Font size: +
10 minutes reading time (2041 words)

DNA አባትነትን ማረጋገጫ ማስረጃ ስላለመሆኑ

ሁሉም ሰው ባዮሎጂካዊ አባት አለው ሁሉም ሰው ግን ህጋዊ አባት ላይኖረው ይችላል፡፡ ይህ አረፍተ ነገር በብዙዎቻችሁ ጭንቅላት እንዴ! የሚል ግርምት እንደሚያጭር እገምታለሁ፡፡ በተለይ ሁሉም ልጅ እኩል ነው ልጆች አባትና እናታቸውን የማወቅ ሕገ መንግሥታዊ መብት አላችሁ የሚለው አነጋገር አብዝቶ ከመሰማቱ የተነሳ በሕግ አባት የሌለው ልጅ ሊኖር ይችላል ብሎ መገመት ሩቅ ሊሆን ይችላል በቀጣዩ ጽሑፍ በመግቢዬ የገለፅኩት ሀሳብ ምን ያህል እውነት እንደሆነ ለማሳየት እታትራለሁ፡፡

በሕገ መንግሥቱ አንቀፅ 36(1)(ሐ) ላይ ለህፃናት ከተደነገጉላቸው መሠረታዊ መብቶች አንዱ ህፃናት እናት አባታቸውን የማወቅ የእነሱንም ክትትልና እንክብካቤ ማግኘት ነው፡፡ ታዲያ ይህ ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ ሊያገኝ የሚችለው በየክልሎቹ የቤተሰብ ሕግና በፌደራሉ የተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት ነው፡፡ ይሁን እንጂ በነዚህ የቤተሰብ ሕጎች ላይ ሁሉም ልጆች እናታቸውን እንጂ አባታቸውን ለማወቅ አልታደሉም የዚህ ጽሑፍ ማጠንጠኛም እነዚህ በሕግ አባታቸውን ለማወቅ ማወቅ አይደለም በሕግ አባት የሌላቸው ልጆች በእንዴት አይነት ሁኔታ የተወለዱ ልጆች ናቸው እጣፋንታቸውስ ምንድን ነው የሚለውን ሀሳብ መፈተሸ ነው፡፡ በተለይም ከእውነትነቱ ይልቅ በእምነትነቱ ይበልጥ የሚገለፀው የአባትንት ጥያቄ በቤተሰብ ሕጉ እንዴት ይመለሳል በተለይም ይህን ጥያቄ ከመመለስ ብኋላ የሚከተሉትን ሌሎች ይሕግ ጥያቄዎችን (ውርስ፣ቀለብ…) ባግባቡ ለበመልስ ይዚህ ጥያቄ ምላሽ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

በሕግ የአንድ ልጅ አባት ማነው?

እንግዲህ የአንድን ልጅ አባትና እናት ለማወቅ በመጀመሪያ መመልከት ያለብን በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ስለ እናትነትና አባትነት ስለማወቅ የተደነገገበትን የሕግ ክፍል በመመልከት ነው በዚህ የሕግ ክፍል መሠረት የአንድን ልጅ አባት በሶስት የተለያዩ መንገዶች ማወቅ ይቻላል፡፡

1.      አባትን በሕግ ግምት ማወቅ (አንቀጽ 126)

እውነቱ ምንም ይሁን በመጀመሪያ የአንድ ልጅ አባት ነው የሚባለው ልጁ በጋብቻ ውስጥ የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ ከሆነ ባልየው ነው፡፡ ልጁ በጋብቻ አብረው በማይኖሩ ይልቁንስ እንዲሁ ከጋብቻ ውጭ እንደባልና ሚስት አብረው በሚኖሩ ሰዎች ግንኙነት ውስጥ የተፀነሰ ወይም የተወለደ እንደሆነ የልጁ አባት የሚባለው በዚህ ግንኙነት ከእናትየዋ ጋር አብሮ የሚኖረው ሰውዬ ነው፡፡

2.     ልጅነት ስለመቀበል (አንቀጽ 131)

