የተከበራችሁ አንባቢዎች ለዛሬው ርዕሰ አንቀፅ መነሻ የሆነኝ የውንብድና ወንጀልን የሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች በአግባቡ ባለመረዳት ወይም በተለያዩ መልኩ በመተርጎም የሚፈፀሙ የክስ አመሰራረት ልዩነቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ያለውን አሰራር እና አንቀፁን እኔ በምረዳው መልኩ በማቅረብ ለአንባቢዎቼ እንደሚከተለው ለውይይት እና አስተያየት ክፍት አድርጊያለሁ፡፡
የቀድሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 636 ስር ተደንግጎ የነበረ ሲሆን በዚህም አንቀፅ መሰረት ወንበዴነት “የስርቆት ወንጀል ለመስራት አስቦ ወይም በስርቆት ወንጀል ተይዞ ወይም ደግሞ በስርቆት ያገኘውን ነገር ለመሰወር በማሰብ” የሃይል ተግባር ፈፅሞ እንደሆነ ተደንግጎ ይገኝ ነበር፡፡ በመሰረቱ ይህ ድንጋጌ ተሻሽሎ በ1996ቱ የወንጀል ህግ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በአንቀፁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት የስርቆት ወንጀል የሚፈፀመው ባለንብረቱ ወይም ሌላ ሰው እንደማያየው ወይም እንደማይዘው በማረጋገጥ ስለሆነ የሰውን ንብረት ከመውሰድ ጋር የሃይል ተግባር ከተጣመረ የንብረት አወሳሰዱ ስርቆት መሆኑ የሚቀር በመሆኑ መሆኑን የወንጀል ህግ ሐተታ ዘምክንያት ያትታል፡፡
በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ መሰረት ውንብድናን ከስርቆት አንፃር መቶረጎሙን በመተው ውንብድና እንደሚከተለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡
ማንም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት አስቦ፣ የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ ዕቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት ለማስቀረት ሲል በሌላ ሰው ላይ የኃይል ድርጊት ወይም ከባድ የሆነ የማገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ የፈጸመ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው ለመከላከል እንዳይችል ያደረገው ሲሆን ከአሥራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራት ይቀጣል፡፡
በመጀመርያ ደረጃ ውንብድና የሚፈፀመው ተገቢ ያለሆነ ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት መሆን ይኖርበታል፡፡ የማይገባውን ብልፅግና የማግኘት ሃሳብ ተንቀሳቃሽ እቃ ለመውሰድ እንጂ የማይንቀሳቀስ ንብረት በመውሰድ ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ከሃሳቡ ቀጥሎ የሚመጣው ውንብድናን የሚያቋቁመው የወንጀል ፍሬ ነገር የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ ዕቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት ለማስቀረት የሃይል ወይም የዛቻ ተግባር መፈፀም ነው፡፡ በአንዳንድ ክሶች ላይ እንደሚታየው ከሆነ ውንብድና ተፈፀመ የሚባለው ንብረት ተወስዶ እንደሆነ ነው፡፡ ነገር ግን በወ/ህ/ቁ. 670 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ተንቀሳቃሽ ዕቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ብሎ ብቻ የሃይል ተግባር መፈፀም በራሱ ወንጀሉን ያቋቁማል፡፡