Font size: +
11 minutes reading time (2277 words)

መጥላት ላለብን የጥላቻ ንግግር የተጨማሪ ሕግ አስፈላጊነት

ኢትዮጵያውን የሚሳተፉባቸውን የማኅበራዊ ሚዲያዎች ለሚጠቀምና ሌሎች ተጠቃሚዎች የሚጽፏቸውን ወይንም የሚጭኗቸውን ጽሑፎች፣ ምሥሎችና ድምፆች ለሚከታተል ሰው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አንድ ግልጽ የሆነ አዝማሚያ እያደገ መምጣቱን ያስተውላል፡፡ ይኼውም ጥላቻን ያዘሉ ንግግሮች መበራከታቸውን ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር እጅግ ብዙ የሆኑ በጎ እሴቶችን የመናጃ መንደርደሪያ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር ጥላቻ ላይ የተመሠረቱ ወንጀሎችን መጥሪያ ነው፡፡ የጥላቻ ንግግር አድልኦና መገለልን ያመጣል፡፡ የጥላቻ ንግግር የአንድን ብሔር አባላት፣ የሃይማኖት ተከታዮች፣ ስደተኞችንና ሌሎች ቡድኖችን እንበለ ምክንያት በጭፍኑ እንዲጠሉ መንገድ ያለሰልሳል፡፡ የከፋው ደግሞ የዘር ማጥፋትን ወይንም ቡድን ጠረጋን ሊያስከትል ይችላል፡፡ በበርካታ አገሮችም ተከስቶ ነበር፡፡

በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ አይሁዶችን የጀርመን ናዚዎች ከማጥፋታቸው በፊት በርካታ አይሁዶች በጀርመንና ሌሎች አገሮች በተሻለ የኑሮ ደረጃ ይመሩ ስለነበር እንደ ባለጠጋ ጥገኛ ተሕዋስያን (Wealthy parasite) ተደርገው ተስለዋል፡፡ ጀርመኖች ደግሞ ከሌሎች የላቁ እንደሆኑ ራሳቸውን ቆጥረዋል፡፡ ሁቱዎች በረሮ እንጂ ቱትሲዎች ብሎ መጥራት አቁመው ነበር፡፡ ይህ እንግዲህ ጥላቻው በሕዝብ ደረጃ ከፍ ባለበት ወቅት ነው፡፡ አጠራሩንም አንዱ ቡድን በጅምላ የሌላውን ተቀብሎ አጽድቆታል ማለት ነው፡፡ ይህ ዓይነቱን ፍረጃም ይሁን ስያሜ መነሻው እውነት እንዲሆን አይጠበቅም፡፡ ሕዝቡም ሲጋራው በምክንያታዊነት አስቦና አሰላስሎ አይደለም፡፡ ምክንያታዊነት የግለሰብ ባህርይ እንጂ የሕዝብ አይደለችም፡፡ ቡድንን ጅምላዊነት ያጠቃዋል፡፡ እንደ ግለሰብ ሲታሰብ ወለፈንድና ሐሰት መሆኑን የምንረዳውን ነገር ከቡድናችን ጋር ስንቀላቀል ግን እንተወዋለን፡፡ የጥላቻ ንግግርም ቡድናዊ ቅርጽ ለመያዝ በእጅጉ የተጋለጠ ነው፡፡ ታሪክም ያሳየን ይኼንኑ ነው፡፡

በርካታ አገሮች ከራሳቸውም ገጠመኝም ይሁን ከሌሎች የታሪክ ጠባሳ በመማር የጥላቻ ንግግሮችን የሚከለክሉ ሕግጋት አውጥተዋል፤ ተግባራዊ ለማድረግም ተቋማትን አደራጅተዋል፡፡ የተለያዩ የሲቪክ ማኅበራትም የጥላቻ ንግግር ምንነቱን፣ ይዘቱን፣ መንስዔውን፣ መዘዙንና ሌሎችም ጭብጦች ላይ በመመርኮዝ ጥናት ያጠናሉ፤ የፍትሕ ተቋማትን ያሠለጥናሉ፤ ሕዝብን የማንቃት ሥራ ይፈጽማሉ፡፡ ብሎም ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ለመገንባት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ በዚህ መንገድ ብዙ ማኅበረሰቦች በሠላምና በመቻቻል እንዲኖሩ እያደረጉ ነው፡፡

