Font size: +
8 minutes reading time (1682 words)

በክልል የተገደበው የመዘዋወር ነፃነት

1. የመዘዋወር ነፃነት አለም አቀፋዊ አንድምታው

የሰው ልጅ ሰው ሆኖ በመፈጠሩ ከሚያገኛቸው አያሌ የተፈጥሮ መብቶች ውስጥ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት በቀዳሚነት ይጠቀሳል፡፡ የሰው ልጆችን ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ከሐይማኖት፤ ከባህል እና ከሌሎች የተፈጥሮ ህግጋት ጀምርን ስንመለከተው ፅኑ መሰረት ያለው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ በአለማችን ታሪክ ይህ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብት በአንዳንድ የታሪክ አጋጣሚዎች ላይ ተገድቦ የነበረ ቢሆንም በአብዛኛው ግን ሰዎች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብታቸው ሲከበር ቆይቷል፡፡ ይሄንን ተፈጥሮአዊ መብት በመጠቀም የተለያዩ የአውሮፓ ሰዎች አዲስ ግኝትን፤ የመካከለኛውና የሩቅ ምስራቅ ሀገሮች ደግሞ ንግድን በማጧጧፍ ለሀገራቸው እና ለአህጉራቸው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አበርክተዋል፡፡ ይህንን ጥቅም ከግምት ውስጥ በማስገባት እንደ ማግና ካርታ (Magna Carta) አይነት ጥንታዊ ሰነዶች ከቦታ ቦታ የመዘዋወር መብትን አውጀዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በታላቋ ሮም የነገሱ አብዛኛው ነገስታት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነትን ሲያከብሩ መቆየታቸውን የታሪክ ድርሳናት ያስረዳሉ፡፡

ይሁን እንጅ አለማችን በታሪኳ ካጋጠሟት ጠባሳ ታሪክ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የሁለተኛው የአለም ጦርነት እና ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ ከተከሰቱ እጅግ አስከፊ የመብት ጥሰቶች መካከል ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ይጠቀሳል፡፡ አንድ ችግር ሲፈጠር ለችግሩ መፍትሄ መስጠት ወይም መንገድ ማበጀት የሰው ልጅ ተፈጥሮአዊ ባህሪው በመሆኑ በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የተፈጠሩ የመብት ጥሰቶችን በማስመልከት የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደው ነበር፡፡ ከተወሰዱ እርመጃዎች መካከል አለም አቀፍ የሰበዓዊ መብት ተቋማትን መመሰረትና አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ሰነዶችም ማዘጋጀት ይጠቀሳሉ፡፡ በዚህም መሰረት በተቋም ደረጃ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ሲቋቋም በሰብዓዊ መብት ሰነድ ደረጃ ደግሞ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) እና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (International Covenant on Civil and Political Rights) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 13[1] ላይ በግልፅ ለመዘዋወር ነፃነት እውቅና የሰጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀፅ 12 ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ በተለይ ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት በአንቀፅ 12 ላይ በመርህ ደረጃ ይህ መብት ገደቦች የሌሉበት ቢሆንም በልዩ ሁኔታ በህግ በተደነገጉ ቀድመ ሁኔታዎች አማካኝነት ሊገደብ የሚችልበት ሁኔታዎች አሉ፡፡ እነዚህ ሁኔታዎች ከብሔራዊ ደህነት፤ ከህዝብ ሞራል እና ጤና ጋር የሚያያዙ ናቸው፡፡ እነዚህን ቅድመ ሁኔታዎችን መሰረት አድርጎ የሚወጣ ህግ ከአድሎ ነፃ የሆነ እና የትኛውንም ህዝብ በተለይ የሚጎዳበት አግባብ ሊኖር እንደማይገባው ይደነግጋል፡፡ በአጠቃላይ አለማችን አሁን በደረሰችበት የአእምሮ ማሰብ አድማስ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የሰው ልጅ ከተሰጡ መሰረታዊ መብቶች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀስ ከመሆኑ አንፃር የአለማችን የህግ ሰዎችም ሆኑ ፖለቲከኞች በአስፈላጊነቱ ዙሪያ ሙሉ ለሙሉ ይስማማሉ ማለት ይቻላል፡፡ በመሆኑም በአለም አቀፍ የልማዳዊ ህግ መስፈርቶች መሰረት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የአለም አቀፍ የልማድ ህግነት ደረጃ ደርሷል ማለት እንችላለን፡፡ በመሆኑም ማነኛውም ሀገር፤ በሀገር ውስጥ ያለ አስተዳደራዊ ክልል እንዲሁም ማነኛውም መንግስታዊ ያልሆነ ተቋም ይህንን መብት የማክበር እና የማስከበር ግዴታ አለበት፡፡

