Font size: +
4 minutes reading time (836 words)

በወንጀል ጉዳይ በዋስትና እንዲፈታ ፍርድ ቤት ያዘዘውን ሰው ፖሊስ ይግባኝ ልል ነው በማለት ግለሰቡን ያለመፍታት የህግ ስልጣን አለው?

የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 19 (6) ስለተያዙ ሰዎች መብት ሲደነግግ የተያዙ ሰዎች በዋስ የመፈታት መብት እንዳላቸው ሆኖም በህግ በተደነገጉ ልዩ ሁኔታዎች ፍርድ ቤት ዋስትና ላለመቀበል ወይም በገደብ መፍታትን ጨምሮ በቂ የሆነ የዋስትና ማረጋገጫ እንዲቀርብ ለማዘዝ እንደሚችል በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ መረዳት የሚቻለው የዋስትና መብት መርህ (Principle) ሲሆን በዋስ አለመፈታት ደግሞ ልዩ ሁኔታ (Exception) መሆኑን ነው፡፡ ይህንን ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌ ለማስፈፀም ተግባር ላይ ያለው የወ/መ/ስ/ስ/ህግ ምዕራፍ 3 ላይ የዋስትና ወረቀት አስፈርሞ ስለመልቀቅ የሚል ርዕስ ያለው ሲሆን በቁጥር 63 ላይ የዋስትና ወረቀት የሚያሰጡ መሰረታዊ ፍሬነገሮችን ይዘረዝራል፡፡ እነዚህ ፍሬነገሮች ዋስትና የሚያሰጡ ሁኔታዎችን የሚያስረዱ ቢሆንም በተቃራኒው በህግ አተረጓጎም መሰረት ዋስትና የሚያስከለክሉ ሁኔታዎችንም በውስጡ አካቶ ይዟል፡፡

በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 67 ላይ የዋስትና ወረቀት በመፈረም ስላላመልቀቅ የሚል ርዕስን የያዘና በዋስትና ወረቀት የመለቀቅ ማመልከቻን መቀበል የማይቻለው በሶስት ሁኔታዎች ሲሆን ሁኔታዎቹም አንደኛ በዋስትናው ወረቀት የተመለከቱትን ግዴታዎች አመልካቹ የሚፈፅም የማይመስል የሆነ እንደሆነ፤ ሁለተኛ አመልካቹ ቢለቀቅ ሌላ ወንጀል ይፈፅም ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን እና በመጨረሻ ምስክሮችን በመግዛት ወይም በማባበል ወይም አስረጂ የሚሆኑበትን ያጠፋ ይሆናል ተብሎ የሚገመት ሲሆን ነው፡፡

የተያዘው ግለሰብ በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 19(3) እና በወ/መ/ስ/ሥ/ህ/ቁ 29(1) መሰረት በአርባ ስምንት (48) ሰዓታት ወይም በሁለት ቀናት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ መብት እንዳለው ህጋዊ ማረጋገጫ አግኝቷል፡፡ ፍርድ ቤቱም በወ/መ/ስ/ሥ/ህ/ቁ 59 መሰረት የተያዘው ወይም የተጠረጠረው ወይም የተከሰሰው ሰው በማረፊያ ቤት እንዲቆይ (Remand) ወይም በዋስትና እንዲለቀቅ ትዕዛዝ ሊሰጥ ይችላል፡፡ በዚህ ጊዜ በተያዘው ወይም በተከሰሰው ሰው እና በፖሊስ ወይም በዓቃቤ ህግ መካከል የዋስትና ክርክር ይደረጋል፡፡ በዚህ የዋስትና ክርክር ወቅት ፖሊስ በህግ በተሰጠው አግባብ የወንጀል ምርመራ ስራውን አከናውኗል ወይስ አላከናወነም? የተያዘው ሰው የተጠረጠረበት/ የተከሰሰበት ጉዳይ የዋስትና መብት ያስነፍጋል ወይስ አያስነፍግም? የሚሉትን ጭብጦች ፍርድ ቤቶች በገለልተኛነት፣ በነፃነት፣ በህግ እና በህግ ብቻ የሚነሱ ፍሬነገሮችን ከህጉ ጋር በአግባቡ በመመርመርና በማገናዘብ የግለሰቦችን ሰብዓዊ እና ህገ-መንግስታዊ የዋስትና መብት የማስጠበቅ ከፍተኛ ሀላፊነትና ግዴታ አለባቸው፡፡፡

በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 9 ላይ ፖሊስ ሰላምን በመጠበቅ ወንጀል እንዳይሰራ የመከላከል፣ የሚፈፀመውንም ወንጀል የማውጣት፣ የወንጀለኞችን የመያዝ፣ የፖሊስ ሰራዊት ባልደረባ እንደዓቃቤ ህግ ሲሾም በወንጀል ነገር ህግን በማስከበር የዓ/ህግን ፅ/ቤትን የመርዳት ተግባራትን እንደሚያከናውን ተደንግጓል፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ደንብ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 96/1996 አንቀፅ 6 ላይ ፖሊስ ኮሚሽኑ የተሰጡትን ስልጣንና ተግባራት በተጨማሪነት ይዘረዝራል፡፡ ከነዚህም ውስጥ ከያዝነው ጉዳይ ጋር ተያያዥነት ያለው በአንቀፅ 6 (7) ላይ የሰፈረው ሲሆን በፌዴራልና በከተማ ነክ ፍርድ ቤቶች የሚሰጠውን ትዕዛዝ ወይም ውሳኔ እንደሚፈፅም ተመልክቷል፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ 720/2004 አንቀፅ 6(3) ላይ ፖሊስ ኮሚሽኑም በተመሳሳይ በፍርድ ቤቶች የሚሰጡትን ትዕዛዞችና ውሳኔዎች የመፈፀም ግዴታ/ተግባር ተሰጥቶታል፡፡

በፍርድ ቤቶች የሚሰጡ ማናቸውንም ትዕዛዝ፣ ብይን፣ ውሳኔ ወይም ፍርድ ማንኛውም ሰው መፈፀም እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ይህን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የፖሊስ ተቋማትም ጭምር ሊያከብሩትና ሊፈፅሙት ይገባል፡፡ በአዲስ አበባም ሆነ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ ህጎቻቸው ላይም የፍርድ ቤቶችን ትዕዛዝና ውሳኔ የመፈፀምና የማስፈፀም ግዴታ ተጥሎባቸዋል፡፡

ፖሊስ በህግ አግባብ ሰውን በመጠርጠር በህግ በተገደበለት ጊዜ ወደ ፍርድ ቤት የመውሰድ አንዱ የፖሊስ ተግባር ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአንዳንድ ጉዳዮች ላይ ፍርድ ቤት የተያዘን ሰው በዋስትና እንዲለቀቅ ውሳኔ ወይም ትዕዛዝ ከሰጠ በኋላ “ፖሊስ በዋስትናው ላይ ይግባኝ ልል ነው በማለት የፍርድ ቤቱን ትዕዛዝ ባለማክበር ፍርድ ቤት እንዲለቀቅ ያዘዘውን ሰው ከህግ አግባብ ውጪ በማሰር የተያዘውን ሰው አለቅም” የማለት ነገር በፖሊስ በኩል ይታያል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሊነሱና ሊታዩ የሚገባቸው ነገሮች የሚከተሉት ይመስሉኛል፡፡ አንደኛ ፖሊስ ማንንም ሰው ወንጀል ሰርቷል ብሎ በበቂ ሁኔታ ከጠረጠረ ወይም ሲሰራ ካየ ወይም ወንጀል ሰርቶ የተደበቀን ሰው የመያዝ፣ የመመርመር እና ለህግ የማቅረብ የህግ ስልጣን ተሰጥቶታል፤ ነገር ግን ይህንን የህግ ስልጣንና ተግባሩን ሲፈፅም እንደማንኛውም ሀላፊነት እንደሚሰማው የመንግስት ተቋም ህግና የህግ ስነ ስርዓትን ብቻ ተከትሎ ነው ስራውን ማከናወን ያለበት፡፡ ይህም ተግባራዊ እንዲሆን በተቋሙ ውስጥ በየደረጃው ያሉ የፖሊስ አመራሮች ሀላፊነት ከፍተኛ ነው፡፡ በዚህም መሰረት ፍርድ ቤት በዋስትና እንዲለቀቅ ያዘዘውን ግለሰብ ፖሊስ በሌላ ወንጀል የማይፈልገው ከሆነ ይግባኝ ለበላይ ፍርድ ቤት ልጠይቅ ነው በማለት የዋስትና መብትን የተፈቀደለትን ሰው አለመልቀቅ ወይም ማሰር ህገ-ወጥ እና ተገቢነት የሌለው ተግባር ነው፡፡