ይህ ጽሑፍ የጥላቻ ንግግርን ምንነትና ከሌሎች ንግግሮች የሚለይበትን መንገዶች ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያን የሕግ ሁኔታ በመቃኘት የተጨማሪ ሕግ ወይንም ሥርዓት አስፈላጊነቱን በአንድ በኩል ከሕገ መንግሥቱ ጋር ለማጣጣም አስቸጋሪነቱን በሌላ በኩል ያሳያል፡፡ ይህን ለማድረግም ደግሞ ዓለም አቀፍ ስምምነቶችንና ድንጋጌዎች በመቃኘት እንዲሁም ከሌሎች አገሮች ሕግና አሠራር ጋር በማነፃፀር ያሉትን ክፍተቶች በመጠቆም ምን መደረግ እንዳለበት ጥቆማ ያቀርባል፡፡

የጥላቻ ንግግር ምንነትና መለያዎቹ

የጥላቻ ንግግርን ምንነት በተመለከት ቁርጥ ያለና ወጥ ብያኔ የለም፡፡ ይሁን እንጂ በርካታ ብያኔዎች የሚጋሯቸው ነጥቦች አሉ፡፡ በመሆኑም ማንኛውም የዘር ጥላቻን፣ የሌላ አገር ዜጋን ወይንም ስደተኛን በጭፍኑ መጥላትን፣ ፀረ ሴማዊነትን፣ ትዕግሥት አልባና አግላይ የሆነ ብሔርተኝነትን፣ ቁጥራቸው አነስተኛ የሆኑ ብሔረሰቦችን ሰበብ እየፈለጉ መገለል እንዲደርስባቸው የሚሰብኩ፣ የሚያሠራጩ፣ የሚያነሳሱ፣ የሚያበረታቱና ትክክል እንደሆኑ ለማስረዳት የሚደረጉ ጥረቶች የያዙ ቃላዊ ገለጻዎች፣ ጽሑፎች፣ ምሥሎችና ሥዕሎች፣ ቅርጻ ቅርጾች በሙሉ የጥላቻ ንግግር ይሰኛል፡፡ ስለሆነም ንግግር (Speech) የሚለው ቃል ድምፅን ብቻ የሚያመለክት አይደለም፡፡ በዚህ ጽሑፍም ውስጥ የጥላቻ ንግግር ሲባል ድምፅን፣ ጽሑፍን፣ ምሥልን፣ ቅርፃ ቅርፅን፣ የድምፅና ምሥል ቅንብሮች፣ ካርቱኖችን ያካትታል፡፡

የጥላቻ ንግግር አድራጊው የተለያዩ ቡድኖችን ባላቸው ማኅበራዊ መሠረትና አቋም ወይንም ርዕዮተ ዓለምም ላይ በመመርኮዝ እነዚህ ቡድኖችን በጥቅል ወይንም በተናጠል አባሎቻቸውን መገለልና መድልኦ እንዲደርስባቸው ማድረግ ነው፡፡ እንደ አይሁዶች፣ ቱትሲዎች፣ ጂፕሲዎች፣ የአውስትራሊያ ነባር ሕዝቦች ብሔርን መሠረት ሊያደርግ ይችላል፡፡ በበርካታ አውሮፓና ሌሎች አገሮችም እንደሚፈጸመው ሃይማኖታዊ መነሻ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ቀለም ላይ የተመሠረት ጥቁሮች ላይ እንደደረሰው ሊሆን ይችላል፡፡ የጥላቻ ንግግር ውጤቱ ከማኅበራዊ ተቋማት ኢኮኖሚያዊ መስክ እንዲገለሉ ወይንም እንዳይሳተፉ ማድረግ ሲከፋው እንዲገደሉ ሊያደርግ ይችላል፡፡

በአጭሩ ዘርን፣ ብሔርን፣ ሃይማኖትና እንደ ስደተኛነት ያሉ ማኅበራዊ መሠረቶችን ምርኩዝ አድርጎ የሚፈጸሙ ንግግሮች ከጥላቻ እስካልጸዱ ድረስ ወይንም ጥላቻ ካዘሉ የጥላቻ ንግግር ይባላሉ፡፡ ሕግም ሲወጣ ይኼንኑ ለመከልከል ነው፡፡ ተናጋሪውንም፣ ጥላቻን ያዘለ ንግግር ካደረገ የወንጀል ኃላፊነት እንዲኖርበት ያደርጋል፡፡ ይሁን እንጂ የጥላቻ ንግግርን በቀላሉ መለየት አዳጋች ነው፡፡ አዳጋችነቱ የንግግሩ ሰለባ ለሆነው አይደለም፤ ለሌላ ወገን እንጂ በማር የተለወሰ ንግግር ሆነው የሚቀርቡ አሉ፡፡ ለምሳሌ፣ ቅኔያዊ ንግግሮች ይሆኑና ስናነባቸው ወይንም ስንሰማቸው ወይንም ስናያቸው በአንዴ የማናስተውላቸው አሉ፡፡ እንዲህ ዓይነቶቹን፣ ከአውሮፓዊው የሕግ አተረጓጎም ልማድ የሚያሳየን በዚህ መጠን የንግግር ነፃነት መገደብ ተገቢ አይደለም በሚል ምክንያት የሚያስቀጡ አለመሆናቸውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ጥላቻ የሌላቸው መሆናቸውን አያሳይም፡፡

