Font size: +
12 minutes reading time (2302 words)

የሕግ የበላይነትን የሚያናጋው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደንብ (የቤት ኪራይ ማእቀብና የሕግ ጥሰቶቹ)

መግቢያ

የአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ቀደም ሲል አውጥቶት የነበረውና የተከራየን ሰው ማስወጣት (በርግጥ ደንቡ ይህን ድርጊት አልከለከለም) እና የኪራይ ዋጋን መጨመር ለማገድ የወጣውን የደንብ ቁጥር 122/13 ማራዘሙን በድጋሜ አስታዉቋል፡፡ ይህ ደንብ የቤት አከራዮች ያከራዬት ቤት ላይ ዋጋ እንዳንይጨምሩ ክልከላ ይጥላል፡፡ በዚህ አጭር ጽሑፍ የደንቡን ህጋዊነት ለሕግ የበላይነት ያለውን መጥፎ ተምስሌትነት በርግጥ ሊፈታ ያሰበውን ችግር ለመፍታት ያለውን ፋይዳ በአጭር ባጭሩ ለመዳሰስ ይሞክራል፡፡ አንባቢያንን ለተራዘመ እና አሰልቺ የንባብ ሂደቶች ላለመዳረግ ጉዳዩን በቀጥታና በጭሩ ለመዳሰስም ተሞክሯል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የሕግ ጥሰቶች

ንብረት እጅግ የሰፋ አድማስ ያለው በሕግ አስቀድመው ከተቀመጡ መጠነኛ ወሰኖች በቀር ባለንብረቱ ንብረቱን እንዳሻው ለመጠቀም፣  ለማዘዝ፣  ለመገልገል የሚችልበት ቁስ ነው (የፍታብሄ ሕግ አንቀጽ 1204)፡፡ ሞቶ እንኳ እንዳሻው ሊጠቀምበት ሕግ መሻቱን በንብረቱ በኩል ሊፈጽምለት ቃል የተሰጠው መሰረታዊ ነገር ንብረት ነው (የፍ/ህ/ቁ1205 እና የውርስ ሕግን ልብ ይሏል)፡፡ ንብረትህን እንዳሸህ ለመጠቀም አንዱ መሰሪያ ደግሞ ውል ነው፡፡ ንብረትህን ገንዘብ ላግኝበት ልሽጠው፣  ወዳጅ ላፍራ ልለግሰው፣   ገቢ ያምጣ ላከራየው ብትል የሕግ መንገዱ ውል ነው፡፡ የውል ሕግ ስር ደግሞ የመዋዋል ነጻነት ነው፡፡ በመሰረቱ ነጻነት እለት እለት የምንሰብከው ዲስኩር እንደመሆኑ ከህገ-መንገስታችን ጀምሮ ከስር ባሉ ሌሎች ህጎችም ቢሆን ተደጋግሞ የተሰበከ ስብከት ቢኖር ነጻነት ነው፡፡ በመሆኑም ሰዎች ነጻነታቸውን ከሚገልጡበት መንገድ አንዱ ውል ነው፡፡ ታዲያ ምንም እንኳ አንዳድ የሕግ አረዳዶች የውል ነጻነትን ገደብ የለሽ ቢያደርጉትም በእኛ አገር የሕግ ስረአት ውል በሕግ አስቀድሞ የተቀመጡ ገደቦች ያሉበት ነጻነት ነው፡፡ (ፍ/ህ/ቁ 1678፣  1681፣ 1710፣  1711፣  1719፣  1731፣  1960) ጨዋታው ነጻ እና በተጨዋቾቹ ፈቃድ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ያለጨዋታ ሕግ አይከናወንም እንደማለት፡፡ እንግዲህ ይህ የጨዋው ሕግ ነው የውል ነጻነት ገደብ፡፡

ከዚህ መሰረታዊ አረዳድ ሳንወጣ በኢትዮያ ውስጥ ካሉ መሰረታዊ ህጎች አኳያ የከተማ አስተዳደሩ የሳታቸውን መሰረታዊ የሕግ ጥሰቶች እንደሚከተለወው እንዳስሳለን፡፡

