Font size: +
11 minutes reading time (2287 words)

የማታለል ወንጀል ከእምንት ማጉደል ወንጀል በምን ይለያል? በድንጋጌዎቹ የወንጀል ክስ ለማቅረብ በመሰረታዊነት መሟላት ያለባቸው የማስረጃ አይነቶችስ ምንድናቸው?

በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን በፍርድ ቤት በመክሰስ ለማስቀጣት በቂና አሳማኝ በሆነ መልኩ ማስረጃ አቅርቦ ማስረዳት በዐ/ህግ በኩል ይጠበቃል፡፡ የተለያየ አይነት ማስረጃን የመመዘን መርህ በወንጀል ክስ ለመክሰስና ጥፋተኛ ለማለት በስራ ላይ የሚውል ቢሆንም በጥቅሉ ሶስት አይነት የማስረጃ አመዛዘን መርህ በስፋት ይታያል፡፡

የመጀመሪያው የማስረጃ አመዛዘን መርህ ዐቃቤ ህግ የሚያቀርበው ማስረጃ በይዘቱ የተፈፀመውን ወንጀል ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በፀዳ መልኩ ማስረዳት የሚጠበቅበት መሆኑን የሚያስገድድ ሲሆን በዚህ የማስረጃ አመዛዘን መርህ አግባብ የዐ/ህግ የማስረዳት ግዴታ ከፍ ባለ መልኩ ተከሳሽ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በፀዳ መልኩ ማስረዳትን ይጠብቃል ፡፡ሁለተኛው የማስረጃ ምዘና መርህ ተከሳሹ ላይ የሚቀርበው የማስረጃ አይነት ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመስራቱ በቂና አሳማኝ በሆነ መልኩ ማስረዳትን የሚጠብቅ ነው፡፡ይህ አይነቱ መመዘኛ መንገድ ከአንደኛው መመዘኛ አነስ ያለ ግዴታ በዐ/ህግ ላይ የሚጥል ሲሆን ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመስራቱ ምንም አይነት ቅጣት ጥርጣሬ የሚጥል ማስረጃ ከማቅረብ ባነሰ አጠራጣሪ ነገር ቢኖርም እንኳ ያለው ማስረጃ ተከሳሹ ወንጀሉን ሰርቷል ለማለት በቂና አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብን እንደግዴታ የሚጥል ነው፡፡ ሶስተኛው የማስረጃ ምዘና መርህ ተመጣጣኝ የማስረጃ መርህ የሚባለው ሲሆን ይህ መመዘኛ መንገድ ከላይ ከተመለከቱት በላላ መልኩ የሚቀርበው ማስረጃ የሁለቱ ወገኖችን ማስረጃ በንፅፅር ሲታይ የተሻለ ያስረዳውን መቅጣት ወይም ነፃ መልቀቅን መሰረት የሚያደርግ ነው፡፡  

ተከሳሽ በፍርድ ቤት ቅጣት ጥፋተኛ ተብሎ እስኪወሰንበት ጊዜ ድረስ ንፁህ ሆኖ የሚገመት እንደመሆኑ በክስ መክሰስ ሂደት ተከሳሹ ወንጀሉን ስለመፈፀሙ በቂና አሳማኝ ማስረጃ የመስበስብና የመክሰስ ግዴታ በዐ/ህግ ላይ የሚያርፍ ይሆናል፡፡ለእያንዳንዱ ወንጀል ምን አይነት ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል የሚለው እንደወንጀሉ አይነት፣ እንደ ተጠርጣሪው ተግባር የሚለያይ ቢሆንም በስፋት በሚያጋጥሙ የወንጀል ተግባራት ላይ ምን አይነት ማስረጃ ቢቀርብ በቂና አሳማኝ ነው የሚለውን መነሻዊ ምልከታ ማድረግና ጠንካራ የውይይት ሀሳቦችን ማንሳት ጥራት ያለው ምርመራ ለማድረግ፣በክስ ሂደት የሚያጋጥሙ በቂ ማስረጃ የማይቀርብባቸውን ክሶች ለማስቀረት ፣የተሻለ ጥራት ያለው ክስ ለመመስረት የሚረዳ ይሆናል፡፡ይህ ፅሁፍም መሰረት የሚያደርገው በተግባር በስፋት ችግር እየገጠመ ካሉ ወንጀሎች መሀከል የተወሰኑትን በመለየት ሰፊ ውይይት ለማድረግ በሚል ሲሆን በዚህ ፅሁፍ ከማታለልና ከእምነት ማጉደል ጋር በተያያዙ እየተነሱ ያሉ ችግሮችን በወፍ በረር ቅኝት ለመዳሰስ የሚሞከር ይሆናል፡፡

