Font size: +
11 minutes reading time (2173 words)

ስለ “የታሰሩ ሰዎች መብቶች” አንዳንድ ነጥቦች

በማያ ጋዜጣ ሐምሌ የታተመ በሰሞኑ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የችሎት ውሎዎች በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ እና በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን የጋራ የወንጀል ሕጉን የማስፈጸም ተግባር ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች፣ የተለያዩ መንግስታዊ መሥሪያ ቤቶች ዳይሬክተሮችን ጨምሮ በሙስና ወንጀል ተጠርጣሪነት ተይዘው የጊዜ ቀጠሮ እየተጠየቀባቸው የሚገኙት እስከ ሣምንቱ አጋማሽ ድረስ ቁራቸው 45 የደረሱ ተጠርጣሪዎች በእሥር ላይ የሚገኙ መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የሕግ እርምጃው ቀጣይነት ያለው መሆኑንም በመንግስት መገናኛ ብዙሃን በኢቢሲ መግለጫ ተነግሯል፡፡ የተጠርጣሪዎችን በእሥር ላይ መዋል ተከትሎ በመንግስትም ሆነ በግል መገናኛ ብዙሃን ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመውታል ተብሎ ስለተጠረጠሩበት ወንጀል ዝርዝር የገንዘቡን መጠን ጨምሮ በስፋት ሲዘገብ እየተመለከትንና በጋዜጦች እያነበብን ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ተጠርጣሪዎቹን በሕግ መሠረት በቁጥጥር ሥር አውሎ፣ ክስ አቅርቦ ጥፋተኝነታቸው በማስረጃ የተረጋገጠባቸውን በህጉ መሠረት እንዲቀጡ ማድረግ መሰረታዊ የህግ ዓላማ እንዲሁም አንደኛው የሕግ አስፈጻሚዎች ሥልጣንና ተግባር ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ በእሥር ላይ የሚገኙት ተጠርጣሪ እሥረኞችን ሕገመንግሥታዊ መብቶችን የማክበሩ ጉዳይም ከተጠያቂነቱና የወንጀል ህጉን ከማስፈጸሙ እኩል ጎን ለጎን ትኩረትን የሚሻ ነው፡፡ የሰዎች መብቶችና ግዴታዎች ሁል ጊዜ ጎን ለጎን በትይዩ የሚፈጸሙ መሆናቸው መሠረታዊ የህግ መርህ ነው፡፡ 

ከላይ የተጠቀሱትን ተጠርጣሪዎችን ጨምሮ ካሁን በፊት በሙስናም ሆነ በሌሎች ወንጀሎች ተጠርጥረው በእሥር ቤት/ በማረሚያ ቤት በሚገኙ ተከሳሾች የፍርድ ቤት ችሎት ውሎዎች የታሰሩ ሰዎችን መብቶች በተመለከተ የሚነሱ ዘርፈ ብዙ የመብት ጥያቄዎች፣ የመብት ጥሰት አቤቱታዎችና ክርክሮች ተደጋግመው ሲነሱ ይስተዋላል፡፡ የዛሬው የጽሁፋችን ርእስና ጭብጥ ሆኖ የተመረጠው ይህንኑ የእስረኞችን መብት ጉዳይ የሚመለከት ነው፡፡ በኢፌዲሪ ሕገመንግስት ከአንቀጽ 13 እስከ 44 ስለ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ከተደነገጉት መካከል በአንቀጽ 21 ሥር በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብት ከሰብአዊ መብቶች መካከል አንደኛው ሕገመንግስታዊ መብት መሆኑን ተደንግጓል፡፡ 
የሕገመንግስቱ አንቀጽ 21 ሁለት ንዑሳን ድንጋጌዎች እንደሚከተለው ይነበባሉ፡- 
(1) በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች ሰብዓዊ ክብራቸውን በሚጠብቁ ሁኔታዎች የመያዝ መብት አላቸው፡፡

(2) ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከሃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር ለመገናኘትና እንዲጎበኟቸውም ዕድል የማግኘት መብት አላቸው፡፡