 

2.  ኢትዮጵያ የመዘዋወር ነፃነትን እንዴት ትመለከተዋለች?

 

የኢትዮጵያን ታሪክ ስንመለከት ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት ከሌሎች መብቶች በተሻለ ሲከበር እንደነበር ማየት እንችላለን፡፡ ከኦሮሞ የጉድፍቻ ባህል ጀምረን እስከ አማራ እና ትግራይ የእንግዳ ተቀባይነት ልማድ ስንመለከት ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ ነፃነት ከህግ አልፎ ህብረተሳባዊ መሰረት እንዳለው እንረዳለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአብዛኛው የኢትዮጵታ ክፍሎች የሚታወቀው “ቤቱ ስትሄድ የሚጮህ ውሻ ብቻ ነው” የሚለው አባባል ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነት የህዝቡ የቆየ ባህል እንደሆነ ያስረዳናል፡፡ በመሆኑም አንድ ማህበረሰብ ለአካባቢው አዲስ የሆነ በተለምዶ አጠራሩ ፀጉረ ልውጥ ወደ ቀየው ሲሄድ የተለየ እንክብካቤ እንደሚደረግለት ለማወቅ የገጠሪቱ ኢትዮጵያን ክፍል አንደ ጊዜ መጎብኘት በቂ ነው፡፡ በተናጠል ከሚደረገው መዘዋወር በተለየ በሀገራችን በተለያዩ የታሪክ አጋጣሚዎች የተነሳ በተከሰቱ የቡድን የህዝብ ዝውውሮች በተሳካ ሁኔታ ተፈፅመው አንዱ ህዝብ ከሌላው ህዝብ ጋር በአሁኑ ሰዓት ለመለየት እስከሚያስቸግር ድረስ ተዋህደው እየኖሩ ይገኛሉ፡፡ይሄንን የኑሮ ዘይቤ በሚያጠናክር ሁኔታ የሚነገር “ሩቅ ካለ ዘመዴ ጎረቤት ያለ ባእድ ይሻለኛል”  የሚለው አባባል እንግዳን ተቀብለው አብረው ከሚኖሩ ህዝቦች በዘለለ በማያውቁት ቀየ በመሄድ ጎጇቸውን የሚቀለሱ ህዝቦች ከሌሎች ህዝቦች ጋር ያላቸውን ተላምዶ የመኖር ባህል ያሳየናል፡፡ በመሆኑም በህግ የተሰጠው ትርጓሜ በቀጣይ የሚታይ ሲሆን በማህበረሳዊ አንድምታው ስናየው በኢትዮጵያ ከቦታ ቦታ የመንቀሳቀስ መብት እንደ ባህል የሚታይ ልማድ ነው፡፡ 

