Font size: +
8 minutes reading time (1514 words)

"ድፍረት" ፊልም - የቅጅ መብት ጥበቃ ለታሪካዊ እውነታ ወይስ ለአእምሮ ፈጠራ?

በአእምሯዊ ንብረት ማዕቀፍ ተካተው በህግ ጥበቃ ከሚደረግላቸው ኢ-ቁሳዊ የንብረት ባለቤትነት መብቶች መካከል የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የቅጅ መብት ጥበቃ ጽንሰ ሃሳብ ውልደት የኃልዮሽ ተጉዞ በታሪክ ተጠቃሽ ወደ ሆነውና  ከታላቋ ብሪታንያ ተነስቶ ወደ ሌሎች የምዕራብ አውሮፓ ሀገራት እና ሰሜን አሜሪካ ወደ ተስፋፋው የኢንዲስትሪ አብዮት ይወስደናል፡፡ የዚህ ዘመን ካፈራቸው እውቅ ሳይንቲስቶች መካከል አንዱ በሆነው ጆን ጉተንበርግ የተፈጠረው የህትመት ማሽን ለቅጅ መብት ጥያቄ መጠንሰስ ምክንያት በመሆን የኋላ የኋላም በወቅቱ የብሪታንያ ንግስት በነበሩት ንግስት አን ስም ለተሰየመው የአን ስታቲዩት (Anne Statute) ተብሎ ለሚታወቀው የህግ ማዕቀፍ እ.ኤ.አ በ1710 ዓ.ም መደንገግ ምክንያት ሆኗል፡፡ የህትመት ማሽኑ መፈጠር በወቅቱ በነበሩ ደራስያን የሚጻፉ መጽሃፍት በፍጥነት እየተባዙ ወደ አንባቢዎች እጅ እንዲደርሱ በማድረግ ከአሳታሚዎች ፍቃድ ውጪ የሚታተሙ መጽሃፍት እየበዙ እንዲመጡ አስገድዷል፡፡ ይህም በአሳታሚዎች ላይ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ ጉዳት እያደረሰ በመምጣቱ በወቅቱ በተሰሚነት እና በገንዘብ አቅም ገናና የነበሩት አሳታሚዎች መንግስት ለመብታቸው መከበር ህጋዊ ሽፋን ይሰጣቸው ዘንድ መወትወታቸውን ተከትሎ ነበር የአን ስታቲዩት (Anne Statute) በሀገረ እንግሊዝ ሊታወጅ የቻለው፡፡

በዚህ መልኩ ወጥ የሆነ የህግ ማዕቀፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ወጥቶለት በሀገረ እንግሊዝ የተጀመረው የቅጅ መብት ጥበቃ በጎረቤት የአውሮፓ ሀገራት እየተስፋፋ የመጣውን የመጻሃፍት ህትመት እና ስርጭት ተከትሎ ድንበር ተሻጋሪ የሆኑ የህግ ከለላዎችን መሻቱ አልቀረም፡፡ በዚህም ሳቢያ ዓለም ዓቀፍ የቅጅ መብት ስምምነቶች አስፈላጊነት አሳማኝ እየሆነ በመምጣቱ ሀገራት በዜጎቻቸው የሚሰሩ የፈጠራ ስራዎች በሌሎች ሀገራት ውስጥ የህግ ከለላ እንዲያገኙ የሚያስችሉ ስምምነቶችን በመፈራረም በድንበር ተወስኖ የነበረው የህግ ከለላ ዓለም ዓቀፋዊ ይዘት እንዲይዝ አድርገዋል፡፡ በዘርፉ ከተደረጉ ስምምነቶች መካከልም የበርን ስነጽሁፍ እና ኪነ ጥበብ ስራዎች ጥበቃ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት እና ዩኒቨርሳል የቅጅ መብት ኮንቬንሽን በቀደምትነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ከፍ ሲል በጥቅሉ በተገለጸው መልኩ እየተስፋፋ የመጣው የቅጅ መብት ጥበቃ ጽንስ ሃሳብ እየጎለበተ እና እየዳበረ መጥቶ በኪነ-ጥበብ እና በስነ-ጥበብ ዘርፍ ከስራ አመንጪዎች ጋር ተጓዳኝ ተሳትፎ ላላቸው እንደ ከዋኝ፣ የድምጽ ሪከርዲንግ ፕሮዲውሰሮች እና የብሮድካስት ተቋማት የተዛማጅ መብቶች ባለቤት እንዲሆኑ በማድረግ የዛሬውን የተሟላ የህግ ጥበቃ ስርዓት መልክ ለመያዝ በቅቷል፡፡

