Font size: +
8 minutes reading time (1503 words)

የንግድ ፈቃድን ማከራየት በወንጀል ያስቀጣል?

በሀገራችን የንግድ ሕግ ሥርዓት መሠረት ነጋዴነት ምን መብቶችና ግዴታዎች አሉበት? ለመሆኑ አንድ ነጋዴ በሥሙ ያወጣውን የንግድ ፈቃድ ለሌላ ሰው ማከራየትና በኪራይ ውል ማስተላለፍ ይችላል? አከራይቶ ቢገኝስ በወንጀል ሊያስከስሰውና ሊያስቀጣው ይችላልን? የነጋዴነት መብቶችና ግዴታዎች በየትኞቹ ህግጋት ይገዛል? የነጋዴዎችን መብትና ግዴታዎች በዋናነት የሚመለከቱት ሕግጋት በአዋጅ ቁጥር 166/1952 የወጣውና ከመስከረም 1 ቀን 1953 ዓ.ም ጀምሮ በሥራ ላይ የዋለው የንግድ ሕግ፣ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅና ደንብ እና ግብርን የሚመለከቱ ሕጎች ሲሆኑ ሌሎች ህግጋትም እንደ የውል ሕግ፣ የኪራይ ሕግ፣ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ፣ የወንጀል ሕግ.... በነጋዴዎች ላይ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የሚያስከትሉት መብትና ግዴታዎች ይኖራሉ፡፡ በዚህ አጭር ጽሁፍ ስለ ነጋዴዎች መብትና ግዴታዎች በዝርዝር ለመጻፍ የማይቻል በመሆኑ ጽሁፉ ለመዳሰስ የሚሞክረው በነጋዴነት የተመዘገበ የንግድ ፈቃድ የተሰጠው ሰው የንግድ ፈቃዱን ለሦስተኛ ወገን በኪራይ ውል ማስተላለፍ ህጋዊ መብት አለው ወይስ የለውም? የሚለውን ጭብጥ ነው፡፡

ጽሁፉን በተጨባጭ የፍርድ ቤት ጉዳይ ለመደገፍ ይቻል ዘንድ የሚከተለውን አንድ ጉዳይ እንመልከት፡-
አቶ ተፈራ… (ስሙ ለጽሑፉ ሲባል የተቀየረ) ባለትዳርና የልጆች አባት ሲሆን በባለቤቱ ሥም በቅድመ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት አገልግሎት በሚል ዘርፍ በአፀደ ሕጻናት አገልግሎት የንግድ ፈቃድ የወጣበትን ድርጅት ለማስተዳደር የውክልና ስልጣን የተሰጠው በመሆኑ በራሱ እየሠራበት እያለ በጤና እና በሌሎች ምክንያቶች ድርጅቱን የማስተማር ልምድ ካለው ሰው ጋር በኪራይ ለማሠራት ተስማምተው በጽሑፍ የኪራይ ውል አስተላለፈው፡፡ ይሁንና ተከራይው ግለሰብ ድርጅቱን እንደ ባለቤቱ/ወኪሉ ሆኖ ለመምራት ባለመቻሉ የተማሪዎች ቁጥር እየቀሰነበትና ኪሣራ እየደረሰበት በመምጣቱ በመሐከላቸው አለመግባባት በመፈጠሩ በፍትሐብሔሩ አለመግባባት ጉዳዩ ወደ ፍ/ቤት ደረሰ፡፡ ተከራይው ግለሰብ የንግድ ፈቃዱን ተከራይቶ መሥራቱን ለተቆጣጣሪ አካላት መረጃ በመስጠቱ አቶ ተፈራ በፖሊስ ለምርመራ እንደሚፈለግ ጥሪ ደርሶት የወንጀል ምርመራ ተደረገበት፡፡ ጉዳዩ በምርመራ ብቻ ሳያበቃ በፌዴራል ዐቃቤ ሕግ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 ድንጋጌዎችን በመተላለፍ የንግድ ፈቃድን ማከራየት ወንጀል ፈጽመሃል በማለት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ ቀርቦበት በወንጀል ተከሳሽ ሳጥን ለመቆም በቃ፡፡ ተከሳሽ ክሱ ደርሶት ስለ ድርጊቱ በፍርድ ቤቱ ሲጠየቅ ድርጅቱን ማከራየቱን ሳይክድ፣ ያከራየሁት መብቴን ተጠቅሜ የድርጅቱን መልካም ዝና እንጅ የንግድ ፈቃዱን ብቻ ነጥዬ ለሌላ ሰው ያላከራየሁ በመሆኑ ጥፋተኛ አይደለሁም በማለት ክርክሩን አቅርቧል፡፡ ከንግድ ሕጉና ከንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንጻር ተከሳሽ በወንጀል ጥፋተኛ ሊሆን ይችል ይሆን? በህጉ መሠረት የንግድ ፈቃድን ማከራየት የንግድ መደብርን ከማከራየት ተለይቶ የሚታይ ነውን? በተከሳሽ ላይ የቀረበውን ክስና የክርክሩን ውጤት ወደኋላ እናቆየውና በቅድሚያ ለጉዳዩ አግባብነት ያላቸውን የህጉን ድንጋጌዎች እንመልከት፡፡

