Font size: +
6 minutes reading time (1172 words)

ጣዕም መቀየሪያዎች የተጨመሩባቸው የሺሻ ትምባሆ ምርቶች መስፋፋትና ሕገ ወጥነት

በኅብረተሰብ ጤና ዘርፍ ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል ለውጥ ካስመዘገቡ አገሮች ተርታ ትመደባለች፡፡ የጤና አገልግሎትን በቀበሌ ደረጃ ለማስፋፋት፣ በተለይም በዝቅተኛ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኘውን የኅብረተሰብ ክፍል ማዕከል ያደረገና በዓለም አቀፍ ደረጃ ዕውቅና የተቸረውን የጤና ኤክስቴንሽን መርሐ ግብር ተግባራዊ በማድረግ፣ የዓለም መንግሥታት ድርጅትን የጤና የሚሊኒየም ግቦችን ለማሳካት ችላለች፡፡ እንደ አብዛኛው ታዳጊ አገሮች ሁሉ ባለፉት ዓመታት የመንግሥት የጤና ፕሮግራሞችና የአጋር ድርጅት ትኩረቶች ውስጥ ወባ፣ ኤችአይቪ/ኤድስና ሳንባ ነቀርሳ የመሳሰሉ ተላላፊ በሽታዎች የመከላከልና ቁጥጥር ሥራ፣ እንዲሁም የሕፃናትና እናቶች ጤናን ማሻሻል በዋናነት ይጠቀሳሉ፡፡ ሆኖም ግን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ የበሽታዎች ሥርጭት ሁኔታ በለውጥ ሒደት ላይ ያለ ሲሆን፣ በተለይም በከተማዎችና በዙሪያቸው ባሉ ሥፍራዎች በመስፋፋት ላይ የሚገኙት የልብ፣ የመተንፈሻ አካላት፣ ስኳርና ካንሰርን የመሳሰሉ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ይጠቀሳሉ፡፡

ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች እየተስፋፉ በመምጣታቸው ምክንያት የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርን የትኩረት አቅጣጫ የሚያሳይ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች መከላከያና መቆጣጠሪያ ብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ስትራቴጂ (National Strategic Action Plan (NSAP) for Prevention & Control of Non Communicable Diseases in Ethiopia) በ2007 ዓ.ም. ተዘጋጅቷል፡፡ ለእነዚህ በሽታዎች ወይም የጤና ሁኔታዎች ዋነኛ ምክንያቶች ተብለው ከተለዩት መካከልም ማንኛውንም ዓይነት የትምባሆ ምርት መጠቀም፣ ከመጠን በላይ የአልኮል መጠጦችን መውሰድ፣ በቂ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግና ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ምግቦችን ማዘውተር ይጠቀሳሉ፡፡

ከብሔራዊ የድርጊት መርሐ ግብር ስትራቴጂው በተጨማሪ በተመሳሳይ ዓመት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለተላላፊ ላልሆኑ በሽታዎች አጋላጭ ከሚባሉት ዋነኛ መንስዔዎች አንዱ የሆነውን የትምባሆ ምርትን በሚመለከት፣ በዓለም የጤና ድርጅት የወጣውን የትምባሆ ምርት ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን አፅድቋል፡፡ ተግባራዊነቱን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን እንዲከታተል ኃላፊነት በአዋጅ ቁጥር 822/2007 ሰጥቷል፡፡

በዚህ አዋጅ መሠረት የትምባሆ ምርት ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን ማፅደቂያ በከፊል ለማስፈጸም ባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ከሁለት ዓመት በፊት የትምባሆ ቁጥጥር መመርያ አውጥቷል፡፡ የትምባሆ ቁጥጥር መመርያው ከአፈጻጸም ጋር በተያያዘ የተለያዩ ክፍተቶች ቢኖሩበትም፣ ሕፃናትንና ታዳጊ ወጣቶችን በእጅጉ ሱስ አስያዥ የሆነው ኒኮቲክ ለሚባለው ንጥረ ነገር ተጋላጭነት ለመቀነስና ብዛት ባላቸው አገሮች እያደገ በመጣው የትምባሆን ምርት ጣዕም መቀየሪያ እንዳይጨመርበት በመከልከል፣ ሊመሰገን የሚገባው የሕግ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡ ተመሳሳይ የሆኑ ድንጋጌዎች የያዘ የትምባሆ ምርት ቁጥጥርን መመርያ በተወሰኑ ክልሎችና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ጭምርም የወጣ ሲሆን፣ ይህን ዓይነት ምርት በክልሎች ውስጥ ለሽያጭ ማቅረብ፣ መሸጥና ማከፋፈል የተከለከለ ነው፡፡ 

የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለሥልጣን ባወጣው የትምባሆ ምርት ቁጥጥር መመርያ ቁጥር 28/2007 መሠረት፣ የትምባሆ ምርት የሺሻ ትምባሆን ጨምሮ ማንኛውንም በከፊልም ሆነ ሙሉ በሙሉ ከትምባሆ ቅጠል የተዘጋጀ በማጨስ፣ በመሳብ፣ በማኘክ፣ በማሽተት ወይም በሌላ መንገድ የሚወሰድ ንጥረ ነገርን እንዲያካትት ሆኖ ተተርጉሟል፡፡ ይህ ማለት ትምባሆ በስፋት በሚታወቀው የሲጋራ ምርት ብቻ ሳይወሰን የሚታኘክን፣ እንዲሁም የተለያዩ የማጨሻ መሣሪያዎችን በመጠቀም የሚጨስ እንደ ሺሻ ትምባሆ ያለን ምርት ያካትታል፡፡ ይህ የትምባሆ ምርት ትርጉም በተወካዮች ምክር ቤት በፀደቀው የትምባሆ ምርት ቁጥጥር ማዕቀፍ ኮንቬንሽን ጋር የተጣጣመ ሆኖ፣ የሺሻ ትምባሆን ወይም በባህላዊ መንገድ የሚዘጋጅ ጋያን በግልጽ እንዲያካትት ሆኖ ነው የተቀመጠው፡፡

የሺሻ ትምባሆን በትምባሆ ምርት ሥር በግልጽ መቀመጡ ሺሻ ከትምባሆ ምርት የተለየ እንደሆነ ለሚገነዘቡ ሰዎች የግልጽነት ችግር ወይም (የግንዛቤ ክፍተት) እንዳይፈጠር ይረዳል፡፡ ስለዚህ ሲጋራና የሺሻ ትምባሆን ጨምሮ ሌሎች በመመርያው የተካተቱ የትምባሆ ምርቶች ወይም ውጤቶች ሕጋዊ ቢሆኑም፣ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግባቸው ለጤና እጅግ ጎጅ የሆኑ ምርቶች ሲሆኑ እነዚህ ምርቶች ሕገወጥ የሚሆኑበትም አግባብ መመርያው ያስቀምጣል፡፡

ምንም እንኳን የሺሻ ትምባሆ ቁጥጥር የሚደረግበት ለጤና እጅግ አደገኛ የሆነ ሕጋዊ ምርት ቢሆንም፣ ሕገወጥ የሚያደርገውም ሁኔታ በትምባሆ ምርት ቁጥጥር መመርያ ቁጥር 28/2007 አንቀጽ 10 ሥር ተቀምጧል፡፡ በዚህ አንቀጽ መሠረት የሺሻ ትምባሆ ሳይቀጣጠል ወይም በሚጨስበት ጊዜ ከትምባሆ ጣዕም ውጪ እንደ ፍራፍሬ፣ ቸኮሌት፣ ቫኒላ፣ ማር፣ ከረሜላ፣ ካካዎ፣ ሜንቶል፣ ሚንት፣ የአልኮል መጠጥ፣ ዕፅዋት (Herbs) ወይም ቅመም (Spice) የመሳሰሉ የተለየ (Distinguishable) ጣዕም ወይም ቃና የሚሰጥ ይዘት ያለው ከሆነ ሕገወጥ እንደሆነ መመርያው ይደነግጋል፡፡ ይህንን ክልከላ ተፈጻሚ ለማድረግም ማንኛውም ሰው እንደዚህ ዓይነት ተጨማሪ ጣዕም ያለው ምርት (Flavored Tobacco Product) ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ በጅምላ መሸጥ፣ ማከፋፈል፣ መሸጥ ወይም ለመሸጥ ማቅረብ እንደማይችል አስቀምጧል፡፡

በተመሳሳይ ሁኔታ የትምባሆ ምርት ይዘቶች ለጤና የሚጠቅም ወይም ጤና ላይ የሚያስከትልን ጉዳት የሚቀንስ የማስመሰል ውጤት የሚፈጥሩ እንደ ቫይታሚን፣ ፍራፍሬና አትክልቶች፣ አሚኖ አሲድ፣ ጠቃሚ ፋቲ አሲዶችና ኃይልንና ጥንካሬን ከመስጠት ጋር የተያያዙ አነቃቂ ውህዶችን የያዘ የትምባሆ ምርት ወደ አገር ውስጥ ማስገባት፣ በጅምላ መሸጥ፣ ማከፋፈል፣ መሸጥ ወይም ለመሸጥ ማቅረብ እንደማይቻል በሌላ ንዑስ አንቀጽ ሥር ይደነግጋል፡፡ 

