Font size: +
7 minutes reading time (1396 words)

ሳይፋቱ ፍቺ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ

ቤተሰብ የአንድ ማኅበረሰብ በጣም ጠቃሚ እና መሠረት የሆነ አካል ነው፡፡ ቤተሰብ አንድ ግለሰብን ከአጠቃላይ ማኅበረሰብ ጋር የሚያገናኝ ታላቅ ድልድይ ነው፡፡ እንዲሁም ተፈጥሮዊ ኢኮነሚያዊ እና ማኅበረሰባዊ ጥቅም አለው፡፡ በእርግጥ ቤተሰብ በቁጥር ትንሽ ሊሆን ይችላል ነገረግን የአንድ ቤተሰብ መፍረስ አጠቃላይ ማኅበረሰቡን ይጎዳል፡፡ ቤተሰብ በጋብቻ እንደሚመሠረት ሁሉ በፍቺ ይፈርሳል፡፡ በተለምዶ በቤተሰብ ሕጋችን ከተቀመጡት ጋብቻ ከሚፈርስባቸው መንገዶች በተጨማሪ ተጋቢዎች ለተለያዩ ምክንያቶች ሲሉ ህጋዊ ፍቺ ሳይፈፅሙ የሚያደርጉት መለያየት አንዱ ሲሆን ሳይፋቱ ፍቺ የሚል ስያሜ ተሰጥቶታል፡፡ ይህ ሳይፋቱ ፍቺ ምንም እንኳን በሕግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ ባይሆንም እንኳን ውርስ ላይ የራሱ የሆነ አስተዋፅኦ አሉት፡፡

2. ጋብቻና ውጤቶቹ

በተሸሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ መሠረት ጋብቻ በተለያዩ ሰነ-ስረዓቶች ለፈፀም ይችላል፡፡ እነሱም በክብር መዝገብ ሹም ፊት፣በሐይማኖት እና በባህል መሠረት የሚፈፀሙ የጋብቻ አይነቶች ናቸው ሲል አንቀፅ 1 ያስቀምጣል፡፡ በተጨማሪም ጋብቻ ከላይ በተጠቀሱት በአንዳቸው ስነ-ስርዓቶች ቢፈፀም እንኳን ውጤቱም አንድ መሆኑን የዚሁ ሕግ አንቀፅ 40 ያትታል፡፡ ጋብቻ በተጋቢዎቹ ላይ ሁለት ዓይነት ውጤት ይኖረዋል፡፡ የመጀመሪያው በተጋቢዎች ግለዊ ግንኙነት ላይ የሚኖረው ውጤት ሲሆን፤ በስሩም የመከባበር ፣የመተጋገዝና የመደጋገፍ ግዴታ ፣ ቤተሰብን በጋራ የመስተዳደር እና በጋራ አንድ ላይ የመኖር ግዴታዎችን ያቅፋል፡፡ ሁለተኛው ውጤት ደግሞ ጋብቻ በተጋቢዎች ንብረት ላይ የሚኖረው ውጤት ነው፡፡ ይህም ተጋቢዎች  ጋብቻቸውን በሚፈፅሙበት ጊዜ በግል የነበሯቸው ንብረቶች ወይም ከጋብቻ በኋላ በውርስ እና በስጦታ በየግላቸው ያገኙዋቸው ንብረቶች የግል ንበረታቸው ሆነው ሲቀሩ ከዚህ ውጪ ያሉ ንብረቶች በሙሉ የጋራ  ንብረት ይሆናሉ፡፡

ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበረሰባዊ፣ ባህላዊ፣ ሰዋዊ እና ፖለቲካዊ መብቶችን ያፀደቀች ሲሆን፣ በሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ 34 ስር ቤተሰብ አለማቀፋዊ መብቶችን ባማከለ ሁኔታ ተገልጿል፡፡ በዚህም መሠረት አንቀጹ ቤተሰብ ለአንድ ማኅበረሰብ ሁነኛ ምንጭ ነው በማለት ያስቀምጠዋል፡፡ በዚሁ አንቀፅ ንዑስ አነቀፅ 5 ስር ሕገ መንግሥቱ ለሀይማኖታዊ እና ባህላዊ ፍ/ቤቶች የቤተሰብ ጉዳይን አንዲያስተናግዱ ቢፈቅድም የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በአንቀፅ 322 እና የክልል የቤተሰብ ሕጎች ቤተሰባዊ ጉዳዮች ለታዩ የሚችሉት በፍ/ቤት ስልጣን ስር ነው በማለት አትተዋል፡፡ ስለ ጋብቻ እና ውጤቶቹ ይህን ያህል ካልን በመቀጠል ደግሞ ጋብቻ የሚፈርስባቸውን መንገዶች እንመልከት፡፡ 

