Font size: +
20 minutes reading time (3967 words)

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት እና ተግባራዊ አፈፃፀሙ

የተፋጠነ ፍትሕ ወይም ዳኝነት ያለመስጠትና የፍርድ ቤቶች በአሠራርና በውሳኔ አሠጣጥ ላይ መዘግየት ደግሞ ዋነኛው የዳኝነት ሠጪው አካል ሊመልሰው የሚገባ የተገልጋዩ ጥያቄ ነው፡፡ ፍትሕ /ዳኝነት/ በመስጠት ላይ ያለ መዘግየት አንድ ጉዳይ ለፍርድ ቤት ቀርቦ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ጊዜ ድረስ ያለውን ያለበቂ እና አሳማኝ ምክንያቶች ያሉ መዘግየቶችን የሚያካትት ነው፡፡

ሁሉም ጉዳዮች እንደየባሕሪያቸውና ፀባያቸው የሚወስዱት የየራሳቸው ጊዜ ያላቸው ቢሆንም ተገልጋዮች ለፍርድ ቤት ያቀረቡት ጉዳይ እስኪወሰን ይፈጃል ወይም ይወስዳል ብለው የሚያስቡት ጊዜ ይኖራል፡፡ ችግሩ የሚያመጣውም በጉዳዮች ላይ ይፈጃል ወይም ይወስዳል ተብሎ ከሚገመተው ጊዜ በላይ እጅግ የተራዘመና ተከታታይ ቀጠሮዎች እየተሰጡ ጉዳዮች ሲጓተቱ ነው፡፡

እጅግ የተራዘመና የተዘገየ የፍትሕ ወይም የዳኝነት አሠጣጥ ሂደት ያለበት ሁኔታና አሠራርም ተከራካሪ ወገኖች ላይ ጥርጣሬ እና እምነት ማጣትን የሚያሳድር ከመሆኑም ባሻገር የፍትሕ ስርዓቱን ውጤታማነት እና ብቃት አጠያያቂ ሊያደርገው ይቻላል፡፡

ፍትሕ ፈላጊ ተገልጋዩም የተቀላጠፈ፤ ተጨማሪ ወጪ የማያስወጣ እና ትክክለኛ ፍትሕ ይፈልጋል፡፡ ይኼ በሌለበት ሁኔታም ተገልጋዩ ፍትሕን ከፍርድ ቤት ከመጠየቅ ይልቅ በራሱ ለማግኘት ይሞክራል፡፡ የዳኝነት ሠጪ አካሉ የተቋቋመበት ዋነኛ ዓላማም አለመግባባቶችና ግጭቶችን ሕግንና ማስረጃን መሰረት አድርጎ በተገቢው ጊዜና ሁኔታ መፍታት እንደመሆኑ ዳኝነት ይሠጠኝ በሚል ለሚቀርቡ አቤቱታዎች የዳኝነት አካሉ የተቀላጠፈ እና ወጪ ቆጣቢ ዳኝነት የመስጠት ግዴታ አለበት፡፡

በዚህ ፅሁፍም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት ምንድን ነው? ሕጋዊ ከለላውና ተግባራዊ አፈፃፀሙስ ምን ይመስላል? በውሳኔ አሰጣጥ ላይ የፍርድ ቤቶች መዘግየት መንስኤው ምንድን ነው? ለተደጋጋሚና ለረጃጅም ቀጠሮዎች መሠጠት ምክንያቶቹ ምንድን ናቸው? መፍትሔዎቹስ ምንድን ናቸው? የሚሉና ሌሎች ነጥቦችን በአጭሩ እንዳስሳለን::

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት ምንድን ነው?

ምክንያታዊ ጊዜ የሚወስድ የፍርድ ሂደት ከዳኝነት ነፃነት፣ ሚዛናዊ የፍርድ አካሄድ፣ የውሳኔዎች ተገማችነት እና የፍርድ ቤቶች ተደራሽነት ያልተናነሰ የዳኝነት ሠጪ አካሉን ውጤታማ ከሚያስብሉ ዋነኛ መመዘኛዎች ጋር አብሮ ይጠቀሳል፡፡

