Font size: +
15 minutes reading time (2971 words)

ሕግ መንግሥቱን በፖለሲ ማዕቀፍ ሥር?

ሰሞኑን በአንድ ካፌ ገብቼ የተደረደሩ ቀን ያለፈባቸው ጋዜጦች ስመለከት የሪፖርተር ጋዜጣ በሚያዚያ 1/2009 የእለተ-እሁድ እትሙ ላይ “ሰበር ሰሚ ችሎት  በክራውን ሆቴል የንግድ ምልክት ላይ የሰጠው የመጨረሻ ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል ተባለ” በሚል ርእስ ባወጣው ዘገባ ላይ ዐይኔ አረፈ። ከዚህ በፊት በርካታ ጉዳዮች ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ስለመቅረባቸው አውቃለሁ። በሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ላይ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ክርክር ተነስቶበት ወደ ጉባኤው ስለመቅረቡ ሳነብ ግን የመጀመሪያዬ ነው።  ምናልባት እኔ ያላወቅኳዋቸው ተመሳሳይ ጉዳዮች ከዚህ በፊት ቀርበው ይሆናል። ያም ሆነ ይህ ርእሰ ጉዳዩ ቀልቤን ስለሳበው ባለጉዳዮቹ  ስለተከራከሩበት ጉዳይና የችሎቱ ውሰኔ  ለማወቅ ጉጉት አደረብኝ። እናም  ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ስለተወሰደው የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔና ስለክርክሩ ከሥሩ ለማየት ወሰንኩ። ስለሆነም የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ቅጂ ፈልጌ በመመልከት የሚከተለውን  የግል እስተያየቴን ለመጻፍ ውደድኩኝ።

ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል የተባለው ውሳኔ ምንነት

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ውሰኔ የሰጠበት ጉዳይ በክራውን ሆቴል  ባለቤት (አመልካች) እና ሲክስ ኮንትኔታል ሆቴልስ (ተጠሪ) ከ2006 ዓ.ም ጀመሮ ከአእምሮ ንብረት ጽሕፈት እሰከ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ብሎም ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበ  ክርክር ነው። ይህ የመዝገብ ቁጥሩ 117013 የሆነውና ሰበር ሰሚ ችሎቱ በሰኔ 22 ቀን 2008 በዋለውና አምስት ዳኞች በተሰየሙበት ችሎት የተወሰነው ውሳኔ ከንግድ ምልክት ጥበቃ ጋር የተያየዘ ክርክር ነው። ወደ ሰበር ሰሚ ችሎት የቀረበው ጉዳይ ከንግድ ምልክት ምዝገባ  ተቃውሞ ጋር በተያየዘ የክራውን ሆቴል ባለቤት በአእምሮ ጽሕፈት ቤት ውሰኔ ቅር ተሰኝተው ለከፈተኛ ፍርድ ቤት ይገባኝ ያሉበት ጉዳይ የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የእእምሮ ጽሕፈት ቤት ውሳኔውን ስለኣጸና የፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረታዊ የሕግ ስህተት ያለበት ስለሆነ በሰበር ታይቶ ይታረምልኝ በማለት ሲሆን፤ ሰበር ሰሚ ችሎቱም ጉዳዩን ከስር መሰረቱ በመፈተሽ መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ብሎ ለአመልካች ወስኗል። 

ጉዳዩ ከመሰረቱ ሲታይ በወርሃ ነሃሴ 2005 “CROWNE PLAZA” በሚል በተጠሪ በኩል  በቀረበው የንግድ ምልክት ምዝገባ ጥያቄ ላይ ተቃውሞ ካለ በቀረበው የጋዜጣ ጥሪ መሠረት አመልካች (CROWN HOTEL) በቃልና በጽሁፍ በተደጋጋሚ ተቃውሞ ያቀርባሉ። ለተቃውሞ ምክንያት የሆነው በሕግ ጠበቃ ያገኘውን የንግድ ምልክት የቀዳሚነት መብቴን ይጥሳል የሚል ነው። ተቃውሞው የተመሠረተው በአዋጅ 501/ 2005 አንቀጽ 6 እና  አንቀጽ 7 መሠረት ሲሆን በተለይም በአንቀጽ 7(1) “ከአንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይ እቃዎች ወይም አግልግሎቶች  ጋር የተያያዘ  የሌላ ሰው ቀዳሚ የንግድ ምልክት ጋር አንድ ዓይነት ወይም መሳከርን ሊያስከትል ተመሳሳይነት ያለው”  ሲሆን ለምዝጋባ በቁ አይደለም ብሎ በሚደነግገው መሠረት እንዲሁም በተጨማሪም በንግድ ምዝጋባ አዋጅ 686/2002 አንቀጽ 24 (3) (ሀ) መሠረት የንግድ መዝጋቢው አካል “ቀደም ሲል ከተመዘገቡት የንግድ ስሞች ጋር አንድ ዓይነት ወይም ተመሳሳይና አሳሳች አለመሆን  24 (3) (በ) መሠረት ደግሞ በንግድ ስም መዝገብ  በተመዘገበ የንግድ ስም ላይ ላይ ከፊቱ ወይም ከኋላው ቃላት በመጨመር ያልቀረበ መሆኑን በማረጋገጥ እንዲመዘገብ በሚደነግገው መሠረት ቀደም ሲል ተመዝግቦ ሥራ ላይ ካለው CROWN HOTEL+ logo ጋር ይመሳሰል። በዚህም በሕግ ጥበቃ ያገኘው መልካም ስሜና ዝናዬ ይነካል የሚል ነበር። እውነት ነው የእእመሮ ንብረት ጽሕፈት ቤት ትኩረት የንግድ ምልክቱ ወይም የፈጠራው ጉዳይ ላይ ሲሆን የንግድ መዝጋቢው አካል ደግሞ በንግድ ስሙ ላይ ያተኩራል። ቀዳሚነት ያለው የንግድ ምልክት “CROWN HOTEL” የሚል ሲሆን፤ አዲሱ የንግድ ምልክት “CROWNE PLAZA” የሚል ነው። የተጨመሩት ነገሮች በ CROWN ላይ” E”  እንዲሁም “PLAZA”  የሚለው ቃል ነው።  ሁሉቱም የሆቴል አግልግሎት ሰጪዎች መሆናቸው ልብ ይሏል። በክርከር ሂደቱ በርካታ ጭብጦት ለክርክር ቀርበው የነበረ ሲሆን የዚህ ጽሑፍ ዓላማ በክርክር ሂደቱ በጭብጥነት ተይዞ እስከ መጨረሻ በዘለቀው  ጭብጥ ላይ ብቻ  የሚያተኵር ይሆናል። 

