Font size: +
36 minutes reading time (7158 words)

አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ የኢትዮጵያ የሕግ ማዕቀፍ - የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓትና የወንጀል ሕጉን መነሻ በማድረግ

በ1995 የወጣው የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት ለተጠረጠሩና ለተከሰሱ ሰዎች በርካታ የሕግ ጥበቃዎችን ያደርጋል። እነዚህ ጥበቃዎች በዋናነት በሕግ ፊት በእኩል የመታየት፣ በሕግ አግባብ የመዳኘት፣ አላግባብ ቤታቸውና አካላቸው ከመበርበር የመጠበቅ፣ ከሕግ አግባብ ውጭ ያለመያዝ፣ በጠበቃ የመወከል፣ ንፁህ ሆኖ የመገመት፣ የፍርድ ሂደታቸው በግልፅ ችሎት ፈጣን በሆነ መልኩ እንዲካሄድ የማድረግ፣ የሚቀርብባቸውን ማስረጃ የመመልከትና መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ፣ ኢሰብአዊ ከሆነና ጭካኔ ከተሞላበት ቅጣት የመጠበቅ እና በአንድ ወንጀል ሁለት ጊዜ ያለመቀጣት መብት ናቸው። እነዚህ መብቶች በአብዛኛው እድሜያቸው ከ18 አመት በላይ በሆኑ ወይም ለአካለመጠን በደረሱ ወጣቶች ላይ የሚተገበሩ ሲሆን አካለመጠን ባልደረሱ ሰዎች ላይ ሁኔታው የተለየ ሆኖ ይገኛል። በወንጀል ለተጠረጠሩና ለተከሰሱ አዋቂ ሰዎች በሕግ የተቀመጡ ጥበቃዎች አካለመጠን ላልደረሱ ሰዎች ሲከለከሉ ወይም በዝምታ ሲታለፉ ይስተዋላል።

በ1960 የወጣው የፍትሐብሔር ሕግ ማንም ሰው ከውልደቱ አንስቶ በሕግ መብቶች የሚሰጡት ስለመሆኑና በህገ-መንግስቱ የተከበሩለትን ነፃነቶች በሙሉ የሚላበስ ስለመሆኑ የደነገገ ሲሆን በኢፌዴሪ ህገ-መንግስት የተመለከቱ ለተከሰሱና ለተጠረጠሩ ሰዎች የሚሰጡ የሕግ ጥበቃዎች አካለ መጠን ላልደረሱ ወጣቶችም በእኩልነት ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል። በመሆኑም አካለ መጠን ለደረሱ ተጠርጣሪዎች በሕግ የተሰጣቸው ጥበቃዎች ያለልዩነት አካለመጠን ላልደረሱ ወጣት ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾችም የሚሰሩ ይሆናል።

ባለፉት ከ50 እስከ 70 አመት ባሉት ጊዜያት ውስጥ በተለያዩ ሀገራት አካለመጠን ያልደረሱ የሕግ ተላላፊዎችን የሚዳኙ ልዩ ፍርድ ቤቶች ሲቋቋሙ ነበር። ልዩ ፍርድ ቤቶቹ ከሀገር ሀገር መጠነኛ የሆነ የመዋቅር ልዩነት ቢኖራቸውም አካለመጠን ያልደረሱ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን ጉዳይ በየሀገራቱ ሕግ መሰረት አይተው ይዳኛሉ። እነዚህ ፍርድ ቤቶች አካለመጠን ያልደረሱ የሕግ ተላላፊዎችን አካለመጠን ከደረሱ የሕግ ተላላፊዎች ጋር በጋራ አንድ ላይ በማድረግ በተመሳሳይ የወንጀል ሕግና የሥነ ሥርዓት ሕግ ከሚዳኙ መደበኛ ችሎቶች ይለያሉ። በዋናነትም በእነዚህ ፍርድ ቤቶች አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶችን ጉዳይ የሚያዩ ልዩ እውቀት ያላቸው ዳኞች መኖራቸው፣ መደበኛውን የሥነ ሥርዓት ሂደት የማይከተሉ ችሎቶች መሆናቸው፣ አካለመጠን የደረሱ ተከሳሾች በሁሉም የምርመራና የክርክር ሂደቶች አካለመጠን ካልደረሱ ተከሳሾች ፍፁም የማይገናኙበት መሆኑ፣ የፍርድ ሂደቱ የሕግ ተላላፊውን ተጋላጭነት ለመቀነስ ሲባል ለህዝብ ግልፅ የማይሆን መሆኑ ከመደበኛ ችሎቶች ልዩ ያደርጋቸዋል። በዋናነትም አላማቸው አጥፊነትን መቅጣት ሳይሆን ለጥፋቱ መነሻ ምክንያት የሆኑ ማህበራዊና ቤተሰባዊ ምክንያቶችን በማወቅ ወጣቱ በድጋሚ የሕግ መተላለፍ እንዳይፈፅም ማስተማር ላይ መሰረት ያደረጉ ችሎቶች ሲሆኑ በአንዳንድ ሀገራት የህፃናቱን ጉዳይ የሚያዩት የአስተዳደር አካላቶች ናቸው። ምንም እንኳን ማስተማርና ሕግ አክባሪ ዜጎች እንዲሆኑ ማድረግ ብዙ ሀገራት አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የሚመለከቱበት እይታ ቢሆንም አንዳንድ ጊዜ ግን መቅጣትና ማስተማርም ጥቅም ላይ ይውላል። በኢትዮጵያም አካለመጠን ያልደረሱ ሰዎች የወንጀል ሕጉን ጥሰው ሲገኙ የሕግ ተላላፊዎቹን ጉዳይ የሚያይ በሕግ የተቋቋመ ራሱን የቻለ ልዩ ፍርድ ቤት ባይኖርም አስተማሪና ተገቢ እርምጃዎችን በመውሰድ ቀጣይ ሕግ እንዳይተላለፉ የሚያደርግ የወንጀልና የሥነ ሥርዓት ሕግ ያለ ሲሆን አልፎ አልፎ በመቅጣት ማስተማርም በህጋችን ተደንግጎ ይገኛል።

የወንጀል ሀላፊነት የእድሜ ወሰን

አሁን ድረስ በአለምአቀፍ ደረጃ ወጥነት ለማምጣት አስቸጋሪ ከሆኑ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የሕግ ተላላፊዎች ጉዳይ ውስጥ አንዱ አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት የሕግ ተላላፊ ተብሎ የሚጀመርበት የእድሜ ወሰን ነው። በሌላ አባባል የህፃንነት እድሜ አብቅቶ የወንጀል ሀላፊነት በየትኛው እድሜ ላይ ይጀመር የሚለው አካራካሪ ጉዳይ ነው። ሀገራት በየህጎቻቸው የወጣት የሕግ ተላላፊዎችን የእድሜ ወሰን የሚወስኑ ሲሆን ለምሳሌ በአሜሪካ 50 የሚደርሱ ግዛቶች በዝቅተኛው የወጣት ሕግ ተላላፊ የእድሜ ወሰን ላይ በልዩነት እድሜን አስቀምጠው ይገኛሉ። ይህ በአሜሪካ ግዛቶች ያለው ልዩነት በአለም ላይ በሚገኙ ሀገራትም ይንፀባረቃል። በአለም አቀፉ የህፃናት መብት ስምምነት ላይ አስተያየት የሚሰጡ የባለሙያ ቡድኖች 12 አመት መነሻ የወንጀል ሀላፊነት መጀመሪያ እንዲሆን ቢመክሩም 25 በሚደርሱ የአለም ሀገራት የወንጀል ሀላፊነት መነሻ እድሜ 7 አመት ነው። አንዳንድ የሙስሊም እምነት ተከታይ የሚበዛባቸው ሀገራት ደግሞ መውለድና መራባት መቻልን የወንጀል ሀላፊነት መነሻ እድሜ አድርገውት ይገኛል። ምንም አይነት መነሻ የወንጀል ሀላፊነት እድሜን ያላስቀመጡ 20 ሀገራት በአለም የሚገኙ ሲሆን እንደ አርጀንቲና፣ ኬፕ ቨርዴ ያሉ ሀገራት ደግሞ 16 አመትን የወንጀል ሀላፊነት መነሻ እድሜ አድርገውት ይገኛል።

የወንጀል ሀላፊነት መጀመሪያ እድሜን ለመወሰን ሀገራት ከፓለቲካዊ ውሳኔ ባለፈ በርካታ ነገሮችን ከግምት ያስገባሉ። ከእነዚህም ውስጥ አንዱ የአእምሮ እድገት ሲሆን የአእምሮ እድገት ከአካላዊ እድገት ጋር የተያያዘ መሆኑ ይነገራል። ለሰው ልጆች አካላዊ እድገት ፈጣን መሆንና መዘግየት የየሀገራቱ እድገትና ብልፅግና የራሱ የሆነ ሚና አለው። ባደጉ ሀገራት የሚገኙ ህፃናት በተሻለ ኢኮኖሚ ውስጥ የሚገኙ በመሆኑ ፈጣን የሆነ አካላዊ እድገትን ያሳያሉ። በዚህም የአእምሮ እድገታቸው ፈጣን ስለሚሆን የወንጀል ሀላፊነት መነሻ እድሜ ዝቅ ብሎ ይጀምራል። ባላደጉ ሀገራት ደግሞ ይህ በተቃራኒው ስለሚሆን የወንጀል ሀላፊነት መጀመሪያ እድሜ ከፍ ይላል።

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች የወንጀል ሕግ በመጣስ ስለሚመጣባቸው ሀላፊነት ከማውራታችን በፊት በወንጀል ሕግ ተጠያቂነት ያለበት በየትኛው እድሜ ላይ ያለ ሰው ነው የሚለውን ማየት ይገባል። በወንጀል ሕጉ አራት አይነት የእድሜ ክፍል ያለ ሲሆን የመጀመሪያው የእድሜ ክፍል ከውልደት እስከ 8 አመት መጨረሻ ጊዜ ያለው እድሜ ሲሆን ሁለተኛው ከ9 አመት እስከ 14 አመት መጨረሻ ያለውን የእድሜ ክፍል ይመለከታል። ሶስተኛው የእድሜ ክፍል ከ 15 አመት እስከ 17 አመት መጨረሻ ያለውን የእድሜ ክፍል የሚመለከት ሲሆን በስተመጨረሻም አራተኛው የእድሜ ክፍል ከ 18 አመት በላይ ያሉ ሰዎችን የሚመለከት ነው።

በመጀመሪያው የእድሜ ክፍል ውስጥ የሚገኙ እድሜያቸው እስከ 8 አመት መጨረሻ ድረስ ያሉና ዘጠኝ አመት ያልሞላቸው ህፃናት በወንጀል ሕጉ ወንጀል ሆነው የተደነገጉ ድንጋጌዎችን ቢጥሱ የወንጀል ሀላፊነት የማይኖርባቸው ሲሆን የወንጀል ሕጉም ተፈፃሚ አይሆንባቸውም። ይህ ማለት ግን በህፃናት አማካኝነት በተፈፀመ ወንጀል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ፍትህ አያገኙም ማለት አይደለም። ህፃናቱን በማሳደግና በመንከባከብ ሀላፊነት ያለባቸው ሰዎች በህፃናቱ ድርጊት በተጎጂዎች ላይ ለሚደርስ ጉዳት የፍትሐብሔራዊና የወንጀል ሀላፊነት ይኖርባቸዋል። በአብዛኛው በህፃንነት እድሜ የወንጀል ሕግ ድንጋጌዎችን የሚጥሱ ልጆች በአስተዳደግ ቸልተኝነት፣ ቤተሰብ ተገቢውን የአስተዳደግ ቁጥጥር ባለማድረጉ የተነሳ ወይም በቤት ውስጥ በሚኖር ተፅእኖ ምክንያት ወደ ወንጀል ድርጊት የሚገቡ ናቸው። ለዚህም ሀላፊነት መውሰድ የሚኖርበት ልጁን በማሳደግና በማስተዳደር ረገድ ሀላፊነት ያለበት ቤተሰብ ይሆናል። የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀፅ 317፣ 2124-25 በህፃናት ድርጊት የተነሳ ለሚመጣ ጉዳት ቤተሰብ፣ አሳዳጊ ወይም የቅርብ ዘመድ አዝማድ ጉዳት የደረበትን ሰው የመካስ ሀላፊነት እንዳለበት ደንግጎ ይገኛል። አሳዳጊ ቤተሰቦች በህፃኑ አስተዳደግ ጉዳይ ከፍ ያለ ቸልተኝነትን የሚያሳዩ ሲሆን ከሞግዚትና ከአስተዳዳሪነት ስልጣናቸው በዐቃቤ ሕግ አመልካችነት በፍርድ ቤት ውሳኔ ሊነሱ ይችላሉ። አሳዳጊ ወይም ወላጅ ወይም የአሳዳጊነት ስልጣን ያለው ሰው የልጅ ማሳደግ ግዴታውን በአግባቡ ካልተወጣ፣ ለህፃኑ መስጠት የሚገባውን የቀለብ መስጠት ግዴታውን ካልፈፀመ በወንጀል ተጠያቂ ይሆናል።

