“ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከል…” ከሕግ አንጻር ሲታይ

በሀገራችን እጅግ አሳሳቢ እና አነጋጋሪ ከሆኑት የወንጀል ድርጊቶች መካከል በአሽከርካሪዎች የሚፈጸመው ወንጀል ቀዳሚውን ሥፍራ ይይዛል ለማለት ይቻላል፡፡ ከትራፊክ ፖሊስ ዕለታዊ ሪፖርት በየዕለቱ እንደምንሰማው በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ እንኳን ያለበትን ሁኔታ ብንመለከት በንብረትና በሰው ላይ፣ ቢያንስ በአንደኛው ላይ አደጋ ሳይደርስ የዋለበት ቀን የለም ለማለት ይቻላል፡፡ የአደጋ ዜናው በ24 ሰዓት፣ በወርና በዓመት ስሌት ሲነገር ስንሰማው እጅግ አሳሳቢ ነገር ነው፡፡ በትርፊክ ፖሊስ የዘወትር ሪፖርት እንደምንሰማውም ብዙውን ጊዜ አደጋው የደረሰው ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል በአሽከርካሪ ጥፋት መሆኑን መዘገቡ የተለመደ ነው፡፡

በዚህ ጽሁፍ ፍተሻ የምናደርግባቸው ነጥቦች አሽከርካሪ አጥፍቷል ወይም በቸልተኝነት ወንጀል ፈጽሟል የሚባለው መቼ ነው; የወንጀል ድርጊቱን ለመከላከል/ለመቀነስ እግረኞችስ ምን ዓይነት ግዴታ አለባቸው; አደጋውን እያባባሱ ያሉት ዋና ዋና ሁኔታዎች ምንድን ናቸው; የሕግ ስርዓታችንና በፍርድ ቤቶች የተሰጠው ቦታስ ምን ይመስላል; የሚሉትንና ተያያዥነት ያላቸውን ነጥቦች ናቸው፡፡

ወደ ዝርዝር ነጥቦች ከመግባታችን በፊት ጭብጡን በፍርድ ቤቶች በታዩና ፍርድ በተሰጠባቸው ጉዳዮች ለመደገፍ ይቻል ዘንድ በቅድሚያ ሶስት ዐቃቤ ህግ የወንጀል ክስ ያቀረበባቸውንና ፍርድ ቤት ፍርድ የሠጠባቸውን ናሙና ጉዳዮችን በአጭሩ እንመልከት፡፡

ጉዳይ አንድ፡ ጊዜው ነሐሴ ወር 2002 ዓ.ም ነው፡፡ በ70ዎቹ የዕድሜ ክልል የሚገኙት አዛውንት ከኦሮሚያ ክልል አርሲ ዞን ለሥራ ጉዳይ በማለት ወደ አዲስ አበባ ይመጣሉ፡፡ አዛውንቱ ሥራ ያሉትም በመንገድ ላይ ገንዘብ ለምኖና አጠራቅሞ ወደመጡበት መመለስ ነበር፡፡ ሥራቸውንም በተክለሃይማኖት አካባቢ ባለው አስፋልት ላይ ቀኑን እንደ ሸማኔ መወርወሪያ ከግራ ወደቀኝ በመመላለስ በትጋት ሲያከናውኑ መዋል ጀመሩ፡፡ የልመና ገንዘቡም በዋናነት ከአሽከርካሪዎች እየተሰበሰበና እየተጠራቀመ ነው፡፡ ይሁንና በአንዲቷ ጎደሎ ቀን ከአንዱ አሽከርካሪ ሳንቲም ተቀብለው በሌላኛው ተሽከርካሪ ተከልለው መንገዱን ከቀኝ ወደ ግራ ሲያቋርጡ ከአንድ የጭነት ተሽከርካሪ አይሱዙ ጋር ይጋጩና ከአስፋልቱ ላይ ይወድቃሉ፡፡ አዛውንቱም የሰበሰቡትን ገንዘብ የት እንዳስቀመጡት ሳይናገሩና እንዳሰቡትም ወደ መጡበት ሳይመለሱ እንደወጡ ቀሩ፡፡ የትራፊክ ፖሊስ የአዛውንቱ ሞት በአሽከርካሪ ጥፋት ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ፕላኑን አዘጋጅቶና ሪፖርቱን ጽፎ ጉዳዩን ለዐቃቤ ህግ አስተላለፈ፡፡ ዐቃቤ ህግም በሪፖርቱ መሠረት ክሱን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 543/2/ ተላልፎ በቸልተኝነት ሰው መግደል የወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡


