Font size: +
8 minutes reading time (1604 words)

የኃይማኖት ነክ ሥራዎች የቅጂ መብቶች

-    ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስራዎች የቅጂ መብት በአዋጁ እንዴት ይታያል?

-    ያለ ባለቤቱ ፍቃድ ማሳተም አለመከልከሉ የቅጂ መብትን ሌላ ሰው እንዲጠቀም መፍቀድ ማለት ነው፤

-    በመፅሔት፣ በጋዜጣ እና በመፅሐፍ የወጡ ስራዎች የሚኖራቸው የቅጂ መብት ጥበቃ ይለያያል?

-    በአለቃ አያሌው ታምሩ ወራሾችና በአንድ አሳታሚና ማተሚያ ቤት መሀከል እስከ ሰበር የደረሰው የቅጂ መብት ጥሰት ክርክር በምን ተቋጨ?

1. ሃይማኖታዊ ስራዎችና የቅጂ መብት

ሟች የአለቃ አያሌው ታምሩ (ነፍሳቸውን ይማርና) የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ / አስተምህሮቶች ላይ የጠለቀ እውቀት የነበራቸው ሊቀ ሊቃውንት ነበሩ። በርካታ ሃይማኖታዊ ስብከቶችን፣ ትምህርቶችን አስተያየቶችን በመስጠት ይታወቃሉ። እኚህ ሰው ታዲያ በርካታ ስራዎቻቸውን ብቻ ሳይሆን ሕጋዊ ወራሾቻቸው የሆኑ ዘጠኝ ልጆችን ትተው ነበር ያለፉት።

አለቃ አያሌው ታምሩ ከሞቱትምህርተ ሃይማኖትየሚል መፅሐፍ ተዘጋጅቶ ገበያ ላይ ይውላል። አሳታሚው አቶ ሳሙኤል ኃይሉ የተባሉ ግለሰብ ሲሆኑ፤ አታሚው ደግሞ ሆራይዘን ማተሚያ ቤት የተባለ የግል ድርጅት ነበር። መፅሐፍ የያዘው የሟችን ፅሁፎች፣ በጋዜጣና በመፅሔቶች ላይ የወጡ ቃለ መጠይቆች፣ መጣጥፎችን፣ ከሟች የመንፈቅ መታሰቢያ ፖስተር ላይ የወጣ የሽፋን ስዕልና የሐዘን መግለጫ ግጥሞችን ያካተተ ነበር። አለመግባባቱ የተከሰተው አሳታሚውም ሆነ አታሚው አለቃ አያሌው ታምሩ ባይኖሩም የፈጠራ ስራዎቻቸውን ለማሳተም ከዘጠኙ ወራሾቻቸው ፍቃድ ባለመጠየቁ ነው።

ዘጠኙ ወራሾች ከሰሱ፡የሟች የአለቃ አያሌው ታምሩ ወራሾች ያለ ፍቃዳችን የአባታችን የፈጠራ ስራዎችትምህርተ ሃይማኖትበሚል ርዕስ ታትመው ለገበያ ወለዋል። ከአባታችን በውርስ በስራዎቹ ላይ ያገኘነው የቅጂ መብቶት ተጥሰዋል። ጥሰቱን የፈፀሙት አሳታሚው 1 ተከሳሽ አቶ ሳሙኤል ኃይሉ አታሚው 2 ተከሳሽ ሆራይዘን ማተሚያ ቤት ናቸው። ስለዚህ የታተሙት መፅሐፍት እንዲወገዱ ህትመቱ እንዲቆም የህሊና ጉዳት ካሳ 100000 ብር (መቶ ሺህ ብር) ከተሸጡት ሦስት ሺህ መፅሐፍት የተገኘ ገቢ ብር ስልሳ ሺህ ወራሾች መፅሐፉን እራሳቸው አሳትመው ቢሸጡ ኖሮ ሊያገኙ የሚችሉትን ብር ሁለት መቶ ሃምሳ ሺህ በአንድነትና በነጠላ እንዲከፈላቸው ክስ መሰረቱ።

