዊ የሚሆነው የሥራ አመንጪው ከሞተበት አመት ቀጥሎ ከአለው አመት January 1 ጀምሮ በመሆኑ በአዋጁ መሠረት የቀመጠው የጥበቃ ግዜ ከሃምሳ አመት በታች ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም  በአዋጁ የተቀመጠ ግዜ ገደብ በስምምነቱ ከተቀመጠው የጥበቃ ግዜ ከሃምሳ አመት በታች ሊሆን የሚችልበትን ሁኔታ በመገንዘብ በበርብን ስምምነት ላይ የተቀመጠው መሠረት የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጁን ማሻሻል አስፈልጎል፡፡ በዚህም በኢትዩጵያ እና በውጪው አለም ባለው የዘመን አቆጣጠር ልዩነት በወራት መካከል የሚፈጠረውን ልዩነት ለማስታረቅ እንዲቻል በበርን ስምምነት መሠረት እ.አ.አ የዘመን መለወጫ የመጀመሪያ ወር የሆነውን ጥር ወር የመጀመሪያ ቀን (January 1) እንዳል በመውሰድ በአዋጅ ማሻሻያ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

4ኛ. አንቀጽ 30፡- “የድምፅ ሪከርዲንግ ለመጠቀም የሚፈፀም ክፍያ”

“ለንግድ ዓላማ የታተመ የድምፅ ሪከርዲንግ ወይም ቅጅው በቀጥታ በብሮድካስቲንግ ወይም ሌላ ለህዝብ ከቀረበ ወይም በይፋ ከተከወነ ተጠቃሚው ለከዋኙ፣ ለድምፅ ሪከርዲንግ ኘሮውዲውሰሩ ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ አንድ ጊዜ ይከፍላል፡፡”

ከላይ በተጠቀሰው ድንጋጌ መሠረት ለንግድ ዓላማ የታተመ የድምፅ ሪከርዲንግ እንደ ካፍቴሪያወች፣ መዝናኛ ቦታዎች ባሉ ህዝብ በተሰበሰበሳቸው ቦታዎች ከቀረበ ወይም ደግሞ በቴሌቪዥን፣ በሬድዩ፣ በተለያዩ ድህረ-ገፆችና በመሳሰሉት የብሮድካስቲንግ ድርጅቶች በቀጥታ ከቀረበ ተጠቃሚው “ተመጣጣኝ የሆነ ክፍያ” አንድ ጊዜ መክፈል እንዳለበት ተቀምጧል፡፡

ድንጋጌው የፈጠራ ባለመብቶችን መብት በማስጠበቅ በኩል ያለው ጠቀሜታ ከፍተኛ ሆኖ ሳለ አንድ የድምፅ ሪኮርዲንግ ተጠቃሚ የሥራው ባለቤት እንዴትና የት መክፈል ለእንዳለበት የሚገልፅ ነገር የለውም፡፡ በተጨማሪም ድንጋጌው በሌሎች ሀገራት በሰፊው እየተሰራበት የሚገኘውን የሮያሊቲ ሥርዓት ግልፅ የማያስቀምጥና የስርዓቱን ሙሉ ይዘት ባካተተ መልኩ የተደነገገ በመሆኑ በአፈፃፀም ደረጃ ከፍተኛ የሆነ ክፍተት የሚፈጥር ነው፡፡ ድንጋጌው በዋናነት ሁለት ክፍተቶች ያሉት ሲሆን የመጀመሪያው ክፍያ ሊፈፀምባቸው የሚገባቸው ሥራዎች የደምፅ ሪኮርበዲንግ ብቻ እንደሆኑ በማድግ ሌሎቹ ሥራዎች ያገለለ ነው፡፡ ሁለተኛ የሚፈፀመው ክፍያ ሥራው ጥቅም ላይ እስከዋለ ድረስ የሚቀጥል መሆን እያለበት ለአንድ ግዜ መወሰኑ የጥበቀውን ዓላማ የሚያሳካ አይደለም፡፡

