ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia)

1.  ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia) ፅንሰ ሃሳብ

ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት (Trial in absentia) ማለት ተከሳሹ በወንጀል ክሱ በፍርድ ቤት ጉዳዩ በመታየት ላይ የሚገኝ ቢሆንም ተከሳሹ ግን በአካል በፍርድ ቤት ሳይገኝ ጉዳዩ በሌለበት በመታየት ላይ የሚገኝ ማለት ነው፡፡ ይህ አይነቱ የህግ ስረዓት በተለያዩ ሃገሮች የሚተገበር ሲሆን በእኛም ሃገር በወንጀል ሥነሥርዓት ህጉ እና በመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ላይ በልዩ ሁኔታ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት ተገቢነቱ መታየት ያለበት ከወንጀል ህጉ አላማ፤ ከፍትህ እና ከሰብዓዊ መብት አንፃር ነው፡፡

2.  ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት ያለው ጠቀሜታ እና ጉዳት

የወንጀል ክስ በሚሰማበት ወቅት የተከሳሽ በፍ/ቤት መገኘት ብዙ አይነት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ በፍ/ቤት በመገኘትም ተከሳሽ ሙሉ መብቶቹ እንዲከበሩ እና ማንኛውም አይነት የተከሳሽ መብቶች እንዳይታለፍ ማድረግ ይችላል፡፡ በዚህም ሳያበቃ በወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ ላይ እውነታውን ከማውጣጣት አንፃር ፋይዳ አለው፡፡ ተከሳሽ በሌለበት የሚታይ ጉዳይ የአንድ ወገንን ማስረጃ ብቻ የሚመዘንበት በመሆኑ ጥፋተኛ የመባል እድልን የሚያሰፋ በመሆኑ ያለጥፋት የሚቀጡ ሰዎችን ሊያበዛ ይችላል፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት ተከሳሽን በመጠበቅ ሊጠፋ የሚችለውን ጊዜ በመቀነስ አፋጣኝ የፍትህ ስርዓት እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ተከሳሽን በመጠበቅ ሊጠፋ ይችል የነበረውን የማስረጃ መሳሳት ይቀንሳል፡፡

3.  ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia) እና የሰብዓዊ መብት

አንድ ሰው የወንጀል ክስ በሚቀርብበት ወቅት ክሱን በአካል ቀርቦ የመደመጥ ተፈጥሯዊ የሆነ ሰብዓዊ መብቱ ሲሆን ይህም መብቱ በህገምንግስት በቂ ከለላ ተሰጥቶታል፡፡ ሆኖም በተወሰኑ የወንጀል ጉዳዮች ላይ ተከሳሾች በሌሉበት ጉዳያቸው ሊታይ የሚችልበት ሁኔታ አለ፡፡ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት (Trial in absentia) የሚፈቀደው በተወሰኑ ጉዳዮች ብቻ ሲሆን ይህም የተደረገበት ምክንያት ሰው ፍ/ቤት ቀርቦ የቀረበበትን ጉዳይ አውቆ እና ተደምጦ ካልተወሰነ የተፈጥሯዊ ፍትሃዊነት መርህን (principle of natural justice) የሚጣረስ በመሆኑ ነው፡፡ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት በላቲን ቋንቋ Audi Alteram Paterm ወይም በእንግሊዘኛ ቋንቋ Hear the other party ማለትም ሌላኛውን ወገን ስማ! በመባል የሚታወቀውን የተፈጥሯዊ ፍትሃዊነት መርህን (principle of natural justice) የሚተላለፍ ነው የሚሆነው፡፡