በፍርድ ሃተታው እንደተመለከተው በአመልካች በኩል ለተቃውሞ መነሻ የሆኑት የሕግ መሰረቶች  የንግድ ምዝገባ አዋጅ እና የንግድ ምልክት ምዝጋባ አዎጅ ሲሆኑ  ጽሕፈት ቤቱ በመጀመሪያ  ተቃውሞውን  ከአዋጅ 501/ 1998 ጋር በማገናዘብ ተቀበሎ የምዝገባ ሂደቱን አቋረጦ የነበረ ቢሆንም ለሁለተኛ ጊዜ ውሳኔውን ሊቀለበሰው ችሏል። ውሳኔው ለአመልካች ከተነገረ በኋላ እንደገና ውሰኔውን በመቀየር የሚከተሉት ምክንያቶችን አቅርቧል። ጽሕፈት ቤቱ የንግድ ምልክቶቹ መመሳሰል ሳይክድ ኢንቨስትመነትን ለማበረታት ይጠቅማል በሚል ሁለቱም የንግድ ምልክቶች እንዲቀጥሉ ወስኗል። አክሎም ጽሕፈት ቤቱ ውሳኔው እንዳይደገም ራሱን አስጠንቅቆ ዘግቶታል። ይህም ውሰኔው ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት ካለው ፍላጎት ውጭ ተገቢ እንዳለሆን ያመነበት ይመስላል። ምክንያቱ ይህንን ውሳኔ ከሰጠ በኋላ ተመሳሰይ ውሳኔ እንዳይደገም በራሱ ላይ እግድ አስቀምጧል። እዚህ ላይ ሊነሳ የሚቸለው ጥያቄ ውሳኔው ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እስከ ሆነ ድርስ የማይደገመበት ምክንያት ምንድ ነው? ከአዲሱ ድርጅት የተሻለ ኢንቨስትመነት ይዘው በተመሳሳይ  የንግድ ምልክት ለሚቀርቡ ባለሃብቶችስ ምን ዓይነት ምላሽ ሊስጥ ነው? ዜጎችን በእኩልና ፍታሃዊ መንገድ ሊያገልግል የቋቋመ ተቋም ልክ እንዳልሆነ አምኖ እንዳይደገም የሚለውን ውሳኔ እንዴት ሊወስን ይችላል? CRROWN HOTELS and Convention Center የሚል የንግድ ምልክት ይዞ ከቀደሙት ሁለቱ ሆቴሎች ይልቅ የተሻለ አቅም ያለው ባለሀብት ለምዝገባ ቢያመለክትስ? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎችን ማንሳት ይቻላል።

የሆነ ሆኖ በጽሕፈት ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኙ አመልካች ጉዳዩን ወደ ከፍተኛ ፍርድ ቤት በይግባኝ ያቀረቡ ሲሆን፣ ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ አጽንቷታል።  ፍርድ ቤቱ የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ ያጸናበት ምክንያት አንደኛ ኢንቨስትመንትን ለማበራታት የሚለው የጽሕፈት ቤቱ የውሳኔ ምክንያት በመቀበል በተጨማሪ ደግሞ  በሆቴሎቹ ሊገለገሉ የሚችሉ ዜጎች በትምህርታቸውና በኢኮኖሚ አቅማቸው የተሻለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ስለ ሆነ ሊደናገሩ አይችሉም የሚል ነው። እነዚህ አመክንዮዎች በእርግጥ የተጠኑና የተረጋገጡ ስለመሆናቸው የሚያከራክር ይሆናል። ምክንያቱም ለረጅም ጊዜ ሥራ ላይ የዋለና በተግባር የተፈተነ ኢንቨስትመንት በመጉዳት አዲስ ኢንቨስትመንት፣ የሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንትን በመጉዳት የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ የሚባሉ ትንታኔዎች ከሃገራዊ ፖሊሲዎችና ከአጠቃላይ አግባብነት ካላቸው መርሆዎች ጋር መሄዳቸው ያጠራጥራል።  እንዲሁም  በሆቴሎቹ የሚጠቀሙ ሰዎች የተሻለ የትምህርት ደረጃ እንዳላቸው እንዴት አስቀድሞ ሊታወቅ ይችላል የሚል ጥያቄም ያስነሳል?  የተጠቃሚዎች የኢኮኖሚ አቅምስ እንዴት መሳከርን ሊያስቀር ይችላል? ወዘተ የሚሉ ጥያቄዎች በአግባቡ ስለመጤናቸው የቀረበ ሀታታ ወይም ትንታኔ የለም። ኢንቨስትመንትን መሳብና ማበረታታት በራሱ የሚደገፍና የተገባ ቢሆንም ሥራ ላይ ያሉትን በማቀጨጭ ወይም በመጉዳት የሚደረግ ማበረታተት ዓላማውን የሳተ ይሆናል።  