በንግድ ሕጉ ስለ ነጋዴዎችና ስለ ንግድ መደብሮች በሚለው ክፍል በአንቀጽ 5 ሥር ስለ ነጋዴነት ትርጉም ሲገልጽ “ነጋዴዎች” የሚባሉት ሰዎች የሞያ ሥራቸው አድርገው ጥቅም ለማግኘት ሲሉ በህጉ የንግድ ሥራዎች ተብለው የተቆጠሩትን ሥራዎች የሚሠሩ ሰዎች መሆናቸውን ተደንግጓል፡፡ በንግድ ሕጉና በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ መሠረት የንግድ ሥራዎች ተብለው ከተዘረዘሩት ሥራዎች መካከል ለምሳሌ፡- ጥሬ ዕቃዎችን ወይም ምርቶችን ገዝተው/አምርተው የሚሸጡ፣ ህንጻዎችን/ዕቃዎችን የሚያከራዩ፣ የሆቴል፣ የምግብ ቤት፣የቡና ቤት፣ የመጠጥ ቤት፣የመኝታ ቤት… አገልግሎት የሚሰጡ፣ የትምህርት አገልግሎት የሚሰጡ፣ የላኪነትና አስመጭነት፣ የጉምሩክ አስተላላፊነት…ወ.ዘ.ተ ሥራ በንግድ መዝገብ ተመዝገበውና የንግድ ፈቃድ አውጥተው የሚሠሩ ሰዎች ናቸው፡፡ ሰዎች የሚለው እንደአግባብነቱ የተፈጥሮ ወይም የሕግ ሰውነት የተሰጣቸውን ሁሉ የሚወክል ነው፡፡ 
በንግድ ህጉ አንቀጽ 100 በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የንግድ ሥራ የሚሠራ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም የውጭ አገር ሰው ወይም የንግድ ማህበር በመዝገብ መግባት እንዳለበት በአስገዳጅነት ተደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 105 እንደተደነገገው አንድ ነጋዴ ለመመዝገብ ማመልከቻ ሲያቀርብ ከሚገልጻቸው መረጃዎች መካከልም የቤተዘመድ ስሙ፣ የተወለደበት ቀንና ቦታ፣ ዜግነቱ፣ የግል አድራሻው፣ የጋብቻ ሁኔታ፣ የንግዱ ዓላማ፣ የንግዱ ሥም፣ ሥራ አስኪያጅ ካለው ስሙንና ሥልጣኑን ይገኙበታል፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች በንግድ መዝገብ የመግባታቸው አስፈላጊነት የንግድ ሥራ ፈቃድ በግለሰቡ ማንነት የተወሰነ እንዲሆን ታስቦ ይሆን? የሚል ጥያቄ ያስነሳል፡፡ በንግድ ህጉ አንቀጽ 112 መነገድን ስለመተው በተደነገገው መሠረት ደግሞ ማንኛውም የተመዘገበ ነጋዴ የተመዘገበውን የንግድ ሥራውን በማናቸውም ምክንያት በተወ ጊዜ ወይም የንግዱን መደብር በአከራየ ጊዜ በሁለት ወር ውስጥ ከመዝገቡ እንዲሰረዝ ማመልከቻ ማቅረብ እንደሚገባው ተደንግጓል፡፡

