Font size: +
9 minutes reading time (1703 words)

"በሕግ አግባብ"ያለአግባብ ስለመታሰር

ካሳ አልባ የፍትሕ ሥርዓቱ ተጎጂዎች

እንዲያው አያድርገውና በወንጀል ተጠርጥረው ጊዜ ቀጠሮ ተጠይቆብዎ አስቸጋሪውን የወንጀል ምርመ

ራ ተቋቁመው ካለፉ በኋላ በዓቃቤ ሕግ ተከሰው የዋስትና መብትዎን ተከልክለው ክራሞትዎ ቂሊንጦ ማረሚያ ቤት ሆነ እንበል፤ በሕግ ጥላ ሥር፡፡

የፍርድ ቤት ቀጠሮዎት በደረሰ ጊዜ እጅዎ በካቴና ተጠፍንጎ ወይም ከሌላ እስረኛ ጋር ተቆራኝቶ ጠመንጃ በወደሩ ፖሊሶች በአይነ ቁራኛ እየተጠበቁ ለወራት ወይም ለዓመታት ነጻነትዎ ተነፍጎ የፍርድ ሂደቱን ሲከታተሉና ሲሟገቱ ከባጁ በኋላ በመጨረሻ ጉዳይዎትን ይመለከት የነበረው ዳኛ የችሎቱን ጠረጴዛ በመዶሻው ግው! በማድረግ ‹‹ከተከሰሱበት ወንጀል በነፃ ተሰናብተዋል ቅንጣት ያህል ጥፋት የለብዎትም›› ብሎ ቢያሰናብትዎ ምን ይሰማዎታል???

እርግጥ ነው፣ ተሟግተው በማሸነፍዎና ንጹህነትዎን በማስመስከርዎ አልያም የእሥር ህይዎትዎ በማክተሙና ፀሐይቱን ያለ አንዳች ከልካይና ተቆጣጣሪ እንዳሻዎ ሊሞቋት በመብቃትዎ ደስታ እና እፎይታ እንደሚሰማዎ አያጠራጠርም፡፡

ነገር ግን በፖሊስ ምርመራ ጊዜ ያለ አግባብ የተንገላቱት፣ ዋስትና በመከልከልዎ ምክንያት ለእሥር የተዳረጉት ለዓመታት ወይም ለወራት ከትዳር ጓደኛዎ ወይም ከቅርብ ዘመድዎ ጋር እንዳሻዎት የመገናኘት መብትዎ የተነፈገው፣ የጀመሩት ቢዝነስ እርስዎ በመታሰርዎ ምክንያት ለኪሳራ የተዳረገው ወ.ዘ.ተ. ያላንዳች ጥፋትዎ መሆኑ አይቆጭዎትም? ከእድሜዎ ላይ እርስዎ ያላዘዙበት፣ ባልሰሩት ኃጢያት ያለአግባብ የተነፈጉት የወራት እና የአመታት ነጻነትዎ አያሳዝንዎትም?

ደግሞ በኩል በወንጀል ተከሰው የዋስትና መብትዎን ተከልክለው አልያም ዋስትና መብትዎ ቢጠበቅልዎትም ዋስ የሚሆን ሰው በማጣትዎ ክራሞትዎ በሕግ ጥላ ሥር ሆነ እንበል፡፡ ለአንድ ዓመት ከስድስት ወር ታስረውና ነጻነትዎ ተነፍጎ ክስዎትን ሲከታተሉ ከከረሙ በኋላ ፍርድ ቤቱ በቀረበብዎት የወንጀል ክስ ጥፋተኛ ነዎት ብሎ እጅዎ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ ተቆጥሮ የስድስት ወር የእሥራት ቅጣት ከወሰነብዎት በኋላ ‹‹ከተፈረደብዎ የእሥራት ቅጣት መጠን አንጻር ሲታይ እስካሁን የታሰሩት በቂ ስለሆነ ከእሥር እንዲለቀቁ ታዟል›› ብሎ ቢወስን አይ! ዓመት ከስድስት ወር ስለታሰርኩ አንድ ዓመት ያለአግባብ የታሰርኩት ይመለስልኝ ይላሉ?