በመሠረቱ የንግድ ምልክት አንድ ዓይነት እንዳይሆን ወይም እንዳይመሳሰል የተፈለገበት ምክንያት የተወሰነ የሞራል ምክንያት ሊኖረው ቢችልም በዋናነት የኢኮኖሚ ምክንያት ነው። ጥቅሙም ለባለ ንግድ ምልክቶቹ  ብቻ ሳይሆን ለተጠቃሚውም ብሎም በአጠቃላይ ለዘርፉ ዋስትና እና ቀጣይነት ጭምር መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል። በንግዱ ዓለም “ከመልካም ሽቶ መልካም ስም ይሻላል” እንደሚባለው መልካም ስም ትልቅ ትርጉም አለው። መልካም ስም የንግድ ተቋሙ ህይወት ነው። በመሆኑም ስም መገንባት ቀላል አይደለም። የተገነባ ስም መውሰድ ወይም ማፍረስ ግን ቀላል ነው። ስለሆነም ነው የሕግ ጥበቃ የሚያስፈልገው። በሁለቱ ተቋማት ያለ የአቅም ልዩነት ምን ያህል እንደ ሆነ ወይም የትኛው የተሻለ  አቅም እንዳለው በውሳኔው ሐታተ የተመለከተ ነገር ባይኖርም  የንግድ ባለቤትነት መለኪያው አቅም ሳይሆን ቀዳሚነት መሆኑ በግልጽ ተደንግጓል። ተጠሪ የንግድ ምልክቱን ለማስመዘገብና እስከ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ የደረሱበት ምክንያት በራሱ  “ስምና የንግድ ምልክት“ በንግዱ አለም ያለው ትርጉም ያመለክታል። በመሆኑም አካረካሪው ጭብጥ ሊሆን ይገባ የነበረው ምልክቶቹ ይመሳሰላሉ ወይስ አይመሳሳሉም  እንጂ “እንዳይደገም” በሚል ገደብና ኢንቨስትመንትን ያበረታታል የሚለው ምክንያት ተገቢነት ያለው አይመስልም።     

የሆነ ሆኖ ከፍተኛው ፍርድ ቤትም የጽሕፈት ቤቱን ውሳኔ አጽንቶቷል። በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ቅር የተሰኙት አመልካች የከፍተኛ ፍርድ ቤት ውሳኔው መሠረታዊ የሕግ ስህተት ስላለበት ይታረምልኝ በሚል አቤቱታ ለሰበር ሰሚ ችሎት አቅርበው፤ ሰበር ሰሚ ችሎቱ በ28 ቀን 2008 በዋለው ችሎት ጉዳዩን ከስር መስረቱ በመመርመር ለአመልካቿ ወስኗል። ሰበር ሰሚ ችሎቱ ለውሳኔው እንደ ምክንያት ያቀረበው ሃተታ በጽሕፈት ቤቱ ተወስኖ በከፍተኛው ፍርድ ቤት የጸናው ውሰኔ አግባብነት ካላቸው ሕጎች ጋር  በማገናዝብ  ውሳኔው መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት ወይስ የለበትም የሚል ጭብጥ በመያዝ ሲሆን፣   ችሎቱ  ጽሕፈት ቤቱም ሆነ ፍርድ ቤቱ  ያቀረቡት ኢንቨስትመንት ለማበረታት የሚሉ አምክንዮዎች በንግድ ምልክት አዋጁም ሆነ በሌላ አግባብነት ባላቸው ሕጎች  በአስገዳጅነት ያልተደነገገ በመሆኑና በተቃራኒው የንግድ ምልክት ጥበቃ አስፈላጊነት በማምረት፣ በማከፋፈል ወይም አግልግሎት በመስጠት ሥራ ላይ የተሰማሩትን ሰዎች  በአግልግሎት ወይም ምርቶች መመሳሳል ምክንያት መሳከር እንዳይፈጠር በማድረግ  ብሔራዊ ኢኮኖሚን ለማዳበርና ለንግድ እና ኢንዱስትሪ ልማት አዎንታዊ አስተወጽኦ  እንዲኖረው በማድረግ በመሆኑ፤ የሕጎቹ መሠረታዊ ዓላማዎች የሚቃረኑ ውሳኔዎች ናችው በማለት ውሳኔው መሠረታዊ የሕግ ስህተት አለበት በማለት የሥር ፍርድ ቤት ውሳኔን ሽሮታል።  

የንግድ ምዝገባ አዋጁን ዓላማዎች እና የፖሊሲ ምክንያቶች የሚገልፀው የአዋጁ መገቢያ የንግድ ምልክት ጥበቃ ያስፈለገበት ምክንያት፣ 

  1. የአምራቾችን እና አከፋፋዮችን ወይም አግልግሎት በመስጠት የተሰማሩትን ሰዎች መልካም ስምና ዝና ስለሚጠብቅ፣
  2. የሸማቾችን ወይም የተጠቀሚዎችን ምርጫ በመምራት ረገድ ትልቅ ሚና ስላለው፣
  3. ብሄራዊ ኢኮኖሚን ስለሚያዳብር
  4. ለንግድና ኢንድስቱሪ ልማት አዎንታዊ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ነው።