1.በንብረት ላይ የሚፈፀም ወንጀል በጠቅላላው

የማታለልም ሆነ የእምነት ማጉደል ወንጀሎች በወንጀል ህጉ በመፀሀፍ ስድስት ውስጥ በንብረት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች ውስጥ ተካተው ይገኛል፡፡መፀሀፉ በሁለት ትላልቅ ርዕሶች ስር ስድስት ምዕራፎችን ይዞ የተዋቀረ ነው፡፡በመጀመሪያው ርዕስ ውስጥ ካሉት ሶስት ምዕራፎች ውስጥ በሁለተኛው ምዕራፍ በሆነው በንብረት ላይ በሚፈፀሙ ወንጀሎች በክፍል አንድ በተንቀሳቃሽ ንብረት ላይ በሚፈፀም ወንጀል ክፍል ውስጥ 19 የተለያዩ ወንጀሎች የሚገኙ ሲሆን በዚህ ክፍል ውስጥ የእምነት ማጉደል ወንጀልም ተካቶ ይገኛል፡፡

በምዕራፍ ሶስት ከተመለከቱ በንብረት መብቶች ላይ በሚፈፀመው ወንጀሎች በክፍል አንድ ላይ ማታለልን የተመለከቱ ድንጋጌዎች የተሸፈኑ ሲሆን ክፍሉ በውስጡ 13 አንቀፆችን ይዟል፡፡ከነዚህ አንቀፆች ውስጥ ለዚህ ፅሁፍ አላማ ሲባል በተደጋጋሚ በስራ ላይ የሚያጋጥሙን ላይ ብቻ ትኩረት በማድረግ ምልከታ ይደረጋል፡፡

1.1.አንቀፅ 692 ፡-አታላይነት

አንቀፅ 692 ላይ የተመለከተው የማታለል ወንጀል በስፋት በአዲስ አበባ የሚፈፀም ወንጀል ሲሆን በድንጋጌው መሰረት ክስ ለመመስረት ህጉ በመስፈርትነት ስላስቀመጣቸው ማቋቋሚያዎች፣ለእያንዳንዱ በህጉ ለተቀመጡ ማቋቋሚያዎች ስለሚቀርቡ ማስረጃዎች ማሳያ የሚሆኑ የክስና የምርመራ መዛግብትን በማመላከት ምልከታ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

በአንቀፁ የአታላይነት ወንጀልን ለማቋቋም አራት መሰረታዊ ማቋቋሚያዎች ያሉ ሲሆን

1ኛ) ተከሳሽ ሆን ብሎ የማይገባ ብልፅግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት በማሰብ አሳሳች የሆኑ ነገሮችን በመናገር ፣የራሱን ማንነት ወይም ሁኔታ በመሰወር ወይም መግለፅ የሚገባውን ነገር በመደበቅ ወይም የሌላውን ሰው የተሳሳተ እምነት ወይም ግምት በመጠቀም ፣በማድረግም ሆነ ባለማድረግ የመግለፅ ተግባር ከፈፀመ

