Font size: +
9 minutes reading time (1722 words)
Featured

ስለ ይርጋ ጥቂት ነጥቦች

ይርጋ ምንድን ነው? ይርጋ ዓላማው (ጠቀሜታው) ምንድን ነው? ይርጋ ጉዳቱስ ምንድን ነው? ይርጋ የሚያስጠብቀው የማንን መብት ነው? የይርጋ መሠረታዊ መርሆዎች ምንድን ናቸው? ይርጋን የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች ምን ይመስላሉ? በይርጋ የማይታገዱ ጉዳዮች ምንድን ናቸው? የሚሉና ሌሎች ተያያዥ ነጥቦች በዚህ ጽሑፍ ይዳሰሳሉ፡፡

የይርጋ ምንነት

ይርጋ የሚለው ቃል መነሻውረጋከሚለው የአማርኛ ቃል ጋር የተያያዘ ሲሆንረጋየሚለውን ቃል ደራሲ ተሠማ ኃብተ ሚካኤልከሠቴ ብርሀን ተሰማበተሰኘውና 2002 .. በድጋሚ ባሳተሙት የአማርኛ መዝገበ ቃላት ላይየሰው ሀሳቡ ከመውጣት ከመውረድ በሀሳብ ከመዞር ከመባከን ከመናወጥ ጠጥ (ፀጥ) አለበሚል ትርጓሜ ተሠጥቶታል፡፡ ከዚህ በመነሳትም ይርጋ የሚለውን ቃል በአንድ ጉዳይ ላይ ክስ የማቅረብ ወይም መብት የመጠየቅ ጉዳይን አስመልክቶ በጉዳዩ ላይ ክስ የሚያቀርብበት ሰው ስለጉዳዩ ያለውን ሀሳብ ከመውጣት ከመውረድ በሀሳብ ከመዞርና ከመባከን ከመናወጥ ከረጋ (ፀጥ) ካለ በኋላ ሊከሰስ ወይም ሊጠየቅ እንደማይገባ ያመለክታል በሚል ልንወስደው እንችላለን፡፡ በሌሎች ፅሁፎች ላይም ይርጋ ማለት አንድ መብቱ ወይም ጥቅሙ የተነካበት ሰው በሌላ ሰው ላይ ክስ፣ አቤቱታ ወይም የይገባኛል ጥያቄ እንዲያቀርብ በሕግ ተለይቶ የተቀመጠ የክስ (አቤቱታ) ማቅረቢያ ጊዜ ነው፡፡ በሕግ የተቀመጠው የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ካለፈ በኋላም በዚያው ጉዳይ ላይ በጣም በውስንና ጥቂት ምክንያቶች ካልሆነ በስተቀር ክስ የማቅረብ መብት ቀሪ ይሆናል፡፡

የይርጋ አስፈላጊነት/ጠቀሜታው/ እና ጉዳቱ

የይርጋ ፅንሰ ሃሳብ እንዲኖር ያስፈለገበት ሶስት መሠረታዊ ምክንያቶች እንዳሉ በተለያዩ ፅሁፎች ላይ ተመልክቷል፡፡ እነርሱም፡-

/ ከሳሽ በተገቢ ትጋትና በቂ ምክንያት መብቱን እንዲጠይቅ ለማስቻል፤   

) ተከሳሽ በጣም ዘግይተው የሚመጡ ክሶችን ለመከላከል ማስረጃዎች እንዳያጣ ለማድረግ፤ እና

) እጅግ ዘግይተው የሚቀርቡ ክሶችና አቤቱታዎች ፍትህ ከማስገኘት ይልቅ በጭካኔ ለማጥቂያ መሳሪያነት ስለሚውሉ ይህንኑ ለመከላከል ስለመሆኑ ይርጋን አስመልክቶ በተፃፉ በርካታ ፅሁፎች ላይ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም የይርጋ ፅንሰ ሃሳብ በሕግ ስርዓት ውስጥ መካተቱ ጠቀሜታው ለተከሳሽ ወገን ነው፡፡ ምክንያቱም ክስ የማቅረቢያ ጊዜ ካለፈ በኋላ ክስ የቀረበበት ተከሳሽ በኃላፊነት ተጠያቂ ሊሆን አይችልምና ነው፡፡