ይላል፡፡ በመሆኑም የንግድ ምልክት ጥበቃ (ጥበቃ ማለት ቀድሞ የተመዘገን ስም አለአግባብ ሌላ ወገን እንዳይጠቀምበት ወይም አመሳሰሎ እንዳይጠቀመበት መከልከል ነው) ዓላማ  የአገልገሎት ሰጪውን ስምና ዝና በመጠበቅ በአግልግሎቱ እንዲቀጥል ለማድረግ፣ ብሔራዊ ኢኮኖሚው እንዲዳብር ለማድረግ፣ ንግዱን ወይም ኢንዱስትሪው አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንዲኖረው ማደርግና የሸማቾችን ጥቅም ለመጠበቅ ነው። ይህንኑ የሕጉ ዓላማ ይዘን የጽሕፈት ቤቱም ሆነ የከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ስንመለከት የአዋጁን ፖሊሲና ዓላማ በቀጥታ የሚቃረን ሆኖ እናገኘዋለን። ምክንያቱ ውሳኔው ከአዋጁ በተቃራኒው ኢንቨስትመንትን ማበረታት የንግድ ምልክቱን በመጠበቅ ፋንታ ለኢኮኖሚ ሲባል ጥበቃውን በማንሳት ወይም በማላላት ነው ከሚል እምነት የሚመነጭ መሆኑ ነው።

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊነሳ የሚችለው መሠረታዊ ጥያቄ ውሳኔው ሊያስከትል የሚችለው ማለቂያ የሌለው  ውዥንብር ነው።  የንግድ ምልክቶቹ  አንድ አይደሉም፣ አይመሳሰሉም ወይም መሳከርን አይፈጠሩም ብሎ መደምደም እና ውሳኔ መስጠት አከራካሪ ሊሆን ቢችልም የፍሬ ነገርና የማስረጃ ጉዳይ ስለሆነ ውሳኔው ተገቢ ባይሆንም አሉታዊ ተጽእኖው ትንሽ ነው። ምክንያቱም ወደ ሌላ የመዛመት አቅሙ ውሱን ነው።  ነገር ግን ቢመሳሰሉም  አንደኛ ተጠቃሚዎች ከፍ ያለ እውቀትና ኢኮኖሚዊ ብቃት ስለላቸው  በቀላሉ አይሳሳቱም በሌላ በኩል ደግሞ ምልክቶቹ ቢመሳሰሉም ኢንቨስትመንትን ሊያበረታታ ይችላል በማለት ጥበቃውን ማላላት ማለቂያ ወደ ሌለው አዙሪት ያስገባል። ምክንያቱም የተሻለ ባለሀብት በመጣ ቁጥር በጣም በርካታ ተመሳሳይነት ያለቸውን የንግድ ምልክቶችን በመፍቀድ ለከፍተኛ ውዝግብ ሊዳርግ ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሁኔታም ባለሀብቶቹም ሆነ በአጠቃላይ ዘርፉ ክፉኛ የሚጎዳ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል።

የፌደሬሽን ምክር ቤትስ ምን ይወስን የሆን?

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ አንቀጽ 62 (1) የፌደሬሽን ምክር ቤት ሕገ መንግሥትን የመተርጉም ስልጣን እንዳለው ደንግጓል። በተመሳሳይም አንቀጽ 83(1) “የሕገ መንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ ሲነሳ በፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ውሳኔ ያገኛል” በሚል ጥቅል አንቀፅ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ የፌደሬሽን ምክር ቤት ስልጣን መሆኑን  ይደነግጋል። ሕገ መንግሥቱ የሕገ መንግሥት ክርክር ጉዳይ ምን ሊሆን ይችላል? የትና መቼ ሊነሳ ይችላል? የሚሉ ጥያቄዎችን በግልጽ አይመልስም። ሆኖም ጉዳዩ በተሻለ መንገድ የተብራራው ስለ ሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ስልጣንና ተግባር በሚደነግገው አንቀፅ 84 ነው። አንቀፅ 84(1) አጣሪ ጉባኤው ሕገ መንግሥትን የማጣራት ስልጣን ይኖረዋል በማለት በተመሳሳይ በጥቅል ሁኔታ ሲደነግግ፣ በንኡስ አንቀፅ 2 የሕገ መንግሥት ተቃርኖ በፌደራሉ መንግሥትም ሆነ በክልል ሕግ አውጪ አካላት የሚወጡ ሕጐች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለክታል። በአንቀጽ 84 (2) እና (3) መሠረት ክርክር ሊነሳ የሚችለው በፍርድ ቤት ከተያዘ አካራካሪ ጉዳይ ጋር በተያያዘ መሆኑን ያመለክታል። ስለሆነም ጥያቄ አቅራቢው ጉዳዩን የያዘው ፍርድ ቤት ወይም ባለጉዳዩ ሊሆኑ እንደሚችሉ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም በአንቀጽ 84 መሠረት ለሕገ መንግሥታዊ ክርክር መነሻ ሊሆን የሚችለው ውሳኔ የፌደራል ወይም የክልል መንግሥታት ሕግ አውጪ አካላት ያወጡት ሕግ እንደሚሆን በሌላ በኩል ደግሞ ጥያቄ አቅራቢዎቹ ፍርድ ቤቶች ወይም ባለጉዳዮች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመለክታል፡፡ እዚህ ላይ ሊነሳ የሚችለው ጥያቄ  የአስፈፃሚው አካላትና ፍርድ ቤቶች ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ውሳኔ ቢወስኑስ? የሚል ይሆናል። የሕገ መንግሥቱን የበላይነት ግምት ውስጥ በማስገባት በማንኛውም  አካል የተወሰነው ውሳኔ ሕገ መንግሥቱን እስከ ተቃረነ ድረስ በፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ሊያገኝ ይገባል የሚለው አረዳድ የበለጠ ምክንያታዊ ነው። ነገር ግን ሕገ መንግሥቱን ከላይ ለተመለከተው ሰው የሕገ መንግሥታዊ ክርክር ምንጮች በሕግ አውጪዎች የሚወጡ ሕጐች ብቻ ይመስላሉ፡፡ እንደዛ ከሆነ ደግሞ የአስፈፃሚዎችና ፍርድ ቤቶች ውሳኔዎች ሕገ መንግሥትን ሊጥሱ አይችሉም፤ ወይም ከፍርድ ቤቶችና ከአስፈጻሚዎች ውሳኔዎች ሕገ መንግሥታዊ ክርክር ሊነሳ አይችልም የሚል ድምዳሜ ላይ ያደርሳል፡፡