የአለምአቀፍ ሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮነቬንሽን አንቀፅ 14(3)d ላይ ተከሳሾች ባሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ መደረጉ መብታቸው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የኢትዮጵያ ህገመንግስት  የታሰረ ሰው ከታሰረ በ48 ሰዓት ውስጥ ፍ/ቤት የመቅረብ መብትን እንጂ በግልፅ በፍርድ ቤት ክሱን ለመስማት የመምጣትን የተከሰሱ ሰዎች መብት ውስጥ አላካተተውም፡፡ ሆኖም ከቀረበ ቡኋላ ስለሚከናወነው ሂደት በሚያትትበት ወቅት በውስጥ ታዋቂነት የተከሳሽን መቅረብ የሚገምት ነው፡፡ የአለምአቀፍ ሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮንቬንሽን የሰብዓዊ መብት ኮሚቴ በአንቀፅ 14(3)a ላይ በሰጠው ማብራሪያ መሰረት በተቻለው መጠን ተከሳሽ ባይመጣም ተከሳሽ ሰለቀረበበት ክስ እና ስለ ችሎት ሂደቱ እንዲያውቅ መደረግ ያለበት ስለመሆኑ አትቷል፡፡ በዚሁ ሰነድ መሰረት ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት (Trial in absentia) ለትክክለኛው ፍትህ አሰጣጥ ሲባል በተወሰነ መልኩ የሚፈቀድ ሲሆን ይህም ሁኔታ ተከሳሽ ክስ የቀረበባቸው መሆኑን በተገቢው ሁኔታ ከተረዱት ቡኋላ በራሳቸው ጊዜ ሳይመጡ የቀሩ እንደሆነ ነው፡፡ ክሱን በፍርድ ቤት የመስማቱ ሂደት ከአለምአቀፍ ሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮነቬንሽን አንቀፅ 14(3)d ጋር የተጣጣመ ነው የሚባለው ተከሳሽ ክስ የቀረበበት መሆኑን እና በችሎት ቀርቦ እንዲከራከር በተገቢው መልኩ ጠሪ ተደርጎ ክሱም የትና መቼ እንደሚሰማ ጭምር ተነግሮት እንደሆነ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ህገ መንግስት መሰረት የሰብአዊ መብት ድንጋጌዎችም ከዚሁ አንፃር የሚተረጎሙ ሲሆን የዚሁ ሰነድ ፈራሚ ሃገር እንደመሆናችንም የኢትዮጵያ ህግ አካል ተደርጎ ይወሰዳል፡፡

ሰብዓዊ መብቶች ፍጹም የሆኑ ወይም ሊገደቡ የሚችሉ ሊሆኑ ይቸላሉ፡፡ ፍትሃዊ የክስ ሂደት መብቶች (Fair trial rights) በመባል ከሚታወቁተ መብቶች መሃከል በህገመንግስቱ አንቀፅ 20 ላይ ተመልክተው የሚገኙት የተከሳሽ የመሰማት መብት፤ ክሱን በአግባቡ ተረድቶ መልስ የመስጠት፤ የቀረበባቸውን ማስረጃ የመከላከል እና የመጋፈጥ መብቶች እንዲሁም በጠበቃ የመወከል መብትን ያካትታል፡፡ በመሆኑም ተከሳሽ በፍ/ቤት ቀርቦ ጉዳዩን መከታተሉ የፍትሃዊ የክስ ሂደት መብቶች (Fair trial rights) አካል ሲሆን እነዚህ የፍትሃዊ የክስ ሂደት መብቶች (Fair trial rights) ፍጹም የሆኑ እና ሊገደቡ ወይም ሊታለፉ የማይችሉ ናቸው፡፡ ይህንንም የአፍሪካ ሰብዓዊ እና የህዝብ መብቶች ቻርተር በአንቀጽ 7 እንዲሁም የአለምአቀፍ ሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮነቬንሽን አንቀፅ 14 ያረጋግጣል፡፡ መብቶቹ በተከሳሽ መቅረብ ላይ የሚመሰረቱ ለምሳሌ በሚረዱት ቋንቋ አስተርጓሚ የመግኘት ከመሳሰሉት ውጪ ያሉት መብቶች ምንም እንኳን ተከሳሽ በችሎት ባይገኝም የተከሰሱ ሰዎች መብቶች ግን ሊከበሩ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ለምሳሌ ተከሳሽ አለመቅረቡ ጥፋተኛ እንደሆነ ተደርጎ መታየት የለበትም፡፡