2ኛ) በዚህ ድርጊት የተነሳ ተበዳዩ ከተታለለ ወይም በአጥፊው የተገለፀውን አምኖ ሊቀበል ይገባዋል፡፡

3ኛ) በሀሰት የተገለፀውን በማመን የፈፀመው ተግባር መኖር አለበት

4ኛ) እንደዚሁም ተበዳዩ በመታለሉ የተነሳ የራሱ ወይም ሶስተኛ ወገን ያጣው የገንዘብ ጥቅም መኖር መቻል አለበት፡፡

እነዚህ በህጉ በመስፈርትነት የተመለከቱት የህግ ማቋቋሚያዎች ስለመከሰታቸው በማስረጃ በበቂና በአሳማኝ በሆነ ሁኔታ ከተረጋገጠ ተጠርጣሪው ላይ ከስ ማቅረብ ይገባል፡፡በተራ ቁጥር አንድ ላይ የተመለከተውን መስፈርት ለማስረዳት በተለይም አሳሳች የሆኑ ንግግሮች ከሆኑ ከግል ተበዳይ ባለፈ ሌሎች ሰዎች ንግግሩን መስማት የሚገባቸው ሲሆን ንግግሩ አሳሳች ስለመሆን አለመሆኑ እንደሁኔታው በአመዛዛኝ ሰው እይታ እየታዩ ወይም ከግል ተበዳዩ ነባራዊ ሁኔታ አንፃር የሚመዘኑ ይሆናል ፣አሳሳች ንግግር የተናገረው ተጠርጣሪ የራሱን ስም፣የስራ ሁኔታና መሰል ማንነትን በመቀየር የተገለፀ ከሆነ እነዚህን ኩነቶች ሊያስረዱ የሚችሉ የሰነድ ወይም የሰው ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል፡፡ሌሎች በህጉ የተመለከቱ ሁኔታዎችንም ቢሆን እንደሁኔታው በሰውና በሰነድ ማስረጃ ሊረጋገጡ የሚገባቸው ናቸው፡፡በሁለተኛነት የተመለከተው የተበዳይ መታለል ወይም ተከሳሹ የተናገረውን የማታለያ ተግባራትን አምኖ ተቀብሏል ለማለት በተራ ቁጥር ሶስትና አራት ላይ የተመለከቱትን ተግባራት ከፈፀመ ነው፡፡ይህም የሚሆነው ከተታለለ በመታለሉ የተነሳ በንብረት ጥቅሙ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተግባር ማድረግ ይኖርበታል፡፡ለተግባራቱ ከሚቀርቡ ማስረጃዎች መሀከል በመታለሉ የተነሳ በንብረት ጥቅሙ ላይ ጉዳት የሚያደርስ ተግባር መፈፀሙን የተመለከቱ ሰዎች ወይም ከባንክ የሚመጡ የሰነድ ማስረጃዎችና ሌሎች ማስረጃዎች ሊቀርቡ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡የሚቀርቡ ማስረጃዎች ከጉዳይ ጉዳይ የሚለያይ በመሆኑ ቁርጥ ባለ ሁኔታ ለመግለፅ አዳጋች ይሆናል፡፡በተግባር ከሚያጋጥሙ ጉዳዮች መሀከል፡፡

ሀ.በከሳሽ ዐቃቤ ህግና በተከሳሽ አየለ (ለዚህ ፅሁፍ አላማ ሲባል ስሙ የተቀየረ ተከሳሽ) በነበረው የክስ ክርክር

ተከሳሹ አደረገ የተባለው ኮንትራክተር ሳይሆን ኮንትራክተር ነኝ በሚል አሁኑኑ ገንዘብ አመጣለሁ በሚል ከግል ተበዳይ የሱቅ መደበር በመሄድ መጠኑ ስልሳ ኩንታል የሆነ ሲምንቶ በመውሰድ የተሰወረ ስለሆነ በሚል በማታለል ወንጀል ተከሰሰ፡፡በክሱ ላይ የተመለከተውን የወንጀል ተግባር ለማስረዳት

 በተራ ቁጥር አንድ ላይ በተመለከተው መስፈርት መሰረት ተበዳዩ ወደ ውል ግንኙነቱ ውስጥ ሊገባ ያስቻለው ተከሳሽ ኮንትራክተር ነኝ በማለት የተናገረው ንግግር ከሆነ ይህ ንግግርም ሀሰተኛ ነው ለማለት እውነትም ተከሳሹ ኮንትራክተር ስለመሆን አለመሆኑ ከሚመለከታቸው የመንግስት ተቋማት ማረጋገጥ የሚገባ ሲሆን እነዚህ ተቋማት ተከሳሹ በስሙ ምንም አይነት ፍቃድ ያላወጣ መሆኑን ካረጋገጡ ተከሳሽ የራሱን ማንነት ኮንትራክተር ሳይሆን ኮንትራክተር ነኝ በሚል በመሰወር አሳሳች ቃል ተናግሯል ሊባል ይችላል፡፡የተከሳሽ ድርጊት በንግግር የሚፈፀም እንደመሆኑ መጠን ግን ከግል ተበዳይ ውጭ ሌሎች ሰዎችም ንግግሩን መስማት ሊኖርባቸው ይገባል፡፡ሌሎች ሰዎች እንኳን ባይሰሙ ተከሳሹ በህገመንገስቱና በወንጀለኛ መቅጫ ስነ ሰርአት ህጉ አግባብ ለፓሊስ ወይም ለፍርድ ቤቱ እንደክሱ አቀራረብ በአማራጭነት ወንጀሉን ስለመፈፀሙ ሊያምን ይገባዋል፡፡በዚህ መሰረት ተከሳሽ ድርጊቱን በንግግሩ ስለመፈፀሙ ከግል ተበዳይ ውጭ የሰሙ ምስክሮች፣በክሱ ላይ የተገለፀውን መጠን ያህል ሲሚንቶንም ሰጥቶ በንብረት መብቱ ላይ ጉዳት የደረሰበት ስለመሆኑ ፣አሳሳች ነገር የፈፀመው ማንነቱን በመቀየር እንደመሆኑ መጠን በትክክልም የኮንትራክተር ማንነት የሌለው ስለመሆኑ በቂና አሳማኝ ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል፡፡

