Font size: +
5 minutes reading time (1011 words)

በኢትዮጵያ ስላሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች አንዳንድ ጉዳዮች

በተለያዩ የአለማችን ክፍሎች የተለያዩ የከፉ የዘር ማጥፋት ወንጀሎች (Genocide)፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (Crimes against Humanity)፣ የጦር ወንጀሎች (War Crimes) እና የወረራ ወንጀሎች (Crime of aggression)፣ በሰላም ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች (Crime against Peace) እንዲሁም ወታደራዊ ወንጀሎች በተለያዩ ሰዎች አማካኝነት በተለያዩ የሰው ልጆች እና ተቋማት ላይ ሲፈፀሙ እንደነበር ታሪክ ይነግረናል፡፡ በአሁን ሰዓትም እነዚህ ወንጀሎች ከመሰራት አልቦዘኑም፡፡ የአንድ ሀገር የመከላከያ ሰራዊት አባል ወይም እንደአግባቡ ማንኛውም ሰው ለሚፈፅሙት የወንጀል ተግባር የሚቀርብባቸውን የወንጀል ጉዳዮች የሚመለከቱ ሀገር አቀፍ ወይም አለምዓቀፍ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች አሉ፡፡ እነዚህ ፍርድ ቤቶች ወታደራዊ ፍርድ ቤት (Military Court) ወይም (Court-Martial) በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህ ፍርድ ቤቶች ከመደበኛው የሲቪል ፍርድ ቤቶች የተለዩ እና ቋሚ ወይም ጊዜያዊ ሆነው-ለተወሰነ ዓላማ እና ጊዜ የሚቋቋሙ ፍርድ ቤቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡

እነዚህ ፍርድ ቤቶች ወይም (Tribunals) በየሀገራቱ ህጎች የሚቋቋሙ ወይም በዓለምአቀፍ ህግ የተቋቋሙ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በአለምአቀፍ ደረጃ ያለው የአለምዓቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት (International Criminal Court)፣ እ.ኤ.አ በ1945 በጀርመን ሀገር የናዚ ወታደራዊ መኮንኖችን ለመዳኘት የተቋቋመው Nuremberg Trial እንዲሁም በአሁን ሰዓት በሀገራችን በመከላከያ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1100/2011 አንቀፅ 28 መሰረት የተቋቋሙት ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

በመከላከያ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1100/2011 አንቀፅ 28 (3) ስለወታደራዊ ፍትህ አካላት ሲዘረዝር በወታደራዊ ሰራዊት ውስጥ የወታደራዊ ፍትህ ስራን የሚያከናውኑ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸውን ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሰረት በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት እነዚህ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በህግ ስላላቸው ስልጣንና ተያያዥ ጉዳዬች በአጭሩ እንደሚከተለው እንዳስሳለን፡፡

2. የፍርድ ቤቶች ስልጣን እና ስለወታደራዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋም

ጉዳዮችን በህግ የመስማትና የማየት እንዲሁም አስገዳጅ ውሳኔ የመስጠት ተግባር የፍርድ ቤቶች ስልጣን ተብሎ ይጠራል፡፡ እነዚህ ጉዳዮች የወንጀል ወይም የፍትሐብሄር ወይም የስራ ክርክር ባህርይ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ የወንጀል ጉዳዮች ደግሞ በራሳቸው ሲቪሎች ወይም ወታደሮች የሚፈፅሟቸው የወንጀል አይነቶች ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ እነዚህን ጉዳዮች የማየት ስልጣን የፍርድ ቤቶች ስልጣን ስለመሆኑ በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 79 (1) ላይ በግልፅ ሰፍሯል፡፡  የፍርድ ቤቶችም ስልጣን በሶስት አይነት መንገድ ይወሰናል፡፡ እነዚህም ሀገራዊ የፍርድ ቤቶች ስልጣን (Judicial Jurisdiction)፣ የፍርድ ቤቶች የሥረ-ነገር ስልጣን (Material Jurisdiction) እና የፍርድ ቤቶች የግዛት ክልል ስልጣን (Local Jurisdiction) በመባል ይታወቃሉ፡፡ እነዚህን የፍርድ ቤቶችን ስልጣን መወሰኛ መንገዶች በአገሪቱ በስራ ላይ ባሉ የተለያዩ መሰረታዊ እና ስነ-ስርዓታዊ ህጎች የሚወሰኑ ይሆናል፡፡ 