ከዚህም በተጨማሪም በህግ ባለሙያ ሊወከል ይገባል፡፡ በህገመንግስቱ አንቀፅ 20 ላይ ተመልክተው የሚገኙት የተከሳሽ መብቶች በመቅረብ ባለመቅረብ ላይ የተመሰረቱ አይደሉም፡፡ በጠበቃ መወከሉ የተሳሳተ ውናኔ ላይ እንዳንደርስ ይረዳናል፡፡ የአውሮፓው የሰብዊ መብት ፍ/ቤት (በPoitrimol v. France App no 14032/88 (ECHR, 23 November 1993) Par 32) ላይ በትክክል እንደተቸው ተከሳሽ በፍ/ቤት ባለመገኘቱ ብቻ በህግ ባለሙያ የመውከል መብቱን ሊያጣ አይገባውም፡፡ ለምሳሌ አንድ ተከሳሽ ከሁለት ክሶች በላይ የቀረበበት እንደሆነ እና የቀረበበት ሁለተኛ ክስም በማንኛውም መልኩ ውድቅ ሊያደርገው የሚቸለውን ፍሬ ሃሳብ ተከሳሽ በህግ ባለሙያ በመወከሉ ሊያነሳው የሚችለው ነገር እነደመሆኑ መጠን ለትክክለኛው ፍትህ አሰጣጥ ሊረዳ የሚችል ይሆናል፡፡ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 20(5) ላይ ተከሳሽ በመረጡት የህግ ጠበቃ የመወከል መበት ያለቸው መሆኑን ከገለፀ ቡኋላ ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትህ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግስት ጠበቃ የማግኘት መብት ያላቸው መሆኑን ያትታል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታም በፍ/ቤት ለቀረቡ ተከሳሾች ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትህ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም በተለይም ሊያስቀጣቸው የሚችለውን የእስራት መጠን ከግምት በማስገባት ከመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ይደረጋል፡፡ ህገመንግስቱ እራሱ ጠበቃ ባለመቆሙ ፍትህ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ መኖሩን ከግምት ያስገባ በመሆኑ እና በተለይም ሊያስቀጣቸው የሚችለውን የእስራት መጠን ከግምት በማስገባት ወይም የቀረበባቸው ክስ ብዛት ወይም ውስብስበነት ከግምት በማሰገባት ተከሳሽ በሌለበት የወንጀሉ ክስ እየተሰማ ቢሆንም ከመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ሊደረግ ይገባል፡፡ ተከሳሽ በሌለበት የወነጀል ክስ መስማት የአንድ ወገን ማስረጃ ብቻ ተሰምቶ የሚወሰን እንደመሆኑ መጠን ተከሳሽ ከቀረበበት የክስ ሂደት የበለጠ ፍትህ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ መኖሩ አያጠራጥርም፡፡ ጠበቃ ቢኖር ደግሞ በተወሰነ መልኩ ይህን ማቅናት የሚችል በመሆኑ እና በጠበቃ መወከላቸው ለፍትህ መስፈን የራሱ አስተዋፅኦ የሚኖረው እስከ ሆነ ድረስ ከመንግስት ጠበቃ እንዲቆምላቸው ሊደረግ ይገባል፡፡

4.  ተከሳሽ በክስ ሂደቱ ላይ መገኘት መብቱ ነው ወይስ ግዴታ?

የተከሳሽ በክስ ሂደት ላይ መገኘት በተለያዩ የሰብዓዊ መብት ሰነዶች እንዲሁም ህገ መንግስታችን ያመለክታሉ፡፡ በዋናነትም የአለምአቀፍ ሲቪል እና ፖለቲካ መብቶች ኮነቬንሽን አንቀፅ 14(3)d ላይ ተከሳሾች ባሉበት ጉዳያቸው እንዲታይ መደረጉ መብታቸው መሆኑን ይደነግጋል፡፡ የኢፌ.ድ.ሪ. ህገ ምንግስትም ተከሳሽ የቀረበበትን ማስረጃ የመጋፈጥ መብት ያለው ስለመሆኑ ይደነግጋል፡፡ ይህም ሊሆን የሚችለው ተከሳሽ በፍ/ቤት ሲገኝ መሆኑ ይታወቃል፡፡ እነዚህን የሰብዓዊ መብት ሰነዶች መነሻ በማድረግ ተከሳሽ በክስ ሂደቱ ላይ መገኘት መብቱ መሆኑን መደምደም ይቻላል፡፡