ስለጥላቻ ንግግር የአሜሪካ መንገድ

አሜሪካ ትልቅ ቦታ የምትሰጠው እሴት ቢኖር ነፃነት (Liberty) ነው፡፡ ነፃ ንግግር  ደግሞ አንድም የሰው ልጅ ህልውና አካል ሲሆን፣ በሌላ መልኩ ደግሞ ነፃነትና ዴሞክራሲ ያለ ነፃ ንግግር ምንጊዜም ጎደሎ እንደሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የአሜሪካ መርህ ነፃነትን ራሱን የሚያጠፋ እስካልሆነ ድረስ ንግግር ላይ ገደብ አይኖርም፡፡ በተለይም ደግሞ የንግግሩ ይዘት ጥላቻን ያዘለ ነው በሚል ሰበብ ብቻ ክልከላ የለም፡፡ ገደብ የሚደረገው ንግግሩ የሚደረገበትን ዐውድ በማየት ይሆናል፡፡ የተደረገው ንግግር የኃይል ድርጊት ላይ የተመሠረተ ሕገወጥ ድርጊት ለማስነሳት ቅርብ ከሆነ ሊገደብ ይችላል፡፡ ካልሆነ ንግግርን መልሶ በንግግር በመጋፈጥ እንጂ በመገደብና በማፈን ዴሞክራሲ አይሰፍንም የሚል ነው የአሜሪካ አካሄድ፡፡

የብዙኃኑ መንገድ

በርካታ አገሮች ከአሜሪካ የተለየ መንገድ ነው የሚከተሉት አገሮች ለተለያየ እሴት ቅድሚያ ይሰጣሉ፡፡ የእሴቶቻቸው መነሻ ደግሞ የራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ነው፡፡ ለአንዳንዶች እኩልት፣ ለሌሎች ሰብዓዊ ክብር ወይንም ተከባብሮና ተፈቃቅዶ መኖር ወይንም የእነዚህ ቅይጥ ሊሆን ይችላል፡፡  እኩልነትን የሚያስቀድሙት አንድን ግለሰብ ከሌላ ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ስለግለሰቡ ነጠላ ሕይወት ወይንም ምርጫ ሳይሆን ከሌሎች ጋር የሚኖረው መስተጋብር ነው ዋና ማጠንጠኛቸው፡፡ ሰብዓዊ ክብርን የሚመርጡ ደግሞ ማንም ሰው የሌላውን ስም ሳያጎድፍ፣ ሳያንኳስስ፣ ሳያጣጥል፣ ሳያገልል ወዘተ. እንዲኖርና መከባበር እንዲሰፍን ይመርጣሉ፡፡ በቡድኖች መካከል ተከባብሮና ተፈቃቅዶ መኖርን የሚመርጡም አሉ፡፡ ለእነዚህ እሴቶች ከፍተኛ ቦታ ለሚሰጡ አገሮች ነፃ ንግግር ለእነዚህ እሴቶች ማጎልመሻ እንደምትሆን ይጠበቃል፡፡ ስለሆነም ሰብዓዊ ክብርን የሚነካ፣ ተቻችሎና ተፈቃቅዶ የሚኖርን ማኅበረሰብ እንዳይኖር እንከን የሚሆን፣ በማኅበረሰብ መከካል ያለው የባህል ሥሪት አንዱ ከአንዱ የሚበልጥ እንደሆነ የሚሰብክ ንግግር እንዲኖር አይፈቀድም ወይንም አይበረታታም፡፡ የኢትዮጵያንም ሕገ መንግሥት ስናጤነው ትልቁ እሴቱ የግለሰቦች ነፃነት ላይ የተመረኮዘና ግለሰብ ዜጎችን ነፃነት ሳይሆን የብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እኩልነትና ተከባብሮና ተፈቃቅዶ መኖርን የመረጠ ስለሆነ ነፃ ንግግር ወይንም ሐሳብን በነፃነት መግለጽ ለእነዚህ እሴቶች ተገዥ መሆኗ ግድ ነው፡፡ የአውሮፓውያኑም መንገድ ይኼው ነው፡፡