የነጋዴነት ሥራ የቫት(የተጨማሪ እሴት ታክስን ጨምሮ) ከግብር ክፍያና በሽያጭ መመዝገቢያ ማሽን ደረሰኝ ግብይት የማከናወን ግዴታ ፣ ከሦስተኛ ወገኖች ወይም የብድርና ሌላ ውል ተዋዋዮች መብት፣ ከወንጀል ኃላፊነት፣ ከሠራተኞች መብት እና ከሌሎች ጉዳዮች ጋር ዘርፈ ብዙ የመብትና ግዴታ ግንኙነት ያለው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻርም የንግድ ፈቃድን በማከራየት የንግዱ ሥራ ቢሠራ በአገልግሎቱ ጥራት፣ በተገልጋይው መብት፣ በንግዱ ቁጥጥር፣ በግብር ክፍያ፣ በተጠያቂነትና በሌሎች ሁኔታዎች ላይ የሚያመጣው አሉታዊ ውጤት ይኖረዋልን? የሚለውን ሥጋቶች ለመከላከል የንግድ ፈቃዱን ላልተፈቀደለት ሰው በኪራይ እንዳይተላለፍ በሕግ መከልከሉ መፍትሔ ይሆናል የሚል ሃሳብ ያጭራል፡፡

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ቁጥር 686/2002 ከመውጣቱ በፊት ከ13 ዓመታት በላይ በሥራ ላይ በነበረው አዋጅ ቁጥር 67/1989 ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ ሳይመዘገብ የንግድ ሥራ መሥራት እንደማይችል፣ የንግድ ድርጅት ለሌላ ሰው በሚተላለፍበት ጊዜ የቀድሞው ፈቃድ ተመላሽ ተደርጎ ድርጅቱ የተላለፈለት ሰው በስሙ ፈቃድ ማውጣት እንዳለበት የተደነገገ ሲሆን በአዋጁ መሠረት በወጣው ደንብ ቁጥር 13/1989 መሰረትም ከአዋጁ በተመሳሳይ ሁኔታ ነጋዴው የቅርብ ጊዜ ፎቶ ግራፉንና ሌሎች ዝርዝር ሁኔታዎችን አሟልቶ መመዝገብ እንዳለበት በአስገዳጅነት ተደንግጓል፡፡ 