የሕገ መንግሥቱን ጥቅል ድንጋጌዎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚያወጧዋቸው  ሕጎች ይበልጥ መዘርዘር እንዳለበት ይታመናል። ስለሆነም ከሕገ መንግሥቱ ይልቅ የሕገ መንግሥት ጉዳዩች አጣሪ ጉባኤ ለማጠናከርና ስልጣንና ተግባሩን ለመዘርዘር በድጋሚ የወጣው አዋጅ 798/2005 አንቀፅ 3 አጣሪ ጉባኤው ሊመረምራቸው የሚገቡ ሕገ መንግሥታዊ የክርክር ጉዳዮችን ይዘረዝራል። አንቀጹ ለሕገ መንግሥት ክርክር ጉዳይ ማንኛውም ሕግ፣ ልማዳዊ አሰራር ወይም የመንግሥት አካል ውሳኔ ወይም የባለስልጣን ውሳኔ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ይገልፃል፡፡ አዋጁ የግጭት መነሻ ስለሚሆኑ ውሳኔዎችም ሆነ ጥያቄ አቅራቢዎች ከሕገ መንግሥቱ በተሻለ በዝርዝር ይገልጻል። ቀደም ሲል እንደተገለጸው ሕገ መንግሥቱን ከላይ በመመልከት ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄዎች ሊነሱ የሚችሉት በፍርድ ቤቶችና ባለጉዳዩች ሲሆኑ በዚህ አዋጅ መሠረት ግን የምክር ቤት አባላት እና አስፈፃሚዎችን ጨምሮ ፍርድ ቤቶች፣ በባለጉዳዮች ወይም ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጥያቄዎችን (ጥያቄውን) ሊያቀርቡ ይችላሉ። በመሆኑም በአዋጅ 798/2005 መሠረት ፍርድ ቤትን ጨምሮ በየትኛውም አካል የተወሰነ ውሰኔ ከሕገ መንግሥቱ ተቀርኗል ወይም ሕገ መንግሥታዊ መብትና ጥቅምን ይነካል ተብሎ እስከ ታመነ ድረስ ወደ አጣሪ ጉባኤው ሊቀርብ ይችላል። በአዋጁ የተቀመጠው አንድ መሠረታዊ ቅድመ ሁኔታ በአስተዳደር አካል ወይም በፍርድ ቤት የሚወሰኑ ውሳኔዎች ወደ አጣሪ ጉባኤው ከመቅረባቸው በፊት የመጨረሻ የመወሰን ስልጣን ባለው አካል የተወሰኑ መሆን ይኖርባቻዋል።  

በመሆኑም ቀደም ሲል የተነሳው የአስፈፃሚ ወይም በፍርድ ቤቶች ውሳኔ ምክንያት ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ተጥሷል የሚል ወገን በአዋጅ 798/2005 አንቀፅ 3 መሠረት ጥያቄውን ማቅረብ ይችላል፡፡ በአዋጅ አንቀፅ 3(1) ‹‹ማንኛውም የመንግሥት አካል›› የተባለው ሐረግ በአዋጁ አንቀፅ 2(6) መሠረት የፌደራልም ሆነ የክልል ሕግ አውጪ፣ ሕግ አስፈፃሚምና ሕግ ተርጓሚ አካል መሆኑ ተመልክቷል፡፡ እናም በፍርድ ቤቶችም ይሁን በአስፈፃሚ የሚወሰኑ ውሳኔዎች በመጨረሻው ባለስልጣን የታዩና ይግባኝ የሌላቸው መሆናቸው ሊረጋገጥ እና የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ከተነሳባቸው ለአጣሪ ጉባኤው ሊቀረቡ ይችላሉ።

ስለዚህ  የፍርድ ቤት ውሳኔ የሕገ መንግሥት ከርክር ሊያስነሳ የሚችለው ጉዳዩ በሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ከተሰጠበት በኋላ ይሆናል፡፡ ይህም ምናልባት ሰበር ሰሚ ችሎቱ ወደ ሰበር አያስቀርብም ብሎ የወሰነበትን ጉዳይም ያካትት ይሆናል። ስለሆነም በጋዜጣው የተመለከተው የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔ ላይ የተነሳው ሕገ መንግሥታዊ ክርክር ጉዳይ  ውስጣዊ ይዘቱ  ለጊዜው ትተን ወደ አጣሪ ጉባኤው መቅረቡ በራሱ ችግር ያለው ጉዳይ አለመሆኑም መረዳት ያስፈልጋል።