 በዚህ የክስ መዝገብ ላይ አከራካሪ የነበረው በሁለቱ ወገኖች መሀከል የነበረው ግንኙነት የውል እንደመሆኑ መጠን ድርጊቱ በማታላል ሳይሆን በውል ህጉ መሰረት ሊገዛ ይገባዋል የሚል ነው፡፡ይህን መሰረት በማድረግ ምንም እንኳን የውል ግንኙነት አለ እንኳ ቢባል ወደ ውል ግንኙነት የተገባው አሳሳች በሆኑ የተከሳሽ አድራጎት ከሆነና በዚያም የተነሳ ውሉ ሊፈፀም የማይቻል ሲሆን ተከሳሹ ላደረገው ተግባር በማታለል አይጠየቅም ማለት ነው ? በውል መሰረት ላልተፈፀመ ግዴታው መጠየቅ በወንጀል ህጉ መሰረት በማታለል ለመጠየቅ ያግዳል ወይ የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳትና መጠየቅ ያሻል?

ለ.በከሳሽ የፌደራል ዐቃቤ ህግና በተከሳሽ አቶ ጌታሁን መሀከል ባለው የክስ ክርክር

ተከሳሽ በቀን 13/2/2012 ዓ.ም ከቀን 30/2/2012 ዓ.ም ጀምሮ የሚመነዘር ገንዘብ የያዘ ቼክ ከተበዳዩ በብድር ለወሰዱት ዕቃ ክፍያ በሚል በስማቸው በመፃፍ ፈርመው የሰጡ ሲሆን የግል ተበዳዩ ቼኩ ለክፍያ በሚያቀርብበት ጊዜ ቼኩ በቀን 11/12/2011 ዓ.ም በተደጋጋሚ ተከሳሹ በቂ ስንቅ የሌለው ቼክ በማቅረባቸው ወይም ለረጅም ጊዜ ባለመንቀሳቀሱ የተነሳ ተዘግቷል በሚል ምላሽ በመስጠቱ የተነሳ በማታለል ወንጀል ክስ ቀርቦባቸዋል፡፡ክሱን ለማስረዳት የቀረቡ ማስረጃዎች

 የግል ተበዳይና ሌላ አንድ የሰው ምስክር

 ተከሳሹ የሰጠው ቼክና የባንኩ መግለጫ

 ቼኩን ተከሳሹ ራሱ ባወጣው አካውንት ወይም የወንጀል ድርጊቱ በሚፈፀም ጊዜ ላይ በውክልና የሚያስተዳድረው ስለመሆኑ ከባንክ ህጋዊ የውክልና ማስረጃ

 ቼኩ ለክፍያ በሚደርስበት ወይም ለክፍያ በቀረበበት ጊዜ በቂ ስንቅ የሌለው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነበር፡፡

ሆኖም ግን የምርመራ መዝገቡ ላይ በተግባር ያጋጠመው ችግር ምንም እንኳን ተከሳሹን በማታለል ወንጀል መክሰስ የሚቻል ቢሆንም ተከሳሹ ባደረገው ድርጊት ተከሳሹ የማታለል ሀሳብ አለው ለማለትና የግል ተበዳይን ቼኩ ገንዘብ አለው ወይም ወደ ባንክ ብወስደው ገንዘብ በባንኩ ይሰጠኛል የሚለውን እምነት በማታለል ተግባር አታሏል ለማለት ቼኩ የሚንቀሳቀስበት አካውንት ስለመዘጋቱ ባንኩ ለተከሳሹ ስለማሳወቁ አለመረጋገጡ ነበር፡፡ባንኩ መዘጋቱን ለተከሳሹ ካሳወቀው የተከሳሹ ተግባር በድርጊት ማድረግ የሌለበትን ክልከላ የተበዳዩን የተሳሳተ እምነት በመጠቀም የማታለል ተግባር ፈፅሟል ለማለት ይቻለል፡፡ከዚህ አንፃር ተከሳሹ ስለመዘጋቱ የሚያውቅ ነበር የሚያስብል ማስረጃ ሊቀርብ ይገባል፡፡በዚህ ተግባሩ የተነሳ ተበዳዩ ስለመታለሉ ደግሞ በንብረት ጥቅሙ ላይ በቼኩ መሰጠት የተነሳ የሚጎዳ ተግባር እንደፈፀመ በሰውና በሰነድ ማስረጃ ማስረዳት ይቻላል፡፡

