የአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ ሥልጣናቸውን የተመለከቱ የተለያዩ ክርክሮች ተነስተዋል፡፡ ዋናው ክርክር በተቋቋመበት ወቅት የተነሳው የሕገ መንግሥታዊነት ጭብጥ ነው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 78 እስከ 80 የዳኝነት አካሉን ሲያዋቅር በተለያዩ ደረጃዎች ያሉት የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች እንደሚቋቋሙ በመግለጽ የፍርድ ቤት ሥልጣን ከመደበኛ ፍርድ ቤቶች የሚወሰዱ ጊዜያዊና ልዩ ፍርድ ቤቶች እንደማይቋቋሙ ደንግጓል፡፡
ይህን መሠረት አድርገው አንዳንዶች በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር የተቋቋመው የከተማ ነክ ፍርድ ቤት (አሁን የከተማ ፍርድ ቤት) ሕገ መንግሥታዊ አይደለም ሲሉ ሞግተዋል፡፡ የፍርድ ቤቱን ሕገ መንግሥታዊነት የሚደግፉ ወገኖች ደግሞ ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 49 በአዲስ አበባ የራስ አስተዳደር ስለፈቀደ አዲስ አበባ እንቅስቃሴዎቿን ለመከታተል የሕግ አውጭ፣ የሕግ አስፈጻሚ እንዲሁም የሕግ ተርጓሚ አካላትን ማቋቋም ትችላለች ብለዋል፡፡ የግራ ቀኙን የሕገ መንግሥታዊነት ለመደገፍ ሌሎችም ምክንያቶች ተጠቅሰዋል፡፡ ያም ሆኖ የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት በአዋጅ ተቋቁሞ መደበኛ የፍርድ ቤት ሥራዎችን መሥራት ከጀመረ ሁለት አሠርት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ፍርድ ቤት በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ሥልጣኖች ተሰጥተውታል፡፡ በተቋቋመበት ወቅት በዋናነት የከተማ አስተዳደሩ የሚያከናውናቸው ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ የአስተዳደርና የቁጥጥር ሥልጣኖችን ከማስፈጸም ጋር የተያያዙ ክርክሮችን ይመለከት ነበር፡፡ ሁከት ይወገድልኝ፣ ደንብ መተላለፍ፣ ከቀበሌ ቤቶች ጋር የተያያዙ ክርክሮች፣ ከመሬት ጋር የተያያዙ ክርክሮችን ተቀብሎ እንዲያስተናግድ ተፈቀደለት፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ደግሞ ከመሬት ጋር የተያያዙት ጉዳዮች በአስተዳደሩ ስም ለተቋቋመ ቦርድ የተሰጠ ሲሆን፣ በምትኩ ጊዜ ቀጠሮ፣ እስከ አምስት ሺሕ ብር የሚደርሱ የፍትሐ ብሔር ክርክሮች፣ የስም ለውጥ፣ የወራሽነት የምስክር ወረቀት፣ የመጥፋት ውሳኔ፣ የባልና የሚስትነት፣ የሞግዚትነት የምስክር ወረቀት የመስጠት ሥልጣን በተሻሻሉ አዋጆች እንዲሠራ ተደርጓል፡፡
ለፍርድ ቤቱ በተለያዩ ጊዜያት ከተሰጡት ሥልጣኖች ለመረዳት የሚቻለው ፍርድ ቤቱ እንዲሠራቸው የተፈለጉት ክርክሮች ውስብስብነት የሌላቸው፣ በአጭር ጊዜ ሊጠናቀቁ የሚገባቸው፣ የገንዘብ መጠናቸው አነስተኛና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር የተያያዙ ሥራዎችን (Municipality activities) መሠረት አድርገው የሚነሱ ክርክሮችን ነው፡፡