በኢትዮጵያ የመንግስት አስተዳደር የመዘዋወር ነፃነትን ስንመለከተው በሰነድ ማስረጃ የተደገፈ የመዘዋወር ነፃነት የሚገድብ ታሪካዊ ክስተት ለማግኘት ያስቸግራል፡፡ በተቃሪኒው የኢትዮጵያ ያለፉት መንግስታት በተለያዩ በተፈጥሮም ይሁን ሰው ሰራሽ በሆኑ ምክናያቶች ለሚከሰቱ ችግሮች መፍትሄ ለመስጠት አንድን ህዝብ ከአንድ አካባቢ አንስተው ወደ ሌላ አካባቢ መወሰድ የተለመደ አሰራር ሆኖ ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ የመዘዋወር ነፃነትን ወጥ በሆነ መንገድ ተቀብላው እንደቆየች የባህል እና መንግስታዊ አሰራሮች ያስረዱናል፡፡ 

 

3.  የመዘዋወር ነፃነትን የሚመለከቱ ህጎች በአሁኗ ኢትዮጵያ

 

ከላይ የተመለከትነው ታሪካዊ እና ማህበረሰባዊ እውነታ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ ነፍስ ዘርቶ እንዲሄድና ተፈፃሚ እንዲሆን በህግ አግባብ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ይሄንን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በ1983 ዓ.ም ጀምሮ ኢትዮጵያን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው ኢህአዴግ የተለያዩ ህጎችን ሲያወጣ የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ድንጋጌዎችን በማካተት እና የመዘዋወር ነፃነት የሚመለከቱ አለምአቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን በመፈረም የመጀመሪያውን ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ጥረት አድርጓል፡፡ በመሰረቱ የአንድን ሃገር በአንድ ጉዳይ ላይ ያላትን የህግ አቋም ስንመለከት ከሀገሪቱ የበላይ ከሆነው ህግ መጀመር የተለመደ ነው፡፡ በዚህም መሰረት በ1995 ዓ.ም የወጣውን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት ስናየው የመዘዋወር ነፃነትን የሚመለከት ድንጋጌ አካቷል፡፡ {tip title="አንቀጽ 32 - የመዘዋወር ነፃነት" content="1. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመሥረት፣ እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው፡፡
2. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ወደ ሀገሩ የመመለስ መብት አለው፡፡" class="blue"}በህገ-መንግስቱ አንቀፅ 32(1){/tip} መሰረት ማነኛውም ኢትዮጵያዊ ወይም በሕጋዊ መንገድ ሀገሪቱ ውስጥ የሚገኝ የውጭ ዜጋ በመረጠው የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወርና የመኖሪያ ቦታ የመመስረት እንዲሁም በፈለገው ጊዜ ከሀገር የመውጣት ነፃነት አለው፡፡ በዚህ አንቀፅ መሰረት አንድ ኢትዮጵያዊ በመረጠው በየትኛውም የሀገሪቱ አካባቢ የመዘዋወር ነፃነት ሲኖረው ከዚህም በላይ ይህ ግለሰብ በተዘዋወርበት አካባቢ በተመቸው ቦታ ላይ መኖሪያውን መስርቶ የመኖር ነፃነት ተሰጥቶታል፡፡ ከዚህ አንቀፅ ጋር በተያያዘ የሕገ-መንግስቱ ሌላው ድንጋጌ {tip title="አንቀጽ 41 - የኢኮኖሚ፣ የማኀበራዊና የባሕል መብቶች" content="1. ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማንኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመስማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፡፡" class="green"}አንቀፅ 41(1){/tip} እንደሚገልፀው ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ውስጥ በማነኛውም የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ የመሰማራትና ለመተዳደሪያው የመረጠውን ሥራ የመሥራት መብት አለው፡፡ ከዚህ አንቀፅ እንደምንረዳው ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ የትኛውም አካባቢዎች በመሄድ የፈለገውን ስራ በመመረጥ የመስራት መብት እንዳለው ነው፡፡ በመሆኑም በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግስት አንቀፅ 31 እና 41 መሰረት ማነኛውም ኢትዮጵያዊ በራሱ ፈቃድ በመረጠው የትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በመሄድ መኖሪያውን የመመስረት እና በፈለገው ሙያ ላይ የመሰማራት መብት አለው፡፡ ከሕገ-መንግስቱ ድንጋጌዎች ስንወጣ ኢትዮጵያ የፈረመቻቸውን አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች በሕገ-መንግስቱ አንቀፅ 9(4) መሰረት የሀገሪቱ ህግ አካል በመሆናቸው ኢትዮጵያ እነዚህን ስምምነቶች የማክበር ግዴታ አለባት፡፡ ከላይ እንደተመለከትነው የመዘዋወር ነፃነትን በሚመለከት ከወጡ እና ኢትዮጵያ ከፈረመቻቸው አለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ስምምነቶች መካከል ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ (Universal Declaration of Human Rights) እና ዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት (International Covenant on Civil and Political Rights) በቀዳሚነት ይጠቀሳሉ፡፡ የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድንጋጌ በአንቀፅ 13 ላይ በግልፅ ለመዘዋወር ነፃነት እውቅና የሰጠ ሲሆን የዓለም አቀፍ የሲቪልና የፖለቲካ መብቶች ስምምነት ደግሞ በአንቀፅ 12 ላይ ተመሳሳይ ድንጋጌ አስቀምጧል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ በራሷ ተነሳሽነት ካፀደቀችው ሕገ-መንግስት በዘለለ በፈረመችው (ባትፈርመው እንኳን የአለም አቀፍ የልማዳዊ ህግነት ደረጃን በደረሱት) የመዘዋወር ነፃነትን በሚመለከቱት እነዚህን አለም አቀፍ ስምምነቶችን የማክበር ግዴታ አለባት፡፡  