ለመሆኑ የታሰሩ ሰዎች ምን መብት አላቸው? መብቶቻቸውስ በየትኞቹ የሀገራችን ህግጋት ጥበቃ ተደርጎላቸዋል? የመብት ጥበቃውስ ከማን ነው? ጠባቂውስ ማን ነው? የት፣ መቼና እንዴትስ ይጠበቃል? ጽሁፉ እንዚህንና ተያያዥ ጭብጦችን ይዳስሳል፡፡

 

1. የታሰሩ ሰዎች መብቶችና ጠባቂ ሕግጋቱ፡-

 

በኢፌዲሪ ህገመንግስት ከአንቀጽ 19 እስከ 23 ድረስ የተደነገጉት አራት አንቀጾች ከወንጀል የፍትህ ሥርዓት ጋር የተገናኙ ሲሆኑ ሦስቱ ቀዳሚ አንቀጾች በሕግ ስለተያዙ ሰዎች መብት፣ የተከሰሱ ሰዎች እና በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብትን በተመለከተ የተደነገጉ ናቸው፡፡ በክልል ሕግጋተ መንግስትም ተመሳሳይ ድንጋጌዎች ተካትተዋል፡፡ ሕገመንግሥቱ ከወንጀል የፍትሕ ሥርዓት ጋር ለሚገናኙ ሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ሽፋንና ትኩረት የሰጠ ስለመሆኑ ከድንጋጌዎቹ ብዛትና ይዘት ለመረዳት ይቻላል፡፡ በጥበቃ ሥር ያሉና በፍርድ የታሰሩ ሰዎች መብቶች ሰብአዊ ወይም የሰው ልጆች ሁሉ መብቶች በመባል የሚታወቁ ሲሆን መብቶቹ ከሰው ልጅ ተፈጥሮ የሚመነጩ፣ የማይጣሱና የማይገፈፉ መሆናቸው ከአምስቱ የሕገመንግስቱ መሠረታዊ መርሆዎች መካከል ሆኖ በአንቀጽ 10 ሥር ተደንግጓል፡፡ ሰዎች በልዩ ሁኔታ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ሊታሰሩ የሚችሉ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ብዙውን ጊዜ የሚታሰሩት በወንጀል በመጠርጠር እና ተከስሰው ጥፋተኝነታቸው ሲወሰን ነው፡፡


በመሆኑም ሰዎች የሚታሰሩት በፍርድ ቤት በወንጀል ጥፋተኛ መሆናቸው ከተፈረደ በኋላ ብቻ ሳይሆን በወንጀል ተጠርጥረው በፍርድ ቤት መያዣ ትዕዛዝ በፖሊስ አማካኝነት ሲያዙና ምርመራ ሲደረግባቸው ጭምር ከመሆኑ አንጻር የታሰሩ ሰዎች እስከ ፍርድ ድረስ ዋስትና ተከልክለው በጥበቃ ሥር የሚቆዩትንና በህገመንግስቱ ድንጋጌ መሠረት ንጹህ ሆነው የሚገመቱትን የሚጨምር ነው፡፡