የተፋጠነ ፍትሕ ምንነትም ብዙውን ጊዜ የሚገለፀው ዘግይቶ የሚሠጥ ፍትሕን በማብራራት ነው፡፡ በመሆኑም የዘገየ ፍትሕ የሚሠጥበትን ሁኔታን በማብራራት የተፋጠነ ፍትሕ ምንነትን መግለፅ ይቻላል፡፡ በፍትሕ አስተዳደር ተቋማት በተለይም በፍ/ቤቶች በኩል የሚሠጥ ዳኝነት ዘግይቷል የሚባለው መቼ ነው? የሚለውን ጥያቄ በተመለከተ የተለያዩ ምሁራን የየራሳቸውን አስተያየት ይሰጣሉ፡፡ ለምሳሌ ቡስካግሊያ እና ዳኮሊያስ የተባሉ ፀሀፊያን ከፍርድ ቤት የሚሠጥ ዳኝነት ዘግይቷል የሚባለው አንድ ጉዳይ ለፍርድ ቤት ቀርቦ በማስረጃ ተጣርቶ እና ተመርምሮ ውሳኔ ተሰጥቶበት እስከሚዘጋ ድረስ ምክንያታዊና በቂ ከሚባል ጊዜ በላይ ከቆየ ነው፡፡ በሌላ በኩል ሸርተፌት የተባሉ ፀሐፊ አስተያየት የፍርድ ስርዓት መዘግየት አለ ሊባል የሚችለው ተከራካሪዎች በክርክር ሂደቱ ያሉባቸውን ግዴታዎች ከተወጡና ፍርድ ቤቱ በበኩሉ የሚጠበቅበትን ሥራ ይሰራል ተብሎ ሲጠበቅ መስራት ሳይችል ሲቀር ነው፡፡

በወንጀል ጉዳዮች ላይ የፍትሕ አስተዳደር ስርዓቱ መዘግየት ምክንያታዊ እና በቂ በሆነ ጊዜ ውስጥ ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚነካ ሲሆን ኒኪ ቶቢ የተባሉ ፀሐፊ በወንጀል ጉዳይ የዳኝነት አሠጣጥ መዘግየት ተጠርጣሪውን ወይም ተከሳሹን ያለ በቂ እና አሳማኝ ምክንያት ለፍርድ አለማቅረብና ማጓተትን የሚጨምር ሲሆን መዘግየት አለ ወይስ የለም የሚለው መታየት ያለበትም ተጠርጣሪው ከተያዘበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻ ውሳኔና ፍርድ እስከሚሠጥ ጊዜ ድረስ ያለው አካሄድ ታይቶ ነው ይላሉ፡፡

የፍትሐብሔር ጉዳዮችን በተመለከተም መዘግየት የፍርድ ቤቶችን ያለበቂና አሳማኝ ምክንያት የተራዘሙና የተንዛዙ ቀጠሮዎች መስጠትን የሚያካትት ሲሆን ቫን ሬሂ የተባሉ ፀሀፊ አንድ ጉዳይ ለፍርድ ቤት ቀርቦ መዝገብ ከተከፈተበት ቀን ጀምሮ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሠጥ ቀን ድረስ ያለበቂና አሳማኝ ምክንያት የሚያልፍ ጊዜያት በሙሉ መዘግየት እንዳለ ያመለክታል ይላሉ፡፡

በአጠቃላይ የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት በወንጀልም ይሁን በፍትሐብሔር ጉዳይ ላይ የዳኝነት ወይም የፍትሕ ጥያቄ ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ ያለመዘግየት ምክንያታዊ በሚባል አጭር ጊዜ ውስጥ ዳኝነት ወይም ፍትሕ የማግኘት መብት ነው፡፡ ይህ መብትም አላስፈላጊና ያልተንዛዙ ቀጠሮዎች ሳይኖሩ የዳኝነት ጥያቄ በቀረበበት ጉዳይ ላይ ውሳኔ የማግኘት መብትን ይጨምራል፡፡

ፍርድ ቤቶች ተደጋጋሚ እና ረጃጅም ቀጠሮዎች የሚሠጡባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ፍርድ ቤቶች ከፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አንስቶ እስከ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በወንጀልም ሆነ በፍትሐብሔር ጉዳዮች ላይ ቀጠሮ የሚሰጡባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ከእነዚህ መካከልም፡-

