Font size: +
10 minutes reading time (1941 words)

የባንክ ዋስትና ሰነዶች (Letter of Guarantees) በኢትዮጵያ ሕግ ያላቸው ሽፋን

የዋስትና ሰነዶች ባንኮች በተለይም ለደንበኞቻቸው ከሚሰጧቸው የብድር አገልግሎቶች መካከል ዋነኞቹ ናቸው። የዋስትና ሰነዶች በተለያዩ ስያሜዎች የሚጠሩ ሲሆን በዚህም መሠረት በእንግሊዝኛ ‘independent undertakings’, ‘performance bonds/guarantees’, ‘tender bonds/guarantees’, ‘independent (bank) guarantees’, ‘demand guarantees’, ‘first demand guarantees’, ‘bank guarantees’, and ‘default undertakings’ በሚሉ ስሞች ሊጠሩ ይችላሉ። ከዚህ በተጨማሪም እነዚሁ ሰነዶች ‘standby Letters of Credit’ ተብለው ሊጠሩ እንደሚችሉ የተለያዩ ጽሑፎች ያሳያሉ። በዚህ መጽሐፍ ውስጥም የዋስትና ሰነዶች የሚለው ጥቅል ስያሜን ለመጠቀም የተሞከረ ሲሆን አንዳንዶቹ ስያሜዎችም የዋስትና ዓይነቶችን የሚያመለክቱ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። የዋስትና ሰነዶች በባንኮች የሚሰጡት ደንበኞች የተለያዩ ስምምነቶችን ከሌሎች ሦስተኛ ወገኞች ጋር ፈጽመው ያለባቸውን ግዴታ በአግባቡ ለመወጣታቸው ከባንኮች ዋስትና እንዲሰጥላቸው በሚያቀርቡት ጥያቄ መሠረት ነው። የዋስትና ደብዳቤ የሚሰጠውም አንድን ሰው የብድር አገልግሎት ወይም እቃዎቸንና አገልግሎቶችን ለሌላ ሦስተኛ ወገን በብቃት እንዲያቀርብ መተማመኛ በመሆን ነው። ዋስትና ሰነድም አንድ ሰው አንድን የተለየና የተወሰነ ሥራ ለሌላ ሰው ለመሥራት ግዴታ ከገባ ይኸው ሰው በውሉ መሠረት የገባውን ግዴታ መፈጸም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላው ሰው የሚያቀርበው ውል ነው። (የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት የሰበር መዝገብ ቁጥር 47004 ተመልከቱ) የዋስትና ሰነዶች የባንክ የብድር ዓይነቶች ወይም የብድር አገልግሎት መሆናቸውን ከማየታችን በፊት ግን የዋስትና ሰነዶች ምን ማለት እንደሆኑ ማየቱ ተገቢነት ይኖረዋል።