በመሆኑም ድንጋጌው የሮያሊቲ ሥርዓትን በተሟላ ሁኔታ ለመዘርጋት የሚያስችል ሌላ ድንጋጌ መተካት ያለበት በመሆኑ ራሱን ችሎ አንድ ድንጋጌ በማካተት በማሻሻያ አዋጁ ውስጥ ተቀምጦል፡፡ በዚሁ መሠረት በማሻሻያ አዋጁ መሠረት የሮያሊቲ የመክፈል ግዴታ በሚል አንቀጽ 38 በማለት አካቶታል፡፡ ድንጋጌው እዳስቀመጠው በአዋጁ መሠረት ጥበቃ የሚያገኝ ማንኛውንም ሥራ ለንግድ ዓላማ ጥቅም ላይ የሚያውል ማንኛውም ሰው የሮያሊቲ ክፍያን ለሚመለከተው የጋራ አስተዳደር ማህበር የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ በሕጉ ታሳቢ የተደረገውን ክፍያ በተሻለ ሁኔታ መፈፀም በሚችሰልበት አግባብ ማስቀመጡ ተገቢ ይሆናል፡፡

   5ኛ. አንቀጽ 35 ፡- የድንበር ቁጥጥር ሥርዓት

በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ከድንበር ጋር ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዩች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ ስርዓቶች ተቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሠረት በአዋጅ ቁጥር 410/1996 አንቀጽ 35 ላይ መወሰድ የሚገባቸውን የድንበር ላይ እርምጃዎች በግልፅ እንደተቀመጠው የጉምሩክ ባለስልጣን የቅጂ ወይም የተዛማጅ መብት ባለቤት በሚያቀርበው ማመልከቻ መብቱን የተጣሱ ናቸው ብሎ ያመነባቸውን እቃዎች በቁጥጥሩ ስር ማዋል እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ የጉምሩክ ባለስልጣን በቁጥጥር ስር ያዋላቸውን እቃዎች ለባለመብቱ በማሳወቅ አመልካቹ እቃው ከተያዘበት ቀን ጀምሮ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ ተገቢውን ህጋዊ ማስረጃ ካላቀረበ  ባለስልጣኑ በእቃዎቹ ላይ ያደረገውን ቁጥጥር እንደሚያነሳ ተጠቅሷል፡፡

በአዋጁ መሠረት ባለስልጣኑ መብት የጣሱ እቃዋችን በቁጥጥር ስር የሚያውለው ከባለመብቱ ከሚርበው ማመልከቻ ሲሆን በራሱ ተነሳሽነት የሚወስደው ምንም አይነት እርምጃ የሌለ በመሆኑ ባለመብቶች ከሀገር በሚወጡ እና በሚገቡ እቃዎች ላይ መረጃ እንዲኖራቸው ወይም ቁጥጥር እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው ነው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ እንደ እኛ አገር ባለች ታደጊ አገር ተግባራዊ ሊሆን መቻሉ ጥያቄ ውስጥ የሚባና ለመተግበር እጅግ አዳጋች የሆነ ነው፡፡

በመሆኑም በአዋጁ ላይ በቀመጠው መሠረት የጉምሩክ ባለስልጣን በባለመብቶች ከሚቀርበው ማመልከቻ በተጨማሪ ባለስልጣኑ ቅድመ ምዝገባ በማድረግ ቁጥጥር የሚያደርግበት እና በራሱ ተነሳሽነት መብት ጥሰት የሚያስከትሉ ናቸው ብሎ በጠረጠራቸው እቃዎች ዝውውር የሚያግድበትን አሰራር በማካተት አዋጁን በማሻሻል አስፈላጊ በመሆኑ በዚህ መልኩ እዲሻሻል ተደርጎል፡፡

6ኛ. አንቀጽ 36 የወንጀል ቅጣት

በዚህ በአዋጅ ቱጥር 410/1996 አንቀጽ 36 ላይ እንደተመለከተው ከሆነ ጥበቃ ያኙ መብቶችን ሆነ ብሎ የጣሰ ሰው ከአምስት አመት እስከ አስር የሚደርስ ቅጣት እንዲሁም ከፍ ባለ ቸልተኝነት እነዚህኑ መብቶች የጣሰ ሰው ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት የሚደርስ ቅጣት የሚጣልበት መሆኑ ተደንግጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ቅጣቱ ወንጀሉን ለመፈፀም ያገለገሉ እቃዎች ወይም መሳሪያዎች እና መብት የጣሱ እቃዎችን መያዝ፣ መውረስ እና ማውደምን እንደሚጨምር ተቀምጧል፡፡