ታዲያ ይህን ተከትሎ ሊጠየቅ የሚገባው ጥያቄ መብት ከሆነ ተከሳሽ መብቱን መተው አይችልም ወይ? የሚለው ነው:: ጥያቄውንም ተከሳሽ በክስ ሂደት ላይ መገኘቱ ግዴታው ነው ወይ? የሚለውን ሳይመለስ ድምዳሜ ላይ መድረስ ተገቢ ባለመሆኑ ቅድሚያ ግዴታው ስለመሆኑ እንመዝናለን፡፡ ተከሳሽ ለተጠረጠረበት ወንጀል በፈ/ቤት ተገኝቶ ምላሽ መስጠቱ እንደግለሰብ ለሚኖርበት ማህበረሰብ ምላሽ መስጠቱ በመሆኑ እና ያገራችንም የወንጀል ሥነሥርዓት ህግ ተከሳሽ ሳይቀርብ የቀረ እንደሆነ ታስሮ የሚቀርብ መሆኑን መደንገጉም ግዴታው መሆኑን ለማመልከት የወጣ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ግዴታው ከሆነ ደግሞ እዚሁ እየኖረ አልቀርብም ማለት የሚችልበት አግባብ የለም፡፡

5.  ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia) የሌሎች ሃገር ልምድ

ኮመን ለው (Common Law) የህግ ስርዓት በሚከተሉ ሃገሮች ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ መስማት (Trial in absentia) በተወሰኑ ልዩ ሁኔታዎች ብቻ የሚፈቀድ ሲሆን በሲቪል ለው (civil law) የህግ ስርዓት በሚከተሉ ሃገሮች ደግሞ በመርህ ደረጃ የሚፈቀድ ሲሆን የተወሰኑ ሃገሮች ደግሞ ክልከላ አውጥቷል፡፡

6.  ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia) በኢተዮጵያ ህግ መሰረት

ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia) በወንጀል ሥነሥርዓት ህጉ እና በመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 ላይ ተደንግጓል፡፡ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ህጉ መሰረት ተከሳሽ ያለ በቂ ምክንያት ነገሩ ሊሰማ በተቀጠረበት ቀን ሳይቀርብ የቀረ እንደ ሆነ አለመቅረቡን ፍ/ቤቱ በመዝገቡ ከጻፈ በኋላ በሌሉበት እንዲሰማ ያዛል ይላል፡፡ ክስ ሊሰማ የሚችለው በመርህ ደረረጃ ተከሳሽ ባለበት ሲሆን በልዩ ሁኔታ ግን ተከሳሽ በሌለበት ከአስራ ሁለት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት የሚያሳስር ወንጀል የሰራ ወይም በቀድሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከቁጠር 354 እሰክ 365 ድረስ ያሉትን ወንጀሎች ፈፅሞ ፅኑ እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በላይ መቀጮ በሚያስቀጣ ወንጅል የተከሰሰ ሲሆን ነው፡፡  

ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት (Trial in absentia) በሶስት አካፍሎ ማየት የሚቻል ሲሆን የመጀመርያው ተከሳሽ ቀድሞውንም ቢሆን ከፖሊስ ምረመራ ወቅት ጀምሮ ያልተገኘበት ሲሆን ወይም በፖሊስ ምረመራ ወቅት ቢኖርም ፍ/ቤት ሊሰማ በተቀጠረበት የመጀመርያ ቀን አንስቶ ያልቀረበ እንደሆነ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ተከሳሽ በክሱ መጀመርያ ቀን የቀረበ ቢሆንም በክሱ ሂደት ላይ ተከላከል ሲባል ወይም ለፍርድ በተቀጠረ ቀን ሳይቀርብ ቢቀርና ቢጠፋ የተለያዩ ዉጤት ይኖሩታል፡፡

የመጀመርያውን ሁኔታ በተመለከት በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 42/1/ለ እና 161 መሰረት የተከሰሰውን ሰው በምርመራ ወቅት ማግኘት ያልተቻለ እንደሆን እና በሌሉበት ክሱ የማይሰማ ከሆን ክስ አይቀርብም፡፡ ሆኖም ተከሳሽ በሌለበት ክሱን መስማት የሚቻል ከሆነ ክሱ ተመስርቶ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ 161 መሰረት ታይቶ ጉዳዩ እልባት የሚያገኝ ይሆናል፡፡ ይህም ፍ/ቤቱ ክሱን ሊሰማ በቀጠረበት የመጀመርያ ቀን አንስቶ ያልቀረበ እንደሆነ ተፈፃሚ የሚሆን ስርዓት ነው፡፡