ሕገመንግስቱ የተያዙ ሰዎች መብት፣ የተከሰሱ ሰዎች መብት እና በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች መብት በሚል የደነገጋቸው በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ከታሰሩ ሰዎች መብቶች ጋር የሚገናኙ ናቸው፡፡ በአንቀጽ 21 የተደነገገው የታሰሩ ሰዎች መብቶች ከጽሁፉ መግቢያ የተመለከቱት ሲሆኑ በአንቀጽ 19 እና 20 ሥር ከተደነገጉት መብቶች መካከል ደግሞ የቀረበባቸው ክስና ምክንያቶቹ በዝርዝር ወዲያውኑ እንዲነገራቸው፣ ላለመናገር መብት ያላቸው መሆኑና የሚሰጡት ማንኛውም ቃል ፍርድ ቤት በማስረጃነት ሊቀርብባቸው እንደሚችል እንደተያዙ ወዲያውኑ ማስገንዘቢያ እንዲሰጣቸው፣ በአርባ ስምንት ሰዓታት ውስጥ ፍርድ ቤት የመቅረብ፣ ፍርድ ቤት በልዩ ሁኔታ ካልከለከለ በዋስ የመፈታት፣ ክስ ከቀረበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለሕዝብ ግልጽ በሆነ ችሎት የመሰማትና የተፋጠነ ፍትህ የማግኘት፣ ክሱ በቂ በሆነ ዝርዝር እንዲነገራቸው፣ በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደ ጥፋተኛ ያለመቆጠር፣ የቀረበባቸውን ማናቸውንም ማስረጃ የመመልከት፣ በመረጡት የሕግ ጠበቃ የመወከል ወይም ጠበቃ ለማቆም አቅም በማጣታቸው ፍትሕ ሊጓደል የሚችልበት ሁኔታ ሲያጋጥም ከመንግሥት ጠበቃ የማግኘት፣… መብቶች ያላቸው ስለመሆኑ በዝርዝር ተደንግጓል፡፡
እነዚህ ህገመንግስታዊ (ተከስሰውም ሆነ ሳይከሰሱ) የታሰሩ ሰዎች መብቶች በዝርዝር የሀገራችን ሕግጋትም በተለይ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነሥርዓት ሕጉና በወንጀል ህጉ ጥበቃ ተደርጎላቸዋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ በፌዴራል ፖሊስና በማረሚያ ቤቶች ፖሊስ አባላት መተዳደሪያና የሥነምግባር ደንቦች የእስረኞችን መብቶች የተመለከቱ ድንጋጌዎች ተካትተዋል፡፡ በፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 720/2004 መሠረት በወጣው የፌዴራል ፖሊስ አባላት መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 268/2005 አግባብነት ያላቸው ዝርዝር ድንጋጌዎች መሠረት ለሕገ መንግስቱ ታማኝ መሆን ለፖሊስ ምልመላነት አንድ መመዘኛ መሆኑን ተደንግጓል፡፡ የሥነ-ምግባር መርሆዎች በሚለው አንቀጽ 44 ሥርም ማንኛውም የፖሊስ አባል መከተል ከሚገባው የሥነ-ምግባር መርሆዎች መካከል የሰዎችን ሕጋዊ መብት በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ፣ በፖለቲካዊ አመለካከት፣ በሀብት፣… በማንኛውም ምክንያት አድልዎ ሳያደርግ ህጋዊ መብታቸውን የማክበር እና የማስከበር፣ ህገመንግስቱን፣ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸውን ዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብት ኮንቬንሽኖች እና ሌሎች ሕጎችን ማክበር እና ማስከበር በሚል የተደነገጉት በተለይ በፖሊስ ጥበቃ ሥር ላሉት የታሰሩ ሰዎች መብቶች ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት አላቸው፡፡
በደንቡ አንቀጽ 51 ማንኛውም የፖሊስ አባል ሕግን በመጣስ በሚወስነው ውሳኔ ወይም በሚፈጽመው ድርጊት ምክንያት ለሚያደርሰው ጉዳት ተጠያቂ እንደሚሆን ተደንግጓል፡፡ እንደሚታወሰው መጋቢት 8 ቀን 2005 ዓ.ም በታተመው በሪፖርተር ጋዜጣ እንደተዘገበው የኢፌዲሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በወቅቱ በሶስት ዓመታት ብሔራዊ የሰብዓዊ መብት የድርጊት መርሐግብር ረቂቅ ሰነድ ላይ በተደረገው ውይይት መንግስት ፖሊሶች በሚፈጽሙት ድብደባና የመብት ጥሰት ላይ እርምጃ እወስዳለሁ ማለቱን መሰማቱ በአንድ በኩል የመብት ጥሰቱን አሳሳቢነት የሚያረጋግጥ ሲሆን በሌላ በኩል የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ ዝግጁነት መኖሩ መገለጹ ለታሰሩም ሆነ ላልታሰሩ ዜጎች ለመብቱ መከበር ትልቅ ተስፋ ነው፡፡ በእርግጥም የፍርድ ቤቶቻችን መዝገቦች እንደሚያስረዱት በእስረኞች ላይ የአካል ደህንነትን መብት ጨምሮ የመብት ጥሰት በሚፈጽሙ የፖሊስ አባላት ላይ አልፎ አልፎም ቢሆን ሕጋዊ እርምጃዎች ሲወሰዱ ይስተዋላል፡፡