ይህ ችግር በአገራችን የፍትሕ ሂደት የተለመደ ሁኗል፡፡ ይህንን ፍራቻም ይመስላል ደረቱን ነፍቶ ንጹህነቱን ተማምኖ በተጠረጠረበት ጉዳይ ፍትሕ አካል ዘንድ ቀርቦ በልበ ሙሉነት ከሚሟገት ሰው ይልቅ ጥፋት አለመሥራቱንና ንጽህናውን ልቦናው ጠንቅቆ እያወቀ ቢሆንም ‹‹እስኪጣራ ለምን እታሰራለሁ›› በሚል ስጋት ከወንጀሉ ፈጻሚ ባልተናነሰ መልኩ ንጹሃኑም ከሕግ ሽሽት እግሬ አውጪኝ ማለታቸው የተለመደ እየሆነ የመጣው፡፡

ምክንያቱም ጉዳዩ ተጣርቶ በመጨረሻ ከሚሰጠው ፍርድ ይልቅ ያለፍርድ የሚደርሰው የሕግ ጥላው ሥር ቅጣት አስፈሪ እየሆነ ነው፡፡

በአንድ ወቅት እንዲህ ሆነ፣ ሁለት ሰዎች በአንድ ወንጀል ተጠርጥረው ተያዙ ምርመራው ተጣርቶም ክስ ቀረበባቸው፡፡ በዋስ ቢለቀቁ ሊጠፉ ይችላሉ ብሎ ዐቃቤ ሕግ ስለተሟገተ ፍርድ ቤቱ የዋስትና መብታቸው ተነፍጎ በማረፊያ ቤት ሆነው በቀጠሯቸው እየተመላለሱ እንዲከራከሩ በየነ፡፡

ክርክሩ ለአንድ ዓመት ከቆየ በኋላ አንደኛ ተከሳሹ ጥፋተኛ ሆኖ ስለተገኘ እጁ ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ በሚቆጠር የአንድ ዓመት እሥራት ሲፈረድበት ሁለተኛውን ተከሳሽ ግን ወንጀሉን ያለመፈጸሙን ፍርድ ቤቱ ስላረጋገጠ በነጻ እንዲሰናበት ወሰነ፡፡

አስገራሚም አሳዛኙም ነገር እዚህ ላይ ነው፤ ሁለቱም ተከሳሾች ከፍርድ በፊት ዋስትና መብት በመከልከላቸው ለአንድ ዓመት ያህል ታስረዋል፡፡ አንደኛ ተከሳሽ ያው እጁ ከተያዘበት ጀምሮ ሲቆጠር የእሥር ጊዜውን ስለጨረሰ እንዲፈታ የመፍቻ ትዕዛዝ ወጣለት፤ ሁለተኛው ተከሳሽም ነጻ ስለሆነ ተብሎ ተፈታ ሁለቱም ተከሳሾች በአንድ ቀን ወደ እሥር ቤት ገቡ በአንድ ቀንም ከእሥር ቤት ወጡ፡፡ (ያው እንግዲህ ወንጀለኛ የሆነው አንደኛ ተከሳሽ ከፍርድ በፊት የታሰረው እሥር እንደ ቅጣት ተቆጥሮለት ቅጣቱን በመጨረሱ፣ ንጹሁ ሁለተኛው ተከሳሽ ግን በሕግ ጥላ ሥር የማይቆጠርለትን ቅጣት ፉት ብሎ፡፡) እናሳ! ከዚህ እሥር ማን አተረፈ? ወንጀለኛው ወይስ ንጹሁ ሰው??? ወንጀለኛውስ በጥፋቱ ይባል ንጹሁ በምን ሃጢያቱ?