ሌላው ደግሞ ተከላከል ሲባል ወይም ለፍርድ በተቀጠረ ቀን ሳይቀርብ ቢቀርና ቢጠፋ ነው፡፡ ይህም በአሰራር ረገድ ከቀድሞ እንዲለይ ተደርጓል፡፡ ለፍርድ በተቀጠረ ቀን ሳይቀርብ ቢቀርና ቢጠፋ ተገቢው ጥረት ተደርጎ ካልተገኘ በሌለበት ይወሰናል፡፡ ተከሳሽ ተከላከል ከተባለ ቡኋላ የቀረ እንደሆነ ዐቃቤ ህግ ተከሳሽ እራሱን እነዲከላክል እድል ተሰጥቶት ለመከላከል ፍቃደኛ ባለመሆኑ ጉዳዩ በሌለበት የጥፋተኝነት ውሳኔ እንዲሰጥ በማንኛውም አይነት ክስ ላይ ይጠይቃል፡፡ በዚህም መሰረት ፍ/ቤቱ የጥፋተኝነት ውሳኔ በመስጠት ቅጣት እንዲተላለፍ ይደረጋል፡፡ ይህም የአሰራር ልምድ የመነጨው  የሰበር ችሎት አንድ ሰው የመከላከያ ማስረጃውን አቅርቦ የጠፋ እንደሆነ በሌለበት ሊወሰንበት የሚችል መሆኑን አስመልክቶ የሰጠው ውሳኔ ተከትሎ ነበር፡፡

መሰረት ተከሳሽ የመከላከያ ማስረጃውን አሰምቶ የጠፋ እንደሆነ ጉዳዩ በሌለበት ውሳኔ ሊሰጥ ይችላል የሚለውን አስፍቶ በመተርጎም ተከላከል ተብሎ ቢጠፋ የጥፋተኝነት ውሳኔ ሊሰጥ እነደሚቻል ተደርጎ እየተሰራበት ነው ያለው፡፡ ሆኖም ይህ ምክንያታዊ ቢሆንም ህጋዊ ግን አይደልም፡፡ ለዚህም የማቀርበው ምክንያት በህጉ ላይ እንደተመለከተው ተከሳሽ ያለ በቂ ምክንያት ነገሩ ሊሰማ በተቀጠረበት ቀን ሳይቀርብ የቀረ እንደ ሆነ አለመቅረቡን ፍ/ቤቱ በመዝገቡ ከጻፈ በኋላ በሌሉበት እንዲሰማ ያዛል ይላል፡፡ ይህም በማንኛውም የክስ ደረጃ መሆኑን የሚያመለክት እንጂ ተከሳሽ በሌለበት ክስ ስለመስማት የተደነገጉት መርሆች ተከሳሽ ከመጀመሪያውን ባለመምጣቱ የሚፈፀም ህግ አይደለም፡፡ ህጉም በየትኛውም ደረጃ ሊፈፀም የሚችል ስለመሆኑ ልዩነት አይፈጥርም፡፡ ሊሆን የሚገባው ተከሳሽ በማንኛውም ደረጃ ሳይቀርብ ቢቀር ሊታይ የሚገባው በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 160 እና ተከታዮቹ ድንጋጌዎች መሰረት በሌለበት ለማየት ከአስራ ሁለት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት የሚያሳስር ወንጀል የሰራ ወይም በቀድሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከቁጠር 354 እሰክ 365 ድረስ ያሉትን ወንጀሎች ፈፅሞ ፅኑ እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በላይ መቀጮ በሚያስቀጣ ወንጀል የተከሰሰ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ህጉም ጉዳዩ በሚታይበት ቀን ይላል እንጂ ክስ በሚሰማበት ቀን አይልም፡፡ ጉዳዩ ደግሞ ክስ መስማት፤ ብይን ወይም መከላከያ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም መጀመርያ ቀን መቅረቱን የሚመለከት ብቻ ሳይሆን ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩን በማንኛውም ደረጃ ቢሆን ለማየት ተፈፃሚ ሊሆን የሚገባ ህግ ከ160 ጀምሮ የተመለከቱት ናቸው፡፡ በዛ ስር የማይወድቁ ከሆነ ተከሳሽ በተገኘበት ወቅት የሚንቀሳቀስ ሆኖ ሊቋረጡ የሚገባቸው ናቸው፡፡ በተለምዶ የሚሰራበት አግባብ ተገቢ አለመሆኑን ሊታይ ይገባል፡፡ ምንም እንኳን የተከሳሽ መብቶች ባለመኖሩ ምክንያት ሊጎሉ የሚችሉ ቢሆንም ለወንጀል ፍትህ አስተዳደሩ ከሚሰጠው ፋይዳ አንፃር ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩ ሊታይ የሚገባው ቢሆንም በተወሰኑ ህጉ ባስቀመጣቸው ልዩ ሁኔታዎች ላይ ብቻ መሆን አለበት፡፡

