የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ስልጣን ከአዲሱ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ አንፃር

በአሁን ሰዓት በሀገራችን ኢትዮጵያ ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ማለትም የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮች ይገኛሉ፡፡ እነዚህም የከተማ አስተዳደሮች ህጋዊ ጥንስሳቸው የአዲስ አበባ ከተማ ህገ-መንግስታዊ መሰረት ያለው ሲሆን የድሬዳዋ ከተማ ደግሞ የቻርተር መሰረት ያለው ነው፡፡ በዚህም መሰረት በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 49 (1) መሰረት የፌዴራሉ መንግስት ርዕሰ ከተማ አዲስ አበባ ነው በማለት ለከተማው እውቅና ሰጥቷል፡፡ የህገ-መንግስቱ አንቀፅ 49 (2) የአዲስ አበባ ከተማ ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ስልጣን እንዳለውም ደንግጓል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ የድሬዳዋ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/96 የድሬዳዋ ከተማን በማቋቋም እራሱን በራሱ እንደሚያስተዳድር ደንግጓል፡፡

ማንኛውም የከተማ አስተዳደር እራሱን በራሱ ሲያስተዳድር በህግ አግባብ የተቋቋሙ ሶስቱ የመንግስት አካላት ማለትም ህግ አውጪ፣ ህግ አስፈፃሚና ህግ ተርጓሚ አካላት ይኖራቸዋል፡፡ በዚህም አግባብ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 እንዲሁም የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በቻርተር አዋጅ ቁጥር 416/96 መሰረት የራሳቸውን የከተማ ፍርድ ቤቶች አቋቋመው በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡ የከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ማለት የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች ማለት እንደሆነ አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 2 (10) በግልፅ አመላክቷል፡፡

እነዚህ የከተማ ፍርድ ቤቶች የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 በስራ ላይ ሲውል ስልጣንና ሀላፊነታቸውን በማሻሻል ብቅ ብሏል፡፡ እነዚህ የከተማ ፍርድ ቤቶች ምን አይነት አዲስ ስልጣን ተጨመረላቸው?፣ በፍትሐብሄር እና በወንጀል ጉዳዮች ስልጣናቸው እስከምን ድረስ ነው? እና በተጨመረላቸው ስልጣን ምክንያት የስራ ጫና ሊኖር ስለሚችል ምን አይነት ዝግጅት ማድረግና በህዝብና በተገልጋዩ ማህበረሰብ አመኔታ ያላቸው ፍርድ ቤቶች ለመሆን ምን ማድረግ ይጠበቅባቸዋል የሚሉትን እንደሚከተለው በአጭሩ እንዳስሳለን፡፡ መልካም ንባብ፡፡

1. የከተማ ፍርድ ቤቶች የፍትሐብሔር ጉዳዮች የዳኝነት ስልጣን

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 5 (1) (ደ) የከተማ ፍርድ ቤቶች (የአዲስ አበባ እና የድሬዳዋ ከተማ) በፍትሐብሔር ጉዳዩች ላይ ከዚህ ቀደም በህጎቻቸው ከነበራቸው ስልጣንና ተግባራት በተጨማሪ የሚከተሉትን ስልጣንና ተግባራት ጨምሮላቸዋል፡፡

ሀ. የፍርድ ክልከላ (Judicial Interdiction) ጉዳዮች

በፍትሐብሔር ህጉ አንቀፅ 351 መሰረት የፍርድ ክልከላ ሊሰጥ የሚቻልባቸውን ሁኔታዎች ሲዘረዝር የአዕምሮ ህመምተኛ ጤናውና ጥቅሙ የሚጠይቅ ሲሆን፣ የአዕምሮ ህመምተኛ ወራሾችን መብትና ጥቅም ለመጠበቅ ሲባል እንዲሁም በእድሜ መግፋት ወይም በሌላ ምክንያት ጤናውንም ሆነ ንብረቱን መጠበቅ የማይችልና የሚያደርገውን ነገር ህጋዊ ውጤቱን የማይረዳ ከሆነ ፍርድ ቤቶች በግለሰቡ ላይ የፍርድ ክልከላ ሊያስተላልፉ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ ግለሰቡ ለምሳሌ የመርሳት በሽታ ያለበት ከሆነ ይህ ግለሰብ የመርሳት በሽታ ያለበት ስለመሆኑ በህክምና ማስረጃ በማረጋገጥና ግለሰቡ የሚያከናውናቸውን የማህበራዊ እንቅስቃሴዎችና የሚሰራቸውን ህጋዊ ተግባራት ውጤት የማያውቅ መሆኑን በምስክሮች ከተረጋገጠ ፍርድ ቤቶች በግለሰቡ ላይ ህጋዊ ተግባራትን እንዳይፈፅም የፍርድ ክልከላ ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡

ፍርድ ቤቶች የፍርድ ክልከላ ከሰጡ በኋላ ውጤቱ ፍርድ ክልከላ የተሰጠበት ሰው በሌላ ሰው ስር ሆኖ ህጋዊ ተግባራትን እንዲያከናውን በፍ/ህ/ቁ 359 (1) ስር ሞግዚትና አስተዳዳሪ ይሾምለታል፡፡ ይህ የፍርድ ክልከላ ስራ ከዚህ ቀደም በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚከናወን የነበረ ሲሆን በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 5 (1) (ደ) መሰረት የከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ሆኗል፡፡

 

ለ. በከተማው ውስጥ ከሚገኝ እድር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች

 

ከዚህ ቀደም በከተማው ውስጥ ከሚገኝ እድር ጋር በተያያዘ የሚነሱ ጉዳዮች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚታዩ የነበሩ ሲሆን በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 5 (1) (ደ) መሰረት በግልፅ የከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ሆኗል፡፡

ሐ. በግለሰቦች መካከል የሚደረጉ እስከ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ብር) የገንዘብ፣ ውል እና ብድር ክርክር ጉዳዮች

የፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጁ ለከተማ ፍርድ ቤቶቹ ከሰጠው ስልጣን ዋነኛውና ትልቁ ይህ ስልጣን ነው፡፡ እንደነዚህ አይነት ክርክሮች በግለሰቦች መካከል የማይቀሩ ጉዳዩች ናቸው፡፡ እንደአዋጁ አገላለፅ የከተማ ፍርድ ቤቶቹ ስልጣናቸው በሶስት ዋና ጉዳዮች ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ እነዚህም፡-

 

1.1 በግለሰቦች መካከል በሚደረጉ ክርክሮች

 

በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 2 (10) መሰረት እና በሌሎች ህጎች ላይ እንደምንመለከተው “ሰው” ማለት የተፈጥሮ ወይም በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው ሰው ነው በማለት ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡ የተፈጥሮ ሰው ማለት ግለሰቦችን ለማለት ነው፡፡ እዚህ ጋር አዋጁ ወጥነት እንዲኖረውና ግልፅነትን ለመፍጠር በተፈጥሮ ሰዎች መካከል የሚደረጉ ክርክሮች በማለት ቢያስቀምጠው የተሻለ ይሆን ነበር፡፡ በመሆኑም በግለሰቦች መካከል የሚደረጉ የተወሰኑ ክርክሮች በከተማ ፍርድ ቤቶች እንዲታዩ ተወስኗል ማለት ነው፡፡ በተቃራኒው የተለያዩ በንግድ ህጉ የሚቋቋሙ ማህበራት (በህግ የሰውነት መብት የሚሰጣቸው) ጉዳዮች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች መታየታቸውን ይቀጥላሉ ማለት ነው፡፡

1.2 እስከ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ብር) ብቻ ያሉ ክርክሮች

በከተማ ፍርድ ቤቶቹ እንዲታዩ የተወሰኑት ክርክሮች የገንዘብ መጠናቸው እስከ ብር 500,000 (አምስት መቶ ሺህ ብር) ብቻ ሆኖ ተገድቧል፡፡ ከዚህ የገንዘብ መጠን በላይ ያሉት ክርክሮች  የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን ይሆናሉ፡፡ በአሁን ሰዓት በሀገራችን ካለው የኢኮኖሚ ሁኔታ እና ከዚህ ቀደም ከነበረው የፍርድ ቤት የክርክር ልምዶች አንፃር ለከተማ ፍርድ ቤቶች ይህ የገንዘብ መጠን ቀላል የሚባል አይደለም፡፡