 

3. ጋብቻ የሚፈርስባቸው መንገዶች

ጋብቻን ለመፈፀም መከተል የሚገቡ ስርዓቶች እንዳሉ ሁሉ ለማፍረስም ራሱን የቻለ ስረዓቶች አሉት፡፡ የተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ በአንቀፅ 74 ንዑስ አንቀፅ አንድ ስር እንደሚያመለክተው ጋብቻ የተፈፀመበት ስርዓት ማናቸውም አይነት ቢሆን የጋብቻው መፍረስና የሚያስከትለው ውጤት አንድ አይነት ነው፡፡

ምንም እንኳን የጋብቻ ፅንሰ ሀሳብ አንድ ወንድ እና ሴትን በትዳር እስከ ህልፈተ ህይወታቸው በፍቅርና በምርጫ ማስተሳሰር ቢሆንም በተግባር ግን ሁል ጊዜ ተፈፃሚ አይሆንም፤ ምክንያቱም ጋብቻ በብዙ ምክንያቶች ይፈርሳል፡፡ እነዚህም ምክንያቶች በሁለት ሲከፈሉ  የመጀመሪያው በህጉ አሰራር መሠረት ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በተጋቢዎች ድርጊት ነው፡፡  (ይህ ሁለተኛው መንገድ ፍቺ ይባላል)

በህጉ አሰራር ጋብቻ የሚፈርሰው የተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ በአንቀፅ 75 (1 እና 2) መሠረት በሚከተሉት መንገዶች ነው፡፡

  • ከተጋቢዎች አንዱ ሲሞት
  • ከተጋቢዎች አንዱ ላይ በፍርድ ቤት የመጥፋት ውሳኔ ሲሰጥ
  • ጋብቻ ለመፈፀም መሟላት ካለባቸው ሁኔታዎች አንዱ በመጣሱ ምክንያት በሕግ መሠረት ጋብቻው እንዲፈርስ ሲወሰን ናቸው፡፡ ለምሳሌ ነፃ እና ሙሉ ፍቃድ አለመኖር፣ተጋቢዎቹ 18 ዓመት ካልሞላቸው እና የስጋ ዝምድና ካላቸው ወ.ዘ.ተ የሚሉ በተሻሻለው የኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ከአንቀፅ 6 እስከ 16 ድረስ የተቀመጡ ናቸው፡፡

