Font size: +
6 minutes reading time (1102 words)

ወንበዴ ማነው? ውንብድናስ ምንድነው?

የተከበራችሁ አንባቢዎች ለዛሬው ርዕሰ አንቀፅ መነሻ የሆነኝ የውንብድና ወንጀልን የሚያቋቁሙ ፍሬ ነገሮች በአግባቡ ባለመረዳት ወይም በተለያዩ መልኩ በመተርጎም የሚፈፀሙ የክስ አመሰራረት ልዩነቶች ናቸው፡፡ በመሆኑም ያለውን አሰራር እና አንቀፁን እኔ በምረዳው መልኩ በማቅረብ ለአንባቢዎቼ እንደሚከተለው ለውይይት እና አስተያየት ክፍት አድርጊያለሁ፡፡

የቀድሞ የወንጀለኛ መቅጫ ህግ አንቀፅ 636 ስር ተደንግጎ የነበረ ሲሆን በዚህም አንቀፅ መሰረት ወንበዴነት “የስርቆት ወንጀል ለመስራት አስቦ ወይም በስርቆት ወንጀል ተይዞ ወይም ደግሞ በስርቆት ያገኘውን ነገር ለመሰወር በማሰብ” የሃይል ተግባር ፈፅሞ እንደሆነ ተደንግጎ ይገኝ ነበር፡፡ በመሰረቱ ይህ ድንጋጌ ተሻሽሎ በ1996ቱ የወንጀል ህግ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ በአንቀፁ ላይ ማሻሻያ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት የስርቆት ወንጀል የሚፈፀመው ባለንብረቱ ወይም ሌላ ሰው እንደማያየው ወይም እንደማይዘው በማረጋገጥ ስለሆነ የሰውን ንብረት ከመውሰድ ጋር የሃይል ተግባር ከተጣመረ የንብረት አወሳሰዱ ስርቆት መሆኑ የሚቀር በመሆኑ መሆኑን የወንጀል ህግ ሐተታ ዘምክንያት ያትታል፡፡

በ1996 ዓ.ም በወጣው የወንጀል ህግ መሰረት ውንብድናን ከስርቆት አንፃር መቶረጎሙን በመተው ውንብድና እንደሚከተለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡

ማንም ሰው ተገቢ ያልሆነ ብልጽግና ለራሱ ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት አስቦ፣ የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ ዕቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት ለማስቀረት ሲል በሌላ ሰው ላይ የኃይል ድርጊት ወይም ከባድ የሆነ የማገላታት ተግባር ወይም ከባድ ዛቻ የፈጸመ፣ ወይም በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው ለመከላከል እንዳይችል ያደረገው ሲሆን ከአሥራ አምስት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እሥራት ይቀጣል፡፡

በመጀመርያ ደረጃ ውንብድና የሚፈፀመው ተገቢ ያለሆነ ብልፅግና ለማግኘት ወይም ለሌላ ሰው ለማስገኘት መሆን ይኖርበታል፡፡ የማይገባውን ብልፅግና የማግኘት ሃሳብ ተንቀሳቃሽ እቃ ለመውሰድ እንጂ የማይንቀሳቀስ ንብረት በመውሰድ ላይ ተፈፃሚነት አይኖረውም፡፡ ከሃሳቡ ቀጥሎ የሚመጣው ውንብድናን የሚያቋቁመው የወንጀል ፍሬ ነገር የሌላ ሰው ንብረት የሆነውን ተንቀሳቃሽ ዕቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም በሚወስድበት ጊዜም ሆነ ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት ለማስቀረት የሃይል ወይም የዛቻ ተግባር መፈፀም ነው፡፡ በአንዳንድ ክሶች ላይ እንደሚታየው ከሆነ ውንብድና ተፈፀመ የሚባለው ንብረት ተወስዶ እንደሆነ ነው፡፡ ነገር ግን በወ/ህ/ቁ. 670 ላይ በግልፅ እንደተደነገገው ተንቀሳቃሽ ዕቃ ለመውሰድ እንዲያመቸው ብሎ ብቻ የሃይል ተግባር መፈፀም በራሱ ወንጀሉን ያቋቁማል፡፡