ሁለተኛ ፖሊስ ዋስትና ሊከለከል ይገባል ብሎ ለሚያስበው ሰው ፍርድ ቤት ዋስትና ፈቅዶበት ከሆነና በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ቅር ከተሰኘ እንደማንኛውም ሰው ይግባኝ የመጠየቅ ህገ-መንግስታዊ ሆነ ስነ-ስርዓታዊ መብት አለው፡፡ ይህንንም የኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 20 (6) እና የወንጀለኛ መቅጫ ስነ-ስርዓት ህግ ቁጥር 75 (1) ላይ በሀያ ቀናት ውስጥ ይግባኝ መጠየቅ እንደሚችል አረጋግጧል፡፡ ይህ የህግ ስርዓት ተቀምጦ እያለ ፖሊስ ይግባኝ ልል ነው በሚል ምክንያት ዋስትና የተፈቀደለትን ሰው አልፈታም የሚልበት የህግ መሰረት የለውም፡፡ በዚህ ረገድ ፖሊስ ማድረግ ያለበት ግለሰቡን በመልቀቅ በህጉ አግባብ ዋስትናው ላይ ይግባኝ በመጠየቅ ጉዳዩ በበላይ ፍርድ ቤት ታይቶ መጥሪያ ለግለሰቡ በህጉ አግባብ በማድረስ በድጋሚ ክርክር በማድረግ ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ ማድረግ ነው፡፡

ይህንን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ የማያከብሩ አካላት ላይ በፍ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 480 መሰረት የማንኛውም ፍርድ ቤት ችሎት ሰብሳቢ ዳኛ ፍርድ ቤቱንና በዚህ ህግ መሰረት የዳኝነትን ስራ አካሄድ  ሥነ ሥርዓት ለማስከበር ማናቸውንም አስፈላጊ መስሎ የታየውን እርምጃ ሊወስድ እንደሚችል እና በዚህም እርምጃ ፍርድ ቤትን የማስከበር ስልጣን ለዳኞች ተሰጥቷቸዋል፡፡ በዚህም መሰረት በገንዘብ መቅጣት፣ በአስተዳደራዊ እርከን ተጠያቂ ማድረግ እና አስፈላጊ ሲሆንም በወንጀል ተጠያቂ የማድረግ እርምጃ መውሰድ ይቻላል፡፡

 በመሆኑም ፖሊስ ፍርድ ቤት የሚሰጠውን ትዕዛዝ በማክበር በህግ የተጣለበትን ግዴታ ሊወጣ ይገባል፤ ፖሊስ ስራውን ሲሰራ በህግና በህግ ብቻ ሊሆን እንደሚገባ ሊዘነጋ የሚገባው ጉዳይ አይደለም፡፡ በተጨማሪ ፖሊስ ለፍትህ ስርዓቱ አጋርነቱን በይበልጥ ማሳየት አለበት፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነ የሚፈለገውን የህግ የበላይነት የማረጋገጥ ጉዳይ አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡ በመሆኑም ለወደፊት በሚመለከታቸው አካላት ከፍተኛ ጥንቃቅ ሊደረግበት ይገባል፡፡ በሌላ በኩል ይህ ተግባር ሲፈፀም ይህንን ተግባር በፈፀሙ የፖሊስ አባሎች ላይ የፍርድ ቤትን ትዕዛዝ ባለማክበር ለሚቀርቡ ቅሬታዎች ተገቢውን ምላሽ መስጠት የሚመለከታቸው የስራ ሀላፊዎችና ተቋማት ድርሻ ነው፡፡ የፖሊስ ተቋማት ወንጀልን የሚከላከሉት ከማህበረሰቡ ጋር በመተባበር በመሆኑ ተቋሙ ሊገነባ የሚያስበውን መልካም ስም እንዳይበላሽበትና ዓላማውን ለማሳካት ሲል በፍርድ ቤት ዋስትና የሚፈቀድላቸውን ሰዎች በአፋጣኝ ሊለቅ ይገባል የሚል እምነት አለኝ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የወንጀል ምርመራና የፍርድ ቤቶች ሚና
በኢትዮጵያ ስላሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች አንዳንድ ጉዳዮች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Sunday, 08 September 2024