በተጋቢዎች ድርጊት ጋብቻ የሚፈርሰው ደግሞ በፍቺ ነው፡፡ ይህም ሁለት አይነት መንገዶች አሉት፡-

  1. በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 77 እስከ 80 መሠረት ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት የወሰኑ እንደሆነ የፍቺ ስምምነታቸውን እና ፍቺው የሚያስከትለውን ውጤት በጽሁፍ ለፍ/ቤት በማቅረብ ፍቺው እንዲፀድቅላቸው ሲጠይቁ ይህ በስምምነት ለመፋታት የሚቀርብ ጥያቄ ይባላል፡፡ በተጨማሪም ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት በሚያቀርቡት ጥያቄ ላይ  ለመፋታት የወሰኑበትን ምክንያት እንዲገልጹ አይገደዱም፡፡ ነገር ግን ተጋብተው ስድስት ወር ያልሞላቸው ባልና ሚስት በስምምነት ለመፋታት አይፈቀድላቸውም፡፡ ፍርድ ቤቱም የፍቺ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ይመክራል፤ ሀሳባቸውን ካልቀይሩ ግን ከሶስት ወር የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡ ባልና ሚስት ሀሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ጀምሮ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ ጉዳያቸውን እንደገና ማንቀሳቀስ ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱ የፍቺ ውሳኔ በሚያስተላልፍበት ጊዜ የባልና ሚስት ነፃ ፈቃድ እና ፍላጎት መሆኑን፤ እንዲሁም ስምምነቱም ከሕግ እና ሞራል ጋር የማይቃረን መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ነው፡፡      
  2. በቤተሰብ ህጉ አንቀፅ 81 እስከ 84 መሠረት ከባልና ሚስት አንደኛው ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት በመሆን ጋብቻቸው በፍቺ እንዲፈርስ ለፍ/ቤት ጥያቄ ሲያቀርቡ ( ይህ ደግሞ የፍቺ ጥያቄ ማቅረብ ይባላል)፡፡ በዚህ አይነት ፍቺ ከባልና ሚስት አንደኛው ወይም ሁለቱም ተጋቢዎች በአንድነት በመሆን የፍቺ ጥያቄ ሲያቀርቡ ፍቺ ለመጠየቅ ምክንያት የሆናቸውን ጉዳይ መግለጽ ይችላሉ፡፡ ፍርድ ቤቱም የፍቺ ጥያቄ በሚቀርብበት ጊዜ ሀሳባቸውን እንዲቀይሩ ይመክራል፤ ጊዜያዊ ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ጉዳዮች ላይ ለምሳሌ ስለሚተዳደሩበት እና ስለሚኖሩበት ሁኔታና ቦታ ፣ስለልጆቻቸው አጠባበቅ ፣እንዲሁም ስለንብረታቸው አስተዳደር ትዕዛዝ ይሰጣል፤ ሀሳባቸውን ካልቀይሩ ግን ባለትዳሮቹ በመረጧቸው ሽማግሌዎች አማካይነት ጉዳያቸውን በዕርቅ እንዲጨርሱ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁንም ሀሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ ከሶስት ወር የማይበልጥ የማሰላሰያ ጊዜ ይሰጣቸዋል፡፡ ባልና ሚስት ሀሳባቸውን የማይለውጡ ከሆነ የማሰላሰያ ጊዜ ካበቃበት ጀምሮ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ፍርድ ቤቱ የፍቺ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ በሌላ በኩል ፍርድ ቤቱ ከፍቺ በኋላ ፍቺው ስለሚያስከትለው ውጤት እንዲስማሙ ባልና ሚስትን ይጠይቃቸዋል፤ መስማማት ካልቻሉ ግን ፍርድ ቤቱ ራሱ የፍቺ ውጤቱ ላይ ውሳኔ ያስተላልፋል፡፡ በመጨረሻም ከባልና ሚስት አንዱ ለፍቺው ምክንያት ከሆኑ በሌላኛው ተጋቢ ላይ ለደረሰው ጉዳት በዳዩ ተመጣጣኝ የሆነ ካሳ እንዲከፍል ሊወሰን ይችላል፡፡   

 

4. ሳይፋቱ ፍቺ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ

4.1 በሕግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ

የዚህ አይነት ፍቺ የሚያትተው በሦስቱም የጋብቻ ስርዓቶች የተፈፀመ ጋብቻ የሚያበቃው በፍ/ቤት ሲቋጭ ነው፡፡ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ በምዕራፍ አራት አንቀፅ 78 እና 82 በሕግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ አካሄዶቹንና ስልጣን ባለው ፍ/ቤት መሆን እናዳለበት ያስቀምጣል፡፡ ይህም ተጋቢዎቹ ከሁለቱ የፍቺ መንገዶች በመረጡት መንገድ መፍታት ሲወስኑ ፍቺውን የመወሰን ስልጣን ያለው ፍ/ቤት መሆኑን ያትታል፡፡ ውድ አድማጮቻችን እስከ አሁን በቤተሰብ ህጉ የተቀመጡ ጋብቻ የሚፈርስባቸው መንገዶችን ተመልክተናል፡፡ በመቀጠል ደግሞ በሀገራችን ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር እና ከሌሎች ሀገሮች ልምድ በመቅሰም በህጉ ከተቀመጡት የፍቺ አይነቶች በተጨማሪ ጋብቻን የሚያፈርስ መንገድ እንመለከታለን፡፡  

4.2 ሳይፋቱ ፍቺ

ሳይፋቱ ፍቺ ማለት በሕግ አግባብ የሚደረግ ፍቺ ሳይሆን በተግባር የፍ/ቤት ውሳኔ ሳይጠብቁ የሚድረግ መለያየት ነው፡፡ ይህም ማለት ሳይፋቱ ፍቺ ህጉ ያስቀመጠውን የፍቺ ስነ-ስርዓት ሳይከተል እንዲሁም የፍ/ቤት ጣልቃ ገብነት ሳይኖረው በተጋቢዎች ስምምነት ብቻ የሚደረግ የፍቺ አይነት ነው፡፡ የዚህ አይነት ፍቺ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ቦታ ያልተሰጠው ሲሆን የፌደራል ጠቅላይ ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ አስከሰጠበት ድረስ የተከለከለ የፍቺ አይነት ነበር፡፡

