ፍርድ ቤት ቅጣት ማቅለያን ወይም ማክበጃን በሌላ ማቅለያ ወይም ማክበጃ ቀይሮ ማቅለል ወይም ማክበድ ይችላል?
የቅርብ ጓደኛው ጋር ተጠግቶ ይኖር የነበረ ግለሰብ፣ ጓደኛው በሌለበት አሳቻ ሰዓት 10000 ብር የሚገመት ቶሺባ ላፕቶፕ ወስዶ ለግል ጥቅሙ አውሏል በሚል የወንጀል ሕግ አንቀጽ 665(1)በመተላለፍ በስረቆት ወንጀል ተከሶ፣ ክሱን በዝርዝር በማመኑ ጥፋተኛ ይባላል::
የቅጣት ማክበጃ አስተያየት የተጠየቀው ዐቃቤ ሕግ የወንጀሉን ደረጃና እርከን ካስቀመጠ በኋላ “ተከሳሹ የስርቆት ወንጀሉን የፈፀመው አስጠግቶ በሚያኖረው የቅርብ ጓደኛው ላይ በመሆኑ በከሐዲነት የፈጸመው ነው፡፡ ስለሆነም በወንጀል ሕግ አንቀጽ 84(1)(ሀ) መሠረት ከብዶአንድ ርከን ከፍ ብሎ ይወሰንልን” ብሎ ይጠይቃል::
ፍርድ ቤቱ የተከሳሹን የቅጣት ማቅለያ አስተያየት ከሰማ በኋላ በሰጠው ዝርዝር የቅጣት ሐተታ ዐቃቤ ሕጉ አቅርቦ የነበረውን የቅጣት ማክበጃ በተመለከተ “… ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን የፈጸመው በከሐዲነት ሳይሆን የተጣለበትን እምነት ወይም ኃላፊነት ያላግባብ በመገልገል በመሆኑ በወንጀል ሕግ አንቀጽ 84(1)ሀ ሳይሆን በወንጀል ሕግ አንቀጽ 84(1)(ለ) መሠረት የቅጣት ማክበጃውን ቀይረን አክበደናል” ብሎ በመጨረሻተከሳሹ ላይ ሁለት ዓመት ቀላል እስራት ወስኖ መዝገቡን ይዘጋል::
በዚህ ባነሳሁት እውነተኛ የፍርድ ቤት ውሎ ፍርድ ቤቱ ቅጣት ማክበጃውን መቀየሩ አግባብ ነውወይስ አይደለም? የሚል ጥያቄ ፈጠረብኝ፡፡ አግባብ ከሆነስ በምን የሕግ መሠረት?