በዚህ አንቀጽ ስር ሊነሳ የሚባ ጉዳይ ቢኖር በአለም አቀፍ ጉዳዩች ላይ ተግባራዊ የሚሆነው የገንዘብ ቅጣት በአዋጅ ላይ ተካትቶ ይገኛል ወይ የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ላይ የሚፈፀም ሕገወጥ ድርጊትን ለመከላከል የወንጀል ቅጣቶችን ማጠናከር አስፈላጊ ጉዳይ ነው፡፡

የፌዴራል ከፍተኛ ፍ/ቤት ውሳኔ ከሰጠባቸው የወንጀል ክስ መጒቦች መረዳት እንደሚቻለው በተለያዩ አጋጣሚዎች ጥፋተኞች በተከሰሱበትና በጥፋተኝነታቸው ከተላለፈባቸው የእስር ቅጣት ባለፈው አዋጅ ላይ ባልተቀመጠበት ሁኔታ በገንዘብ መቀጣታቸውን መረዳት ይቻላላ፡፡

የሌሎች አገራት ምርጥ ተሞክሮ የሚያሳያው እውነታም ይህ ነው፡፡ ለምሳሌ በጀርመን እና  በብሩበንዲ ሕግ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ላይ የሚፈፀም ሕገ-ወጥ ድርጊት ከእሥራት ባለፈ በገንዘብ ቅጣት የሚያስቀጣ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህና በተጨማሪ በTRIPS ስምምነት አንቀጽ 61 ላይ ሀገራት የማስፈራራት አቅም ያለው የንዘብ ቅጣት በህጎቻቸው ላይ እንዲካተቱ የሚደነግግ በመሆኑ የቅጣት ድንጋጌው መሰል የገንዘብ ቅጣት እንዲያካትት ማድግ አስፈላጊ ነው፡፡ በመሆኑም ቅጅና ተዛማጅ መብቶች ላይ የሚፈፀሙ የመብት ጥሰቶች ደረጃን፣ ወንጀሉ የሚፈፀምበትን ሁኔታ እና የቅጣት መጠኑ በማስፈራራት ረገድ (Deterrence effect) የሚኖረው ሚና ታሳቢ በማድግ ከብር 5‚000 የማያንስ እና ከብር 50‚000 የማይበልጥ የገንዘብ ቅጣት በማሻሻያው እንዲካተት ተደርጓል፡፡

 በአዋጅ 410/96 ውስጥ ያልተካተቱ በአዋጅ 872/2007 በአዲስ የተካተቱ ተጨማሪ ጉዳዩች

ዕደ ጥበብን/Applied Art/

በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ መረት የዕደ-ጥበብ ሥራዎች በአዋጁ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ሥራዎች ውስጥ በግልጽ አልተካተተም፡፡ በሌላ በኩል በዓለም አቀፋ የበርን ስምምነት የዓደ-ጥበብ ሥራዎች ጥበቃ ከሚደረግላቸው ሥራዎች ውስጥ የሚካተት በመሆኑ የቅድና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅን ከዚህ ዓለም አቀፍ ጋር ማስተሳሰር የሚባ ነው፡፡ ስለሆነም በቅጅና ተዛማጅ መብቶች አዋጅ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ሥራዎች ውስጥ የዕደ-ጥበብ ሥራዎች በግልጽ እንዲካተቱ በማድረግ ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ ስለተገኘ በማሻሻያ አዋጁ ውስጥ ዕደ-ጥበብ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ ሆኖ እንዲካተት ተደርጎል፡፡

የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበራትን በተመለከተ

የቅጅ መብት የጋራ አስተዳደር ማህበራት (copyright collective management societies) አባሎቻቸውን በመወከል ሮያሊቲ ከተጠቃሚዎች የሚሰበስቡ ሲሆን የተሰበሰበውን ሮያሊት መልሰው ለአባሎቻቸው የሚያከፋፍሉ ናቸው፡፡

የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁ.410/96 የጋራ አስተዳደር ማህበራትን በተመለከተ የሚለው ነገር የለም፡፡ ስለ ማህበራቱ መቋቋም፣ የሮያሊቲ ክፍያ ከተጠቃሚዎች ላይ የመሰብሰብ ስልጣን እንዲሁም የሬያሊቲ ክፍያ አሰባሰብና ተያያዥ የሆኑ ጉዳዩች በአዋጁ ላይ አልተካተቱም፡፡ በዚህም የተነሳ በአገራችን እየተንቀሳቀሰ ባለው የኢትዩጵያ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበር ላይ የሮያሊቲ ክፍያ አሰባሰብን በተመለከተ የሕግ መሠረት ጥያቄ ይነሳል፡፡ የመጀመሪያው የጋራ አስተዳደር ማህበሩ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ላይ የሮያሊቲ ክፍያን ከተጠቃሚዎች ላይ የመሰብሰቡ ስልጣን ያልተሰጠው በመሆኑ ማህበሩ የሮያሊቲ ክፍያን ከማህበሩ አባላት ወጪ ከሚገኙ ተጠቃሚዎችን ላይ የመሰብሰብ ስልጣን የለውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ማህበሩ የበጎ አድራጎት ድርጅት ማህበራት አዋጅ ቁ.621/2001 መሠረት በማድግ የተቋቋመ ማህበር በመሆኑ የሮያሊስቲ ክፍያ ከተጠቃሚዎች የመሰብሰብ ስልጣን የለውም የሚል የመከራከሪያ ሀሳብ ይቀርባል፡፡ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ማህበራት አዋጅ ቁ.621/2001 አንቀጽ 55 ላይ እንደተጠቀሰው “ማህበር ማለት ዓላማው ትርፍ ለማግኘት ያልሆነ የአባላቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅ እና ተመሳሳይ ህጋዊ ዓላማዎችን ለማከናወን እንዲሁም ተመሳሳይ ዓላማ ካላቸው ተቋማት ጋር ለመተባበር በአባላቱ ስምምነት የተመሰረተ የሰዎች ስብስብ ነው፡፡” በዚህ መነሻነት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበርም ሆነ ሌሎች በአገራችን የሚገኙ የሙያ ማህበራትተ ዓላማ ትርፍ ለማግኘት የሚቋቋሙ ሳይሆን የአባላቱን መብትና ጥቅም ለማስጠበቅና ሌሎች ህጋዊ ተግባራትን ለማከናወን በመሆኑ ከማህበሩ አባላት ውጪ ከገኙ ግለሰቦችና ድርጅቶች ማንኛነውም አይነት ክፍያ ለመሰብሰብ ስልጣን የላቸውም፡፡ በመሆኑም የኢትዩጵያ የቅጂና የተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበራት ከማህበሩ አባላት ውጪ ካሉ ግለሰቦችና ድርጅቶች የሮያሊቲ ክፍያ ለመሰብሰብ አሁን በአገራችን ባለው የሕግ ማዕቀፍ መሠረት ስልጣን የሌላቸው በመሆኑ የቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁ.410/96 ይህን ጉዳይ በማካተት እንደገና ተሻሽሎ እንዲቀርብ ማድግ አስፈላጊ ነበር፡፡

የሌሎች አገራት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት የቅጅና ተዛማጅ መብቶች የጋራ አስተዳደር ማህበራት (copyright collective management societies) አባባሎቻቸውን በመወከል ሮያሊቲ ከተጠቃሚዎች የመሰብሰብና መልሶ ለአባሎቻቸው የማከፍፈል ስልጣን በኮፒራይት ሕጎች ላይ የተቀመጠ በመሆኑ በሮያሊቲ ክፍያ አሰባሰብ ላይ የሚነሳ የሕግ ጥያቄ የለም፡፡ በመሆኑም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ የጋራ አስተዳደር ማህበራትን ሮያሊቲ የመሰብሰብ ስልጣንና ሌሎች ተያያዥ የሆኑ ጉዳዩችን ማካተት ያለበት ነው፡፡

ይህንንም መነሻ በማድረግ በማሻሻያ አወጁ ቁጥር 872/2007 ውስጥ የጋራ አስተዳደር ማህበር በማለት አንድ ክፍል በማካተት ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች እንዲፈቱ አድርጎል፡፡