የሺሻ ትምባሆን በሚመለከት ሁለት ዋና ዋና የግንዛቤ ክፍተቶች በኅብረተሰቡ ውስጥ ይስተዋላሉ፡፡ እነዚህም ሁሉም የሺሻ ምርቶች በሕግ የተፈቀዱ እንደሆኑና ሺሻ ከትምባሆ የተለየ ምርት እንደሆነ ማሰብ ናቸው፡፡ እነዚህ እሳቤዎች ትክክል አይደሉም፡፡ በመጀመርያ ደረጃ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መዝናኛ ቤቶች፣ እንዲሁም ሕጋዊ ባልሆኑ የሺሻ ማስጨሻ ቤቶች በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው ከትምባሆ ሞላሰስ የሚዘጋጅ የሺሻ ምርት ነው፡፡ ስለዚህ ሺሻ የትምባሆ ምርት አይደለም የሚለው እሳቤ ትክክለኛ ያልሆነ ድምዳሜ ነው፡፡ ይህ ማለት ግን ከትምባሆ ቅጠል ውጪ የሚዘጋጅ ሌላ ዓይነት ሺሻ የለም ማለት አይደለም፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በአሁኑ ጊዜ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ያለው የሺሻ ትምባሆ እንደ ፍራፍሬ፣ ሜንቶልና ሚንት የመሳሰሉ ተጨማሪ ጣዕም የተጨመረበት ምርት በመሆኑ፣ የትምባሆ ቁጥጥር መመርያ ስለሚጥስ ሕገወጥ ነው፡፡

ስለዚህ በዚህ ዓይነት ምርት ላይና ሺሻውን በሚያቀርቡ የመዝናኛ ቤቶች ላይ የሕግ አስፈጻሚ አካላት አግባብ ያለውን ዕርምጃ ለመውሰድ የሕግ መሠረት አላቸው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ የሚስተዋለው የግንዛቤ ችግር ፖሊስና ደንብ አስከባሪዎችን ጨምሮ ሌሎች የሕግ አስፈጻሚ አካላት በሺሻ ቤቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የሕግ መሠረት የላቸውም የሚለው ድምዳሜ ትክክል አይደለም፡፡ ለምሳሌ ከትንሽ ወራት በፊት ‹በታዲያስ አዲስ› የሸገር ሬዲዮ ፕሮግራም ላይ አንድ የሕግ ባለሙያ ቀርበው የባለሥልጣኑን የትምባሆ መመርያን በመጥቀስ የሺሻ ምርቶች ሕጋዊ እንደሆኑ፣ እንዲሁም ፖሊስ በእነዚህ ምርቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ የሕግ መሠረት እንደሌለው የቀረበውና በማኅበራዊ ድረ ገጸች የተሠራጨው የሕግ ትንተና፣ የመመርያውን አንቀጽ 10 ካለማየትና በስፋት በጥቅም ላይ እየዋለ የሚገኘው የሺሻ ምርት ሕጋዊ ያልሆነ ጣዕም የተጨመረበት ምርት እንደሆነ ካለመረዳት የመነጨ ነው፡፡

ተጨማሪ ጣዕም ከሌለው ምርት ጋር ሲነፃፀር ተጨማሪ ጣዕም የሚጨመርበት የትምባሆ ምርት በተለይ ሕፃናትን በእጅጉ እንደሚስብ፣ የበለጠ ሱስ እንደሚያሲዝና ልጆችን በማማለል ለማጨስ እንደሚያነሳሳ በጥናት የታወቀ እውነታ ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች ተጨማሪ ጣዕም የሚሰጡ ነገሮች በተጨመረበት የትምባሆ ምርት ምክንያት፣ ትምባሆ ማጨስ የጀመሩ ከአሥራ ስምንት ዓመታት በታች ያሉ ልጆችን የሚመለከት በተደረጉ የኅብረተሰብ ጤና ቅኝትና ኢፒዲሚዮሎጅ ጥናቶች መሠረት በትምባሆ ምርት ውስጥ እንደ ፍራፍሬ፣ ማር፣ ከረሜላ፣ ካካዎ፣ ሜንቶልና ሚንት የመሳሰሉ ተጨማሪ ጣዕምን መጨመር ምርቶቹ ሳቢ በመሆናቸው ለበለጠ ሱሰኛነት አጋላጭ እንደሚሆኑ ታውቋል፡፡