ሁል ጊዜም ቢሆን የአንድን ልጅ አባት በተ.ቁ 1 በተገለፀው መንገድ ማወቅ አይችልም በመሆኑም ልጅን በተ.ቁ 1 በተገለፀው የሕግ ግምት መነሻነት የልጁን አባት ማወቅ ያልተቻለ እንደሆነ በ2ተኛ ደረጃ የተቀመጠው መንገድ ልጁን ልጄ ነው ብሎ በሕጉ በተቀመጠው ስርኣት መሠረት የልጁን ልጅነት የሚቀበል ሰው የተገኘ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም መንገድ ሁልጊዜም ቢሆን ልጁ አካለ መጠን ያልደረሰ እንደሆነ የእናትየዋን ይሁንታ ልጁ አካለ መጠን ደርሶም እንደሆነ የልጁን ይሁንታ ወይም አምኖ መቀበል ይጠይቃል፡፡

3.     አባትን በፍርድ ስለማወቅ (አንቀፅ 143)

የመጨረሻው የአንድ ልጅ አባትነት የሚታወቀው በፍርድ ሲሆን ይሄው በሕጉ ተቆጥረውና ተለይተው በታወቁ 5 ምክንያቶች ብቻ ፍ/ቤት በሚሰጠው የፍርድ ውሳኔ አባት ሊታወቅ ይችላል፡፡ እነዚህ ምክንያቶችም 1ኛ እናቲቱ ልጁ በተፀነሰበት ጊዜ ተደፍራ ተጠልፋ ከሆነ 2ኛ አገባሻለሁ በሚል የተስፋ ቃል በተንኮል ድርጊት፣ ስልጣንን የያለአግባብ በመጠቀም ወይም በሌላ ተመሳሳይ መንገድ በእናቲቱ ላይ የማሳት ድርጊት ተፈፅሞባት ከሆነ 3ኛ አባት ነው የተባለው ሰው በማያሻማ ሁኔታ አባትነቱ የሚያረጋግጥ ደብዳቤ ወይም ሌሎች ፅሁፎች ትቶ እንደሆነ 4ኛ በሕግ የታወቀ ግንኙነት ሳይኖራቸው ለረዥም ጊዜ እናቲቱ ከአንድ ሰው ጋር ቀጣይነት ያለው የግብረ ሥጋ ግንኙነት ፈጽማ ከሆነ 5ኛ አባት ነው የተባለው ሰው ልጁን በመንከባከብ ወይም በማሳደግ ተግባር ላይ የተሳተፈ ከሆነ ለፍርድ ቤት በሚቀርብ ክስ አማካኝነት ከፍ ሲል ከተገለፁት ምክንያቶች የአንዱን ምክንያት መኖር በማስረጃ በማረጋግጥ የልጁ አባት በፍርድ እንዲታወቅ ማድረግ ይቻላል፡፡

ከዚህ ቀጥሎ የሚመጣው ጥያቄ ታዲያ በርግጥ ከፍ ሲል በተገለፁት ምክንያቶች ሁሉም ልጆች አባታቸውን ማወቅ ይችላሉ ወይም ለሁሉም ልጅ ከፍ ሲል በተቀመጡት መንገዶች አባት ሊገኝ ይችላል፡፡ እንግዲህ እዚህ ጋር ነው የጽሑፍ አርዕስት የሆነው አባት አልባው ልጅ የሚመጣው፡፡