በስራ ላይ ያለው ህገ-መንግስት አንቀፅ  9 (1) እና 9 (4) ህገ-መንግስቱ የሀገሪቱ የበላይ ህግና ኢትዮጵያ ያፀደቀቻቸው አለምአቀፍ ስምምነቶች የሀገሪቱ ህግ አካል መሆናቸውን ከአንቀፆቹ ጣምራ ንባብ መረዳት ይቻላል፡፡ በዚህም አግባብ የመከላከያ ሰራዊት አባላት በኢትዮጵያ የወንጀል ህግ ወይም በዓለምአቀፍ ህግ ወይም በወታደራዊ ተግባር ላይ ከሚደረጉት ወንጀሎች አንዱን ከፈፀመ የመከላከያ አባሉ በወታደራዊ ፍርድ ቤት ይዳኛል፡፡ በመከላከያ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1100/2011 አንቀፅ 28 (3) ስለወታደራዊ ፍትህ አካላት ሲዘረዝር በወታደራዊ ሰራዊት ውስጥ የወታደራዊ ፍትህ ስራን የሚያከናውኑ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች መቋቋማቸውን ይደነግጋል፡፡ እነዚህ ፍርድ ቤቶች በሁለት ደረጃ የተቋቋሙ ሲሆን አንደኛ ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት እና ሁለተኛ ደግሞ ይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በመባል እንደሚጠሩ የአዋጁ አንቀፅ 37 (1) እና (2) በግልፅ ያመለክታል፡፡ በመሆኑም በአሁን ሰዓት በኢትዮጵያ ውስጥ እነዚህ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በህግ ተቋቁመው በስራ ላይ ይገኛሉ፡፡

እነዚህ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች የተፈፀመው ወንጀል በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 28 መሰረት በስብዕና ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች፣ በወንጀል ህጉ ከአንቀፅ 269- አንቀፅ 322 ከተዘረዘሩት ውስጥ (ዓለምዓቀፍ ህጎችን በመጣስ የሚፈፀሙ ወንጀሎች-ለምሳሌ ዘር ማጥፋት (Genocide)፣ በሰብዓዊ ድርጅቶች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች እና ወታደራዊ ወንጀሎች) አንዱ ከሆነ ወይም በዓለምዓቀፍ ህግ (የዘር ማጥፋት፣ በሰው ልጆች ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ወዘተ) ወይም በወታደራዊ ተግባር ላይ ከሚደረጉት ወንጀሎች አንዱ ከሆነ የመከላከያ ሰራዊቱ አባል የሚዳኘው በኢፌዲሪ የወንጀል ህግና በኢትዮጵያ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የመከላከያ አዋጁ በማንኛውም የመከላከያ ሰራዊት አባል ላይ እንዲሁም እንደአግባብነቱ በሲቪሎችም ላይ ተፈፃሚ ይሆናል፡፡

3. ስለወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ስልጣንና ተግባር

በመከላከያ አዋጁ መሰረት ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤትና ይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በሀገራችን አሉ፡፡ ቀዳሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ በአዋጁ አንቀፅ 37 መሰረት በተለያዩ የወንጀል ጉዳዮች ላይ የዳኝነት ስልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ከነዚህም ጉዳዮች ውስጥ በወንጀል ህጉ ከአንቀፅ 284-322 በተደነገጉት ወታደራዊ ወንጀሎች ተጠያቂ የሚሆኑ ሰዎች፣ በሰራዊት አባላት መካከል በሚፈፀም  የግድያ፣ የድብደባ እና የአካል ማጉደል ወንጀሎች፣  ማንኛውም የሠራዊት አባል በአገር ውስጥ በጦር ሜዳ ግዳጅ ላይ ሆኖ በሚፈፅማቸው ማናቸውም ወንጀሎች፣ በውጭ አገር ግዳጅ ወይም በጦር ሜዳ ግዳጅ ከተሰማራ የጦር ክፍል ጋር የዘመተ የሠራዊት አባል ወይም ሲቪሎች በሚፈፅሟቸው ማናቸውም ወንጀሎች፣ በአገር ውስጥ የጦር ክተት አዋጅ በታወጀበት ወይም የጦር አደጋ ምልክት በተሰጠበት ጊዜ ከሠራዊቱ ጋር የዘመቱ ሲቪሎች፣ የመደበኛ ፖሊስ አባላት እና ሚሊሻዎች በሚፈጽሟቸው ማናቸውም ወንጀሎች፣ የጦር ምርኮኞች ከተማረኩ በኋላ በሚፈፅሟቸው ማናቸውም ወንጀሎች እና ሌሎች በህጉ የተጠቀሱ ስልጣኖች አሉት፡፡

  

4. ፍርድ ቤቶቹ ስለሚመሩበት የሥነ-ስርዓት ህጎች

እንደማንኛውም መደበኛ ፍርድ ቤት ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ስራቸውን ሲሰሩ የሚመሩበት ህጎች አሉ፡፡ ከነዚህም ውስጥ በስራ ያለው የወንጀል ስነ-ስርዓት ህጉ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከዚህ ህግ በተጨማሪ የሀገሪቱ ህገ-መንግስት እንደአግባብነቱ ተፈፃሚነት አለው፡፡ ለምሳሌ በህገ-መንግስቱ ውስጥ የተጠቀሱትን ስለተያዙ ሰዎች መብት፣ ስለተከሰሱ ሰዎች መብት-የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት (ወታደራዊ ወንጀል የፈፀሙ ሰዎች በወታደራዊ ፍርድ ቤት የመቅረብ) ለህዝብ ግልፅ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት፣ በጥበቃ ስርና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት፣ የወንጀል ህግ ወደኋላ ሄዶ የማይሰራ ስለመሆኑ እና በአንድ ወንጀል ድጋሚ ቅጣት ስለመከልከሉ የሚደነግጉት ህገ-መንግስታዊ ድንጋጌዎች በዚህ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችም ተግባራዊ ይሆናሉ፡፡