በፌዴራል ማረሚያ ቤቶች የጥበቃ አባሎች መተዳደሪያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 137/1999 ህግም ለፌዴራል ፖሊስ አባላት ከተደነገጉት ተመሳሳይ የሙያ ሥነምግባር ግዴታዎች ተደንግገዋል፡፡ በህግ ሥርዓታችን ስለ ታራሚዎች አያያዝም የሚመለከት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 138/1999 የወጣ ሕግ አለን፡፡ በዚህ ደንብ መሠረት መሠረታዊ መርሆዎች ተብለው ከተደነገጉት መካከል በጾታ፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በፖለቲካ አመለካከት፣… ልዩነት ያለማድረግ እና የተላለፈባቸው ቅጣት የሚጥለው ገደብ ከሌለ በቀር የታራሚዎች ሰብአዊ ክብራቸው እንዲጠበቅ ማድረግ የሚሉት ይገኙበታል፡፡ በደንቡ ስለ እስረኞች/ታራሚዎች ክፍሎች ማሟላት ስለሚኖርባቸው ሁኔታዎች፣ ስለ ልብስ፣ መኝታ፣ ጽዳት፣ ምግብ፣ ህክምና፣ ከጎብኝዎች ጋር ስለሚደረግ ግንኙነት፣ ስለ መጻጻፍ፣ ትምህርትና ሥልጠና፣ ምክር አገልግሎት፣ መረጃ የማግኘት መብት… እና ሌሎች ዝርዝር መብቶች ተደንግገዋል፡፡


የታሰሩ ሰዎች መብቶች ሀገራችን በተቀበለቻቸው ዓለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ስምምነቶችም ተደንግገዋል፡፡ ለምሳሌ በሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን መብቶቹ በዝርዝር ተደንግገዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም ከዛሬ 60 ዓመታት በፊት እ.ኤ.አ በ1955 በጄኔቭ ባካሄደው የመጀመሪያ ኮንግረስ ተቀባይነት አግኝቶ እ.ኤ.አ በ1977 ስለ እስረኞች የአያያዝ ደረጃ መደበኛ ደንቦችን አጽድቋል፡፡ በዚህ ሰነድ ውስጥ የተመለከቱት የእስረኞች አያያዝ ደንቦች ከላይ በተጠቀሰው የሀገራችን የታራሚዎች አያያዝን የሚመለከት የሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ጋር ተመሳሳይ ይዘት ያላቸው ናቸው፡፡ በመሆኑም በሀገራችን ከሕገመንግስቱ ጀምሮ የእስረኞችን መብትና አያያዝ የሚመለከቱ ብዙ ዘመናዊ ሕጎች አሉን፡፡ አንዳቸውም ሕግጋት የታሰሩ ሰዎች ሰብአዊ መብቶች እንዲጣሱ አይፈቅዱም፡፡ ሀገራችን በህጉ አፈጻጸም እንጅ በመብቱ ዙሪያ የሕግ ችግር የለባትም ለማለት ይቻላል፡፡
የእስረኞችን መብት አለማክበርና አለማስከበር ወይም መጣስ ሕገመንግስቱን አለማክበርና አለማስከበር ወይም መጣስ ነው፡፡ ሕግን ማክበር የሰውን ልጅ መብት ወይም ሰውን ማክበር ሲሆን የሰውን ልጅ መብት መጣስ ደግሞ ሕግን መጣስ ነው፡፡ የሰውን ልጅ መብቶች በመጣስ ህግን ማክበርና ማስከበር ወይም የሕግ የበላይነትን ማስከበር አይቻልም፡፡ የሕግ የበላይነት ሊከበር የሚችለው ሕጉ ማንኛውም የወንጀልም ሆነ የፍትሐብሔር ሕግ በሕግ መሠረት ብቻ ሲፈጸምና ሲተረጎም ብቻ ነው፡፡ ሰዎች በወንጀል ተጠርጣሪነትም ሆነ የእሥራት ቅጣት ተወስኖባቸው የሚታሰሩት የሕዝብን ወይም የሰዎችን ጥቅምና ሰላም በማስከበር የወንጀል ሕጉን ዓላማ ለማሳካት እንጂ ሌላ ግለሰባዊ ወይም ተቋማዊ ዓላማና ግብ የለውም፡፡ መብቶቹ በመጣሳቸው የሚጠቀም፣ በመከበራቸው ደግሞ የሚጎዳ ወገን የለም፡፡ የመብቶቹ አለመከበር ግን ታሳሪ ዜጎቹን በእጅጉ የሚጎዳና የማይተካ አካላዊና ሥነልቦናዊ ጉዳት ሊያስከትል ይችላል፡፡