የዋስትና ደብዳቤ አንድ ደንበኛ የፈለገውን የንግድ እንቅስቃሴዎችና ግንኙነቶችን እንዲፈጽም ለማስቻል ደንበኛው ለአቅራቢው ወይም የአገልግሎት ተግባር ለመፈጸም የተዋዋለውን ደንበኛ ሥራውን እንዲያከናውን ለማስቻል የሚሰጥ ደብዳቤ ሲሆን የዋስትና ደብዳቤውን የሚያዘጋጀው ባንክም ሰነዱ የተዘጋጀለት ደንበኛ ግዴታውን መወጣት ባይችል ለተጠቃሚው በቀጥታ ግዴታውን እንደሚወጣ በማረጋገጥ  የሚዘጋጅ ነው። የዋስትና ሰነዶችን በተመለከተ የሕግ ሽፋን የሰጠው የተባበሩት መንግስታት ኮንቬንሽን (UN Convention on Independent Guarantees and Standby Letters of Credit) የዋስትና ደብዳቤ ምን ማለት እንደሆነ እና የዋስትና ደብዳቤ ዓይነቶችንም ለመዘርዘር ሞክሯል። በዚሁ አለም አቀፍ ሕግ መሠረትም የዋስትና ደብዳቤ በአዘጋጁ (በብዛት ባንኮች ሲሆኑ) ደብዳቤው ለተዘጋጀለት ተጠቃሚ ዋስትና የተገባለት ግዴታ በባለዕዳው የማይከፈል ቢሆን የዋስትና ደብዳቤውን የጻፉት ባንኮች ባለዕዳውን ተክተው ክፍያውን (ዕዳውን) ለመክፈል ዋስትና እንደሚሆኑ በመግለጽ የሚሰጥ ደብዳቤ ነው። ይሁንና ይህ ኮንቬንሽን የሚያገለግለው አለም አቀፍ የሆኑ ግብይቶችን በተመለከተ እንደሆነ ተገልጿል። ኮንቬንሽኑንም የፈረሙት ሀገሮች ጥቂት በመሆናቸው ሁሉም ሀገሮች በዚህ ስምምነት መሠረት ይዳኛሉ ባይባልም አብዛኛው ሀገራት ግን የዋስትና ሰነዶችን በተመለከተ በሚያወጧቸው ሕጎች የዚህን ስምምነት አንቀጾች ከግንዛቤ በመክተት ሊሆን ይችላል። ኮንቬንሽኑ በተለይም የተለያዩ ዓይነት የዋስትና ደብዳቤ ዓይነቶች እንዳሉ ደንግጓል።

በኢትዮጵያ ሕግ ከዋስትና ሰነዶች ጋር በተያያዘ መነሳትና መዳሰስ ካለበት ዋና ነጥቦች መካከል የዋስትና ደብዳቤ ምን ማለት እንደሆነ፤ የዋስትና ደብዳቤ ምን ምን ነገሮችን ማካተት እንዳለበት፤ የዋስትና ደብዳቤዎች ያላቸው ሕጋዊ አስገዳጅነት፤ የዋስትና ሰነዶች ከሌሎች የዋስትና ዓይነቶች (እንደ ሰው ዋስትና እና የንብረት ዋስትና) ጋር ያላቸው አንድነት እና ልዩነት፤ እንዲሁም የዋስትና ሰነዶች እየተሰራባቸው ካለው ልማዳዊ አሰራር መነሻ ያደረገ ሌላ ሕግ አስፈላጊነት እና የመሳሰሉት ነጥቦች መብራራት ያለባቸው ናቸው።

ዋስትና የገንዘብ፣ የሰው እንዲሁም የንብረት እና የሰነድ ዋስትና ሊሆን ይችላል። እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች ግን በየራሳቸው ልዩነት ያላቸው ሲሆን ሁሉንም በተመሳሳይ መልኩ ትርጉም በመስጠት ወይም አንዱን በአንዱ እያቀያየርን መጠቀም በመደረታዊነት ያሉትን የተለያዩ የዋስትና ዓይነቶች እና ያላቸውን ጠቀሜታ የሚያጠፋ ይሆናል። በዋናነት በንብረት፤ በሰው እና በሰነድ ዋስትና መካከል ያለውን ልዩነት ለመገንዘብ የፍትሐብሔር ሕጉን ድንጋጌዎች መመልከት ያስፈልጋል።