በቅርብ ሰሞንስ በየሚዲያው እና በየማህበረሰብ ድረ-ገጾች ለአንድ ዓመት ተኩል ሲናፈስ የሰነበተውን የዞን ዘጠኝ ጦማሪዎች መታሰር እና የፍርድ ሂደት እና የመለቀቅ ዜና መመልከት ብቻ እኮ በቂ ነው፡፡ እነሱ በአሸባሪነት ተጠርጥረው ተያዙ፡፡ በወንጀል ምርመራ ወቅት የሚያጋጥማቸውን መንገላታት ብንተወው እንኳ ስማቸው ከሽብርተኝነት ጋር መያያዙ ሊያስከትልባቸው የሚችለው የሥነልቦና ጉዳት፣ በዓመት ከምናምን ወር የእሥር ቆይታቸው ወቅት ሰርተው ሊያገኙት የሚችሉት ኢኮኖሚያዊ ገቢ፣ በእነዚህ ግዜያት ውስጥ ነጻነታቸውን በመነፈጋቸው የደረሰባቸው በገንዘብ የማይተካ ጉዳት ወ.ዘ.ተ. በንጹህ ሰው ላይ የደረሰ መሆኑ ተረጋግጦ እንኳ ‹‹ነጻ ናችሁ›› በሚል ፍርድ ብቻ መሰነባበቱ ፍትሕን ያሰፍናል? የእነሱ ጉዳይ ጀሮ-ገብ ሆኖ በየሚዲያው ስለተናፈሰ እንጂ የስንቱ ንጹህ ሰው ነጻነት ነው በሕግ አግባብ ግን ያለአግባብ የተደፈጠጠው?

ለዚህ ተጠያቂ ሊሆን የሚገባው ሕጋችን እና ጠቅላላ የፍትሕ ሥርዓታችን ነው፡፡ በእርግጥ የወንጀል ሕግ እና የወንጀል ፍትሕ ሥርዓቱ ዋና ዓላማው በአገሪቱ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ፣ በመንግሥትና በሕዝብ ጥቅም እንዲሁም በግለሰቦች ደህንነት እና መብት ላይ የሚፈጸሙ የወንጀል ድርጊቶችን አጥፊዎችን ተከታትሎ ለፍርድ በማቅረብ ተገቢውን ቅጣት ማስቀጣት መቻል በመሆኑ አጥፊውን ለፍርድ አቅርቦ ለማስቀጣት ሲባል አጥፊውን ከንጹሃኑ መለየት ያስፈልጋል፡፡ 

አጥፊውን ለመለየት መጀመሪያ ወንጀሉን ፈጽመዋል ተብሎ የሚጠረጠሩ ተጠርጣሪዎች ተይዘው ምርመራ ደረግባቸዋል፡፡ ገበሬ ምርቱን ከግርዱ ለመለየት ምርቱንም ግርዱንም በአንድ ላይ እንደሚያበራይና እንደሚወቃ ሁሉ የፍትሕ ሥርዓታችንም ወንጀለኛውን ለይቶ ለመቅጣት በጥርጣሬ ንጹሁንም ሆነ ወንጀል ፈጻሚውን ደባልቆ በሕግ ጥላሰ ሥር (በእሥር) በማቆየት ያጣራል፡፡ ያው ታሳሪው ጥፋተኛ ሆኖ ከተፈረደበት ሳይፈረድበት የታሰረውን የእሥራት ጊዜ ከተፈረደበት እሥርት ላይ እንዲቀነስለት እንደ ቫት ያወራርዳል፡፡ ታሳሪው ንጹህ ሆኖ ከተገኘ ግን ከፍርድ በፊት ለታሰረበት ካሳ እንኳ አይሰጠውም፡፡