  1. በሌለው ስልጣን ደንብ ስለማውጣቱ፡፡

ከተማ አስተዳደሩ በከተማዋ ያሉ ቤቶችን የኪራይ ሁኔታ ለመወሰን የሚያስችል ደንብ ለማውጣት ሕግ ይፈቅድለታል ወይ የሚለው ጥያቄ የመጀመሪያው ነጥብ ነው፡፡ በመሰረቱ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቻርተር አዋጅ ቁጥር 361/95 (ከዚህ በኋላ ቻርተሩ እየተባለ የሚገለጽ) አንቀጽ  11 መሰረት  ከተማ አስተዳደሩ  በቻርተሩ ላይ ተለይተው በተሰጡ ጉዳዮች ላይ ሕግ የማውጣት እና የዳኝነት ስልጣን ያለው ሲሆን ለፌደራል መንግስቱ ስራ አስፈጸሚ ተቋማት ተለይተው ባልተሰጡ ጉዳዮች ላይ ደግሞ ሕግ የማስፈጸም ስልጣን ብቻ ተስጥቶታል፡፡ በተጨማሪም በቻርተሩ አንቀጽ 14/2/ለ መሰረት የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ እንዲያወጣ ስልጣን በሰጠው ጉዳዮች ላይ ደንብ ሊያወጣ ስልጣን አለው፡፡ ስለዚህ የከተማ አስተዳደሩ በሁለት መንገድ ሕግ የማውጣት ስልጣን አግኝቷል ማለት ነው፡፡ አንድም በቻርተሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ስልጣን ናቸው ተብለው ተቆጥረው በተሰጡት ጉዳዮች ላይ ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ደንብ እንዲያወጣ ስልጣን ሲሰጠው ነው፡፡ ከዚህ ወጭ ያሉት ስልጣኖች የሕግ አስፈጻሚነት እንጅ የሕግ አውጭነት ስልጣኖች ባለመሆናቸው አሁን ለያዝነው ጉዳይ ጠቃሚ ባለመሆናቸው ታልፈዋል፡፡

የከተማው አስተዳደር የቤት ኪራይን በተመለከተ ደንብ ሲያወጣ የደንቡን መሰረት በገለጸበት የደንቡ መግቢያ ላይ ይህ ደንብ ማለትም የደንብ ቁጥር 122/13 የአስተዳደሩን የአስፈጻሚ አካላትን እንደገና ለማደራጀት ስልጣን እና ተግባራቸውን ለመወሰን በወጣው የአዋጅ ቁጥር 64/11(ከዚህ በኋላ የስራ አስፈጻሚ አዋጁ ተብሎ የሚገለጽ) አንቀጽ  97 መሰረት እንደወጣ ይገልጻል፡፡ ይህን ደንብ ስንመለከት ደግሞ የከተማ አስተዳደሩ ካቢኔ አዋጁን ለማስፈጸም ደንብ የማውጣት ስልጣን ተሰጥቶታል ይለናል፡፡ እንግዲህ ካቢኔው ደንብ የማውጣት ስልጣን የተሰጠው አዋጁን ለማስፈጸም ብቻ ሲሆን አዋጁ የወጣው ደግሞ ለከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በቻርተሩ አማካኝነት ቆጥሮ የሰጠውን ስልጣን እና ተግባር በስራ ላይ ለማዋል መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ ስለዚህ በዚህ ቻርተር መሰረት ስለ ቤት ኪራይ ሕግ ለማውጣት ከፍ ሲል እንደገለጽነው አንድም በቀጥታ በጉዳዩ ላይ ደንብ እንዲያወጣ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስልጣን ሊሰጠው ይገባል፤  አንድም ይህ ጉዳይ በቻርተሩ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ስልጣን ስር የወደቆ ጉዳይ ሊሆን የተገባ ነው፡፡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስለ የቤት ኪራይ ሁኔታ ደንብ እንዲያወጣ የሰጠው ስልጣን ስለሌለ እዚህ ጋር የሚመጣው ጥያቄ የከተማ አስተዳደሩ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቆጥሮ በሰጠው ስልጣን ውስጥ በርግጥ በአዲስ አበባ ከተማ ባሉ የግለሰቦች ቤት የኪራይ ጉዳይ የከተማ አስተዳደሩ ስልጣን ተደርጎ ተቀምጧል ወይ? ቢቀመጥስ በዚህ ጉዳይ ላይ ሕግ የማውጣት ስልጣን አለው ወይ? የሚለው ይሆናል፡፡