በወንጀል ሕጉ ከተመለከቱ የእድሜ ክፍፍሎች ውስጥ ሁለተኛው የእድሜ ክፍል እድሜያቸው 9 አመት የሞላቸውና 14 አመትን የጨርሱ የሕግ ተላላፊዎችን የሚመለከት ሲሆን እነዚህን የሕግ ተላላፊዎች ሕጉ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ይላቸዋል። እነዚህ ወጣት የሕግ ተላላፊዎች በወንጀል ሕጉ የተመለከቱ የወንጀል ተግባራትን ፈፅመው ሲገኙና መፈፀማቸውም በበቂና አሳማኝ ማስረጃ ሲረጋገጥ የሚወሰድባቸው እርምጃ አዋቂ ሰዎች ላይ ከሚወሰደው የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃ አይነት ይለያል። ጥፋተኝነቱ በተረጋገጠበት ወጣት የሕግ ተላላፊ ላይ የሚወሰዱ ልዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ቅጣቶች በወንጀል ሕጉ ከአንቀፅ 157- 168 ተደንግገው የሚገኙ ሲሆን እነዚህ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ቅጣቶች በወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ተፈፃሚ የሚሆኑ ናቸው። በአዋቂ ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ መደበኛ ቅጣቶች ለወጣት ወንጀል አድራጊዎች ተፈፃሚነት አይኖራቸውም። አንድ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይም ቢሆን ልዩ የሆኑ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ቅጣቶች በሚወሰዱበት ጊዜ አስቀድሞ ወጣት ወንጀል አድራጊው በወንጀል ሕጉ አንቀፅ 23 መሰረት የወንጀል ተግባር፣ በአጥፊ የሀሳብ ክፍል ላይ ሆኖ የፈፀመ ስለመሆኑና ድርጊቱም በሕጉ የተመለከተውን ጎጂ ውጤት ያመጣ ስለመሆኑ በበቂና አሳማኝ ማስረጃ ሊረጋገጥ ይገባዋል። ይህ ሳይሆን በፊት በቀጥታ ልዩ የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣትን በወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ተፈፃሚ ሊደረግ አይችልም። በወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ ላይ ስለሚጣል ልዩ የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣት እንዲሁም ስነ-ስርአታዊ ጉዳዮች ከዚህ በኋላ ባለው ርዕስ በሰፊው ይብራራል።

በወንጀል ህጋችን ላይ የተመለከተው ሶስተኛው የእድሜ ክፍል እድሜያቸው 15 አመት የሞላቸው ሆነው እስከ 17 አመት መጨረሻ ያሉ ወጣቶችን የሚመለከት ነው። በዚህ የእድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ የወንጀል ሕጉ መደበኛ ድንጋጌ የሚፈፀምባቸው ሲሆን በሕጉም የሚታዩት እድሜያቸው ከ 18 አመት በላይ እንደሆኑ አዋቂ ወንጀል አድራጊዎች ነው። ነገር ግን ሕጉ የእድሜያቸውን ለጋነት ከግምት በማስገባት ሕግ ተላላፊዎቹ ጥፋተኛ ሲባሉ እድሜያቸውን መሰረት በማድረግ ቅጣትን ማቅለል እንደሚገባ፣ የነገሩ ሁኔታ አስፈላጊ መስሎ ከታየም አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የሕግ ተላላፊዎች ላይ የሚወሰደውን ልዩ እርምጃና ቅጣት ፍርድ ቤቶች እንዲመርጡ ስልጣን የሰጣቸው ሲሆን በዚህ የእድሜ ክፍል ላይ በሚገኙ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ የሞት ቅጣት መቅጣትና መፈፀም አይቻልም።

የመጨረሻው የእድሜ ወሰን እድሜያቸው ከ 18 አመት በላይ የሆኑ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን የሚመለከት ሲሆን በእነዚህ አዋቂ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ መደበኛው የወንጀልና የሥነ ሥርዓት ህጎች ተፈፃሚ ይሆናሉ።

አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ የሚወሰድ ልዩ የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣት

በአብዛኛው ለአካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ለሚፈፅሙት የሕግ መጣስ ድርጊት ምክንያቱ በህፃንነት የእድሜ ጊዜ በተገቢው መልኩ ስርአት ይዘው ባለማደጋቸው፣ የወላጅና የአሳዳጊ ፍቅርና እንክብካቤ በማጣት ተገልለው በማደጋቸው ወይም በአሳዳጊዎቻቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተነሳ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን መጠለያ ፣ትምህርትና ምግብ ባለማግኘታቸው የተነሳ በሚፈጠርባቸው ተፈጥሯዊ ጭንቀት ነው። በዚህ ሁኔታ ውስጥ በማለፋቸው የተነሳ ወንጀል የፈፀሙ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች ላይ ምን አይነት የማስተማሪያና የማስተካከያ መንገድ መከተል ይገባል የሚለው አሁን ድረስ በሕግ ባለሙያዎችና በፓሊሲ አውጭዎች ዘንድ ፅንፍ ይዞ የሚያከራክር ጉዳይ ነው። በአንድ ወገን ወንጀል እንዲፈፅሙ መነሻ ምክንያት የሆነውን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ፓለቲካዊና አከባቢያዊ ሁኔታ በመለየት በድጋሚ ወደ ጥፋት እንዳይገቡ የሚያድርግ አስተማሪ እርምጃ መውሰድ ይገባል የሚል መንግስትን ለሁሉም አባትና አራቂ አድርጎ የሚያይ እሳቤ ያለ ሲሆን በሌላ በኩል አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ሕግ የጣሱት መርጠውና ፈልገው በምርጫቸው በመሆኑ ላጠፉት ጥፋት የተለየ ልዩነት መውሰድ ሳያስፈልግ በመደበኛው ስርአት አግባብ መቅጣትና መጠየቅ ይገባል የሚል እሳቤ አለ።

በአለም አቀፍ ደረጃ አካለመጠን ባልደረሱ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ምን ያህል ወንጀል ይሰራል የሚለውን በትክክል ለማወቅ የመረጃ አያያዝ ልዩነት መኖር፣ የወንጀል ሕግ በየሀገራቱ ልዩነት መኖሩ፣ የየሀገራቱ ወጣት የሕግ ተላላፊ ማነው የሚለው ላይ የእድሜ ወሰን አከላለል ልዩነት መኖሩ ከባድ ቢያደርገውም የወጣቶች የሕግ መተላለፍ በከፍተኛ መጠን እያደገ የመጣ አለምአቀፋዊ ችግር መሆኑ ግን የማይካድ ነው። በ 2011 ዓ.ም በዩናይትድ ኔሽን አማካኝነት በወጣ ሪፓርት መሰረት በአሁን ሰአት ከ 1 ሚሊየን በላይ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች በየሀገራቱ ያሉ ህጎችን በመጣስ በቁጥጥር ስር ውለው እንደሚገኙ የሚያመላክት ሲሆን በአንዳንድ ሀገራት አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች በሕግ ስርአት መሰረት በቁጥጥር ስር ውለው የሚገኙ ሲሆን ብዙዎቹ ግን ፍትሐዊ የሆነ ስርአትን ባልተከተለ መንገድ በቁጥጥር ስር ውለው የሚገኙ ናቸው። በሪፖርቱም በሀይል የሚፈፀሙ አነስተኛ ወንጀሎች በአለምአቀፍ ደረጃ በብዛት አካለመጠን ባልደረሱ ወጣቶች የሚፈፀሙ ወንጀሎች ሲሆኑ ብዙውን ጊዜም ወንጀሎቹ በብዛት በቡድን በመሆን ወይም ከአንድ ቡድን ጋር ለመቀላቀል በሚል እንደሚፈፀሙ፣ ድህነትና ስራአጥነት፣ እኩል እድል ያለማግኘት፣ የመድሎ መኖር፣ በአካባቢው የእፅና የመሳሪያ ዝውውር መንሰራፋትና የትምህርት እድል አናሳ መሆን ለወጣቶቹ በወንጀል ድርጊት ተሰማርቶ መገኘት እንደዋነኛ ምክንያት ተጠቃሽ እንደሚሆኑ ተገልጿል። በተጨማሪም ወንጀሎቹ በስፋት በከተሞች አከባቢ እና ከሴቶች ይልቅ በወንዶች በብዛት እንደሚፈፀሙና ወጣቶቹን መልሶ ለማረቅ ማህበረሰባዊ ቅጣቶችና የቤተሰብ ክትትል እጅግ ጠቀሜታ ያላቸው ስለመሆኑ ተገልጿል።

አስገዳጅ የሆኑ የወጣት የሕግ ተላላፊዎችን ጉዳይ የሚመለከቱ ስምምነቶችና የአንዳንድ ሀገራት የሕግ ማዕቀፎች ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን ማስተማርንና በድጋሚ ወንጀል በማይፈፅሙበት አእምሮአዊ ሁኔታ ውስጥ በማድረግ (Rehabilitation and integration) ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀልን ቅድሚያ ይሰጣሉ። በዚህ ስርአት መሰረት የወጣት የሕግ ተላላፊዎችን የፍርድ ሂደት ከመደበኛ ስርአት ውጭ ራሱን በቻለ ልዩ ሕግና ስርአት መምራት፣ በእስርና በገንዘብ መቅጣትን እንዳይኖር ማድረግ ፣የሚኖር ከሆነ ደግሞ የመጨረሻ የቅጣት አማራጭ አድርጎ መጠቀም፣ በወጣት የሕግ ተላላፊዎች ላይ የሞት ቅጣትን ተግባራዊ አለማድረግ ለወጣት ሕግ ተላላፊዎች ከሚሰጡ የተለዩ ጥበቃዎች ውስጥ ናቸው። መንግስት የወንጀል ሕግን ተላልፈው የተገኙ ወጣቶች ወንጀል ለመፈፀም መነሻ ምክንያት የሆናቸውን ማህበራዊና ሌሎች የህይወት ምስቅልቅሎች በማጥናት ወደ መልካም ዜጋነት የመመለስ አባታዊ የሚመስል ሀላፊነት አለበት። ወጣቱን በሰራው ድርጊት ከመውቀስና ከመቅጣት አባዜ በመውጣት ወደ ጥፋት ለመግባት መንስኤ የሆኑ ችግሮቹን በመፍታት በቀጣይ ወደ ተመሳሳይ የወንጀል ሕግ መተላለፍ እንዳይገባ ጥረት ሊደረግ ይገባል። አንዳንድ ጊዜ በዚህ ሂደት ውስጥ ማህበረሰቡ፣ ተበዳይ፣ አጥፊውና ቤተሰቦች ተሳታፊ እንዲሆኑ ማድረግ የሚገባ ሲሆን በዚህ ስርአት ውስጥ የሚገኝ ፓሊስ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ ወንጀል ፈፅሞ ሲያገኝ ወንጀሉ ቀላል ከሆነና ለመጀመሪያ ጊዜ ከተፈፀመ በተግሳፅ ወጣቱ ፓሊስ ጣቢያ ሳይሄድ እንዲለቀው የማድረግ ምርጫ የሚሰጥ ሲሆን ወንጀሉ ከባድ ከሆነና ወይም ቀላል ወንጀል ሆኖ በተደጋጋሚ ከተፈፀመ የወጣቶችን ጉዳይ ብቻ ወደሚያይ ፓሊስ ጣቢያ ይወስደዋል። በፓሊስ ጣቢያው የሚገኙ መርማሪዎችና ሰራተኞች ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን ለመመርመርና ስላጠፉት ድርጊት ለማወቅ የሚያስችል ልዩ እውቀት ያላቸው መሆን ይገባቸዋል። በፍርድ ቤት ትዕዛዝ በምርመራ ክፍል መደበኛ ምርመራ ከመደረጉ በፊት በሌሎች አማራጮች ለምሳሌ ወጣቱ ይቅርታ እንዲጠይቅ በማድረግ፣ ማህበረሰባዊ ግልጋሎት በማሰጠት ወይም ቤተሰብ፣ ተጎጂና ወጣቱ በሚሳተፉበት የሽምግልና ሂደት የወጣቱ ድርጊት ወደ ሙሉ ስርአትና ክስ እንዳይገባ በማድረግ በፓሊስ ጣቢያ ደረጃ የሚፈታበት አማራጭ የችግር መፍቻ መንገድን መከተል ከግምት ይገባል። በወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ፍርድ ቤት የሚታዩ ጉዳዮች በቁጥር ውስን የሆኑ፣ በሌሎች መንገዶች መፈታት ያልተቻሉ፣ ያስከተሉት አሉታዊ የህዝብ ጉዳት ከፍተኛ የሆኑት ብቻ ናቸው። የወጣት ወንጀል አድራጊዎችን ጉዳይ የሚመለከቱ ፍርድ ቤቶች የወጣቱን ጤናማ እድገት ለመጠበቅና መልሶ ከህብረተሰቡ ጋር በቀላሉ ለመቀላቀል እንዲያስችል በሚል የፍርድ ሂደቶቹን በዝግ ችሎት የሚያስችሉ ሲሆን በወጣቱ ላይ ምስክር ሆነው የሚቀርቡ ምስክሮችንም መስቀለኛ ጥያቄ መጠየቅ አይቻልም። ከዚህም ባለፈ አብዛኛውን ለምስክሮች የሚነሱ ጥያቄዎች በዳኞች አማካኝነት የሚጠየቁ ሲሆኑ እውነትን በማውጣት ሂደቱ የዐቃቤ ሕግና የወጣቱ ጠበቆች ተሳትፎ እጅግ ያነሰ እንዲሆን ይደረጋል። አንድ ወጣት ሕግ ተላላፊ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ አብዛኛው የሚወሰዱበት እርምጃዎች በትምህርቱ እንዲጎለብትና ያልተሟሉለት ኢኮኖሚያዊ ችግሮቹ እንዲቀረፉ የሚያደርጉ እንዲሁም ከክፍ አድራጊዎች ጋር እንዳይቀላቀል በመከላከል ሀላፊነት የሚሰማው ዜጋ እንዲሆን የሚያስችሉ እርምጃዎች ናቸው። ከእነዚህ እርምጃዎች ውስጥ ወጣቱ ማህበራሰባዊ አገልግሎት እንዲሰጥ በማድረግ የፀባዩን መሻሻል መከታተልም ይገኝበታል። ነገር ግን ወጣቱ ለህብረተሰቡ ስጋት ከሆነና በቀደሙት የማስተካከያ እርምጃዎች መሻሻል ካለሳየ ነፃነትን የሚያሳጡ ቅጣቶች እንደመጨረሻ አማራጭ ይወሰዳሉ። ወጣቱ ነፃነቱን አጥቶ የሚቆይባቸው ማዕከላትም የማስተማርና መልካም ዜጋ ሆኖ እንዲወጣ የማድረግ አቋም ሊኖራቸው የሚገባ ሲሆን ወጣቱ ወደ አዋቂነት ሲሸጋገር ግን ከነዚህ ማዕከላት እንዲወጣና ከአዋቂዎች ጋር ተቀላቅሎ ቅጣቱን እንዲፈፀም ሊደረግ ይገባል። ይህ አይነት መንገድ በዋናነት ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን ወደ መልካም ዜጋነት የሚለውጥና በድጋሚ ሕግ ተላላፊዎች እንዳይሆኑ የሚያደርግ ስርአት ነው።