ጉዳይ ሁለት፡ ጊዜው በስድስተኛው ወር በ2002 ሲሆን አሽከርካሪዋ ሴት ነች፡፡ አሽከርካሪዋ ባለቤቷ ከዚህ ዓለም በሞት ሲለይ የነበራቸውን ጅምር ቤት በመሸጥ ሁለት ህጻናት ልጆቿን ለማሳደጊያ ይሆናት ዘንድ በማሰብ አንድ ትንሽ ላዳ ታክሴ በመግዛት ሹፌር ቀጥራ ገቢ ማግኘት ጀመረች፡፡ ሴትዮዋ ያላት የመንጃ ፈቃድ 2ኛ ሆኖባት እንጅ 3ኛ ቢሆን ኖሮ ታክሲዋን ራሷ በማሽከርከር ገቢዋን የተሻለ የማድረግ ሀሳቡ ነበራት፡፡ ሀሳቧን ከግብ ለማድረስም 3ኛ ደረጃ አሽከርካሪነት የሙያ ፈቃድ ለማግኘት ልምምድ ጀመረች፡፡ ነገር ግን ልምምዱ በተፈቀደላቸው አሰልጣኞችና የመለማመጃ ተሸከርካሪዎች ብቻ የተወሰነ አልነበረም፡፡ ከዚህ አልፎ በራሷ ታክሲ እና በሹፌሯ አለማማጅነት ልምምዷን በኮተቤ አስፋልት ቀጠለች፡፡ ይሁንና እንኳን በ3ኛ ደረጃ መንጃ ፈቃድ የሚነዳውን ተሸከርካሪ ማሽከርከር ይቅርና ችሎታዋ በ2ኛ ደረጃ ለሚሽከረከረውም አጥጋቢ አልነበረምና ከኋላ በተከተላትና ድምጹን በሰማቸው ከባድ ተሸከርካሪ ምክንያት በድንጋጤ ከመንገዱ በመውጣት በከባድ ቸልተኝነት የመንገዳቸውን ቀኝ ጠርዝ ይዘው ይጓዙ ከነበሩት ሴት ህጻናት ተማሪዎች መካከል በአንዷ ላይ የሞት አደጋ፣ በሁለቱ ላይ የአካል ጉዳት አደጋ በማድረስ ግቢ ጥሳ በመግባት በንብረትም ላይ ጉዳት የማድረስ ድረጊት ይፈጸማል፡፡ የትርፊክ ፖሊስም አደጋው የደረሰው ከመንጃ ፈቃድ ደረጃ ውጭ ደንብ በመተላለፍ፣ በአሽከርካሪ ጥፋት ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል የተፈጸመ መሆኑን በመግለጽ ፕላኑን አዘጋጅቶና ሪፖርቱን ጽፎ፣ አለማማጁንም ከምስክሮች መካከል አድርጎ (እያለማመደ የነበረ መሆኑን ክዷል) ጉዳዩን ለዐቃቤ ህግ አስተላለፈ፡፡ ዐቃቤ ህግም በሪፖርቱ መሠረት ክሱን በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 543/2/ እና 559/2/ ተላልፎ በቸልተኝነት ሰው መግደል እና የአካል ጉዳት ማድረስ እንዲሁም በመንጃ ፈቃዱ ደንብ በመተላለፍ ሦስት የወንጀል ክሶችን በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡ 