በአሁን ወቅት በአገራችን በሥራ ላይ የሚገኘው ሕግ አንድ በወንጀል የተጠረጠረ ንጹህ ሰው ጉዳዩ ተጣርቶ በነጻ እስኪሰናበት ድረስ የጊዜ ቀጠሮ እስረኛ ሆኖ ነጻነቱ ተገፎ (በሕግ ጥላ ሥር ሆኖ) የወንጀል ምርመራ ሊጣራበት እንደሚችል ከመደንገግ አልፎም ምርመራው ተጣርቶ በዓቃቤ ሕግ ክስ ተመሥርቶ ፍርድ ቤት ከቀረበ በኋላም አንድም ከተከሰሰበት ወንጀል ክብደት እና ግዝፈት አንጻር ሕጉ የዋስትና መብት እንዳያገኝ ብሎ ከከለከለ (የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 63 መሠረት) አልያም ወንጀሉ የዋስትና መብት የማያስከለክል ቢሆንም ዓቃቤ ሕግ ተሟግቶ ካስከለከለ (የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 67 መሠረት) ወይም ደግሞ ተጠርጣሪው ዋስ ማቅረብ ካልቻለ ንጹህነቱ አልያም እኩይነቱ በፍርድ እስኪረጋገጥ ድረስ ተከሳሹ በሕግ ጥላ ሥር የሕግ እስረኛ ሆኖ እንዲቆይ ሕጉ ያስገድዳል፡፡ እዚህ ላይ ነው እንግዲህ የሕግ ጥላው ሥር የንጹህ ሰው ቅጣት የሚጀምረው፡፡

በእነዚህ በተጠቀሱት የሕግ አንቀጾች ሰበብ በእሥር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን እንዲከታተሉ የተደረጉት ንጹሃን ሰዎች መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ ምክንያቱም በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ድንጋጌም ሆነ በሕገ መንግሥታችን ማንም ሰው በፍርድ ቤት የጥፋተኝነት ፍርድ እስኪወሰንበት ድረስ ንጹህ ሆኖ የመገመት መብት እንዳለው የተደነገገ በመሆኑ፡፡ ስለዚህ ንጹሃን እስረኞች ደግሞ ሽንጣቸውን ይዘው ተሟግተው ንጹህ መሆናቸውን በማስመስከር ነጻነታቸውን በፍርድ የማረጋገጥ እድሉ እንሚኖራቸውም ልብ ሊባል ይገባል፡፡

እነዚህ ንጹሃን የወንጀል ተጠርጣሪዎች በታሰሩበት በእያንዳንዱ ቀናት የሚደርስባቸው ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነልቦናዊ ጉዳቶች እንዳሉ ይታመናል፡፡ አንድ ሰው በመታሰሩ ምክንያት በደህና ግዜ የጀመረው የንግድ ሥራው (ቢዝነሱ) ሊከሥርበት ይችላል፡፡ በተከሰሰበት ወንጀል ምክንያትም ከመሐበረሰቡ መገለል ሊያጋጥመው ይችላል፤ በመታሰሩ ምክንያት ትዳሩ ሊፈርስና ቤተሰቡ ሊበተን ይችላል፤ በመታሰሩ ምክንያት የሥራ ዋስትናውን ሊያጣ ይችላል፣ በመታሰሩ ምክንያት የትምህርት ዕድሉ ሊጨናገፍበት ይችላል፣ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ደግሞ ለአይምሮ ወይም ለስነ-ልቦና ችግር ሊዳርገው ይችላል፤ መታሰር እነዚህን ሁሉ አደጋዎች የማድረስ አቅም እንዳለው የሚያጠራጥር አይሆንም፡፡ ሕገ መንግስታችን በአንቀጽ አሥራ ዘጠኝ ስለ ተያዙ (ስለ ታሰሩ) ሰዎች መብት ሲዘረዝር ‹‹ . . . ፍትሕ እንዳይጓደል ሁኔታው የሚጠይቅ ከሆነ የተያዘው ሰው በጥበቃ (በእሥር) እንዲቆይ ፍ/ቤቶች ማዘዝ ይችላሉ›› በማለት የደነገገ ቢሆንም ፍትሕ እንዳይጓደል ሲባል ሳይፈረድበት ጥፋተኛነቱ በውል ሳይረጋገጥ እንዲታሰር የተደረገው ግለሰብ ንጹህ ሆኖ ሲገኝ ለታሰረበት ወይም በመታሰሩ ምክንያት የደረሰበት ጉዳት እንዴት ቸል ሊባል ይችላል?