በተለይ መሰል ተግባራት በማታለል የወንጀል ተግባር ውስጥ የሚያርፉ ቢሆንም ነገር ግን በቼክ የማታለል ወንጀል ውስጥም(በአንቀፅ 693) ሊያርፍ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡ይህም የሚሆነው በተለይም ቼኩ ለክፍያ በሚደርስበት ወይም ለክፍያ በሚቀርብበት ጊዜ በቂ ገንዘብ ስላለመኖሩ በባንክ የተረጋገጠ ከሆነ ነው፡፡ይህ አስተሳሰብ ግን የራሱ ውስንነት አለበት እርሱም ቼኩ የተዘጋ ከሆነ ከመነሻው አካውንት ውስጥ ስላለው ገንዘብ ማጣራት አስፈላጊ አይደለም የሚለው ነው፡፡ይህ አጠራጣሪ ሁኔታ የሚያጋጥም ሲሆን በስነ ስርአት ህጉ አንቀፅ 113 መሰረት ዋና ክሱን በቼክ በማታለል ወንጀል በመከሰስ በአማራጭ በማታላል ቢከሰስ አግባብ ይመስላል፡፡

ሐ.ከሳሽ የፌደራል ዐቃቤ ህግ እና ወ/ሮ አልማዝ (ለዚህ ፅሁፍ ሲባል ስማቸው የተቀየረ)

በዚህ የክስ መዝገብ ከሳሽ የፌደራል ዐቃቤ ህግ ለክሱ መነሻ ያደረገው ተከሳሽ ከአምስት አመት በፊት የተሰጣትን ውክልና የግል ተበዳይ ከሻረችባቸው በኋላና ስለመሻረሙም በሶስት ምስክሮች ፊት መሻሪያውን ካነበብላቸው በኋላ ተከሳሽ በውክልና ሲያስተዳድሩት የነበረውን ንበረት ለሶስተኛ ወገን ሸጠዋል በሚል በማታለል ወንጀል ነው፡፡የውክልናው ማስረጃ የተሻረው በውጭ ሀገር ሆኖ ምንም እንኳን በሚመለከተው በሀገር ውስጥ በሚገኘው የውልና ማስረጃ ተቋም ባይመዘገብም ተከሳሽ ግን ስለመሻሩ ታውቅ ነበር፡፡

በማስረጃ ዝርዝር ውስጥ በክሱ አግባብ የሰውና የሰነድ ማስረጃ የቀረበ ቢሆንም በክስ ክርክሩ አከራካሪ የነበረው የተከሳሽ ድርጊት ንብረቱን የገዙትን ሰዎች አላሳሰትም የሚል ነበር ምክንያቱም ንብረቱን የገዙት ሰዎች ቤቱን ሲገዙ በውልና ማስረጃ የተከሳሽ ውክልና(ተከሳሽ ሌላ ሰው የወኩለበት የውክልና ውክልናም) አልተሻረም የሚል ነው፡፡

በድርጊት ደረጃ ተከሳሽ ውክልናው መሻሩን እያወቀች ሌላ ውክልና በንብረቱ ላይ ሰጥታ ንብረቱ እንዲሸጥ ማድረጓ መግለፅ የሚገባትን ነገር በመደበቅ በመስፈርት አንድ ላይ የተመለከተውን ተግባር አሟልታለች ቢባልም በዚህ ጊዜ ግን ንብረቱን የገዙት ሰዎች በራሳቸው ባረጋገጡት መሰረት ውክልና ስለመሻሩ በሚመለከተው የመንግስት አካል ባለመመዝገቡ የተነሳ አልተታሉም የሚል ክርክር ይነሳል፡፡ከዚያም ባለፈ ገንዘባቸውንና ቤታቸውን ለማግኘት በህግ ጥረት እያደረጉ ስለሆነ ያጡት የገንዘብ ጥቅም የለም የሚባል ክርክር እየተነሳበት ይገኛል፡፡በሌላ በኩል ደግሞ በተከሳሽዋ ተግባርና በገዢዎች መግዛት ውክልናውን ያነሳች የግል ተበዳይ የሆነችው ሶስተኛ ወገን ጥቅሟ ስለተጎዳባት ተከሳሽ በማታለል ልትጠየቅ ይገባል የሚል ሀሳብ ይነሳል፡፡