 አባት አልባነት

በሕግ ከታወቁት ግንኙነት ውጪ ማለትም ከጋብቻ እና እንደ ባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ግንኙነት ውጭ ልጆች መወለዳቸው በብዛት የምንመለከተው አጋጣሚ ነው፡፡ ሁሉም ልጅ ልጄ ነው የኔ ነው የሚለው አባት እንደማያገኝም ግልፅ ነው፡፡ በሕጉ በፍ/ቤት ክስ መሠረት በፍርድ አባትን ለማወቅም ሕጉ ክስ ለማቅረብ በቂ ናቸው በማለት የፈቀዳቸውን ምክንያቶችንም ለይቶ እና በቁጥር በ5 ብቻ ወስኖ አስቀምጧቸዋል፡፡ አባትነትን ለማረጋገጥ ከፍ ሲል ከተገለፁት ምክንያቶች ውጭ አባትነት ሊረጋገጥ እንደማይችል ሕጉ አባትነት ማወቂያ መንገዶች በማለት መንገዶቹን በደረጃ ጭምር በዝርዝር ማስቀመጡ፤ እንዚህ ምክንያቶችም ብቸኛ መንገዶች መሆናቸውን የአንቀፆቹ አቀራረፅ በራሱ አስረጅ ሲሆን ይህም መንገዶቹን በሚሳዩት ድንጋጌዎች ስር "ከዚህ በላይ በተመለከተው ድንጋጌ የልጁ አባት ያልታወቀ እንደሆነ…" በሚል ሀረግ ስር ሶስቱም መንገዶች መቀመጣቸው በተለይም በቤተስብ ሕጉ አንቀፅ 145 ላይ አባትነት ከላይ ከተዘረዘሩ ምክንያቶች ውጭ በፍርድ ሊታወቅ አይችልም በማልት በግልፅ መደንገጉ ሲታይ ሕጉ አባትንት ማወቂያ ብሎ ከዘረዘራቸው ምክንያቶች ውጭ አባትንት ሊታወቅ የማይችል በተለይም አንዲት ሴት በሕግ ከሚታወቁት ግንኙነቶች ውጭ እንዲሁም በሕጉ ተዘርዝረው ከተቀመጡት አምስት ምክንቶች ውጭ አርግዛ ብትወልድ  ለምሳሌ ሳትደፈር፣ ሳትታለል፣ ቀጣይ የሆነ የግብረ ስጋ ግንኙነት ከአንድ ሰው ጋር ሳይኖራት፣ የልጁን አባት ማን እንደሆነ የሚያረጋግጡ ፅሁፎች ሳይኖሩ፣ ልጁ ከተወለደ በኋላም ልጁን በመንከባከብ በማሳደግ ተግባር ላይ የሚሳተፍ ሰው ሳይኖር ልጅ ቢወለድ ይህ ልጅ በሕግ አባት የሌለው ልጅ ሆነ ማለት ነው፡፡ ለዚህ አይነተኛ ምሳሌ ሊሆን የሚችለው እናቲቱ በአንድ ቀን የፍቅር ግንኙነት ወይም አዳር ውይም ቀጣይ ተብሎ በማይገለፅ ግንኙነት ከአንድ ሰው ጋር በፈፀመችው የግብረ ስጋ ግንኙነት ምክንያት የተወለደ ልጅ ከፍ ሲል በገለፅኳቸው መንገዶች አባቱ ሊታወቅ አይችልም፡፡ በመሆኑም ሕጉ ልክቶ አና ልይቶ ባስቀመጣቸው አባትን የማወቂያ መንገዶች  የዚህ ልጅ አባት አይታወቅም በመሆኑም በሕግ ከሚታወቁት መንገዶች ውጭ ምናልባትም በሳይንሳዊ የምርመራ ዘዴ የልጁ ባዮሎጅካል አባት ሊታወቅ ይችላል እንጅ የልጁ ህጋዊ አባት ሊታወቅ አይችልም በዚህ ግንኙነት የተወለደን ልጅ በተመለከተ  ህጋዊ አባት እንጂ ባዮሎጅካል አባት መሆን  ልጁን ከአባቱ ጋር አባትየውን ከልጁ ጋር በመብት እና በግዴታ ሊስተሳስር የማይችል በሕግ ፊት ትርጉም የሌለው ግንኙነት ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ግን ባዮሎጅካል አባት ህጋዊ አባት መሆን አይችልም እየተባለ ሳይሆን በዚህ ጉዳይ ባሎጅካል አባት መሆን ትርጉም የለውም ለማለት ብቻ ነው፤ ይህ አረፍተ ነገር እንዴት እውነት እንደሆነ በቀጣዩ አርአስት ስር ስለምነመለስበት ይበልጥ ግል     ፅ ይሆናል፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳ ባዮሎጂካዊ በሆነው መንገድ ልጁን ያስገኘ አባት ቢኖርም በሕግ ከልጁ ጋር በመብትና በግዴታ  የሚተሳሰር ህጋዊ አባት ግን አይኖርም፡፡ ለዚያ ነው ሁሉም ሰው ባዮሎጂካል አባት አለው ሁሉም ሰው ግን ህጋዊ አባት ላይኖረው ይችላል በሚል የተነሳ ነው፡፡