የይርጋ ፅንሰ ሃሳብ በሕግ ስርዓት ውስጥ መካተቱ ተከሳሹን የሚጠቅመውን ያህል በአንፃሩ የፅንሰ ሃሳቡ መኖር መብት ጠያቂውን ወይም ከሳሹን በእጅጉ የሚጎዳ ነው፡፡ በይርጋ ጊዜያት መለያየት፣ ትክክለኛ የይርጋ ጊዜን ባለማወቅ፣ ሕግን ባለማወቅ እንዲሁም በቸልተኝነት የሕግ ድጋፍና በቂ ማስረጃ እያላቸው በርካቶች መብታቸውን አጥተዋል በርካታ ክሶችም በይርጋ ምክንያት ውድቅ ተደርገው በርካታ መዛግብት ተዘግተዋል፡፡ ክስ አቅርቦ መብትን ለመጠየቅ የሚያስችል በቂ ማስረጃ እና የሕግ ድጋፍ እያለ ተከሳሽን ለመጥቀም ሲባል የይርጋ ፅንሰ ሀሳብ በሕግ ድጋፍ ተሠጥቶት በመካተቱ በርካታ መብት ጠያቂዎችን መብት አሳጥቶ ሕግ ተላላፊዎችን ከኃላፊነት ተጠያቂነት ነፃ ማውጣቱ የማይዋጥላቸው በርካቶች ቢኖሩም የይርጋ ጽንሰ ሃሳብ በመላው ዓለም በስፋት ተቀባይነት ያገኘ የሕግ ፅንሰ ሀሳብ ሆኗል፡፡

ይርጋን አስመልክቶ የሚነሱ መሠረታዊ ነጥቦች

ይርጋን አስመልክቶ በህጎች ውስጥ የሚካተቱ ድንጋጌዎችም ሁሉም ጉዳዮች ተመሳሳይ የይርጋ ጊዜ የሌላቸው በመሆኑ በጉዳዮች ላይ ክስ የማቅረብ መብት በይርጋ የሚታገድ ስለመሆን አለመሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ጉዳይ ክስ ለማቅረብ የተቀመጠውን ጊዜ፣ የይርጋ ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ከመቼ ጀምሮ እንደሆነ፣ እንደየጉዳዩ ባህሪ በህጉ የተመለከተውን የይርጋ ጊዜ ባለጉዳዮቹ ሊያሻሽሉት የሚችሉት ስለመሆን አለመሆኑ፣ በሕግ የተቀመጠው የይርጋ ጊዜ ሊቋርጥ የሚቻልባቸውን ምክንያቶች እና እንደጉዳዩ ዓይነት ሌሎች ተያያዥ ነጥቦችን መዳሰስ ይጠበቅበታል፡፡

ክስ ለማቅረብ የሚቀመጡ የይርጋ የጊዜያት

ይርጋን አስመልክቶ በሕግ ውስጥ የሚካተቱ ድንጋጌዎች በዋናነት የሚያመላክቱት ክስ ለማቅረብ ወይም መብት ለመጠየቅ የሚቻልበትን የጊዜ ገደብ ነው፡፡ ክስ ለማቅረብ ወይም መብት ለመጠየቅ እንዲቻል በሕግ የሚቀመጠው የጊዜ ገደብም እንደጉዳዩ ክብደት፣ ባሕሪና ሁኔታ የተለያየ ሲሆን ለሁሉም ጉዳዮች የተቀመጠ ተመሣሣይ የክስ ማቅረቢያ ወይም መብት የመጠየቂያ ጊዜ የለም፡፡ በመሆኑም ሕግ አውጪው እንደ ጉዳዩ ዓይነት በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ክስ ለማቅረብ ወይም መብት ለመጠየቅ እንደሚቻል የተለያዩ የክስ ማቅረቢያ ጊዜያት በሕጎች ውስጥ ተካተዋል፡፡