በመርህ ደረጃ አንድ ህግ ሲዎጣ የወጣውን ህግ ተፈፃሚነቱን ለማረጋግጥ እንዲያስችል ህጉ የሰጠውን መብት ጥሰው በተገኙ አካላት ላይ ቅጣት ማስቀመጥ የተለመደ ነው፡፡ በዚህ መሰረት ስንመለከተው የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ማነኛውንም ጥሰት የፈጠረ አካል ላይ የወንጀል ቅጣት እንደሚጠብቀው በ2004 ዓ.ም የወጣው የወንጀል ህግ ያስረዳናል፡፡ በዚህ የወንጀል ህግ አንቀፅ 607 መሰረት ማንም ሰው በሕግ ሥልጣን ሳይኖረው ሌላው ሰው በኢትዮጵያ ውስጥ በነፃ እንዳይዘዋወር የከለከለ እንደሆነ በቀላል እስራት ወይም መቀጮ እንደሚቀጣ በመግለፅ ጥፋቱን የፈፀመው የመንግስት ሰራተኛ ከሆነ ግን ጉዳዩ በአንቀፅ 407 መሰረት እንደሚታይ ይገልፃል፡፡ የወንጀል ህጉ አንቀፅ 407 ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀምን የሚመለከት ሲሆን እንደቀረበው ጉዳይ ቅጣቱ ከአንድ አመት እስከ 15 ዓመት ከባድ ቅጣት ሊደርስ ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ እንደቀረበው ማስረጃና ጉዳዩ ከተፈፀመበት ሁኔታ አንፃር ጉዳዩን ዘር ማጥፋትን ወደ ሚመለከተው አንቀፅ 269 (ሐ) መሰረት የሚታይበት የህግ አግባብ ተቀምጧል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ሰዓት ባለው የኢትዮጵያ ህግ አንፃር የመዘዋወር ነፃነት በህግ ሙሉ ለሙሉ እውቅና የተሰጠው ሲሆን ከዚህ በተጨማሪም ይሄንን ነፃነት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መገደብ ከቀላል እስራት እስከ ሞት ድረስ የሚያስቀጣ የወንጀል ሃላፊነትን ያስከትላል፡፡

 

4. በክልል የተገደበው የመዘዋወር ነፃነት

 