·    መዝገቡን መርምሮ ብይን ወይም ውሳኔ ለመስጠት በቂ ጊዜ ስላልተገኘ በድጋሚ መርምሮ ለመወሰን፣

·    ክርክሩ ወይም የምስክሮች ድምፅ የተቀዳበት መቅረፀ ድምፅ ወደ ፅሁፍ ተገልብጦ ስላልደረሠ አልተመረመረም በድጋሚ መርምሮ ለመስራት፣

·    የችሎቱ ዳኛ በሕመም/እክል ምክንያት ስላልመጡ በቀጣይ ለመስራት፣

·    ችሎቱ ዛሬ መስራት ስለማይችል በቀጣይ ለመስራት፣

·    የድምፅ ቀራጭ ሠራተኛ ስለሌለ በቀጣይ ለመስራት፣

·    የድምፅ መቅረጫ ካሴት ስለሌለ በቀጣይ ለመስራት፣

·    መብራት ባለመኖሩ ለችሎቱ በቂ ብርሀን ስለሌለ፣

·    መብራት ስለሌለና ድምፅ መቅረፅ ስለማይቻል፣

·    ዳኞች ስላልተሟሉ በተሟሉ ጊዜ ለመስራት፣

·    ዳኞች ስብሰባ ላይ መሆናቸው በሌላ ጊዜ ለመስራት፣

·    የችሎት ስራ ለመስራት የሚያስችል አዳራሽ ባለመኖሩ በቀጣይ ለመስራት፣

·    የፍርድ ቤቱ መዝገብ ተፈልጎ ለጊዜው ሊገኝ ባለመቻሉ ሲገኝ ለመስራት፣

·    ዐቃቤ ሕግ በችሎት ስላልቀረበ በቀረበ ጊዜ ለመስማት፣

·    ከፍተኛ የመዝገብ ብዛትና መጨናነቅ ስላለ በቀጣይ ለመስራት፣

·    ሕገ መንግሥታዊ ግዴታዎች/ሕገ መንግሥቱ ለተከሰሱ ሰዎች የሠጠው ጠበቃ የማግኘት መብት፣ አስተርጓሚ የማግኘት መብት፣ መከላከያ ማስረጃ በበቂ ጊዜና ሁኔታ አዘጋጅቶ የማቅረብ መብት ወዘተ ቀጠሮ ለመቀየር በምክንያትነት የሚቀርቡበት ጊዜ አለ/፣

·    አስተርጓሚ ስለሌለ ሲቀርብ ለመጠባበቅ፣

·    ማረሚያ ቤት ወይም ፖሊስ በተለያየ ምክንያት በእስር ላይ የሚገኙ ተከሳሾችን ለችሎት ያላቀረበ በመሆኑ ሲቀርቡ ለመጠባበቅ፣

ተደጋጋሚ እና ረጃጅም ቀጠሮዎች ለመስጠት ከበስተጀርባ ያሉ ምክንያቶች ምንድን ናቸው?

ፍርድ ቤቶች ተደጋጋሚ እና ረጃጅም ቀጠሮዎች ለመስጠታቸው የተለያዩ ምክንያቶች ቢሰጡም ከራሱ ከሚሠጡት ምክንያትና ከሚታዩ ነባራዊ ሁኔታዎች በመነሻነት ተደጋጋሚ ቀጠሮ የሚሰጥባቸውን ከበስተጀርባ ያሉ ምክንያቶች ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ እነዚህም፡-

·    በፍርድ ቤቶች እየታዩ ከሚገኙ ጉዳዮች ጋር ተመጣጣኝ ቁጥር ያላቸው ዳኞች እና ሌሎች ሠራተኞች ያለመሾምና ያለመቅጠር፣

·    በፍርድ ቤት የሚታዩ ጉዳዮችን በቀላሉ ተረድተው በታታሪነት፣ በእውቀት እና ስነምግባር ላይ ተመስርተው ለመስራት የሚችሉ ዳኞችን በበቂ ሁኔታ ያለመሾም፣

·    ለፍርድ ቤቶች የተሟላ ቁሳቁስና አቅርቦት አለመኖር፣

·    ለእያንዳንዱ ችሎት በቂ የሆነ እና ሁሉም አቅርቦቶች የተሟላለት የማስቻያ አዳራሾች አለመኖር፣

·    የፍርድ ቤቶችን አሠራር ሊያቀላጥፉ እና ብቃታቸውን ሊጨምሩ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሚፈለገው መጠን አለመጠቀም፣