በሌላ በኩል ወጣት የሕግ ተላላፊዎች ወደ ሕግ መተላለፍ የሚገቡት አውቀውና ፈልገው፣ ሕግ መተላለፍ የሚያስገኘውን ጥቅምና ጉዳት አመዛዝነውና በምርጫቸው መርጠው ስለሆነ ሌሎች አዋቂ ሰዎችን ለመመርመርና ለመቅጣት የሚኬድበትን የሕግ ስርአት በመከተል ምንም አይነት ልዩ ስርአትና ሂደት ሳያስፈልግ ላጠፉት ጥፋት ተመጣጣኝ የሆነ ቅጣት መቀጣት ይኖርባቸዋል የሚል እሳቤም አለ። በዚህ እሳቤ መሰረት እነዚህ ወጣቶች ወንጀል ለመፈፀም ያነሳሳቸው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ከግምት ሳይገባ የፈፀሙት ድርጊት የወንጀል ሀላፊነት እንዲያመጣባቸው ይደረጋል። በመርህ ደረጃም ልዩ የሚባል ስነ-ስርአታዊ ሂደትና የተለየ የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣትን ለወጣት የሕግ ተላላፊዎች አይበጅም። ይህ አይነቱን እሳቤ በሚከተሉ በአንዳንድ ሀገራት ለአብነትም በቻይና በወጣትነት ወይም ከ 75 አመት በኋላ ወንጀል መፈፀም ቅጣትን ከሚያቀል በስተቀር ሌላ የሚያስገኘው የጎላ ጥቅም የለም። በቻይና የወጣቶችን የወንጀል ሕግ መተላለፍ የሚዳኝ ራሱን የቻለ የወጣት ወንጀል አድራጊዎች ፍርድ ቤት ቢኖርም የዚህ ፍርድ ቤት ተግባር መደበኛውን የቻይና ሀገር የወንጀል ሕግ ስራ ላይ ማዋል ነው።

ከነዚህ ስርአቶች ባለፈ ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን በማህበረሰብ አቀፍ የፍትህ ስርአት እንዲያልፉ ማድረግንም የሚከተሉ ሀገራት አሉ። ማህበረሰብ አቀፍ የፍትህ አገልግሎት በዋናነት ወጣት የሕግ ተላላፊዎች የወንጀል ሕግ ጥሰው ሲገኙ ተበዳዮችን፣ ወጣቱንና ማህበረሰቡን አንድ ላይ በማድረግ ፍትህ እንዲገኝ ማድረግን የተለመ ሲሆን በዚህ ሂደት ውስጥ በደል የደረሰበት ተበዳይ እንዲካስ፣ ጥፋት የፈፀመው ወጣትም እንዲገሰፅና ላጠፋው ጥፋት ሀላፊነት እንዲወስድ ይደረጋል። በሂደቱ ውስጥም ማህበረሰቡ በተለያየ መንገድ ተሳታፊ እንዲሆን የሚደረግ ሲሆን ስርአቱ መደበኛው የወንጀል ፍትህ ስርአት ያጠፉ ሰዎችን የተደጋጋሚ የተበዳይነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ፣ ላጠፉት ጥፋትም እንዳይፀፀቱና ለዳግም ወንጀል መስራት እንዲነሳሱ የሚገፋፋ፣ ተበዳዮችና ማህበረሰቡ በፍትህ አሰጣጥ ሂደቱ ከመጀመሪያው አንስቶ በተገቢው መጠን እንዳይሳተፉ የሚያገልና ለደረሰባቸው በደልም ተገቢውን ካሳ እንዳያገኙ የሚያደርግ፣ በብዙ መልኩ በችግሮች የተተበተበ ስለሆነ ወጣቶቹ በማህበረሰብ አቀፍ የፍትህ ስርአት እንዲያልፉ ማድረግ ከመደበኛው የወንጀል ፍትህ ስርአት የተሻለ አማራጭ መንገድ እንደሆነ አድርጎ ያስባል። ከዚሁ ሞዴል ጋር ተመሳሳይነት ያለው ሌላው እሳቤ የወጣት የሕግ ተላላፊዎች ላይ በመደበኛው የወንጀል ፍትህ ስርአት ውስጥ የሚሳተፉ አካላቶች የሚኖራቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆን ይገባዋል የሚለው እሳቤ ነው። በዚህ እሳቤ መሰረት ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን ፓሊስ በምርመራ ሂደት፣ ዐቃቤ ሕግም በመክሰስ ፣ፍርድ ቤትም አከራክሮ ውሳኔ በመስጠት ሂደት ውስጥ ሲያሳልፋቸው ሂደቱ በራሱ የወንጀለኛነት ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርግ በመሆኑ የወጣት የሕግ ተላላፊዎች ጉዳይ በሚታይበት ጊዜ የሁሉም አካላቶች ተሳትፎ ዝቅ ሊል ይገባል ይላል። ስለዚህ ማህበረሰብ አቀፍ የፍትህ አገልግሎት ማበጀት፣ በማቆያ ቦታዎች ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን እንዲቆዩ አለማድረግ፣ ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን ከአዋቂዎች ነጥሎ ጉዳያቸው እንዲታይ ማድረግ፣ በወንጀል ሕግ መሰረት ወንጀለኛ ናችሁ ማለትን ማስወገድ ይገባል የሚል ፅንሰ ሀሳብ ይንፀባረቅበታል።

አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰድ የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣት በኢትዮጵያ ሕግ

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ በወንጀል ጥፋተኛ የተባሉ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ወንጀል መስራታቸው በበቂ ሁኔታ ተመስክሮባቸው ጥፋተኛ የተባሉ እንደሆነ ፍርድ ቤቶች በአዋቂዎች ላይ የሚወስዱትን መደበኛውን ቅጣትና እርምጃ (ordinary penalites and measures) የሚወስዱባቸው አይሆንም:: ከዚህ ይልቅ በህጋችን ተደንግገው የሚገኙ ወጣቶቹን እንዲታረሙ ለማድረግ የሚያስችሉ በርካታ ልዩ የጥንቃቄ እርምጃዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ። ለመጀመሪያ ጊዜ አጥፊ በሆኑ ወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች መልካም ፍሬ ካላስገኙና ወጣቱ ለሁለተኛ ጊዜ የወንጀል ሕግ ጥሶ ከተገኘ ልዩ ቅጣት በወጣቱ ላይ ይጣላል። ለመጀመሪያ ጊዜ የወንጀል ሕግ ጥሶ ጥፋተኛ በተባለ ወጣት ወንጀል አድራጊ ላይ ልዩ ቅጣት የማይጣልበት ሲሆን ለሁለተኛ ጊዜም ቢሆን የወንጀል ሕግን መጣሱ በተረጋገጠበት ወጣት የሕግ ተላላፊ ላይ ልዩ ቅጣት የሚጣልበት የመጀመሪያው እርምጃ ፍሬ አለማፍራቱ በፍርድ ቤቱ ሲረጋገጥ ብቻ ነው።

በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች በዋናነት ወጣት ወንጀል አድራጊው አእምሮው ደካማ በመሆኑ፣ የአእምሮው እድገት የዘገየ ከሆነ፣ አእምሮው ከታመመ ፣የሚጥል በሽታ ካለበት፣ በአልኮል መጠጥ ሱሰኝነት የተጠመደ ወይም በናርኮቲክና ሳይኮትሮፒክ ወይም በሌሎች ምክንያቶች ህክምና የሚስፈልገው ከሆነ ህክምና ወደሚያገኝበት ተቋም መላክን፣ ወንጀል አድራጊው በበጎ አስተዳደግ ካለደገ ወይም በእንዝላልነት የተተወ ወይም ጠባዩ ወደ መጥፎ ስራ ያዘነበለ ከሆነ በጠባቂ ስር ሆኖ ቁጥጥር እየተደረገበት ትምህርት እዲያገኝ ማድረግን፣ የተፈፀመው ወንጀል ቀላል ከሆነና ወጣት ወንጀል አድራጊው ይህንኑ ተረድቶ ለመታረም ዝግጁ ከሆነ ተግሳፅና ወቀሳን፣ ጥፋቱ ከባድ ካልሆነና ለአካለመጠን ያልደረሰው ወንጀል አድራጊ በቀላሉ የሚታረም መስሎ ከታየ በትምህርት ቤቱና በመኖሪያ ቤቱ ብቻ ተወስኖ በእረፍት ጊዜው ለእድሜው የሚስማማ ስራ እንዲሰራ ማድረግን እንዲሁም የወጣት ወንጀል አድራጊው ፀባይ ወይም የቀድሞ ታሪኩ መጥፎነትን እንዲሁም የወንጀሉን ከባድነትና አፈፃፀሙን ከግምት በማስገባት ወደ ጠባይ ማረሚያ ተቋም መላክን ያካትታል። ወጣት ወንጀል አድራጊዎችን ወደ ህክምና ተቋም የመላክና ቁጥጥር በማድረግ ትምህርት መስጠትን የሚመለከቱ የጥንቃቄ እርምጃዎች አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ወንጀል አድራጊ ለአካለመጠን እስኪደርስ ወይም ከዚያ በፊት የህክምና ወይም የትምህርት ተቋሙ እርምጃው አላማውን አሳክቷል እስከሚል ድረስ የሚቀጥሉ ናቸው። ወደ ጠባይ ማረሚያ የመላክ የጥንቃቄ እርምጃ በመሰረቱ ከአንድ አመት እስከ አምስት አመት ለሚደርስ ጊዜ ሊሆን የሚችል ሲሆን ዳኞች ወጣቱ ጠባይ ማረሚያ ለምን ያህል ጊዜ እንደሚቆይ በግልፅ በፍርድ ውሳኔያቸው ላይ ማስፈር አለባቸው። ይህ ውሳኔ ወጣቱ በሕግ ከተወሰነለት ለአካለመጠን ከሚደርስበት ዘመን በላይ አያልፍም። ከዚህ በላይ የተመለከቱትን የጥንቃቅ እርምጃዎችን ፍርድ ቤቶች ለወጣት ወንጀል አድራጊው ጠቃሚ ሆኖ ሲያገኙት ወጣቱን የሚጠብቁና የሚያስተምሩ የተቋማት አስተዳደሮች የሚያቀርቡትን አስተያየት በመቀበል አስቀድሞ የተሰጠውን ትዕዛዝ መለወጥ ይችላሉ። በዚህም በጠባይ ማረሚያ እንዲቆይ ተብሎ የተሰጠ ትዕዛዝን ጊዜውን ማሳጠር ወይም ማርዘም ወይም በሌላ የጥንቃቄ እርምጃ መቀየር እንዲሁም ሌሎች ትዕዛዛትን መቀያየርን ጨምሮ እንዲቀሩና እንዲቆሙ ማድረግ ይቻላል። በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የጥንቃቄ እርምጃዎች የሚወሰዱት እድሜውን፣ ጠባዩን፣ የአእምሮና የሞራል እድገቱን፣እንዲሁም ቅጣቱ ወይም የጥንቃቄ እርምጃዎቹ በጥፋተኛው ላይ ሊያመጡ የሚችሉትን መልካም ለውጦች ከግምት በማስገባት ነው። ለዚህም ሲባል አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ የወጣቱን ህይወትና ባህሪ በተመለከተ የባለሙያ አስተያየት የሚጠየቅ ሲሆን ሁል ጊዜም እርምጃው ለወጣቱ አስተማሪ፣ ጠባቂና በቀጣይ በወንጀል ተግባር ውስጥ እንዳይገባ የሚያስተካክለው መሆኑ ከግምት ይገባል። በዚህም የኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ ከወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች አንፃር አስተምሮ የመመለስ (rehabilitative model) ስርአትን ተከትሏል ማለት ይቻላል።

በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎች ፍሬ ካላፈሩና ወጣት ወንጀል አድራጊው በድጋሚ በወንጀል ድርጊት ውስጥ ገብቶ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ ልዩ የቅጣት እርምጃዎች በወጣቱ ላይ እንዲወሰዱ ይደረጋል። በወጣቱ ላይ የሚወሰደው ልዩ ቅጣት በወንጀል ሕጉ ልዩ ክፍል ስለወንጀሎች በተደነገገው ድንጋጌ ላይ የተመለከቱትን ቅጣቶች መውሰድን አይመለከትም። ልዩ የሚባሉ ቅጣቶች በዋናነት የገንዘብና የእስር ቅጣትን ያካተቱ ናቸው። የመቀጮ ቅጣት ለአካለመጠን ያልደረሰው ወንጀል አድራጊ መቀጮ መክፈሉ ቅጣት ሆኖ የሚሰማው ፣የሚያስተምረውና ከጥፋቱ የሚመልሰው ከሆነና ይህንንም መቀጮ ራሱ ለመክፈል የሚችል ሲሆን የሚጣል የቅጣት አይነት ነው። ወጣቱ ወንጀል አድራጊ ከባድ የሆኑ 10 አመትና ከዚያ በላይ ወይም በሞት በሚያስቀጡ ወንጀሎች ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ ወጣቱ ላይ የእስር ቅጣት በመጣል ወደ ፀባይ ማረሚያ ተቋም ወይም ወደ መደበኛ እስር ቤት ሊላክ ይችላል። ወጣት ወንጀል አድራጊው ታስሮ ሊቆይበት የሚችልበት የእስራት ጊዜም ከአንድ አመት እስከ 10 አመት ሊዘልቅ ይችላል። በእስር ቤት ተይዞ የመቆየቱ ቅጣት የሚፈፀመው በቀላል እስራት ደንብ አፈፃፀም በመሆኑ የተነሳ በወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ የመብት መሻር ተጨማሪ ቅጣቶች በመርህ ደረጃ ተፈፃሚ አይሆንባቸውም።

በወጣት የሕግ ተላላፊዎች ላይ የሚወሰዱ የጥንቃቄ እርምጃዎችም ሆነ ቅጣት የታሰበውን የማስተማር አላማ እንዲያሳኩ ለማድረግ በመደበኛው ቅጣት ጊዜ ተከትለው የሚመጡ ውጤቶች እንዳይኖሩ ሆኗል። በወጣቶቹ ላይ የሚጣል ማንኛውም አይነት የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣት የተወሰደበት የፍርድና የክርክር ሂደት ችሎቱ ለህዘብ ግልፅ እንዳይሆን ይደረጋል፤ የወንጀል ታሪካቸው ለህዝብ እንዲገለፅ ካለመደረጉም ባለፈ በመሰየም መልካም ስም እንዲመለስ የማድረግ ሂደቱ ቀላል እንዲሆን ተደርጓል። የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 176(1) አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ፍርድ ቤት በቀረበ ጊዜ በሙሉ ነገሩ የሚሰማው በዝግ ችሎት ሲሆን ከምስክሮች፣ ልዩ አዋቂ፣ ከወላጆችና ከሞግዚት፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅት ወይም ፍርድ ቤቱ ሲያዝ ዐቃቤ ሕግ ከሚገኝ በስተቀር ሌላ ማንም ሊገኝ አይችልም። ለአካለመጠን ያልደረሰ ወንጀል አድራጊን በሚመለከት የሚሰጡ የፍርድ ውሳኔዎች ምንጊዜም በህዝብ መገኛኛ ዘዴዎች አይገለፁም።

የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 174 የቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃ በወንጀለኞች መዝገብ ላይ የሚመዘገበው ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የመንግስት የአስተዳደርና የፍርድ ባለስልጣኖች አስፈላጊውን መረጃ ለመስጠት እንዲያገለግል ብቻ ስለሆነ በማንኛውም ምክንያት የዚህን የመዝገብ ቅጂ ለነገሩ ባዕድ ለሆኑ ሰዎች መግልፅን በፍፁም ከልክሏል። አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት በወንጀል ተቀጥቶ የነበረ ስለመሆኑ ወጣቱን ለሚቀጥሩ ወይም የወጣቱን የኋላ ታሪክ ማወቅ ለሚፈልጉ የመንግስትም ሆነ የግል ድርጅቶች የሚገለፅ አይሆንም። አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት ወንጀል አድራጊ በወንጀል ጥፋተኛ በመባሉ የተነሳ የተወሰደበትን የጥንቃቄ እርምጃ እንዲሰረዝለት በ 2 አመት ጊዜ ውስጥ አቤቱታ ማቅረብ የሚችል ሲሆን የተወሰደበት ቅጣት እስር ከሆነ ግን አምስት አመት መጠበቅ ይኖርበታል። የጥንቃቄ እርምጃ ብቻ የተወሰደበት አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት የሕግ ተላላፊ ከመነሻውም በወንጀል ሕጉ እንደተቀጣ ተደርጎ አይቆጠርም። ከዚህ ድንጋጌ አንፃር የሕጉ ዋና አላማ ወጣት የሕግ ተላላፊዎችን አስተምሮ ወደ መልካም ዜጋ ለመመለስና ወንጀለኛ ናችሁ በሚል መድሎ እንዳይደርስባቸው ለማድረግ ነው። በወጣት ወንጀል አድራጊዎች ላይ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚወሰድ የጥንቃቄ እርምጃ ጥቅም ላይ ሊውልበት የሚችልበት ሁኔታ ወጣቱ በድጋሚ የወንጀል ሕግ ተላልፎ ሲገኝ መወሰድ ያለበት እርምጃ እስር ይሁን ወይስ አይሁን የሚለውን ለመወሰን ብቻ ነው።

አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ በምርመራና በክርክር ሂደት ተግባራዊ የሚደረግ ሥነ ሥርዓት

በወንጀል ሕጉ ላይ በወንጀልነት የተመለከቱ ተግባራትን የፈፀሙ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የሕግ ተላላፊዎች በቅጣት ረገድ የሚወሰድባቸው እርምጃ አዋቂ ከሆኑ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ከሚወሰደው የቅጣት አይነት በይዘትም ሆነ በአላማ የተለየ ነው።

የወንጀል ሕጉ በአግባቡ ተግባራዊ ሆኖ የህዝብና የሀገር ሰላም የማረጋገጥ አላማውን እንዲያሳከ ለማድረግ አተገባበሩን የሚመራ ስነ-ስርአታዊ ሕግ ሊኖር ያስፈልጋል። የወንጀል ተግባር ተፈፅሞ ሲገኝ ወንጀሉን ማን ፈፅመው? እንዴት ተፈፀመ? የሚሉና ሌሎች የምርመራ ተግባራት በመንግስት ባለስልጣናት ይከናወናል። የወንጀል ምርመራ የመጨረሻ ግቡ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን በሕግ ስርአት መሰረት እንዲጠየቁ በማድረግ የህዝብን ጥቅም ማስጠበቅ ቢሆንም በሂደቱ የተጠርጣሪዎችን በነፃነት የመንቀሳቀስና ሌሎች መብቶቻቸው አላግባብ ሊጣስ ይችላል። ወንጀልን በመከላከልና ተፈፅሞም ሲገኝ አጥፊዎችን በመጠየቅ የህዝብን ጥቅም የማስጠበቅ ተግባር የግለሰቦችን መብት ከሕግ ስርአት ውጭ ካለመጣስ ጋር ተጣጥሞ ሊተገበር ይገባዋል።

በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የሕግ ተላላፊዎች ወንጀል ፈፅመው ሲገኙ አቤቱታና ክስ እንዴት ይቀርብባቸዋል? እንዴት ይታሰራሉ? ምርመራው በምን አግባብ ይከናወናል? የክስ አቀራረብና እምነት ክህደት ቃል እንዴት ይሰጣሉ? የክርክር ፣ፍርድ፣ ቅጣትና የይግባኝ ስርአቱ ምን ይመስላል የሚለውን በተመለከተ በአዋቂ ተጠርጣሪዎች ላይ ተግባራዊ ከሚደረገው መደበኛ ሥነ ሥርዓት በተለየ መልኩ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከአንቀፅ 171 ጀምሮ በተደነገጉ 10 አንቀፆች ተሸፍኖ ይገኛል። ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎቹ ከ 9 አመታቸው ጀምሮ 15 አመት እስኪይዙ ባለው ጊዜ ውስጥ የወንጀል ሕጉን ጥሰው በሚገኙበት ጊዜ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ የተመለከተው ልዩ የሥነ ሥርዓት ሕግ የሚገዛቸው ይሆናል።

በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ወንጀል ፈፅሟል ተብሎ የሚጠረጠር ሰው መያዙ አስፈላጊ ከሆነ በፓሊስ መጥሪያ ወይም በፍርድ ቤት የማሰሪያ ትዕዛዝ ከተያዘ በኋላ በ 48 ሰአት ውስጥ በአቅራቢያው በሚገኝ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እንዲቀርብ ተደርጎ ለምርመራ በሚል ተጨማሪ ጊዜ ተጠይቆበት በእስር ይቆያል ወይም በዋስትና ይለቀቃል። አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት ወንጀል አድራጊን በተመለከተ ወንጀሉ በተፈፀመበት አከባቢ የሚገኝ መደበኛ የወንጀል የምርመራ ጉዳዮችን የሚመለከተው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ከወጣቱ ጋር የተያያዙ የምርመራ ሂደቶችን የሚከታተል ይሆናል። ፍርድ ቤቱ በወጣቱ ላይ የቀረበውን የክስ አቤቱታ ከመዘገበና ምርመራውን ከተከታተለ በኋላ የወጣቱን ጉዳይ የመመልከት የግዛት ስልጣን ከሌለው መዝገቡን ስልጣን ላለው መደበኛ የወንጀል ፍርድ ቤት ያስተላልፋል።

በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አዋቂ ወንጀል አድራጊዎች በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስቀጣ ወንጀል እጅ ከፍንጅ ሲፈፅሙ ተጠርጣሪዎችን በመያዝ የወንጀል ምርመራ ይጀመራል። እጅ ከፍንጅ ከሆኑ ወንጀሎች ውጭ ያሉ ሌሎች ወንጀሎች በአዋቂ ወንጀል አድራጊዎች ተፈፅመው ሲገኙ ፓሊስ በግል ተበዳዩ ወይም ከማንኛውም ሰው በሚደርሰው አቤቱታ ወይም ጥቆማ መነሻነት ምርመራ በማድረግ በወንጀሉ የሚጠረጠረውን ሰው በፓሊስ መጥሪያ ወይም በፍርድ ቤት ትዕዛዝ/ያለትዕዛዝ የሚይዘው ይሆናል። አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ሲሆንስ??። የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 172(1) ላይ እንደተመላከተው ‹‹ወጣት የወንጀል አድራጊ በወንጀል ተግባር ውስጥ ገብቶ በተገኘ ጊዜ ወላጁ ወይም ሞግዚቱ ፣ፓሊስ ወይም ዐቃቤ ሕግ አቅራቢያ ወደ ሚገኘው የወረዳ ግዛት ፍርድ ቤት ወዲያውኑ ይዞት ይቀርባል ይላል››። ይህ ድንጋጌ በርካታ ጥያቄዎች ይነሱበታል። ከነዚህ መሀከል በዚህ ድንጋጌ መሰረት ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊን ማሰር ይቻላል ወይ? ከታሰረስ ከመነሻው ፓሊስ ማስረጃ የመሰብሰብ ስልጣን አለው ወይ? የሚታሰረውስ በምን አግባብ ነው? መጥሪያ በመስጠት ወይስ የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ በማውጣት የሚሉት ይገኝበታል።

አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት የወንጀል አድራጊ በወንጀል ክስ አቅራቢነት የሚያስቀጣ የእጅ ከፍንጅ ወንጀል ከሰራ ወንጀሉ በተፈፀመበት ቦታ ላይ ያለ ፓሊስ ወይም ማንኛውም ሰው ወጣቱን ያለፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ የሚይዘው ሲሆን በዚህ ሁኔታ ፓሊስ አስቀድሞ ማስረጃ የሚሰበስብበት አግባብ አይኖርም። ተጠርጣሪው ከተያዘ በኋላ ወዲያውኑ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ ያለበት ሲሆን ፓሊስ ተጠርጣሪውን ከያዘ በኋላ ምንም አይነት ማስረጃ ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሊሰበስብ አይችልም። በወጣቱ ላይ የሚቀርብን አቤቱታም ሆነ ምስክርነት የመመዝገብ ሀላፊነት ያለበት ፍርድ ቤት ሲሆን ይህ በአዋቂ የወንጀል አድራጊዎች ላይ ከሚፈፀመው መደበኛ ስርአት የተለየ ነው። ወጣት የወንጀል አድራጊው የፈፀመው ወንጀል ከእጅ ከፍንጅ ውጭ የሆነ ወንጀል ከሆነ ፓሊስ ተጠርጣሪውን ከመያዙ በፊት ለመጠርጠር የሚያስችለውን ማስረጃ አስቀድሞ መሰብሰብ ይኖርበታል። ምንም አንኳን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 172 ወጣቱ እንዴት መያዝ አለበት የሚለውን ግልፅ ምላሽ ባይሰጠንም አዋቂ ወንጀል አድራጊዎች በሚያዙበት አግባብ በፓሊስ መጥሪያ አማካኝነት ወይም በፓሊስ መጥሪያ መያዝ ካልተቻለ በፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ወጣቱ ሊያዝ ይገባዋል። ፓሊስ ወጣቱን ከመያዙ በፊት ጠርጥሮ ለመያዝ የሚስችለውን አሳማኝ ማስረጃ መሰብሰብ ይኖርበታል። ። የሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 172 (1) በይዘቱ ሲታይ ወጣቱ ተጠርጣሪ ድንጋጌው ላይ በተጠቀሱት ሰዎች አማካኝነት ወዲያውኑ ወደ ፍርድ ቤት መቅረብ አለበት ከማለት ውጭ ስለመያዝ ያለው ምንም ነገር የለም። ነገር ግን ፓሊስም ሆነ ሌሎች ሰዎች ወጣቱን ወደ ፍርድ ቤት በማቅረብ ሂደት አካሉን ይዘው እንዳይንቀሳቀስ የሚያደርጉ በመሆኑ በውስጡ የእስር ፅንሰ ሀሳብ እንዳለ መረዳት ይቻላል። በመሆኑም በወጣቶች ላይ ብቻ ተግባራዊ በሚሆነው ልዩ የሥነ ሥርዓት ሕግ ወጣቱን በምን አግባብ መያዝ አለበት የሚለውን የሚገዛ ድንጋጌ ባይኖረውም አዋቂ ሰዎች ተጠርጣሪ ሲሆን በመደበኛው የሥነ ሥርዓት ሕግ በሚያዙበት አግባብ አካለመጠን ያልደረሰው ወጣትም መያዝ ይኖርበታል። ወጣቱን ተጠርጣሪ ፓሊስ በሚይዝበት ጊዜ በማህበረሰቡ ዘንድ የወጣቱን መልካም ስም ለመጠበቅና የመያዙን ሂደት ህዝብ እንዳያውቅ ለማድረግ ሲባል ከፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ ይልቅ በፓሊስ መጥሪያ በቁጥጥር ስር ለማድረግ ጥረት ቢደረግ መልካም ነው።

በፓሊስ ቁጥጥር ስር የሆነ ወጣት ወንጀል ፈፃሚ ከሌሎች አዋቂ ታሳሪዎች ጋር መቀላቀል የሌለበት ሲሆን ከእጅ ከፍንጅ ወንጀሎች ውጭ ባለ ሁኔታ ወጣት ወንጀል አድራጊው ወንጀል መፈፀሙን የሚያውቅ ማንኛውም ሰው ወይም ቤተሰብ ወይም ዐቃቤ ሕግ ወጣት ወንጀል አድራጊውን ከያዘው በኋላ ወዲያውኑ በአቅራቢያው ለሚገኝ የወረዳ ፍርድ ቤት ማቅረብ አለበት። በአዋቂዎች ላይ ተፈፃሚነት ባለው መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ ፓሊስ ተጠርጣሪውን በቁጥጥር ስር ካዋለው በኋላ አስፈላጊ የሚባሉ ማስረጃዎችን በራሱ የሚሰበስብ ሲሆን አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት ወንጀል አድራጊ ከሆነ ግን በወጣቱ ላይ የሚቀርብን አቤቱታና አቤቱታው ላይ የሚመሰክሩ ሰዎችን ፍርድ ቤት የሚመዘግብ ሲሆን በምርመራ መዝገቡ ላይ መከናወን ያለበትን የምርመራ ስራ ላይ ለፓሊስ መመሪያና ትዕዛዝ ይሰጣል። አካለመጠን ያልደረሰን ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ በማስተማር በቀጣይ ወንጀል እንዳይሰራ በማድረግ ወደ ማህበረሰቡ መቀላቀል የወንጀለኛ ሕግና የሥነ ሥርዓት ሕጉ ዋና አላማ በመሆኑ የተነሳ ወጣቱ የፈፀመው የወንጀል አይነት ምንም ያህል ከባድ ቢሆን ወጣቱ በፓሊስ ጣቢያ በሚገኙ ማረፊያ ቦታዎች እንዲቆዩ አይደረግም። የምርመራው ሂደት ወጣቱ በፍርድ ቤቱ ከቀረበ በኋላ የሚቀጥል ከሆነ ወይም መዝገቡ ወደ በላይ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚያስፈልገው ከሆነ አካለመጠን ያልደረሰውን ወጣት ወላጆቹ፣ሞግዚት ወይ ዘመድ እነርሱም ከሌሉ እራሱን ለቻለ ድርጅት እንዲሰጥ ተደርጎ በቀጣይ ቀጠሮዎች እዲያቀርቡት ይደረጋል። በሕጉ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች በማቆያ ቦታዎች እንዳይታሰሩ ለማድረግ ጥረት ቢደረግም ወጣቱ ወይም ወጣቱን ለማቅረብ ሀላፊነት የተሰጣቸው ሰዎች በቀጣይ እንዲያቀርቡት የሚያስደርግ አስገዳጅ የዋስትና ስርአት ግዴታ አልተቀመጠም። በመደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አዋቂው ሰው በወንጀል ተጠርጥሮ ከተያዘ በኋላ በራስ ዋስትና ወይም በቂ የሰውና የገንዘብ ዋስ እንዲያሲዝ ተደርጎ እንዲለቀቅ የሚደረግ ሲሆን በቀጣይ በሚኖሩ የችሎት ቀጠሮዎች በፍርድ ቤት የማይገኝ ከሆነ ዋስትና የገቡ ሰዎች ያሲያዙት ዋስትናቸው ለመንግስት ገቢ ተደርጎ ተጠርጣሪው እንዲያዝ ትዕዛዝ ይሰጣል። መሰል ስርአት አካለመጠን ላልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ተፈፃሚ አለመሆኑ በቀጣይ የወጣቱ በችሎት የመገኘት እድል ላይ የራሱ አሉታዊ ተፅእኖ የሚኖረው በመሆኑ ወጣቱን በሀላፊነት የሚረከቡ ሰዎች የዋስትና ግዴታ እንዲገቡ ማድረግ ይገባል። አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን በፓሊስ ጣቢያ ማቆያ ቦታዎች ውስጥ በማሰር ምርመራ ማድረግ አለመቻሉ፣እንደተያዙም ወዲያው በአቅራቢያ ወደሚገኝ ፍርድ ቤት መቅረብ የሚገባቸው መሆኑ፣ፍርድ ቤት ከቀረቡም በኋላ በምርመራና በክርክር ወቅት በአሳዳጊ ወይም በቤተሰብ እጅ እንዲቆዩ የሚደረጉ መሆኑ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶችን ወይም አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶችን በመጠቀም ወንጀል በሚፈፅሙ ሰዎች ላይ ምርመራን በአግባቡ ለማከናወን አዳጋች መሆኑ እሙን ቢሆንም ወጣቶቹን በፓሊስ ማቆያ እንዲቆዩ በማድረግና በመመርመር በድጋሚ ወደ ወንጀል ድርጊት እንዳይገቡ በማድረግ የሚገኘውን ጥቅም ሕጉ መምረጡን መረዳት ይቻላል።

አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን በተመለከተ ፓሊስ በዳኛ ትዕዛዝ እየተመራ ምርመራ ማከናወኑ፣ ዐቃቤ ሕግ በመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በሚከናወኑ የምርመራና የክርክር ሂደት እንዳይገኝ መደረጉ፣የችሎቱ የክርክር ስርአት መደበኛውን ሂደት አለመከተሉን አስከትሎ የሚመጣው ጥያቄ በወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊው ላይ ክስ የሚመሰርተው ማነው? ክስስ እንዲመሰረት የሚወስነው ማነው የሚለው ነው። በአዋቂ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ተፈፃሚ በሚሆነው መደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ላይ ፓሊስ የምርመራ መዝገቡን ሲያጠናቅቅ የምርመራ መዝገቡን ለዐቃቤ ሕግ ያቀርባል። ምርመራ መዝገቡ የቀረበለት ዐቃቤ ሕግም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 40 እና 42 ላይ በተመለከተው አግባብ በቂ ማስረጃ ካለ ክስ ይመሰርታል ወይም ጥፋተኛ ለማስደረግ የሚያስችል በቂ ማስረጃ ከሌለ፣ተከሳሹ ካልተገኘና ተከሳሹ በሌለበት የማይከሰስ ወንጀል ከሆነ ወይም ክሱ በይርጋ የሚቋረጥ ከሆነ መዝገቡን ይዘጋዋል። ለህዝብ ጥቅም አስፈላጊ በመሆኑ የፍትህ ሚንስቴሩ ክስ እንዳይመሰረት ትዕዛዝ ከሰጡ መዝገቡ ላይ ክስ እንዳይቀርብ ይደረጋል። በግል አቤቱታ አቅራቢነት በሚያስጠይቁ ወንጀሎች ላይ በቂ ማስረጃ የለም በሚል ዐቃቤ ሕግ መዝገቡን ከዘጋ በኋላ ለግል ተበዳዩ በሚሰጠው ፍቃድ መነሻነት የግል ተበዳዩ ክስ ሊያቀርብ ይችላል። በምርመራ መዝገቡ ላይ ዐቃቤ ሕግ ተጨማሪ መሰብሰብ ያለበት ማስረጃ አለ ብሎ ካመነ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ ቁጥር 38 መሰረት ተጨማሪ የምርመራ ትእዛዝ ሊሰጥ ይችላል። አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ወጣቱ የፈፀመው ወንጀል 10 አመትና ከዚያ በላይ በሆነ ፅኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ ከሆነ ምርመራውን የሚከታተለው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቂ ማስረጃ እንዲሰበሰብ ካደረገ በኋላ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲያቀርብ ትዕዛዝ ካልሰጠ በስተቀር በሌሎች የወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ በወጣቱ ላይ ክስ ማቅረብ አይችልም። በዚህም ሁኔታ ቢሆን ለዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ የሚሰጠው ምን አይነት ማስረጃ ሲኖር ነው? በቂ ማስረጃ ስለመኖሩ በመመርመር ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ የሚሰጠው ማነው? በሌሎች ከባድ ባልሆኑ ወንጀሎች ላይ ክስ እንዴት ይመሰረታል? ማን ይመሰርታል የሚሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ።

በቅድመ ክስ የምርመራ ጊዜና በክርክር ወቅት በአብዛኛው ዐቃቤ ሕግ በሂደቱ እንዲገኝ የማይደረግ ሲሆን የወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በወጣቱ ላይ አቤቱታ የመመዝገብና ምርመራውን የመምራት ስልጣን ይኖረዋል። የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የተከታተለውንና የመራውን የምርመራ መዝገብ በመመልከት የዐቃቤ ሕግን ተፈጥሯዊ የመክሰስና የመዝጋት ሚና በመተካት በቂ ማስረጃ በሚኖርበት መዝገብ ላይ ዋናው ክርክር ይደረግ፣ከባድ ወንጀል ሲሆን ደግሞ የወንጀሉን ከባድነትና በቂ ማስረጃ መኖሩን በማየት በዐቃቤ ሕግ አማካኝነት ክስ እንዲመሰረት ትዕዛዝ የሚሰጥ ይሆናል። በተጣራው የምርመራ መዝገብ ላይ ጥፋተኛ ለማስባል የሚያስችል በቂ ማስረጃ ከሌለ ወይም መዝገቡ ላይ ክስ እንዳይቀርብ የሚያስደርጉ በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ 42 ላይ የተመለከቱ ምክንያቶች መኖራቸውን የወረዳው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ካረጋገጠ መዝገቡን የሚዘጋው ይሆናል። መዝገቡ የተዘጋው በቂ ማስረጃ የለም በሚል ከሆነና ወንጀሉም በግል ክስ አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስጠይቅ ወንጀል ከሆነ ፍርድ ቤቱ ለግል ተበዳዩ በራሱ ክስ ማቅረብ እንዲችል ፍቃድ ሊሰጠው ይችላል።