ፍትሕ እንዳይዛባ ሲባል ከላይ በተመለከቱ የዋስ መብትን በሚያስከለክል ሕግ መሠረት ዋስትና መብት ተነፍገው በእሥር ሲማቅቁ ቆይተው ንጹህነታቸውን በፍርድ ያሳወጁ ንጹሃን (የሕግ ጥላው ሥር ንጹሃን ተቀጪዎች) ለፍትሕ ሲባል ያለአግባብ ታስረው ነጻነታቸውን በማጣት ለጉዳት ለተዳረጉበት ለፍትሕ ሲባል የሚካሱበት መንገድ እንዴት አይኖርም? የፍትሕ አንዱ ዓላማው ተጎጂውን መካስ አይደል እንዴ? ተጎጂው የማይካስ ከሆነስ የሕጉ አሰራር በራሱ ፍትሕን የሚያዛባ መሆኑ አይደል?

በሌሎች አገሮች እንደ ስዊድን፣ ጃፓን የመሳሰሉት አገሮች የሕግ ሥርዓት መሠረት በወንጀል ተከሰው ተይዘው የታሰሩ ተከሳሾች በተከሰሱበት ወንጀል ወንጀለኛ አለመሆናቸው ከተረጋገጠ ወይም ክሱ እንዲቋረጥ ከተደረገ ታሳሪዎች ያለአግባብ ነጻነታቸው ተነፍጎ በእሥር ለቆዩበት ካሳ እንዲከፈላቸው መንግሥትን መጠየቅ የሚያስችላቸው ሕግ አርቅቀው ተግባራዊ የሚያደርጉ ሲሆን፤ ጃፓን ከካሳ በተጨማሪ ታሳሪው ያለ አግባብ ስለመታሰሩና ስለ መልካም ስሙ ታሳሪው በመረጠው የአገሪቱ ሦስት ጋዜጦች ታትሞ እንዲወጣ ታደርጋለች፡፡

እንደ እነ ኦስትሪያ፣ ኖርወይ፣ እና ስፔን ባሉ የሕግ ሥርዓት ደግሞ ንጹሃን ታሳሪዎች ካሳ ሊከፈላቸው የሚገባ መሆኑን ቢቀበሉትም ካሳ የመጠየቅ መብት የፍታብሔር ጥያቄ እንደመሆኑ መጠን የካሳ ይከፈለኝ ጥያቄ አቅራቢው ካሳ ሊከፈለኝ ይገባል የሚልበት ምክንያት ንጹህ ሆኜ እያለ ለእሥር ተዳረኩ የሚል በመሆኑ ንጹህ መሆኑን እንደገና በፍታብሔር ክርክሩ ላይም በማስረጃ ማረጋገጥ ይገባዋል ይላሉ፡፡ ለዚህም እንደ ምክንያት የሚያቀርቡት በወንጀል እና በፍታብሔር ክርክሮች የሚተገበረው የማስረጃ ምዘና ሥርዓት ልዩነትን ነው፡፡ በፍታብሔር ጉዳይ የማስረጃ ምዘና ሥርዓቱ አብላጫውኑ ባስረዳ (Preponderance of Evidence) ሲሆን በወንጀል ክርክር ጉዳይ የማስረጃ ምዘና ሥርዓቱ ደግሞ ‹‹ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ›› (Beyond a reasonable doubt) ተብሎ የሚታወቀው የማስረጃ ምዘና ስታንዳርድ ነው፡፡