1.2.እምነት ማጉደል

የእምነት ማጉደል ወንጀል ከማታለል የሚለይበት መሰረታዊ ነገር

1.በእምነት ማጉደል ወንጀል ተከሳሽ(ተጠርጣሪ) ንብረቱን እንዲሰጠው ተበዳዩን የሚናገረው ወይም የሚያደርገው ተግባር የለም፡፡ንብረቱ ወደ ተከሳሹ እጅ እንዲገባ ተበዳዩ ዋናው ምክንያት ነው፡፡በማታለል ጊዜ በተበዳይ የንበረት መብት ጥቅም ላይ የመነሻ ድርጊት የሚመጣው ከተከሳሽ በተለያየ መልኩ በሚገለፅ የማታለል ተግባር ነው፡፡በውስን ሁኔታዎች በእምነት ማጉደል በሚፈፀሙ ወንጀሎች ተጠርጣሪዎች በሚያደርጓቸው ተግባራት ተበዳይ የንብረት መበት ጥቅማቸው ላይ ጉዳት የሚያርሱበት ሁኔታ ቢኖርም ይህ ሊያጋጥም የሚችለው ግን በተበዳይና በተጠርጣሪ መሀከል ጥብቅ የሆነ ግንኙነት ሲኖር ነው፡፡ለምሳሌ ሁለት ጓደኛሞች በጣም ለረጅም ጊዜ በጓደኝነት በሚያሳልፉበት ሁኔታ አንደኛው ጓደኛ ንብረት ጠይቆት በሌላኛው ጓደኛ ቢሰጠው ንብረቱን የሰጠው ሰው ተታሎ ሳይሆን ካላቸው የእርስ በእርስ መተማመን ነው ተብሎ ይታሰባል፡፡በዚህ ጊዜ ከማታለል ይልቅ የእምነት ማጉደል ተግባራቶች ተፈፅመዋል ሊባል ይችላል፡፡

2.በማታለል ጊዜ ተበዳዩ በመታለሉ የተነሳ ነው የንብረት ጥቅሙ ላይ ጉዳት የሚደርሰው፡፡በእምነት ማጉደል ወቅት ግን የንብረት ጥቅም ላይ ጉዳት የሚደርሰው ተበዳዩ ንብረቱን በአደራ ወይም ለአንድ አግልግሎት በራሱ ተነሳሽነት ሰጥቶ ተከሳሽ አደራውን በማጉደሉ የተነሳ የሚኖር የንብረት ላይ ጉዳት መድረስ ነው፡፡ተከሳሽ አንድ ጊዜ አስደውለኝ በሚል ከተከሳሽ ላይ ስልክ ቢወስድና ስልኩን ይዞ ቢሰወር ተበዳዩ ስልኩን የሰጠው በተከሳሹ ንግግር የተነሳ ይመልስልኛል በሚል እምነት ተታልሎ ነው እንጂ በአደራ መልክ እንዲጠብቅለት ወይም ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት በራሱ አነሳሽነት የሰጠው ባለመሆኑ በእምነት ማጉደል ሊከሰስ የሚገባው አይሆንም፡፡(ውይይት ሊደርገበት ይችላል)

የእምነት ማጉደል ወንጀል በመሰረታዊነት ለማቋቋም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 675 ላይ የተመለከተው መስፈርት

      1.ተከሳሹ ተገቢ ያልሆነ ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለማስገኘት በሚል

1.1.የሌላ ሰው የሆነውንና ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ወይም በአደራ የተሰጠን ዋጋ ያለውን ተንቀሳቃሽ ነገር ወይም ጥሬ ገንዘብ በሙሉ ወይም በከፊል ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው ያደረገ ወይም የወሰደ፣ያስወሰደ፣የሰወረ ለአንድ የተወሰነ አገልግሎት የተሰጠውን ዕቃ ለራሱ ወይም ለሌላ ሰው አገልግሎት ያዋለ

1.2.ተከሳሹ ላልተገባ ጥቅም ለማግኘት ሲባል አደራውን አጉዱሏል ለማለት በተለየ ሁኔታ በአደራ የተሰጠውን እቃ ወይም ጥሬ ገነዘብ ሲጠየቅ ለመክፈል ወይም ለመመለስ፣ዕቃው ያለበትን ቦታ ለማሳየት ወይም ለተገቢው አገልግሎት ስለማዋሉ ለማስረዳት ካልቻለ ብቻ ነው ላልተገባ ጥቅም ሲባል እምነት አጎደለ የሚባለው፡፡ተከሳሹ ሲጠየቅ እከፍላለሁ ወይም እመልሳለሁ ካለ በእምነት ማጉደል የማንጠይቀው ሲሆን ዕቃውን ለተገቢው አገልግሎት አውየዋለሁ የሚልም ከሆነ የግድ ማጣራትና መመርመር ይገባል፡፡