ለዚህ ምላሽ ለማግኘት ደግሞ በቻርተሩ ላይ ለከተማ አስተዳደሩ የተሰጡ ስልጣኖችን መመለከት በቂ ነው፡፡ ለከተማ አስተዳደሩ ስልጣን እና ሃለፊነት የተሠጠው በቻርተሩ አንቀጽ  11 እና 14 ላይ ነው፡፡ በነዚህ አንቀጾች ላይ የቤት ኪራይ በተመለከተ በተለየም የግለሰቦችን ቤት የኪራይ ሁኔታ በተለየም ዜጎች በሌላ ሕግ የተጎናጸፉትን መብት ለመገደብ የሚያስችል ስልጣን እንዳለው የሚነግረን ድንጋጌ አናገኝም፡፡ ነገር ግን በቻርተሩ አንቀጸ 11 እና 14  ድንጋጌዎችን ላይ የከተማው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ፖሊሲና የልማት እቅድ የማውጣት ስልጣን ተስጥቶታል፡፡ እነዚህ አገላለጾች በከተማ ደረጃ የከተማው ህዝብ ልማት እና የኢኮኖሚ ጥያቄዎች ለመመለስ ስለሚወሰዱ እርምጃዎች እንጅ የግለሰብ ንብረትን መቆጣጠር የሚመለከተን ስልጣንን ይጨምራል ብሎ ለመረዳት አስቸጋሪ ነው፡፡ ሕግ ግለጽ ካልሆነ ሊተረጎም ይገባዋል ብለን በመነሳት ይህን አስፍተን በመተርጎም የግለሰብ ቤቶችን የኪራይ መብት የመገደብ ደንብ ማውጣት ይችላል ብለን ብንቀበል እንኳ የቤት ኪራይን በተመለከተ የኢትዮፕያ የፍታብሄር ሕግ በወቅቱ እንደ ህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሚቆጠረው  የሕግ መወሰኛ እና የሕግ መመሪያ ምክር ቤት በኩል በአዋጁ አንቀጽ 2896 እና ተከታዮቹ ላይ በአከራይና ተከራይ ግንኙነቶች ላይ ግልጽ እና ዝርዝር ሕግ ወጥቷል፡፡ በተለይም የኪራይ ዋጋን በተመለከተ በፍ/ህ/ቁ አንቀጽ 2950 መሰረት የኪራይ ልክ በተዋዋይ ወገኖች እንደሚወሰን ይህ የላተደረገ እንደሆነ ማዘጋጃ ቤት ግለሰቦችን ብቻ በተመለከተ አስቀድሞ ባስቀመጠው ታሪፍ ወይም በቦታው ልማድ መሰረት ዋጋ እንደሚያወጣ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡

በሌላ በኩል የማይንቀሳቀስ ንብረትን ማከራየት ከንብረት መብቶች ውስጥ አንዱን እና መሰረታዊ በመሆኑ በንብረት መጠቀምን በተመለከተ በሕግ አስቀድመው ከተቀመጡ የተወሰኑ ገደቦች በቀር እንዳሻው መጠቀም መብት መሆኑን በፍ/ህ/ቁ አንቀጽ 1204፣ 1205፣ 1206 በህገ መንግስቱ አንቀጽ 40 እና 41 መሰረት በግለጽ ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ እንግዲህ የከተማ አስተዳደሩ ይህ ህገመንግስታዊና በአዋጅ ደረጃ ያለን መብት ነው ግለጽ ባልሆነ ስልጣኑ ህገ መንግሰቱንና የበላዩ የሆነው የፍታብሄር ሕግ በሚቃረን መልኩ መብቶቹ እንዲታገዱ የሚል ትእዛዝ ያስተላለፈው፡፡

የከተማ አስተዳደሩ የፌደራል መንግስቱ አካል እንደመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ ስልጣን የሚመነጨው ከህገ-መንገስቱና ከፌደራሉ መንግስት ህጎች ነው፡፡ በመሆኑም በማንኛው መመዘኛ የፌደራሉ መንግስ ሕግ አወጥቶ በሚያስተዳድራቸው ጉዳዪች ላይ ከተማ አስተዳሩ ስልጣን ሊኖረው አይችልም፡፡ በሌላ በኩል  በሕግ አተረጓጎም መርህ መሰረትም አንድ ደንብ በህገ-መንግስት እና በአዋጅ ደረጃ የተደነገገን ዝርዝር መብት በሚቃረን መለኩ ሊወጣ አይችልም፡፡ እነዚህን የበላይ ህጎች በተቃረነበት ሁኔታ ተፈጻሚ ሊሆን አይችልም፡፡