·    ጉዳዮች ለፍርድ ቤት ከቀረቡበት ቀን ጀምሮ እንደጉዳዩ ውስብስብነትና ቅለት በአማካይ ታይተው ውሳኔ ሊሠጥባቸው የሚገባበትን ጊዜ የሚያመለክት ሕግ አለመኖሩን(በዚህም ምክንያት ምን ያስቸኩላል ቀስ ተብሎ ይወሰናል የሚል አስተሳሰብ መኖሩ)፣

·    ዳኞች ቀጠሮ በሠጡበት ቀን ትክክለኛ ሠዓት አለመገኘታቸው፣

·    ዳኞች በስራ ቀንና ሠዓት በስብሰባዎችና ስልጠናዎች ሌሎች ጉዳዮች ላይ እንዲሣተፉ ማድረግ፣

·    አንዳንድ ዳኞች መስራት እየቻሉ ቀጠሮ መስጠትን እንደልማድ መውሰዳቸው፣

·    በመዛግብት ላይ ከቀጠሮ በፊት በቂ ዝግጅት አለማድረጋቸው፣

የፍርድ ቤቶች መዘግየት ምን ያስከትላል?

ዳኝነት ተጠይቆባቸው በፍርድ ቤቶች የሚቀርቡ መዛግብት ላይ የተቀላጠፈ ውሳኔ ከመስጠት ይልቅ በረጃጅምና ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች ፍርድ ባለመስጠት የሚኖረው መዘግየት በርካታ ችግሮችን ያስከትላል፡፡ ከእነዚህ መካከልም፡-

·    የዜጎችን መሠረታዊ የህዝብ አገልግሎት ተጠቃሚነት መጉዳቱ፣

·    በጊዜ ሂደት የማስረጃዎች መመናመን በተለይም ምስክሮችን በተፈለጉ ጊዜ ያለማግኘት በስተመጨረሻ የፍትሕ መጓደል ማምጣቱ፣

·    በተለየ ሁኔታ ከተከራካሪዎች መካከል የተወሰኑት ላይ ጉዳት ሊያመጣ መቻሉ፣  

·    የኢኮኖሚ ትብብርና ልማት ተቋም (OECD Organization for Economic Corporation and Development) የተባለው ድርጅት ከተለያዩ ሀገራት በሠበሠበው መረጃ መነሻነት በሠራው ጥናት የፍርድ አሰጣጥ ሂደት በአማካኝ በ10% ከዘገየ ተገልጋዮችና ማህበረሰቡ በፍትሕ ስርዓቱ ላይ የሚኖራቸው እምነት በ2% እንደሚቀንስ እንዳመለከተው ሕብረተሰቡ አለመግባባትና ክርክሮችን በሕግ አግባብ በፍርድ ቤቶች ከመፍታት ይልቅ ወደአልሆነ የበቀል መንገድ በማምራት በፍትሕ ሥርዓቱ ላይ ያለውን የሕዝብ አመኔታ መቀነሱ፣

·    በፍትሐብሔር ክርክሮች ላይ ወለድ እንዲከፈል የሚወሰንበት ወገን የተጋነነ የወለድ ክፍያ እንዲከፍል በር የሚከፍት መሆኑ፣

·    ፍትሕ የማግኘት መብትን መጉዳቱ፣

· በወንጀል ጉዳይ የዋስትና መብት ተከልክለው ወይም ዋስ የሚሆናቸው አጥተው በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸውን የሚከታተሉ ሰዎችን መብት በእጅጉ የሚጎዳ መሆኑ፣

·    በወንጀል ጉዳይ የዋስትና መብት ተከልክለው ወይም አጥተው በእስር ጉዳያቸውን ሲከታተሉ ቆይተው በስተመጨረሻ በነፃ የሚለቀቁ ሰዎችን ባልሰሩት ወንጀል እንዲቀጡ ማድረጉ፣

·    ክርክር በረዘመ ጊዜ የተከራካሪ ወገኖች የክርክር ወጪ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱ፣

·    በወንጀል የተከሠሠ ሰው ጥፋተኛ እስካልተባለ ድረስ ነፃ ሆኖ የመገመት መብት አለው ከሚለው መርህ በተቃራኒ በተከሳሽ ላይ ከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና መፍጠሩ፣

·    ተበድለናል መብታችን ተነክቷል የሚሉ ሰዎች ላይም የሥነ ልቦና ጫና መፍጠሩ፣

·    አንዳንዴም በተከሰሱበት ጉዳይ ጥፋተኛ ሆነው ቢፈረድባቸው ከሚጣልባቸው ቅጣት በላይ እንታሰሩ ማድረጉ በዋናነት የሚጠቀሡ ናቸው፡፡    

የፍርድ ቤቶች መዘግየት /ቀልጣፋ አለመሆን/ በሰብዓዊ መብቶች ላይ ያለው ተፅዕኖ ምንድን ነው?

የፍርድ ቤቶች መዘግየት ወይም ቀልጣፋ አለመሆን በዋናነት ሦስት የሰብዓዊ መብቶችን ይሸረሽራል ወይም ይጥሳል፡፡ እነርሱም 1ኛ/ ፍትሕ የማግኘት መብት፣ 2ኛ/ ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት መብት እና 3ኛ/ አድልዎ የሌለበትና ሚዛናዊ ዳኝነት የማግኘት መብት ናቸው፡፡

ፍትሕ የማግኘት መብት /The Right to Justice/

ፍትሕ የማግኘት መብት አቤቱታን፣ ቅሬታን ወይም ክስን ብቁ ለሆነ የዳኝነት አካል አቅርቦ እንዲታይና ውሳኔ እንዲያገኝ የማድረግ መብት ነው፡፡ ዳኝነት ይሰጠኝ በሚል ለሚቀርቡ አቤቱታዎችና ክሶችም በተገቢ ጊዜ ውስጥ ያለበቂ ምክንያት ውሳኔ ሳይሰጥ በተራዘሙ ተደጋጋሚ ቀጠሮዎች መዘግየት ለተከራካሪ ወገኖች ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ የሚያመዝንና ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚጥስ ነው፡፡ የፍርድ ቤቶች አሠራር ውጤትም በመዘግየት ምክንያት ፍትሐዊና ሚዛናዊ መሆን ካልቻለ ፍትሕ የማግኘት መብትን ይሸረሽራል፡፡ ተከራካሪ ወገኖችም በፍርድ ቤት የተንዛዛ አሠራር ምክንያት ጉዳያቸው በፍርድ ቤቶች ታይቶ እንዲወሰን ከማድረግ ይልቅ በሌላ ሁኔታ መብታቸውን ለማስከበር የሚሞክሩ ከሆነ በህግ አግባብ ፍትሕ የማግኘት መብት አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡

ውጤታማ መፍትሄ የማግኘት መብት/The Right to Effective Remedy/

በብዙ ሀገራት የዳኝነት አካል የተቋቋመበት ዋነኛው ምክንያት በተበደሉ ሰዎች ላይ የተፈፀመውን ሕገወጥ ተግባር በመለየት ውጤታማ መፍትሔ ለመስጠት ነው፡፡ ፍርድ ቤቶችም የቀረበላቸው ጉዳይ የወንጀልም ይሁን የፍትሐብሔር የሚሠጡት መፍትሔ ውጤታማ መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ውጤታማ መፍትሔ የመስጠት ሒደቱም አላስፈላጊ በሆነ መዘግየት የሚስተጓጉል ከሆነ ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት መብት የሚጥስ ይሆናል፡፡

በአላስፈላጊ መዘግየት ሲጓተት በቆየ ጉዳይ ላይ ከረጅም ጊዜ በኋላ የሚሠጥ ውሳኔም ዋጋ የሌለውና አንዳንድ ጊዜም ሊፈፀም የማይችል ሊሆን ይችላል፡፡ በክርክር ሂደቶች ላይ ከረጅም የክርክር ጊዜ በኋላ እንዲከፈሉ የሚወሰኑና የሚታዘዙ የገንዘብ ጥቅሞችና ዋጋ ክስ ከቀረበበት ጊዜና ፍርድ በሚሠጥበት ጊዜ ያላቸው አቅም መለያየት ብዙውን ጊዜ ውጤታማ መፍትሔ ላለመሰጠቱ በምሳሌነት ይጠቀሳል፡፡