የፍትሐብሔር ሕጉ የሰው ዋስትናን (Suretyships or Guaranteership) በተመለከተ ከአንቀጽ 1920 እስከ 1951 ድረስ ባሉት ድንጋጌዎች ሰፊ ሽፋን ሰጥቷል። እነዚህ የሕጉ ድንጋጌዎች ግን የሚገለጹት ስለ ሰው ዋስትና ሲሆን በዚህም መሠረት ግለሰቦች ራሳቸውን ለአንድ ብድር ዋስትና አከፋፈል ባለዕዳው በገባው ውል መሠረት ግዴታውን መፈጸም እንዲችል ለማረጋገጥ የሚሰጡት ዋስትና ነው። በፍትሐብሔር ሕጉ ላይ የተገለጹት ዋስትናን የተመለከቱት ድንጋጌዎች ከውል ሕግ ጋር የሚያያዙ በመሆናቸው የባንክ የብድር ግንኙነቶችን አስመልክቶ በባንክ የሚዘጋጁትን የዋስትና ደብዳቤዎችን የማይወክሉና የማይመለከቱ ናቸው። በባንክ የሚዘጋጁት የዋስትና ደብዳቤዎች በባንኮች ከመዘጋጀታቸው በፊት ዋስትና ደብዳቤው እንዲዘጋጅለት የጠየቀው ደንበኛ የዋስትና ደብዳቤውን ከማግኘቱ በፊት ለደብዳቤው መሠረት የሆኑ ሁለት ዓይነት የተለያዩ እና በራሳቸው የቆሙ ውሎችን ይዋዋላል። አንደኛው ውል የዋስትና ደብዳቤው እንዲዘጋጅለት የጠየቀው ሰው ሊፈጽመው የገባው የአገልግሎት ወይም የአቅርቦት ወይም ሌላ ግዴታን የተመለከተና ከሦስተኛ ወገን ጋር የሚገባው ውል ነው። ሁለተኛው ውል ደግሞ የዋስትና ደብዳቤውን ከባንክ እንዲፈቀድለት የሚጠይቀው ሰው ከባንኩ ጋር የሚገባው ውል ነው። ይህ ውል የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት ጥያቄ ያቀረበው ሰው ደብዳቤው በባንኩ እንዲጻፍለት ባንኩ የሚጠይቀውን ዓይነት ዋስትና ማለትም የንብረት ወይም የጥሬ ገንዘብ ዋስትና በማቅረብ የሚዋዋለው የመያዣ ውል ነው። እነዚህ ሁለት ውሎችም እርስ በእርሳቸው የማይገናኙ እና በራሳቸው የቆሙ ናቸው ማለት ይቻላል። የዋስትና ደብዳቤው ደግሞ ከእነዚህ ውሎች በኋላ በባንኮች የሚሰጥ የዋስትና ሰነድ ሲሆን ይህንን በባንኮች ተዘጋጅቶ ለባለእዳው የሚሰጠውን ደብዳቤ ግን እንደ ውል ልንቆጥረው የምንችለው ሳይሆን በቅድሚያ ባንኮች እና የዋስትና ሰነዱን የጠየቀው ሰው በገቡት የመያዣ ውል አማካኝነት የሚዘጋጅ ደብዳቤ እንደሆነ የሚቆጠር ነው።  