በመሠረቱ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔ ለተካረካሪ ወገኖች ብቻ ሳይሆን ከጉዳዩ ጋር የተመሳሰለ ጉዳይ ላላችው ወገኖች ሁሉ ከፍተኛ ትርጉም ያለው ነው። ምክንያቱ የፌደራል ፍርድ ቤቶች እንደገና ለማሻሻል በወጣ አዋጅ 454/1997 መሠረት ከአምስት ያላነሱ ዳኞች ውሳኔ የሰጡበት  የሰበር ጉዳይ ወይም ትርጉም በየትኛውም ደረጃ ባለው የክልልም ሆኖ የፌዴራል ፍርድ ቤት ተፈፃሚ ይሆናል፡፡ ይህ መሆኑ ጉዳይ ላይ የተለያዩ ትርጉምና ውሳኔ እየተሰጠ በህብረተሰቡ ዘንድ አላስፈላጊ መደናገርና መሳከር የሚያስቀር በመሆኑ ሊደገፍ የሚገባ ጉዳይ ነው። በሌላ በኩል ደግሞ የሰበር ሰሚ ችሎት ውሰኔ ራሱ ችሎቱ እስኪቀይረው ድረስ እንደ ሕግ ሆኖ የሚያገለግል ስለሆነ  በክርክር ሂደቱ ተሳታፊ ስለሆኑ  የባለጉዳዮች መብትና ጥቅም ብቻ ሳይሆን የሌሎችን ተመሳሳይ ጉዳይ ያላቸው ዜጎች ጥቅም የሚነካ ስለሚሆን በጥንቃቄ ሊታይ ይገባዋል። 

ጋዜጣው የአጣሪ ጉባኤው ጉዳዩን ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ለውሳኔ መላኩ ብቻ ሳይሆን   ውሳኔው ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልጋዋል ያለበትን ምክንያትም እና አስተያየት    ቀንጨብ አድርጎ አስነብቧል። አጣሪ ጉባኤው አጣርቶ ወደ ፌደሬሽን ምክርት የሚያቀርበው ጉዳይ ተራ አስተያየት ሳይሆን ለመጨረሻ ውሰኔ የሚቀርብ የውሳኔ ሃሳብ መሆኑ በሕገ መንግሥቱም ሆነ በአዋጁ ተደንግጓል። በመሆኑም አስተያየቱ እንደ ተራ አስተያየት ሳይሆን ስልጣን ባለው አካል የቀረበ ለመጨረሻ ውሳኔ የቀረበ ሃሳብ ነው ማለት ነው።  ከሕገ መንግሥቱ መንፈስም ሆነ በአዋጅ 798/2005 ላይ ከተዘረዘሩት ጉዳዮች ለመረዳት እንደሚቻለው ጉባኤው የሚመለከታቸው ጉዳዮች የፖሊሲ አማራጭ ሃሳቦችን ሳይሆን፤ ውሳኔው በሕገ መንግሥቱ ጥበቃን ካገኙ መብቶችና ጥቅሞች ጋር ይጋጫል ወይስ አይጋጭም የሚል መሆን አለበት። ሕገ መንግሥታዊ ዓላማዎችን ወደ መሬት ከማውረድ አንጻር ልዩ ልዩ የፖሊሲ አማራጮች ሊቀርቡ ይችላሉ። በሕገ መንግሥቱ ማእቀፍ ስር ስለ ሚቀርቡ የፖሊሲ አማራጭ ጉዳዮች የፖለሲ አውጨዎችና ስልጣን የያዘው አስፈጻሚ ጉዳይ እንጂ የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ ወይም የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ አይደለም። በሕገ መንግሥቱ ማዕቀፍ ስር እስከሆነ ድረስ የፖሊሲ አማራጮች በፖሊሲ ባለድርሻ አካላት መካከል የሚደረጉ ክርከሮችና በፖሊሲ አውጭዎች ብሎም በዜጎች ምርጫ ውሳኔ የሚስጠባቸው እንጂ ሕገ መንግሥታዊ ክርክር የሚደረገባቸው ሊሆኑ አይገባም። የፖሊሲ አማራጭ ጉዳይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ የሚሆን ከሆነ መንግሥትና ሕዝብ እንደየወቅቱ  ነገር ግን የሕገ መንግሥቱ የፖሊሲ መርሆዎችን ሳይጥሱ አማራጮችን መቀያየር አይችሉም ማለት ነው። በመሆኑም  የኢንቨስትመንትን አማራጭ ወይም አእምሮ ንብረት ጥበቃ  ጉዳይ አጥብቦ መተርጐምና አስፍቶ መተርጐም ጉዳይ የሕግ አውጨዎችና ፍርድ ቤቶች ጉዳይ መሆን አለበት። የአጣሪ ጉባኤው አስተያየት መታየት ያለበት ከፖሊሲ አማራጭና ከወቅታዊ የኢንቨስትመንት ፍላጎት አንጻር ሳይሆን ከራሱ ከሕገ መንግሥቱ ዓላማና ግልጽ ድንጋጌዎች አንጻር ነው። ሕገ መንግሥቱ በወቅታዊ ፍላጎት የሚገራ ከሆነ ሕገ መንግሥቱን ከፖሊሲ አማራጭ በታች የሚያደርግ ይሆናል። በመሆኑም  አጣሪ ጉባኤው አንድም ሰበር ሰሚ ችሎቱ ለውሳኔው መነሻ ያደረጋቸው ሕጎች ከሕገ መንግሥቱ ይጋጫሉ ወይስ አይጋጩም? ወይም ደግሞ  ችሎቱ  ሕጉን የተረጐመበት መንገድ በሕገ መንግሥት ጥበቃ ካገኙ መብቶችና ጥቅሞች ጋር በሚጋጭ መልኩ  ነው ወይስ አይደለም? የሚሉ መሆን አለባቸው።