ጉዳይ ሶስት፡ ቀኑ ሐምሌ 29 ቀን 2003 ዓ.ም ከጠዋቱ 4 ሰዓት ነው፡፡ ቦታውም በአዲስ አበባ ከተማ የኮንዶሚንየም ቤቶች የበዛበት ሰፈር ነው፡፡ ዕድሜው 8 ዓመት የሚሆነው ህጻን ከሌሎች ሁለት ዕኩዮቹ ከሆኑት ህጻናት ጋር አባሮሽና ሌሎች ጨዋታዎችን ዕየተጫወቱ ከጎድጓዳው ሥፍራ ወጥተው መንታ አስፋልት መንገዱን ከግራ ወደ ቀኝ በሩጫ እያቋረጡ እያለ ህጻኑ በመካከለኛ ፍጥነት እየተሸከረከረ ከነበረ የቤት አውቶሞቢል ጋር ይጋጫል፡፡ በቦታው ከነበሩት የዓይን ምስክሮች ለመረዳት እንደተቻለው መኪናው ህጻኑን ይግጨው፣ ህጻኑ በፈጣን ሩጫው ምክንያት ከመኪናው ይጋጭ ግራ በሚያጋባ ሁኔታ ህጻኑ ከአስፋልት ላይ ወደመጣበት አቅጣጫ ይወድቃል፡፡ ሾፌሩ ሀኪም ቤት በወውሰድ የህጻኑን ነፍስ ለማትረፍ ጥረት ቢያደርግም ውጤት ሳያስገኝ ህጻኑ እስከዘላለሙ ያሸልባል፡፡ የትራፊክ ፖሊስ የህጻኑ ሞት በአሽከርካሪ ጥፋት ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል የተፈጸመ መሆኑን እንደተለመደው በመግለጽ ፕላኑን አዘጋጅቶ፣ ሪፖርቱን ጽፎና ምስክሮችንም ዘርዝሮ ጉዳዩን ለዐቃቤ ህግ አስተላለፈ፡፡ ዐቃቤ ህግም በሪፖርቱ መሠረት ክሱን በአሽከርካሪው ላይ በ1996 ዓ.ም የወጣውን የወንጀል ህግ አንቀጽ 543/2/ ተላልፎ በቸልተኝነት ሰው መግደል የወንጀል ክስ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት አቀረበ፡፡


ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱት ሦስቱም አደጋዎች የተፈጸሙት በአዲስ አበባ ከተማ ሲሆን በተለያዩ ትራፊክ ፖሊሶች የባለሙያ ምርመራ ተደርጎባቸው በሪፖርቶቹ መሠረት በአሽከርካሪዎቹ ላይ በዐቃቤ ህግ ክስ ተመስርቶባቸዋል፡፡ ክሶቹም የቀረቡት በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ወንጀል ችሎት ነው፡፡ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤቱ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት በመስጠት በአሽከርካሪዎች ምክንያት በቸልተኝነት የሚፈጸሙ ሰው የመግደል የወንጀል ድርጊቶችን ብቻ የሚዳኙ ሁለት ልዩ ችሎቶች አቋቁሞ ፈጣን ፍትህ እየሰጠ ይገኛል፡፡ ፍርድ ቤት በተካሳሾቹ ላይ የቀረበውን ክስ በኢፌዲሪ ሕገመንግስትና በወንጀል ሕግጋቱ አግባብነት ያላቸው ድንጋጌዎች መሠረት ክርክሩንና የግራ ቀኙን ማስረጃዎች ሰምቶ በሦስቱም ጉዳዮች ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ለመሆኑ በትራፊክ ፖሊስ ተመሳሳይ የጥፋተኝነት ሪፖርት የቀረበባቸውና በዐቃቤ ሕግም የወንጀል ክስ የቀረበባቸው በተከሳሽ ሣጥን ውስጥ የቆሙት ሦስቱም አሽከርካሪዎች ለእግረኛ ቅድሚያ በመከልከል በወንጀል ሕጉ መሠረት በቸልተኝነት ወንጀል ፈጽመዋል; በድርጊቶቹ ክቡር የሆነው የሰው ሕይዎት የተቀጠፈ በመሆኑ ሊቀጡና ወደ ወህኒ ሊወርዱ ይገባል; የተጎጅዎችስ አስተዋጽኦ ነበረበት; በቸልተኝነት ወንጀል ተፈጸመ የሚባለው ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ ነው;