ከዚህ አንፃር ከአስራ ሁለት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት የሚያሳስር ወንጀል የሰራ ወይም በቀድሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከቁጠር 354 እሰክ 365 ድረስ ያሉትን ወንጀሎች ፈፅሞ ፅኑ እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በላይ መቀጮ በሚያስቀጣ ወንጅል የተከሰሰ ሲሆን ነው፡፡ የመጀመርያውን በተመለከተ ህጉ ከአስራ ሁለት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት የሚያሳስር ወንጀል የሰራ እንደሆነ ነው የሚለው፡፡ ለምሳሌ ከባድ ማታለል ከ5 እስክ 15 አመት ያሰቀጣል ይላል፡፡ ይህን የተወሰኑ ፍ/ቤቶች ተቀብለው ተከሳሽ በሌለበት ጉዳዩን አይተው ውሳኔ ይሰጣሉ፡፡ ሆኖም ይህ ወንጀል 5 አመትም 10 አመትም 15 አመትም ሊያስቀጣ የሚችል ነው፡፡ ህጉ ከአስራ ሁለት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት የሚያሳስር ወንጀል የሰራ የሚለው ስለመነሻ ቅጣት እንጂ ስለመድረሻ ቅጣት የሚገለፅ ባለመሆኑ እንዲህ አይነት ጉዳዮች በሌሉበት ሊታዩ የሚችሉ አይደለም፡፡ ጉዳዩ በይግባኝ ደረጃም ቢሆን በሌለበት ለማየት ተከሳሽ የተከሰሰበት ወንጀል በሌለበት ሊታይ የሚችል ነው ውይ የሚለው መታየት አለበት፡፡

ከዚህም ባለፈ ተከሳሽ በሌለበት የወንጀል ክስ ስለመስማት የተመለከተው ህግ በወ/መ/ሥ/ሥ/ህ/ቁ. 161 መሰረት አንደ ምሳሌ ወስደን ብንመለከት በአንቀፁ እንደተደነገገው አንድ ሰው በሌለበት የሚዳኘው ያለበቂ ምክንያት ጉዳዩ በሚሰማበት ቀን የቀረ እንደሆነ ነው፡፡ አንድ ሰው በውጭ ሃገር ታስሮ የሚገኝ ከሆነ የዛ አገር መንግስት ካልፈቀደለት በስተቀር ከእስር መውጣት አይችልም፡፡ በእስራቱ ምክንያት የቀረ መሆኑ እየታወቀ በሌለበት ጉዳዩ መታየቱ ከህጉ አንፃር ተገቢነት የሌለው ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ በመገናኛ ብዙሃን የመረጃ ነፃነት አዋጅ ቁጥር 590/2000 አንቀፅ 43(5) መሰረት ተከሳሽን በአድሻው ባለመገኘቱ የተነሳ መጥሪያ ለማድረስ ያልተቻለ እንደሆነ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹ በ7 ቀናት ካልቀረበ ጉዳዩ በሌለበት ታይቶ የሚወሰን መሆኑን የሚገልፅ መጥሪያ በጋዜጣ እንዲወጣ ትዕዛዝ ይሰጣል ይላል፡፡ ይህም አንቀፅ በማንኛውም በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት ሲፈፀም ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ስለሆነም በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት ሲፈፀም በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ህጉ መሰረት የተቀመጡት መስፈርቶች ከግምት ሳይገቡ ማለትም ተከሳሽ የተከሰሰበት ወንጀል ከአስራ ሁለት አመት በታች በማያንስ ፅኑ እስራት የሚያሳስር ወንጀል የሰራ ወይም በቀድሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ ከቁጠር 354 እሰክ 365 ድረስ ያሉትን ወንጀሎች ፈፅሞ ፅኑ እስራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በላይ መቀጮ በሚያስቀጣ ወንጅል የተከሰሰ ቢሆንም ባይሆንም በመገናኛ ብዙሃን አማካኝነት የወንጀል ድርጊት የተፈፀመ በመሆኑ ብቻ በሌለበት ይታያል ማለት ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

liability for a defective software
The State of Cybercrime Governance in Ethiopia

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 20 April 2024