በ-ያለእድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶች
ጋብቻ ክቡር፣ ምኝታውም ቅዱስ እንደ ሆነ የሀይማኖት መጻህፍት ያስተምራሉ፡፡ ከዚህም ሌላ ጋብቻ የህብረተሰብ ተፈጥሯዊ መነሻ የሆነው ቤተሰብ የሚመሰረትበት በመሆኑ ከመንግስትና ከህብረተሰብ ያላሰለሰ የህግ ጥበቃ ይደረግለታል፡፡ ይህም ጉዳይ በበርካታ አለም አቀፋዊ፣ አህጉራዊና ብሄራዊ ህጎች እውቅና አግኝቷል፡፡
ይሁንና የጋብቻው ክቡርነትም ይሁን የምኝታው ቅዱስነት የሚረጋገጠው እንዲሁም መንግስትና ህብረተሰብ ህጋዊ ጥበቃ የሚያደርጉለትን ቤተሰብ ለመመስረት ብቁነት የሚኖረው ጋብቻው በህግ መሰረት የተፈጸመ ሲሆን ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ በተቃራኒው በአማራ ክልል ከሚመሰረቱ ትዳሮች መሀከል ሰማኒያ ሁለት ከመቶ የሚሆኑት ያለ እድሜ ጋብቻ የሚፈጸምባቸው ናቸው፡፡
ከላይ የተገለጸው አሀዝ ከፍተኛነት ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነ ሲሆን ጽሁፉ ያለ እድሜ ጋብቻን ምንነት፣ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ስለ ያለ እድሜ ጋብቻ ያላቸውን አቋምና ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያጋጥሙ ችግሮችን በአጭሩ ይዳስሳል፡፡ በመቀጠልም በያለ እድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶችንና ያለ እድሜ ጋብቻ መፈጸም የሚያስከትለውን የህግ ተጠያቂነት በዝርዝር ይመለከታል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻ ምንነትና የሰብአዊ መብት ስምምነቶች አቋም
ኢትዮጵያ ውስጥ ከ140 በላይ የሚሆኑ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ አንዱና ዋናው ደግሞ ያለ እድሜ ጋብቻ ነው፡፡ በዚህ ያለ እድሜ ጋብቻ የአማራ ክልል በሀገር ደረጃ ቀዳሚውን ስፍራ የያዘ ሲሆን ይሄው ድርጊት ከገጠሩ የክልሉ ክፍሎች አልፎ በከተሞች አካባቢም ይፈጸማል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ከተጋቢዎቹ ጥንዶች ሴቷ፣ ወንዱ ወይም ሁለቱም ከ18 አመት በታች ሲሆኑ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በአፍሪካ የህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 21 (2) ስር በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድልዋዊ ልዩነት ለማስወገድ በተደረገው ስምምነት አንቀጽ 16 (2) መሰረትም አንድ ሰው ለጋብቻ የሚበቃበት አነስተኛ እድሜ መወሰን ይኖርበታል፡፡
በተመሳሳይ ሁኔታ በኢ.ፌ.ዲ.ሪም ሆነ በአማራ ክልል ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 34 (1) ላይ እንደተጠቀሰው በሕግ ከተወሰነው የጋብቻ እድሜ ላይ የደረሱ ወንዶችም ሴቶች የማግባትና ቤተሰብ የመመስረት መብት አላቸው፡፡ ነገር ግን በስምምነቱም ይሁን በሕገ-መንግሥቶቹ በሕግ መወሰን ያለበት እድሜ ስንት እንደ ሆነ ተለይቶ አልተቀመጠም፡፡
በመሆኑም ለጋብቻ የሚያበቃን አነስተኛ እድሜ ለማወቅ ህጻን ማን ነው ለሚለው ጥያቄ ምላሽ ማግኘት ያሻል፡፡ ምላሹም በአፍሪካ የህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተር አንቀጽ 2 ላይ ተጠቅሷል፡፡ ይሄው አንቀጽ “ህጻን ማለት እድሜው ከ18አመት በታች የሆነ ማንኛውም ሰው ነው” በማለት ሲተረጉም የህጻናት መብቶች ስምምነትም በአንቀጽ 1 ህጻን ለሚለው ቃል ተመሳሳይ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡
በዚሁም መሰረት በኢ.ፌ.ዲ.ሪ የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 7 (1) እና በአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 18 (1) “ወንዱም ሆነ ሴቷ አሥራ ስምንት አመት ሣይሞላቸው ጋብቻ መፈጸም አይችሉም” በማለት ተደንግጓል፡፡ ሆኖም ግን በእነዚህ አንቀጾች ንኡስ አንቀጽ (2) መሰረት የተለየ ከባድ ምክንያት ሲያጋጥም ተጋቢዎቹ በራሣቸው ወይም ከተጋቢዎቹ በአንዳቸው ወላጆች ወይም በአሣዳሪዎቻቸው በሚቀርብ ጥያቄ የፍትሕ ሚኒስትሩና የክልሉ ፍትሕ ቢሮ ይህንኑ እድሜ በሁለት አመት ዝቅ አድርገው ወደ 16 አመት ሊያወርዱት ይችላሉ፡፡
ከፍ ሲል የተጠቀሱት ሕጎች ሕጋዊ ጋብቻ ለመፈፀም ወንዶችና ሴቶች ዕድሜያቸው 18 ዓመት መድረስ እንዳለበት ቢደነግጉም ህጉ ወጥነት ባለው ሁኔታ ተግባራዊ አልተደረገም፡፡ እንዲያውም በገጠር የሚገኙ አብዛኞቹ የህብረተሰብ ክፍሎች ህጉ ስለመኖሩ ግንዛቤው የላቸውም፡ ስለሆነም በዕድሜ የገፉ ወንዶች ለአካለ-መጠን ያልደረሱ ሴቶችን የማግባት ባህላቸው ስር የሰደደ ሊሆን ችሏል፡፡
የአለእድሜ ጋብቻ ገፈት ቀማሾች ብዙን ጊዜ ሴት ህጻናት ሲሆኑ ወንዶች ልጆችም አልፎ አልፎ በድርጊቱ ሲጠቁ ይስተዋላል፡፡ ያለዕድሜ ጋብቻ ለመፈጸም ባህላዊ ምክንያቶቹ ጾታዊ ተፅዕኖ፣ ከጋብቻ በፊት የሚፈፀም ወሲብንና እርግዝናን መከላከል፣ ወገን ከወገን ማገናኘት ወዘተ የሚሉ ሲሆኑ ቁሳዊ ምክንያቶቹ ደግሞ ድህነት፣ አለመማር፣ የልጅ ልጅ ለማየት መፈለግ የመሳሰሉት ናቸው፡፡ ምክንያቶቹ ምንም ይሁኑ ምን ያለ እድሜ ጋብቻ በሴት ልጆች ላይ የሚፈጸም ከፍተኛ በደል መሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያጋጥሙ ችግሮች
ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚያጋጥሙ ችግሮች በርካታ ናቸው፡፡ እነዚህም ችግሮች ከአካባቢ አካባቢ፣ ከባህል ባህልና ከሓይማኖት ሓይማኖት ይለያያሉ፡፡ በዚህ ረገድ በእየለቱ ስራ ላይ በተግባር ከሚያጋጥሙትና ለአብነት መነሳት ካለባቸው ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ለአካለ መጠን ያልደረሰችውን ወይም 18 አመት ያልሞላችውን ለመዳር ዕድሜዋ ለጋብቻ የደረሰ ሌላ ሴት ልጅ ወደ ቅድመ-ጋብቻ የእድሜ ምርመራ ልኮ ማስመርመር በቀዳሚነት የሚጠቀስ ችግር ነው፡፡ ለምሳሌ፡- በእድሜዋ ለጋብቻ ያልደረሰችውን ህጻን ለመዳር ወይም ለማግባት አስበው ለዕድሜ ምርመራው ከ18 እስከ 20 ዓመት የምትገመት ሌላ ልጅ ልከው ሲያስመረምሩ በህብረተሰቡ እየተጋለጡ ጋብቻው ሳይፈጸም የሚቀርባቸው ሰዎች ቁጠር ቀላል አይደለም፡፡
2. ከእድሜ የህክምና ማስረጃ ጋር በተያያዘ የህክምና ባለሙያዎች ከዚህ እስከዚህ የሚል ማለትም ከ16-18 ወይም ከ17-18 ዕድሜ የሚል ማስረጃ ስለሚሰጡ የተጋቢዋ ወላጆችና አግቢዋ18 ዓመት ያልሞላትን ልጅ 18 ዓመት ሞልቷታል በማለት ጋብቻው እንዲፈጸም ያደርጋሉ፡፡ ፍርድ ቤቶችም ለሴት ህጻናቱ የተሻለ ጥቅም ከመወገን ይልቅ እንዲህ ዓይነቱን ማስረጃ ስለሚቀበሉ ጋብቻውን በፍትሐብሔር ከሶ ለማስፈረስና በወንጀል ለመክሰስ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ይህም ሁኔታ ያለ እድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚደረገውን ጥረት በማደናቀፍ ላይ ይገኛል፡፡