1.3.በአደራ የተረከብኩት ንብረት ጠፍቶብኝ ነው ፣ተሰርቆብኝ ነው የሚባሉ ምላሾች ተከሳሹን ነፃ ለማውጣት መስፈርት አይሆንም፡፡

1.4.ለአንድ አገልግሎት የተሰጠን ዕቃ ላልተገባ አገልግሎት ለራሱ ወይም ለሶስተኛ ወገን መጠቀሙ የተረጋገጠበት ሰው በ675(3) ስር የተመለከተውን መከላከያ ተጠቅሞ ለማጣራት መሞከር ከግምት የሚገባ አይሆንም፡፡(ህጉ በአደራ የወሰደውን እቃ ወይም ጥሬ ገንዘብ በሚል አመለከተ እንጂ ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት የተሰጠን ዕቃ ወይም ገንዘብ አለማለቱ ታሳቢ ተደርጓል)

1.5.በጥገና ውል ፣ በመጓጓዝ ውል፣በኪራይ ውል፣በብድር የሚወሰድ ገንዘብ፣በዕቃው ስራ በመስራት ገንዘብ ለማስገባት በሚል ከአሰሪ ሰራተኛ ቅጥር ውጭ ባለ የውል ግንኙነት የሚወሰዱ ዕቃዎች ውልን መሰረት ተደርገው የተወሰዱ ገንዘቦች ወይም እቃዎች አደራ ላይ መሰረት ተደርገው ወይም ያለውል ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ያልተሰጡ በመሆናቸው የተነሳ በእምነት ማጉደል ወንጀል ሊያስጠይቁ የሚችሉ አይሆንም፡፡

1.6.ነገር ግን በውክልና ውል ግንኙነት ተወካይ ፣በስራ ምክንያት ሰራተኛ ምንም እንኳን የአሰሪ ሰራተኛ የውል ግንኙነት ቢኖርም፣የህግ ወይም የገንዘብ አማካሪ (ጠበቃ፣የንብረት አስተዳዳሪ ፣ሂሳብ አጣሪ )አገልግሎት ለመስጠት በሚል የአገልግሎት የውል ግንኙነት ቢኖራቸውም በዚህ ግንኙነት የተነሳ የተረከባቸው ንብረቶች፣ገንዘብ ወይም ለአንድ ለተወሰነ አገልግሎት ተብሎ የተሰጠውን ዕቃ ለራስ ማድረግና መሰል በህጉ የተከለከሉ ተግባትን መፈፀም በወንጀል የሚያስጠይቅ ይሆናል፡፡(የወንጀል ህጉ አንቀፅ 676 ላይ በተመለከተው መሰረት)

አንቀፁን ከመተግበር አንፃር በተግባር የሚያጋጥሙ ችግሮች

1.ተከሳሾ በፓሊስ ጣቢያ ሲጠየቁ በተለይም ለአንድ ለተወሰነ አግልግሎት የተሰጣቸውን ገንዘብ ለተባለው አገልግሎት እንዳዋሉት ጠቅሰው ሳለና ይህንንም የሚያስረዳ የሰውና የሰነድ ማስረጃ እንዳላቸው እየጠቆሙ ለማጣራት ያለመሞከር፡፡የእምነት ማጉደል ወንጀል ልዩ ባህሪይ በተለይም ተከሳሾች በአደራ ስለተሰጣቸው ዕቃዎች ወይም ጥሬ ገንዘብ የግድ መጠየቅ ያለባቸው ሲሆን ከሚሰጡት ምላሽ በመነሳት ዕቃውን ለመመለስ ወይም ለመክፈል የሚስማሙ ከሆነ ወይም በአደራ የተሰጣቸውን ዕቃ ለተባለው አገልግሎት ማዋላቸውን ከተናገሩ ማጣራትና ማስረጃቸውን በዝርዝር በመመልከት አስቀድሞ በማጥራት ውሳኔ ሊሰጥ ይገባል፡፡ተከሳሾች የሰጡትን ቃል ባለማጣራት የተነሳ ለፓሊስ የእምነት ቃል ሲሰጡ በአደራ የወሰዱትን ዕቃ ለተገቢው አለማ አውለናል በሚል ያመለከቷቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃ በፍርድ ቤት በማቅረብ ተገቢውን ፍትህ ማግኘት ቢችሉም ነገር ግን አስፈፃሚው አካል አስቀድሞ በማጣራት የተከሳሾችን መጉላላት መቀነስ ይቻላል፡፡

