Font size: +
3 minutes reading time (624 words)

የረዳት አብራሪው ኃይለመድህን አበራ የወንጀል ክስ ጉዳይ በየትኛው አገር ፍ/ቤት መታየት አለበት?

ፌቡራሪ 17/2014 እ.ኤ.አ. ዕለተ ሰኞ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነ በበረራ ቁጥር ET 702 የተመዘገበ ቦይንግ 767 የመንገደኞች ማመላለሻ አውሮፕላን ከአዲስ አበባ በሱዳን በኩል አድርጎ ወደ ጣሊያን ሲበር በረዳት አብራሪው ሃይለመድህን አበራ ተገድዶ ስዊዘርላንድ ጄኔቭ ማረፉን ተከትሎ የስዊዘርላንድ መንግስት ረዳት አብራሪውን ለኢትዮጵያ አሳልፎ እንደማይሰጥና በስዊዘርላንድ መንግስት የህግ ከለላ እንደሚደረግለት እንዲሁም ረዳት አብራሪው ያቀረበው የፖለቲካ ጥገኝነት ጥያቄም ከፍርድ ሂደቱ በኋላ ምላሽ እንደሚያገኝ ጉዳዩም በስዊስ ሃገር ፍ/ቤት የሚዳኝ መሆኑን መግለጹን ከተለያዩ ሚዲያዎች መገንዘብ ችለናል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የፌደራል አቃቤ ህግ የወንጀል ህግ 507(1)ን በመተላለፍ አውሮፕላንን ያላግባብ መያዝ ወይም ማገት ወንጀል እና የወንጀል ህግ አንቀጽ 508(1)ን በመተላለፍ አውሮፕላንን አስጊ ሁኔታ ላይ መጣል ወንጀል ፈጽመሟል በማለት በረዳት አብራሪው ኃይለመድህን አበራ ላይ ሁለት የወንጀል ክሶችን መስርቷል፡፡

ተከሳሹም በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጥሪ ቢደረግለትም ሊገኝ ባለመቻሉ (ለፎርማሊቲ እንጂ በጋዜጣ ጥሪ እንደማይመጣ ይታወቃል) ጉዳዩ በሌለበት መታየቱ ቀጥሎ የአቃቤ ህግ ምስክሮች ከተሰሙ በኋላ ፍ/ቤቱ በቀን 07/07/07 ዓ/ም በዋለው ችሎት በወንጀል ህግ አንቀጽ 507(1) ስር አውሮፕላንን ያላግባብ መያዝ ወንጀል ስር ጥፋተኛ ነው ብሎ ሲወስን በሁለተኛው ክስ ግን ነፃ ነው ብሎታል፡፡

እዚህ ላይ ሊነሳ የሚገባው ዋና ጥያቄ የስዊዘርላንድ መንግስት ረዳት አብራሪውን አሳልፌ አልሰጥም የፍርድ ሄደቱ በስዊዘርላንደስ ሃገር ይታያል ባለበት ሁኔታ የፌደራል ዓቃቤ ህግ በፌደራል ከፍተኛ ፍ/ቤት በረዳት አብራሪው ላይ የወንጀል ክስ ማቅረቡና ፍ/ቤቱም ጉዳዩን ተቀብሎ ማስተናገዱ ከወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጋችን እና ከወንጀል ህጋችን አኳያ ሲታይ አግባብ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ማንሳት እወዳለሁ፡፡

በኢትዮጵያ መርከብም ሆነ በኢትዮጵያ አውሮፕላን ላይ ከኢትዮጵያ ግዛት ውጪ የሚፈጸም ወንጀልን በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደ ተፈጸመ ይቆጠራል ተብሎ በወ/መ/ስ/ስ/ህጋችን አንቀጽ 104 ላይ ተደንግጓል፡፡ በኢትዮጵያ ግዛት የተፈጸመን ወንጀልን ለመዳኘት የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች የዳኝነት ስልጣን እንዳላቸው ቅቡል ነው፡፡ ከዚህም የተነሳ ተፈጸመ የተባለው ወንጀል ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሆነው በበረራ ቁጥር 706 ቦይንግ 767 ላይ በመፈጸሙ በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 104 መሠረት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ እንደተፈጸመ ስለሚቆጠር የኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ረዳት አብራሪው የፈጸመውን ድርጊት በተመለከተ የሚቀርቡለትን የወንጀል ክሶች ተቀብለው ማስተናገድ ይችላሉ በማለት በቀላሉ ድምዳሜ ላይ ልንደርስ እንችላለን፡፡