ከአሜሪካን ውጭ ያሉት አገሮች በሙሉ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል አድርገዋል ማለት አይደለም፤ ያደረጉትም ቢሆኑ ተመሳሳይ ይዘት የላቸውም፡፡ ወንጀል ያደረጉበት ነባራዊ ምክንያትም ይለያያል፡፡ ወንጀል እንዲሆን በተለያዩ ምሁራንም የሚቀርበው ክርክር እንዲሁ ወጥ አይደለም፡፡ ወንጀል የሆነባቸውም አገሮችም ሕጎቻቸውን እንዲሰረዙ የሚቀርብ ክርክርና ውትወታ አለ፡፡ ኢትዮጵያም ወደፊት ይኼንን የሚመለከት ሕግ የምታወጣ ከሆነ ትርፍና ኪሳራዎቹን ለመለየት በሁለቱም ጎራ ከሚነሱት መከራከሪያዎች የተወሰኑትን ብቻ አቀርባለሁ፡፡

ንግግር፣ የጥላቻም ቢሆን ወንጀል መሆን የለበትም ባዮች

የመጀመሪያው መከራከሪያቸው ንግግርን ወንጀል በማድረግ ከሚገኘው ጥቅም ይልቅ፣ ጥላቻ ባለው ንግግር የሚፈጠረውን ጉዳት መታገስ የሚያስገኘው ይበልጣል የሚል ነው፡፡ ንግግርን ማፈን በርካታ መብቶችን እንዲጣበቡ ያደርጋል፣ በርም ይከፍታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ማንኛውም መጥፎ ሐሳብ የሚጠፋውና ማምከኛ ሊሆን የሚችል ተቃራኒ ሐሳብ በማቅረብ እንጂ ንግግሩን በመከልከል አይደለም፤ መንግሥትም የምንናገረውን ነገር ይዘቱን ሊመርጥልን አይገባም፤ ግለሰቦችም ክፉን ከበጎ ለይቶ የማወቅ አቅምም ችሎታም ስላላቸው ይኼንኑ ነፃነታቸውን ማክበር ተገቢ ነው፡፡ ሕግም ቢሆን ክፉ የማሰብንና የመናገርን ባሕርይን ሊቀይር አይችልም፤ ስለሆነም ወንጀል ማድረጉ ፋይዳ ቢስ ነው ይላሉ፡፡

የጥላቻ ንግግር ይከልከል የሚሉት መከራከሪያዎች

ጥላቻን ያዘለ ንግግር በብዙ ምክንያት ጠቃሚ አይደለም፣ አስጸያፊ ነው ይላሉ፡፡ ለዚህ ከሚያቀርቡት ምክንያቶች ውስጥ የሚከተሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የንግግሩ ሰለባ የሚሆኑትን የአንድ ቡድን አባላት እንደ ጠላት እንዲቆጠሩ ያደርጋል፤ ለብዙ ነገሮች ተጠርጣሪዎች እንዲሆኑ ያመቻቻል፡፡ ሌላው መከራከሪያ ደግሞ ከሌሎች የማኅበረሰብ አባላት በእኩልነት አይታዩም፡፡ ለምሳሌ እንደ ተገንጣይ የሚሳሉ ከሆነ የመገንጠል ፍላጎት ከሌላቸው ጋር እኩል ተደርገው አይታዩም፡፡ ከዚህ ሌላ ደግሞ፣ በማኅበራዊ አቋማቸው ዝቅ ተደርገው እንዲታዩ ያደርጋል፡፡ ከሌሎች የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር  የተረጋጋና ቅንነት የተሞላበት ግንኙነት እንዳይኖር እንቅፋት ይፈጥራል፡፡ በግለሰቦችና በቡድኖች መካከልም ጥርጣሬና ውጥረት እንዲሰፍን ያደርጋል፡፡ አንዱ የሃይማኖት ተከታይ ወይንም የብሔር አባላት የበለጠ ለአገር አሳቢ ሌላውን ጠላት አድርጎ የመሳል አዝማሚያን ይፈጥራል፡፡ ችሎታቸውንና አቅማቸውን በተገቢው ሁኔታ እንዳይጠቀሙ ያደርጋል፤ የተወሰኑ ሰዎችን ባሕርይ ለጠቅላላው የማሳደግ አዝማሚያን ስለሚያበረታታ የቡድኑን አባላት በሙሉ ተጠቂና ሰለባ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ በመሆኑም ጥላቻ አዘል ንግግር መከልከል አለበት ይላሉ፡፡