በተለይም በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 107(1) ላይ ልጁ በጉዲፈቻ አማካኝነት አባት ካለገኘ ወይም የልጁን ልጅነት የሚቀበል ሰው ከሌለ በስተቀር በሕግ ከታወቁት ማለትም ከጋብቻና እንደ ባልና ሚስት አብሮ ከመኖር ግንኙነቶች ውጪ ባለ በሕግ እውቅና ካልተሰጣቸው ግንኙነቶች የተወለዱ ልጆች ከእናታቸው ጋር ካልሆነ በስተቀር ከሌላ ሰው ጋር ማናቸውም አይነት ህጋዊ ግንኙነት አይኖራቸውም በማለት በግልፅ ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህ ድንጋጌ ልጆች ሁሉ እኩል ናቸው እናት እና አባታቸው የማወቅ የነሱንም እንክብካቤ የማግኝት መብት አላቸው ከሚለው የሕገምንግሰቱ አንቀፅ 36 አኳያ፣ የሁሉንም ልጆች መብት ከማሰከበር አኳያ እንዲሁም በቤተሰብ ሕጉ ውስጥ በተለይም በአንቀፅ 143 መሰረት አባትነት በሕግ ተለይተው የታወቁ ምክንያቶች በማለት በገለፅናቸው 5 መንገዶች  እንደሚረጋገጥ በተደነገገብት ሁኔታ ልጁ በሕግ ከታወቁት ግንኙነቶች (ጋብቻ እና እንደ ባልና ሚሲስት አብሮ ከመኖር) የተወለደ ካልሆነ በስተቀር ከእናቱ ጋር ብቻ እንጅ ከሌላ ሰው ጋር ህጋዊ ግንኑነት የለውም ማለቱ እራሱን በራሱ የሚቃራን፤ የድንጋጌውን ህጋዊ ውጤት ያላገናዘበ፤ ግብታዊነት የሚታይበት ቢያደርገውም ሕግ አውጭው ይህ ጉዳይ እንደተፈለገ ልቅ እናዳይሆን መፈለጉን ይልቁንስ ጉዳዩን አጥብቦና ወስኖ ማስቀምጥ መፈለጉን ያሳያል፡፡ (የዚህን አንቀጽ ተገቢነት እና ሕገ መንግሥታዊ መሠረት ያለው መሆኑ አለመሆኑ እንዲሁም በቤተሰብ ሕጉ ካሉ ሌሎች ድንጋጌዎች ጋር ያለውን መጣረስ በተመለከተ በዚሁ ዌብ ሳይት አንቀፁን በተመለከተ የፃፍኩት ትችት ብትመለከቱ ይበልጥ ደስ ይለኛል)   

"DNA" አባትነትን መካጃ እንጂ ማወቂያ ማስረጃ ስላለመሆኑ

DNA ወይም ሌላ አይንት የሳይንስ የምርምራ ውጤት ብዙ ጊዜ በሙያ አጋሮቼም ይሁን በፍርድ ቤቶች ልማድ የአንድን ሰው አባት ለማረጋገጥ እንደሚቀር ቅቡል ማስረጃ ሲቆጠር እመለከታለሁ፡፡ በዚሁ ፅሁፍ አቅራቢ እምነት ግን DNA አንድ ሰው የልጁ አባት አይደለም ለማለት የሚቀርብ ማስተባባያ ማስረጃ እንጂ ሰውዬው የልጁ አባት ነው ለማለት የሚቀርብ ማረጋገጫ ማስረጃ አይደለም፡፡ ይህም እንዴት ትክክል እንደሆነ ለማሳየት የተወሰኑ ሐሳቦችን መሰንዘር ያስፈልጋል፡፡