የተከሳሾች መልስ፡መቼም ክስ ቀርቦበት አዎን አጥፍቻለሁ ብሎ የሚያምን ወይም ዝም የሚል ብዙ አይገኝም። 1ኛው ተከሳሽ አቶ ሳሙኤል አለቃ አያሌው የሥራው አመንጪ መሆናቸውን የሚያሳይ ማስረጃ አልቀረበም የጽሁፍ ስራዎቹ የአለቃ የግል ስራዎች ሳይሆኑ የኦርቶዶክስ /ክርስቲያንን ወቅታዊ ሃይማኖታዊ ጥያቄዎችን አስመለክቶ ያላቸውን የእምነት አቋም የገለፁበት በመሆኑና ስራውን የማሰራጨት የእርሳቸው ብቻ መሆኑን የሚያሳይ ነገር የለም በሚል ክሱን ሲቃወም። በፍሬ ነገሩ ላይ ደግሞ ሟች ስራውን የማሰራጨት መብታቸውን አልጠበቁም። ስራዎቹ በቤተክርስቲያኒቷ አውቀት ላይ ስለተመሰረቱ አለቃ የስራው አመንጪ እንደማይባሉ ስራው ወጥ /ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ/ ባለመሆኑ የሕግ ጥበቃ እንደሌለው ሟች የጀመሩትን የሃይማኖት ትምህርት ለህዝብ በማሰራጨታቸው አቶ ሳሙኤል ሊከሰስ አይገባም ብለዋል።

ሁለተኛ ተከሳሹ ሆራይዘን ማተሚያ ቤት ደግሞ ምንጩ የአለቃ አያሌው ታምሩ መሆኑ በመገለፁ ሊጠየቅ እንደማይገባ የሠራተኞችን ፍቃድ መጠየቅ ያለበት 1 ተከሳሽ አታሚው እንጂ አታሚው ስራው የሟች ፈጠራ መሆኑን ማስረጃ አለመቅረቡን በራሱ አነሳሽነት ያለማተሙንና የሟች ስራ መሆኑን ስለማያውቅ የቀረበበት ክስ ውድቅ እንዲሆን ጠየቀ።

//ቤት ምን ወሰነ፡ክሱ የቀረበለት የፌ///ቤት የዘጠኙን የአለቃ አያሌው ወራሾችና የሁለቱን ተከሳሾች ክርክር መርምሮ ሁለተኛ ተከሳሽ የሆነውን ሆራይዘን ማተሚያ ቤትን ከክሱ ነፃ ሲያደርግ 1 ተከሳሽ አቶ ሳሙኤል ግን ያቀረበውን መከራከሪያዎች ባለመቀበል የቅጂ መብት ጥሰሀል መፅሐፍ መታተሙ ይቋረጥ የታተሙትም ይወገዱ ከመፅሐፍ ሽያጭ የተገኘው ብር ስልሳ ሺህ እና ወራሾች ላይ ለደረሰ የህሊና ጉዳት ብር መቶ ሺህ በድምሩ አንድ መቶ ስልሳ ሺህ ካሳ እንዲከፈል ወሰነበት።

ዘጠኙ ወራሾችም 1 ተከሳሽም ይግባኝ ጠየቁ፡ለማ ለፌ///ቤት። የአለቃ አያሌው ወራሾች 2 ተከሳሽ የነበረው ማተሚያ ቤቱ ነፃ መባሉ አለአግባብ ነው የሚል ይግባኝ ሲያቀርቡ 1ኛው ተከሳሽ የመፅሐፍ አሳታሚ አቶ ሳሙኤል በስራ /ቤት የቅጅ መብት ጥሰሃል ኃላፊ ነህ መባሌ አለአግባብ ነው አሉ። /ቤቱ 1 ተከሳሽ የአቶ ሳሙኤልን ይግባኝ አያስቀርብም ብሎ ሲሰርዘው የአለቃ አያሌውን ወራሾች ይግባኝ ደግሞ በመቀበል ማተሚያ ቤቱ በከ//ቤት ነፃ የተባለው ከሕግ ውጭ ነው በአንድነትና በነጠላ ከአቶ ሳሙኤል ጋር የሟችን ስራ ከነ ፎቶ ግራፋቸው ያለ ወራሾች ፍቃድ አትሞ በማውጣቱ የተወሰነውን ካሳ የመክፈል ኃላፊነት አለበት ሲል ወሰነ።

አሳታሚና አታሚ ለሰበር አቤቱታ አቀረቡ፡አሳታሚው አቶ ሳሙኤል ስራው የሟች ወጥ ስራ ያለመሆኑንና ሟች ስራው ለህዝብ እንዳይሰራጭ ባላደረጉበት ሁኔታ የቅጅ መብት ጥበቃ አለው ተብሎ መወሰኑ እንዲሁም መከላከያ ማስረጃ በስር /ቤት ሳላሰማ መወሰኑ የሕግ ስህተት ነው አለ።