የንግግር ነፃነት የሚገደብባቸው ምክንያቶች

በሕገ መንግሥታችን አንቀጽ 29(6) ላይ በማያሻማና በግልጽ ቋንቋ እንደተገለጸው ሐሳብን በፕሬስና በማናቸውም መገናኛ ብዙኃን ማንኛውም ሰው ሲገልጽ የሐሳቡ ይዘት ምንም ይሁን ምን፣ ሐሳቡ በመገለጹ የሚያስከትለው ውጤት ምንም ይሁን ምን፣ መከልከል አይቻልም፡፡ ከዚህ የምንረዳው አንዱ ነጥብ አንድን ቡድን (ምሳሌ ብሔር) ባህል የሚተች ይዘት ያለው ጽሑፍ ማተም ወይንም ማሠራጨት አይቻልም የሚል ሕግ ሊኖር አይችልም፡፡ በመሆኑም ይዘቱን መሠረት በማድረግ ሐሳብን የመግለጽ ክልከላ አይኖርም ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንድ ጽሑፍ ታትሞ በመውጣቱ የመንግሥትን ተአማኒነት ያሳጣል በማለት መከልከል አይቻልም፡፡ ጠንከር ስናደርገው ደግሞ አንድ ጽሑፍ መውጣቱ አንድን ብሔር ከሌላው ጋር ሊያጋጭ ይችላል በሚል ምክንያት ክልከላ አይኖርም፡፡ የሚከለክል ሕግም ማውጣትም አይቻልም፡፡ ይህ ደግሞ የሚያስከትለውን ውጤት በማሰብ ብቻ መገደብ አይቻልም ማለት ነው፡፡ ወንጀል ማድረግማ ፈጽሞ አይታሰብም፡፡

በሕግ የሚገደብባቸው ምክንያቶች ‘የወጣቶችን ደኅንነት የሚያናጉ፣ የግለሰብን መብት የሚጥሱና ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ የአደባባይ መግለጫዎችን ማድረግ፣ የጦርነት ቅስቀሳ ማድረግ’ ብቻ ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከአራቱ ውጪ በሌሎች ምክንያት ፈጽሞ ሐሳብን በነፃነት በማናቸውም የፕሬስ ውጤቶችም ይሁን በኤሌክትሮኒክ መንገድ እንዳይገለጹ መከልከል ወይንም ወንጀል ማድረግ ፈጽሞ ሕገ መንግሥቱን መጣስ ነው፡፡ ከላይ ተገለጹትን ግቦች ለማሳካት ሲባል ብቻ ነው የንግግርን ነፃነት መገደብ የሚቻለው፡፡ ጥላቻ ያዘሉ ንግግሮችን ለመገደብ መነሻዎቹ እነዚህ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ አንፃር ሕጉ ቢወጣ፣ ሕገ መንግሥታዊ ይሆን ዘንድ ንግግሮቹ የጦር ፕሮፓጋንዳ፣ የወጣቶችን አስተዳደግ ላይ ችግር የሚፈጥሩ ከሆነ፣ ወይንም የግለሰብን መብት ወይንም ክብርና ሰብዓዊ ክብር የሚቃረኑ ንግግሮችን ብቻ ነው በጥላቻ ንግግርነት ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉት፡፡ ከእነዚህ ውስጥ ሕገ መንግሥታዊ ለማድረግ የሚቻለው በአንዱ ብቻ ነው፡፡ የአንድን ግለሰብ ብሔሩን፣ ሃይማኖቱን፣ ዘሩን ወይንም ሌላ ማኅበራዊ መገለጫን መሠረት አድርጎ የሰውን ክብር (Individual Honour) ወይንም ሰብዓዊ ክብርን (Human Dignity) የሚጻረሩ ንግግሮችን አስቀድሞ ሕግ በማውጣት መገደብ ይቻላል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ በመነሳት በሥራ ላይ ያሉትን ሌሎች ሕጎችን እንቃኝ፡፡

ሃይማኖትን፣ ፖለቲካን፣ ዘርን (ብሔርን አይልም) መሠረት ያደረገ በሐሰት የሚያነሳሳ፣ የሚያጥላላ፣ የሚስፋፋ ማናቸውም ድርጊት ወንጀል እንደሆነ በወንጀል ሕጉ በግልጽ አለ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም አንድ ሃይማኖት ጋር የተያያዙ ማናቸውንም ጸያፍና የአማኙን ስሜት የሚነካ ድርጊት የፈጸመ ሰው በደንብ መተላለፍ ሊቀጣ የሚቻልበት ሕግ አለ፡፡ ሕዝብን በተለያዬ መንገድ ወደ ግጭትና አመጽ የሚመሩ ንግግሮችን ማድረግ ወንጀል እንደሆነ በመደበኛው የወንጀል ሕግም ይሁን የኮምፒውተር ወንጀሎችን ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ላይ አሉ፡፡ እንዲሁም በርካታ ሕጎች ብሔርን፣ ዘርን፣ ሃይማኖትን፣ ጾታን፣ የፖለቲካ አቋምን መሠረት አድርጎ አድልኦ መፈጸም እንደማይቻል ተደንግጓል፡፡ ይህ እንግዲህ በተወሰነ መልኩ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል መሆናቸውንና በሌሎች አስተዳደራዊም ይሁን ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ብሔርን ወይንም ሃይማኖትን መሠረት አድርጎ በሚኖር ያልተገለጠ ውስጣዊ ጥላቻ ቢኖር እንኳን አድልኦ ማድረግ የተከለከለ መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በርካታ ዓለም አቀፍ ሰነዶችን ኢትዮጵያ ስላጸደቀች እነዚህ ስምምነቶችም የዘር፣ የብሔር፣ የሃይማኖትና ሌሎች ነገሮችን ታሳቢ ያደረገ ማዳላት ስለሚከለክሉ ያው የአገራችን ሕጎች ናቸውና እነሱም አሉን፡፡ ነገር ግን ክልከላው የወንጀል ስላልሆነ በወንጀል አያስቀጡም፡፡ በመሆኑም እነዚህ አገራዊም ይሁኑ ዓለም አቀፋዊ ሕጎች የንግግር ነፃነት ወይንም መብት ፍጹማዊ ስላልሆነ በምን ሁኔታ እንደሚገደቡ፣ ከገደቡ ሲታለፍም ሊያስቀጡ መቻላቸውንም ነው ለመግለጽ የተሞከረው፡፡