ሀገራችንም በ1957ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ እና በ1960 ዓ.ም በደነገገችው የፍትሐብሔር ህግ የቅጅ መብት ጥበቃን የሚመለከቱ ድንጋጌዎች በማካተት የፈጠራ ስራ አመንጪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የህግ ከለላ እንዲኖራቸው ማድረግ ችላለች፡፡ ሆኖም የእነዚህ ህጎች ወሰንም ሆነ አተገባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ በአይነት እና በይዘት እየጨመረ የመጣውን የፈጠራ ስራዎች ግብይት ሊመጥኑ የሚችሉ ባለመሆናቸው በ1996 ዓ.ም የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁ. 410/96 ን በመደንገግ ተግባራዊ እያደረገች ትገኛለች፡፡

የዚህ ጽሁፍ ዋነኛ ዳሰሳ የቅጅ መብት ጥበቃ ለታሪካዊ እውነታ ወይስ ለአእምሮ ፈጠራ? የሚለውን ርዕሰ ጉዳይ በአሁን ወቅት በስራ ላይ በሚገኘው የሀገራችን የህግ ማዕቀፍም ሆነ በዓለም ዓቀፍ ስምምነቶች ተቀባይነት ባገኙ ዓለም ዐቀፋዊ መርሆች እይታ መቃኘት ነውና የቅጅን መብት ጥበቃ አጀማመር ታሪካዊ ዳራ በዚህ መልኩ ከጠቆምኩ ወደዚሁ አንኳር ነጥብ ላምራ፡፡ መግቢያዬ ላይ እንደጠቆምኩት የቅጅ መብት ጥበቃ ጽንሰ ሃሳብ የጀመረው ለአእምሮ ፈጠራ ውጤት ለሆኑ የስነ ጽሁፍ ስራዎች ጥበቃ በመስጠት ነው፡፡ ለእነዚህ የፈጠራ ስራዎች ጥበቃ ለማድረግ የተደነገጉ የህግ ማዕቀፎች ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻሉ መጥተው ሌሎች በኪነ ጥበብ፣ በስነ ጥበብ እና በሳይንሳዊ መስክ የተሰሩ የፈጠራ ስራዎች የጥበቃው አካል እንዲሆኑ ተደርገዋል፡፡ በሀገራችን የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ አንቀጽ 2(30) ስር እንደተደነገገው በአዋጁ ጥበቃ የሚያገኙ ስራዎች እንደ መጽሃፍ፣ ቡክሌት፣ መጣጥፍ፣ ንግግር፣ ሌክቸር፣ ለአንድ ለተወሰነ የህብረተሰብ ክፍል የሚደረግ መልዕክት አዘል ንግግር፣ የሃይማኖት ስብከት እና በይዘት ደረጃ ሌላ በቃል የቀረበ ስራ፣ ድራማ፣ ድራማዊ የሙዚቃ ስራ፣ በእንቅስቃሴ ብቻ የሚቀርብ ድራማ /ፓንቶምይምስ/፣ የመድረክ ውዝዋዜ፣ የሙዚቃ ስራ፣ ኦድዮቪዥዋል ስራ፣ የፎቶግራፍ ስራ፣ የስዕል ስራ፣ ካርታ፣ ፕላን፣ ስዕላዊ መግለጫ፣ የንድፍ ስራ እንዲሁም የጥልፍና የፊደል ቅርጽ ስራዎች፣ ኪነ - ህንጻ፣ የሀውልት፣ የቅርጻ ቅርጽ እና የኮምፒውተር ፕሮግራሞችን እና የመሳሰሉትን ያካትታል፡፡ ከዚህ የህግ ድንጋጌ በግልጽ መረዳት የምንችለው የቅጅ መብት ባለቤት ለመሆን በመጀመሪያ ደረጃ ከላይ ከተዘረዘሩ ወይም መሰል ስራዎች መካከል የአንዱ ባለቤት መሆን የግድ ይሆናል፡፡ በቅጅ መብት ጥበቃ ዘርፍ የመጀመሪያ ሰፊ ተቀባይነት ባገኘው የበርን የስነ ጽሁፍ እና የኪነጥበብ ስራዎች ጥበቃ ዓለም ዓቀፍ ስምምነት አንቀጽ 2 ላይም በግልጽ እንደተመላከተው የስምምነቱ አባል ሀገራት የቅጅ መብት ጥበቃ እንዲሰጡ የሚገደዱት ከላይ በተዘረዘሩት የስራ ዘርፎች አስቀድሞ የተሰራ ስራ ሲኖር ብቻ ነው፡፡