2.በህጉ የተመለከተውን ‹‹ተከሳሾች ሲጠየቁ›› የሚለው አገላለፅ አንዳንድ ጊዜ ለመተርጎም አስቸጋሪ መሆን፡፡በፓሊስ ጣቢያ ሲጠየቅ በቂ ምክንያት ሳያቀርብ ቀርቶ ክስ ከተመሰረተ በኋላ ፍርድ ቤቱ ሲጠይቀው እከፍላለሁ ወይም ሌላ ነገር ቢል መዝገቡ ሊቋረጥለት ወይም ፍርድ ቤቱ ክሱን ሊያቋረጥው ይገባል ወይ የሚለው አከራካሪ ሲሆን ይስተዋላል፡፡ሲጠየቅ የሚለው በየትኛው ደረጃ ነው የሚለው በግልፅ ያልተመለከተ መሆን፡፡በዚህ ፀሀፊ እምነት ተጠርጣሪው/ተከሳሹ ሲጠየቅ የሚለው የህጉ አነጋገር ለመተርጎም ከመነሻው ተጠርጣሪው የት እና በማን፣በምን ሁኔታ ነው ሊጠየቅ የሚችለው የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ተጠርጣሪው በሶስት ሁኔታዎች በአደራ ስለተረከበው ወይም ለአንድ አገልግሎት ስለተሰጠው ዕቃ ወይም ገንዘብ በሶስት ሁኔታዎች ሊጠየቅ ይችላል፡፡አንደኛ አደራ የሰጠው ሰው የሚጠይቅበት ሁኔታ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በፓሊስ ጣቢያና በፍርድ ቤት በምርመራ ወቅት እንዲሁም በስተመጨረሻ በፍርድ ቤት በክርክር ወቅት የእምነት ክህደት ቃል በሚጠየቅበት ጊዜ ነው፡፡በተበዳይ የሚቀርብ ጥያቄ ትልቁ ምክንያት ተጠርጣሪ አደራውን በልቷል ወይስ አልበላም የሚለውን በግል ግንኙነታቸው መሰረት ለማጣራት ሲሆን በዚህ ወቅት ተጠርጣሪው አደራውን አለመብላቱን ካሳወቀና ካስረዳው ከመነሻው እምነት አጎደለ ሊባል አይችልም፡፡በምርመራ ወቅት የሚቀርብ ጥያቄ አላማው ተጠርጣሪ የሆኑ ሰዎች ወንጀሉን ፈፅመዋል ወይም አልፈፀሙም የሚለውን እውነታ ለማጣራት ሲሆን በዚህ ወቅት ተጠርጣሪው እምነቱን እንዳላጎደለ በተለያየ መልኩ ካስረዳ ከምርመራ አላማ አንፃር ተጠርጣሪው ወንጀሉን አልፈፀመም ፡፡ስለዚህም በህጉ የተመለከተው ‹‹ሲጠየቅ›› የሚለው ትርጉም እስከዚህ ደረጃ ያሉ መጠየቆችን በማካተት ተጠርጣሪን ነፃ ማድረግ ይቻላል፡፡ከዚህ በኋላ ያለው ሶስተኛው መጠየቅ ግን ተከሳሹ ጥፋተኛ ነው ወይስ አይደለም የሚለውን ለመወሰን የሚደረግ ጥያቄ በመሆኑ የተነሳ ምንም እንኳን ተከሳሹ መልሻለሁ ፣ለተገቢው አገልግሎት አውያለሁ ቢልም መዝገቡ ሊቋረጥለት የሚገባ አይሆንም፡፡በፍሬ ነገር ደረጃ ምርመራ እስከሚደረግ ባለው መጠየቅ በአደራ የተሰጠውን እቃ ወይም ንበረት መመለሱን ወይም ለመክፈል ወይም ለተገቢው አለማ ስለማዋሉ ካስረዳ ከመጠየቅ ነፃ ከሚሆን በስተቀር በፍርድ ደረጃ ያሉ መመለሶች ወይም ያንን እንደሚያደርግ መግለፁ ነፃ ሊያደርገው አይገባም፡፡ በዚህ ደረጃ ያሉ ራስን ለመከላከል የሚገለፁ ሁኔታዎች አደራን ካለመፍራት ሳይሆን ፍርድ ቤት የሚጥልበትን ቅጣት እንዳይጣልበት ከማድረግ የሚመጬ ይመስላል፡፡

3.በስተመጨረሻም ምንም እንኳን ሁለቱም ወንጀሎች በንብረት ላይ ጉዳት በማድረስ በሚፈፀሙ የወንጀል ምዕራፍ ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም ከአተገባበር አንፃር የሚያጋጥሙ ወጣ ገባዎችን በአፅኖት በመመልከትና ችግሮችን በመፍታት ወደ ወጥነት የቀረበ ውሳኔ መስጠት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ የወንጀል ፍትህ ስርአቱን ከውሳኔ አሰጣጥ አንፃር ተገማች እንዲሆን ለማድረግ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አለው፡፡ 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Seerri dhaddacha ijibbaataatin hiikoo itti kenname...
ዳኛ የወል ዳኛ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 07 September 2024