ስለ ግለሰቦች ቤት የኪራይ ሁኔታ የከተማ አስተዳደሩ ደንብ የማውጣን ስልጣን አለኝ ብሎ አምኖም ቢሆን ቸርተሩ እንደሚያዘው ሌሎች በአስተዳደሩ ስልጣን ስር ያሉ ጉዳዮች እንዲደረጉ ባዘዘው መልኩ በተጠናና በፖሊሲ እና በእቅድ ደረጃ በመያዝ ዘላቂ እና ዝርዝር ሕግ በማውጣት እንጅ ለተወሰነ ጊዜ ብቻ የሚቆይ የመብት እቀባ የማድረግ ስልጣን አይሰጠውም፡፡ ከፍ ሲል አስፈተን በመተርጎም ሕግ የማውጣት ስልጣን ቢኖረው እንኳ በማለት በገለጽናቸው የከተማውን ህዝብ ኢኮኖሚያው ሁኔታ ማሻሻልም ቢሆን  መብትን በዘፈቀደ አግጃለሁ በማለት የሚሳኩ አይደሉም፡፡ አስቀድሞ በወጣ ዝርዝር ሕግ መሰረት የሚመሩ ናቸው፡፡ በመሰረቱ የከተማ አስተደዳሩ በኪራይ ሁኔታ ላይ ሕግ አውጥቷል ከማለት ይልቅ አስቀድሞ በሕግ የተረጋገጠን መብት ገድቧል ማለት የተሻለ አነጋገር ነው፡፡ ጥያቄውም ይህ ነው፡፡ የከተማ አስተዳሩ በሌሎች የበላይ ህጎች የተረጋገጠጡ (የተወሰኑት ከዚህ በታች በዝርዝር ይቀርባሉ) መብቶችን አግዶ የማቆየት ስልጣን ከየት አመጣው ?

እዚህ ላይ ሳይጠቀስ የማይታለፈው ጉዳይና ደንቡን በመመርመር በቀላሉ መዳት እንደሚቻለው ደንቡ አስቀድሞ የነበርን መብት የሚገድብ በመሆኑ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባህሪ ያለው ነው፡፡ አስቸኳይ ጊዜ አወጅ ማወጅ የሚያስፈልገው ክስተት ካጋጠመ ደግሞ ይህ የማድረግ ስልጣን የፌደራል መንግስቱ በመሆኑ የከተማ አስተዳደሩ እንዲህ አይነቱን አዋጅ ለማውጣት ስልጣን የለውም፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ የፌደራል መንግስቱ ከተማ በመሆኗም የራሷን አስቸኳይ ጊዜ ለማዋጅ ስልጣን አልተሰጣትም፡፡ እዚህ ላይ የአዲስ አበባ ከተማ ራስ ገዝነት እስከ ምን የሚል መሰረታዊ ጥያቄ ለማንሳት ቦታው ባለመሆኑን ታልፏል፡፡

  1. የመዋዋል ነጻነት፡፡

በመግቢያው ላይ ለመግለጽ እንደተሞከረው ነጻነታችን ከሚያረጋግጡባቸው መንገዶች አንዱ ውል ሲሆን የውል መሰረታዊ አላባ ደግሞ የመዋዋል ነጻነት ነው፡፡ የመወዋል ነጻነት በኢት ዮዽያ ህጎች መረን የተለቀቀ ነጻነት ባለመሆኑ ገደቦች ቢኖሩበትም ነገር ግን ውሉ ለግለሰቦቹ ለራሰቻው ለ3ኛ ወገኖች እና ለህዝብ አጠቃላይ ጥቅም ሲባል የራሱ የጫዋታ ሕግ አለው፡፡ ከዚህ በተረፈ የመዋዋል ነጻነት ሳይኖር ውል አለ ማለት አይቻለም፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ የፍ/ህ/ቁ 1696 ብንመለከት የፈቃድ ጉድለት ያለበት ውል ፈራሽ ነው ይለናል፡፡ በዚህ መሰረት የከተማ አስተዳደሩ ስለ ኪራዩ የጊዜ ቆይታ ስለዋጋው ጉዳይ ጣልቃ በመግባት የሚወሰን ከሆነና አከራዩ ቤቱን ማከራይት የቀጠለው በከተማ አስተዳሩ ደንባዊ ትእዛዛ ከሆነ፤  ውጣ ብለው እቀጣለሁ ብሎ ከፈራ፤  የቤቱን የኪራይ ልክ በቀደመው እንዲቀጥል ከተማ አስተደሩ ከወሰነ ውሉ የፈቃድ ጉድለት አለበት ማለት ነው፡፡ አከራዩ ቤቱን ማከራይት የቀጠለው በርግጥ ውሉን መቀጠል ፈልጎ ሳይሆን የለምክንያትና የለበቂ ስልጣኑ እንደርጎ ዝንብ ጥልቅ ባለው የከተማ አስተዳደሩ ደንብ ምክንያት በመሆኑ የአከራይ የተከራይ ግንኙነት የፈቃድ ጉድልት የለበትም ሊባል አይችልም፡፡