ለምሳሌ አንድ አሽብር የተባለ ሰው በጨለማ አንድ ሰው ሲመጣ ይመለከትና ጩቤውን ከኪሱ አውጥቶ “ቁም ያለህን አምጣ” በማለት ተበዳይን ደረቱ ላይ ይወገዋል፡፡ ወድያው በአካባቢው የነበረ ሰው ድምፅ ሰምቶ ሲመጣ ተጠርጣሪው ምንም ንበረት ሳይወስድ ጥሎ ይጠፋል፡፡ ይህ ከላይ የተቀመጠው በእውነተኛ ክስተት ላይ የተመሰረተው ምሳሌ እንደሚያሳየው ይህ ክስ ሊቀርብ የሚገባው ከባድ ውንብድናን በሚመለከት ተደንግጎ በሚገኘው አንቀፅ 671 መሰረት ነበር፡፡ ይሁንና ክስ ተረቆ የነበረው በአካል ጉዳት ነበር፡፡ ይህም ስህተት የመነጨው ንብረት ባለመወሰዱ ውንብድናን አያቋቁምም በሚል መነሻ ነው፡፡ በመሰረቱ በአንቀፁ ላይ የሃይል ተግባሩ ወይም ዛቻው የተፈፀመው ተንቀሳቃሽ ዕቃ እንዲያመቸው መሆኑ ብቻ በቂ ነው፡፡ አንዳንድ ዐቃቢያነ ህጎች ይህንን በአግባቡ ቢረዱም ክሱን ከወ/ህ/ቁ. አንቀፅ 670 ወይም 671ን ከአንቀፅ 27(1) በማጣመር በሙከራ ያቀርባሉ፡፡ ንብረት ባለመወሰዱ ብቻ ክሱ ሙከራ ሆኖ ሊቀርብ የሚገባው አይደለም፡፡ ይልቁንም ዛቻ ወይም የሃይል ተግባሩ ተንቀሳቃሽ ዕቃ

ü  ለመውሰድ እንዲያመቸው ወይም

ü  በሚወስድበት ጊዜም ወይም

ü  ከወሰደ በኋላ የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት

ንበረቱን መውሰድ ከሶስቱ አማራጮች ውስጥ አንደኛው ሲሆን ንብረት ለመውሰድ አስቦ ዛቻ ወይም የሃይል ተግባር መፈፀም በራሱ ወንጀሉን ፍፃሜ እንዳገኘ ያስቆጥረዋል፡፡ ስለዚህ በሙከራ ሊቀርብ የሚገባው አይደለም፡፡

የገጠመውን ተቃውሞ ውታማነት ለማስቀረት ሲባል የሚፈጸመው ተግባር የሚከተሉትን ሊያካትት ይችላል፡፡

ü  የኃይል ድርጊት ወይም

ü  ከባድ የሆነ የማንገላታት ተግባር ወይም

ü  ካባድ ዛቻ የፈጸመ፣ ወይም

ü  በማናቸውም ሌላ መንገድ ይህን ሰው ለመከላከል እንዳይችል ያደረገው እንደሆነ ነው፡፡   

እነኚህን በአማራጭ የቀረቡ ፍሬ ነገሮች በሚመለከት የሚፈፀመው የአሰራር ልዩነት የሚመነጨው የኃይል ድርጊት ወይም ማንገላታት ወይም ሰው ለመከላከል እንዳይችል ማድረግ ማለት ምንድን ነው? ከሚል የትርጉም ልዩነት መነሻ ነው፡፡ በምሳሌ ለማስረዳት ያክል በከተማችን አዲስ አበባ የምትኖር ወ/ሪት ስናፍቅሽ የምትባል ቆንጆ በመሃል አራት ኪሎ ከወደጇ ጋር በዘመኑ አለ የሚባል ስልክ ይዛ እያወራች ስትጓዝ አንድ ስሙ ማንጠግቦህ የሚባል ጎሮምሳ ሞባይሏን ከእጇ በመንጠቅ ሲሮጥ በተባበሩ የአካባቢው ሰዎች ይያዛል፡፡ ይህ ከላይ የተቀመጠው ምሳሌ በከተማው የሚስተዋል ሲሆን ክስ የሚቀርበውም በአብዛኛው በወ/ህ/ቁ. 665 በስርቆት ወይም በወ/ህ/ቁ. 713 አስገድዶ መጠቀም ሲሆን በተወሰኑ ክሶች ላይ በወ/ህ/ቁ. 670 ውንብድና ሆኖ ይታያል፡፡ ታድያ እዚህ ጋር ሊጠየቅ የሚገባው ቁምነገር ይህ የመንጠቅ ተግባር ስርቆት፤ አስገድዶ መጠቀም ነው ወይስ ውንብድና? የሚለው ነው፡፡ በሌላ አነጋገር መንጠቅ የሃየል ድርጊት ወይም የሚያንገላታ ተግባር ነው ወይ? የሚለው ነው፡፡