በአዲሱ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጅ ስለህጉ ዓላማዎች በመግቢያውና በአንቀጽ 3 ሥር እንደተገለፀው የንግድ ምዝገባ አፈፃፀምና የንግድ ፈቃድ ሥራ አሰጣጥ ስርዓት ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማስገኘት እንዲችል፣ የንግዱ ዘርፍ የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚደግፍበትን ሁኔታ የማጠናከር፣… የንግዱ ህብረተሰብ ከመንግስት ሊያገኝ የሚገባውን አገልግሎት ለማቀላጠፍ፣… ህገወጥ እንቅስቃሴን ለመግታት እንዲቻል አለማቀፍ የንግድ ሥራ አመዳደቦችን በመከተልና አስፈላጊ መስፈርቶችን በማስቀመጥ የክትትል ስርዓት መዘርጋት ማስፈለጉ ከህጉ ዓላማዎች መካከል መሆናቸው ተመልክቷል፡፡ በአዋጁ የትርጓሚ አንቀጽ ሥር “ነጋዴ”(Business Person) ማለት የሙያ ሥራው አድርጎ ጥቅም ለማግኘት ሲል በንግድ ሕጉ አንቀጽ 5 የተዘረዘሩትን ሥራዎች የሚሠራ ወይም አገልግሎት የሚሰጥ ወይም የንግድ ሥራ ነው ተብሎ በሕግ የሚወሰነውን ሥራ የሚሠራ ማንኛውም ሰው ነው፣ የሚል ትርጉም ተሰጥቶታል፡፡ በአንጻሩ “የንግድ ሥራ‘’ ማለት ከላይ እንደተጠቀሰው በተተረጎመው መሠረት ነጋዴ የሚሠራው ሥራ ነው ተብሎ ተተርጉሟል፡፡ የንግድ ህጉን ጨምሮ የትርጉም ድንጋጌዎቹ ነጋዴነት በንግድ መዝገብ መመዝገብን የሚያስረዳ የንግድ ምዝገባ ምስክር ወረቀትና የንግድ ፈቃድ የሚያስፈልገው የሙያ ሥራ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ የነጋዴነት ሥራ በግብር ከፋይ መለያ ቁጥርነት የሚያገለግል ልዩ የምዝገባ መለያ ቁጥርም ይሰጠዋል፡፡

በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 5 እና 6 ከንግድ ሕጉ በተመሳሳይ ሁኔታ በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የሚተዳደር ሀገር አቀፍ ተፈፃሚነት ያለው የንግድ መዝገብ መቋቋሙና ማንኛውም ሰው በንግድ መዝገብ ሳይመዘገብ ማናቸውም የንግድ ፈቃድ የሚያስፈልገውን የንግድ ሥራ መሥራት እንደማይችል ተደንግጓል፡፡ 

የንግድ ሥራ ፈቃድ የተሰጠው ሰው መብትና ግዴታን አስመልክቶ በአዋጁ አንቀጽ 34 ሥር ከተደነገጉት መብትና ግዴታዎች መካከል የንግድ ሥራ ፈቃዱን በንግድ ቤቱ ውስጥ በግልጽ በሚታይ ቦታ የማስቀመጥ እና የንግድ ፈቃዱን ለሌላ ለማንኛውም ሰው እንዲገለገልበት ወይም በመያዣነት እንዲይዘው ወይም እንዲከራየው አሳልፎ ያለመስጠት ግዴታዎች ይገኙበታል፡፡ የንግድ ፈቃድን ለሌላ ሰው አስተላልፎ መስጠት በሕግ የተከለከለ መሆኑ የንግድ ሕጉ በሥራ ላይ ከዋለበት ከ1953 ዓ.ም ጀምሮ እና አሁን በሥራ ላይ ያለውን የንግድ ምዝገባና ፈቃድ ሕግ ጨምሮ የንግድ ህጉን ለማስፈጸም በወጡት ሌሎች ሕጎችም በግልጽ ተደንግጓል፡፡ በሌላ በኩል የንግድ መደብርን መሸጥ፣ በመያዣነት መስጠት፣ መለወጥና ማከራየት በሕግ የተፈቀደ ተግባር ከመሆኑ አንጻር የንግድ መደብር የንግድ ፈቃድን ይጨምራል ወይስ አይጨምርም የሚለው ጥያቄ ብዙውን ጊዜ ሲያከራክር ይስተዋላል፡፡ ሕጉ ጥያቄውን የሚመልስ ድንጋጌን አካትቷል፡፡ በአንቀጽ 41 የንግድ መደብር ለሌላ ሰው በሚተላለፍበት ጊዜ የቀድሞው የንግድ ሥራ ፈቃድ ተመላሽ ተደርጎ፣ አግባብ ያለው ባለሥልጣን ከተቀበለው፣ የንግድ ሥራ መደብሩ የተላለፈለት ሰው በስሙ የንግድ ሥራ ፈቃድ ማውጣት እንዳለበት ተደንግጓል፡፡ የንግድ መደብር በማንኛውም ሕጋዊ መንገድ ለሌላ ሰው ሲተላለፍ በቅድሚያ የንግድ መደብሩ በተላለፈለት ሰው ወጪ ማስታወቂያ በጋዜጣ ታትሞ እንዲወጣ እንደሚደረግም ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም ከመንግስት በኪራይ በተያዘም ሆነ በግል የንግድ ቤት የወጣ የንግድ ፈቃድን ከንግድ መደብሩ ጋርም ሆነ ለብቻው ለሌላ ሰው በኪራይ ማስተላለፍ በንግድ ህጉም ሆነ በንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ የተከለከለ መሆኑን በግልጽ መደንገጉ ልብ ሊባል የሚገባው ነገር ነው፡፡