የመዋል ነጻነትን በመሰረቱ ሃገሪቱ በፍጹማዊነቱ ሳይሆን በአንጻራዊነቱ የመትቀበለው የኢኮኖሚ ፖሊሲዋ ጭምር መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ በመሆኑ እንዲህ አይነቱ በዘፈቃደ ያለጥናት መብትን በመገደብ ደረጃ የወጣ ደንብ የሀገራዊ ኢኮኖሚያ ፖሊሲው አካል ነው ለማለት አስቸጋሪ ነው፡፡

በፍታብሄር ህጉ ላይ ውል በተመለከተ የውል ነጻነት መሰረታዊ ጉዳይ በመሆኑ ውል ያለፈቃድ እንዳይደረግ ከፍተኛ የመካላከል ስራ የሰራል፡፡ በተንኮል፣  በማጭበርበር፣  በመገደድ በሀይል፣ ፣  በስህተት፣  አንደኛውን ወገን እጅግ የሚጠቅም በሆነ መነገድ በመዋል፣  በመብት በማስፈራራት፣  በይሉኝታና በመሳሰሉ ጉዳዮች ህጉ ያስቀመጠውን መስፈርት የሚያሟሉ ከሆነ ውሉን ለማፍረስ በቂነት ያላቸው ምክንያቶች ሆነው በሕግ መጠቀሳቸው ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ጋር ከተማ አስተዳደሩ የሌውን ስልጣን ተጠቅሞ ያወጣውን ደንብ መጣስ የሚያስከትለውን ቅጣት በመፍራት የቀጠለ የኪራይ ውል የፈቃድ ጉድለት የለበትም ለማለት አይቻልም፡፡ ያም ቢሆን የመዋዋል ነጻነት መገደቡ ብቻ ሳይሆን መወዋዋል እራሱ መከልከሉ ለዚህ በቂ ማሳያ ነው፡፡ በመሰረቱ የመዋዋል ነጻነቱ አንዱ ማሳያ አልዋልም ማለትንም ጭምር ነው፡፡

  1. የመስራት እና መተዳደሪያን የመምረጥ ነጻነት፡፡

ዜጎች የመሰላቸውን ስራ መስራት እና መተዳደሪያቸውን የመምረጥ ህገ-መንግስታዊ መብት ያላቸው መሆኑ አከራካሪ አይደለም (ህገ-መንግስት አንቀጽ 41)፡፡ በመሆኑም ሃብትና ንብረታቸውን በማፍሰስ በሰሩት ቤት ገቢ ማግኘት ይህን ገቢ ደግሞ መተዳደሪያቸው ማድረግ ህገ-መንግስታዊ መብት መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ እዚህ ጋር ግን ከተማ አስተዳደሩ በወጣው ደንብ በውል ግዴታ ሳይኖርበት ያከራየውን ሰው ውጣልኝ የማለት በቤቱ ላይ ኪራይ የመጨመረ መብቱን ሲገድብ መተዳደሪያውን በተመለከተ ገደብ እያደረገ ነው፡፡ በተለይ ቁጠራቸው ቀላል የማይባሉ ሰዎች ኑሯቸውን ከዚሁ የቤት ኪራይ ከሚገኝ ሀብት ላይ የሚደጉሙ መሆኑ እቀባው የጥቂት ሰዎች ጉዳይ ባለመሆኑ ጥንቃቄ የሚፈልግ ጉዳይ ነበር፡፡ ከተማ አስተዳደሩ ተከራዮች በኪራይ ዋጋ መጨመር ሳቢያ ያለባቸውን ጫና ለማቅለል በመንግስት ጭምር የታመነውን የኑሮ ውድነት ወይም የዋጋ ንረት እና ኢንፍሌሽን ባለበት ሁኔታ መንግስት ችግሩን ባይፈታለት እንኳ የራሱ በሆነ ሃብትና ንብረት ችግሩን እንዳይቀርፍ የቤት ኪራይ አትጨምርም፣  ተከራይ ማስወጣት አትችልም የሚለው ክልከላ ይህ ህገ-መንግስታዊ መብት አደጋ ላይ የሚጥል ለመሆኑ አስረጂ አያስፈልገውም፡፡ ስለዚህ እጅህ ላይ ያለህን ሀብት ተጠቅመህ ኑሮህን ማሸነፍ ተከልክለሃል እንደማለትም ነው፡፡ መንግስት በራሱ መንገድ ሊያሻሽለው የሚገባውን የኑሮ ውድነት በዜጎች ኪሳራ ለማካካስ እንደመሞከር ያለ ድርጊት ነው፡፡