የአእምሯዊ ንብረት ትሪቡናል/ የዳኝነት ሥልጣን

በነባሩ አዋጅ ቁጥር 410/1996 ላይ እንደተመለከተው ማንኛውንም በቅጂና ተዛማጅ መብቶች ጥሰትን በተመለከተ የሚነሱ ፍትሐብሔራዊ ክርክሮችን የሚዳኘው መደበኛው ፍርድ ቤት እደሆነ በአንቀጽ 33 እና 34 ተደንግጎል፡፡ ይህ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች በባህሪያቸው ለየት ያለ የተወሰነ እውቀትን በጉዳዩ ዙሪያ የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የማስረጃዎቻቸው በባህሪያቸው ውስብስብ በመሆናቸው በመደበኛ ፍርድ ቤት ላይ ከመደበኛ ሥራቸው ላይ ጫና የሚያሳድሩ እና የጉዳ መጎተትን የሚያስከትሉ በመሆናቸው እና በተግባርም ይህው እያጋጠመ ያለ ችግር ነው፡፡ በመሆኑም እነዚህን ችግሮች ለመፍታት ሲባል በተሸሻለው አዋጅ ቁጥር 872/2007 ውስጥ መፍቴ ማሰቀመጥ ተገቢ ሆኖ ተገኝቶላ፡፡ በዚሁ መሠረትም በተሸሻለው አዋጅ ውስጥ በቅጂና ተዛማጅ መብቶች የሚነሱ ከውል ውጭ ስለሚደርስ ሃላፊነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በስተቀር የፍትሐብሔር ክርክሮችን የመዳኝት ስላጣን የሚኖረው በአእምሮዊ ንብረት ጽ/ቤት በሚያቆቁመው የአእምሮዊ ትሪቡናል እደሚሆን ደንግጎል፡፡ ነገር ግን ይህ ትሪቡናል እስኪቋቋም ድረስ ክርክሩን የመዳኘት ስልጣኑ የመደበኛው ፍርድ ቤት ሆኖ እንደሚቀጥል ተጠቅሶል፡፡ ይህ ትሪቡናል ከተቆቆመ በሆላ በሚሰጠው ውሳኔ ላይ የሕግ ስህተት አለ የሚል ተከራካሪ ለከፍተኛው ፍርድ ቤት በ60 ቀናት ውስጥ ይግናኙን ማቅረብ እደሚችልም ተገልፆል፡፡

ማጠቃለያ

የሥነ ጽሑፍ፣ ዕደ-ጥበብ፣ የኪነ ጥበብ፣ ሳይንሳዊ ፈጠራዎች እና ተመሳሳይ የፈጠራ ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ በሚከናወኑ ሥራዎች ላይ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች በሕግ እውቅና መስጠትና ጥበቃ ማድረግ አዳዲስ ፈጠራዎች እንዲበራከቱ እና የሚጠበቅባቸውን በህላዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሳይንሳዊና ቴክኖሎጂያዊ እድገት በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲያመጡ እንዲሁም የፈጠራው ባለቤቶች ከሥራቸው እንዲጠቀሙ በማድረግ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይኖረዋል፡፡

የኮፒራይት ኢንዱስትሪ በአንድ አገር ኢኮኖሚያዊ፤ ማህበራዊና ባህላዊ እድገት ውስጥ የሚኖረው ፋይዳ ከፍ ያለ ነው፡፡  የኮፒራይት ኢንዱስትሪው ይህንን ጠቀሜታ ሊያስገኝ የሚችለው ለዘርፉ ተገቢው ትኩረት ሲሰጠውና በዘርፉ የተሰማሩ ሰዎች ከሥራቸው ተጠቃሚ የሚሆኑበትንና ለበለጠ ሥራ እንዲነሳሱ የሚበረታቱበትን ሁኔታ መፍጠር ሲቻል ነው፡፡ በዚህ ረገድ የቅንጅትና ተዛማጅ መብት ጥበቃ አዋጅ መውጣት አንዱና ዋነኛው መገለጫ ነው፡፡

ነገር ግን የሕጉ መውጣት ብችውን ፋይዳ የለውም ይልቁንም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ይህን መብት በማክበርና በማስከበር የበኩሉን ድርሻ ሲወጣ የታለመው ግብ ሊሳካ የሚችለው፡፡ በመሆኑም ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባዋል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ዳኛ  እግዜር! ዳኛ ከችሎት ይነሳ!
የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 145 አፈፃፀም ላይ የሚስተዋል መሠረታ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 19 May 2024