ኢትዮጵያውን የሚሳተፉባቸውን የማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚጠቀምና ሌሎች ተጠቃሚዎች የሚጽፏቸውን ወይንም የሚጭኗቸውን ጽሑፎች፣ ምሥሎችና ድምፆች ለሚከታተል ሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ግልጽ የሆነ አዝማሚያ እያደገ መምጣቱን ያስተውላል፡፡ ይኼውም ጥላቻን ያዘሉ ንግግሮች መበራከታቸውን ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር እጅግ ብዙ የሆኑ በጎ እሴቶችን የመናጃ መንደርደሪያ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ ወንጀሎችን መጥሪያ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር አድልኦና መገለልን ያመጣል፡፡ የጥላቻ ንግግር የአንድን ብሔር አባላት፣ የሃይማኖት ተከታዮች፣ ስደተኞችንና ሌሎች ቡድኖችን እንበለ ምክንያት በጭፍኑ እንዲጠሉ መንገድ ያለሰልሳል፡፡ የከፋው ደግሞ የዘር ማጥፋትን ወይንም ቡድን ጠረጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በበርካታ አገሮችም ተከስቶ ነበር፡፡
በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አይሁዶችን የጀርመን ናዚዎች ከማጥፋታቸው በፊት በርካታ አይሁዶች በጀርመንና ሌሎች አገሮች በተሻለ የኑሮ ደረጃ ይመሩ ስለነበር እንደ ባለጠጋ ጥገኛ ተሕዋስያን (Wealthy parasite) ተደርገው ተስለዋል፡፡ ጀርመኖች ደግሞ ከሌሎች የላቁ እንደሆኑ ራሳቸውን ቆጥረዋል፡፡ ሁቱዎች በረሮ እንጂ ቱትሲዎች ብሎ መጥራት አቁመው ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ጥላቻው በሕዝብ ደረጃ ከፍ ባለበት ወቅት ነው፡፡ አጠራሩንም አንዱ ቡድን በጅምላ የሌላውን ተቀብሎ አጽድቆታል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን ፍረጃም ይሁን ስያሜ መነሻው እውነት እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ሕዝቡም ሲጋራው በምክንያታዊነት አስቦና አሰላስሎ አይደለም፡፡ ምክንያታዊነት የግለሰብ ባህርይ እንጂ የሕዝብ አይደለችም፡፡ ቡድንን ጅምላዊነት ያጠቃዋል፡፡ እንደ ግለሰብ ሲታሰብ ወለፈንድና ሐሰት መሆኑን የምንረዳውን ነገር ከቡድናችን ጋር ስንቀላቀል ግን እንተወዋለን፡፡ የጥላቻ ንግግርም ቡድናዊ ቅርጽ ለመያዝ በእጅጉ የተጋለጠ ነው፡፡ ታሪክም ያሳየን ይኼንኑ ነው፡፡
በርካታ አገሮች ከራሳቸውም ገጠመኝም ይሁን ከሌሎች የታሪክ ጠባሳ በመማር የጥላቻ ንግግሮችን የሚከለክሉ ሕግጋት አውጥተዋል፤ ተግባራዊ ለማድረግም ተቋማትን አደራጅተዋል፡፡ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራትም የጥላቻ ንግግር ምንነቱን፣ ይዘቱን፣ መንስዔውን፣ መዘዙንና ሌሎችም ጭብጦች ላይ በመመርኮዝ ጥናት ያጠናሉ፤ የፍትሕ ተቋማትን ያሠለጥናሉ፤ ሕዝብን የማንቃት ሥራ ይፈጽማሉ፡፡ ብሎም ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ ማኅበረሰቦች በሠላምና በመቻቻል እንዲኖሩ እያደረጉ ነው፡፡
ይህ ጽሑፍ የጥላቻ ንግግርን ምንነትና ከሌሎች ንግግሮች የሚለይበትን መንገዶች ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያን የሕግ ሁኔታ በመቃኘት የተጨማሪ ሕግ ወይንም ሥርዓት አስፈላጊነቱን በአንድ በኩል ከሕገ መንግሥቱ ጋር ለማጣጣም አስቸጋሪነቱን በሌላ በኩል ያሳያል፡፡ ይህን ለማድረግም ደግሞ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎች በመቃኘት እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ሕግና አሠራር ጋር በማነፃፀር ያሉትን ክፍተቶች በመጠቆም ምን መደረግ እንዳለበት ጥቆማ ያቀርባል፡፡