5. ስለይግባኝ ስርዓት

እንደማንኛውም ሰው በወታደራዊ ፍርድ ቤት በተሰጠ ውሳኔ ላይ በውሳኔው ቅር የተሰኘው ሰው በኢፌዲሪ ህገ-መንግስት አንቀፅ 20 (6) መሰረት ይግባኝ የመጠየቅ ህገ-መንግስታዊ ሆነ ስነ-ስርዓታዊ መብት አለው፡፡ በዚህ አግባብ በቀዳሚው ወታደራዊ ፍርድ ቤት ታይተው በሚወሰኑት የወንጀል ጉዳዮች ላይ ቅሬታ ያለው ሰው ለይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤቱ የይግባኝ አቤቱታውን ማቅረብ እንደሚችል በአዋጁ በግልፅ ተመልክቷል፡፡ ይህ ይግባኝ ሰሚ ወታደራዊ ፍርድ ቤት በሰጠው ውሳኔ ላይ ቅሬታ ያለው ሰው ደግሞ በአዋጁ አንቀፅ 40 መሰረት በውሳኔው ላይ መሰረታዊ የሆነ የህግ ስህተት ካለ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ቅሬታው ማቅረብ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡

 

  1. ማሳረጊያ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ ሲቪል ግለሰቦች እና የመከላከያ አባል በነበሩ ሰዎች አማካኝነት የተለያዩ የከፉ ወንጀሎችን በሀገራችንና በህዝቦቿ ላይ ሲፈፅሙና ወንጀሎቹም ሲፈፀሙ ይስተዋላል፡፡ በአሁን ወቅት ሀገራችን ኢትዮጵያ ተገዳ አንድነቷን ለመጠበቅና ህገ-መንግስቱን ለማስከበር በገባችበት ጦርነት-ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት፣ በጦርነቱ ጊዜ እና ከጦርነቱ በኋላ በማንኛውም ሰው ወይም/እና በሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት የሆኑ ወይም/እና በነበሩ ሰዎች ወታደራዊ ወንጀሎች እየተፈፀሙና ሊፈፀሙ ስለሚችሉ ተጠርጣሪዎችን ስልጣን ባለው ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች በማቅረብ ተገቢውን ፍትህ የሚያገኙበት፣ የመከላከያ አዋጁ ተግባራዊ የሚሆንበት፣ ጥፋተኞች በስም የሚለዩበት፣ የሚሸማቀቁበት እና የሚታሰሩበት (Naming, Shaming and Jailing) እንዲሁም የህግ የበላይነት የሚረጋገጥበት እና በኢትዮጵያ ያሉ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶችን አቅም የምንፈትሽበት ጊዜው አሁን ነው፡፡ ሲቪል ሰዎችን በወታደራዊ ፍርድ ቤቶች መዳኘት እንደማይቻል በህገ-መንግስቱ ተከልክሏል፡፡ የመከላከያ አባል የነበሩ ሰዎች በፈፀሙትና በተጠረጠሩበት ወንጀል ጉዳያቸውን በመደበኛ ፍርድ ቤቶች መዳኘትም ተገቢነት የለውም፡፡ እነዚህ ግለሰቦች በወታደራዊ ሰራዊት ውስጥ የነበሩ ከሆኑ ጉዳያቸው መታየት ያለበት በመከላከያ አዋጁ መሰረት በተቋቋሙት ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች ነው፡፡ በተጨማሪም ከኢትዮጵያ ወታደራዊ ፍርድ ቤቶች አቅም በላይ የሚሆኑትን እና ዓለምዓቀፍ የወንጀል ባህርይ ያላቸውን ወንጀሎችና ወንጀለኞችን ለአለምአቀፉ ወንጀለኞች ፍርድ ቤት (International criminal Court) የሚቀርቡበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ሰላም፣ የህግ የበላይነት፣ ፍትህ  እና ዲሞክራሲ ለሀገራችን ኢትዮጵያ!!!

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በወንጀል ጉዳይ በዋስትና እንዲፈታ ፍርድ ቤት ያዘዘውን ሰው ፖሊስ ይግባኝ ልል ...
ማቀባበል (Facilitating Act of Bribery)

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - ጌታዬ አባይ on Wednesday, 03 May 2023 14:41

መሳተፋ እፈልጋለሁ

መሳተፋ እፈልጋለሁ
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024