ከፍ ሲል አባትነትን ማወቂያ መንገዶች በሚለው ርእስ ስር በተገለፀው ሀሳብ መሠረት በሕጉ የአንድን ልጅ አባትነት ለማወቅ የተቀመጡ መንገዶች ሶስት ናቸው፡፡ከእነዚህ አማራጮች ውጭ በሕግ የአንድ ልጅ አባትነት ሊታወቅ የሚችልበት እድል የለም ሕጉ ከነዚህ ሶስት መንገዶች ውጪ አባትነት ሊታወቅ እንደማይችል ይበልጥ ሲያረጋግጥ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ አንቀፅ 145 ላይ በተለይም በሕግ ግምትና ልጅነት የሚቀበል  አባት ካላተገኘ በስተቀር ከፍ ሲል ከተገለፁት ምክንያቶች ውጪ አባትነት በፍርድ ሊታወቅ እንደማይችል በግልፅ ደንግጎ ይገኛል፡፡ ይህ ማለት ደግሞ በሕጉ ተለይተው የተቀመጡ ምክንያቶች መኖራቸውን በማስረጃ በማረጋገጥ አባትነት በፍርድ ይታወቃል እንጂ ከነዚህ ምክንያቶች ውጪ እንዲሁም በDNA ምርመራ አባት መሆኑ ይረጋገጥልኝ በማለት አባትነት በፍርድ ሊታወቅ አይችልም፡፡ እነዚህ በሕግ የታወቁ  5 ምክንያቶች ሲኖሩ አባት የሚታወቀው ደግሞ እነዚህ ምክያቶች መኖራቸውን በሌላ ማስረጃ በማረጋገጥ እንጂ እነዚህ ምክንያቶች በሌሉበት የDNA ማስረጃ በማቅረብ ወይም እንዲቀርብ በመጠየቅ ሊረጋገጥ አይችልም፡፡ ይልቁንስ የDNA ፅንሰ ሀሳብ በቤተሰብ ሕጉ ሊካተት የቻለው እና በማስረጃነት ተቀባይነት እንዳለው የተገለፀው በሕግ እውቅና የተሰጣቸው ምክንያቶች በመኖራቸው ወይም በነዚህ ምክንያቶች መነሻነት አባትነት በፍርድ እንዲረጋገጥ  ክስ በመቅረቡ ክሱ የቀረበብት ሰው የተባሉት ምክንያቶች ቢኖሩም እሱ ግን የልጁ አባት አለመሆኑን ለማስረዳት ወይም ለማስተባበል የሚቀርበው የማስረጃ አይነት ነው፡፡ ይህ ስለመሆኑ በሕጉ አንቀፅ 144/ሀ/እና/ሐ/ ላይ ሰውየው የልጁ አባት ላለመሆኑ ከተረጋገጠ ወይም አባት ነው የተብለውና ክስ የቀረበበት ሰው በደም ምርመራ ወይም በሌላ አስተማማኝ የህክምና ዘዴ የልጁ አባት ሊሆን የማይችል መሆኑ ሲረጋገጥ በፍርድ ቤት የልጁ አባትነት ይታወቅልኝ በሚል የቀረበው ክስ ተቀባይነት አያገኝም በማለት ግልፅ በሆነ ቋንቋ አስቀምጧል፡፡

በተጨማሪም በፍርድ አባትነት እንዲታወቅ ከሚቀርቡት 5ቱ ምክንያቶች በፍርድ ቤት ክስ በመቅረቡ ብቻ ሳይሆን በሕጉ ግምት አባት ነህ በተባለ ሰውም ቢሆን ማለትም በፀና ጋብቻ ውስጥ ያለ ባል ወይም እንደባልና ሚስት አብሮ በመኖረ ግንኙነት ውስጥ ያለ ሰው ምንም እንኳ በዚህ ግንኙነት ውስጥ እያሉ የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ የሱ ነው የሚል የሕግ ግምት ቢኖርም ይህ ሰው ይህ በግንኙነት መሀል የተወለደ ልጅ የኔ አይደለም ብሎ ካመነ ለፍርድ ቤት የመካድ ክስ የማቅረብ ይህን በሕጉ የተያዘ ግምት ማስባበል ይችላል ይህ የሕግ ግምት ከሚስተባበልባቸው መንገዶች ውስጥ አንዱና መሠረታዊው የማያጠራጥር ማስረጃ ደግሞ DNA ነው ማለት ይቻላል ይህም ስለመሆን በቤተሰብ ሕጉ አንቀፅ 167 እና ተከታዮቹ የተቀመጡት ድንጋጌዎች ገፅ ንባብ ዋቢ ናቸው፡፡ ምንም እንኳ የመካድ ክስ እንዲሁ በዘፈቀደ የሚቀርብ ክስ ባይሆንም አሳማኝ ምክንያቶች መኖራቸውን ፍረድ ቤቱ ካመነ ሰውየው አባት አለመሆኑ በማያጠራጥር ሁኔታ ለማስተባበል ሕጉ የፈቀደለት የማስረጃ አይንት የዘረመል የምርመራ ውጤት ነው፡፡