3. ከእድሜ የህክምና ማስረጃው ባሻገር ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስፈረስ የሠው ማስረጃም ለፍርድ ቤት ሊቀርብ ይችላል፡፡ ሆኖም ያለ እድሜ ጋብቻው ሲፈፀም ያዩ ሰዎች የተጋቢዎቹ ቤተሰቦች ስለሚሆኑ ፍርድ ቤት ቀርበው ለመመስከር ፈቃደኛ አይሆኑም፡፡ በመሆኑም እንዲህ አይነት ሰዎች ባሉበት አካባቢ ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቆም የሚደረገውን ሂደት ፈታኝ ያደርገዋል፡፡
4. ዕድሜያቸው ለጋብቻ ያልደረሰ ሴት ልጆች በተለይ በገጠር አካባቢ ለመምህራን፣ ለጤናና ለግብርና ሰራተኞች በቤት ሰራተኝነት ተቀጥረው ሲሰሩ በዚያው ወደ ጋብቻ ይገባሉ፡፡ ይህም ጉዳይ ያለዕድሜ ጋብቻን ለመከላከል ከሚያጋጥሙ እንቅፋቶች አንዱ ሆኖ ይታያል፡፡
5. ከህክምና ተቋማት ርቀው የሚገኙ ሴት ልጆች ዕድሜያቸውን ለማስመርመር ብዙ ብዙ ይቸገራሉ፡፡ ስለዚህ ወደ ህክምና ተቋማቱ የመሄጃና መመለሻ ገንዘብ እጦት ስለሚያጋጥማቸው የእድሜ ምርመራ ሳያደርጉ ለማግባት ይገደዳሉ፡፡ ስለሆነም የህክምና ተቋማት ርቀትና ድህነት ያለእድሜ ጋብቻን ለማስቆም ከሚያጋጥሙ ችግሮች ውስጥ የሚመደቡ ናቸው፡፡
6. ህብረተሰቡ የሴት ህጻናት ልጆቹን እድሜ ለማስመርመር ፈቃደኛ ካለመሆኑ ባለፈ ያለዕድሜ ጋብቻ ተፈፅሞ ሲገኝ አያጋልጥም፡፡ ሰርጉንም የሚፈጽመው በማህበር፣ በሰደቃ፣ በደቦና በሌሎች ተመሳሳይ ድግሶች አመካኝቶ ነው፡፡ ይህም ያለዕድሜ ጋብቻን ቁጥጥር አስቸጋሪ ሊያደርገው ችሏል፡፡
7. አንድ ወንድ እድሜዋ ለጋብቻ ያልደረሰችን ሴት ሊያገባት ሲፈልግ ለቤተሰቦቿ በገበሬነት ተቀጥሮ ይሰራል፡፡ ከዚያ በኋላም ቀስ ቀስ እያለ ህጻን ልጃቸውን ያገባል፡፡ እንዲህ አይነቱ ድርጊትም ከላይ እንዳየናቸው ችግሮች ሁሉ ያለዕድሜ ጋብቻን ለማስቀረት አስቸጋሪ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡
ያለእድሜ ጋብቻን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ህብረተሰቡ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከፍ ሲል ከተመለከቱት ችግሮች አብዛኞቹ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ በራሱ በህብረተሰቡ የሚፈጸሙ ናቸው፡፡ በእነዚህና ሌሎች መሰል ምክንያቶች ለማስቆም ባልተቻለው ያለእድሜ ጋብቻ በርካታ የህጻናት መብቶች ይጣሳሉ፡፡ እነዚህ መብቶች ምን ምን ናቸው ተብሎ ለሚነሳ ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት ይቻል ዘንድም ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ተዳሰዋል፡፡
ሀ. በህይወት የመኖር መብት
ሁሉም አለማቀፋዊና አህጉራዊ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ያለ ምንም ልዩነት ጥበቃ የሚያደርጉለት መብት ቢኖር በህይወት የመኖር መብት ነው፡፡ የኢ.ፌ.ዲ.ሪና የአማራ ክልል ሕገ-መንግስቶችም በተመሳሳይ በአንቀጽ 15 ማንኛውም ሰው በህይወት የመኖር መብት አለው በማለት ደንግገዋል፡፡ ይሁንና ይሄው የመብቶች ሁሉ እናት የሆነው መብት በተለያዩ ምክንያቶች ይጣሳል፡፡ ከምክንያቶቹም ግንባር ቀደሙ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊትነት የተፈረጀው ያለእድሜ ጋብቻ ነው፡፡