ሕገ መንግሥቱን የሚገዳደሩ ሕጎች

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሕገ መንግሥቱ ከጸደቀ ወዲህ ከላይ ከገለጽናቸው መሥፈርቶች ጋር የማይሄዱ በርካታ ድርጊቶች ወንጀል ሆነዋል፡፡ ለምሳሌ የመንግሥትን ስም ማጥፋት፣ መንግሥትን መስደብ፣ አገራዊ ዓርማንና ባንዲራን መስደብ፣ ሌሎች አገሮችን፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትን፣ ዓርማዎቻቸውንና ባንዲራዎቻቸውን መስደብና ስም ማጥፋትና የአገርን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉ ወታደራዊና ኢኮኖሚያዊ መረጃዎች ለጠላት አገር አሳልፎ መስጠት ወዘተ፡፡ በዓለም ላይ በሕገ መንግሥቷ የአገር ደኅንነትን አደጋ ላይ የሚጥል መረጃም ቢሆን እንኳን ያልከለከለች ኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን አትቀርም፡፡ ይሁን እንጂ ሕገ መንግሥቱ ላይ ከሰፈረው በእጅጉ በራቀና በተቃረነ ሁኔታ ባንዲራን መስደብ፣ የመንግሥት ስም ማጥፋት የመሳሰሉትን ወንጀል ሆነዋል፡፡ በየትኛውም አገር ደግሞ የአገሮችን የደኅንነት ሁኔታ አደጋ ላይ የሚጥል መረጃን ለጠላት መንገርን ወይንም መግለጽን መከልከል ሕገ መንግሥታዊ ነው፡፡

 በዚህ ረገድ ሕገ መንግሥታችን ከየትኛውም ዓለም አቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ሰነድ ይሻላል፡፡ የብዙዎቹ መለኪያዎች በሕግ መደንገግና ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ አስፈላጊ መሆን ሲሆኑ የሁለተኛውን መሥፈርት አስፈላጊነቱን የመወሰን በአብዛኛው የተተወው ለሚመለከታቸው አገሮች ነው፡፡ እነዚህ መሥፈርቶች፣ እንደፈለጉ ለመፈንጠዝ የተመቹ ሲሆኑ በተቃራኒው የእኛ ሕገ መንግሥት የመረጣቸው ደግሞ ጥብቅ እንዲሁም ለመለካት የማያስቸግሩ መሥፈርቶችን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ከላይ እንዳየነው መንግሥት አሁን ባለው አሠራር ከቀጠለ የጥላቻ ንግግርን በተለይ ብሔርን ከብሔር፣ አንድ የሃይማኖት ተከታይን ከሌላው ለማጋጨት የሚያነሳሱ፣ ወይንም ጥላቻን በቡድኑ ላይ የሚነዙ ንግግሮች መከልከል አይሳነውም፡፡ ብዙ ያልተሳኑትን ሕጎች ዓይተናል፡፡