በመሠረቱ አንድ ወንጀል ተደረገ የሚባለው ወንጀሉን የሚያቋቁሙት ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች በአንድነት ተሟልተው ሲገኙ ብቻ መሆኑን በአዋጅ ቁጥር 414/1996 የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 23/2/ በግልፅ ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም አንድን ድርጊት ወንጀል ነው ብሎ ለመወሰን ሕጋዊ፣ ግዙፋዊ እና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች ተጣምረው መገኘት የግድ ይላል፡፡ ሕጋዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉት ደግሞ ለጉዳዩ አግባብነት አለው ተብሎ የተጠቀሰውን ድንጋጌ ለማቋቋም ሙሉ በሙሉ መሟላት ያለባቸው ነጥቦች ሲሆን ግዙፋዊና ሞራላዊ ፍሬ ነገሮች የሚባሉትን ደግሞ እንደየ ቅደምተከተላቸው ከድርጊት ማድረግ ወይም አለማድረግና ከሐሳብ ክፍል ጋር በሕጉ የተመለከቱትን ሁኔታዎች የሚመለከቱ ናቸው፡፡ የወንጀሉ ማቋቋሚያ ነጥቦች ከላይ የተመለከቱት ሲሆኑ በክርክር ሂደት የሚረጋገጡት ፍሬ ነገሮች የተጠቀሰውን ሕግ የሚያቋቁሙ መሆን አለመሆናቸውን ለማረጋገጥ ሕጉ ቸልተኝነት አለ የሚለው ምን ምን ሁኔታዎች ሲሟሉ እንደሆነ መመልከቱ ተገቢነት ይኖረዋል፡፡


በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 57 በግልፅ እንደሰፈረው “ለድርጊቱ ኃላፊ ሊሆን የሚገባው ሰው አስቦ ወይም በቸልተኝነት አንድ ወንጀል ካላደረገ በቀር በወንጀል ጥፋተኛ አይሆንም’’፡፡ በአንፃሩ አንድ ሰው “የፈፀመው ድርጊት በሕግ የሚያስቀጣ ቢሆንም ምንም ጥፋት ሳያደርግ ወይም ከአቅም በላይ በሆነ ኃይል ምክንያት ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ ነገር የተፈፀመ ወይም የደረሰ ሆኖ ሲገኝ በወንጀል ሕግ ሊፈረድበት አይገባውም በማለት የወንጀል ሕጉ አንቀፅ 57/2/ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ የሕጉ አጠቃላይ ይዘትና መንፈስ መገንዘብ የሚቻለው በአንድ ድርጊት ምክንያት አንድን ሰው በወንጀል ጥፋተኛ ነው ለማለት ከሳሽ የሆነው ዓቃቤ ሕግ ድርጊቱ የተፈፀመው ሆነ ተብሎ ወይም በቸልተኝነት መሆኑን ማስረዳት የሚጠበቅበት መሆኑን ነው፡፡ ድርጊቱ ሆን ተብሎ ወይም በቸልተኝነት የተፈፀመ ለመሆኑ ማስረጃ ካላቀረበ ወይም ድርጊቱ ከአቅም በላይ ወይም በድንገተኛ አጋጣሚ የተፈፀመ መሆኑን የሚያስረዳ ማስረጃ በተከሣሽ በኩል ከቀረበ የተከሰሰውን ሰው በወንጀል ሕግ ጥፋተኛ ብሎ መፍረድ ከሕጉ መንፈስ ውጪ ነው፡፡ በወንጀል የተከሰሰ ሰው ቸልተኛ ነበር? ወይስ አልነበረም? የሚለው ጥያቄ በወንጀል ሕጉ በአንቀፅ 59 የሰፈረውን ድንጋጌ መሠረት በማድረግ የሚወሰን ነው፡፡ የዚሁ አንቀፅ ንዑስ አንቀጽ አንድ አሁን ለተያዘው ጉዳይ ቀጥተኛ አግባብነት ያለው በመሆኑም የሕጉን ይዘት እንዳለ ማስቀመጡ ጠቃሚ ነው፡፡ ይኸውም፡- ማንም ሰው በቸልተኝነት የወንጀል ተግባር አድርጓል የሚባለው፡-