የይርጋ ጊዜ መቆጠር ስለሚጀመርበት ሁኔታ

ክስ የማቅረቢያ ወይም መብት የመጠየቂያ ጊዜ መጠን በሕግ ውስጥ ከተካተተ በኋላ በመቀጠል ሊካተት የሚገባው የተቀመጠው የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ከመቼ ወይም ከምን ሁኔታ ጀምሮ መቆጠር እንደሚጀምር ማመልከት ነው፡፡ ለምሳሌ በንግድ ሕግ ቁጥር 674 (1) ላይ በኢንሹራንስ ውል ምክንያት የሚቀርብ ክስ መቅረብ ያለበት በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መሆኑን ያመለክትና የይርጋ ጊዜው መቆጠር የሚጀምረው ለክሱ ምክንያት የሆነው ጉዳት ከደረሰበት ቀን ጀምሮ ወይም በጉዳዩ ጥቅም ያላቸው ወገኖች ጉዳቱን ካወቁበት ቀን ጀምሮ መሆን እንዳለበት መገለፁ እንደጥሩ ምሳሌ ሊወሰድ ይችላል፡፡

በሕግ የተቀመጠ የይርጋ ጊዜ ስለሚሻሻልበት ሁኔታ

በሕግ ላይ የሚቀመጠ ክስ የማቅረቢያ ወይም መብት የመጠየቂያ ጊዜ እንደ ጉዳዩ እና ሕጉ ልዩ ባህሪ በሚመለከታቸው አካላት በውል ሊያጥር ወይም ሊረዝም ስለሚችልበት ሁኔታ ሊካተት ይችላል፡፡ በህጉ የተቀመጠ የይርጋ ጊዜን ማሻሻል እንደሚቻል ወይም እንደማይቻል በህጉ ማመላከት ተዋዋይ ወገኖች ወይም ሌሎች የሚመለከታቸው ወገኖች ይርጋን አስመልክቶ ተጨማሪ መብት እንዳላቸው ወይም እንደሌላቸው ከማስገንዘብ ባለፈ መብቱ በሕግ ከተሰጠ በሚያመች መልኩ የይርጋ ጊዜን የማሻሻል ዕድል የሚሰጥ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ የንግድ ሕጉ አንቀጽ 674 (3) በኢንሹራንስ ውል ምክንያት የሚቀርብ ማንኛውም ክስ በሁለት ዓመት ጊዜ ውስጥ መቅረብ አለበት የሚለው በአንቀፁ ንዑስ ቁጥር አንድ የተመለከተውን የይርጋ ጊዜ ተዋዋይ ወገኖች በውል ለማሣጠር እንደማይችሉ የተከለከለ መሆኑ እና በተግባር የኢንሹራንስ ጉዳዮችን አስመልክቶ በሕጉ የተመለከተው የሁለት ዓመት የይርጋ ጊዜ በተዋዋይ ወገኖች በውል የሚራዘምበት ሁኔታ መኖሩ እንደምሳሌ ሊወስድ የሚችል ነው፡፡

የይርጋ ጊዜ ስለሚቋረጥበት ሁኔታ

በሕግ ላይ የሚቀመጥ ክስ የማቅረቢያ ወይም መብት የመጠበቂያ ጊዜ ሊቋረጥና የይርጋ ጊዜ አቆጣጠር እንደ አዲስ ሊጀመር የሚችልባቸው ሁኔታዎች ሌላው ከይርጋ ጋር ተያይዞ የሚካተት ፅንሰ ሃሳብ ነው፡፡ ክስ ለማቅረብ ወይም መብት ለመጠየቅ በህጉ የተቀመጠ ጊዜ ካለፈ በኋላም ቢሆን ክስ ለማቅረብና ለማስወሰን ከሚያስችሉ ከሳሽ የሆነ ወይም መብት ጠያቂ ወገንን ከሚጠቅሙ የይርጋ መርሆች አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1845 ላይ ውል እንዲፈጸም ወይም ካለመፈፀሙ የተነሳ ስለሚደርስ ጉዳት ወይም ውሉ እንዲፈርስ የመጠየቅ መብት በአስር ዓመት ጊዜ ውስጥ ሊጠየቅ እንደሚገባ የሚያመለክት ሲሆን በቁጥር 1851 እና 1852 መሰረት በአስር ዓመት ጊዜው ውስጥ ለምሳሌ በዘጠነኛው አመት ላይ ባለዕዳው ዕዳውን ካመነ፣ በከፊል ከከፈለ፣ መያዣ ወይም ዋስ ከሠጠ ወይም ባለገንዘቡ መብቱ እንዲታወቅለት ለፍርድ ቤት ክስ አቅርቦ ለባለዕዳው አስታውቆ እንደሆነ ይርጋው ሊቋርጥ እንደሚችልና ከተቋረጠበት ጊዜ ጀምሮ እንደገና እንደ አዲስ የይርጋ ዘመን መቆጠር እንደሚጀመር በግልፅ የተመለከተ መሆኑን በማሳያነት መወሰድ ይችላል፡፡

የይርጋ መከራከሪያን ሊያነሳ የሚችለው ማን ነው?