በወረዳው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በቂ ማስረጃ በመኖሩ የተነሳ በራሱ በፍርድ ቤቱ ወይም በሌላ ስልጣን ባለው ፍርድ ቤት አማካኝነት ክርክር እንዲደረግ ውሳኔ ከተሰጠ አካለመጠን ባልደረሰ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ ላይ ክስ የሚዘጋጀው በማን አማካኝነት ነው የሚለው ጥያቄ ቀጥሎ የሚነሳ ነው። በወንጀል የተከሰሰ ሰው ጥፋተኛ ተብሎ የሚቀጣው በሕግ ወንጀል የተባለን ድርጊት አጥፊ በሆነ የሀሳብ ክፍል ላይ ሆኖ ሕጉን ሲተላላፈና ይህም በፍርድ ቤቱ በአግባቡ መረጋገጥ ሲችል ነው። በፍርድ ቤቱ የክርክር ሂደት የተከሰሰው ግለሰብ ድርጊት በአግባቡ እንዲረጋገጥ የተከሰሰበት ክስ ግልፅ በሆነ መልኩ ተዘጋጅቶ ክርክሩ ከመጀመሩ በፊት ሊደርሰው ይገባል። የክሱ አስቀድሞ መድረስ አስፈላጊነት ተከሳሽ የሚሆነው ግለሰብ አስቀድሞ በተከሰሰበት ክስ ላይ ራሱን አዘጋጅቶ መከላከል እንዲችል ለማድረግ ነው። የሚቀርብበት ክስ የተጣሰውን የሕግ ድንጋጌ፣የተከሳሹን ድርጊትና የሀሳብ ክፍሉን ፣ድርጊቱ የተፈፀመበትን ጊዜና ቦታ እንዲሁም ሌሎች አስፈላጊ ዝርዝሮችን የያዘ መሆን አለበት። በአዋቂ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ተግባራዊ በሚሆነው መደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ መሰረት በተከሳሽ ላይ የሚቀርቡ ክሶች ከተላለፈው ድንጋጌ ጋር የተቀራረቡ መሆን የሚገባቸው ሲሆን በክርክር ሂደት ክሱ በማስረጃ ካልተረጋገጠ ተከሳሹ በነፃ ይለቀቃል።

አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን የክስ አቀራረብ በተመለከተ መነሻ ተደርጎ ሊታይ የሚገባው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 108(3) ነው። በዚህ ድንጋጌ መሰረት አካለመጠን ያልደረሰውን ወጣት ጉዳይ የሚመለከተው መደበኛ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በወንጀሉ ከባድነት መነሻ ዐቃቤ ሕግ ክስ እንዲመሰርት ትዕዛዝ ካልሰጠ በስተቀር ክስ በመመስረት ሂደት ውስጥ ተግባራዊ የሚሆነው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ከአንቀፅ 109 ጀምሮ ያሉት ድንጋጌዎች ተፈፃሚነት የላቸውም በማለት አስቀምጦ ይገኛል። ይህ ድንጋጌ ሁለት አይነት የክስ መክሰስ ስርአት አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን በተመለከተ በኢትዮጵያ ተግባራዊ እንደሚደረግ ያሳያል። የመጀመሪያው አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት የሕግ ተላላፊ የፈፀመው ወንጀል 10 አመትና ከዚያ በላይ በሆነ ፅኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ ወንጀል ከሆነ ዐቃቤ ሕግ መደበኛውን የክስ ስርአት በመከተል ክስ ያዘጋጃል። በዚህ ጊዜ አዋቂ ወንጀል አድራጊዎች ወንጀል ሲሰሩ የሚዘጋጀው አይነት ክስና የክስ ዝርዝር እንዲሁም ሌሎች በሕግ የተቀመጡ ጥበቃዎች አካለመጠን ላልደረሰው ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ ተፈፃሚነት ይኖራቸዋል። በሌላ በኩል አካለመጠን ባልደረሱ ወጣቶች የሚፈፀሙ በርካታ ከ 10 አመት ፅኑ እስራት በታች የሚያስቀጡ ቀላል ይዘት ያላቸው ወንጀሎችን በተመለከተ መደበኛ ክስ ሳይዘጋጅ ክርክር ይደረጋል። በዚህ ጊዜ ከመደበኛ ክስ ይልቅ በወጣቱ ላይ አመልካቾች(ተበዳይ) ወይም ፓሊስ ለፍርድ ቤቱ የሚያቀርበው አቤቱታ ክሱን ተክቶ ለወጣቱ የሚነበብለት ይሆናል። በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀፅ 172 መሰረት አካለመጠን ያልደረሰውን ወጣት ወደ ወረዳው ፍርድ ቤት የወሰደ ቤተሰብ፣ሞግዚት፣ዐቃቤ ሕግ ወይም ፓሊስ የወንጀሉንና የምስክሮችን ዝርዝር ለፍርድ ቤቱ የሚገልፅ ሲሆን አስፈላጊ በሆነ ጊዜ የአቤቱታ ማመልከቻ ለፍርድ ቤቱ በመግለፅ በመዝገብ ይፃፋል። ይህ የተመዘገበ አቤቱታ ከ 10 አመት በታች የሚያስቀጡ ወንጀሎችን አካለመጠን ባልደረሰው ወጣት በሚፈፀሙ ጊዜ እንደ ክስ ሆኖ ያገለግላል። ለወጣቱ አቤቱታው ይነበብለታል፣ካማነ ባመነው መሰረት ፍርድ ለመስጠት መነሻ የሚሆን ሲሆን ካለመነ ደግሞ ለቀጣይ የክርክር ሂደቶች ጥቅም ላይ ይውላል። አካለመጠን ባልደረሰ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ ላይ አቤቱታ የሚያቀርቡት አብዛኛዎቹ ሰዎች የሕግ እውቀት የሌላቸው በመሆኑ የተነሳ ክስን ሊተካ በሚችል መልኩ የወጣቱን የወንጀል ድርጊት ፣የተላለፈውን የወንጀል ሕግ ድንጋጌ፣ወንጀል የፈፀመበትን የሀሳብ ክፍል በሚገባ ገልፀው ለፍርድ ቤቱ ያስመዘግባሉ ተብሎ አይጠበቅም። ይህም ወጣቱ የተከሰሰበትን ክስ በሚገባ አውቆ ራሱን በአግባቡ እንዳይከላከል ከማድረግ ባለፈ ፍትሀዊ የሆነ የፍርድ ሂደት እንዳይኖር በር ይከፍታል። በመሆኑም ምርመራውን፣ የያስከስሳል አያስከስስም የሚለውን ትዕዛዝ የሚሰጠው የወረዳ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አካለመጠን ባልደረሰው ወጣት ላይ የሚቀርበው አቤቱታ በወጣቱ ላይ የሚቀርብ ክስ መሆኑን ከግምት አስገብቶ ክስ ሊይዛቸው የሚገቡ ፍሬ ነገሮችን በያዘ መልኩ አቤቱታውን ሊመዘግብና ለወጣቱ አስቀድሞ እንዲደርሰው ሊያደርግ ይገባል።

አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ ላይ የሚቀርበው መደበኛ ክስ ወይም ክሱን የተካው አቤቱታ በችሎት እንዲነበብለት ከተደረገ በኋላ ክሱን እንደሚያምን ወይም እንደሚክድ በዳኛው ይጠየቃል። በአዋቂ የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ ተግባራዊ በሚደረገው በመደበኛው የሥነ ሥርዓት ሕግ ክሱ ለተከሰሰው ሰው ከተነበበለት በኋላ ጥፋተኝነቱን እንደሚያምን ወይም እንደሚክድ የሚጠየቅ ሲሆን የክሱን ፍሬ ነገር ሙሉ በሙሉ ያመነ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ጥፋተኛ የሚለው ሲሆን ክሱን ከካደ ወይም ደግሞ መብቱን ጠብቆ ምላሽ ከሰጠ እንደካደ ይቆጠራል። በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 134 መሰረት ተከሳሹ ሙሉ በሙሉ ክሱን ቢያምንም እና ጥፋተኛ ተብሎ ቢመዘገብም ፍርድ ቤቱ አስፈላጊ ነው ብሎ ካመነ ዐቃቤ ሕግና ተከሳሹ የየራሳቸውን ማስረጃ እንዲያቀርቡ ሊያዝ ይችላል። በተሰጠ የእምነት ቃል መሰረት ተደርጎ ጥፋተኛ ከተባለ በኋላ ተከሳሽ ጥፋተኛ አይደለሁም ካለ ወይም በይዘቱ መካዱን የሚያሳዩ ሁኔታዎች መኖራቸውን ፍርድ ቤቱ ከተረዳ የእምነት ቃሉ ተሰርዞ እንደካደ በመቁጠር ጥፋተኝነቱ የሚሰረዝ ይሆናል። አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን በተመለከተ የተከሰሱበትን ክስ አውቀውና ተረድተው ሲያምኑ ወይም ሲክዱ በእምነታቸው መሰረት ጥፋተኛ በማለት ወይም ስለካዱ ክርክር እንዲቀጥል ከማድረግ በዘለለ በአዋቂ የወንጀል ፈፃሚዎች ላይ በተቀመጠው አግባብ ዝርዝር ድንጋጌ አልተቀመጠም። አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን በተመለከተ የተቀመጠው ልዩ ድንጋጌ አላማው የተሻለ ጥበቃ ለወጣቶቹ መስጠት እንደመሆኑ መጠን ለአዋቂዎች የተሰጡ የተሻሉ ድንጋጌዎች በልዩ ድንጋጌ ውስጥ ካልተካተቱ የአዋቂዎችን ድንጋጌ መጠቀም ያለውን ክፍተት ለመሙላት ይጠቅማል። በመሆኑም የእምነት ክህደት ቃል በሚሰጥበት ጊዜ አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ድርጊቱን መፈፀሙን ቢያምንም የወንጀሉን ከባድነትና ሌሎች ከባቢያዊ ሁኔታዎችን ከግምት በማስገባት ክሱን የሚደግፍ ወይም የሚከላከል ማስረጃ እንዲቀርብ ፍርድ ቤቶች ማዘዝ የሚችሉ ሲሆን ከታመነ በኋላ መካድም አካለመጠን ላልደረሱ ወጣቶች ጥቅም ላይ ሊውል ይገባል። የእምነት ቃል አሰጣጡም የተከሰሰበትን ክስ አውቆ በሙሉ ከማመን በዘለለ መብቱን ጠብቆ ማመን ወይም ዝም ማለቱ መካዱን እንደሚያሳይ ፍርድ ቤቱ ከግምት ሊያስገባ ይገባል።

አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊ ክሱ ወይም አቤቱታው ከተነበበለት በኋላ የቀረበበትን ክስ ከካደ ወይም መብቱን ጠብቆ ካመነ ወይም ደግሞ የወንጀሉን ድርጊት ሙሉ በሙሉ አምኖ ፍርድ ቤቱ ክሱን የሚደግፍ ማስረጃ እንዲቀርብ ካዘዘ ቀጣዩ የሚመጣው ጥያቄ የክርክር ሂደቱ የሚደረገው ወጣቱ በጠበቃ ተወክሎ ነው ወይስ አይደለም የሚለው ነው። በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 20(5) ላይ እንደተደነገገው ማንም በወንጀል የተከሰሰ ሰው በመረጠው ጠበቃ ተወክሎ የወንጀል ክርክሩን የማድረግ መብት አለው። ተከሳሹ በራሱ ጠበቃ ለማቆም አቅም ከሌለውና ያለጠበቃ ተወክሎ ክርክር ካደረገ ፍትህ የሚጓደል ከሆነ በመንግስት ወጪ ጠበቃ ይመደብለታል። ይህ ህገ-መንግስታዊ የመብት ድንጋጌ ለሁሉም ክስ ለሚመሰረትባቸው ተከሳሾች ላይ ተፈፃሚነት የሚኖረው ነው። ከዚህ የህገ-መንግስቱ ድንጋጌ በተቃረነ መልኩ ተከሳሽ የሚሆኑት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች ሲሆኑ በፍርድ ቤቱ አማካኝነት የመንግስት ጠበቃ የሚቆምላቸው አንድም የተከሰሱበት ድንጋጌ ከ 10 አመት በላይ ፅኑ እስራት ወይም በሞት የሚያስቀጣ ሲሆን ወይም አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ዘመዶች ፣ሞግዚት ወይም ቤተሰቦቹ በፍርድ ቤቱ ያልቀረቡ ከሆነ ነው። ይህ ድንጋጌ በብዙ መልኩ ክፍተቶች ያሉበት ነው። የመጀመሪያው ክፍተት በህገ-መንግስቱ የተመለከተውን በአቅም ማጣት የተነሳ ፍትህ የሚጓደል ሲሆን በመንግስት ጠበቃ ለተከሳሾች ይመደባል የሚለውን መስፈርት አለመጥቀሱ ነው። በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 174 መሰረት ፍርድ ቤቱ ጠበቃ ለማቆም የወንጀሉን ከባድነት እና ለወጣቱ ቅርብ የሆኑ ሰዎች በፍርድ ቤት አለመገኘትን መስፈርት ያደረገ ሲሆን ይህን መስፈርት ያሟላ በራሱ ጠበቃ ለማቆም የሚችል አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት በመንግስት ጠበቃ ሊቆምለት ይችላል። በዚህም ድንጋጌው በህገ-መንግስቱ ለተከሳሾች የተሰጠውን ጠበቃ በመንግስት የመመደብ መብት በእጅጉ የሚገድብ ነው። ሌላው የድንጋጌው ክፍተት አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት በራሱ ወይም በቤተሰቡ አማካኝነት ጠበቃ ለማቆም የማይችል ሆኖ ነገር ግን ቤተሰቡ ወይም ሞግዚቱ ፍርድ ቤት መቅረብ ከቻለ በመንግስት ጠበቃ የማግኘት መብት አይኖረውም። ይህም ማለት በአብዛኛው ጊዜ በሕግ ምንም አይነት እውቀት የሌላቸው የወጣቱ ቤተሰቦች ጠበቃውን ተክተው አካለመጠን ላልደረሰው ወጣት ይከላከሉለታል ማለት ነው። አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ቤተሰቦች በወንጀል ቢከሰሱ በራሳቸው ጠበቃ ማቆም ካልቻሉና በዚህም ፍትህ የሚጓደል ከሆነ መንግስት ጠበቃ የሚመድብላቸው ሆኖ የእነርሱ ተወላጆች ሲከሰሱ ግን ጠበቃ ሆነው ፍርድ ቤት ይቀርባሉ። አካለመጠን ያልደረሰውን ወጣት በሕግ አግባብ መወከል የማይችሉ ሰዎች እንዲወክሉት ይሆናል። በዚህም የተነሳ ይህ ድንጋጌ የፍትሐዊነት ጥያቄ የሚነሳበት እንዲሆን አድርጎታል። ከፍትሐዊነት ጥያቄም በዘለለ ሕግ አውጭው በዚህ መልኩ ለምን ድንጋጌውን ሊቀርፀው ፈለገ የሚል ጥያቄም እንዲነሳ ምክንያት ይሆናል። በመሰረቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ በ ኮመን ሎው (common law legal system) ሀገራት ተግባራዊ የሚደረገውን ሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች ማስረጃቸውን ለፍርድ ቤቱ በማቅረብ በሙግትና በተጠየቅ እውነትን ፈልጎ የማውጣት መንገድን አልተከተለም። ለዚህም በሚመስል መልኩ በክርክሩ ዐቃቤ ሕግ በመርህ ደረጃ እንዳይገኝ ማድረግን፣የግል ጠበቆችም በውስን ጉዳዮች ብቻ እንዲገኙና ዳኞች ክሱን ደግፈውም ሆነ ለመከላከል የሚቀርቡ ምስክሮችን ዋና ጥያቄና የማጣሪያ ጥያቄ የመጠየቅ መብት እንዲኖራቸው በማድረግ የወጣቱ ጥቅም በመንግስት እንዲከበር እውነትም ከሙግት ይልቅ ፍርድ ቤት መር በሆነ ስርአት እንዲገኝ ለማድረግ የተሞከረው። ይህ አይነቱ በሥነ ሥርዓት ሕጉ የተቀመጠው ስርአት በአብዛኛዎቹ የኮንቲኔታል ሎው ሀገራት ተግባራዊ የሚሆን ሲሆን አካለመጠን ባልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ላይ የኛም ሀገር ሕግ ተመሳሳይ መንገድን የተከተለ በመሆኑ የጠበቆች ተሳትፎ ውስን እንዲሆን ሆኗል። ምንም እንኳን የሥነ ሥርዓት ሕጉ ምልከታ በዚህ መልኩ የተቀረፀ ቢሆንም በተቃራኒው የወንጀል ሕጉ አካለመጠን ባልደረሱ ወጣቶች ላይ በወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ሲገኙ የተለያዩ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ቅጣቶችን ከመጣል ባለፈ አልፎ አልፎ የመብት መታጣት እንደ ቅጣት እንዲጣል መደረጉ ሲታይ በወንጀል ሕጉና በሥነ ሥርዓት ሕጉ መሀከል ተቃርኖዎች መኖራቸውን መመልከት ይቻላል። አካለመጠን ባልደረሱ ወጣቶች ላይ በወንጀል ሕጉ የተመለከቱ የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣት በአግባቡ በጠበቃ ሳይወከሉና እራሳቸውን ሳይከላከሉ እንዲጣልባቸው ማድረግ ፍትሐዊ የሆነ የሙግት ስርአትን አለመከተል በመሆኑ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 20(5) ስር በተመለከተው አግባብ አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት በራሱ ወይም በቤተሰቡ አማካኝነት ጠበቃ ለማቆም የገንዘብ አቅም ከሌለውና በዚህም ፍትህ የሚዛባ ከሆነ መንግስት ጠበቃ ሊመድብለት ይገባል።

በአከራካሪ ጭብጦች ላይ እውነትን ፈልጎ ለማውጣት በችሎት ማስረጃ በማቅረብ እንዲሰማና እንዲጠየቅ ማድረግ አንዱ መንገድ ነው። በአዋቂ ሰዎች ላይ ተፈፃሚ በሚሆነው መደበኛ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ክስ የተመሰረተበት አዋቂ ሰው ክሱ በግልፅ ችሎት እንዲነበብለት ከተደረገ በኋላ ክሱን የካደ እንደሆነ ዐቃቤ ሕጉና ተከሳሹ የየራሳቸውን ማስረጃቸውን ያቀርባሉ። ዐቃቤ ሕግ ክሱን የሚደግፉለትን ማስረጃዎች ምን እንደሚያስረዱለት ያለመድልዎ ጭብጥ ካሲያዘ በኋላ ማስረጃው የሰው ምስክር ከሆነ ቃለ መሀላ እንዲፈፅም በማድረግ ዋና ጥያቄና ድጋሚ ጥያቄ የሚጠይቅ ሲሆን ተከሳሹ መስቀልያ ጥያቄ በመጠየቅ ምስክሩ እውነተኛ ስለመሆኑ ይመረምራል። በዐቃቤ ሕግ በኩል የቀረቡት የሰውና ሌሎች ማስረጃዎች በቂ ከሆኑ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ተከላከል የሚለው ሲሆን ተከሳሹ መከላከያ የሚሆኑትን ማስረጃዎችን በማቅረብ ዋና ጥያቄና ድጋሚ ጥያቄ የሚያቀርቡ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ በበኩሉ መስቀለያ ጥያቄ የሚያቀርብ ይሆናል። በሁለቱም ተከራካሪ ወገኖች የሚቀርቡ ማስረጃዎችን ፍርድ ቤቱ በማንኛውም ጊዜ ጥያቄ መጠየቅ የሚችል ሲሆን ተከራካሪ ወገኖች ከሚያቀርቡት ማስረጃ ውጭ ፍርድ ቤቱ ለፍትህ አስፈላጊ መሆኑን ካመነ በራሱ ማስረጃ ጠርቶ ሊያጣራ ይችላል። አካለመጠን ላልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች ተብሎ የተደነገገው ልዩ የሥነ ሥርዓት ድንጋጌ በአንቀፅ 176(2) ላይ በግልፅ እንዳስቀመጠው አካለመጠን ያልደረሰውን ወጣት የሚሰማው ችሎት በሌላ ነገር ተሰይም ከሚያነጋረው አኳሀንና ሁኔታ በተለየ ሁኔታ እንደሆነ ነው። በመደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በመርህ ደረጃ የወንጀል ክርክሮች በግልፅ ችሎት እንዲታዩ ይደረጋል። አካለመጠን ያልደረሱ ወጣት የወንጀል ሕግ ተላላፊዎችን በተመለከተ ፍርድ ቤት በቀረቡ ጊዜ ነገሩ በሙሉ የሚሰማው በዝግ ችሎት ነው። ማስረጃ በሚሰማበት ጊዜ ከምስክሮች፣የምስክርነት ቃላቸውን ከሚሰጡ ልዩ ዐዋቂዎች ፣ከወላጅ፣ከሞግዚት ወይም ከበጎ አድራጎት ድርጅት በስተቀር ማንም ሰው በችሎት እንዲገኝ አይደረግም። ጉዳዩ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ብቻ ሲሆን ዐቃቤ ሕግ እንዲገኝ ይፈቀድለታል። ይህ የሥነ ሥርዓት ሕጉ ድንጋጌ አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ችሎቱ ለህዝብ ግልፅ በመሆኑ የተነሳ በሚፈጠርበት እፍረት ከህብረተሰቡ ጋር በቀላሉ ለመቀላቀል እንዳይቸገር ያደርገዋል። ሆኖም ግን ሁል ጊዜም አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች ጉዳያቸው በችሎት በሚታይበት ጊዜ ችሎቱን በዝግ እንዲሆን ማድረግ መሰረት የሌላቸው ሀሰተኛ ወሬዎች ህብረተሰቡ ውስጥ እንዲዛመት በማድረግ ለወጣቱ ይበልጥ ጎጂ የሚሆኑበት ሁኔታ ከመኖሩም ባለፈ መገኘት ይችላሉ ተብለው በሕግ ከተዘረዘሩት ሰዎች ውስጥ ተጎጂዎች፣የተጎጂ ቤተሰቦች እንዲሁም የተከሳሹ ጠበቃ እንዲኖር አለመደረጉ በፍርድ ሂደቱ ላይ ጥርጣሬ እንዲፈጠር መነሻ ይሆናል። በመሆኑም ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ በተመለከተው አግባብ ጥብቅ የሆነ የዝግ ችሎት መርህን መከተል አግባብ አይሆንም።

በዝግም ሆነ በከፊል ዝግ በሆነ ችሎት በሚደረጉ አካለመጠን ያልደረሰ ወጣት በሚሳተፍባቸው ችሎቶች ላይ የሚደረግ የማስረጃ አሰማም ሂደት ከመደበኛው ስርአት በእጅጉ የራቀ ነው። አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት የተከሰሰበትን ክስ የካደ እንደሆነ ለክሱ ደጋፊ ወይም ተከላካይ ማስረጃዎን ፍርድ ቤቱ እንዲቀርቡ በመጥሪያ ይጠራቸዋል። በመደበኛው ስርአት ክሱን የሚደግፍ ማስረጃ በዐቃቤ ሕጉ አማካኝነት የሚጠራ ሲሆን አካለመጠን ባልደረሱ ወጣቶች ችሎት የዐቃቤ ሕግን ሚና ተክቶ ሀላፊነት የሚወስደው ፍርድ ቤቱ በመሆኑ የተነሳ ዳኘው ክሱን ሊደግፉ ይችላሉ ብሎ የሚያምንባቸውን ማስረጃዎች እንዲመጡ በመጥሪያ ያዛል። ተከሳሹም ክሱን ሊከላከሉለት የሚችሉ ማስረጃዎችን ለፍርድ ቤቱ ሲያመላክት በፍርድ ቤቱ አማካኝነት እንዲጠሩ መጥሪያ ይላክላቸዋል። በመደበኛው ስርአት ተከራካሪ ወገኖች የሚጠሩዋቸውን ምስክሮች የተለያየ ይዘት ያላቸውን ጥያቄዎች በዋና ፣በመስቀለኛና በድጋሚ ጥያቄ ጊዜዎች የሚጠይቁዋቸው ቢሆንም አካለመጠን ባልደረሱ ወጣቶች ጊዜ ግን ችሎት ክሱን ደግፈውም ሆነ ተከላክለው የሚመጡ ማስረጃዎችን ዋናና ድጋሚ ጥያቄዎችን በመጠየቅ እውነቱን የሚያወጣ ይሆናል። በዚህም ምስክሮቹ በሙሉ የፍርድ ቤቱ ምስክሮች ናቸው ለማለት ይቻላል። በምስክር መስማት ሂደት እውነት ነጥሮ እንዲወጣ ለማድረግ ይረዳ ዘንድ ተከሳሽ ክሱን የሚደግፉትንም ሆነ ለመከላከል የሚቀርቡትን ማስረጃዎች መስቀለኛ ጥያቄ እንዲጠይቅ ይደረጋል። አልፎ አልፎ ምስክርነቱን መስማቱ ለወጣቱ አስፈላጊ በማይሆንበት ጊዜ ለአብነትም ስለቤተሰቦቹ ሁኔታ ወይም ስለቀድሞው ባህሪ ማብራሪያ በሚሰጥበት ጊዜ ወጣቱ በችሎት እንዳይገኝ የሚደረግ ቢሆንም ይህ ሁኔታ ግን የወጣቱን መስቀለኛ ጥያቄ የመጠየቅ መብቱን እንዳይጎዳ መጠንቀቅ ይገባል። አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት የክርክር ሂደቱ መደበኛውን ስርአት አይከተልም ቢባልም በዚሁ ምክንያት ግን ለምስክርነት የመጡ ሰዎች ምስክርነታቸውን ከመስጠታቸው በፊት ቃለ-መሀላ አይፈፅሙም ወይም ደግሞ የማስረጃ ምዘናው የመደበኛውን ስርአት አይከተልም ማለት አይደለም። በመደበኛው ስርአት ያለው የቃለ-መሀላና የማስረጃ መዝና መርህ አካለመጠን ላልደረሱ ወጣቶች ተፈፃሚነት ይኖረዋል። አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች ክስ በሚመሰረትባቸው ጊዜ የምስክሮችን አስፈላጊነት በመለየት እንዲመጡ በማድረግ፣ ምስክሮችን ጠይቆ እውነት በማውጣት ሂደት የዐቃቤ ሕግ ሚና በፍርድ ቤት የተተካ ቢሆንም በከፍተኛ ፍርድ ቤት በሚደረጉ የክርክር ሂደቶች ዐቃቤ ሕግ በችሎት እንዲገኝ ይደረጋል። የዐቃቤ ሕግ በከፍተኛ ፍርድ ቤት መገኘት በሕጉ ተመላክቶ ቢገኝም ልክ እንደመደበኛው ስርአት ምስክሮችን የመጠየቅ ሀላፊነት ግን አልተሰጠውም። በማስረጃ መስማት ሂደት አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ልክ እንደአዋቂ ተከሳሾች ቃለ-መሀላ ሳይፈፅም በራሱ ጉዳይ ምስክር መሆን ይችላል ወይስ አይችልም የሚለውን በተመለከተ ሕጉ የሚለው ነገር የለም። በመደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አዋቂ ተከሳሾች በተመሰረተባቸው ክስ ላይ ቃለ-መሀላ ሳይፈፅሙ ቃላቸውን ለፍርድ ቤቱ እንዲሰጡ ይደረጋል። መሰል ድንጋጌ አካለመጠን ላልደረሱ ወጣቶች ያልተደነገገ ቢሆንም በአሳማኝ አመክንዮ ስርአቱ ለእነርሱም እንዲሰራ ቢደረግ ትክክለኛ ፍትህ ለመስጠት ይረዳል።