በመሆኑም የዋስትና ደብዳቤው የሚዘጋጀው በባንኮች በመሆኑና በደብዳቤው ላይ የሚፈርመውም የሚያዘጋጀው ባንክ ብቻ በመሆኑና የዋስትና ደብዳቤው ላይ ዋስትና የተገባለት ሰውም ፊርማውን የማያኖር ሲሆን በደብዳቤው ላይም የምስክሮች ፊርማም ሆነ ስም በአብዛኛው አይቀመጥም። በመሆኑም ይህ ሁኔታ የሚያሳየው ደብዳቤውን ውል ለማለት የውል መሠረታዊ ሁኔታዎችን ያላሟላ መሆኑን ሲሆን ውል ነው የምንል ቢሆን እንኳን ከራስ ጋር የተደረገ ውል እንደሆነ ከመቆጠር ውጪ ሌሎች ውሎች የሚያሟሉትን ነጥቦች የሚያሟላ አይደለም። በዚህም መሠረት የዋስትና ደብዳቤን ለማዘጋጀት በአብዛኛው የሚቀርበው የመያዣ ንብረት በመሆኑና የሰው ዋስትና በፍትሐብሔር ሕጉ በተቀመጠው መሠረት የዋስትና ደብዳቤ ለመጻፍ እንደመያዣ የማይቀርብ በመሆኑ በሰው ዋስትናና በሰነዶች ዋስትና መካከል መሠረታዊና ሰፊ ልዩነት እንዳለ መገንዘብ ያስፈልጋል ማለት ነው። በመሆኑም ይህ የዋስትና አገልግሎት በዋናነት ሰውን እንደዋስትና ወይም እንደ መያዣ ማቅረብን የሚመለከት አይደለም። ለዚህም ይመስላል የፍትሐብሔር ሕጉ ራሱ የሰው ዋስትናን እንደ አንድ የዋስትና ዓይነት በዘረዘረበት የሕጉ ድንጋጌዎች አሁን ባንኮች የሚጠቀሙባቸውን የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና፣ የውል ማስከበሪያ ዋስትና፣ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና ደብዳቤዎችንና ሌሎችንም የተለያዩ ቅድመ ሁኔታዎችን መሠረት አድርገው እና ለተለያዩ ዓላማ የሚውሉትን የዋስትና ዓይነቶችም ቢሆን ለመዘርዘር ያልቻለው።

በሀገራችን በተለይም እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች በአለም አቀፍ ደረጃም በተገባር ላይ መዋል የጀመሩትና ይህ ልማድም ወደ ሀገራችን ገብቶ በባንኮች መተግበር የጀመረውም የንግድ ሕጉና የፍትሐብሔር ሕጉ ከወጡ በኋላ በመሆኑ የዋስትና ሰነዶን በተመለከተ የፍትሐብሔር ሕጉን መሠረት በማድረግ የሚሰጡ የፍርድ ቤት ውሳኔዎችም ሆነ የሕግ ትርጉሞች በመሠረታዊነት እነዚህ በባንኮች በአገልግሎት ላይ የሚውሉ የዋስትና ሰነድ ዓይነቶችን የማይወክሉ የሚሆኑት። በአለም አቀፍ ደረጃም ቢሆን የዋስትና ሰነዶችን በተለይም (Independent Letter of Guarantees)  በተመለከተ በኮድ መልክ የወጣውና በአብዛኛው ሀገሮችና ተቋማት አገልግሎት ላይ የሚውለው URDG 458 የሚባለው ሰነድ ሲሆን ሰነዱም ከጥቂት አመታት በኋላ URDG 758 በሚል ተሻሻሎ ቀርቧል። ስለዚህም የዋስትና ሰነዶች ታሪካዊ አመጣጥና በተግባር አገልግሎት ላይ መዋል የጀመሩትም የኢትዮጵያ የፍትሐብሔርና የንግድ ሕግ ከወጡ በኋላ መሆኑን መገንዘብ ይቻላል።

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰበር መዝገብ 47004 በተሰጠ አስገዳጅ የሕግ ውሳኔ መሠረት የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና ውል በፍትሐብሔር ሕግ ድንጋጌዎች መሠረት የሚገዛ መሆኑን ገልጿል። ሰበር ችሎቱ በርካታ ትንታኔዎችን በጉዳዩ ላይ ለመስጠት የተጓዘበት ርቀት ጥሩ የሚባል ቢሆንም በመሠረታዊነት ግን ውሳኔው ሁሉንም የሕግ ባለሙያ ሊያስማማ የሚችል አይመስልም። ለዚህም ዋነኛ ምክንያቱ በውሳኔው ላይ የዋስትና ሰነድን የዋስትና ውል ሲል የገለጸው ሲሆን ከላይ በተመለከትነው መሠረት ግን ሰነዱ በባንኮች ተዘጋጅቶ የዋስትና ተጠቃሚውም ሆነ አበዳሪው በዚህ ሰነድ ላይ ምንም ዓይነት የስምምነት ፊርማ ሳያስቀምጡ፤ እንደሌሎች ውሎችም ምስክሮች መኖርም ሆነ መፈረም ሳያስፈልጋቸው በባንኮቹ ብቻ ተፈርመው ለዋስትና ተጠቃሚው የሚሰጡ ሰነዶች ናቸው።