በፍትሐብሔር ጉዳይ ላይ የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕጉ ቁጥር 244 (2) ላይ ይርጋን ጨምሮ የሚቀርቡ ሌሎች የክስ መቃወሚያ ምክንያቶችን ተከራካሪ ወገኖች ሊያቀርቡ ይችላሉ በሚል የሚያስቀምጥ ቢሆንም ከተለመደው አሰራርና ሁኔታ ለመመልከት እንደሚቻለው ይርጋን በመቃወሚያት የሚያቀርበው ክስ የቀረበበት ወገን (ተከሳሽ) ነው፡፡ ምክንያቱም ከሳሽ የሆነ ወገን የሚያቀርበው ክስ በይርጋ የሚታለፍ ቢሆንበት እንኳን በራሱ ጊዜ ሊያነሳና የራሱን ክስ ውድቅ ሊያስደርግ ስለማይችል በፍትሐብሔር ጉዳይ ከሳሽ የሆነ ወገን ይርጋን በመከራከሪያነት ሊያነሳ የሚችለው በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 236 መሰረት ከተከሳሽ ወገን የተከሳሽ ከሳሽ ክስ ከቀረበበት ብቻ ነው፡፡

በወንጀል ጉዳይ ላይ ይርጋን በመቃወሚያነት አንስቶ ለመከራከር የሚችለው ተከሳሽ ዐቃቤ ሕግና ፍርድ ቤቶች ስለመሆናቸው በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ አንቀጽ 130 እና በወንጀል ሕግ 216 (2) ላይ ተመልክቷል፡፡

ፍርድ ቤቶችን በተመለከተ በተከራካሪ ወገኖች በኩል ይርጋ በመከራከሪያነት ካልቀረበ ፍርድ ቤቶች በራሳቸው ይርጋን እንደ አንድ የመከራከሪያ ወይም የክርክር ነጥብ አንስተው ሊመረምሩ ይችላሉ ወይ? የሚለው ነጥብ ተያይዞ ሊነሳ የሚገባው ነው፡፡

የፍትሐብሔር ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶችን በተመለከተ ሊወስኑና ዳኝነት ሊሰጡ የሚገባቸው በተከራካሪ ወገኖች በተነሱና ዳኝነት በተጠየቀባቸው ነጥቦች ላይ ብቻ በመሆኑ እንዲሁም በፍትሐብሔር ሕጉ ቁጥር 1856 (2) ሥር ዳኞች በገዛ ሥልጣናቸው የይርጋውን ደንብ መከላከያ ለመጥቀስ አይችሉም በሚል የተመለከተ በመሆኑ የፍትሐብሔር ጉዳዮችን የሚመለከቱ ፍርድ ቤቶች የይርጋ መከራከሪያ በተከራካሪ ወገኖች ካልተነሳ ፍርድ ቤቶች በራሳቸው ጊዜ ይርጋን በመከላከያነት ሊያነሱና ሊወስኑ አይችሉም፡፡

የወንጀል ጉዳዮችን የሚመለከቱ ችሎቶችን በተመለከተ እንደ ፍትሐብሔር ችሎቶች ይርጋ በተከራካሪ ወገኖች በመከራከሪያነት ባይነሳም ፍርድ ቤቶች በማንኛውም ጊዜ ክሱ በይርጋ ስለመታገዱ አንስተው ጉዳዩን ሊያዩ እንደሚገባ በወንጀል ህጉ አንቀጽ 216 (2) ላይ ተመልክቷል፡፡                         

በወንጀል ጉዳዮች ላይም ዐቃቤ ሕግ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ እና አሁን ባለው አሠራር መሠረት ምርመራ በሚጣራበት ወቅት እንዲሁም በምርመራ መዝገቡ ላይ ሕጋዊ አስተያየትና ውሳኔ በሚሠጥበት ወቅት ጉዳዩ በይርጋ የሚታገድ ስለመሆን አለመሆኑ የመመልከትና ጉዳዩ በይርጋ የሚታገድ ከሆነም በይርጋ ምክንያት ክስ አያስቀርብም በሚል መዝገቡን የመዝጋት ኃላፊነት እንዳለበት የወንጀል ሕጉ አንቀጽ 216 (2) ያመለክታል፡፡ 

ይርጋ በመከራከሪያነት የሚነሳው መቼ ነው?

በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ተከራካሪ (ተከሳሽ) ይርጋን በመቃዋሚነት አንስቶ ለመከራከር የሚችለው በፍ///// 234 መሰረት ለቀረበው ክስ (አቤቱታ) የመከላከያ መልስ በጽሑፍ ሲሰጥ መሆን እንዳለበት እንዲሁም በወንጀል ጉዳይ ላይ ተከሳሽ ለፍርድ ቤቱ ማንነቱን ካስመዘገበና ክስ ከተነበበለት በኋላ ይኼውም በፍሬ ጉዳዩ ላይ ክስና መከራከሪያ ከመቅረቡ ማስረጃም ከመሠማቱ በፊት እንደሆነ በሕግጋቱ ተመልክቷል፡፡ በመሆኑም ይርጋን በመከራከሪያነት ማቅረብ የሚቻለው ክስ ከመሰማቱ እና ለክሱ ምክንያት የሆነው ነገር በተከሳሽ በኩል ተፈፅሟል አልተፈፀመም የሚለው ላይ ክርክር ከመደረጉ በፊት በክስ መቃወሚያ ደረጃ ስለመሆኑ በፍ///// 244 (2) () እና በወ////// 130 (2) () እንዲሁም (3) ላይ ተመልክቷል፡፡

ይርጋን አስመልክቶ የጠበቆች ኃላፊነት ምንድን ነው?

ጠበቆች የደንበኞቻቸውን ጉዳዮች በሚመለከቱበት፣ የክስ መልስ በሚሠጡበት እንዲሁም ክርክር በሚያደርጉበት ወቅት ይርጋን አስመልክቶ የተጣለባቸው ሕጋዊ ኃላፊነት አለ፡፡ ይኸውም በሚኒስትሮች ምክር ቤት የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ሥነ - ምግባር ደንብ ቁጥር 57/1992 አንቀጽ 25 መሠረት ጠበቆች የደንበኞቻቸውን ጉዳይ ይዘው በሚከራከሩበት ወቅት ለደንበኞቻቸው በሕግ የተፈቀደላቸውን የይርጋና ሌሎች ተመሳሳይ መብቶችን በተቃውሞነት ሳያቀርቡ ሊቀሩ የሚችሉት ሁኔታውን ለደንበኞቻቸው ካስረዱ በኋላ ደንበኞቻቸው ጠበቆች ይርጋን በመከራከሪያነት እንዳያቀርቡ በጽሑፍ ፍቃዳቸውን ሲሰጡ ብቻ ይርጋን በመከራከሪያነት ሳያቀርቡ ማለፍ እንደሚችሉ ተመልክቷል፡፡ ከዚህ ውጭ ግን በሁሉም ጉዳዮች ላይ ጠበቆች በሕግ እስከተፈቀደ ድረስ ይርጋን በመከራከሪያነት ማንሳት እንዳለባቸው በአስገዳጅነት ተመልክቷል፡፡ ሆኖም ጠበቆች በሕጉ ከተመለከተው ሁኔታ ውጭ የደንበኞቻቸውን ልዩ ፍቃድ በጽሑፍ ሳያገኙ ቀርተው ይርጋ በመከራከሪያነት ሊያቀርቡ እየተገባቸው በመከራከሪያነት ሳያቀርቡ ቢቀሩ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች ጠበቆች ፍቃድ አሰጣጥና ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 199/1992 አንቀጽ 24 (3) ሥር የተመለከቱትን የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ከማግኘት እስከ ጥብቅና ፍቃድ መሰረዝ የሚደርሱ የተለያዩ ቅጣቶችን ያስከትላል፡፡   

በይርጋ የማይታገዱ ጉዳዮች ምንድን ናቸው?