አታሚው ሆራይዘን ደግሞ እኔ አታሚ እንደመሆኔ ሌላ ሰው እንዲታተም ባቀረበልኝ ስራ መጠየቄ አላግባብ ነው። ስራው ወጥ ሳይሆን ሟች መፅሐፍ ቅዱስ ጠቅሰው ቤተክርስቲያኗን ወክለው ሲያስተምሩ የነበሩት የቤተክርስቲያን ስራ በመሆኑና ሟች ከሀሳቡ አመንጪ ፍቃድ ውጨ ማባዛት ማሰራጨት ማተምወዘተ የሚል ያስቀመጡት ክልከላ ስለሌለ ለቅጅ መብት ጥሰት ኃላፊ ነህ በመባሌ የሕግ ስህተት ተፈፅማል ስለዚህ ይታረምልኝ የጠ//ቤት ውሳኔ ይሻር አለ። የፌ///ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የአሳታሚውና የአታሚውን አቤቱታ መርምሮ ለሰበር ያስቀርባል ካለ በኋላ የአለቃ አያሌው 9 ወራሾች በተጠሪነት ቀርበው መከራከሪያቸውን እንዲያቀርቡ አዞ የፅሁፍ መከራከሪያ ያቀረቡ ሲሆን፤ የግራ ቀኙን የፅሁፍ ክርክሮች መርምሮ በሰ.. 68369 ጥር 4 ቀን 2004 . በዋለው ችሎት ውሳኔ ሰጥቷል። ውሳኔው የፌ///ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ቅፅ 13 ላይ ታትሞ ወጥቷል፤ ሙሉውን ማንበብ የፈለገ ገፅ 576 ላይ ያገኘዋልና ወደዚያ መርቼዋለሁ። የመጨረሻውን ውሳኔ ከማየታችን በፊት በክርክሩ ላይ የተነሱ አበይት የሕግ ነጥቦችን እናንሳ።

2. ሃይማኖታዊ ስራዎች የፈጠራ ስራዎች ናቸው?

በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አወጅ ቁጥር 410/96 በአንቀፅ 2() የቅጅ መብት ሊያመነጩ የሚችሉ ሥራዎች የሥነ ጽሁፍ የኪነጥበብ እና ሳይንሳዊ መስኰች ውጤቶች ሲሆኑ በተለይ ብሎ ከዘረዘራቸው ሥራዎች ውስጥ አንዱ የሃይማኖት ስብከቶች (Sermons) ናቸው። ስለዚህ ከሃይማኖታዊ ስራዎች በተለይ ስብከቶች እንደ ፈጠራ ስራ የሚቆጠሩ ሲሆን፤ የቅጅ መብት ጥበቃ ለማግኘት በአዋጁ አንቀጽ 6(1) ወጥ (ኦርጅናል) የሆነ የሥራ አመንጪው የአእምሮ ፈጠራ ሥራውን በመፍጠሩ ብቻ ጥበቃ ያገኛል። ሌሎች ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ሥራዎችን በተመለከተ በመጣጥፍ መልክ በአንቀፅ 2(30) () ላይ ለተወሰነ ክፍል የሚደረግ መልዕክት አዘል ንግግር ወይም ሌላ በቃል የቀረበ ስራ በሚለው ስር ሊወድቁ ስለሚችሉ ወጥ ከሆኑ የፈጠራ ስራ በመሆናቸው የቅጅ መብት ጥበቃ ይደረግላቸዋል።

የፌ///ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በመነሻችን ላይ ያነሳነውን ክርክር ሲወስን በሰጠው ትንተናም ሟች አለቃ አያሌውየኦርቶዶክስ / አገልጋይ በነበሩበት ጊዜ ስለሃይማኖቱ የሰጡትን አስተያየት ማንም ሰው ለማሳተም የሚችልበት አግባብ አለ ወይስ የለም?” ብሎ በመጠየቅ ከሃይማኖት ስብከት ውጨ ያሉ ሌሎች ሃይማኖት ነክ ስራዎች ያላቸውን የመብት ጥበቃ የሚያስረግጥ ትርጓሜ ሰጥቷል። ለጥያቄው መልስ ሲሰጥም “…ሐሳቡ የኦርቶዶክስ / ሃይማኖታዊ ትምህርት ነው ቢባል እንኳን ሟቹ (አለቃ አያሌው) ሐሳቡን የገለፁበት ቅርፅ ግን የራሳቸው የፈጠራ ስራ በመሆኑ በሕጉ ጥበቃን ለማግኘት የሚያስችለውን መመዘኛ ማሟላቱን በበታች /ቤቶች በተደረገው ክርክር ተረጋግጧል።ሕጉ በዋነኝነት ጥበቃ የሚያደርገው የሐሳቡን አገላለፅ ቅርፅ እንጂ ሀሳቡን ራሱን አይደለም።በሚል የሰጠው ትርጓሜ ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸው ስራዎችም መጨመራቸው የሃይማኖቱ ነባር አስተምህሮቶች ወይም ቅዱሳት መፅሐፍት ቢሆኑም የሥራው አመንጪ ሃሳቦቹን ለማስተላለፍ የተጠቀመበት ቅርፅ ግን የራሱ የፈጠራ ስራ በመሆኑ ሕጉ ጥበቃ እንደሰጠው የሚያሳይ ነው። በመሆኑም ሃይማኖታዊ ይዘት ያላቸውም ቢሆኑ ሥራዎቹ የፈጠራ ስራ እስከሆነ ድረስ የቅጅ መብት ጥበቃ አላቸው።