የአለም አቀፍ ህግ ሙህራን አንድ ሃገር ሰብዓዊ መብቶችን ለማክበር የሚጠበቅባትን ደረጃዎች ያስቀምጣሉ፡፡ ከእነዚህ ደረጃዎች ውስጥ በቀዳሚነት የሚጠቀሰው የህግ ማእቀፍ መዘርጋት ሲሆን ከዚህ በመቀጠል ግን ተቋማትን መመስረትና ሌሎች የወጣውን ህግ የሚያስፈፅሙ እርምጃዎች መውሰድ ከብዙ በጥቂቱ ይጠቀሳሉ፡፡ ህግ ማውጣት የሚያወሩትን ላውራ (talking the talk) የሚባል ዋስትና የሌለው እርምጃ በመሆኑ ሌሎች የወጣውን ህግ በትክክል የሚያስተገብሩ እርምጃዎች (walking the talk) መውሰድ በአለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ዘንድ ትኩረት ሲሰጥበት ቆይቷል፡፡ሐገራችን ኢትዮጵያ ከቀድሞ መንግስታት ጀምሮ እስከአሁን ድረስ አለም አቀፍ ስምምነቶችን የመፈረም ችግር ሳይታይባት ቆይቷል፡፡ ይሁን እንጅ በየጊዜው ከሚከሰቱ ችግሮች እንደምንረዳው እነዚህ የሚዎጡ ህጎችና የሚፈረሙ ስምምነቶች በተለይ በአስፈፃሚ አካላት ተነበው የማያውቁ በአልፎ ሂያጅ ብቻ ለትምህርትነት የሚያገለግሉ ሰነዶች ሁነው ቆይተዋል፡፡ የመዘዋወር ነፃነትን በተመለከተ ጉዳዩን ይበልጥ የሚያወሳሰብ እና ከላይ ያየናቸውን የወግ እና የባህል ሁኔታዎችን ጥያቄ ውስጥ ባስገባ መልኩ መከሰት የጀመረው የመብት ጥሰት በተለይም ሀገሪቱ የፌደራል ስርዓትን መከተል ጀምሬያለሁ ባለች ማግስት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ሁሉም አካባቢዎች በቋንቋ እና በተለያዩ ማንነቶች መሰረት በክልል ከመከፋፈላቸው ጋር ተያይዞ በተለያየ አጋጣሚዎች የመዘዋወር ነፃነት ትልቅ እክል ሲገጥመው ቆይቷል፡፡ በተለይም የአማራ ብሔር ተወላጅ የሆኑ ሰዎች ከ1983 ዓ.ም ጀምሮ ከአብዛኛው የሃገሪቱ አካባቢ ቤት ንብረታቸው እየተቀማና እየተቃጠለ፤ አለፍ ሲልም ህፃናትና አዛውንት ሳይቀሩ ሲገደሉ እና ሲፈናቀሉ መቆየታቸውን በተለያዩ አጋጣሚዎች መረጃዎች ቀረበው ተሸፋፍነው አልፈዋል፡፡ ይህ የአማራ ተወላጆች ላይ ብቻ ሲፈፀም የነበረው የመፈናቀል እና የመዘዋወር ነፃነትን የመነጠቅ ድርጊት ባለፉት አራት እና አምስት አመታት አድማሱን አስፍቶ በኦሮሞ እና በትግራይ ተወላጆች ላይም ተፈፅሟል፡፡ ይሁን እንጅ በአማራ ብሔር ተወላጆች ላይ የሚፈፀመው የመፈናቀል እና የመዘዋወር ነፃነትን የመነጠቅ ወንጀል እንደሌሎች ሁሉ በጊዜ እና በቦታ የተገደበ እና ጊዜያዊ አለመሆኑን በዚህ አመት ተፈፀሙትን ሁነቶች ብቻ መመልከት ይበቃናል፡፡ በተለይ ከሰሞኑን ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በቦሎ ዲዴሳ ቀበሌ መስተዳደር ተፃፈ ተብሎ የተሰራጨውን ደብዳቤ እና ከክልሉ ተፈናቅለው ባህርዳር የሚገኙትን ህፃናት፤ አዛውንቶች እና ሴቶችን ስንመለከት ጉዳዩ በቶሎ የህግ እርማት ካልተሰጠው ለሃገሪቱ ህልውናን የሚፈታተን ሁኔታ ይፈጥራል፡፡ የፁሁፉ አላማ አይደለም እንጅ የተለያዩ በሀገሪቱ በግልፅ የተፈፀሙ የመንቀሳቀስ መብትን የሚጥሱ ሁኔታዎችን መዘርዘር ይቻል ነበር፡፡

