Font size: +
7 minutes reading time (1394 words)

የውርስ ጉዳይን የተመለከቱ የይርጋ ገደቦች

ማንኛውም ሰው አንድ የፍርድ ውሰኔ ሊያገኝ የሚገባ ጉዳይ ያለው እንደሆነ ጉዳዩን ለማየት በሕግ ሥልጣን ለተሰጠው አካል ሊያቀርብ ሚችልበት የጊዜ ገደብ በልዩ ልዩ የሕግ ድንጋጌዎች ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡ ይህን መሰል የጊዜ ገደብ በሕግ አጠራር ይርጋ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን ትርጓሜውም በሕግ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ባለመብት የሆነ ወገን መብቱን ለመጠየቅ ተገቢውን ትጋት ማድረግና የመብት ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት ሲሆን ይሄን ሳያደርግ ቢቀር ግን መብቱ በይርጋ (በጊዜ ገደብ) ቀሪ የሚሆን ይሆናል የሚል ነው፡፡

የይርጋ ዘመናቸው ያለፈባቸው ጉዳዮች ለፍርድ ቤት በሚቀርቡበት ወቅት ተከራካሪ ወገን የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ የማቅረብ መብት ያለው መሆኑ በሥነ-ሥርዓት ሕጎቻችን ላይ ተመልክቶ ያለ ሲሆን በዚህም ጊዜ ፍርድ ቤቶች የታቃውሞውን አቀራረብ ግራ ቀኙ ከሚያቀርቡት የመከራከሪያ ነጥቦችና የይርጋ ጥያቄው ከቀረበበት የሕግ ክፍል አንጻር መርምረው የቀረበው ጥያቄ የጊዜ ገደብ ያለፈው ከሆነ መዝገቡን በይርጋ ታግዷል በማለት በብይን ዘግተው አቤቱታ አቅርቢውን ሊያሰናብቱ ይችላሉ፡፡    

የውርስ ጉዳይን በተመለከተ ሟች ከሞተ አንስቶ ወርሾች የወራሽነት ጥያቄያቸውን የሚያቀርቡበት፤ ኑዛዜ ሚቃወም ወገን ያለ እንደሆነ ኑዛዜውን ሚቃወምበት፤ የውርስ ሀብት ክፍፍል ጠያቂ ጥያቄውን የሚያቀርብበት የጊዜ ገደብ በፍ/ብሔር ህጋችን እና የፌ/ጠ/ፍ/ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጣቸው አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜዎች ላይ በሰፊው የተመለከተ  በመሆኑ በዚህ ጽሑፍ እነዚህ ነጥቦችን ለመዳሰስ እሞክራለሁ፡፡  

ኑዛዜን ለመቃወም የተቀመጠ ጊዜ ገደብ

ኑዛዜ ፈራሽ ነው የሚል ክስ የሚቀርብበትን የጊዜ ገደብ በተመለከተ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 973 እና 974 ላይ ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በቁጥር 973 ላይ የተመለከተው ተፈጻሚ ሚሆነው ኑዛዜ ፈራሽ ነው የሚለውን ክስ ኑዛዜው ሲነገር በነበሩ ሰዎች የቀረበ እንደሆነ ነው፡፡ ይህም ማለት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 973/1/ ላይ እንደተገለጸው “ኑዛዜ ሲነበብ የነበሩ ወይም የተወከሉ ሰዎች ኑዛዜው አይጸናም ወይም አንዱ በኑዛዜው የተነገረው ቃል አይጸናም በማለት ክስ ለማቅረብ ያላቸውን ሀሳብ መግለጫ ወይም ስለ ክፍያው በሂሳብ አጣሪው የቀረበውን የድልድል አመዳደብ ሀሳብ ለመቃወም ኑዛዜው ከተነበበት አንስቶ በሚቆጠር የአስራ አምስት ቀን ጊዜ አላቸው”፡፡

በሌላ መልኩ ደግሞ ኑዛዜው ሲነበብ ያልነበሩ ሰዎች መቃወሚያቸውን መቼ ሊቀርቡ ይችላሉ ለሚለው በፍ/ሕ/ቁ 974/1/ እና 2 ላይ የተገለጸ ሲሆን በዚህም መሰረት “ በኑዛዜ ንባብ ሥነ-ሥርዓት ላልነበሩ ወይም በኑዛዜው ንባብ ሥነ-ሥርዓት በወኪልነት ላልሰሙ ሰዎች እንዲሁም ኑዛዜው በሌሉበት የተነበበ እንደሆነ ከዚህ በላይ የተገለጸው የጊዜ ገደብ ለመቁጠር መነሻ የሚሆነው ሥለ ክፍያው ድልድልና አመዳደብ ሀሳቡን ከተነገራቸው ቀን አንስቶ ነው”፡፡