በቅርቡ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ታይቶ ከፍተኛ አድናቆት የተቸረው እና በሀገራችንም በከፍተኛ ጉጉት ሲጠበቅ ቆይቶ ነሐሴ 28 ቀን 2006 ዓ.ም. በተካሄደው የምርቃት ስነ ስርዓት ላይ በቅጅ መብት የይገባኛል የክስ አቤቱታ ሳብያ ለፍርድ ቤት እግድ የተዳረገው "ድፍረት" ፊልም ለዚህ ጽሁፍ ርዕሰ ጉዳይ አይነተኛ ማሳያ ሊሆን የሚችል ነው፡፡ የፊልሙን በእውነተኛ ታሪክ ላይ መሰራት እና በፊልሙ ውስጥ ተተረከ የተባለው እውነተኛ ታሪክ ባለቤት በሆነችው ወ/ሮ አበራሽ በቀለ የቀረበውን የባለቤትነት ይገባኛል ጥያቄ ተከትሎ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረበው የክስ አቤቱታ እንደሚያሳየው ክሱ የፊልሙ ፕሮዲውሰር የእውነተኛ ታሪኳን ባለቤት ፍቃድ ሳያገኝ በታሪኩ ላይ የተመሰረተ ፊልም መስራቱ የቅጅ መብት ጥሰት በመሆኑ ፕሮዲውሰሩ በክሱ የተመለከተውን የገንዘብ ካሳ ከከሳሾች አንዷ ለሆነችው ወ/ሮ አበራሽ በቀለ እንዲከፍል የቀረበ ነው፡፡ ማንኛውም መብቴ ተጥሷል የሚል አካል ጉዳዩን ለሚመለከተው የዳኝነት አካል አቅርቦ ዳኝነት መጠየቁ ህጋዊ እና በምንም መሠረት ሊነቀፍ የሚችል ባይሆንም እንዲህ ያሉ አስተማሪ እና የህጉን ይዘት እና መንፈስ ከመሰረቱ እንድንፈትሽ የሚያስገድዱን ጉዳዮች ሲያጋጥሙ የክሱ ይዘት ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ ህግ አንጻር ያለውን እንደምታ መመልከቱ ከዚህ በኋላ ለሚመጡ መሰል የህግ ጥያቄዎች አስተማሪነቱ ጉልህ በመሆኑ መሰል ሃሳቦችን በውይይት ማዳበሩ ለዘርፉ እድገት የራሱን አስተዋጽኦ ማበርከቱ የሚካድ አይሆንም፡፡ በነገራችን ላይ ከፍ ሲል የተጠቀሰው ጉዳይ በሽምግልና ድርድር እልባት ያገኘ በመሆኑ ይህ ጽሁፍ በፍርድ ቤት የተያዘን ጉዳይ ለማብራራት የቀረበ አለመሆኑ ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ይህንን ታሳቢ በማድረግ ውይይታችንን ስንቀጥል ከላይ በተጠቆመው ጉዳይ ሊነሱ ከሚችሉ ጥያቄዎች መካከል ለመሆኑ ፊልሙ መነሻ ተደረገበት የተባለውን ታሪክ ወይም አንድ ሰው የኖረውን ታሪክ በቅጅ መብት ህግ እንዲያስጠብቅ የሚያስችለው ህጋዊ መሰረት አለው ወይ ? ፣የታሪክ እውነታ በቅጅ መብት ጥበቃ ህግ አይን የፈጠራ ውጤት ነው ወይ ?፣ እንዲሁም የቅጅ መብት ህግ የሚያስጠብቀው ሃሳብን (idea) ወይስ ሃሳቡ የተገለጸበትን መንገድ (expression) ? የሚሉት ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሊነሱ የሚችሉ ዋነኞች የቅጅ መብት ጥበቃ ጽንሰ ሃሳብ እና የህግ ማዕቀፍ አንኳር ነጥቦች ናቸው፡፡