  1. የዜጎች እኩልነት፡፡

እኩልነት የሕግ የበላይነት መሰረታዊ አምድ ነው፡፡ እንግዲህ እዚህ ላይ የከተማ አስተዳደሩ ደንቡን ለማውጣት ምክንያት የሆነው የተከራይ በኪራይ ዋጋ መማረር ነው፡፡ ከፍ ሲል ባለው ክፍል እንደተገለጸው በርካታ ሰዎች ኑሯቸውን ከቤታቸው ኪራይ በሚገኝ ገንዘብ እንደሚደጉሙ አከራካሪ አይደለም፡፡ ስለዚህ የከተማ አስተዳደሩ የቤተ ኪራይ ዋጋ መጨመርን ብሎም ከቤት ማስወጣትን ሲከለክል ለነዚህ ሰዎች ምን አይነት አማራጮችን አስቀመጠ የሚለው ጥያቄ መሰረታዊ ነው፡፡ በመሰረቱ ከተማ አስተዳደሩ በደንቡ መግቢያ ላይ የኪራይ ጭማሪ እየተደረገ ያለው  የገበያ ዋጋን ባላገናዘበ መልኩ ነው ሲል መንግስት በተለያየ አግባብ እዳመነው የቤት ኪራይ ለመጨመር በቂ ኢኮኖሚያዊ ምክንያት መኖሩ አከራካሪ አይመስለኝም፡፡ መንግስት ራሱ በሚሰጣቸው አገልግሎቶች ጭምር ዋጋ ጨምሮ እንዳሳየን የኑሮ ውድነት ከፍ ማለቱ፣  የዋጋ ግሽበት ከሚፈለገው መጠን በላይ መሆኑ፣  የዜጎች የመግዛታ አቅም መዳከሙ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣማቸው የማይካድ እውነት ነው፡፡ የነዚህ ሁሉ ድምር ኢኮኖሚውን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጎዳው አጠያያቂ አይደለም፡፡

በዚህ እውነታ ውስጥ ሆኖ ራሱ የአገልግሎት ክፍያዎችን ጨምሮ (የኢትየያ ባህር ትራንስፖርእና ሎጅስቲክ አገልግሎት የዋጋ ጭማሬን ልብ ይሏል፡፡) ዜጎች ዋጋ እንዳይጨምሩ መከልከል ተገቢ አይደለም፡፡ ስለዚህ በቤት ኪራይ መጨመር ምክንያት የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የማይችል ተከራይ እንዳለ ሆኖ ያለ የቤት ኪራይ ጭማሪም የኑሮ ውድነቱን መቋቋም የማይችል አከራይም አለ፡፡ ከሁሉ በላይ በአከራይ እና ተከራይ መካከል ያለው ግንኙነት ፍታህዊ እና በጥናት ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ከማድረግ ባለፈ አንዱ የንብረት መብቱን እንደይጠቀም በመከልከል የኑሮ ውድቀነት የከበደውን ተከራይ ለመካስ መሞከር ትክክለኛ አቅጣጫም ፍትሃዊም አይሆንም፡፡

በተለይ ደግሞ ለንግድ ቤታቸውን የሚያከራዩ አከራዮችን አይመለከትም የሚለው የደንቡ ክፍል እጅግ አስገራሚ ነው፡፡ ቤታቸውን ለንግድ የሚያከራዩ አከራዮች ከግለሰብ አከራዮች ይልቅ በአመዛኙ የተሻለ ኢኮኖሚያዊ አቅም ያላቸው መሆኑ  ብሎም በንግድ ቤቶች ላይ የሚጨመር የኪራይ ዋጋን በመጨረሻ የሚሸከመው ሸማቹ መሆኑ እየታወቀ በግለስብ አከራዮች እና በነጋዴ አከራዮች መካከል የተደረገው ልዩነት ደንቡን በጥናት ላይ የተመሰረተ እርምጃ ነው ብሎ ለመቀበል አስቸጋሪ ያደረገዋል፡፡

