በዚህ ጽሑፍ ስለ ግብር ስወራ ምንነት፣ በተለያዩ የግብር ዓይነቶች ሥር የግብር ስወራ ስለሚያቋቋሙ ድርጊቶች፣ ለግብር ስወራ መነሻ ሊሆኑ ስለሚችሉ ምክንያቶች እንዲሁም የመከላከያ መንገዶቹ ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡ ይህንን ጽሑፍ ለመጻፍ መነሻ የሆነኝ የፌደራል መጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የጉምሩክና ታክስ ወንጀል ችሎት ዳኛ ሆኜ ስሠራ በነበርኩበት ጊዜ የኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ለግብር ስወራ የወንጀል ክሶች ለማስረዳት ሲያቀርባቸው በነበሩ የታክስ ኦዲቶች ላይ የሚጠቀሱ ግኝቶች ናቸው፡፡ የተለያዩ የግብር ስወራ ወንጀሎች ፈጽመዋል በማለት ተከሰው በፍርድ ቤት ሲቀርቡ ለነበሩ ተከሳሾች ይቀርብ የነበረው ማስረጃ፣ በታክስ ኦዲተሮች የሚሠራ የታክስ ኦዲት ግኝቶች ዝርዝር የሚገልጽ የጽሑፍ ማስረጃ እንዲሁም ይህንኑ የታክስ ኦዲት የሠሩ ባለሙያዎች በሙያ ምስክርነት ቀርበው የሚሰጡት የምስክርነት ቃል በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
በኢትዮጵያ ገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን የሚሠሩ የታክስ ኦዲቶች አንዳንዶቹ በትክክል የግብር ስወራ ስለመፈጸሙ በአግባቡ የሚያስረዱ ሲሆን፣ አንዳንዶቹ ደግሞ በጣም የተጋነኑ፣ ሙያዊ ላልሆነ ግምት የተጋለጡ እንዲሁም ለወንጀል ክስ የማስረዳት ብቃታችው ምክንያታዊ የሆነ እርግጠኝነት የማይፈጥሩ ናቸው፡፡ ግብር ስወራ በአገር ኢኮኖሚ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ የሚፈጥር የዕድገት ፀር የሆነ ሕገወጥ ድርጊት በመሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ ሁሉም ኅብረተሰብ ሊከላከለው የሚገባ ድርጊት ነው፡፡ ነገር ግን ግብር ያልከፈሉ ሁሉ ግብር ሰውረዋል ማለት አይደለም፡፡ ምክንያቱም ግብር ላለመከፈል መነሻው ግብር መሰወር ብቻ ላይሆን ይችላል፡፡
በሌላ በኩል ግብር ሳይከፈል የቀረው መክፈል የነበረበት ሰው ለመክፈል አቅም በማጣቱ ወይም መከፈል የሚገባው የግብር መጠን ሳይከፈል የቀረው ጥፋት በሌለበት ስህተት (Genuine error) ምክንያት ሊፈጠር ይችላል፡፡ ግብር ስወራ የሚመለከተው ደግሞ በስህተት ምክንያት ወይም አቅም በማጣት የታወቀ የግብር ግዴታ ሳይከፈል ለሚቀር ግብር ሳይሆን ሆነ ተብሎና እያወቁ የተለያዩ የማታለያ፣ የተንኮልና አሳሳች ነገሮች በመፈጸም ሊከፈል የሚገባ የግብር መጠን እንዲሰወር የሚያደርግ ሕገወጥ አካሄድን ነው፡፡
በአገራችን ግብር አለመክፈል የሚያስከትለው የወንጀልና የፍትሐ ብሔር ኃላፊነት በተመለከተ ያለው አሠራር ሲታይ ከሕጉ ጋር የተጣጣመ ነው ለማለት የሚያስቸግር ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በመጀመሪያ ግብር አለመክፈል በወንጀልና በፍትሐ ብሔር እንዲሁም በፍትሐ ብሔር ብቻ የሚያስጠይቅባቸው ሁኔታዎች ለየብቻ ተለይቶ ሲሠራበት አይታይም፡፡ በዚህም ግብር የመሰወር ድርጊት የፈጸመ ግብር ከፋይ በወንጀልና በፍትሐ ብሔር ሊጠየቅ ሲገባው የፍትሐ ብሔራዊ ኃላፊነቱ ከተወጣ ጤነኛ ባልሆኑ አካሄዶች እንዲሁም በግብር ሰብሳቢው መሥሪያ ቤት ፈጻሚዎች የግንዛቤ እጥረት ምክንያት የወንጀል ክስ የማይቀርብባቸው ትክክለኛ ያልሆኑ አሠራሮች አሉ፡፡