አንድ ታሪክ እራሱን ችሎ በቅጅ መብት ጥበቃ ህግ የህግ ከለላ አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ የመጀመሪያው ማመሳከሪያ ሊሆነን የሚችለው ነጥብ የቅጅ መብት ጽንሰ ሃሳብ መነሻ ትንተና ነው፡፡ የቅጅ መብት ጥበቃ ኢ-ቁሳዊ ከሆኑ የንብረት ባለቤትነት መብቶች መካከል አንዱ በመሆኑ በጽሁፉ መግቢያ ላይ ተጠቁሟል፡፡ ይህም የቅጅ መብት ባለቤትነት የንብረት መብት ባለቤትነት አንደኛው ገጽታ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ አንድ ሰው ደግሞ የንብረት ባለቤት ሊሆን የሚችለው ንብረቱ ቀድሞውኑ በርሱ የተፈጠረ ወይም የተሰራ ሲሆን አልያም በአጠቃላይ የንብረት ህግ መርህ መሰረት ህጋዊ በሆነ መልኩ ከሌላ ባለቤት ወደ እርሱ የተላለፈ እንደሆነ መሆኑን አጠቃላዩን የንብረት ህግ በማየት መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አንጻር የአንድን ታሪክ ባለቤትነት ስናነሳ በታሪኩ ውስጥ የተገለጸውን ሃሳብ ባለቤትነት ማንሳታችን መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በመሆኑም የታሪኩ ባለቤት ነኝ የሚለው የባለቤትነት ጥያቄ በታሪኩ ውስጥ ያለው ሃሳብ ባለቤት ነኝ የሚል የህግ ውጤት ያለው ይሆናል፡፡ በአንድ ሃሳብ ላይ ደግሞ የቅጅ መብት ባለቤትነት የማይቋቋም ስለመሆኑ በቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ ቁ. 410/96 አንቀጽ 5(ሀ) ስር በግልጽ ተመላክቷል፡፡ በሌላ በኩል አዋጁ ጥበቃ የሚደረግላቸውን ስራዎች በአንቀጽ 2(30) ስር ሲዘረዝር የቅጅ መብት ባለቤትነትን ለማቋቋም አስቀድሞ የተሰራ የፈጠራ ስራ መኖር እንዳለበት የሚያስገንዝብ ነው፡፡ ይህም የቅጅ መብት ጥበቃ ህግ ሊያሳካ ከሚፈልገው ዓላማ እና በዓለም ዓቀፍ ደረጃ ተቀባይነት ካገኙ መርሆች አንጻር ሲታይ ሰዎች በአንድ በተወሰነ ጊዜ እና ቦታ በተፈጠረ የታሪክ ክስተት ላይ የባለቤትነት መብት ሊያቋቁሙ የሚችሉበትን የህግ አግባብ ሳይሆን ይህን የታሪክ ክስተት ተከትሎ ዕውቀታቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጊዜያቸውን እና ገንዘባቸውን አውጥተው ለሚሰሩዋቸው የፈጠራ ስራዎች ህጋዊ ከለላ ለመስጠት የቆመ መሆኑን መረዳት ይቻላል፡፡