የፍርድ መዘግየት በፍጥነትና በአጭሩ ታይተው እንዲወሰኑ የሚቀርቡ ክሶችና አቤቱታዎች ላይ ከረጅም ጊዜ ቆይታና መዘግየት በኋላ ፍርድ መሠጠቱም ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት መብትን እንደሚነካ ያሳያል፡፡

ሚዛናዊ ፍትሕ የማግኘት መብት /The Right to Fair Trial/

ሚዛናዊ ፍትሕ የማግኘት መብት የሚከበረው የዳኝነት አካሉ ነፃ እና ገለልተኛ ስለሆነ ብቻ ሳይሆን የተቀላጠፈ ፍትሕ ሲሰጥም ጭምር ነው፡፡ የፍትሕ ሒደቱ ያለበቂ ምክንያት ከዘገየና ከተራዘመ ሚዛናዊ ፍትሕ የማግኘት መብት ሊነካ ይችላል፡፡ ይኸውም የፍርድ ሂደቱ በተራዘመ ጊዜ የተከራካሪ ወገኖች እውነት እየደበዘዘና እየተዳፈነ የሚሄድ ከመሆኑም ባሻገር የፍርድ ቤቶች ዋነኛ ዓላማ በጉዳዩ ላይ ሚዛናዊ ፍርድ ከመስጠት ይልቅ ጉዳዩ ላይ የሆነውን ውሳኔ በመስጠት ማጠናቀቅ ስለሚሆን ሚዛናዊ ፍትሕ የማግኘት መብት ይሸረሽራል፡፡

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚመለከቱ የሕግ ድንጋጌዎች ምን ይመስላሉ? 

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚመለከቱ ዓለም አቀፍ፣ አሕጉር አቀፍ እና ሀገር አቀፍ የሕግ ማዕቀፎች ያሉ ሲሆን ሁሉም ድንጋጌዎች የፍትሕ ጥያቄ ተገቢና ምክንያታዊ በሆነ ጊዜ ውስጥ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ያለመክታሉ፡፡ እነዚህም፡ -

ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች

የሲቪልና የፖለቲካ  ምብቶች ዓለም አቀፍ ቃልኪዳን

በቃልኪዳኑ አንቀፅ 14 /3/ /ሐ/ ላይ በወንጀል ጉዳይ ተከሶ የቀረበ ሰው “አግባብ በሆነ ሁኔታ ሳይዘገይ የመዳኘት” መብት ያለው መሆኑን እንዲሁም በቃል ኪዳኑ አንቀፅ 14 /1/ ላይ ሚዛናዊ ፍትሕ የማግኘት መብት በጥቅሉ መቀመጡ የፍትሕ ጥያቄና አቤቱታ ሳይዘገይ በተቀላጠፈ ሁኔታ ምላሽ ሊሰጠው እንደሚገባ ያመለክታል፡፡ ቃልኪዳኑ ዳኝነት “ሳይዘገይ” ይሰጣል በሚል ያመልክት እንጂ አንድ ጉዳይ ዘግይቷል ወይም አልዘገየም ለማለት በመለኪያነት የተቀመጠ የጊዜ ገድብ የለም፡፡ ሆኖም ባደጉት ሀገራት ካለው አሠራርና የቃልኪዳኑን አፈፃፀም ከሚከታተለው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ ግምገማ እንደምንረዳው “ሳይዘገይ” የሚለው አገላለፅ የሚታየው ለዳኝነት እንደቀረበው ጉዳይ ሁኔታ ነው፡፡ በዚሁ መሠረትም አንድ ጉዳይ ዘግይቷል ወይም አልዘገየም ለማለት የወንጀሉን አደገኛነት፣ የጉዳዩን ውስብስብነት፣ ለመዘግየቱ የተከራካሪ ወገኖች አስተዋፅኦ፣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የወሰደበት ጊዜና ሌላ አሳማኝ ምክንያት መኖር አለመኖሩ ከግምት ሊገባ እንደሚገባ ተመልክቷል፡፡