ያለእድሜ ጋብቻ እድሚያቸው ሳይደርስ የሚያገቡ ሴት ህጻናትን ጤንነትና ደህንነት አደጋ ላይ የመጣል ቀጥተኛ ውጤት አለው፡፡ ከዚህም አልፎ በውስብስብ እርግዝናና በልጅነት ወሊድ ሳቢያ አያሌ ህጻናትን ለሞት ይዳርጋል፡፡ ጥናቶች እንደሚያሳዩት ከ10 እስከ 14 አመታቸው ያገቡ ህጻናት በወሊድ ምክንያት የመሞት እድላቸው ለጋብቻ እድሜ ከደረሱት ከ5 እስከ 7 እጥፍ የሚበልጥ ሲሆን እድሚያቸው ከ15 እስከ 19 የሚሆኑት ደግሞ እድሚያቸው 20ና ከዚያ በላይ ከሆኑት በወሊድ የመሞት እድላቸው በእጥፍ ይበልጣል፡፡
በመሆኑም ያለእድሜ ጋብቻ የህጻናት እናቶችን ህይወት በመቅጠፍ የመሪነት ደረጃ ይዟል፡፡ ከዚህም ባሻገር 18 አመት ካልሞላቸው እናቶች የሚወለዱ ልጆች የመሞት እድላቸው 19 አመትና ከዚያ በላይ የሆኑ እናቶች ከሚወልዷቸው ህጻናት 60 ጊዜ ይበልጣል፡፡ ስለዚህ ያለእድሜ ጋብቻ የህጻናት እናቶችን ብቻ ሳይሆን በልጅነት አቅማቸው የወለዷቸውን ህይወት ጭምር የሚቀጥፍ አስከፊና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑን ማንኛውም ሰው ሊገነዘበው ይገባል፡፡
ለ. የትዳር ጓደኛን የመምረጥ መብት
የልጃቸውን ባል ወይም ሚስት መምረጥ ለብዙ ወላጆች የተለመደ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ እድሚያቸው ለጋብቻ ያልደረሱ ሴቶችም ሆኑ ወንዶች ልጆች ያለፈቃዳቸው እንዲያገቡ ይገደዳሉ፡፡ ይህም ድርጊት ያለእድሜ ጋብቻ እንዲፈጸም ያስችላል፡፡
በተግባር እየሆነ ያለው ከፍ ሲል የተገለጸው ቢሆንም ጋብቻ ያለተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈቃድ መመስረት እንደሌለበት የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች ሁሉ ያውጃሉ፡፡ በዚሁም መሰረት በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና ባህላዊ መብቶች አለማቀፍ ቃልኪዳን አንቀጽ 10 (1) ላይ በግልጽ እንደተመለከተው ጋብቻ በተጋቢዎች ፈቃድ የሚመሰረት ይሆናል፡፡
በሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለምአቀፍ ቃልኪዳን መሰረትም ያለተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈቃድ ጋብቻ መመስረት የለበትም፡፡ በሴቶች ላይ የሚደረግ ማንኛውንም አድልዋዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ስምምነትም እንዲሁ በአንቀጽ 16 (1) /ለ/ የትዳር ጓደኛን የመምረጥና ጋብቻን በውዴታና በነጻ ፍላጎት የመፈጸም መብት ለተጋቢዎች ብቻ የተሰጠ መሆኑን ይደነግጋል፡፡
ከእነዚህ አለማቀፍ የሰብአዊ መብት ስምምነቶች ጋር በተመሳሳይ ሁኔታ የኢ.ፌ.ዲ.ሪና የአማራ ክልል ሕገ-መንግስት አንቀጽ 34 (2) ጋብቻ በተጋቢዎች ነጻና ሙሉ ፈቃድ ላይ ብቻ እንደሚመሰረት ይገልጻል፡፡ ይሄው ድንጋጌ በኢ.ፌ.ዴ.ሪና በአማራ ክልል የቤተሰብ ሕግ አንቀጽ 6ና 17 እንደቅደምተከተላቸው ቃል በቃል ሊባል በሚያስችል መልኩ የሚጸና ጋብቻ ተፈጸመ የሚባለው ተጋቢዎቹ ለመጋባት ነጻና ሙሉ ፈቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ ነው በሚል ሰፍሮ ይገኛል፡፡
ነገር ግን ከላይ በተብራሩት የሰብአዊ መብት ስምምነቶችም ሆነ በብሄራዊ ሕጎች ከፍተኛ ትኩረት የተሰጠው የትዳር ጓደኛን በነጻና ሙሉ ፈቃድ የመምረጥ መብት ለተጋቢዎች ወላጆች የተሰጠ ያህል በመብቱ ሲጠቀሙ የሚስተዋሉት እነሱ እንጂ ተጋቢዎቹ አይደሉም፡፡ ስለሆነም መብቱ ከሚከበርበት ይልቅ የሚጣስበት ጊዜ ይበልጣል፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለቱ ተጋቢዎች ተመራርጠው፣ ወደውና ፈቅደው የሚጋቡበት እድል በጣም ጠባብ ከመሆኑም ባለፈ የወደፊት እጣፋንታቸውንም ለመወሰን እንቅፋት ሆኗል፡፡