አብዛኛዎቹ ጉዳዮች ላይ ክስ ለማቅረብ ወይም መብትን ለመጠየቅ የሚቻልባቸው ሁኔታዎች በጊዜ ገደብ ተለክቶ ክስ የማቅረቢያ ጊዜ ተቀምጦላቸዋል፡፡ ሆኖም ጥቂት በሆኑ ጉዳዮች ላይ ክስ የማቅረቢያ ወይም መብት የመጠየቂያ ጊዜ ገደብ እንደሌለውና ክስ ለማቅረብ ምክንያት የሆነው ድርጊት ከተፈፀመበት ጊዜ ጀምሮ ያለምንም ጊዜ ገደብ በማንኛውም ጊዜ ክስ ለማቅረብ ወይም መብት ለመጠየቅ የሚቻልባቸው ጉዳዮች እንዳሉ በተለያዩ ሕጎች ውስጥ ተመልክቷል፡፡ እነርሱም፡-

ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውር እና ስደተኞችን በሕገ-ወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በወጣ አዋጅ ቁጥር 909/2007 አንቀጽ 25 መሠረት በአዋጁ የተመለከቱ ከሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር ጋር የተገናኙ ወንጀሎችን በፈፀመ ሰው ላይ የሚቀርብ የወንጀል ክስ በይርጋ አይታገድም፤     

ሽብርተኝነትን አስመልክቶ በወጣው አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 24 መሰረት የሽብርተኝነት ወንጀል በፈፀመ ሰው ላይ የሚቀርብ የወንጀል ክስ በይርጋ አይታገድም፤  

በዓለም አቀፍ ሕግና ልምድ መሠረት በተለይም ይርጋ በጦር ወንጀሎች እና በሰብዓዊነት ላይ የሚፈፀሙ ወንጀሎች ላይ እንዳይፈፀም ለማስቀረት በተደረገው ስምምነት እና በሮም የዓለም አቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ማቋቋሚያ መሰረት የዘር ማጥፋት፣ በሰብአዊነት ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎች እንዲሁም የጦር ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ሰዎች ላይ የሚቀርቡ ክሶች በይርጋ የማይታገዱ ናቸው፤

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1206 እና የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 10 የሰበር መዝገብ ቁጥር 43600 ላይ በሰጠው አስገዳጅ ውሳኔ መሰረት የማይንቀሳቀስ ንብረትን አስመልክቶ ባለመብት የሆነው ሰው መብት ሳይኖረው በእጁ ካደረገው ሰው ወይም ከያዘው ሰው ላይ ሃብቱ ይገባኛል ሲል የሚያቀርበው የመፋለም ክስ በይርጋ ቀሪ ሊሆን አይችልም፡፡

በፍትሐብሔር ሕግ ቁጥር 1678 1716 እና 1718 እንዲሁም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በቅፅ 14 የሰበር መዝገብ ቁጥር 79394 እና ቅፅ 12 የሰበር መዝገብ ቁጥር 43226 መሠረት የውል መሠረታዊ ዓላማ በሕግ ያልተፈቀደና የተከለከለ ሆኖ ሲገኝ ፍርድ ቤቶች/ዳኞች ሕገ ወጥ የሆነው ውል በቀረበላቸው ማንኛውም ጊዜ ሕጋዊ ውጤትና ተፈፃሚነት የለውም በማለት ለመወሰን የሚችሉና ሕገ ወጥ የሆነውን ውል ውድቅ ለማድረግ በሕጉ የተደነገገው የይርጋ ጊዜ ገደብ መቃወሚያ ሊሆን አይችልም፡፡ 

በአጠቃለይ ይርጋ በሀገራችንም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሕግ ተቀባይነት ያለው ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን ተከራካሪዎች፣ ዓቃቤ ሕግ፣ ፍርድ ቤቶች እና ጠበቆች በጥንቃቄ ሊያጤኑት የሚገባ ለክርክር የቀረበን ጉዳይ እጣ ፈንታ ሊወስን የሚችል ፅንሰ ሀሳብ ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

DNA አባትነትን ማረጋገጫ ማስረጃ ስላለመሆኑ
ዓለም አቀፍ ስምምነቶች በኢትዮጵያ የሕግ ሥርዓት ያላቸው ደረጃ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 23 July 2024