በፍ/በ/ህ/ቁ 973/2/ ላይ በተገለጸው መሰረት ኑዛዜ ከፈሰሰበት ጊዜ ከአምስት ዓመት በኋላ ወይም ኑዛዜ የሌለ እንደሆነ ሟች ከሞተ ከአምስት ዓመት በኋላ ስለ ኑዛዜው መጽናትና ስለክፍያው አመዳደብ አጣሪው ያቀረበውን የድልድል ሀሳብ በማናቸውም አስተያየት ቢሆን መቃወሚያ ሊቀርብበት አይችልም፡፡      

ከዚህ በላይ ከተገለጹት የሕግ ድንጋጌዎች ጋር በተያያዘ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 82585 በቅጽ 15 ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን በትርጓሜውም “በፍ/ብ/ሕ/ቁ 973 እና 974 ድንጋጌዎች አቤቱታ አቅርቢው ኑዛዜ ሲነበብ የነበረ ወይም የተወከለ የመሆን አለመሆን መስፈርት መሰረት በማድረግ ይርጋው መቁጠር የሚጀምርበትን ጊዜ እና ፍጹም የሆነ የይርጋ ጊዜ በቁጥር 974/2/ ከመደንገጋቸው በስተቀር ሁለቱም ድንጋጌዎች ኑዛዜው ፈራሽ ነው የሚል ክስ የሚቀርብበትን ስርዓት የሚደነግጉ በመሆቸው ተያያዥነት አላቸው በማለት ኑዛዜ መኖሩን ማወቅ እና የኑዛዜውን ሙሉ ይዘት ማወቅ የተለያዩ ጉዳዮች ናቸው ሲል በፍ/ብ/ህ/ቁ 973/1/ የተመለከተው የ15 ቀን ጊዜ ገደብ የክስ ማቅረቢያ ጊዜ ሳይሆን የመግለጫ ማቅረቢያ ጊዜ ነው፡፡ በመሆኑም ስለ ኑዛዜ መኖር እንጂ ስለድልድሉ የማያውቅ ወራሽ መግለጫ የማቅረብ ግዴታ ስለማይኖርበት ጊዜው መቁጠር የሚጀምረው በኑዛዜው የተደረገውን ድልድል ካወቁበት ቀን ጀምሮ ነው” በማለት ውሳኔ ሰጥቷል፡፡

በሟች የተደረገ ኑዛዜ ከውርስ የነቀለኝ በመሆኑ ሊፍርስ ይገባል በማለት ኑዛዜው ሲነበብ በነበረ አመልካች የሚቀርብ የክስ አቤቱታ ሊቀርብ ሚገባው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 973 መሰረት በተገለጠው የጊዜ ገደብ ነው ወይስ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1123 በተገለጸው ጊዜ ውስጥ ነው? የሚለው አከራካሪ ጉዳይ በመሆኑ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 152134 በቅጽ 23 ላይ አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በውሳኔውም መሰረት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 973 ስለ ኑዛዜ መነበብ እንዲሁም ኑዛዜ ሲነበብ የነበሩ ሰዎች ኑዛዜው እንዲፈርስ አቤቱታ የሚያቀርቡበትን ሥርዓትና ጊዜውን በሚመለከት የሚደነግግ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ ኑዛዜው ከውርስ ነቅሎኛል /ነቅሎናል/ በማለት ኑዛዜው እንዲፈርስ የሚቀርብን ወይም የቀረበ አቤቱታን የሚመለከት አይይለም፡፡ በመሆኑም ኑዛዜው ከውርስ የመንቀል ውጤት ያለው በመሆኑ እንዲፈርስ በሚል የሚቀርብ የዳኝነት ጥያቄ ሊታይ የሚገባው በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1123 መሰረት ነውእንጂ በአንቀጽ 973 መሰረት አይደለም በማለት አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ ስለዚህ ከዚህ በላይ በተጠቀሰው የሕግ ትርጓሜ መሰረት ኑዛዜ ሲነበብ የነበረ አመልካች ኑዛዜው ከውርስ ነቅሎኛል በማለት የሚያቀርበው የክስ አቤቱታ ሊቀርብ ሚገባው በፍ/ህ/ቁ 973  መሰረት ሳይሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1123 መሰረት በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ውስጥ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡               