ሐ. የመማር መብት
ሀገሮች ለማሳካት የሚደክሙለት “ትምህርት ለሁሉም” የሚለው መሰረታዊ አላማ ወንዶችንም ሆነ ሴት ህጻናትን በእኩል ደረጃ ይመለከታል፡፡ ሆኖም ግን ህብረተሰባችን ከትምህርት ይልቅ ለጋብቻ የበለጠ ዋጋ ስለሚሰጥ ያለእድሜ ጋብቻ በመፈጸም የአላማውን መሳካት በማደናቀፍ ላይ ይገኛል፡፡ ስለዚህ በመማር ላይ ሳሉ ያለእድሜ ጋብቻ የተፈጸመባቸው ሴት ህጻናት ከጋብቻው በኋላ በስራ ጫና፣ በወሊድና በቤተሰብ ግፊት ትምህርታቸውን ለመቀጠል አይችሉም፡፡
የመማር መብት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ሁሉን አቀፍ ዕውቅና አግኝቷል፡፡ በዚሁም መሰረት የሰብዓዊ መብቶች አለም አቀፋዊ መግለጫ በአንቀጽ26 ንኡስ አንቀጽ (1) በግልጽ እንደሚለው ማንም ሰው የመማር መብት አለው፡፡ የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች ስምምነት በ አንቀጽ 13 (1) እንደሚደነግገውም ማንኛውም ሰው ትምህርት የማግኘት መብት ያለው መሆኑን የስምምነቱ አባል አገሮች ሊያውቁ ይገባል፡፡
የህጻናት መብቶች ስምምነት በበኩሉ በአንቀጽ 28 የህጻናትን የመማር መብት ደረጃ በደረጃና ለሁሉም እኩል እድል መስጠት በሚለው መርህ ላይ በመመስረት የስምምነቱ ተዋዋይ አገሮች ተግባራዊ ማድረግ እንዳለባቸው በማያሻማ ሁኔታ አስቀምጧል፡፡ የአፍሪካ ህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተርም በአንቀጽ 11 ማንኛውም ህጻን የትምህርት መብት አለው ሲል ይደነግጋል፡፡
የመማር መብት በዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ሰነዶች ብቻ ሳይሆን በኢ.ፌ.ዴ.ሪና በአማራ ክልል ሕጎችም ከፍተኛ ትኩረት ያገኘ ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ሕገ-መንግስቶቹን ጨምሮ የመማር መብትን ለማስከበር የሚችሉ ብዙ ብዙ ፖሊሲዎች ጸድቀዋል፤ ሕጎችም ወጥተዋል፡፡
ሆኖም ግን ምን የሰብአዊ መብት ስምምነት ቢፈረም፣ ምን ፖሊሲ ቢጸድቅና ምን ሕግ ቢወጣ የሴት ህጻናትን ትምህርት የሚገታውን ያለእድሜ ጋብቻ ለማስቆም በሚችልበት አቅም ልክ አልደረጀም፡፡ በመሆኑም ሴቶች ልጆች ያለእድሜ ጋብቻ ሲፈጽሙ ከትምህርታቸው ጋር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቆራርጠው ይቀራሉ፡፡ ያልተማሩ ሴቶች ደግሞ ራሳቸውንም ሆነ ቤተሰቦቻቸውን በገንዘብ ሊደግፉ አይችሉም፡፡ በተለይም ባሎቻቸው ሲሞቱባቸው፣ ሲተዉዋቸውና ሲፈቷቸው ቀጣይነት ላለው ድህነት ይጋለጣሉ፡፡
መ. የጤና መብት
ባለእድሜ ጋብቻ አማካኝነት ወደ ትዳር የሚገቡ ሴት ህጻናት በእድሜ ብዙ ከሚበልጧቸው ባሎቻቸው ጋር የግብረ-ስጋ ግንኙነት ለመፈጸም በአካልም ሆነ በስነ-ልቦና ብቁ አይደሉም፡፡ በተጨማሪም ግንኙነቱን ተከትሎት ለሚመጣው እርግዝናና ወሊድ አካላዊም ይሁን አእምሯዊ ዝግጁነት የላቸውም፡፡ ይህ ደግሞ በተራው ሽንትና ሰገራን መቆጣጠር እንዳይችሉ ለሚያደርግ ፊስቱላ ለተባለ በሽታ ያጋልጣቸዋል፡፡
ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ከሚያጋጥሟቸው ውስብስብ ችግሮች በላይ ያለእድሜ ጋብቻ የፈጸሙ ሴት ልጆችን ህይወት ይበልጥ የከፋ የሚያደርገው ለአባላዘር በሽታዎች የመጋለጥና በኤችአይቪ ኤድስ የመያዝ እድላቸው ከፍተኛ መሆኑ ነው፡፡ ይህም ባሎቻቸው አስቀድሞ ከነበራቸው የግብረ-ስጋ ግንኙነት ጋር ይያያዛል፡፡ የባሎቻቸው ጥገኛ መሆንና ያላቸው የእድሜ ልዩነት ደግሞ ስለጤናማ ወሲብ እንዳያስቡ እንዲሁም ስለታማኝነት እንዳይገነዘቡ ያደርጋቸዋል፡፡