በእርግጥ የፍራፍሬ፣ ሜንቶል ወይም ሚንት ቃናን የመሳሰሉ ተጨማሪዎች ትምባሆ በሚጨስበት ጊዜ በጉሮሮ ላይ የሚፈጠረው የማይስማማ ስሜት ወይም እንደ ማሳል ያለን የሰውነት ተፈጥሯዊ ምላሽ ስለሚደብቅ ወይም ስለሚቀንስ፣ ለሚያጨሰው ሰው የትምባሆ ጭሱን በቀላሉ ወደ ሳንባ ማስገባት ያስችላል፡፡ ይህ ደግሞ ለሺሻ ትምባሆ አምራቾች የኒኮቲን ጥገኛ የሆነን ወጣት ለመመልመል ዓይነተኛ የሆነ መንገድ ነው፡፡ ልጆችም የትምባሆን ጎጂነት በአግባቡ ከመረዳታቸው በፊት የኒኮቲን ጥገኛ ይሆናሉ፡፡ ጣዕም መቀየሪያዎችን በሺሻ ትምባሆ ውስጥ መጨመር የተከለከለበት ዋነኛ የኅብረተሰብ ጤና ምክንያት ይኼው ነው፡፡ በተለያዩ አገሮች የትምባሆ አምራች ኢንዱስትሪ የወጡ የውስጥ ሰነዶችም እንደሚያሳዩት አምራቾች የትምባሆ ሱሰኛ የሚሆን የወደፊት አጫሽ ወይም ተጠቃሚ ለመፍጠር ታዳጊ ልጆችንና ወጣቶች ላይ ከማነጣጠር ባሻገር ብዙ ዓይነት መንገድ እንደሚከተሉ ይታወቃል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ጣዕም መቀየሪያዎች የተጨመረበት ሕገወጥ የሺሻ ትምባሆ መጠቀም በአዲስ አበባ፣ በአንዳንድ የክልል ከተሞች ባሉ የምሽት መዝናኛ ቤቶች፣ እንዲሁም ሕጋዊ ባልሆኑ የሺሻ ማስጨሻ ቤቶች በስፋት እየታየ ነው፡፡ በእነዚህ ቦታዎች የሚቀርቡ የሺሻ ምርቶች ሁሉም በሚያስብል ሁኔታ በሕግ የተከለከሉ እንደ ፍራፍሬና ሜንት ይዘቶች ያላቸው ምርቶች ከመሆናቸው ባሻገር፣ ወደ አገር ውስጥ የገቡበትም መንገድም ሕጋዊ መንገድ የተከለ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ እነዚህ ምርቶች ሕፃናትን፣ ወጣቶችንና ሴቶችን በተለየ ሁኔታ ሱሰኛ በማድረግ የኒኮቲን ጥገኛ የማድረግ አቅማቸው ጣዕም መቀየሪያዎች ካልተጨመረባቸው የትምባሆ ምርቶች አንፃር ከፍተኛ በመሆኑ፣ የፌዴራልና ክልል አስፈጻሚ አካላትን ትኩረት ይሻል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ጣዕም መቀየሪያዎች በተጨመረባቸው የሺሻ ትምባሆዎች ማጨስ ለጀመረ ወጣት ሲጋራ ለማጨስ በር ከፋች እንደሆኑ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ግማሽ ያህሉ የኢትዮጵያ የሕዝብ ቁጥር ከ15 ዓመታት በታች፣ እንዲሁም ወደ 70 በመቶ ደግሞ ከ30 ዓመታት በታች የሆነ ወጣት እንደመሆኑ መጠን፣ የኅብረተሰብ ጤናን ከማጎልበትና ወጣቶችን ከመጠበቅ አንፃር ከፍተኛ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ በተለይ ፖሊስና የደንብ አስከባሪዎች እነዚህን ምርቶች ለመሰብሰብና በሺሻ ማስጨሻ ቤቶች ላይ ዕርምጃ ለመውሰድ በቂ የሕግ ሥልጣን ስላላቸው አስተዋጽኦ ማድረግ እንደሚችሉ ባለሙያዎች ይስማሙበታል፡፡

ጸሐፊው የማቲዎስ ወንዱ የኢትዮጵያ ካንሰር ሶሳይቲ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ናቸው፡፡ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡ 

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ስለ “የታሰሩ ሰዎች መብቶች” አንዳንድ ነጥቦች
Note on Invalidation of Suspect Transaction under ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024