በመሆኑም ሀገሪቱን የሚያስተዳድራት አካል የሚከተሉትን ጥያቄዎች ተመልክቶ አስፈላጊውን መልስ በመስጠት መፍትሄ ማምጣት ይኖርበታል፡፡ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግስት አንድ ግለሰብ ከሚኖርበት አካባቢ ወደ ሌላ አካባቢ ሄዶ እንዳይሰራ በሚከለክል መልኩ በክልል መስተዳድሮች የማፈናቀል ስራ ሲሰራ በተዘረጋው የህግ ማእቀፍ አማካኝነት አጥፊዎች ወደ ህግ እንዲይቀርቡ የማይደረግበት ምክናያት ምንድን ነው? በተለይም የክልል መስተዳድሮች በክልል የመስራት መብትን ለዚህ ክልል ተወላጅ ብቻ በመቁጠር የተለያየ ግፎችን እና ወንጀል ሲሰሩ ጉዳዩ የሚመለከተው አቃቤ ህግ ለምን ዝምታን መረጠ? እነዚህን ጉዳዮች እልባት ይሰጣሉ ተብለው የተቀመጡት የሕገ-መንግስቱና የወንጀል ህጉ ድንጋጌዎች በዳኞችችን ተነበው በአጥፊዎች ላይ የሚበየኑት መቸ ይሆን? በተለይም በአሁኑ ሰዓት እንኳን መፈናቀልን የሰፈር ፀብን በተለያየ ማስረጃ በሚያዝበት ወቅት የማስረጃ ጥያቄ እንደ ችግር ሊነሳ አይችልም፡፡ እንደዛ ከሆነ በሽህዎች የሚቆጠሩ ወጣቶችን በሽብርተኘነት የሚከስ አቃቢ ህግ እንዴት በግልፅ ወንጀል የሰራን የክልል ባለስልጣን ለመጠየቅ ወኔ አጣ? የትላንት አምራች ዜጎች ዛሬ ተፈናቅለው ሸራ ዘርግተው በየጎዳናው የወደቁ ለማን አቤት ይበሉ? በተለያዩ የማህበራዊ ድረገፆች የሚታዩ ማስረጃዎችን እንደ በቂ ጥርጣሬ በመውሰድ ምርመራ ለመጀመር የሚስችለውን የፖሊስ ወኔ ማን ሰለበው? በአጠቃላይ ጥያቄው ህግ ይከበር ነው! ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ስራቸውን ይስሩ! ወንጀለኞች ወደ ህግ ይቅረቡ፡፡ አሁንም በዙ ነፍሶች መልስን ይሻሉ፡፡ ጉዳዩን በተዳፈነ ቁጥር እያበጠ ስለሚሄድ አላስፈላጊ ነገር ውስጥ እየተገባ ነው፡፡  

 

በህዝቦቿ እኩልነት የምታምን ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!   

 

[1](1) Everyone has the right to freedom of movement and residence within the borders of each State. (2) Everyone has the right to leave any country, including his own, and to return to his country.

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የንግድ ፈቃድን ማከራየት በወንጀል ያስቀጣል?
ተደራሽ ግን ርካሽ ዳኝነት - የኦሮሚያ ወረዳ ፍርድ ቤቶች ምልከታ
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024