ሆኖም ጋዜጣው ላይ የተዘረዘሩትና የአጣሪ ጉባኤው ናቸው የተባሉት ነጥቦች የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔንና ሕጎቹን የተረጐመበት መንገድ ከሕገ መንግሥቱ አንጻር ሳይሆን ከፖሊሲ አማራጮች አንጻር የታየ መሆኑ መናገር ይቻላል። ለምሳሌ ቀደም ሲል እንደተገለጸው የትኛው የአተረጓጐም ዘዴ ኢንቨስትመንትን ሊስብ ይችላል የሚል ጥያቄ አንስቶ  የመተንተኑ ጉዳይ የሕገ መንግሥት ትርጉም ጉዳይ ሳይሆን የፖሊሲ አማራጭ ትንታኔ ነው።       

በሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔ ቅር የተሰኙ ተጠሪ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ስልጣኑን አለአግባብ በመተላለፍ ሕገ መንግሥትን በሚጥስ መልኩ ውሰኔ ሰጥቷል። በውሳኔውም ጥቅሜን ተጎድቷል በማለት ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባኤ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።  በሪፖርተር ጋዜጣ ዘገባ መሠረት የሰበር ሰሚ ችሎቱ ሕጎቹን አጥብቦ በመተርጉሙ ምክንያት ከሕገ መንግሥቱ የሚጻረር ትርጉም ሰጥቷል በማለት ጉዳዩ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል ብሎ ለፌደሬሽን ምክር ቤት  አስተያየቱን አቅርቧል። አጣሪ ጉባኤው የሰበር ሰሚ ችሎቱ ውሳኔ ሲተች፤ ችሎቱ የንግድ ምልክት ጥበቃ ሕጉም ሆነ ሌሎች ተዛማጅ ሕጎቹ መተርጎም የነበረበት አስፍቶ እና የኢኮኖሚ ልማትን ለማረገጋጥ፣  አዳዲስ የውጭ ኢንቨስትመንትን ለማስፋፋት በሚያስችል መልኩ እና ተጨማሪ የሥራ መስኮች እንዲፈጠሩ በሚያስችልና ለኢንቨስትመንት ሰፊ እድል በሚሰጥ መልኩ ነበር። ነግር ግን  ሕጎቹን በጠባቡ በመተርጐሙ ከሕገ መንግሥት ጋር ተቃርኗል ብሎም ተችቷል።  ከሪፖረተር ዘገባ ለመረዳት እንደተቻለው የአጣሪ ጉባኤው አመክንዮ በአእምሮ ንብረት ጽሕፈት ቤቱ ተወስኖ በከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ለጸናው ውሳኔ መነሻ ከነበረው የኢኮኖሚ ጥቅምና ኢንቨስትመንት ማበረታት አመክንዮ ጋር ይመሳሰላል።  

ቀደም ሲል እንደተገለጸው በሰበር ሰሚ ችሎት ብሎም በፌደሬሽን ምክር ቤት የሚወሰነው ውሳኔ በክርከሩ ሂደት በቀጥታ የተሳተፉ ወገኖች ብቻ ሳይሆን ሁሉም ዜጎች ይልቁንም በዘርፉ የተሰማሩትን ባለሃብቶችና ተጠቃሚዎችን የሚመለከት ስለሆነ ጉዳዩ ከፍ ባለ ጥንቃቄ መታየት እንዳለበት አያከራክርም። የሕገ መንግሥት ትርጉም ሲባል ከወቅታዊ የኢንቨስትመንት ፍላጎት ወይም የውጭ ሃብት ከመሳብ አንጻር ይታይ ከተባለ መንግሥት እንደየወቅቱና አስፈላጊነቱ የፖሊሲ ለውጦች ባደረገ ቁጥር የሕገ መንግሥት ትርጉምም ሊቀያይር ይችላል ማለት ነው። ይህ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ የበላይ ሆኖ ፖሊሲዎችን መግራት ሲገባው በወቅታዊ የፖሊሲ አማራጮች የሚገራ ያደርገዋል። ስለሆነም ሕገ መንግሥት ከወቅታዊ ፖሊሲዎቹና ፍላጎቶች በላይ መሆኑ፤ ይልቁንም ወቅታዊ ፖሊሲዎችና አማራጭ ኢንቨስትመንቶች በሕገ መንግሥቱ ማእቀፍ ስር መታየት እንዳለባቸው ሊመሠረት ይገባል። ከአእምሮ ንብረት ጋር በተያያዘ ሃገራት እንደየወቅታዊ የሃገራቸው ፍላጎትና እድገታቸው  ጥብቅ ወይም ለቀቀተኛ ፖሊሲን መከተል የተለመደ ነው። አንዳንድ ሃገራት ፈጠራን ለማነቃቃት ጥብቅ የአእመሮ ንብረት ጥበቃ ሕግ ያስፈልጋል ብለው የሚያምኑ ሌሎች ደግሞ የለም የአእመሮ ንብረት ጥበቃው ለቀቅ ሲደረግ ፈጠራ ይበረታታል ብለው የሚያምኑም አሉ። ዞሮ ዞሮ የሁለቱም ዓላማ አንድ ሲሆን፤ እንደዚህ ዓይነት ክርክር የፖሊሲ ክርክር እንጂ የሕገ መንግሥት ክርክሮች ሊሆኑ አይችሉም። በመሆኑም በሃገራችን ከአእምሮ ንብረት ጥበቃ ጋር በተያያዘ የሚኖረው አተረጓጐም የላላ ይሁን ወይስ የጠበቀ የሚል መወሰን ያለበት በሕገ መንግሥት ትርጉም  ሳይሆን በአስፈጻሚውና ሕግ አውጪው ነው። የፍርድ ቤት የሕግ አጥብቦ ወይም አስፈቶ መተርጎም ሕገ መንግሥትን ይቃረናል ማለት አላስፈለጊ ዝርዝር ውስጥ መግባት ነው።  ለመሆኑ አጥበቦ መተርጎም ከሕገ መንግሥቱ ጋር ይቃረናል ከተባለና ውሳኔው ከተቀለበሰ የአስፍቶ መተርጐም ሂደቱ ማለቂያው የት ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል። የመስፋትና መጥበብ ርቀቱስ ምን ያህል ነው? ለምሳሌ የፌደሬሽኑ ምክር ቤት የሰበር ሰሚ ችሎቱ  ውሳኔን ከቀለበሰው፤ ውሳኔው በተቀለበሰ ማግስት ሌላ በተመሳሳይ ቢዝነስና ስም ለመሰማራት የተሻለ ካፒታል ይዞ የሚመጣ ቢኖርስ?  አንድ ባለሃብት የተሻለ ሃብት ይዤ ስለመጣሁ፣ የተሻለ የሥራ እድል እፍጥራለሁና የሌላ ሰው የንግድ ምልክት ተነጥቆ  ይሰጠኝ ቢልስ? በዚህ ሂደት ማን ዋስትና ሊኖረው ይችላል? በመሠረቱ አንድ የንግድ ምልክት አንድ ዓይነት ነው ወይስ አይደለም፣ ይመሳሳላል ወይስ አይመሳሰልም፣ የሚሉት ጥያቄዎች የፍሬ ነገር ጥያቄዎች እንጂ የሕግ ይባስ ብሎ ደግሞ የሕገ መንግሥት ጥያቄዎች ሊሆኑ እንዴት ይችላሉ? በእኔ አስተያየት የንግድ ምልክቶቹ አይመሳሰሉም ወይም መሳከርን ሊፈጥሩ አይችሉም የሚል ክርክር ካለ በባለሙያ ትንተና የሚፈታ የፍሬ ነገር (Fact) ጉዳይ እንጂ የሕገ መንግሥት ጉዳይ ሊሆን አይችልም።    