የፍትሐብሔር ጉዳዮችን ወይም ክርክሮችን በተመለከተም በቃል ኪዳኑ አንቀፅ 14 (1) እና 26 ላይ በተመለከተው ሚዛናዊ ፍትሕ የማግኘት መብት እና በሕግ ፊት እኩል የመሆን መብት መሠረት ፍርድ ቤቶች ሳይዘገዩ የተቀላጠፈ ፍትሕ/ዳኝነት የመስጠት ኃላፊነት እንዳለባቸው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚቴ በጠቅላላ አስተያየቱ ቁጥር 13 ምዕራፍ 3 ላይ አመልከቷል፡፡

ሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች

በሌሎች ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ስምምነቶች ሚዛናዊ ፍትሕ የማግኘት መብትን የሚመለከቱ ድንጋጌዎችን የያዙ በመሆኑ ሳይዘገይ የተቀላጠፈ ፍትሕ የማግኘት መብት በዚህ ስር የሚሸፈን ይሆናል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሕፃናት መብቶች ስምምነት አንቀፅ 40 (2) (ለ) (3) ላይ ሕፃናት የወንጀል ድርጊት ፈጽመዋል ተብለው ሲከሰሱ ጉዳዩ ሳይዘገይ በፍጥነት እንዲታይ የተመለከተ መሆኑና አራተኛው የጄኔቫ ሰምምነት አንቀፅ 71 ላይ በጦርነት ጊዜ ሲቪሎችን ለመጠበቅ በተመለከተው ድንጋጌ መሠረት የተከሰሱ ሰዎች ሲኖሩ በተቻለ ፍጥነት ለፍርድ ሊቀርቡ እንደሚገባ የተመለከተ መሆኑ እንደተጨማሪ ዓለም አቀፍ የሕግ ጥበቃ ሊወሰድ ይችላል፡፡

አህጉራዊ የሕግ ጥበቃዎች

የአፍሪካ የሰዎችና የሕዝቦች ቻርተር

በቻርተሩ አንቀፅ 7 (1) (መ) ላይ ማንም ሰው የደረሰበትን በደል ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ አድሎአዊ ባልሆነ ፍርድ ቤት ወይም የፍርድ አካል የመዳኘት መብት እንዳለው ተመልክቷል፡፡

የአፍሪካ ሕፃናት መብቶችና ደሕንነት ቻርተር

በቻርተሩ አንቀፅ 17 (2) (ሐ) (4) ላይ ወጣት ጥፋተኞች ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ሲከሰሱ ገለልተኛ በሆነ የዳኝነት አካል ጉዳያቸውን በተቻለ ፍጥነት የማስወሰን ግዴታ በመንግሥታት ላይ ተጥሏል፡፡

ሀገራዊ የሕግ ጥበቃዎች

የኢ.ፌ.ዲ.ሪ. ሕገ መንግሥት

ሕገ መንግሥቱ በአንቀፅ 20 (1) ላይ የተከሰሱ ሰዎች ክስ ከቀርበባቸው በኋላ ተገቢ በሆነ አጭር ጊዜ ውስጥ በመደበኛ ፍርድ ቤት ለህዝብ ገልፅ በሆነ ችሎት የመሰማት መብት ያላቸው መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ይህ የህገ መንግሥት ድንጋጌ የሚመለከተው የወንጀል ጉዳይን ብቻ ቢመስልም በፍትሐብሔር ጉዳዮችም ቢሆን ሳይዘገይ ውሳኔ የማግኘት መብት ሚዛናዊ ፍትሕ በማግኘት መብት ስር የሚሸፈን በመሆኑ የሕግ ከለላ የለውም ለማለት አይቻልም፡፡  

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት እና የፍርድ ቤቶች አሠራርን የሚያመላክቱ ማሳያዎች ምን ይመስላሉ?

 ፍርድ ቤቶች ውሳኔ በሠጡባቸው ጉዳዮች ላይ መዝገብ ተከፍቶ ውሳኔ እስከሚሠጥበት የመጨረሻ ቀን ድረስ እንደ ጉዳዩ ዓይነት፣ ውስብስብነት፣ የተከራካሪ ወገኖች ክርክርና የሚቀርቡ ማስረጃዎች አይነት የሚወስደው ጊዜ የተለያየ ነው፡፡ በመሆኑም በምን ዓይነት ጉዳዮችና ሁኔታዎች ምን ያህል ጊዜ ይወስዳል? የሚለውን ለፍርድ ቤት ቀርበው ከተወሰኑ ውሳኔዎች በመነሳት እንደሚከተለው ማሳየት ይቻላል፡፡