ይሁንና ብዙ የንግድ መደብሮችና የንግድ ቤቶች ከንግድ ፈቃድ ጋር ተከራይተው የሚሠራባቸው መሆኑን በፍርድ ቤት ከሚቀርቡ ዋቢ ጉዳዮችና በ2004 ዓ.ም የተከራይ አከራይን በሚመለከት የወጣውን መመሪያ ተከትሎ ከታዩት አለመግባባቶች ለመረዳት ይቻላል፡፡ አከራይና ተከራይዎችም ቢሆኑ ውሉን ሲዋዋሉ ትኩረት የሚሰጡበት ጉዳይ በኪራይ ገንዘቡ መጠን ላይ ያተኮረ ነው፡፡ የንግድ ፈቃድን ማከራየቱ ባለንግድ ፈቃዱን ወይም ሕጋዊ ወኪሉን በሕግ የሚያስጠይቀው በማከራየቱ ተግባር ብቻ የተወሰነ ሳይሆን የገቢዎችና ጉምሩክ ሕግጋትንም በመተላለፍ ያለሽያጭ ማሽን ደረሰኝ በመሸጥ፣ የቫት ደረሰኝ ባለመቁረጥና በሌሎች ግብር ነክ ወንጀሎችም ሊያስከስስና ሊያስቀጣ እንደሚችል ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ በከተማችን በፌዴራል ፍርድ ቤቶች የወንጀል ክስ ከሚቀርብባቸው ተከሳሽ ነጋዴዎችና ሠራተኞች ከሚያለቅሱባቸው ጉዳዮች መካከል ከፊሎቹ የንግድ ፈቃድን ከማከራየት ህገወጥ ተግባር ጋር የተያያዙ መሆናቸው ይታያል፡፡ በመሆኑም “አሁን ምን ይባላል ድስት ጥዶ ማልቀስ አስቀድሞ ነበር እንጅ ቀምሞ መደቆስ” የሚለው አባባል እንዳይፈጸምብን በንግድ ሥራችን የምንፈጽማቸውን ማናቸውንም ተግባራት በሥራ ላይ ከማዋላችን በፊት የሀገራችን ሕግ ምን ይላል? የሚለውን መፈተሽና ጠይቆ መረዳት ያልታሰበ ወጪን ብቻ ሳይሆን ሳያስቡት ወህኒ ቤት መግባትንም ያስቀራል፡፡


ለመሆኑ ከላይ በዝርዝር እንደተመከተው የንግድ ፈቃድን ማከራየት በህግ የተከለከለና የሚያስከስስ የወንጀል ተግባር ከሆነ ያጠፋ መቀጣቱ አይቀሬ ነውና ስለቅጣቱስ ሕጉ ምን ይላል? ቅጣቱ በገንዘብ ወይስ በእሥራት ወይስ በሁለቱም? በገንዘብ ብቻ ከሆነ እንኳን ከኪራዩ ገንዘብ ሊሸፈን ይችላል፡፡\

የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አዋጁ አንቀጽ 60 ስለ ቅጣት ይናገራል፡፡ በድንጋጌው መሠረት በአዋጁ መዝጋቢው መሥሪያ ቤት ወይም አግባብ ያለው ባለሥልጣን የሚወስዳቸው አስተዳደራዊ እርምጃዎች እንደተጠበቁ ሆነው ወንጀሉ አግባብ ባለው ሌላ ሕግ የበለጠ የሚያስቀጣ ካልሆነ በስተቀር ወንጀሉ መፈጸሙ በፍርድ ቤት ሲረጋገጥ፡- የንግድ ፈቃድን በኪራይ አሳልፎ መስጠትን የከለከለውን ድንጋጌ ተላልፎ የተገኘ እንደሆነ ከብር 30,000(ሰላሳ ሺ ብር) እስከ ብር 60,000(ስልሳ ሺ ብር) በሚደርስ የገንዘብ መቀጫ እና ከ3(ሦስት) እስከ 5(አምስት) ዓመት በሚደርስ ጽኑ እስራት እንደሚቀጣ ተደንግጓል፡፡ ከድንጋጌው በግልጽ ለመረዳት እንደሚቻለው ጥፋቱ አስተዳደራዊ እርምጃውን ጨምሮ ሦስት ተደራራቢ ቅጣት ያስከትላል፡፡

በፍርድ ቤቶች በሚቀርቡ የንግድ ፈቃድን የማከራየት ወንጀል ጉዳዮችም ከክርክሩ ጅማሮ እስከ መደምደሚያው የሚያረጋግጠው ከላይ የተመለከተውን እውነታ ነው፡፡

በዚሁ መሰረት ለጽሁፉ በዋቢ ጉዳይነት የተጠቀሰው ተከሳሽ በዐቃቤ ሕግ ተጠቅሶ ክስ በቀረበበት አዋጅ ቁጥር 686/2002 አንቀጽ 34/7/ እና አንቀጽ 60/3/ መሠረት ጥፋተኛ ተድርጎ ፍ/ቤቱ የግራቀኙን የቅጣት ማክበጃና ማቅለያ ምክንያቶች ከግምት በማስገባት በብር 30,000(ሰላሳ ሺ ብር) የገንዘብ መቀጮ እና የ1 ዓመት ከ6 ወር ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ህዳር 14 ቀን 2005 ዓ.ም ተወስኖበት ወደ ወህኒ ቤት ገብቷል፡፡ ባላሰበው ነገር በወንጀል ጥፋተኛ መሆኑና ቅጣቱ ለተፈራ፣ ለቤተሰቦቹና ጓደኞቹ አስገራሚ ጉዳይ ሆኖባቸዋል፡፡ ተፈራ በቤተሰቡና በጠበቃ በመታገዝ በጥፋተኝነቱና በቅጣቱ ውሳኔ ለፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ቅሬታውን በማቅረብ ለጊዜው በዋስትና ሆኖ ከዐቃቤ ሕግ ጋር የተከራከረ ቢሆንም ዐቃቤ ህጉን ረትቶ በነጻ ለመሰናበት በለስ ሳይቀናው ቀርቶ ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ጥፋተኝነቱንና የቅጣቱን ውሳኔ መጋቢት 5 ቀን 2005 ዓ.ም በዋለው ችሎት በሰጠው ፍርድ እንዲጸና በመወሰኑ ተመልሶ ወደ ማረሚያ ቤት ተልኳል፡፡

ተፈራ ለጽሁፉ በምሳሌነት ተጠቀሰ እንጂ ሌሎችም በተለያየ የንግድ ዘርፍ ያወጡትን የንግድ ፈቃድ በራሳቸው ወይም በወኪላቸው በማከራየታቸው ምክንያት የተነሳ በወንጀል ጥፋተኛ ሆነው ተገኝተው በእስራት የተቀጡና ለማረሚያ ቤት የተዳረጉ ብዙዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም ነጋዴዎችና ወኪሎች ንግድ ፈቃድ የማከራየትን ጦስ ቆም ብለን ልናስብበት የሚገባ መሆኑ የጽሁፉ መልዕክታችን ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ራስን በራስ የማስተ...
በክልል የተገደበው የመዘዋወር ነፃነት

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 23 July 2024