አካለመጠን ባልደረሱ ወጣቶች ላይ የሚከናወነው ፍርድ ቤት መር የሆነው እውነትን ፈልጎ የማውጣት ሂደት ክሱን የሚደግፋና የሚከላከለው ማስረጃ ተሰምቶ ከተጠናቀቀ በኋላ ተከሳሹ ላይ የጥፋተኝነት ወይም የነፃ መውጣት ፍርድ በመስጠት ይጠናቀቃል።  በወጣቱ ላይ የቀረበው ማስረጃ በቂና አሳማኝ ካልሆነ የነፃ መውጣት ፍርድ ይሰጣል። የቀረበው ማስረጃ ወንጀል ስለመሰራቱ በቂና አሳማኝ ከሆነ የጥፋተኛነት ፍርድ የሚሰጥ ሲሆን በወንጀል ሕጉ ላይ የተመለከቱ የጥንቃቄና የቅጣት እርምጃ ከመጣሉ በፊት ስለወጣቱ የቀድሞ የወንጀል ታሪክና ባህሪ ማጥናት አስፈላጊ ከሆነ ፍርድ ቤቱ የአዋቂ ምስክሮችን ቃል ይሰማል። ተከሳሹም ስለቀድሞው ታሪኩና ባህሪው የራሱን ምስክሮች እንዲቀርቡ በማድረግ በፍርድ ቤት እዲመረመሩለት ማድረግ ይችላል። ስለቀድሞ ባህሪና የጥፋተኝነት ታሪክ ማስረጃ የመስማት ሂደቱ በፍርድ ቤቱ አማካኝነት ከተጠናቀቀ በኋላ በዚህ ፅሁፍ በተራ ቁጥር 03 ላይ የተመላከቱ የጥንቃቄ እርምጃዎችና ቅጣቶች እንደሁኔታው በወጣቱ ላይ እንዲፈፅሙ ትዕዛዝ ይሰጣል። ፍርድ ቤቱ አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት ወላጆች ወይም ሀላፊ የሆኑ ሰዎች ወጣቱን በማሳደግ ሀላፊነታቸውን በሚገባ አልፈፀሙም ብሎ ካመነ ማስጠንቀቂያና ምክር ወይም ወቀሳ የሚሰነዝርባቸው ሲሆን ያልተወጡት ግዴታ ከፍ ያለ ከሆነና በዚህም የተነሳ ወጣቱ ወንጀል ወደ መጣስ ተግባር ገብቶ ከተገኘ በቤተሰቦቹ ወይም በአሳዳጊዎቹ ወጪ ለወጣቱ ሌላ አሳዳጊ ወይም ሞግዚት ወይም ይህን መሰል ስራ ወደሚሰራ ድርጅት እንዲገባ ትዕዛዝ መስጠት ይችላል።

በመደበኛ ፍርድ ቤቱ በሚሰጡ የፍርድና የቅጣት እርምጃዎች ላይ አካለመጠን ያልደረሰው ወጣት በህጋዊ ወኪሉ አማካኝነት ይግባኝ ማቅረብ እንደሚችል ስለይግባኝ ድንጋጌዎችን የያዘው መደበኛው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ አንቀፅ 185(2) ላይ ተመላክቶ ይገኛል። ነገር ግን በዚህ ድንጋጌ ላይ በርካታ ጥያቄዎች ይነሳሉ። ወጣቱ በሚያቀርበው ይግባኝ ላይ ከከፍተኛ ፍርድ ቤት ውጭ ባሉ የወንጀል ጉዳዮች ዐቃቤ ሕግ ባልተሳተፈበትና ፍርድ ቤቱ ዐቃቤ ሕጉን በተካበት ሁኔታ ማን ነው መልስ ሰጪ የሚሆነው? ዐቃቤ ሕግ በመደበኛው ፍርድ ቤት በሚሰጠው ውሳኔ ላይ መንግስትን ወክሎ ይግባኝ ማቅረብ አይችልም ወይ? ስነ-ስርአቱስ በምርመራ ወቅትና በክርክር ሂደት እንዳለው ወጣቱን ካልተገባ ክርክር በመጠበቅ ማስተማር ላይ መሰረት ያደረገ ነው የሚሉና የመሳሰሉ ጥያቄዎች ይነሳሉ። በይግባኝ በሚቀርበው አቤቱታ የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔ ላይ ከሆነ ዐቃቤ ሕግ መልስ ሰጪ ሆኖ መቅረቡ ከመነሻው በፍርድ ቤቱ ተገኝቶ ክርክሩን የታደመ በመሆኑ የዐቃቤ ሕጉ መልስ ሰጪ መሆን አመክንዮዊ ሊሆን ይችላል። በሌሎች ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ላይ ዐቃቤ ሕግን የተካው ፍርድ ቤት መልስ ሰጪ ወይም በራሱ ውሳኔ ላይ ይግባኝ ባይ እንዲሆን ማድረግ አግባብ አይሆንም። በመሆኑም በየትኛውም ፍርድ ቤት በሚወሰኑ ውሳኔዎች ላይ ዐቃቤ ሕግ በሂደቱ ቢገኝም ባይገኝም ለወጣቱ ይግባኝ መልስ ሰጪ በመሆንና የመንግስት ጥቅም ተነክቶባቸዋል ብሎ ባመነባቸውም ጉዳዮች ይግባኝ ሊያቀርብ ይችላል።

ማጠቃለያ

ድህነትና ስራ አጥነት በከፍተኛ ሁኔታ በተስፋፋባቸው እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሀገራት ለመኖር የሚያስፈልጉ መሰረታዊ ቁሶችን አለማግኘት በሚፈጥረው ስነ-ልቦናዊ ችግር አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች በለጋ እድሜያቸው ወደ ወንጀል እንዲገቡ መንሰኤ ነው። የከተሜነት መስፋፋትና የደሀው ማህበረሰብ ክፍል በቂ ትምህርት፣ጤናና የመሰረተ ልማት አቅርቦት እንዳይኖረው መሆኑ ችግሩን ይዞ ወደ ደጃፍ እንዲወጣና በወንጀል የሚገኝ ገቢን ለኑሮው መደጎሚያ ሲያደርገው ይስተዋላል። የሰላም መታጣትና የቀን ተቀን የግጭት ወሬዎች የመንግስትን አስተዳደር በማዳከምና የቁጥጥር ስርአት እንዲላላ በማድረግ ስርአት አልበኝነት የተለመደ የሰዎች ባህሪ ይሆናል። ይህ ሁላ አከባቢያዊ አጋላጭ ሁኔታ ደካማ ከሆነ የቤተሰብ ቁጥጥርና አስተዳደግ ጋር ተዳምሮ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶችን ሳይወዱ በግዳቸው የወንጀል ሕግ ተላላፊዎች እንዲሆኑ ያደርጋቸዋል።

አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶችን የእድሜያቸውን ለጋነት፣ተጋላጭ ያደረጋቸውን ከባቢያዊ ሁኔታ መሰረት በማድረግ በወንጀል ፍትህ ስርአት በሚገባ ከታከሙ በቀጣይ ወደ ወንጀል ከመግባት እንዲታረሙ ማድረግ የሚቻል ሲሆን በትክክለኛው መንገድ ካልታረሙና ካልታከሙ ግን በድጋሚ ወደ ወንጀል ተግባር የመግባት እድላቸው ከፍ ያለ ነው።

በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግ የወንጀል ሕጉን የተላለፉ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶች ወንጀል መስራታቸው ከተረጋገጠ በአዋቂ ሰዎች ላይ ከሚወሰደው ቅጣትና የጥንቃቄ እርምጃ በተለየ ልዩ የጥንቃቄ እርምጃና ቅጣት እንዲወሰድባቸው ይደረጋል። የጥንቃቅ እርምጃዎቹና ቅጣቶቹ ዋና አላማም ወጣቱን የሕግ ተላላፊ በማስተማር በቀጣይ ከክፉ ስራ እንዲጠበቅ አድርጎ ከማህበረሰቡ ጋር መቀላቀል ነው። የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶችን የምርመራና የክርክር ሂደት ለመምራት በ10 ድንጋጌዎች ለመሸፈን ቢሞክርም በብዙ መልኩ ክፍተት ያለባቸው ናቸው። ምንም እንኳን የሕጉ አላማ እውነትን ፈልጎ በማውጣት ከመደበኛው የሥነ ሥርዓት መንገድ በተለየ መልኩ በፍርድ ቤት ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት ምርመራና ክርክር ማድረግን መርህ ቢያደርግም በመደበኛው የሥነ ሥርዓት ሕጉ የተመለከቱ በምርመራና በክርክር ሂደት ተከሳሽን ለመጠበቅ ተብሎ የተቀመጡ ድንጋጌዎችን ሳይዝ ቀርቷል።

አካለመጠን ያልደረሱ ወጣቶችን ጉዳይ ብቻ የሚመለከት ልዩ ስልጠና የወሰዱ ዳኞችና የአስተዳደር ሰራተኞች ያሉበት ፍርድ ቤት አለመኖር፣ለወጣቱ ጠበቃ የሚመደብበት ስርአት ህገ-መንግስታዊ መርህን ያልተከተለ መሆኑ፣የክስ አመሰራረቱ ወጣቱ ራሱን ለመከላከል በሚያስችለው አግባብ አለመሆኑና ሌሎችም ክፍተቶች በልዩ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ላይ ቢኖርም ለአዋቂ ተከሳሾች ተግባራዊ የሚሆነውን መደበኛውን የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግን ተግባራዊ በማድረግ መሙላት ይገባል።

Download this article with full citation

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በሌላ ሰው ይዞታ ላይ ቤት የሰራ ሰው መብት - አንዳንድ ነጥቦች 
በደርግ ዘመን አዋጅ ቁጥር 47/67 ተግባራዊ በሆነበት ወቅት ያላግባብ የተወረሱ...

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - kalkidan on Wednesday, 04 October 2023 18:31

አቢሲኒያዎች ዌብሳይታችሁን ለአጠቃቀም ምቹ ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ። በተለይ ሊቁ ወርቁ ለትጋትህ ምስጋና ይገባሃል በእወነት

አቢሲኒያዎች ዌብሳይታችሁን ለአጠቃቀም ምቹ ስላደረጋችሁ አመሰግናለሁ። በተለይ ሊቁ ወርቁ ለትጋትህ ምስጋና ይገባሃል በእወነት
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 07 November 2024