ሀ) ድርጊቱ በወንጀል ሕግ የሚያስቀጣ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል እያወቀ አይደርስም በሚል ግምት ወይም ባለመማዛዘን፣ ወይም 
ለ) ድርጊቱ በወንጀል የሚያስቀጣ ውጤት ሊያስከትል እንደሚችል ማወቅ እያለበት ወይም እያቻለ ባለመገመት ወይም ባለማሰብ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ ነው፡፡


በዚህ ድንጋጌ መሠረት አንድ ሰው በቸልተኝነት ወንጀል ፈፅሟል የሚባለው ውጤቱን እያወቀ ውጤቱ አይደርስም ከሚል መነሻ ድርጊቱን የፈፀመ እንደሆነ ወይም ደግሞ የወንጀል ውጤት የሚያስከትል መሆኑን ባያውቅም ውጤቱን ማወቅ ነበረበት ወይም ጥረት ቢያደርግ ውጤቱን ማወቅ ይችል ነበር ማለት ሲቻል ነው፡፡ በመሆኑም ቸልተኝነት አለ ለማለት ሕጉ የሚጠቀምበት ዋነኛ መስፈርት የተከሰሰው ሰው በድርጊቱና በውጤቱ መካከል ያለውን ግንኙነት አስመልክቶ ያለው ወይም ሊኖረው የሚገባው ግንዛቤ ነው፡፡ ድርጊቱን የፈፀመው ሰው የነበረው ዕውቀትና ግንዛቤ ወይም ሊኖረው የሚገባው ዕውቀትና ግንዛቤ የሚመዘነው የሰውዬው ዕድሜ፣ ያለው የኑሮ ልምድ ፣ የትምህርት ደረጃው፣ ሥራውና የማህበራዊ ኑሮ ደረጃውን ግምት ውስጥ በማስገባት እንደሆነም የሕጉ አንቀፅ 59/1/ ይደነግጋል፡፡


ይህንን የወንጀል ህጉን ድንጋጌዎችና አንድምታ አሽከርካሪዎች ብቻ ሳይሆኑ እግረኞችም ጭምር ልብ ሊሉት ይገባዋል፡፡ ከወንጀል በተጨማሪም የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 208/2003 እና የአዲስ አበባ አስተዳደር የመንገድ ትራፊክ ደህንነት ደንብ ቁጥር 27/2002 ድንጋጌዎች በሁሉም ወገኖች ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ አሽከርካሪዎች ከፍተኛ የህግ ግዴታና ኃላፊነት ያለባቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ ሁል ጊዜ የምንሰማው ግን ብዙዎች አሽከርካሪዎች ልብ የማንለው መዝሙርም “አትቸኩል ትደርሳለህ፣ አሽከርክር ረጋ ብለህ፣… ሁሌም ረጋ ብለን በትዕግስት እንንዳ ፣ ሕይዎት እንዳንቀጥፍ አካል እንዳንጎዳ፣ ከባድ ኃላፊነት እንዳለብን አውቀን…፤” የሚነግረን የአሽከርካሪ ኃላፊነት ዘርፈ ብዙ መሆኑን ነው፡፡
እግረኞችስ በትእግስት መጓዝ፣ መንገድ ስናቋርጥ ግራ ቀኙን ማየት፣ በማታ አንጸባራቂ ልብስ መልበስ፣ በዜብራ መንገድ መጠቀም፣ መንገድ ላይ አለመቆምና ሞባይል አለማውራት፣ ፈጠን ብሎ መሻገር፣ አሽከርካሪን መሳደብንና መገላመጥን ማስወገድ፣ ከዕይታ ተከልሎ አለማቋረጥ፣ ግራን ይዞ መጓዝ፣ በመንገድ ላይ ዕቃ አለማስቀመጥና አለመነገድ… አይኖርብን ይሆን; ወይስ ግዴታው የአሽከርካሪ ብቻ ነው;