በየጊዜውና በየወቅቱ የሚወጡት አለማቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ሁሉ የጤና መብትን የተመለከተ ድንጋጌ የያዙ ናቸው፡፡ ዋና ዋናዎቹን ስንመለከት የኢኮኖሚ፣ የማህበራዊና የባህላዊ መብቶች ስምምነት አንቀጽ 12(1) “ማንኛውም ሰው ሊደርስበት ወደሚችል ከፍተኛ የአካልና የአእምሮ ጤንነት ወደተሟላበት የኑሮ ደረጃ የመድረስ መብት ያለው መሆኑን” ያውጃል፡፡ የአፍሪካ የሰዎችና የህዝቦች መብቶች ቻርተርም በተመሳሳይ በአንቀጽ 16 (1) “ማንኛውም ሰው የአካልም ሆነ የአእምሮ ጤንነቱ በሚኖርበት ማህበረሰብ ሊደረግ በሚችልበት ደረጃ እንዲጠበቅለት የማድረግ መብት አለው” በማለት ደንግጓል፡፡
የአፍሪካ ህጻናት መብቶችና ደህንነት ቻርተርም በአንቀጽ 14 (1) “እያንዳንዱ ህጻን የላቀ የአካል፣ የአእምሮና የመንፈስ ጤንነት የማግኘት መብት” እንዳለው ሲደነግግ በሴቶች ላይ የሚደረግን ማንኛውንም አድሏዊ ልዩነት ለማስወገድ የተደረገው ስምምነት አንቀጽ 12 (1) ደግሞ ስምምነቱን የተቀበሉ አገሮች በጤና አገልግሎቶች እኩል ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በሴቶች ላይ የሚደረግን አድልዎና ልዩነት ለማስወገድ አስፈላጊውን እርምጃ መውሰድ እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡
ከዚህ በላይ የተጠቀሱት የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀጽ 9 (4) መሰረት የሀገሪቱ የሕግ አካል ቢሆኑም ከስምምነቶቹ በተጨማሪ አንቀጽ 90 (1ን) መሰረት አድርገው ሁሉም ኢትዮጲያዊ የጤና አገልግሎቶች እንዲያገኝ በሚያስችል መልኩ በብዛት የተቀረጹ ፖሊሲዎችና የወጡ ህጎች አሉ፡፡ እነዚህ ፖሊሲዎችና ሕጎች በአማራ ክልልም ተፈጻሚነት ያላቸው ሲሆን የጤና መብት በክልሉ ሕገ-መንግስታዊ ዋስትና ያገኘ መብት ነው፡፡
የእነዚህ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ሁሉ መኖር፣ የብሄራዊና ክልላዊ ሕጎች መበራከት ያለእድሜ ጋብቻን ማስቀረት አልቻለም፡፡ በመሆኑም ባለእድሜ ጋብቻ ምክንያት ሴት ህጻናት ከእርግዝና ጋር ተያይዘው ለሚከሰቱ ውስብስብ ችግሮች ይጋለጣሉ፤ በአካል ሳይደረጁና በአእምሮም ሳይበስሉ ያለእድሚያቸው ልጅ ይወልዳሉ፡፡ ይህም የራሳቸውንም ሆነ የልጆቻቸውን ህይወት አደጋ ላይ ይጥላል ብሎም ለሞት ይዳርጋቸዋል፡፡ ከዚህም ሌላ ፊስቱላን ጨምሮ በአባላዘር በሽታዎችና በኤችአይቪ ኤድስ ስለሚያዙ ጤናማ ህይወት የመምራት ተስፋቸው ይጨልማል፡፡
ሠ. ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት
በሀገራችን ከ140 በላይ የሚሆኑ ጐጂ ልማዳዊ ድርጊቶች መኖራቸውን በዚህ ጽሁፍ መጀመሪያ ላይ ተመልክተናል፡፡ በጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶቹ የሚጠቁት ደግሞ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸው የማይታበል ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ነው አብዛኞቹ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ሴቶችና ህጻናት ከማንኛውም ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት የመጠበቅ መብት አላቸው ሲሉ በግልጽ የሚደነግጉት፡፡