በመሆኑም በዚህ ሰነድ ላይ እንደውል ለመቆጠር ቢያንስ ሁለት ወገኖች በውሉ ስለመስማማታቸው በጽሑፍ በሆነ ሰነድ ላይ መፈረምና ምስክሮችም ስማቸውንና ፊርማቸውን ማስቀመጥ እንደሚገባቸው የውል ሕግ እያስገደደ እነዚህ ነጥቦች ባልተሟሉበት ሁኔታ ሰነዱን ውል ማለት መሠረታዊ የውል መርህን የሚጥስ ነው። ሌላው የሰበር ትንታኔው የዋስትና ውል ብሎ የጠራውን ሰነድ በፍትሐብሔር ሕጋችን አንቀጽ 1920 እስከ 1951 የተቀመጠ መሆኑን በመጥቀስ የዋስትና ውል በችሮታ ላይ የተመሠረተ ግዴታ መሆኑን በመግለጽ ዋሱ ዋስ በመሆኑ የሚያገኘው ጥቅም የሌለ በመሆኑ አንድ ሰው ባለእዳው ሳይጠይቅ ወይም ሳያውቅ ዋስ መሆን እንደሚችል መመልከቱ ግንኙነቱ የግድ ጥቅም ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን የሚያሳይ ነው በሚል ያስቀመጠው ነው። (የፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 921ን ይመልከቱ) ይህ ትንታኔም በአንድ በኩል የሰው ዋስትናን ከሰነድ ዋስትና ጋር ለማመሳሰል የተደረገ ይመስላል። ይሁንና ስለሰው ዋስትና የተቀመጠው ይህ ትንታኔ በምንም መልኩ የሰነድ ዋስትናን የሚወክል አይደለም። ምክንያቱ ደግሞ በባንኮችም ሆነ በኢንሹራንስ ድርጅቶች የሚሰጡ የሰነድ ዋስትናዎች እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ በችሮታ የሚሰጡ ሳይሆን በተለይ ባንኮች የሰነድ ዋስትናዎችን ለመጻፍ ከተጠቃሚው ጋር የንብረት ወይም የገንዘብ መያዣ ውል የሚገቡ ሲሆን የዋስትና ሰነዶቹንም ለተጠቃሚው የሚጽፉት የዋሰትና መጠኑን መሠረት አድርገው በሚቀበሉት የገንዘብ ኮሚሽን እንጂ በችሮታ አለመሆኑ ነው።

ችሮታም የሰው ዋስትና መሠረታዊ መለያ ባህሪ እንጂ ለሰነዶች ዋስትና የሚሰራ ጉዳይ አይደለም። የሰነድ ዋስትና ለመጻፍም ባለእዳው ሳያውቅ መጻፍ የማይቻል ሲሆን የሰነድ ዋስትናን ለመጻፍ የግዴታ ባለእዳው በአካል ቀርቦ ለባንኩ ማመልቻ ማስገባትና ለሰነዱ መጻፍ መሠረት የሆነውን የመያዣ ውል መዋዋል ግድ የሚል ነው። በመሆኑም የሰነድ ዋስትና ለመስጠት የባለእዳው መቅረብና ስለዋስትናው ማወቅ የግድ ነው። በሌላ በኩል ከላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው የዋስትና ሰነድ የፍትሐብሔር ሕጉ ከወጣ በኋላ የመጣ ጽንሰ ሀሳብ በመሆኑ ይህንን ግዴታ ወደፍትሐብሔር ሕጉ ወስደን ትርጉም ለመስጠት መሞከሩ አግባብ ያልሆነ መሆኑ ነው። በመሆኑም የሰበር ችሎቱ የሰነድ ዋስትናን ከሰው ዋስትና ጋር ለማዛመድ የሞከረበት ትንታኔው ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ተቀባይነት ያለው አይመስልም።ይህ የሚያመለክተንም በመሠረቱ እነዚህ የዋስትና ዓይነቶች በልማድ ባንኮች በተግባር በሰፊው ይጠቀሙባቸው እንጂ አገልግሎታቸው ተለይቶ እንዴት እንደሚዘጋጁ እና በምን ሕግ እንደሚገዙም የሚገልጽ ግልጽ የሕግ ደንጋጌ አሁን ባሉት የንግድ ሕግም ሆነ በፍትሐብሔር ሕግ ውስጥ የሌለ መሆኑን ነው።