ከላይ ከተጠቀሱት የጥንቃቄ እርምጃዎች መካከል ዋናዋናዎቹ በደንብ ቁጥር 208/2003 አንቀጽ 55 እስከ 62 “ስለ እግረኞች” በሚለው ርዕስ ሥር በዝርዝር ተደንግገዋል፡፡ በደንብ ቁጥር 27/2003 ሕግም በ1956 ዓ.ም የወጣው ደንብ ተጠቅሶ እግረኛ የሕጉን የትራፊክ ክልከላዎች ሲጥስ በተሸከርካሪ ለሚደርስበት የትራፊክ አደጋ ለጥፋቱ እንዳደረገው አስተዋጽኦ መጠን በሙሉ ወይም በከፊል ኃላፊ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ እግረኞችም የድርሻችንን ልንወጣ ይገባል፡፡ የትራፊክ ፖሊሶችም እግረኛ ሲያጠፋና አደጋው በእግረኛ ጥፋት መድረሱ ከተረጋገጠ ሁል ጊዜ ለእግረኛ ቅድሚያ መከልከል ከሚለው ዶግማዊ ዘገባ በመውጣት የእግረኛውንም አስተዋጽኦ ቢነግሩን አደጋውን ለመከላከልና ለመቀነስ ይጠቅማል እንጅ ጉዳት የለውም፡፡


ፍርድ ቤትም ውሳኔ የሚሰጠው የሕይዎት፣ የአካልና የንብረት ጉዳት ስለደረሰና ክስ ስለቀረበ ብቻ ሳይሆን የአደጋውን አደራረስ ሁኔታ መርምሮ ጥፋቱ የሹፌሩ መሆን አለመሆኑን መዝኖ መሆኑ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ከላይ በምሳሌነት ከተጠቀሱት ጉዳዮች መካከል በመጀመሪያ እና በሦስተኛነት በተጠቀሱት አዛውንቱና ህጻኑ ጉዳይ ተከሳሾችን በነጻ እንዲሰናበቱ የወሰነ ሲሆን በሁለተኛው ጉዳይ ደግሞ የጥፋተኝነትና ከ4 ዓመት በላይ የእስራት ቅጣት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡ ከእግረኞቹ በተጨማሪ የትራፊክ አደጋ ለመድረሱ ብዙ ነገሮች አስተዋጽኦ አላቸው፡፡ ከእነዚህም መካከል በዋናነት የመንጃ ፈቃድ ሰጭዎች፣ አሰልጣኞች፣ የመንገድ ሰሪዎችና የአስፋልት ላይ ጉድጓዶች/ብልሽት፣ የተሽከርካሪዎች ቴክኒካዊ ብቃትና ምርመራ፣ የአሽከርካሪዎች ጤንነትና እድሜ፣ የወላጆች/ሞግዚቶች ህጻናትን የመቆጣጠር ግዴታን አለመወጣት፣ መንገድ ላይ ንግድና ልመና… የመሳሰሉት ተጠቃሾች ናቸው፡፡ በመሆኑም አግባብነት ያላቸው አካላት አሽከርካሪን ብቻ ሳይሆን እግረኛን ጨምሮ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት ቢቆጣጠሩና እግረኞችና ሁላችንም የበኩላችንን ግዴታ ብንወጣ ተግባራችን ሥልጡን ውጤቱም መልካም ይሆናል፡፡

(በአዲስ ጉዳይ መጽሄት ቅጽ 6 ቁጥር 134 ጥቅት 2005 ዓ.ም የታተመ)

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

አንዳንድ ነጥቦች ስለአዲሱ የመንገድ ትራፊክ መቆጣጠሪያ ማሻሻያ ደንብ ቁጥር 39...
የታክስ ይግባኝ ኮሚሽን እና የአዲስ አበባና ድሬዳዋ ከተሞች ራስን በራስ የማስተ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 29 March 2024