1.3 የገንዘብ፣ ውል እና ብድር ክርክር ጉዳዮች

የመጨረሻው መሰረታዊ የሆነ የከተማ ፍርድ ቤቶች የስልጣን መሰረት መወሰኛ በግለሰቦች መካከል የሚደረገው እስከ ብር አምስት መቶ ሺህ ድረስ ያለው ክርክር የገንዘብ፣ የውል እና የብድር መሰረት ያለው መሆን አለበት፡፡ በገንዘብ፣ በውልና በብድር ላይ ያልተመሰረተ እስከ አምስት መቶ ሺህ ብር ያለ የግለሰቦች ክርክር በከተማ ፍርድ ቤቶች የሚታይ አይደለም፡፡ለምሳሌ በቼክ ላይ የተመሰረተ የገንዘብ ይከፈለኝ ጥያቄ እንደእኔ አመለካከት በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚታይ ነው፡፡ ምክንያቱም በአንድ በኩል ቼክ ከንግድ ጋር የተያያዘ ጉዳይ ሲሆን በሌላ በኩል በአዋጅ ቁጥር 1234/2013 አንቀፅ 5 (1) (ቸ) መሰረት የሚተላለፉ የገንዘብ ሰነዶችን በተመለከተ የሚነሱ ክርክሮችን (ቼክን ይጨምራል) አይቶ የመወሰን ስልጣን የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ስልጣን እንደሆነ የሚደነግግ በመሆኑ ነው፡፡ በተጨማሪም ከውል ውጪ የሚመነጩ የገንዘብ ይከፈለኝ የካሳ ወይም ሌላ ጥያቄዎች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የሚታዩ ይሆናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የገንዘብ እና የውል ጉዳዮች በባህሪያቸው ዘርዝሮ መጨረስ ባይቻልም እንደየጉዳዩ አይነት በከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ስር የሚድቁ ናቸው ወይስ አይደሉም የሚሉ ጉዳዮች ሲያጋጥሙ በጥንቃቄ ማየት ይጠይቃል የሚል ሀሳብ አለኝ፡፡

2. የከተማ ፍርድ ቤቶች የወንጀል ጉዳዮች የዳኝነት ስልጣን

የከተማ ፍርድ ቤቶቹ በህጎቻቸው እንደፍትሐብሔር ጉዳይ ሁሉ የወንጀል ጉዳዮችን የማየት ስልጣን አላቸው፡፡ የፌዴራል ፍ/ቤቶች አዋጅ ቁጥር 1234/2013 በአንቀፅ 4 (16) ስር የከተማ ፍርድ ቤቶቹ በቻርተር አዋጆቻቸው የተሰጣቸውን የወንጀል ጉዳይ የዳኝነት ስልጣን ሲዘረዝር የደንብ መተላለፍ፣ የብርበራ ትዕዛዝ፣ የመያዣ ትዕዛዝ፣ የእምነት ቃል (በወ/መ/ስ/ስ/ህ/ቁ 35 መሰረት የሚሰጥ)፣ የጊዜ ቀጠሮና የዋስትና ጉዳዮችን መርምሮ ትዕዛዝ የመስጠት ስልጣን ያላቸው መሆኑን በመግለፅ በተጨማሪነት በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱ የወንጀል ጉዳዮችን እንዲመለከቱ የከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ተሰጥቷቸዋል፡፡

የኢፌዲሪ የወንጀል ህግ በተለያዩ ድንጋጌዎች ስር በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱ የወንጀል ጉዳዮችን ዘርዝሯል፡፡ ለዚህ ፅሁፍ ሲባል በግል አቤቱታ የሚቀርቡ ጉዳዮችን በውጭ አገር መንግስት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች እና ሌሎች ጉዳዮች በሚል ለሁለት ከፍለን እንመለከታለን፡፡

ሀ. በውጭ አገር መንግስት ላይ የሚደረጉ ወንጀሎች

በወንጀል ህጉ አንቀፅ 268 አነጋገር መሰረት በውጭ አገር መንግስት ወይም ድርጅቶች ላይ የሚቀርቡት የወንጀል ክሶች ተበደልኩ የሚለው መንግስት ወይም ድርጅት ወንጀለኛው እንዲቀጣለት ሲጠይቅ (የግል አቤተታ ሲያቀርብ) እና ጠቅላይ ዓ/ህግ ሲፈቅድ ብቻ እንደሆነ ደንግጓል፡፡ በዚህም መሰረት በግል አቤቱታ አቅራቢነት የሚያስከስሱ የወንጀል ጉዳዮች የሚከተሉትን ያካትታል፡፡

  • በውጭ አገር መንግስት ላይ የሚደረግ የተቃዋሚ ድርጊት (የወንጀል ህግ አንቀፅ 261)፣
  • የውጭ አገር መንግስትን ግዛት መጣስ (አንቀፅ 262)፣
  • የውጭ አገር መንግስታትን ማዋረድ (አንቀፅ 264)፣
  • የታወቁ የውጭ ሀገር ምልክቶች ማዋረድ (አንቀፅ 265)፣ እና
  • በመንግስታት መካከል የተቋቋሙ ድርጅቶችን ማዋረድ (አንቀፅ 266) ናቸው፡፡