የዋስትና ሰነዶች በሁኔታ ላይ የተመሠረቱና በሁኔታ ላይ ያልተመሠረቱ ሊሆኑ ይችላሉ። በሁኔታ ላይ የተመሠረተ ዋስትና የሚባለው ዋሱ ባለዕዳው ግዴታውን በማንኛውም ሁኔታ ሳይወጣ ቢቀር ግዴታውን ያልተወጣው በምንም ምክንያት ይሁን ምክንያቱን መጠየቅ ሳይጠበቅበት የተባለው ግዴታ እንዳልተፈጸመ በአበዳሪው ሲገለጽለት በዋስትና ደብዳቤው የጊዜ ገደብ ውስጥ መሆኑን በማረጋገጥ የሚከፈሉ የዋስትና ደብዳቤዎች ናቸው። በሁኔታ ላይ የተመሠረቱ የዋስትና ደብዳቤዎች ደግሞ ዋሱ ለአበዳሪው የዋስትና ግዴታውን ለመወጣት እንዲያስችለው ባለአዳው (ዋስትና የተገባለት ሰው) ግዴታውን ያልተወጣው በማን ጥፋት ነው የሚለውን ካረጋገጠ በኋላ እና ጥፋቱ የባለእዳው መሆኑ ከተረጋገጠ በኋላ የሚወጣው ግዴታ ነው።

ባንኮች በአሁኑ ወቅት እየሰጡዋቸው ካሉ የዋስትና ሰነድ ዓይነቶች ውስጥ የመልካም ሥራ አፈጻጸም ዋስትና፣ የጨረታ ማስከበሪያ ዋስትና፣ የውል ማስከበሪያ ዋስትና፣ የቅድመ ክፍያ ዋስትና፣ የአቅራቢነት ዋስትና ሰነዶች (ደብዳቤዎች) ናቸው። እነዚህ የዋስትና ሰነዶች በአብዛኛው ባንኮች ለደንበኞች የሚያዘጋጁላቸው ደንበኞች ለባንኮች በሚያቀርቡት የመያዣ ንብረቶች መሠረት የመያዣ ውል ከተዋዋሉ በኋላ ነው። አንዳንድ ጊዜ ግን የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት የጠየቀ የባንክ ደንበኛን ባንኮቹ ተመጣጣኝ የሆነ ገንዘብ በዝግ ሂሳብ እንዲያስቀምጡ በማድረግ በምትኩ ግዴታቸውን ለመወጣት መተማመኛ የሚሆኑ ሰነዶችን ይሰጣሉ። ይህ ዓይነቱ ዋስትና የገንዘብ ዋስትና ይባላል። በብሔራዊ ባንክ መመሪያ ቁጥር sib/24/2004 መሠረት የገንዘብ ዋስትና ሰነድ አንድ ሰው አንድን የተለየና የተወሰነ ሥራ ለሌላ ሰው ለመሥራት ግዴታ ከገባ ይኸው ሰው በውሉ መሠረት የገባውን ግዴታ መፈጸም የሚችል መሆኑን ለማረጋገጥ ሌላው ሰው የሚያቀርበው ውል ነው።