በአጠቃላይ አንድ ኑዛዜ ፈራሽ ነው በሚል ስለሚቀርብ መግለጫ እና እንዲሁም መግለጫው እና ክሱ ሊቀርብ ስለሚገባው የጊዜ ገደብ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 973 እና 974 ተደንግጎ ይገኛል፡፡ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 973 ተፈጻሚነት የሚኖረው ኑዛዜ ሲነበብ በነበሩ ወይም በተወከሉ ሰዎች ጉዳይ ሲሆን በአንቀጽ 974 ድንጋጌ ደግሞ ተፈጻሚነቱ በኑዛዜ ሥነ-ሥርዓት ባልነበሩ ወይም ባልተወከሉ ሰዎች ጉዳይ ነው፡፡ ኑዛዜ ሲነበብ የነበረ አመልካች ኑዛዜው ከውርስ ነቅሎኛል በማለት የሚያቀርበው የክስ አቤቱታ ሊቀርብ ሚገባው በፍ/ህ/ቁ 973  መሰረት ሳይሆን በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1123 መሰረት ነው፡፡

የወራሽነት ጥያቄ ለማቅረብ የተቀመጠ ጊዜ ገደብ   

የወራሽነት ጥያቄን ለማቅረብ የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000 ላይ የተመለከተ ሲሆን ወደዚህ ነጥብ ከመግባቴ በፊት ወራሽነት ጥያቄ ማለት ምን ማለት ነው የሚለውን እደሚከተለው ለመዳሰስ እሞክራለሁ÷

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 996(1) ላይ በተገለጸው መሰረት ወራሽ የሆነ ሰው የሟቹ ወራሽ መሆኑንና ከውርሱ ላይ የሚያገኘውን ድርሻ የሚያመለክት የወራሽነት የምስክር ወረቀት እንዲሰጠው ለፍርድ ቤት ጥያቄ ማቅረብ ይቻላል በማለት የተገለጸ ሲሆን ይህ ማለት ፍ/ቤቱ የወራሽነት ምስክር እንዲሰጠው ወራሹ ሲፈልግ የሚጠይቀው እንጂ ሟችን ለመውረስ የግድ ከፍ/ቤቱ የወራሽነት ማስረጃ ማምጣት እንዳለበት የሚያስገድድ አይደለም፡፡ ሆኖም ግን በተግባር እንደሚስተዋለው ስመ ንብረቱ ለማዛወር እና ከሌሎች የሟች መብቶች ለመጠቀምና ለመስራት በፍ/ቤቱ የተረጋገጠ የወራሽነት የምስክር ወረቀት መጠየቁ የተለመደ አሰራር ሆኗል፡፡  

ከዚህ በላይ የተጠቀሰውን መሰረት በማድረግ አንድ ሰው ዋጋ ያለው የወራሽነት ማስረጃ ሳይኖረው ውርሱን ወይም ከውርሱ አንዱን ክፍል በእጁ ያደረገ እንደሆነ እውነተኛው ወራሽ ወራሽነቱን እንዲታወቅለትና የተወሰዱበት የውርስ ንብረቶች እንዲመለሱለት በዚህ ሰው ላይ የወራሽነት ጥያቄ  ክስ ሊያቀብበት ይችላል በማለት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 999 ላይ ተደንግጓል፡፡ ስለዚህ ይህን መሰል የክስ አቤቱታ አቤቱታ መቼ ሊቀርብ ይገናል ለሚለው የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000/1/ ላይ የጊዜ ገደብ ተቀምጧል፡፡ 

በዚሁ መሰረት ከሳሽ መብቱንና የውርሱን ንብረት በተከሳሽ መያዛቸውን ካወቅ ሶስት ዓመት ካለፈ በኋላ ስለ ወራሽነት ጥያቄ የሚቀርበው ክስ ተቀባይነት ሊያገኝ አይችልም፡፡ በሌላ መልኩ በአንቀጽ 1000(2) ላይ እንደተገለጸው “ሟቹ ከሞተበት ወይም ከሳሹ በመብቱ ለመስራት ከቻለበት ቀን አንስቶ አስራ አምስት አመት ካለፈ በኋላ ከዘር የወረደ ርስት ካልሆነ በቀር የውርስ ጥያቄ ክስ በማናቸውም አስተያየት ቢሆን ተቀባይነት አያገኝም የሚለው ተደንግጎ ይገኛል፡፡  