ለ. ሌሎች በግል አቤቱታ የሚቀርቡ የወንጀል ጉዳዮች

በወንጀል ህጉ ውስጥ ሌሎች በግል አቤቱታ የሚቀርቡ የወንጀል አይነቶች ተዘርዝረው የሚገኙ ሲሆን የሚከተሉትን ያካትታል፡፡

ሰነዶችን የማጥፋት (አንቀፅ 380 (2)) ወንጀል ሆኖ ወንጀሉ ግን የተፈፀመው በቤተሰብ አባል፣ ቅርብ ዘመድ፣ በጥቅም ወይም በፍቅር በተሳሰረ ወይም አብሮት በሚኖር ሰው ላይ ሲሆን፣ በሞያ ወይም በስራ ምክንያት የታወቀ ምስጢር መግለፅ (አንቀፅ 399(1))፣ታስቦ የሚፈፀም ቀላል የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል (አንቀፅ 556 (1))፣ በቸልተኝነት የሚፈፀም ቀላል የአካል ጉዳት ማድረስ ወንጀል (አንቀፅ 559 (1 እና 3))፣ የእጅ እልፊት ወንጀል (አንቀፅ 560 (1)፣የዛቻ ወንጀል (አንቀፅ 580) እንዲሁም በወንጀል ህጉ አንቀፅ 583 (1)፣ 593፣ 603፣ 606፣ 613 (1-4)፣ 615፣ 618፣ 625፣ 642 (2)፣ 643 (2)፣ 652(1-2)፣ 658፣ 667፣ 679፣ 680፣ 685፣ 686(1)፣ 689-691፣ 700፣ 704፣ 705፣ 717-719 እና አንቀፅ 725 በማጭበርበር እዳ መክፍል አለመቻል ወንጀሎች በግል አቤቱታ ሲቀርብባቸው ብቻ የሚታዩ የወንጀል ጉዳዮች ሲሆኑ እነዚህም ጉዳዮች በፌዴራል ፍርድ ቤቶች መታየታቸው ቀርቶ የከተማ ፍርድ ቤቶች ስልጣን ሆነዋል፡፡

3. ከከተማ ፍርድ ቤቶቹ ምን ይጠበቃል?

ከላይ እንደተመለከትነው የከተማ ፍርድ ቤቶቹ ስልጣናቸው በህግ ከፍ በማለቱ የፍርድ ቤቶቻቸው ተገልጋይ ቁጥር በሰውም ሆነ በጉዳይ እንደሚጨምር ይገመታል፡፡ በዚህም መሰረት ተቋማቱ ለአስተዳደር ሰራተኞቻቸው፣ ለዳኞቻቸውና ለድጋፍ ሰጪ ሰራተኞቻቸው አዋጁን በተመለከተ ስልጠና ቢሰጡ፣ ፍርድ ቤቶቹ ከዚህ ቀደም በህግ ከተሰጣቸው ስልጣን አንፃር ዳኞቻቸው ሲያዩዋቸው የነበሩት ጉዳዮችና ህጎች ውስን የነበሩ በመሆኑ ብቃት ያላቸው ዳኞችን ለማየት እንዲቻል ተከታታይ ስልጠናና ድጋፍ ቢደረግላቸው ህጉንና ስነ-ስርዓቱን የተከተለ ህጋዊ የክርክር ሂደትና ጥራት ያለው ውሳኔ ለማየት ያስችላል፣ አገልግሎት ከማግኘት ጋር፣ ፋይል ከመክፈት፣ የዳኝነት ክፍያ ከመክፈል ወ.ዘ.ተ ጋር ተያይዞ የሚነሱ የቀደሙ አስተዳደራዊ ችግሮችን በቅድሚያ ወጥ የሆነ አሰራር በማበጀት (የተጨመረላቸውን ስልጣን ታሳቢ በማድረግ) በተገልጋዩ ማህበረሰብ ቅሬታ እንዳይኖርና ፈጣን አገልግሎት ለመስጠት እንዲቻል የራሳቸውን ጥረት ማድረግ ቢችሉ፣ አስፈላጊ ሲሆን ከፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጋር የልምድ ልውውጥ በማድረግ በጎ የሆኑትን የስራ መመሪያዎችና ሁኔታዎችን መቅሰም ቢቻል እና ቅሬታ ሲኖር አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚችል ሰራተኛና አመራር ቢኖር በፌዴራል ፍርድ ቤቶች አዋጅ የተሰጣቸውን ተጨማሪ ስልጣንና ሀላፊነቶች በአግባቡ ለመወጣት እንዲችሉና ተገልጋዩም ማህበረሰብ ረክቶ የሚመለስበትና የህግ የበላይነትና መልካም አስተዳደር የሰፈነበት የስራ ሁኔታ በከተማ ፍርድ ቤቶች አካባቢ ይፈጠራል የሚል እምነት አለኝ፡፡ መጪው ጊዜ መልካም የሰላም፣ የጤናና የስራ ዘመን ይሁንልን!!!

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Ethiopian Courts’ Stance on Pathological Arbitrati...
What You Should Know About the Establishment of a ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 23 May 2024