የወንጀል ሕግ ዓላማውም በ1997 ዓ.ም በወጣው የኢፌዲሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 1 እንደተደነገገው “ለጠቅላላው ጥቅም ሲባል የአገሪቱን መንግስት፣ የሕዝቦቹን፣ የነዋሪዎቹን፣ ሰላም፣ ደህንነት፣ ሥርዓት፣ መብትና ጥቅም መጠበቅና ማረጋገጥ ነው፡፡” በሚል ተደንግጓል፡፡ በመሆኑም የታሰሩ ሰዎች አያያዛችን ከወንጀል ሕጉ ዓላማ ውጭ እና የታሰሩ ሰዎችን መብት በጣሰ ሁኔታ እስረኞች ሀገሬ እንዲህ ነበረችን፣ ምን ዓይነት ሀገር እየሆንን ነው፣ መታሠር እንዲህ ከቤተሰብ፣ ከጓደኛ፣ ከሕግ አማካሪ… መገናኘት የሚከለከልበት ነውን፣ የፀሐይ ብርሃን የሚከለከልበት ነውን፣ ድብደባና ስቃይ የሚያስከትል ነውን፣ ተገቢው ሕክምና የማይገኝበት ነውን?… የሚሉ የመብት ጥያቄዎች የሚያስነሳና በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተአማኒነትን የሚያሳንስ መሆን አይገባውም፡፡ በተለይ የታሰሩ ሰዎች መብት ጥሰት የሚፈጸመው በጠባቂዎቻቸውና በአስተዳዳሪዎቻቸው በፖሊስ እጅ በሚገኙ እንዲሁም ፍርድ ቤት ቀርበው በምርመራ ላይ ባሉ ወይም በተፈረደባቸው በማረሚያ ቤት በሚገኙ ዜጎች ላይ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ጉዳይ ነው፡፡

 

2. የታሰሩ ሰዎችን መብት ጠባቂው ማን ነው? ጥበቃውስ ከማን ነው?

 

