በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርአት ውስጥ የወንጀል ምርመራ አላማ ስለ ወንጀል የማወቅ፣ ወንጀል እንዳይፈፀም የማስቆም፣ ወንጀሉ ከተፈፀመ ጉዳቶችን የመቀነስ፣ የወንጀል ኢላማ የሆኑትን ሰዎች፣ ንብረቶች ወይም ጥቅሞችን የመከላከል፣ ወንጀል ፈፃሚዎችን ለሕግ የማቅረብ ወይም የወንጀል ተጎጂዎችን መብቶችና ጥቅሞችን ማስከበር እንደሆነ የኢትዮጵያ ወንጀል ፍትሕ ፖሊሲ ይገልፃል፡፡ ጠበብ አድርገን ስናየው ደግሞ የወንጀል ምርመራ (Investigation) ማለት የአንድን ወንጀል መፈፀም ወይም አለመፈፀም እንዲሁም ማን እንደፈፀመው ለማረጋገጥ የሚረዳ ማስረጃን የማሰባሰብ ሂደት ነው፡፡ ፖሊስም ይህን ተግባር ሲያከናውን ሕገ መንግስቱ፣ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርአት ህጉና ሌሎች ህጎች ባስቀመጡት ድንጋጌዎች መሠረት ማከናወን የሚገባው ሲሆን፣ በዚህ ሂደት የሚኖር የመብት ጥሰት ካለም ተጠያቂነትን ያመጣል፡፡ ወንጀል ከተሰራ በኋላ ፖሊስ በሁለት መንገድ ምርመራ ሊጀምር ይችላል አንደኛው ግለሰቦች ወንጀል ተፈፀመብኝ ብለው በሚያቀርቡት አቤቱታ መሠረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የወንጀሉ ድርጊት ከፈተፈፀመ በኋላ ወንጀሉ ሲፈፀም ያዩ ወይም የሰሙ ግለሰቦች በሚያደርሱት ጥቆማ መሠረት ነው፡፡
ፖሊስ ከላይ በገለፅነው መልኩ መረጃ ደርሶት ምርመራ ሲያከናውን የምርመራው አካል የሆነው አንዱና በጥንቃቄም መከናወን ያለበት ተግባር ተጠርጣሪውን መያዝ ነው፡፡ ምክንያቱም የወንጀል ድርጊት እስከተፈፀመ ድረስ የህብረተሰቡን ህይወት፣ ንብረትና ሰላም ለመጠበቅ ሲባል ወንጀል ፈፃሚዎችንና የወንጀል ድርጊት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋል አስፈላጊ በመሆኑ ነው፡፡ ፖሊስ እስርን ተግባራዊ ለማድረግ በሁለት መንገድ ማለትም በፍርድ ቤት ትእዛዝና ያለ ፍርድ ቤት ትእዛዝ ናቸው፡፡ በመርህ ደረጃ ያለመያዝ ወይም ያለመታሰር መብት ሕገ መንግስታዊ ከለላ ያገኘ መብት በመሆኑ ከመያዝ ጋር ተያይዞ የሚከናወኑ ተግባራት በጥንቃቄ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡
በዚች አነስተኛ ጽሑፍ መያዝ (arrest) ምንነትና ጥቅሙ፣ መያዝ በሀገራችን እንዴት እንደሚተገበርና በሀገራችን ያለው ሁኔታ ምን እንደሚመስል ለማየት ጥረት የሚደረግ ሲሆን እንዲሁም በቀጣይ መያዝን አስመልከቶ ቢስተካከሉ ወይም በሕግ ደረጃ የሕግ ሽፋን ቢሰጣቸው የምላቸውን ሀሳቦች በአስተያየት መልኩ አቀርባለሁ፡፡
ስለመያዝ (arrest) ምንነት
ስለ መያዝ በኢትዮጵያ የወንጀል ሕግም ሆነ የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ-ሥርአት ሕግ ላይ ትርጉም ያልተሰጠው ሲሆን፣ በሌሎች የተለያዩ ሰነዶች ላይ የተሰጠውን ትርጉም ስንመለከት፣ ብላክ ሎው ዲክሽነሪ arrest የሚለውን ፅንሰ ሀሳብ ” it is a seizure or forcible restraint, the taking or keeping of a person in custody by legal authority especially in response to criminal charges”. መያዝ ወይም በሀይል ይዞ ማቆየት ማለት አንድን ሰው በተለይ ለወንጀል ክስ መልስ እንዲሰጥ በህጋዊ ባለስልጣን ወደ ማቆያ መውሰድ ወይም መጠበቅ ማለት ነው በማለት ተርጉሞታል፡፡