በመሆኑም በዚህ ፀሀፊ እምነት በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ መሠረት DNA አባትነትን ማስተባበያ እንጂ ማረጋገጫ ማስረጃ አይደለም የሚለው ሀሳብ እጅግ ሚዛን የሚደፋ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ ይሁን እንጅ ይህ በቤተሰብ ሕጉ ያለው የፀሃፊው እውነት በበርካታ ምክንያቶች ተገቢ ባለመሆኑ፡፡ በቤተሰብ ሕጉ የአባትነት ድንጋጌ ላይ ያለውን ትችት ለማጉላት የሚከተለውን አውጇል፡፡

አዋጅ ቁጥር RFC 2009 አባት የሌለው ልጅ በቤተሰብ ሕጉ ውስጥ የተገኘ መሆኑን ለማመላከት የወጣ አዋጅ

መግቢያ

ይህ አቀራረብ በተሻሻለው የቤተሰብ ሕግ ያለውን ክፍተትና እውነት ለአንባቢያን ለማሳየት ለጉዳዩ ትኩረት  ለመስጠት ያህል እንዲሁ ፀሀፊው የተከተለው መንገድ በመሆኑ እንደአንድ የፅሁፍ አቀራረብ ብቻ እንዲታይልኝ እየጠየኩ ይህም ፀሃፊው የተሸሻለው የቤተሰብ ሕግ ስለአባትነት የደነገገው የሕግ ክፍል የተረጎመበት መንገድ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል፡፡

1.      አጭር ርዕስ

ይህ አዋጅ አባት አልባ ልጅ በቤተሰብ ሕጉ ውስጥ ስለመኖሩ ለማመልከት የወጣ አዋጅ ቁጥር RFC 2009 ተብሎ ሊጠቀስ ይችላል፡፡

2.     ሕጉ የሚፀናበት ጊዜ

ይህ የ2009 አባት አልባ ልጅ በቤተሰብ ሕጉ ውስጥ ስለመኖሩ ለማመላከት የወጣ አዋጅ የቤተሰብ ሕጉ እስለሚሻሻልበት ያልታወቀ ጊዜ ድረስ የፀና ይሆናል፡፡

ምዕራፍ 1

አባትነትን ስለማወቅ

ጠቅላላ

1.      አባትነትን ስለማወቅ(መሠረቱ)

አባትነት በሶስት መሠረታዊ መንገዶች ይታወቃል፡፡ ይሄውም በሕግ ግምት፣ ልጅነት በመቀበል እና በፍርድ ቤት ውሳኔ አባትነት ሊታወቅ ይችላል፡፡

2.ባል አባት ነው ተብሎ የሚገመት ስለመሆኑ

በጋብቻ ውስጥ የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ አባቱ ነው የሚባለው ባልየው ነው፡፡በዚህ መሠረት ጋብቻው በተፈፀመ 180 ቀናት በኋላ ወይም ጋብቻው በፈረሰ በ300 ቀናት ውስጥ የተወለደ ልጅ በጋብቻ ውስጥ እንደተፀነሰ ይቆጠራል ለዚህም ተቃራኒ ማስረጃ ማቅረብ አይችልም፡፡

3. ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብሮ መኖር

ጋብቻ ሳይፈፀም እንደባልና ሚስት አብረው በሚኖሩበት ጊዜ የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ አባት በዚሁ ግንኙነት ከእናትየዋ ጋር አብሮ የሚኖረው ሰው ነው በአንቀጽ 2 የተቀመጠው የመፀነሻ ጊዜ ለዚህ አንቀፅ ተፈፃሚነት ይኖረዋል፡፡

4.     ልጅነትን ስለመቀበል

ሁልግዜም ቢሆን በሕጉ ግምት ብቻ አባትነት ሊታወቅ ስለማይችል አንድ ሰው አንድን የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ የርሱ ልጅ መሆኑን አምኖ በመቀበል ቃሉን በሕግ አግባብ የሰጠ እንደሆነ የልጁን አባት ተቀበለ ይባላል ይሁን እንጂ ልጁ አካለመጠን ያላደረሰ እንደሆነ ይህ የመቀበል ሁኔታ እናቲቱ እውነትነት  ያለው መሆኑን ካላመነች በስተቀር ዋጋ አይኖረውም፡፡ እንዲሁም ልጁ አካለ መጠን አድርሶ እንደሆነ ልጁ ይህ የሰውየውን መቀበል አምኖ ካልተቀበለው በስተቀር ዋጋ አይኖረውም፡፡