ከአኩሪ የነፃነት ታሪካችን እንደምንማረው ሀገራችንን ከሌሎች ብዙዎቹ የአፍሪካ ሀገራት ልዩ የሚያደርጋት አንዱ መሠረታዊ ነገር ከአምስቱ ዓመት የጣልያን ወረራ በቀር ነጻነቷን የጠበቀች በቅኝ ገዥዎች ያልተገዛች መሆኗ ነው፡፡ በአምስቱ የጠላት ወራራ ዓመታት አባቶቻችን በግፍ ተገድለዋል፣ ታስረዋል፣ ተገርፈዋል፣ በእሳት ተቃጥለዋል፣ በአደባባይ ተሠይፈዋል፣ ተሰልበዋል፣ የእናቶች ጡጣቸው ተቆርጧል…፡፡ እነዚህ ሁሉ የመብት ጥሰቶች በጠላት ተፈጽመውብናል፡፡ ዛሬ መብቶቻችንን የሚጥስ የውጭ ጠላት የለብንም፡፡ ዛሬ በተለይም የታሰሩ ሰዎች መብት የሚጣሰው በራሳችን ዜጎች ሕግንና ሰብአዊ መብትን የማክበርና የማስከበር ኃላፊነት በተጣለባቸው ወገኖች ሲሆን አስከባሪዎቹም ተመሳሳይ ወገኖች ናቸው፡፡ መብቱ እየተጣሰ የሚገኘው በውጭ ሀገር ዜጎችና አካላት ሳይሆን በራሳችን ነው፡፡ መብቱ የሚጣሰው በሕግ ተፈቅዶ ሳይሆን የሕግ ክልከላ ተደርጎበት ነው፡፡ አባቶቻችን ሀገርን በማስከበሩ ተግባር በጀግንነት ለዓለም አርዓያ እንደሆኑ ሁሉ የዛሬው ትውልድ ደግሞ በዓለማችን ለብዙ ነገሮች መለኪያ በሆነው ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችን በማክበሩና አፈጻጸሙ በአርአያነት ሊጠቀስ ይገባዋል!! በሕግ ረገድ ከሌሎች ሀገራት ያነሰና ወደኋላ የቀረን ነን ለማለት አይቻልም፡፡ መሠረታዊ ችግራችን የአመለካከትና የአፈጻጸም ነው፡፡ አፈጻጸሙ ደግሞ በእኛው በሰው ልጆች የሚፈጸም ነው፡፡ የሀገር ገንዘብ ወጪ ሆኖ መማራችንና መሰልጠናችን የዜጎችን መብት በማክበር ተግባራችንን እንድንፈጽም ነው፡፡ የዛሬ የሕግ አውጭ አባል፣ ሕግ አስፈጻሚ፣ መርማሪ ፖሊስ፣ ከሳሽ ዐቃቤ ህግ፣ ፍርድ ሰጭ ዳኛ፣ እሥረኛ ጠባቂ፣ ዳይሬክተር፣… ነገ ዕጣ ፈንታችን አይታወቅም፣ አስበንም ሆነ በቸልተኝነት በፈጸምነው ተግባር ወይም ባልፈጸምነውም ተግባር ቢሆን በተጠርጣሪነት እሥረኞች የመሆን አጋጣሚው ስለሚኖር በማናቸውም ሚና ቢሆን ሥራችንን ሥንሠራ መብቱን በማስከበሩ ሂደት ራሳችንን በተከሳሹ/በእስረኛው/በተጠርጣሪው እግር አቁመን ተግባራችንን በሕጉ መሠረት ልንፈጽም ይገባናል፡፡ መብቱን የማስከበሩ ኃላፊነት ግዑዝ አካል ለሆነው ለመንግሥት ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ ሰብአዊ መብቶችንም ሆነ የሕግ የበላይነትን የማስከበሩ ነገር በግለሰቦች/ተቋማት ግዴታነት ብቻ የሚታይ ሳይሆን ሥርዓት መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ነው በፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 943/2008 በአዋጁ ዓላማ መግለጫ በመግቢያው አዋጁ የወጣበት አንደኛው ምክንያት የመንግሥት ሥራዎች በሕግ መሠረት መመራታቸውን የሚያረጋግጥ እንዲሁም የህግ የበላይነትን የሚያስከብር ተቋም እንደገና ማደራጀት አስፈላጊ መሆኑን የተገለጸው፡፡


ስለ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ማክበርና ማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ በተነሳ ቁጥር ተጠቃሽ በሆነው ድንጋጌ በኢዴዲሪ ሕገመንግስት አንቀጽ 13 መሠረት በማንኛውም ደረጃ የሚገኙ የፌዴራል መንግስትና የክልል ሕግ አውጭ፣ ሕግ አስፈጻሚ እና የዳኝነት አካሎች በህገመንግስቱ የተካተቱትን የሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶችና ድንጋጌዎች የማክበርና የማስከበር ኃላፊነትና ግዴታ ያለባቸው መሆኑን ተደንግጓል፡፡ በዚህም መሠረት በየደረጃው የሚገኙ የፌዴራልና የክልል ፍርድ ቤቶች፣ አስፈጻሚ አካላት፣ የፌዴራል እና የክልል ወይም የከተማ ፖሊስ ኮሚሽኖች፣ ማረሚያ ቤቶች፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ፍትህ ቢሮዎች፣ የሕግ ባለሙያዎችና ማህበራት… የታሰሩ ሰዎችን መብት ጨምሮ ሁሉንም በሕግ ጥበቃ የተደረገላቸውን የሰው ልጆች መብቶች በማክበሩና በማስከበሩ ሂደት ሁላችንም የየራሳችን ድርሻ አለን፡፡ ኃላፊነቱና ባለግዴታነቱ በተቋማቱ ስም ይገለጽ እንጂ በፈጻሚና በአስፈጻሚነት ተጠያቂነቱ የሚያርፈው በየተጠቋማቱ ውስጥ በሚገኙ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ግለሰቦች ላይ ነው፡፡