የተጨማሪ ሕግ ወይንም ሥርዓት አስፈላጊነት

ኢትዮጵያ ከአሁን በፊት ስለሰብዓዊ መብት አፈጻጸሟ ሪፖርት ስታቀርብ በተሰጣት ግበረ መልስ ውስጥ የጥላቻ ንግግርን ወንጀል ማድረግ አንዱ ነበር፡፡ በበጎም ተቀብላው ነበር፤ ምንም እንኳን ሕግ ማውጣቱ ላይ እመርታ ባታሳይም፡፡ ስለምን ሕግ ያስፈልገናል ብንል በርካታ ምክንያቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡ የጉዳዩ አሳሳቢነትም መንግሥትም የተረዳው ይመስላል፡፡ በቴሌቪዥን የተለያዩ ፕሮግራሞች ሲቀርቡ ተመልክተናል፡፡ በተለይ ደግሞ በማኅበራዊ ሚዲያ ስለሚተላለፉና ስለሚሠራጩ የጥላቻ ንግግሮች፡፡ ይሁን እንጂ ይህንን ከሚያስፋፉት ውስጥ አንደኛው መንግሥት ራሱ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ አንዱን የመንግሥት አድራጎት ብቻ እንመልከት፡፡ እሱም መንግሥታዊ ፍረጃን ይመለከታል፡፡ እርግጥ ነው የአገራችን መለያ ከሆነ ቆይቷል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የዓረብ ቅጥረኞች፣ በደርግ ገንጣይ፣ አስገንጣይና ወንበዴዎች፣ በኢሕአዴግ ደግሞ ነፍጠኛ፣ ትምክህተኛና ጠባብ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማው አሁን ያለው የአገራችንን ሁኔታ ስለሆነ ጠባብ፣ ትምክህተኛና ነፍጠኛ የሚሉትን ቃላት ብቻ እንደ ምሳሌ ይወስዳል፡፡ ስለሆነም እነዚህ ስያሜዎች ከጥላቻ ንግግር አንፃር በአጭሩ ለማየት ይሞክራል፡፡ የሁለቱን ትርጉም ኢሕአዴግ ካወጣቸው ሰነዶች በመነሳት እናስቀምቸጣው፡፡

ጠባብ ብሔርተኝነት ወይንም ጠባቦች የሚባሉት ሌሎች ብሔር፣ ብሔረሰቦችን በጭፍን በጠላትነት የሚያዩ ሲሆኑ፣ አብሮ የመኖር ጥያቄን ፈጽሞ የማስተናገድ ፍላጎት ተደርገው ይቆጠራሉ፡፡ ትምክህተኛ ብሔርተኝነት ወይንም ትምክህተኞች የሚባሉት አመክንዮታዊነት በጎደለውና ከልክ ባለፈ ሁኔታ የራስን ብሔር፣ ቋንቋና ባህል ከሁሉም በላይ ልዕልና እንዳለው የሚያምን፣ ከዚህ ባለፈም ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የራሳቸውን ማንነት በመካድና በመተው ትምክህተኛውን ብሔር የበላይ ነው ብለው እንዲያምኑና ያንን ማንነት እንዲላበሱ የሚፈልግ የብሔርተኝነት ዘውግ ነው፡፡

ከእነዚህ የብሔርተኝነት ዓይነቶች ኢሕአዴግ የሚዋጋቸው እንደሆኑ ይገልጻል፡፡ በዋናነት እነዚህ የብሔርተኝነት ዓይነቶች ለሁለት የብሔር የተሰጡ ስያሜዎች እንደ ይታወቃል፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ተበደለ የሚሉትን ጠባብ፣ የአማራ ሕዝብ በዚህ በዚህ ቦታ ችግር እየደረሰበት ነው የሚሉትን ትምክህተኛ እያሉ መፈረጅ የዕለት ተዕለት ሥራ ሆኗል፡፡ እንዲህ ዓይነት የመፈራረጃ ሐሳቦች ግልጽና የማያወላዱ መለያ ባሕርያት ስለሌላቸው ከመሬት ተነሥቶ ለመኮነንና ለመውቀስ ቀላል ናቸው፡፡ እነዚህ ፍረጃዎች፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚነኩ መሆናቸው የሚወላዳ አይደለም፡፡ የሰፊነት ወይንም መለኪያ በሌለበት የብሔሩን መብት የጠየቀን ኦሮሞ ሁሉ ጠባብ ማለት ዞሮ ዞሮ ኦሮሞ ስለሆነ የሚመጣ ንግግር ነው፡፡ የተለያዩ ዜግነትን መሠረት ያደረጉ መብቶች የሚጠይቅን  አማራ ሁሉ ትምክህተኛ ማለት አማራ ከመሆኑ የሚመነጭ ነው፡፡ ስለሆነም ጥላቻን የሚሳድግና የሚበረታታ ነው፡፡ ይህ ስለመሆኑ ለማረጋገጥ ደግሞ ኦሮሞን በአማራ ዘንድ እንዴት እንዲሳል እንደተደረገ ማወቅ ይበቃል፡፡ አማራም በኦሮሞ ዘንድ እንዲሳል የተደረገውም ተመሳሳይ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን አካሄድ ለማስቀረት እነዚህን ወደ ብሔር ያጋደሉ ፍረጃዎችን እንደ ጥላቻ ንግግር በመውሰድ ወንጀል ብናደርጋቸው የተሻለ ይሆናል፡፡ ዋነኛው የጥላቻ ንግግር ፈጻሚ መንግሥት ስለሆነ ማለት ነው፡፡ ምናልባት የጥላቻ ንግግርን ወንጀል እንዲደረግ አስተያየት የሰጡት አገሮች ምንን መሠረት አድርገው እንደሆነ ባይታወቅም ቅሉ ጠባቦች፣ ትምክህተኞችና ነፍጠኞች እያሉ የሰብዓዊ ክብርን የሚነካና የሚያሸማቅቅ ነው፡፡ ከላይ የጥላቻ ንግግር ወንጀል እንዲሆን ከሚሟገቱት ምሁራን ክርክሮች ጋር ስናስተያያቸው ተመሳሳይ ውጤት ማምጣቸው አይቀሬ ነው፡፡