ከብዙዎቹ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶች ጥቂቶቹን ስናይ የህጻናት መብቶች ስምምነት በአንቀጽ 24 (3) ተዋዋይ አገሮች ለህጻናት ጤና ጠንቅ የሆኑ ባህላዊ ልምዶችን ለማስወገድ ተገቢና ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉ እርምጃዎችን ይወስዳሉ ሲል በአስገዳጅነት ደንግጓል፡፡ የአፍሪካ ህጻናትና ደህንነት ቻርተርም ጎጂ ከሆኑ ማህበራዊና ባህላዊ ልምዶች መጠበቅ በሚል ርእስ ስር በአንቀጽ 21 የቻርተሩ ተዋዋይ አገሮች በህጻናት ደህንነት፣ ክብር፣ ጤናማ እድገትና ጉልምስና ላይ ተጽእኖ የሚያሳድሩ ጎጂ ማህበራዊና ባህላዊ ልማዶችን ለማስወገድ ማናቸውንም ተገቢ እርምጃዎች መውሰድ እንዳለባቸው ይገልጻል፡፡
ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት ከፍ ሲል በተጠቀሱት ስምምነቶች ላይ ብቻ የተወሰነ አይደለም፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪና የአማራክልል ሕገ-መንግስቶችም ተመሳሳይ ድንጋጌ ይዘዋል፡፡ ይሄውም ሴቶች ከጎጂ ባህል ተጽዕኖ የመላቀቅ መብታቸውን መንግስት ማስከበር እንዳለበት በአንቀጽ 35 (4) በአስገዳጅ መልኩ ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ሆኖም ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብት የተለያዩ ሀይማኖታዊና ባህላዊ ሰበቦች እየተጠቀሱበት ከሚከበርበት ይልቅ የሚሻርበት ጊዜ ይበዛል፡፡ በተለይ ደግሞ ያለእድሜ ጋብቻ እንዲህ አይነት ምክንያቶችን በማቅረብ ከሚፈጸሙት ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ ከዚህም አኳያ ያለእድሜ ጋብቻ አለማቀፍ ስምምነቶቹንና ብሄራዊ ሕጎቹን ዋጋ እያሳጣ ለዘመናት ሊዘልቅ ችሏል፡፡
ያለ እድሜ ጋብቻ መፈጸም የሚያስከትለው የህግ ተጠያቂነት
ያለ እድሜ ጋብቻ ዘመናትን ያስቆጠረ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት መሆኑ አስረጅ አያሻውም፡፡ ተፈጽሞም ሲገኝ ሁለት አይነት የሕግ ኃላፊነቶችን ያስከትላል፡፡ የመጀመሪያው የፍትሓብሄር ሲሆን ሌላኛው የወንጀል ተጠያቂነት ነው፡፡
የፍትሓብሄር ተጠያቂነቱን የሚያስከትሉት የኢ.ፌ.ዴ.ሪና የአማራ ክልል የቤተሰብ ሕጎች ናቸው፡፡ የወንጀል ኃላፊነቱ ደግሞ በአገር አቀፍ ደረጃ ተፈጻሚነት ባለውና በ1997 ዓ.ም ተሻሽሎ በወጣው የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የወንጀል ሕግ በግልጽ ተመልክቷል፡፡
የቤተሰብ ሕጎቹ በአንቀጽ 17 እና 28 እንደቅደምተከተላቸው ጋብቻ ለመፈጸም አስፈላጊ የሆነ ሁኔታ አልተሟላም በማለት ሊፈጸም የታሰበ ጋብቻ እንዳይፈጸም ተቃውሞ ማቅረብ እንደሚቻል ሲደነግጉ በአንቀጽ 18 እና 29 ደግሞ ጋብቻ እንዳይፈጸም መቃወም የሚችሉ ወገኖችን ለይተው አስቀምጠዋል፡፡ በዚህም መሰረት በእድሜ ምክንያት ሲሆን ወላጆች፣ አቃቤ ህግ ወይም ሌላ ማንኛውም ያገባኛል የሚል ሰው መቃወሚያውን ለጋብቻ አስፈጻሚው አካል በማቅረብ ያለእድሜ ጋብቻው እንዳይፈጸም ማድረግ ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ተቃውሞ ሳይቀርብበት የተፈጸመ ያለእድሜ ጋብቻም ቢሆን የሚጸና አይደለም፡፡ ይህም በተጠቃሾቹ የቤተሰብ ሕጎች አንቀጽ 31 እና 42 በማያሻማ ሁኔታ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም እድሜአቸው ከአሥራ ስምንት አመት በታች በሆኑ ሰዎች መካከል የተፈጸመ ጋብቻ በማንኛውም ሰው ወይም በአቃቤ ሕግ ለወረዳ ፍ/ቤት በሚቀርብ ጥያቄ እንዲፈርስ መደረጉ አይቀሬ ነው፡፡