ሳይፋቱ ፍቺ የሚለው ፅንሰ ሀሳብ እንዲመጣ ምክንያት የሆነው ወይም የተደረገው የጋብቻ ውጤቶች መቆም ነው፡፡ በአብዛኛው ጋብቻ ሲኖር ግላዊ እና ንብረታዊ ውጤቶች አብሮ ይኖራለሁ ተብሎ ይገመታል፤ እንዲሁም ጋብቻ ሲፈርስ እነኚህ ውጤቶች አብረው እንደሚቆሙ ይታወቃል፡፡ ስለዚህ በህጉ የሚታመነው ጋብቻ ከነውጤቶቹ የሚቋረጠው በሕግ አግባብ በሚድረግ ፍቺ ነው፡፡

የሳይፋቱ ፍቺ ፅንሰ ሀሳብ የሚያትተው የጋብቻ ምስክር ወረቀት መኖር  በራሱ ብቻ ጋብቻ መኖሩን አይመለከትም ነገር ግን ለጋብቻ መኖር ግላዊ ውጤት በጣም አስፈለጊ ነው፡፡ ስለዚህ  ጋብቻ በሕግ አግባብ ሳይፈርስ ቢቀርም እንኳን ግላዊ ውጤቱን ካጣ በተግባር ፈርሷል ማለት ይቻላል፡፡ በተጨማሪም የጋብቻ ግላዊ ውጤት ለንብረታዊ ውጤት መኖር መሰረታዊ ነው፡፡ ስለዚህ የጋብቻ ግለዊ ውጤት መቋረጥ ከጋብቻ በፍ/ቤት በፍቺ ከመቋረጥ ያልተናነሰ ውጤት አለው በማለት ያትታል፡፡ ይህንንም ምክንያት በመቀበል የ.ፌ.ጠ.ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ አስተላልፎበታል፡፡ ከዚህ በመቀጠልም በሰበር ሰሚ ችሎት የተላለፈውን ውሳኔ እና አንድምታዎቹን እንዳስሳለን፡፡

4.3 የፌ.ጠ.ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት መ/ቁ. 20938

የዚህ ክርክር ጭብጥ ሀሳብ አመልካች (ሁለተኛ ሚስት) እና መልስ ሰጪ (የመጀመሪያ ሚስት) አንድ ሰውን በተለያየ ጊዜ አግብተው የነበረ ሲሆን ባለቤታቸው በሞተ ጊዜ የወራሽነት መብት ላይ እኔ ነኝ ሚስት በሚል ባለመስማማታቸው ነው፡፡ የመጀመሪያ ሚስት ከሟች ጋር በ1966 ጀምሮ በትዳር ሲኖሩ ቆይተው 1985 ዓ.ም ህጋዊ ፍቺ ሳይፈፅሙ ተለይተው የነበረ ሲሆን፤ ሁለተኛ ሚስት ደግሞ 1987 ላይ ሟችን አግብተው እየኖሩ ሟች ከዚህ ዓለም በሞት አስከተለዩበት ጊዜ 1989 ዓ.ም ድረስ አንድ ላይ ቆይተው እንደነበር አስረድተዋል፡፡

በዚህም ሁኔታ በማድረግ የፌ.መ.ደ.ፍ/ቤት የመጀመሪያ ሚስት ከሟች ጋር ህጋዊ ፍቺ ስላልፈፀሙ ሟች አስከሞቱበት ድረስ ህጋዊ ሚስት እንደሆኑ አትቷል፡፡ ሁለተኛዋ ሚስት ይግባኝ ቢሉም የፈ.ከ.ፍ/ቤት የስር ፍ/ቤት ውሳኔ አጽንቷል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎቱ ከሁለቱ ሚስት ነን ባዮች መካከል ውርሱ የሚገባትን ለመለየት ጋብቻ መኖሩን ፣ የጋብቻ ውጤቶች መኖራቸውንና ከሟች ጋር  የነበራቸውን ግንኙነት ከግምት አስገብቷል፡፡ በዚህም መሠረት የአሁኗ መልስ ሰጪ በ1966 የተጋቡትን የጋብቻ ውል ስታቀርብ አመልካች ደግሞ 1987 ከሟች ጋር ጋብቻ መፈፀሟን የሚያሳይ የጋብቻ ምስክር ወረቀት አቅርባለች በዚህም ምክንያት ሰበር ሰሚ ችሎት የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ እንደሚያትተው ጋብቻ ግላዊና ንብረታዊ ውጤቶች አሉት በሚለው መሠረት ሟች ከመልስ ሰጪ ጋር 1985 ዓ.ም ተጣልተው መልስ ሰጪ ወደ አ/አ ሟች ደግሞ አመልካችን አግብተው  ወደ አጋሮ መሄዳቸውን ተመልክቶ በማስረጃም ተረጋግጧል፡፡ ስለዚህም ችሎቱ ከዚህ መዝገብ የተረዳውን እንደሚከተለው አስቀምጧል፡-