ባንኮችም የዋስትና ሰነድን ለደንበኞች በመስጠት የሚያገኙት ገቢ በወለድ መልክ ገንዘብን መቀበልንና የዋስትና ጊዜው ሲያልቅ የሚመለስ ገንዘብም በዋስትና ተጠቃሚው በኩል እንዲከፈል አይጠበቅም። በመሆኑም የዋስትና ሰነድ መጻፍ በተለምዶ የሚታወቀውን የአበዳሪና ተበዳሪ የብድር ግንኙነትን አይፈጥርም። ይልቁንም ባንኮቹ ለሚሰጡት የዋስትና ሰነድ የሚቀበሉት ተመጣጣኝ የሆነ ኮሚሽን ብቻ ነው። ይህ ሁኔታ ታዲያ በተለይ የዋስትና ሰነድ እንደ ብድር አገልግሎት የሚታይ አይደለም ለሚሉት ወገኖች እንደ አንድ መከራከሪያ ሀሳብ ይነሳል። ምክንያቱም የባንክ የብድር ግንኙነት የአበዳሪና የተበዳሪ ግንኙነትን ለመፍጠር አበዳሪው ለተበዳሪው በገንዘብ የሆነ ብድር የመስጠትንና ተበዳሪውም ይህንኑ የብድር ገንዘብ በዓይነትም ሆነ በጥሬው የመመለስ ግዴታን የሚጥል መሆኑ ግልጽ ነው።ይሁንና ግን የዋስትና ደብዳቤ ለዋስትና ተጠቃሚው ሲጻፍ ባንኮቹ የዋስትና ደብዳቤ እንዲጻፍለት የጠየቀውን ደንበኛቸው የገባውን ግዴታ እንዲፈጽም መተማመኛ ከመስጠት ባለፈ ለደንበኛቸው የሚሰጡት የብድር ገንዘብ የለም።

ሌላው  መነሳት ያለበት ጉዳይ ባንኮች በሚያዘጋጂዋቸው የዋስትና ደብዳቤዎች ላይ የሚጠቀሱ የሰነዱን ይዘቶች የተመለከቱት ነጥቦቸ ናቸው። በተግባር በባንኮች የሚዘጋጁት የዋስትና ሰነዶች የተለያዩ ቢሆኑም የሰነዶቹ ይዘት ግን አንዳንድ የሕግ ክርክሮችን ሲያስነሱ ይታያሉ።የአንዳንድ የዋስትና ደብዳቤዎች ይዘቶች በተለይም ዋስትና ሰጪውን ተቋም ሳይቀር ባለገንዘቡ የዋስትና ሰጪው እና ወራሾቹ በጋራም ሆነ በተናጠል በደብዳቤው በተቀመጡት ግዴታዎች መሠረት ራሳቸውን ህጋዊ ግዴታዎች ውስጥ ገብተዋል፤ የዋስትና ቦንዱም ለተጠቀሰው የገንዘብ መጠን በቦንዱ ውስጥ በሰፈሩት ህጋዊ ስምምነቶች እና ድንጋጌዎች መሠረት ሆኖ ይህንን ቦንድ ምንም ዓይነት ቅድመ ሁኔታ ሊቀርብበት የማይችል የሚያደርጉ ናቸው፤ ማንኛውም ድርጊት ወይም ሳይፈጸም የቀረ ነገር በመኖሩ ሳቢያ ኪሳራ የሚደርስ መሆኑን ዋስትና የተሰጠው ባለገንዘብ ከደረሰበት ይህንኑ በዋስትና ጊዜው ውስጥ ለዋሱ ማሳወቅ አለበት የሚሉና የመሳሰሉት ይገኙበታል። በመሠረቱ አንዳንዶቹ ግዴታዎች በልማድ የተጻፉ ከመሆናቸው ውጪ በተለይ የዋሱን ወራሾች ሁሉ ተጠያቂ የሚያደርጉት የዋስትና ግዴታዎች ባንኮችን በተመለከተ ሊፈጸሙ የሚችሉም ስላልሆኑ በአብዛኛው በሰነዶቹ ይዘት ላይም ጥንቃቄን ማድረግ ያስፈልጋል። የዋስትና ደብዳቤም በጊዜ ገደብ የተወሰነ ግዴታ ሲሆን ደብዳቤውም በግልጽ ዋስትና የተገባለትን የገንዘብ መጠን ማመልከት ይገባዋል።