ያለእድሜ ጋብቻ ላይ የሚወሰደው እርምጃ ጋብቻው እንዲፈርስ በማድረግ ብቻ አይቆምም፡፡ ይልቁንም ከጋብቻው መፍረስ በኋላ የወንጀል ተጠያቂነቱ ይከተላል፡፡ ይሄውም በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 647 ስር በተደነገገው አግባብ በሕግ የተከለከለ ጋብቻን ያስፈጸመ፣ የፈጸመና ለዚህ ዓይነቱ ጋብቻ ምስክር የሆነ ሰው ከሦስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል፡፡
በተለይ ደግሞ የወንጀል ሕጉ በአንቀጽ 648 ስለ ያለእድሜ ጋብቻ ወንጀልነት ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም አግባብ ባለው የቤተሰብ ሕግ ከተፈቀደው ውጭ ማንም ሰው አስቦ ዕድሜዋ አስራ ሶስት ዓመት ወይም ከዚያ በላይ የሆነችን ልጅ ካገባ ከሶስት ዓመት በማይበልጥ እስራት፤ ወይም ዕድሜዋ ከአስራ ሶስት ዓመት በታች የሆነችን ልጅ ካገባ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ጽኑ እስራት ይቀጣል፡፡ ይሁንና ጋብቻው የፍትሓብሄር ክስ ቀርቦበት አስቀድሞ ካልፈረሰ በቀር ከፍ ሲል በተጠቀሱት አንቀጾች መሰረት የወንጀል ክስ ሊቀርብ አይችልም፡፡
እንደማጠቃለያና የመፍትሄ ሀሳብ
ያለእድሜ ጋብቻ ጎጂነት፣ አጥፊነትና አስከፊነት በድፍን አለም ይታወቃል፡፡ ስለዚህን በሁሉም አለማቀፋዊ፣ አህጉራዊና አገራዊ ሕጎች መወገዙ ቢያንስበት እንጂ አይበዛበትም፡፡ ሆኖም ግን ውግዘቱ ጎልብቶ ያለእድሜ ጋብቻን ማስቆሙ ይቅርና መቀነስ አልቻለም፡፡
በዚህም ያለእድሜ ጋብቻ ገፈት ቀማሾቹ ብዙን ጊዜ ሴት ህጻናት ሲሆኑ ወንዶች ልጆችም አልፎ አልፎ በድርጊቱ ሲጠቁ ይስተዋላል፡፡ ያለእድሜ ጋብቻን ለመቀነስ ብሎም ለማስቀረት በሚደረገው ጥረት የአንበሳውን ድርሻ መያዝ ያለበት ህብረተሰቡ ነው፡፡ ሆኖም ያለእድሜ ጋብቻውን በመፈጸም አለያም በማስፈጸም የራሱን እጅ ስለሚያስገባ ድርጊቱ ለዘመናት ሊዘልቅ ችሏል፡፡
ስለሆነም ይህን ስር የሰደደ ጎጂ ልማዳዊ ድርጊት ቢቻል ለማስወገድ ካልሆነም ለመቀነስ መንግስትም ሆነ መላው ህብረተሰብ ያላሰለሰ ርብርብና ትብብር ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡ እንደዚሁም የባህልና የሀይማኖት አባቶች ያለእድሜ ጋብቻን ጎጂነት ተረድተው ለተከታዮቻቸው ማስተማርና መስበክ ይኖርባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል ሕጋዊ ጋብቻ ለመፈፀም ወንዶችና ሴቶች ዕድሜያቸው 18 ዓመት መድረስ እንዳለበት የሚደነግጉት ህጎች መሬት ላይ ወርደው ሊፈጸሙ ይገባል፡፡ ከዚህም ባሻገር ያለእድሜ ጋብቻ በብዛት በሚፈጸምበት በገጠር አካባቢ የሚኖሩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለነዚህ ህጎች በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
በተለይ የአማራ ክልል በሀገር ደረጃ ቀዳሚ ስፍራ የያዘበትን ያለእድሜ ጋብቻ ለማስቆም የማያዳግም እርምጃ መውሰድ አለበት፡፡ ይህንንም ለማሳካት በክልሉ ባለዕድሜ ጋብቻ ዙሪያ የሚሰሩ የፍትህ አካላት፣ የህክምና ተቋማት፣ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ውጤት አምጪ የተቀናጀ ሥራ ሊሰሩ ይገባቸዋል፡፡
When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.
Comments