Font size: +
6 minutes reading time (1280 words)

የውል ሕግ ይርጋዎች ከተመረጡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔዎች ጋር ተገናዝቦ የቀረበ

በዚህ ጽሁፍ በፍትሐብሔር ሕጉ ስለ ውል በተደነገገው ክፍል ስር የተጠቀሱ አጠቃላይ የይርጋ ድንጋጌዎችንና በልዩ የውል ሕግ ክፍል በተለይም የስጦታ ውል፣ የአደራ ውል፣ የሽያጭ ውል ውልን መሰረት በማድረግ የተደነገጉ የይርጋ ድንጋጌዎችንና የመያዣ ውል ቀሪ ስለሚሆንበት የሕግ አግባብ ከፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት አስገዳጅ ከሆኑ የሰበር ውሳኔዎች አግባብ ዳሰሳ ለማድረግ ተሞክሯል፡፡

የይርጋ ጽንሰ ሀሳብ 

ይርጋ ማለት አንድ ሰው በሕግ ሊጠይቅ የሚያስችለውን መብትና ጥቅሙን በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመጠየቁ መብት እያለው መብቱን የሚያጣበትና በህጉ የተቀመጠው ጊዜ እስኪሞላ ድረስ ምንም መብት ያልነበረው ሰው ደግሞ በግዜ ቆይታ መብት የሚያገኝበት የሕግ ስርዓት ነው፡፡ ስለዚህ ይርጋን በጥቅሉ መብት ፈጣሪ እና መብት ገዳይ በሚል በሁለት ማዕቀፍ ከፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ በፍትሐብሔር ህጋችን ስለ ውል በተጠቀሱ አጠቃላይና ልዩ ክፍሎች ላይ ልዩ ልዩ የይርጋ ድንጋጌዎች ተመላክተው ይገኛሉ፡፡ ከዚህ በታች ከጠቅላላ የውል ህግ ይርጋዎች ጀምሮ በልዩ ክፍሉ የተመላከቱትን ለመዳሰስ ተሞክሯል፡፡

የጠቅላላ ውል ይርጋ

የጠቅላላ ውልን መሰረት በማድረግ የሚቀርበው ክርክር ውል ይፍረስልኝ (invalidation of contract) እና የውል ይፈጸምልኝ (performance of contract) የተመላከቱ ናቸው፡፡ የውል ይፍረስልኝ ጥያቄ የሚቀርበውም የተዋዋዮች ፈቃድ ጉድለትንና የችሎታ ማጣትን (lack of consent and capacity) በተመለከተና የውሉ ህጋዊነት፣ውሉ ኢ-ሞራላዊና የውሉን ፎርም በሚመለከት ነው፡፡

የችሎታ ማጣትን መሰረት በማድረግ የሚቀርቡ ክርክሮች በተመከተ ይርጋው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810(1) በተጠቀሰው አኳሀን ሁለት ዓመት ነው፡፡ ይህም ጊዜ መቆጠር የሚጀምረው ውሉ የማይረጋበት ምክንያት ከቀረ ጊዜ ጀምሮ ነው፡፡ 

የውል ይፍረስልኝ ምክንያቶች የውሉ ህጋዊነት፣ውሉ ኢ-ሞራላዊ እና የውሉ ፎርምን የሚመለከት ከሆነ ደግሞ ይርጋው 10 ዓመት ይሆናል፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 48012 በቅጽ 12 ላይ በሰጠው የሕግ ትርጓሜ “ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1808(1)  ከፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810(2) ጋር በጋራ በማገናዘብ ስንመለከተው በቁጥር 1810(2) የተመለከተው የሁለት ዓመት የጊዜ ገደብ የሚያገለግለው ውሉ በፈቃድ ጉድለት ወይም በችሎታ ማጣት ምክንያት እንዲፈርስ የሚቀርብ ጥቄን በሚመለከት ብቻ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል ሲል በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1808(2) ስር የተዘረዘሩትን ምክንያቶች መነሻ በማድረግ ውል እንዲፈርስ የሚቀርብ የዳኝነት ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 መሰረት በሁለት ዓመት ይርጋ ጊዜ ውስጥ እንዲቀርበ ህጉ አያስገድድም ” በማለት ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ የውለታን ጉዳይ ህጋዊነት አስመልክቶ የሚቀርቡ ክሶች የይርጋ ጊዜ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1810 ስር የሚሸፈን ሳይሆን እንደማንኛውም የውል ጉዳዮች በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1845 በተደነገገው 10 ዓመት ይርጋ የሚታይ ይሆናል፡፡ ተዋዋይ ወገኖች በህግ ፊት የሚጸና ውል ተዋውለው ከሆነ በውሉ መፈጸም ተጠቃሚ የሆነው ወገን ውሉ ይፈጸምለት ዘንድ ጥያቄውን ለፍርድ ቤት ማቅረብ ይችላል፡፡ ይህን ጥያቄ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ነው ማቅረብ የሚቻለው የሚለውን በተመለከተ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 36756 በቅጽ 8 ላይ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በትርጓሜውም የውል ይፈጽምልኝ ይርጋው 10 ዓመት ሲሆን ይህም ይርጋ መቆጠር የሚጀምረው ውሉ ከተደረገ ቀን ጀምሮ ሳይሆን ውሉ መፈጸም ከሚቻልበት ቀን ጀምሮ ነው፡፡ የጠቅላላ ውል ይርጋን በዚህ መልኩ ከተመለከትን በልዩ የውል ህግ ክፍሎች የጠቀሱትን ይርጋዎች ከዚህ በታችን ለመቃኘት እንሞክራለን፡፡