በወንጀል ክርክር ጉዳይ የማስረጃ ስታንዳርዱ ‹‹ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ›› የሆነበት ምክንያት Blackstone’s ratio ተብሎ በሚታወቀው ‹‹አንድ ንጹህ ሰው ያለ አግባብ ከሚቀጣ አሥር ጥፋተኞች ቢያመልጡ ይሻላል›› (It is better than ten guilty persons escape than that one innocent suffer) በሚለው በእንግሊዝያዊው የሕግ ፈላስፋ ሰር ዊሊያም ብላክስቶን የተነገረውና በኋላም አለም አቀፍ ተቀባይነት ባገኘው የሕግ መርህ (Principle) መሠረት ነው፡፡ የሰር ዊሊያም ብላክስቶን የሕግ ፍልስፍና ውጤት መጀመሪያ በአገሩ በእንግሊዝ ከዛም በአሜሪካ ተጽእኖውን ካሳረፈ በኋላ ዛሬ ብዙ ሃገሮች በወንጀል ጉዳይ የሚከተሉትን Beyond a reasonable doubt የተባለውን የማስረጃ ምዘና ሥርዓት መወለድ ምክንያት መሆኑን ምሁራን ይስማሙበታል፡፡

ይህ የማስረጃ ሥርዓት አንድ ሰው ጥፋተኛ ነው ለማለት የቀረበው ማስረጃ ከምክንያታዊ ጥርጣሬ በላይ ተከሳሹ ጥፋተኛ ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ መሆን አለበት የሚል ሲሆን እነ ኦስትሪያን የመሳሰሉት አገራትም ተከሳሹ የወንጀል ድርጊቱን ያልፈጸመ መሆኑን ቅንጣት ጥርጣሬ መፍጠሩ ብቻ ከወንጀሉ ነጻ ሊያደርገው ስለሚችል የማስረጃ ምዘና ሥርዓቱ ለተከሳሹ የሚያግዝ በመሆኑ ተከሳሹ በወንጀል ጥፋተኛ ከመባል ያመለጠው በዚህ የማስረጃ ምዘና ሥርዓት ሊሆን ስለሚችል ለካሳ አከፋፈል የፍትሃብሔር ጥያቄ ግን የፍትሐብሔሩ የማስረጃ ምዘና ሥርዓት በሆነው ከሃምሳ በመቶ በላይ በአብላጫ ማስረዳት (Preponderance of Evidence) በሚለው የማስረጃ የምዘና ሥርዓት መሠረት ንጹህ መሆኑን በፍታብሔር ክርክሩ በአብላጫ (ከሃምሳ በመቶ በላይ) በማስረጃ ካረጋገጠ ብቻ ካሳ ሊከፈለው ይገባል ብለው ያምናሉ፡፡

ከላይ በተጠቀሱት በእነ ኦስትሪያም ሆነ በእነ ስዊድን የሕግ ሥርዓት መሠረት ምንም እንኳ የካሳ አጠያየቅ ሥርዓታቸው የማስረጃ ምዘና ሥርዓትን መሠረት አድርገው ቢለያዩም፤ በመርህ ደረጃ በወንጀል ተጠርጥረው ለእሥር የተዳረጉ ንጹሃን የእሥራት ሰለባዎች ለፍትሕ ሲባል ያለ አግባብ በመታሰራቸው ምክንያት ለደረሰባቸው ቁሳዊ እና ሞራላዊ ጉዳት ለፍትሕ ሲባል ካሳ የማግኘት መብት እንዳላቸው የተቀበሉ እና ለዚህም አፈጻጸም ተገቢውን የሕግ ማእቀፍ ቀርጸው ተግባራዊ በማድረጋቸው ንጹሃን የወንጀል ተጠርጣሪዎችም ‹‹እስኪጣራ ለምን እታሰራለሁ›› በሚል ስጋት ከፍትሕ መድረክ ከመሸሽ ይልቅ ያለአግባብ ከታሰሩ መንግሥት ኪሳራውን የሚከፍል መሆኑን ተማምነው ከሽሽት ይልቅ ንጹህነታቸውን በሕግ እንዲያረጋግጡ እምነት እና ድፍረት የሚያጎናጽፋቸው ከመሆኑም ባሻገር፤ መንግሥትም ከፍተኛ ካሳ ላለመክፈል (ላለመክሰር) ሲል ግለሰቦችን እንዲሁ በዘፈቀደ ለረጅም ግዜ እንዲታሰሩ ከማድረግ ይልቅ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲወስድ ያደርገዋል ተብሎ ይታመናል፡፡