በዚህ ረገድ በአንቀፅ 664(1) ላይ በቤተዘመድ መሃከል የሚፈፀም ወንጀል በግል አቤቱታ የሚቀርብ ስለመሆኑ ሲደነግግ “እንደ ውንብድና፣ መንጠቅ ወይም ማስፈራራት ከመሳሰሉት በኃይል ወይም በማስገደድ ከሚፈጸሙ ወንጀሎች” ብሎ ሲደነግግ መንጠቅ የሀይል ተግባር ስለመሆኑ ጥቆማ ሰጥቷል፡፡ መንጠቅ የሃይል ተግባር ነው ተብሎ የሚቆጠር ከሆነ ደግሞ የመንጠቁ ተግባር የተፈፀመው የሰው ንብረት ለመውሰድ መሆኑ ከተረጋገጠ የውንብድናን ወንጅል የሚያቋቁም እንጂ ስርቆት ሊሆን የሚገባው አይደለም፡፡ በመሆኑም የኃይል ድርጊት ወይም ማንገላታት ወይም ሰው ለመከላከል እንዳይችል ማድረግ የሚለው ፍሬ ነገር በጥንቃቄ ሊታይ የሚገባው ነው፡፡

ስርቆት በመሰረቱ አዩኝ አላዩኝ በማለት የሚፈፀም ወንጀል ለመሆኑ የወንጀል ህግ ሐተታ ዘምክንያት ያትታል፡፡ በመሆኑም ባለቤቱ እያየ ነጥቆ መሮጥ የመሰለ የሀይል ተግባር በመፈፀም ንብረት መውሰድ ስርቆት ተብሎ ሊወሰድ የሚገባው አይደለም፡፡ ንብረትን ነጥቆ መውሰድን በወ/ህ/ቁ. 713 ስር አስገድዶ መጠቀም ነው እያሉ ክስ መመስረት በአሁኑ ጊዜ እየተለመደ የመጣ ቢሆንም ይህ ከባድ ስህተት ስለመሆኑ አፅኖት ሰጥቼ መግለፅ እፈልጋለሁ፡፡ ምክንያቱም በወ/ህ/ቁ. 713 ስር አስገድዶ መጠቀም የሚለው አንቀፅ በመሰረቱ የሚገኘው ከስርቆት እና ውንብድና በተለየ ምዕራፍ ስር ሲሆን በዚህ ምዕራፍ ስር የህሊናን እና የሰውን ችግር መሰረት በማድረግ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ስር ተደንግጎ የሚገኝ ነው፡፡ አስገድዶ መጠቀም ተፈፀመ ለማለት በመጀመርያ ከውንብድና ወንጀል ውጪ መሆን ይኖርበታል፡፡ ውንብድናን የሚያቋቁም ፍሬ ነገር ተሟልቶ ከተገኘ ወደ አአስገድዶ መጠቀም መሄድ አይኖርብንም፡፡ ከዚህም ባለፈ በአስገድዶ መጠቀም ጊዜ የግል ተበዳይ ላይ የሚደርስ የሃይል ወይም የዛቻ ተግባር ቢኖርም ንብረቱን የሚሰጠው ተበዳይ እራሱ እንደሆነ እንጂ በውንብድና ወቅት እንደሚታየው ተጠርጣሪው እራሱ በሃይል ሲውስድ ወይም ለመውሰድ አስቦ ወይም ከወሰደ ቡኋላ የቀረበበትን ተቃውሞ ለማስቀረት በሚል የሃይል ወይም የዛቻ ተግባር ሲፈፅም አይደለም፡፡ ተበዳይም ከውንብድና ወንጀል ውጪ የሃይሉን ተግባር ወይም ዛቻውን ፈርቶ ንብረቱን እራሱ የሰጠው እንደሆነ ብቻ ነው በዚህ አንቀፅ የሚሸፈነው እንጂ ነጥቆ መውሰድ አስገድዶ መጠቀምን በሚመለከት የተደነገገው አንቀፅ ስር የሚሸፈን አይደለም፡፡