"የአሁኗ መልስ ሰጪ ምንም እንኳን ከሟች ጋር ቀደም ብሎ የተፈፀመ ጋብቻ የነበራቸው ቢሆንም በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት በነበረው ጋብቻ መቀጠል  አለማቻላቸውን እና ሁለቱ በየፊናቸው የየራሳቸውን ህይወት መጀመራቸው ነው"፡፡

በተጨማሪም ሰበር ሰሚ ችሎቱ እንዳተተው ምንም እንኳን የመልስ ሰጪ እና የሟች ጋብቻ በፍቺ ባይፈርስም ጋብቸው የሚስከትለው ግላዊ እና ንብረታዊ ውጤቶች ግን ተቋርጧል፤ ይህንንም ሁለቱም ተለያይተው የየራሳቸውን ህይወት መጀመራቸው ያሳያል፡፡ ስለዚህም ምንም እንኳን ጋብቻ በፍ/ቤት በማድረግ ፍቺ ባይቋረጥም የጋብውቻው ግላዊ ውጤት መቋረጥ በግልጽ ስለሚታይ ጋብቻው በፍቺ  ተቋርጧል ሲል ውሳኔ አስተላልፏል፡፡

5. መደምደሚያ

ቤተሰብ የአንድ ህብረተሰብ መሰረታዊ አካል ነው፡፡ ጋብቻም ቤተሰብ የሚመሠረትበት መንገድ ሲሆን በውስጡም ግላዊ እና ንብረታዊ ውጤቶች አሉት፡፡ጋብቻ የሚቋረጥባቸው መንገዶች መካከል ፍቺ እንዱ አና ዋነኛው መሆኑን የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ያትታል፡፡ ከፍቺ እና ህጉ ከሚያስቀምጠቸው ሌሎች ምክንያቶች በቀር ጋብቻ አይፈርስም፡፡

የፌ.ፍ/ቤቶች ማሻሻያ  አዋጅ ቁ.454/2005 እንደሚያትተው በፌ.ጠ.ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሚተላለፉ ውሳኔዎች አስፈላጊውን ቴክኒካዊ እና ኣካሄዳዊ ስነ-ስርዓቶች እና ግዴታዎች ካሟላ እንደ ሕግ ይቆጠራል፡፡ በዚህም መሠረት ሰበር ሰሚ ችሎቱ በመ/ቁ.20938 በቀን 11/08/99 ዓ.ም ባሳተላለፈው ውሳኔ ምንም እንኳን ጋብቻ በፍ/ቤት በሚደረግ ፍቺ ባይቋረጥም ግላዊ ውጤትን ካጣ እንተቋረጠ ይቆጠራል ሲል አትቷል፡፡

ስለዚህ ምንም እንኳን በሀገራችን የቤተሰብ ሕግ ስለ ሳይፋቱ ፍቺ የሚለው ፅንሰ-ሀሳብ ባይኖርም በፌ.ጠ.ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ መሠረት የአንድ ጋብቻ ግላዊ ውጤት ከተቋረጠ ጋብቻው እንደተቋረጠ ይወሰዳል፤ ይህም ማለት ሳይፋቱ ፍቺ በኢትዮጵያ የቤተሰብ ሕግ ስር እንደ አንደ የፍቺ አይነት ይቆጠራል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የፌዴሬሽኑ አባል ክልሎች የፌዴራሉን መንግሥት ሕጎች አልፈፅምም ማለት ይችሉ ይሆ...
Rocks of Hope: Interrogating PM DR Abiy Ahmed’s Re...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024