እንደማጠቃለያም የዋስትና ውል ማለት ሁለት ሰዎች ባደረጉት የባለገንዘብነትና የባለእዳነት ግዴታ ግንኙነት ውስጥ ከእነዚህ ተዋዋዮች ውጪ የሆነ ሌላ ሦስተኛው ባለእዳው እዳውን በሙሉ ወይም በከፊል ያልተከፈለ መሆኑ ከተረጋገጠ ወይም ግዴታውን በውሉ በተመለከተው አኳኋን በአግባቡ ያልተወጣ ከሆነ እኔ በባለእዳው ስፍራና አቋም ሆኘ እዳውን እከፍላለሁ ወይም ግዴታውን እወጣለሁ ሲል ለባለገንዘቡ ማረጋገጫ የሚሰጥበት በሕግ አግባብ ከተረጋገጠ ከበስተጀርባው ለአፈጻጸሙ የሕግ ጥበቃ የሚያገኝ ውል ነው በማለት የፌደራል ሰበር ሰሚ ችሎት ማብራሪያ ሰጥቷል። ይሁንና ግን የዋስትና ሰነዶች ከአገልግሎታቸው አንጻር በህጋችን ላይ ግልጽና ሰፊ ሽፋን የተሰጣቸው አይደሉም። በተለይም በንግድ ሕጉን ውስጥ እነዚህ ሰነዶች እንደ ብድር አገልግሎት የሚቆጠሩ መሆንና አለመሆናቸውን በሚገልጽ መልኩ እንዲሁም የተለያዩ ዓይነት የዋስትና ደብዳቤዎችን አገልግሎት እና በምን ሁኔታ ሊጻፉ እንደሚችሉ በሚገልጽ መንገድ የተቀመጠ ግልጽ ድንጋጌ ያስፈልገናል። በመሆኑም የንግድ ሕጉ የዋስትና ደብዳቤዎችን የተመለከተ ሰፊ የሕግ ሽፋን መስጠትና ማካተት ይጠበቅበታል። ከዚህም ጋር ተያይዞ የዋስትና ሰነዶችን ልዩ ባህሪያትና በተግባር ያሉትን የባንኮችን አሰራሮች በመፈተሽ ዝርዝር የሕግ ድንጋጌ ማስቀመጡ አስፈላጊ ነው።

DOWNLOAD THIS ARTICLE WITH FULL CITATION HERE

ይህ ጽሑፍ በቅርቡ ‘የኢትዮጵያ የባንክ እና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ሕግ’ በሚል ካሳተምኩት መጽሐፍ ክፍል በከፊል የተቀነጨበ ነው። በመጽሐፉ ከባንክና ከሚተላለፉ የንግድ ሰነዶች ጋር ተያይዞ አዳዲስ የሕግ ጉዳዮችና የሕግ ትንታኔ የቀረበበት ነው። መጽሐፉን ማግኘት የሚፈልግ ማንኛውም ሰው መጽሐፉን ከጃፋር መጽሐፍት ማከፋፈያ (ለገሀር) እና ኤዞፕ መጽሐፍት መደብር (ፒያሳ ጊዮርጊስ አካባቢ) ማግኘት ይችላል።

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ሕግ መንግሥቱን በፖለሲ ማዕቀፍ ሥር?
DNA አባትነትን ማረጋገጫ ማስረጃ ስላለመሆኑ
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 10 October 2024