በአስገድዶ መጠቀም ወቅት የመስጠቱ ፍላጎት ምንም እንኳን ከዛቻው ወይም ከሃይል ተግባሩ የሚመነጭ ቢሆንም ተበዳይ በራሱ ጊዜ የሰጠው ንብረት መሆን ይኖርበታል፡፡ እዚህ ጋር ትኩረት ሊደረግበት የሚገባው የሃይል ማነስ ወይም መብዛት ሳይሆን በዋናነት በአስገድዶ መጠቀም ወቅት የተወሰነ የተበዳይ ፍቃድ መኖሩ ነው፡፡ በርግጥም ተጠርጣሪው ጥቅም ያለበትን ነገር ሲወስድ የተበዳይ ፍቃድ ምንጭ ዛቻው ወይም የሃይል ተግባሩ እንጂ በበጎ ፍቃድ አለመሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ይህ ተበዳይ ከሚደርስንኝ የሃይል ተግባር ወይም ዛቻ ይልቅ ንብረቱን መስጠት ይሻለኛል የሚል ምርጫ ውስጥ ይገባል፡፡ በተቃራኒው በውንብድና ጊዜ ተበዳይ ንበረቱን ለመስጠት ከመስማማት ይልቅ እንደሚቃወም እንደውም የሃይል ወይም የዛቻው ተግባር የሚፈፀመው የገጠመውን ተቃውሞ ውጤታማነት ለማስቀረት ሲባል መሆኑን የወንጀል ህጉ አንቀፅ 670 ስር ተደንግጎ ይገኛል፡፡

Robbery differs from extortion in that the property is taken against the will and without the consent of the victim, unlike extortion, where the victim consents, although unwillingly, to surrender money or property.

በሁለቱ አንቀፅ መሃከል ያለው ሌላው ልዩነት የዛቻ ወይም የሃይል ተግባር አይነት መነሻ አድርጎ ነው፡፡ በባህርያቸው በውንብድና ወቅት ሊደርስ የሚችለው ጉዳት በቅርብ የሚደርስ (the treat of immediate physical harm i.e. imminent) ነው፡፡ በተቃራኒው በአስገድዶ መጠቀም ወቅት ሊደርስ የሚችለው ጉዳት አፋጣኝ ላይሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ አበበ የተባለ ግለሰብ ለወ/ሮ ብርቄ ገንዘብ በባንክ ካላኩለት በስተቀር ከባለቤታቸው ጓደኛ አቶ ዘውዱ ጋር ያደረጉትን አመንዝራ እንደሚያጋልጡ ሊዝቱ ይችላሉ፡፡ ከዚህም እንደምንረዳው ወ/ሮ ብርቄ ሚስጥራቸው ከሚወጣ ይልቅ ገንዘቡን መስጠት ይመርጣሉ፡፡ ገንዘቡም ወድያው እንደውንብድና የሚወሰድባቸው አይደለም፡፡

በመሆኑም ከላይ በወ/ህ/ቁ. 670 ስር የተመለቱትን የውንብድና ማቋቋምያ ፍሬ ነገሮች ከግምት በማስገባት እና በወ/ህ/ቁ. 671 ስር ማክበጃ ምክንያቶችን መነሻ ተደርጎ ተገቢው ክስ ሊቀርብ የሚገባው ስለመሆኑ እና ዳኞችም ይህንኑ ልዩነት በአግባቡ ሊያስተውሉት ይገባል እላለሁ፡፡

 

አመሰግናለሁ!

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ተከሳሽ ምስክር መሆን ይችላል?
Constitutionality of Constitutional Interpretation...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 05 October 2024