3. በሥራው ላይ ያለ ባለቤቱ ሕጋዊ ፍቃድ ስራውን ማባዛት አለመከልከሉ የቅጂ መብት ጥበቃውን ያሳጣዋል?

በአለቃ አያሌው ወራሾች ላቀረቡት ክስ ተከሳሾች ካነሱአቸው የመከራከሪያ ነጥቦች አንዱ ሟቹ ስራቸውን እንዳይባዛ ወይም እንዳይሰራጭ አልከለከሉም ስለዚህ በመፅሐፍ መልክ አሳትመን በማሰራጨታችን የቅጂ መብት ጥሰት አልፈፀምንም የሚል ነው።

ለዚህ ክርክራቸው መነሻ ያደረጉት የአዋጁን አንቀፅ 13 ሲሆን፤ የቅጁ ኢኮኖሚያዊ መብቶች ሥራውን ማባዛት ብሮድካስት ማድረግ ወይም ሥራን በሌላ መንገድ የማሰራጨት መብትን ለስራ አመንጪው ወይም ለሥራው ባለቤት በራሱ የመስራት ሌሎች እንዲሰሩት የመፍቀድ መብቱን ቢሰጥም የሥራ አመንጪውን ስም እስከጠቀሰ ድረስ የማባዛት ብሮድካት የማድረግ ወይም ለህዝብ የማሰራጨት መብቱ የሥራው አመንጪ ወይም የቅጅ ባለመብቱ መሆኑን በቅጅው ላይ በግልፅ የተጠቀሰ ነገር ከሌለ የቅጂ መብት ባለቤቱ ሌሎች እንዳያሰራጩ እንዳይባዙ መከልከል እንደማይችል የተቀመጠው ድንጋጌ ነው።

ይሁን እንጂ ይህ ድንጋጌ አላማው ለህዝብ መረጃ ለመስጠት አገልግሎት የሚባዙና የሚሰራጩ ስራዎችን ባለመብቱ እስካልከለከለ እንደተፈቀዱ ለመግለፅ ነው። የሥራዎቹ አይነትም በአንቀፅ 13(1) ላይ ተወስኖ የተመለከተ ሲሆን “… በወቅታዊ የኢኰኖሚ የፖለቲካ ወይም የሃይማኖት ጉዳዮች ላይ በጋዜጣ በመፅሔት የወጡ ወይም ተመሳሳይ ባህሪ ኖሮአቸው ብሮድካስት የተደረጉ መጣጥፎችን በሌላ ጋዜጣ ወይም መፅሔት ማባዛትን በብሮድካሰቲንግ ወይም በሌላ መገናኛ ብዙሃን ለህዝብ ማድረስንበሚል ሌላ ሰው ባለመብቱ በግልፅ ካልከለከለ ሊያባዛ ወይም ሊያሰራጭ የሚችልበትን ሁኔታ ለይቶ አስቀምጦታል። ሆኖም ግን ሥራዎቹ በመፅሐፍ ወይም በሌላ መልክ የወጡ የፈጠራ ስራዎች ከሆኑያለደራሲው ወይም ያለ አሳታሚው ፍቃድ በማንኛውም መንገድ ማባዛት ማሰራጨት ክልክል ነውተብሎ በለመድነው መልክ አለመቀመጡ የቅጂ መብት ጥበቃውን የሚያሳጣው አይደለም። በተጨማሪም በጋዜጣ በመፅሔት ወይም ተመሳሳይ ባህሪ ባላቸው ማሰራጫዎች የወጡ ስራዎችን ለሚመለከት ባለቤቱ በግልፅ ያለፍቃዱ እንዳይሰራጩ ባይከለከልም ያለ ባለቤቱ ፈቃድ በመፅሐፍ መልክ አሳትሞ ማውጣት ግን የመብት ጥሰት ነው። የፌ///ቤት ሰበር ባነሳነው ክርክር ላይ በሰጠው ትንተና “… ለህዝብ መረጃ አገልግሎት ዓላማ የሚበዙና የሚሰራጩ ከሆነ በስራው ባለቤት በወጡበት መንገድ ከሚሆን በቀር በመፅሐፍ መልክ ታትመው የሚበዙበት አግባብ የሌለ መሆኑን ከአዋጁ አንቀጽ 13(1) ድንጋጌ ለህዝብ ስለማሰራጨትና ሰለማባዛት ሕጉ ከሰጠው ትርጎሜ ጋር ተዳምሮ ሲነበብ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። በአዋጅ አንቀፅ 13(10) ስርመፅሔትየሚለው ቃል “Periodical” የሚለውን የእንግሊዘኛ ቃል የሚተካ መሆኑን ሕጉ የሚያሳይ በመሆኑ ይኸው ቃል በማንኛውም መለኪያ መፅሐፍ የሚለውን ቃል አይተካም።በማለት በመፅሔት በጋዜጣ የወጡ ስራዎችን ያለ ባለቤቱ ፍቃድ በመፅሐፍ መልክ ማሳተም የቅጂ መብት ጥሰት ነው በሚል ድምዳሜ አስቀምጧል።