ከዚህ በላይ በአንቀጽ 1000(1) እና (2) ላይ የተመለከቱት የጊዜ ገደቦች ከሌሎች የውርስ ሕግ ድንጋጌዎች በተለይም 1ኛ) አንድ ወራሽ የሟች ኑዛዜ ተጠቃሚ መሆን የሚችለው ኑዛዜ በእጁ እንደሚገኝ ለውርስ አጣሪው አቅርቦ ውርስ አጣሪው ኑዛዜውን በሚነበብበት ሰዓት ራሱ ወይም ወኪሉ ካልነበረ ወራሹ ኑዛዜው ከፈሰሰበት ቀን አንስቶ በአስራ አምስት አመታት ውስጥ መቃወሚያ ካላቀረበ ከዚያ በኋላ ሊቀርብ እንደማይችል በፍ/ሕ/ቁ 974(2) የተመለከተው በፍ/ሕ/ቁ 1000(1) ካለው የጊዜ ገደብ ጋር እንዴት ተጣጥሞ ተግባራዊ ይሆናሉ ከሚለው ጋር ጥያቄ የሚያስነሳ ሲሆን በሌላ መልኩ በፍ/ሕ/ቁ 1000(1) እና (2) አተረጓጎምና አፈጻጸም እንዴት መሆን አለበት በሚል አልፎ አልፎ ጥያቄ ሲያስነሳ ይስተዋላል፡፡ ስለዚህ በእነዚህ የሕግ ማዕቀፎች ላይ የተጠቀሱት የጊዜ ገደቦች በተመለከተ መከተል የሚገባንን የሕግ ትርጓሜ እንደሚከተው ለማብራራት ተሞክሯል÷ የፍ/ብ/ሕ/ቁ 974/2/ ተፈጻሚ የሚሆነው የሟች ውርስ የሚያጣራ ፤በሕግ በኑዛዜ ወይም  በፍርድ ቤት የተሾመ የውርስ አጣሪ ፤ሟች አድርጎታል የተባለው ኑዛዜ አግኝቶ የኑዛዜውን ፎርምን የኑዛዜውን ዋጋ መኖር ፤የሟች ያለኑዛዜ ወራሾች ወይም አራት አካለመጠን ያደረሱ ሰዎች ባሉበት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 968 በተመረመረበት ሁኔታ ነው፡፡ ሆኖም ግን ኑዛዜ ያለ መሆኑን ለውርስ አጣሪው ሳያሳውቅ ቀጥታ የኑዛዜ ወራሽ መሆኑ እንዲታወቅለት ለፍ/ቤት አመልክቶ የወራሽነት የምስክር ወረቀት በመውሰድ የሟች ንብረት በእጁ ያደረገ ሰው ወይም በሀሰት የሟች ያለኑዛዜ ወራሽ ነኝ ብሎ የሟችን ንብረት ከወሰደው ሰው ለማስመለስ አግባብ የሆነው የይርጋ ገደብ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 968 የተጠቀሰው ሳይሆን በፍብ/ሕ/ቁ 1000/1/ የተመለከተው ተፈጻሚነት ሊኖረው ይገባል፡፡

በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000/1/ እና 1000/2/ አስመልክቶ የተለያዩ አተረጓገሞች የሚስተዋሉ ሲሆን ለዚህ ጽሁፍ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 30158 ፤26422 እና 34011 በቅጽ 7/6/6/ እንዲሁም በቅጽ 11 በሰ/መ/ቁ 52407 የሰጠውን አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ለመዳሰስ ሞክሬያለው፡፡ በዚሁ አግባብ በፍ/ሕ/ቁ 1000/2/ ላይ ሟች ከሞተ አስራ አምስት አመት በላይ ወይም ተከሳሹ በመብቱ ሊሰራበት ከቻለበት ቀን አንስቶ አስራ አምስት ዓመት ውስጥ ክስ ካልቀረበ አስራ አምስት ዓመት ካለፈው  በኋላ ክስ ሊያቀርብ የሚቻለው ከዘር የወረደ ርስት በሆነ ንብረት ላይ ነው፡፡  