ለማጠቃለል ያህል የአእምሮ  ንብረት ጥበቃ መብቶች በሰፊ ወይም ልል መሆን አለባቸው የሚለው ከርክርና ለየትኞቹ ባለሀብቶች ቅድሚያ ይሰጥ የሚለው ክርክር የፖሊሲና የአዋጭነት ክርክር እንጂ የሕገ መንግሥት ክርክር ሊሆን አይችልም። እንዲህ ዓይነት ጉዳዮች ወደ ሕገ መንግሥታዊ ክርክር የሚመጡ ከሆነ እያንድንዱ የፍርድ ቤት ውሳኔም ሆነ የአስተዳደር ውሳኔ ሕገ መንግሥታዊ ክርክር የማይሆንበት ምክንያት የለም። እንዲህ ዓይነት ነገር ደግሞ ዞሮ ዞሮ መንግሥትን ሽባ የሚያደርግና የፖሊሲ ምርጫ ነጻነትን የሚገፋ ነው የሚሆነው። መንግሥት ኢንቨስትመንትን ለማበረታት በርካታ እድሎችን ፈጥሯል። ወዲፊትም እንደሁኔታው ምቹና ሳቢ ሁኔታዎችን ይፈጥራል ተብሎ ይታመናል። ቀዳሚነት ያለውንና በሕግ ጥበቃው የጸና የንግድ ምልክትን በመንጠቅ ወይም ደግሞ በመስጠት ኢንቨስተመንት አበረታታለሁ  የሚል  አመክንዮ ግን አዋጪና ዘላቂነት ያለው ሊሆን አይችልም። ከዚያ አልፎም የቀዳሚነት መብት ያገኙትን ባለሃብቶችና የፈጠራ ሰዎችን መልካም ስምና ዝና በመጉዳት ለወደፊት ባለህብቶንና የፈጠራ ሰዎችን ማበራታት አይቻልም። የእእምሮ ንበረትና የንግድ ምልክት መብቶችን አጥብቦ ውይም አስፍቶ የመተርጐሙ ጉዳይ  የሕገ መንግሥት ጉዳይ ካለመሆኑም ባሻገር በዘርፉ የተሰማሩትን ብሎም ወደፊት ሊመጡ የሚችሉትን ባለሃብቶችና የፈጠራ ሰዎችን ሊያደካም የሚችል መሆኑ ለመገንዘብ የሚከብድ አይደለም። የፌደሬሽን ምክር ቤት የሰበር ሰሚ ችሎት ውሳኔውን ከቀለበሰው  በንግድ ምልክት መብት ላይ ብቻ ሳይሆን በአጠቀላይ በአእምሮ ንብረት ጥበቃ ፖለሲ ላይ የሚኖረው አንድምታ በጣም ትልቅ ስለሆነ ጉዳዩ ከተካራከሪ ግለ ሰቦች በላይ የሆነ ጉዳይ እንደሆነ ታምኖ በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል። 

የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ ካየሁ በኋላ በዚህ ጉዳይ ላይ በሌላ አስተያየት እመለሳለሁ። 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሦስተኛ ወገኖች መብትና የግልግል ሂደት
የባንክ ዋስትና ሰነዶች (Letter of Guarantees) በኢትዮጵያ ሕግ ያላ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 14 December 2024