5.     በፍርድ ቤት ውሳኔ አባትነት እንዲታወቅ ስለማድረግ

ከዚህ በላይ ባሉት ምክንያቶች አባትነት ያልታወቀ እንደሆነ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት ምክንያቶች ብቻ አባትነት በፍርድ ሊታወቅ ይችላል፡፡

5.1/ ልጁ በተፀነሰ ጊዜ በእናቲቱ ላይ የመደፈረ ወይም የመጠለፍ ተግባር ሲኖር

5.2. በተንኮል፣ ስልጣንንነ በመጠቀም አገባሻለሁ በሚል ተስፋ ወይም በሌላ ተመሳሳይ ተግባር ልጁ በተፀነሰ ጊዜ በእናቲቱ ላይ የማሳት ተግባር ከተፈፀመ

5.3. አባት ነው የተባለው ሰው በፃፋቸው የማያሻሙ አባት መሆኑን የሚገልፁ ፅሁፎች ያሉ እንደሆነ

5.4. በሕግ በታወቀ የእርግዝና ጊዜ ውስጥ ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የግብረ ስጋ ግንኙነት በሁለቱ መካከል ያለ እንደሆነ

5.5. ልጁን በመንከባከብ በማሳደግ ተግባር ውስጥ እንደ አባት የሚሳተፍ ሰው ያለ እንደሆነ ነው፡፡

5.6. ከዚህ በላይ ከተዘረዘሩት ምክንያቶች ውጪ አባትነት በፍ/ቤት ሊታወቅ አይችልም፡፡

6.     አባት የሌለው ልጅ ስለመኖሩ

1.         ከፍ ሲል በተገለፁት መንገዶች ልጁ አባት ያላገኘ እንደሆነ ልጁ ከእናቱ ጋር ካልሆነ በስተቀር ከአባቱ ጋር ምንም አይነት ህጋዊ ግንኙነት አይኖረውም ይሁን እንጂ ስለጉዲፈቻ የተደነገጉ ድንጋጌዎች እንደተጠበቁ ናቸው፡፡

2.        በተለይም በአንድ ቀን ግንኙነት ወይም አዳር ወይም ቀጣይነት በሌላው ግንኙነት እናቲቱ የግብረ ስጋ ግንኙነት በመፈፀሟ የተፀነሰ ወይም የተወለደ ልጅ በአንቀጽ 4 መሠረት ወይም በጉዲፈቻ ሕግ መሰረት በልጅነት የሚቀበለው ሰው ከሌለ በስተቀር በሕግ አባት እንደሌለው ይቆጠራል፡፡

ምዕራፍ 2

ስለ ደም ምርመራ (DNA)

በጠቅላላው

7.     የደም ምርመራ አባትነት ማስተባበያ እንጂ ማረጋገጫ ማስረጃ ስላለመሆኑ

1.         አባትነት የሚታወቀው በዚህ አዋጅ ከአንቀፅ ከ1 እስከ 5 በተመለከተው አግባብ በመሆኑ አባትነት በደም ምርመራ ሊታወቅ አይችልም፡፡

2.        ይሁን እንጂ በክፍል 1 በተገለፁ መሰረት በሕግ ግምት ወይም በፍርድ ቤት ክስ አባትነህ የተባለው ሰው በርግጥም የልጁ አባት ስላለመሆኑ ለማረጋገጥ የሕጉን ግምት ወይም የቀረበው ክስ ለማስተባበል ሲባል በማስረጃነት ሊያቀርበው ይችላል፡፡

8.     አዋጅ የማውጣት ስልጣን

ይህ አዋጅ ከልጆች መብት ጥቅም አኳያ ተገቢነት የለውም  በተለይም በሕገመንግሥቱና በአለም አቀፍ ስምምነቶች ላይ የተቀመጠውን የህፃናት መብት ይሸረሸራል የሚል ከሆነ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሊሽረው ይችላል፡፡

9. ይህ ሕግ በሌላ እንደገና በሚሻሻል የቤተሰብ ሕግ እስከሚሻር ድረስ የፀና ይሆናል፡

አዲስ አበባ

መጋቢት 15 ቀን 2009 ዓ.ም

ሙሉጌታ በላይ

በማናቸውም ፍ/ቤት

የሕግ አማካሪና ጠበቃ

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የባንክ ዋስትና ሰነዶች (Letter of Guarantees) በኢትዮጵያ ሕግ ያላ...
ስለ ይርጋ ጥቂት ነጥቦች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Thursday, 07 November 2024