የመንግሥት እንዲህ ዓይነት ንግግሮችን መጠቀሙን መተው የጥላቻ ንግግር ወንጀል በማደረግ የሚገኘውን ግብ ለማሳካት ይረዳል፡፡ ብሎም ሌሎች ግለሰቦችምና ብሔሮች የሚኖራቸውን ግንኙነት የተሻለ ያደርጋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ የተጻፈውን አንድ የፖለቲካ ማኅበረሰብ ለመገንባት ይረዳል፡፡ በተጨማሪም የጥላቻ ንግግር ወንጀል ማድረግ ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን እንደታየው መንግሥት የተለየ ሐሳብ ያላቸውን ለማፈን ከሆነ ግን የበለጠ ቅራኔ ከመፍጠር የሚዘል ፋይዳ አይኖረውም፡፡ የንግግር ነፃነት ላይ ገድብ የሚጣለው ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ደግሞ መቻቻልና ብዙኃነት ከመለያ ባህርያቱ መካከል ናቸው፡፡ መቻቻልን የሚያጠፋና ብዙኃነትን የሚቃረንን ንግግር ደግሞ ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ ጠንቅ ነው፡፡ እንዲህ ዓይነት ንግግሮችን መታገስ ደግሞ ውሎ አድሮ ራሱን ዴሞክራሲን ያጠፋል፡፡ ስለሆነም ዴሞክራሲን ራሱን ከጥፋት ለመታደግ የዴሞክራሲ መገለጫ የሆነው የንግግር ነፃነት ላይ ገደብ እንዲኖር ግድ ይላል ማለት ነው፡፡

ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ግንባታ የሚያስፈልጉ ነገሮች ደግሞ ከአገር አገር ሊለያዩ ይችላሉ፡፡ ፈረንሳይና ቱርክ ሃይማኖታዊ የሆኑ ጉዳዮች ወደ መንግሥታዊ ተቋማት ብቅ ማለትን ለዴሞክራሲ እንደ ጠንቅ ያዩታል፡፡ ጀርመን የናዚና የፋሽስት አዝማሚያ፣ በስፔን ደግሞ መገንጠልን የሚያነሳሳ ወይም የሚደግፍ፣ በእስራኤል የአገሪቱን መኖር የማይቀበል ወዘተ. ለዴሞክራሲያዊ ማኅበረሰብ ፀር እንደሆነ ይቆጠራል፡፡ ይሁንና እነዚህን ጉዳዮች አስቀድሞ በሕግ ማሳወቅን ይጠይቃል፡፡

ለማጠቃለል አገራዊ አንድነት ለማጠናከር በተለይ ብሔር ላይ የተመሠረቱ የጥላቻ ንግግሮችን ወንጀል ቢሆኑ ይጠቅማል፡፡ ከሌሎች አገሮች ልምድ ስናስተያየው በቂ ሕግ የለንም፡፡ መንግሥትም እንዲሁ ለጥላቻ ንግግር መሪነቱን ባይዝ ጥሩ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁሉንም የጥላቻ ንግግሮች በፍርድ ቤት ብቻ እንዲታዩ ማድረግ የበለጠ የብሔርና የሃይማኖት ብጥብጥ ሊያስነሳ ስለሚችል በርካታ አገሮች እንደሚያደርጉት ንግግሮቹ የተላለፉበትን ሚዲያ መነሻ በማድረግ ቅድሚያ በእርቅና በሽምግልና ሊያልቁ የሚችሉበትን ዘዴ መሻት ነው፡፡ አዲሱ ዘመን የጥላቻ ንግግር የሚቀርበት ይሁንልን፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ቅጥ አልባ ቅጣቶች በኢትዮጵያ ሕጎች    
ሕዝባዊ የግዴታ አገልግሎት መስጠት (የግዴታ ሥራ) እንደ ወንጀል ቅጣት

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 14 July 2024