የታሰሩ ሰዎችም መብት ሆነ ሌሎች መብቶች መከበር ጾታ፣ መደብ፣ ዘር፣ ሙያ፣ የሀብት ደረጃ፣ ሥልጣን፣…. የሚለይ አይደለም፡፡ በደርግ ሥርዓት በግፍ የታሠሩትንና ያለፍርድ የተገደሉትን ባለሥልጣኖችና ባለሃብቶችን ጨምሮ በሀገራችን በቀደሙት የመንግሥት ሥርዓት መለዋወጥ የነበሩትን እሥረኞች ሳንቆጥር፣ በአሁኑ የፌደራል መንግሥት የ25 ዓመታት የፍትህ ታሪክ በፍርድ ቤቶቻችን በተለያዩ ወንጀሎች ክስ ከቀረበባቸው ወይም ከታሰሩ ሰዎች ማንነት አንጻር ናሙና ብንወስድ የደርግ ባለሥልጣናት፣ ጠቅላይ ሚኒስትሮች፣ የክልል መሪዎች፣ ሌሎች ባለሥልጣናት፣ የባንክ ኃላፊዎች፣ ባለሃብቶች፣ መሀንዲሶች፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ ዳኞች፣ ዐቃብያነ ህግ፣ ፖሊሶች፣ መርማሪዎች፣ ፕሮፌሰሮች፣ ሐኪሞች፣ ጋዜጠኞች፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች፣ ወታደራዊ ባለማዕረጎች፣ ሾፌሮች፣… ከሳሾችና ፈራጆች ሳይቀሩ እስረኞች የሆኑበትና የሚሆኑበት አጋጣሚ መኖሩ በግልጽ የታዬ እውነታ ነው፡፡ ይህ እውነታ የሚያስተምረን ነገር የመብት ማክበሩና ማስከበሩ ጉዳይ ዛሬ በእስር ላይ ያሉትንና ቤተሰቦቻቸውን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ዜጎችን የሚመለከት ወሳኝና አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡


በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ሥልጣን ሥር የሚወድቁ ወንጀሎችን በተመለከተ ምርመራ እንዲጀመር ለማድረግ፣ ምርመራው በሕግ መሠረት መከናወኑን ለማረጋገጥ፣ ክስ አቅርቦ ለማስቀጣት… በአጠቃላይ የፌዴራል ሕጎችን የማስፈጸም ሙሉ ሥልጣኑ በአዋጅ ቁጥር 943/2008 አንቀጽ 6 መሠረት ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በዝርዝር መሰጠቱን ተመልክቷል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ በአዋጁ አንቀጽ 5 ሥር የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ እና በሥልጣንና ተግባሩ ድንጋጌ አንቀጽ 6/8/ሐ ሥር በፖሊስ ጣቢያና በማረሚያ ቤት ቁጥጥር ሥር ያሉ ሰዎችን የመጎብኘት፣ አያያዛቸው እና ቆይታቸው በሕግ መሠረት መፈጸሙን የማረጋገጥ፣ ሕገወጥ ተግባር እንዲታረም እንዲሁም ሕግን ተላልፈዋል በተባሉ ሰዎች ላይ በህግ መሠረት እርምጃ ይወስዳል ወይም እንዲወሰድ ያደርጋል… በማለት ሥልጣን ተሰጥቶታል፡፡ ይህም ለፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕጉ የሕግ አስፈጻሚ አካል ወንጀል በመፈጸም የተጠረጠሩ ሰዎችን የመክሰሱንና የማስቀጣቱን ተግባር የታሠሩ ሰዎችን መብቶችን ከማስከበሩ ተግባር ጋር ጎን ለጎን የማስኬድ ኃላፊነት እንዳለበት ስለሚያስገነዝብ የታሠሩ ሰዎች መብት ጉዳይ ልዩ ትኩረት የሚሻ ነው፡፡