  1. የንብረት መብት፡፡

በመግቢያው ላይ  እንደተገለጸው ንብረት እጅግ የሰፋ መብት ያለው ባለመብቱ አስቀድሞ በወጣ ሕግ መጠነኛ ገደብ ከሚደረግብት በቀር ባለሃብቱ ያሻውን የሚያደረግብት ቁስ ነው፡፡ የንብረት ሁነኛ መብቶች ንብረቱን መቆጣጥር ወይም መያዝ፣  ሌሎች እንዳይጠቀሙበት መከልከልና ንብረቱን ማውደምንም ቢጨምርም (ልዩ ገደቦች እንደተጠበቁ ናቸው) አንድ ንብረት በርግጥ ንብረት ነው ሊባል የሚችለውም በንብረቱ መጠቀም ስንችል ነው፡፡ በንብረቱ ለምን ባለንብረቱ ይጠቀምበታል የሚለውን ጥያቄ ፈላስፋው ጆን ሎክ  ሲያብራራው ግለሰቡ ንብረቱን በማፍራት ሂደት በገንዘብ በጉልበት ወይም በአንዳች ነገር ከንብረቱ ጋር ግንኙነት ስላለው ከሌሎች ይልቅ በንብረቱ መጠቀም ለሰውየው የተገባ ነው ሲል ይከራከራል፡፡ ለንብረቱ መገኘት የተሻለ አስተዋጽኦ ያለው ሰው በንብረቱ የመጠቀም ተፈጥሮአዊ መብት ይጎናጸፋል፡፡ ይህ መብት በሕግ ሲገደብ በርግጥ የበለጠ ሊሳካ የተፈለገ ጥቅም መኖሩ ይህ ጥቀም ደግሞ የብዙሃኑ ጥቅም መሆኑ በርግጥ ደግሞ የተባለው ነገር የብዙሃኑን ጥቅም የሚያስከብር መሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል (Utilitarian Approch)፡፡ ይህ መሆኑ  ከተረጋገጠም በኋላ አስቀደም በወጣ እና በሚታወቅ ሕግ ካልሆነ በቀር በድንገትና ባልተጠና ዘፈቀዳዊ ገደብ በማድረግ የሚሳካ አይደለም፡፡

  1. መጥፎ የሕግ አቀራረጽ (Bad Drafting)

አስተዳደሩ ያወጣው ደንብ ሌላው ችግር አሳከዋለሁ ያለውን ነገር እንኳ በትክክለኛ ቋንቋ እና በተገቢው የሕግ አቀራረጽ ይዞ አለመቅረቡ ነው፡፡ በደንቡ መግቢያ ላይም ሆነ ክልከላ በሚለው አንቀጽ 4 ላይ የተከለከው ነገር የቤት ኪራይ መጨመር እንጅ ከቤት ማስወጣት አለመሆኑን ደንቡ በመመልከት ብቻ በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ ይሁን እንጅ በደንቡ አንቀጽ 5 ላይ ደንቡ ያልከለከለውን ነገር የወረዳ ስራ አስፈጻሚ ከቤት የማስወጣት ተግባርን እንዲያስቆሙ ስልጣን ሲሰጥ እንመለከተዋለን፡፡ በሌላ አነጋገር ከቤት ማስወጣት ባልተከለከለበት ሁኔታ ወረዳዎች  ከቤት የማስወጣት ድርጊትን እንዲያስቆሙ ስልጣን ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ህገ-ወጥ ድርጊት እንዲፈጽሙ ህጋዊ ሽፋን ይሰጣቸዋል እንደማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን ደንቡን ጥሰው የተገኘን ሰው የገንዘብ መቆጫ እንዲቀበሉ በመፍቀድ የዳነኝት ስልጣን ጭምር ይሰጣቸዋል፡፡ በመሆኑም ከቤት ማስወጣትንም ሆነ ዋጋ መጨመረን ለመከልከል ታስቦ ከሆነ ሁለቱንም ድርጊቶች በደንቡ አንቀጽ 4 ላይ በግለጽ ሊከለከሉ ሲገባ ይህ አልተደረገም፡፡ በዋናው እና መሰረታዊ ሕግ ላይ ያልተከለከለ ወይም ያልተፈቀደ ነገር ደንቡን የሚስፈጽመው አካል ስልጣን ሆኖ ሊደነገግ አይችልም፡፡

 