ይሁን እንጂ ተከሳሽ የሆነው ረዳት አብራሪ ሃይለመድህን ክሱ በሌለበት በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁጥር 161 መሠረት መታየቱ የቀጠለ በመሆኑና የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህጋችን 161(3) የተከሰሰው ግለሰብ የውጭ አገር መንግስት ጥገኛ እንደሆነና ጥገኛ ያደረገው መንግስት አሳልፎ ያልሰጠው እንደ ሆነ በወንጀለኛ መቅጫ ህጉ ቁጥር 12 መሠረት ተፈጻሚ እንደሚሆን የሚደነግግ በመሆኑ፡፡ ረዳት አብራሪው በስዊስ አየር ላይ እያንዣበበ የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁና አውሮፕላኑን ካሳረፈ በኋላ እጁን ለጄኔቭ ፖሊሶች መስጠቱን ተከትሎ የስዊዘርላንድ መንግስት አሳልፎ የማይሰጠው መሆኑን ካረጋገጠ በኢትዮጵያ መንግስት ሊወሰድ የሚገባው እርምጃ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ቁጥር 12 (በተሸሻለው የወንጀል ህግ አንቀጽ 12 መሠረት የኢትዮጵያ መንግስት ለስዊዘርላንድ መንግስት በስዊዘርላንድ አገር ጉዳዩ እንዲታይ መጠየቅ ነበረበት፡፡

የወንጀል ህግ አንቀጽ 12(1)

“የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ወንጀል አድርጎ ወደ ውጭ ሃገር በመሸሹ ምክንያት ሳይከሰስ ወይም ሳይቀጣ የቀረ እንደሆነና ከሸሸበትም አገር ተላልፎ ሊሰጥ ያልተቻለ እንደሆነ በዚያው አገር ጉዳዩ እንዲታይ የኢትዮጵያ መንግስት ሊጠይቅ ይችላል።” ይላል ድንጋጌው።

አንቀጽ 12(1) "ሊጠይቅ ይችላል" የሚለው ሃረግ አስገዳጅ ባይመስልም ወደዚህ አንቀጽ የመራው የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ ቁጥር 161(3) ግን ተከሳሹ ውጭ አገር ጥገኛ ሆኖ ተላልፎ ሊሰጥ ካልተቻ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 12 መሰረት ይፈጸማል ማለቱ ለዚህ ጉዳይ በልዩ ሁኔታ አንቀጽ 12ን አስገዳጅ ያደርገዋል ብየ አስባለሁ። ይህ እንዲህ ከሆነ-

ከላይ የተመለከተው ድንጋጌ የውጭ አገር ዜጋ በኢትዮጵያ ውስጥ ወንጀል አድርጎ ወደ ውጭ አገር ለሸሸ ተከሳሽ ስራ ላይ የሚውል ሲሆን ይህንኑ ሁኔታ በተመሳሳይ መልኩ ኢትዮጵያዊ ዜግነት ያለው ሰውም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ወንጀል ፈጽሞ ወደ ውጭ አገር ለሸሸም በተመሳሳይ መልኩ ስራ ላይ ሊውል እንደሚችል የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ህግ አንቀጽ 161(3) ይመራናል፡፡

ስለዚህ የወንጀል ህግ አንቀጽ 12(1) መሠረት የኢትዮጵያ መንግስት ሊወስደው የሚገባ ህጋዊ እርምጃ ረዳት አብራሪ ኃይለመድህን አበራን የስዊዘርላንድ መንግስት አሳልፌ አልሰጥም ማለቱን ተከትሎ ጉዳዩ በስዊዘርላንድ አገር ፍርድ እንዲያገኝ መጠየቅ እንጂ በኢትዮጵያ ፍ/ቤቶች ክስ መስርቶ ውሳኔ መስጠቱ ተገቢነት የሌለውና የአገሪቱን የወንጀል ህግ እና የወንጀለኛ መቅጫ ስነ ስርዓት ድንጋጌዎች የጣሰ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ከዚህ አንጻር የፌደራል ከፍተኛው ፍ/ቤት ረዳት አብራሪው በወንጀል ህግ አንቀጽ 507(1)ን በመተላለፍ ንብረትነቱ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የሆነውን በበረራ ቁጥር 706 የተመዘገበውን ቦይንግ 767 አውሮፕላንን መያዝ ወይም ማገት ጥፋተኛ ነው በማለት መጋቢት 07/2007 ዓ/ም የሰጠው ውሳኔ ህጋዊነት አጠያያቂ ነው የሚል ድምዳሜ ላይ መድረስ እንችላለን፡፡

እስኪ በዚህ ዙሪያ ምን አስተያየት ይኖራችኋል?

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በ-ያለእድሜ ጋብቻ የሚጣሱ መብቶች
የቤት ኪራይ ግብር

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 07 November 2024