  • የስጦታ ውል ይፍረስልኝ ይርጋ

ስጦታ ማለት በልዩ ውል የሚታይ የውል ስምምነት ሲሆን ይህም ስምምነት አንዱ ተዋዋይ ወገን ስጦታ ሰጪ ሌላኛው ተዋዋይ ደግሞ ስጦታ ተቀባይ ሆኖ ስጦታ ሰጪው ለተቀባዩ ችሮታ በማድረግ ሀሳብ ከንብረቶቹ አንዱን የሚለቅበት ወይም ግዴታ የሚገባበት ውል ነው፡፡ ይህም ስጦታ ውል እንደመሆኑ መጠን የሰጪው የአእምሮ ሁኔታ፣ ውሉ ህገወጥ በሆነ ሁኔታ የተደረገ ከሆነ፣ውሉም በመንፈስ መጫን ተከናውኖ የሆነ እንደሆነ፣ስጦታ ተቀባዩ በስጦታው ላይ የተመላከተውን ግዴታ ያልፈጸመ እንደሆነ ስጦታው እንዲቀነስ ወይም እንዲፈርስ ለፍርድ ቤት ጥያቄ ሊቀርብ ይችላል፡፡ ጥያቄው በምን ያህል የጊዜ ገደብ ውስጥ ሊቀርብ ይገባል ለሚለው በፍ/በ/ሕ/ቁ 2441(1) ላይ እንደተገለጸው “ስጦታ እንዲቀነስ ወይም እንዲሻር የሚቀርበው ጥያቄ ስጦታ ከተደረገበት ቀን አንስቶ እስከ ሁለት ዓመት ለዳኞች ካልቀረበ በቀር ዋጋ የለውም” በሚል ተጠቅሷል፡፡ በሁለት ዓመት የይርጋ ጊዜ የሚታገደው ለስጦታው መፍረስ ምክንያት የሆነው የስጦታው ውል የተደረገው በመንፈስ መጫን ነው በሚል ምክንያት ከሆነ ነው፡፡ በተከራካሪ ወገኖች የሚቀርበው መከራከሪያ የስጦታ ውሉ ለሞራልና ለህግ ተቃራኒ ስለሆነ ይፍረስልኝ የሚል ከሆነ የይርጋ ጊዜው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2441(1) የተጠቀሰው የሁለት ዓመት የይርጋ ጊዜ ሳይሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1845 የተመላተው የአስር ዓመት ይርጋ ነው ( ይህም በፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 105652 በቅጽ 18 በተሰጠው ውሳኔ ላይ ተመላክቷል)፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2464(1) ላይ እንደተጠቀሰው ስጦታው የተደረገው ገደብ ወይም ግዴታ ባለበት አግባብ ከሆነ ስጦታ ሰጪው ተቀባዩ ግዴታውን ባለመፈጸሙ ምክንያት ስጦታው እንዲፈርስ ለመጠየቅ ይችላል፡፡ ይህ የውል ይፍረስልኝ ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2441(1) ላይ በተመለከተው በሁለት ዓመት ጊዜ የሚገዛ አለመሆኑን ጠቅሶ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 42346 በቅጽ 10 ላይ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

የስጦታ ይፈጸምልኝ ጥያቄ 

በፍትሐብሔር ህጉ ስለ ስጦታ ውል በተደነገገው ክፍል ስጦታ በምን የህል ጊዜ መፈጸም እንዳለበት የተጠቀሰ የጊዜ ገደብ የለም፡፡ ሆኖም ግን ስጦታ ውል እንደመሆኑ የሚፈጸምበት የጊዜ ገደብ በህግ በግልጽ ባይቀመጥም ገደብ ሊኖረው እንደሚገባ ግልጽ ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 42691 በቅጽ 10 ላይ በሰጠው የህግ ትርጓሜ “የስጦታ ውልን የሚገዙ ድንጋጌዎች ግልጽ የሆነ ገደብ ባያስቀምጡም የስጦታ ውል ይፈጸምልኝ ጥያቄ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1676(1) እና 1845 መሰረት በ10 ዓመት ይርጋ ቀሪ ይሆናል” ሲል ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