ርስት የሚለው ቃል በፍ/ሕ/ቁ 1130 እና ስለ ንብረቶች በሚናገረው የፍ/ብሔር የህጉ ክፍል መሬት የሚያመለክት መሆኑን መገንዘብ ይቻላል፡፡ በኢትዮጲያ ቋንቋዎች ጥናትና ምርምር ማዕከል የተዘጋጀው የአማርኛ መዝገበ ቃላት ርዕስት የሚለው መሬትን የሚመለከት መሆኑን ጠቅሶ ትርጓሜ ሰጥቷል፡፡ በዚሁ አግባብ ከዘር የወረደ ርዕስት የሚለው ቤትን አያጠቃልልም የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡ በርዕስት የሚተላለፍ መሬት ብቻ ማለት ሰለሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000/2/ መሰረት ለተወላጆች የሚተላለፍ መሬት ብቻ ነው የሚል መደምደሚያ ላይ መድረስ ይቻላል፡፡

በኢፌድሪ ህገ መንግስት መሰረት መሬት የመንግስትና የህዝብ ሀብት በመሆኑ ከዘር የወረደ ርዕስት ካልሆነ በስተቀር በማለት በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000/2/ ላይ የተገለጸው የተሻረ እና ተፈጻሚነት የሌለው ነው በማለት አስገዳጅ ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡  

የፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000/1/ አፈጻጸምን በተመለከተ የፌ/ጠ/ፍ/ቤት በሰ/መ/ቁ 32407 በቅጽ 11 ላይ ትርጓሜ የሰጠ ሲሆን በዚህም መሰረት በወራሾች መካከል የሚነሳ የውርስ ንብረት ክርክር በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1000/1/ በተደነገገው አግባብ በሶስት አመት ጊዜ ውስጥ መቅረብ ያለበት ሲሆን ወራሽ በሆነ እና ወራሽ ባልሆነ ተከራካሪ ወገን መካከል የሚቀርበው የውርስ ንብረት ይገባኛል ጥያቄ በፍ/ብ/ህ/ቁ 1677 እና 1845 መሰረት በአስር አመት ጊዜ ውስጥ ካልቀረበ መብቱ በይርጋ የሚታገድ ይሆናል፡፡

የክፍፍል ጥያቄ በይርጋ የማይታገድ ስለመሆኑ

ወራሾች ተለይተው የውርስ ሀብቱ ድርሻ ታውቆ ግን ክፍፍል ሳይደረግ የቆየ የውርስ ሀብት ያለ እንደሆነ በፍ/ብ/ሕ/ቁ 1062 በተገለጸው መሰረት እያንዳንዱ የጋራ ወራሾች ውርሱን እንከፋፈል በማለት በማንኛውም ጊዜ ለመጠየቅ የሚችሉ በመሆኑ የክፍፍል ጥያቄ በይርጋ የማይታገድ ይሆናል፡፡

መደምደሚያ

በአጠቃላይ አንድ ሰው ከዚህ አለም በሞት የተለየ እንደሆነ የውርስ ጉዳዩን በተመለከተ ወራሽ የሆነ ወገን ኑዛዜን ሚቃወምበት፤የወራሽነት ጥያቄ ሚያቀርብበትና ክፍፍል የሚጠይቅባቸው የጊዜ ገደቦች ከዚህ በላይ በተገለጸው አግባብ ተፈጻሚ ሚሆኑ ሲሆን ባለመብት የሆነ ወገን ጥያቄውን በህጉ በተመለከተው የጊዜ ገደብ ውስጥ ያላቀረበ እንደሆነ ውጤቱ መብቱን እስከማጣት የሚደረስ ይሆናል፡፡       

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የኢትዮጵያ ዜግነትን መልሶ ስለማግኘት - የኢትዮጵያ ዜግነትን ያለባለሥልጣኑ (ኤ...
Is US action under the Ambit of International Law?...

Related Posts

 

Comments 1

Abebe
Guest - ሙሓመድ ዓሊ on Sunday, 04 February 2024 11:33

ወራሾች ተለይተው የውርስ ድርሻ ትውቆ ሲባል አንዴት ነው ?

ወራሾች ተለይተው የውርስ ድርሻ ትውቆ ሲባል አንዴት ነው ?
Already Registered? Login Here
Abebe
Friday, 13 December 2024