ስለዚህ ከላይ በተጠቀሱት አገሮች ልምድ መሠረት የፍትሕ መዛባትን ለማስወገድ ሲባል በወንጀል የተጠረጠረ ንጹህ ሰው በሕግ አግባብ ታስሮ መጨረሻው በወንጀል ጥፋተኛ ሊያደርገው የሚገባ ነገር ያለመኖሩ አስከተደረሰበት ድረስ ይህ ንጹህ ሰው በሕግ አግባብ ለደረሰበት ጉዳት በሕግ አግባብ ሊካስ ይገባዋል፡፡

ሕግ ፍትሕን ሊያመጣ የሚችለው የሌሎችን ስህተት በማረም ብቻ ሳይሆን ሕግ ራሱ በሕግ አግባብ የሚፈጽመውን ስህተት የሚያርም ወይም በሕግ አግባብ የፈጠረውን ክፍተት መድፈን የሚችልበት ሌላ ሕግ ወይም የሕግ አግባብ ሲኖረው ነው፡፡ ለሕጉ ለራሱ ሕግ ሊበጅለት ይገባል ማለት ነው፡፡አለበለዚያ ሕጉ በከፈተው ክፍተትና በፍትሕ አካላት የእርግጠኝነት ስህተት ወይም ቸልተኝነት ሳቢያ ወራት አልፎም ዓመታትን ለእሥራት የተዳረገ ሰለባ ያለ አግባብ ለታሰረበት እና ለተንገላታበት በመታሰር ምክንያት በሕይወቱ ላይ ለሚደርሰው መመሰቃቀል ተገቢውን ካሳ እንዲያገኝ የሚያደርገው የሕግ ማእቀፍ በሌለበት የተጠርጣሪው ወይም የተከሳሹ ነጻ መባል ምን ሊፈይድ? ምክንያቱም ተከሳሹ በመከሰሱ ብቻ ሳይፈረድበት እንደ ወንጀለኛ ታስሯል፣ በሕግ ጥላ ሥር ሆኖ ተንገላቷል፤ ፍርዱ በሕግ ጥላ ሥር ቅጣቱን እንዲቀበል ለተደረገው ንጹህ ሰው በቅጣቱ ምክንያት ያጣውን ነገር ካልመለሰለት፤ ፍርዱ በሕግ ጥላ ሥር ቅጣቱን እንዲቀበል ለተደረገው ንጹህ ሰው የደረሰበትን የህሊና ጉዳት ካላጠገነለት፤ ይህ ሁሉ ከሆነ በኋላ ‹‹ነጻ ነህ›› የሚል ፍርድ ለንጹህ ሰው ምን ሊበጀው?

በመጨረሻም Z.W. Staatman የተባለውን አምስተርዳሙን ምሁር አባባል በመጥቀስ ልሰናበት 
‹‹Detention is a necessary evil, and as long as there is no other measure, it cannot be abolished and the state has a right to employ it. But should the individual be made to bear the consequences of this clear example of our institutional imperfection?›› ቸር እንሰንብት፡፡ ሃሳባችሁን ጣል ጣል አድርጉ!

{advpoll id='3' view_result='0' width='350' position='center'}

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

Corporate Social Responsibility as a New Way of Ad...
የሕግ ሙያ አገልግሎትን መቆጣጠር፣ የሕዝብ ጥቅም፣ የግለሰብ ፍላጎትና የውድድር ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024