በሌላ በኩል አንድ ሰው የኖረውን ታሪክ በቅጅ መብት ጥበቃ ህግ እንዲጠበቅለት ለማድረግ ይችላል ወይ ? የሚለው ጥያቄ አንድ ሰው ለኖረው ህይወት ደራሲ እርሱ ራሱ ነው ወይ? የሚለውን ጥያቄ ማጫሩ አይቀርም፡፡ ምክንያቱም በቅጅ መብት ጥበቃ ህግ የአእምሮ ፈጠራ ውጤት ያልሆነ ስራ ሊጠበቅ አይችልምና ነው፡፡ በአጠቃላይ የህይወት መርህ እንደሚታወቀው አንድ ሰው የዕለት ተዕለት ህይወቱን እራሱ በፈቀደው እንዲሁም እንዲኖር በተገደደውም መንገድ ነው የሚመራው፡፡ ስለዚህ ሙሉ ለሙሉ የእከሌ ህይወት የራሱ የአእምሮ ፈጠራ ውጤት ነው ልንል የምንችልበት ዕድል ጠባብ ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር አንድ በተግባር የተኖረ ህይወት በአንድ በተወሰነ መልኩ እስካልተገለጸ ድረስ በታሪክነት ወይም በሃሳብ ደረጃ የሚቀር ነው የሚሆነው፡፡ በአንድ ቀላል ምሳሌ ለማየት ያክል አንድ ሰው የዕለት ተዕለት ህይወቱን በዕለት ማስታወሻው ላይ የሚጽፍ ቢሆን እና አንድ የፊልም ፕሮዲውሰር የዚህን የዕለት ማስታወሻ ጸሃፊ ፍቃድ ሳይጠይቅ የማስታወሻውን ጽሁፍ ወደ ፊልም ቢቀይረው የባለታሪኩ የህይወት ታሪክ በጽሁፍ መልክ ወደ አንድ የፈጠራ ስራ አይነት በመቀየሩ ሳብያ ጸሃፊው በጽሁፉ ላይ ያለው የቅጅ መብት ተጥሷል ልንል እንችላለን እንጂ በታሪኩ ላይ ያለው የባለቤትነት መብት ተጥሷል ልንል አንችልም፡፡