  • የመያዣ ውል ቀሪ የሚሆንበት

የማይንቀሳቀስ ንብረት መያዣ በቀጥታ በህግ ወይም በፍርድ ወይም በውል አልያም ደግሞ በኑዛዜ ሊቋቋም ይችላል፡፡ የመያዣ ውል ቀሪ የሚሆንበት ጊዜ በተመለከተ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3058(1) ላይ የተጠቀሰ ሲሆን በዚህ ድንጋጌ መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መብት ውጤት የሚኖረው ከተጻፈበት ቀን አንስቶ እስከ አስር ዓመት ድረስ ነው፡፡ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 78444 በቅጽ 14 ላይ በሰጠው ትርጓሜ ንብረት በመያዣ የያዘ አካል የማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ያለው የመያዣ መብት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3058(1) የተደነገገው 10 ዓመት በማለፉ ምክንያት ውድቅ ሆኖበታል የሚባለው ይህ ጊዜ ከማለፉ በፊት በመያዣ መብት መገልገል ያልጀመረ እንደሆነ ነው፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 3058(1) ላይ የተጠቀሰው ድንጋጌ(የማይንቀሳቀስ ንብረት የመያዣ መብት ውጤት የሚኖረው ከተጻፈበት ቀን አንስቶ እስከ 10 ዓመት ነው) የሚለው የይርጋ ድንጋጌ አይደለም፡፡ ይህን በመጥቀስ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 44800 በቅጽ 10 ላይ በሰጠው ትርጓሜ ድንጋጌው ይርጋን የሚመለከት ሳይሆን የመያዣ ውል ቀሪ የሚሆንበት ነው ሲል ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

  • ሽያጭ ውል ይርጋ

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2892 በተጠቀሰው መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረት የገዛ ሰው ውሉ እንደ ቃሉ ዓይነት እንዲፈጸምለት ለማድረግ የተለየ ጥቅም እንዳለው ሆኖ ይገመታል፡፡ ስለዚህ ውሉ እንደ ቃሉ ዓይነት እንዲፈጸምለት ለማስገደድ ይችላል፡፡ ስለሆነም ሻጩ ውሉን አንደ ውሉ ቃል ከመፈጸም መዘግየቱ ከተረዳበት ጊዜ አንስቶ እስከ አንድ ዓመት ድረስ ውሉ እንዲፈጸምለት ካልጠየቀ በቀር ገዥው ውሉን በግዴታ አንዲፈጽም የማድረግ መብቱን ያጣል፡፡ በዚህ ድንጋጌ የእንግሊዘኛው ትርጓሜ the buyer shall lose the right to demand the specific performance of the contract where he fails to demand it within one year after he has ascertain the delay of the seller በማለት ይደነግጋል፡፡ በአማርኛው መዘግየቱን ከተረዳበት በሚለው ቃል እና በእንግሊዘኛው ascertained በሚለው መካከል ልዩነት ያለ ሲሆን የድንጋጌው መንፈስ ገዥው በአንድ አመት ውስጥ አንዲፈጸምለት ለፍርድ ቤት ክስ ማቅረብ ያለበት ሻጭ በሽያጭ ውሉ መሰረት ለመፈጸም ፈቃደኛ አለመሆኑን ካረጋገጠበት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ የእንግሊዘኛውን የቃል አጠቃቀም በማየት ለመረዳት ይቻላል፡፡ ይህን ጉዳት በተመለተ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰ/መ/ቁ 38935 በቅጽ 8 ላይ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ትርጓሜውም በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1731(1) እና 1732 መሰረት ተዋዋይ ወገኖች የውል ቃል መሰረት በማድረግ ውሉን የመፈጸም ፍላጎትና ቅን ልቦና ያላቸው መሆኑ የውል ሕግ ግምት የሚወስድበት ጉዳይ በመሆኑ ገዥ በሽያጭ ውሉ በገባው የውል ቃል መሰረት አንዲፈጸም የተለያዩ የተስፋ ቃሎችን ሲሰጠው የቆየ መሆኑ የማስረዳት ግዴታ የለበትም፡፡ በተቃራኒው የፍ/ብ/ህ/ቁ 2892(3)  ን ጠቅሶ የሚከራከር ሻጭ ከገዥ ጋር ባደረገው የሽያጭ ውል መሰረት ለመፈጸም ፍላጎት የሌለው መሆኑ ገዥ በማያሻማ ሁኔታ እንዲያውቅና አንዲረዳው ያደረገ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ አለበት፡፡ በአጠቃላይ ሻጭ በገባው የሽያጭ ውል ቃል መሰረት ለመፈጸም ፍላጎት የሌለው መሆኑን በማሻማ ሁኔታ ለገዥ ካሳወቀውና ገዥም ይህንኑ ከተረዳው እና ካረጋገጠ ከአንድ ዓመት በኋላ የውል ይፈጸምልኝ ክስ ገዥ ያቀረበ መሆኑን የማስረዳት ግዴታ የለበትም፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2892(3) ላይ ያለው ይርጋ ተፈጻሚነት የሚኖረው ገዥ ለሻጭ በውሉ መሰረት የመፈጸም ፋላጎት የሌለው መሆኑን በማያሻማ ሀኔታ ገዥ እንዲያውቀው ያደረገበት ቀን መነሻ በማድረግ መሆን ይገባዋል፡፡ አንዲሁም የፍ/ብ/ህ/ቁ 2875፣2892(3) እና 2331 ተጣምረው ሲታዩ ውሉ የሚፈጸምበት ቀን በጥብቅ ወይም በቁርጥ የተወሰነ መሆኑ በተገለጸ ጊዜ ነው፡፡ በመሆኑም ሻጭ በውሉ መሰረት የመፈጸም ፍላጎት የሌለው መሆኑን ለገዥ በማያሻማ ሁኔታ ያሳወቀ መሆኑን ባላስረዳበት ሁኔታ ወይም የሽያጭ ውሉ የሚፈጸምበትን ጥብቅ የጊዜ ገደብ ባልገለጸበት ሁኔታ ተፈጻሚነት ያለው የይርጋ ጊዜ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2892(3) የተገለጸው ሳይሆን በ1845 የተገለጸው ነው በማለት ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡

  • የአደራ ውል ይርጋ

አደራ ማለት በአደራ ሰጪና በአደራ ተቀባይ መሀከል አንድን እቃ ወይም ዋጋ ያለውን ንብረት ተቀብሎ በአደራ እንዲያስቀምጥለት በግራ ቀኙ መሀከል የሚገባ የውል ግዴታ ነው፡፡ ይህንንም ንብረት በአደራ ውል ሲረካከቡ አደራ ተቀረባዩ ንብረቱን ለመመለስ በውሉ የተወሰነ ጊዜ ሊቀመጥለትም ሆነ ምንም አይነት የተወሰነ ጊዜ በውሉ ላይቀመጠ ይችላል፡፡ በእነዚህ ሁለት ሁኔታዎች አደራ አስቀማጩ ንብረቱን ለመረከብ ቢፈልግ በይርጋ ሊታገድ የሚችልበትን የህግ አጋግባብ አስመልክቶ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 48048 በቅጽ 10 ላይ የህግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በትርጓሜውም “አደራ ተቀባዩ በአዳራ የሚጠብቀውን እቃ የሚመልስበት የጊዜ ገደብ በውል ተመልክቶ ከሆነ ይህ ጊዜ ሲያበቃ እቃውን መመለስ ያለበት መሆኑ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2781(1) የተመለከተ ሲሆን በውል ላይ የተቀመጠው የጊዜ ገደብ ከሌለ ግን አደራ ሰጪው እንደጠየቀ ወዲያውኑ እቃው እንደሚመለስ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 2989(1) ስር ተመላክቷል” በማለት ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ከእነዚህ ድንጋጌዎች ከሰበር ሰሚ ውሳኔ አኳያ ስንመለከታቸው አደራ ተቀባይ እቃውን የሚመልስበት የጊዜ ገደብ ከሌለ በቀር አደራ ሰጪው በአደራ እንዲቀመጥ የሰጠው እቃ ያለምንም የጊዜ ገደብ በማንኛውም ጊዜ እንዲመለስለት መጠየቅ የሚችል መሆኑን እንረዳለን፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የመንግሥትና የግል አጋርነት አዋጅና መመሪያ ይዘት አጭር ማብራሪያ
መመሪያ የማውጣት ሥልጣን እና ሌሎች ጉዳዮች ከአስፈጻሚ አካላት ሥልጣንና ተግባር...

Related Posts

 

Comments 2

Abebe
Guest - Hijezu Hamdino (website) on Wednesday, 23 August 2023 14:34

I am intersted to gain knoweledge about law

I am intersted to gain knoweledge about law
Abebe
Guest - Ayansa Seyoum on Wednesday, 11 October 2023 11:21

Thank you very much!!I appreciate it,they way you express it.

Thank you very much!!I appreciate it,they way you express it.
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 07 November 2024