መፍት

የቤት ኪራይን እንደመሰረታዊ ፍጆታ መቁጠር

ይህ ጽሑፍ የኪራይ ጉዳይ አንገብጋቢ አይደለም ስረአት እንዲይዝ አንዳች እርምጃ አያስፈልገውም የሚል መነሻ የለውም፡፡ ይህ ጽኁፍ የሚተቸው ህብረተሰቡን ለማገልግል እና አንዳች ማህራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግርን ለመቅርፍ ህገ-ወጥ መንገድ መከተልን ነው፡፡  አሁን ባለው የኑሮ ውድነት ተከራዮች የወር ገቢያቸውን እስከ 2/3ኛ የሚደረስውን ለኪራይ እንደሚያወጡ ይፋዊ ያለሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ምክንያት እየተባባሰ ከመጣው የኑሮ ውድነት ጋር ተደምሮ መኖር ልብዙዎች ከባድ መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ እንደዚህ አይነት ስር የሰደደና ሰፊ ችግር ያለበት ከተማ ደግሞ ችግሩን በጥናት ላይ ተመርኩዞ በተጠናና በዝርዝር ሁሉን አቀፍ የሆነ ሕግ እና ስረአት በማበጀት እንጅ በዘፈቀደ አስቀድሞ በሕግ የተረጋገጠን መብት በደንብ በመገደብ ይሳካል የሚል እምነት የለኝም፡፡ በመሰረቱ የአከራይ እና ተከራየ ጉዳይ ምናልባት አብዛኛሁ ከሚለው አገላለጽ ባለፈ የሁሉም የከተማውን ዜጎችን የሚመለከት መሆኑ አከራካሪ አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ውስጥ ማንኛውም ሰው አከራይ ወይም ተከራይ ነው ወየም ደግሞ የሚያከራይ ወይም የተከራየ የቅርብ ሰው አለው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በዚህ ዘረፍ የሚንቀሳቀሰው ገንዘብም በቀላሉ የሚገመት አይደለም፡፡ ስለዚህ ይህ እጅግ ትኩረት የሚፈልግን ጉዳይ በዝምታ ሲመለከቱ ቆይቶ በድንገንት እና በዘፈቀዳዊ ደንብ በማውጣት መብትን በማቀብ ለማከም መሞከር መፍትሄ ሊሆን አይችለም፡፡

በመሆኑም እንደዚህ ፀኃፊ እምነት የቤት ኪራይ እንደ አንድ መሰረታዊ ፍጆታ እቃ ወይም አገልግሎት፤ አከራይን እንደ ነጋዴ ተከራይን ደግሞ እንደ ሸማች መቁጠር መፍትሄ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ እቃ መሰረታዊ ፍጆታ ከሆነ አከራይ ነጋዴ ተከራይ ደግሞ ሸማች ነው ካልን ደግሞ የዋጋ ቁጥጥር ማድረግ ግንኙነቱ አሁን ስራ ላይ ባለው የሸማቾች አዋጅ ወይም ራሱን የቻለ ሕግ እንዲኖረው በማድረግ የኪራይ ጉዳይ ተከራይን የሚያማረር አከራዩንም የሚጎዳ እንዳያሆን አድርጎ ለመቅረጽ እድል የሚሰጥ ይመስለኝል፡፡

በሌላ በኩል የቤት ኪራይ ሳይከፍሉ በቤቱ ላይ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሱ በፍርድ ቤት ክስ ቀርቦ ውጡ እስኪባሉ ድረስ በማናለብኝነት የሚኖሩ ተከራዪችንም ቢሆን ከፍርድ ቤት ውጭ ባለ ማቅቀፍ እንዲስተናገዱ በማድረግ የአከራይ እና ተከራይ ግኙነት ጤናማ እንዲሆን ማድረግ የሚቻልበት ሰፊ እድል አለ፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የሽያጭ ውልን የተመለከቱ አንዳንድ ነጥቦች ከሰበር ውሳኔ ጋር ተገናዝቦ የቀረበ
Snapshot Note on the Determination of Residency un...

Related Posts

 

Comments 2

Abebe
Guest - fentahun on Friday, 13 October 2023 08:40

ኪራይ ዋጋን መጨመር ለማገድ የወጣውን የደንብ ቁጥር 122/13 እባክህ ደንቡ ካለህ በኢሜይል fantahunbekalu@gmail.com ሼር አርገኝ፡፡ አመሰግናለሁ!

ኪራይ ዋጋን መጨመር ለማገድ የወጣውን የደንብ ቁጥር 122/13 እባክህ ደንቡ ካለህ በኢሜይል fantahunbekalu@gmail.com ሼር አርገኝ፡፡ አመሰግናለሁ!
Abyssinia Law | Making Law Accessible! on Friday, 13 October 2023 14:30

Please check your email.

Please check your email.
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 05 October 2024