እንዲሁም አንድ የታሪክ እውነታ በራሱ በቅጅ መብት ጥበቃ ህግ አይን ሲታይ የፈጠራ ስራ ሊሆን የማይቸል መሆኑ ከፍ ሲል ከተገለጸው ሃሳብ ጋር ተያይዞ የሚታይ ነው፡፡ ምክንያቱም የህጉ ትኩረት የታሪክ እውነታው ከተገለጸበት መንገድ ጋር እንጂ ከራሱ ከታረኩ ጋር አይደለም፡፡ ሌላው ከዚሁ ተነጥሎ የማይታየው እና በበርካታ ሀገራት በሚገኙ የዘርፉ ምሁራን ጭምር አከራካሪ የሆነው ርዕሰ ጉዳይ የቅጅ መብት ጥበቃ ህግ የሚያስጠብቀው ሃሳብን (idea) ወይስ የሃሳቡን አገላለጽ (form of expression) የሚለው አብይ ጉዳይ ነው፡፡ ይህ የሃሳብ - ግልጸት ንጽጽር (expression-idea dichotomy) የአንድ ሃሳብ አመንጪዎች ህጋዊ የባለቤትነት ከለላ ሊሰጣቸው ይገባል በሚሉ እና በአንጻሩ ደግሞ ማንም ሰው የአንድ ሃሳብ ብቸኛ ባለቤትነት መብት (monopoly of ideas) ሊሰጠው አይገባም ይህም የሚሆን ከሆነ የሌሎችን የማሰብ ነጻነት የሚያጠብ ነው በሚል የሚከራከሩ ናቸው፡፡ ይህንንም ተከትሎ በርካታ ሀገራት በቅጅ መብት ጥበቃ ህጎቻቸው ማንኛውንም ሃሳብ ከጥበቃ ወሰን ውጪ በማድረግ ለሁለተኛው መከራከሪያ ሃሳብ እውቅና ይሰጣሉ፡፡ ሀገራችንም ይህንኑ በሰፊው ተቀባይነት ያገኘ መርህ በመከተል በአዋጁ አንቀጽ 5 (ሀ) ላይ ማንኛውም ሃሳብ የቅጅ መብት ጥበቃ እንደማይደረግለት በግልጽ ደንግጋለች፡፡

በመሆኑም ከዚህ ጽሁፍ ርዕሰ ጉዳይ ጋር ተያይዞ በተነሳው የ "ድፍረት" ፊልም የባለቤትነት ጥያቄ ላይ የቀረቡት የህግ እና የአመክንዮት መሠረቶች በዋናነት ከቅጅና ተዛማጅ መብቶች ጥበቃ አዋጅ አንጻር ሲታዩ ከህጉ መንፈስ እና ዓላማ በእጅጉ የራቁ እና ከቅጅ መብት ጽንሰ ሃሳብ ያፈነገጡ መሆናቸውን ማየት ይቻላል፡፡ ይህም የህጉ አፈጻጸም እና አተገባበር ያለበትን ጅምር የእድገት ደረጃ ታሳበ በማድረግ በዘርፉ ላይ ለሚነሱ መሰል ጉዳዮች ሊሰጡ የሚገባቸውን ተጨማሪ ሃሳቦች አስፈላጊነት የሚያሳይ ነው፡፡ በአእምሯዊ ንብረት ጥበቃም ሆነ የቅጅና ተዛማጅ መብቶች ባለቤትነትን በልዩ ሁኔታ ለማረጋገጥ የሚወጡ የህግ ማዕቀፎች በአንድ በኩል ለፈጠራ ባለሙያዎች ተገቢውን ህጋዊ ከለላ በመስጠት የፈጠራ ስራዎችን ለማበረታታት ያለሙ እና በሌላ በኩል ደግሞ የሰፊውን ህብረተሰብ የተጠቃሚነት መብት ሚዛን ለማስጠበቅ የቆሙ በመሆናቸው መሠረታዊ ዓላማቸውን ሳይስቱ ተግባራዊ ሊደረጉ ይገባል፡፡ ለዚህም የህግ ባለሙያዎች ለህጉ መርህ መጠበቅ እና ለሙያቸው ታማኝ በመሆን የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ አያጠያይቅም፡፡ ይህም በቀጣይ ሊያጋጥሙ የሚችሉ መሰል የህግ ጥያቄዎችን ለማስተናገድ በዘርፉ ባለሙያዎች ዘንድ በቂ ግንዛቤ እንዲፈጠር በር የሚከፍት አጋጣሚ በመሆኑ ትምህርት ሊወሰድበት ይገባል፡፡  

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሳይበር ክልልና የሀገሮች የለአላዊነት ስልጣን እስከ ምን ድረስ
Interim measures of protection in International Co...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 21 November 2024