በእርግጥም የመብቱን ማክበርና ማስከበር ጉዳይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ መሥሪያ ቤትን ወይም ዐቃብያነ ህግን ብቻ ሳይሆን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በዋናነት እስረኞቹ በጥበቃቸው ሥር ያሉ መርማሪዎችና ሌሎች የፖሊስ አባላት፣ የእስራት ትዕዛዞች የሚሰጡና ክርክሩን የሚሰሙ ዳኞች፣ ጠበቆች፣ ጋዜጠኞች፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ሠራተኞች፣ ተመራማሪዎች፣ ሌሎች ባለሙያዎች፣ የሚመለከታቸው ሲሆን ሌሎችም ዜጎች ቢያንስ ስለ ጉዳዩ መረጃና ጥቆማ ለሚመለከተው አካል በመስጠትና የአመለካከት ለውጥ እንዲመጣ ግንዛቤ በመፍጠር የየራሳቸው አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል፡፡ ችግሩ የአፈጻጸም ወይም የአመለካከት ነው ሊባል ከሚችል በቀር የህግ፣ የተቋም፣ የበጀት፣ ያለመማር ወይም የሰው ኃይል አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በሀገራችን በየተቋማቱ ያሉት ፖሊሶች፣ መርማሪዎችና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለሙያዎች ሁሉ የሕገመንግስቱን ድንጋጌዎች ጨምሮ ስለ ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብት መሠረታዊ ዕውቀት ያላቸውና በየጊዜውም የግንዛቤ ሥልጠና የሚሰጣቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የመብቶቹ መጣስ ካለማወቅና ከግንዛቤ ጉድለት ነው ለማለት አያስደፍርም፡፡

 
አንድ ሰው ከፍርድ በፊት በወንጀል መከሰሱም ሆነ መታሰሩ ብቻውን ወንጀለኛ አያደርገውም፡፡ በፍርድ ጥፋተኛነቱ እስካልተወሰነበት ድረስ በተከሰሰበት ወንጀል እንደጥፋተኛ ሆኖ ያለመቆጠር ሕገመንግስታዊ መብት ያለው ስለመሆኑ በኢፌዲሪ ሕገመንግሥት አንቀጽ 20/3/ የተደነገገው ሊከበር ይገባዋል፡፡ ከተጠረጠረበትና ከተከሰሰበት ወንጀል ዋስትና ተከልክሎ ለሁለትና ሦስት፣ ከዚያም በላይ ለዓመታት በእስር ቆይቶ በነጻ የሚለቀቅበት ሁኔታም እንዳለ ከግምት መግባት አለበት፡፡ በመሆኑም በፍርድ ሂደት ሳይቀር ከትንሹ እንኳን ብንጀምር በሕግ ተደንግጎም ባይሆን በልማድ የፍትሐብሔር ጉዳይ ተከራካሪ ወገኖች አንቱ እየተባሉ ሲጠሩና ፍርድም በዚሁ አነጋገር ሲጻፍ፣ በወንጀል ጉዳይ ግን ትናንት በክብር የሚጠሩ ባለሥልጣን፣ ባለሃብት፣ ምሁራን፣…. የነበሩና የዕድሜ ባለፀጋ አረጋውያን እስረኞችን ሳይቀር ከእሥረኞች አጃቢ እስከ ዳኛ ክበር በመንሳት አንተና አንቺ ተብሎ የሚጠራበት ሁኔታ ምክንያቱ ተከሳሹን እንደ ወንጀለኛ በመቁጠር ወይስ ሌላ? 
ስለዚህ የታሰሩ ሰዎች በነጻነት የመንቀሳቀስ መብታቸውና አንዳንድ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ መብቶቻቸው ለጊዜው ከሚገደቡ በስተቀር ሰብአዊ ክብራቸውና ሌሎች መብቶቻቸው የህግ ጥበቃ ያላቸው መሆኑ ሊሠመርበት የሚገባ ነው፡፡ የታሰሩ ሰዎች ከመታሰራቸው በፊት ለሀገራቸው አገልግሎት ያበረከቱ፣ በእስር ቤትም ሆነውና ከእስር ከተፈቱ በኋላም በነፃ የተለቀቁትም ወደቀደመ ክብራቸው በመመለስ እንዲሁም ወንጀል መፈጸማቸው ተረጋግጦ የተቀጡትም ቢሆኑ ከጥፋታቸው ታርመው ለሀገራቸው የራሳቸውን አስተዋጽኦ የማበርከት ዕድሉና አቅሙ ያላቸውም ሊሆኑ እንደሚችሉ ሊታሰብ ይገባል፡፡ ስለሆነም ለታሠሩ ሰዎች መብቶች መከበር ሁሉም ባለድርሻ አካል ግዴታውን ሊወጣ ይገባል እንላለን፡፡

 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ዘመን ሲለወጥ ያልተለወጡት ድንጋጌዎች
ጣዕም መቀየሪያዎች የተጨመሩባቸው የሺሻ ትምባሆ ምርቶች መስፋፋትና ሕገ ወጥነት

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024