4. የማተሚያ ቤቶች ኃላፊነት፡-

የሕትመቱን ስራ የሚያከናውኑ ማተሚያ ቤቶች የቀረበላቸውን ስራ የራሱ የአሳታሚው ካልሆነ በቀር የሌላ ሰው ስራ ወይም ምስል ያለበት ሲሆን አሳታሚው ይሄንን ስራ ለማሳተም ከስራው ባለቤት ወይም ከወራሾቹ ፍቃድ እንዳለው ማረጋገጥ አለባቸው። በፍ// 26 እና 29 ላይ ያለባለቤቱ ፍቃድ የማንንም ሰው ፎቶ ግራፍ ማባዛትም ሆነ ማሰራጨት እንደማይቻል በመደንገጉና በፍ/// 2027 ላይ አንድ ሰው የወል ግዴታ ባይኖርበትም በሚሰራው ስራ ሌላ ሰው ላይ ለደረሰው ጉዳት ኃላፊ በመሆኑ አታሚዎች ከሚመጣላቸው ሥራ ውስጥ ባለቤቱ ወይም ባለምስሉ ሌላ ሰው ከሆነ ፍቃዱን መስጠቱን ሳያረጋግጡ ካሳተሙ ለሚደርሰው ኃላፊነት ከአሳታሚው ጋር በአንድነትና በነጠላ ተጠያቂ ይሆናሉ።

በአንድነትና በነጠላ ማለት ባለመብቱ ከአንደኛቸው ወይም ከሁሉም እንደምርጫው የተወሰነለትን ካሳ ወይም ገንዘብ በሕግ አስገድዶ መቀበል የሚያስችለውን የስራ የማስፈፀም መብት የሚሰጥ ከአንድ በላይ የሆኑ ሰዎች ላይ የሚኖር ኃላፊነት ነው።

በመጨረሻስየፌ///ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ክርክሮቹን መርምሮ የአለቃ አያሌውን ስራዋች ያለወራሾች ፍቃድ በመፅሐፍ በማሳተማቸው አሳታሚው (አቶ ሳሙኤል ኃይሉ) እና አታሚው (ሆራይዘን ማተሚያ ቤት) ለወራሾች በውርስ የተላለፈውን የቅጂ መብት በመጣሳቸው በአንድነተና በነጠላ አንድ መቶ ስልሳ ሺህ ብር የጉዳት ካሳ እንዲከፈሉ በፌ///ቤት የተሰጠው ውሳኔ ላይ የተፈፀመ የሕግ ስህተት የለም ብሎ ውሳኔውን በማፅናት አሰናብቷቸዋል። የሟች የአለቃ አያሌው ዘጠኝ ወራሽ ልጆቻቸው ከመቶ ስልሳ ሺህ ብር ካሳ በተጨማሪ ያለ ፈቃዳቸውትምህርተ ሃይማኖትየሚለው መፅሐፍ ተከሳሾች ማሳተማቸውን እንዲያቆሙና የታተሙና ወደፊት የሚታተሙት መፅሐፍት እንዲወገዱ በስር /ቤት የተሰጠው ትዕዛዝም ፀንቶላቸው ክርክሩ ለመጨረሻ ጊዜ እልባት አግኝተል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በፍርድ የተከለከለ ሰው ሞግዚት ፍቺ የመጠየቅ ሥልጣን አለው ወይ? በፌዴራል መጀ...
በ-ያለእድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 07 November 2024