የወንጀል ጉዳዮች

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በርካታ ዓይነት የፍትሐብሔር እና የወንጀል ጉዳዮች የሚታዩ ሲሆን በውሱን ጉዳዮች ላይ በተለየ ሁኔታ እጅግ ፈጥነው ውሳኔ የሚሰጥባቸው ጉዳዮች እንዳሉ ሆኖ በአብዛኛው ጉዳዮች ላይ የተፋጠነ ዳኝነት ይሰጣል ለማለት አያስደፍርም፡፡ ለዚህ ማሳያውም በፍርድ ቤቶቹ የታዩ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ከአፈፃፀምና ከሚጣለው ቅጣት አንፃር ቀላል የሚባሉ እንደ ስድብና ማዋረድ፣ ዛቻ፣ ስም ማጥፋት ወዘተ ያሉ የወንጀል ጉዳዮችን ክስ ቀርቦ በፍርድ ቤት መዝገብ ከተከፈተበት ቀን ጀምሮ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ የሚወስደው ጊዜ፡-  

  • ተከሳሽ የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን ካመነ ከአንድ ወይም ሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ በአብዛኛው የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፤ /በብዛት ከሁለት እስከ ሦስት ቀጠሮ ይኖራል/
  • ተከሳሽ የቀረበበትን ክስ ክዶ የሚከራከር ከሆነ ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል /የቀጠሮ ብዛቱም በአማካይ ከ5 እስከ 8 ይደርሳል/  

ከአፈፃፀምና ቅጣት አንፃር መካከለኛ በሚባሉ እንደ ስርቆት እና እምነት ማጉደል ባሉ የወንጀል ጉዳዮችን ክስ ቀርቦ በፍርድ ቤት መዝገብ ከተከፈተበት ቀን ጀምሮ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ የሚወስደው ጊዜ፡-  

·         ተከሳሽ የቀረበበትን የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን ካመነ ከአንድ ወይም ሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥ ይታያል፤ /በአብዛኛው ከሁለት እስከ ሦስት ቀጠሮ ይኖራል/

  • ተከሳሽ የተከሰሰበትን  የወንጀል ድርጊት አልፈጸምኩም በሚል ክዶ የሚከራከር ከሆነ በአማካኝ ከሦስት እስከ ሰባት ወራት ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፤ /በአብዛኛው ከአራት እስከ ሰባት የሚደርሱ ቀጠሮች ይሰጣሉ/

ከአፈፃፀም እና ከሚጣለው ቅጣት አንፃር እንደ ከባድ ስርቆት፣ የጉምሩክ ወንጀሎች፣ አስድዶ መድፈር ወንጀልና ሌሎች ከበድ ያሉ የወንጀል ጉዳዮችን ክስ ቀርቦ በፍርድ ቤት መዝገብ ከተከፈተበት ቀን ጀምሮ ውሳኔ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ የሚወስደው ጊዜ፡-  

·  ተከሳሽ የቀረበበትን የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን ካመነ ከአንድ እስከ ሁለት ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ /በብዛት ከሁለት እስከ ሰባት ቀጠሮ ይኖራል/

·       ተከሳሽ የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት አልፈፀምኩም በሚል ክዶ የሚከራከር ከሆነ በአማካይ ከአራት ወራት እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ይሰጣል /ከአምስት እስከ አስር የሚደርሱ ቀጠሮዎች ይሰጣሉ/

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

በአንድ ዳኛ የሚያስችሉ ችሎቶች

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአንድ ዳኛ የሚያስችሉ የወንጀል ችሎቶች ላይ በአንድ ዳኛ የሚታዩ ጉዳዮች ላይ ተከሳሽ የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን ሲያምን ከአንድ ሳምንት እስከ አንድ ወር ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ተከሳሽ ክዶ በሚከራከር ጊዜ ጉዳዩ ተጀምሮ እስከሚያልቅ ድረስ በአብዛኛው ከስድስት ወራት እስከ አንድ አመት ከሦስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን የቀጠሮ ብዛቱም በአብዛኛው ከስምንት እስከ አስራ አምስት ይደርሳል፡፡ የይግባኝ ወንጀል ችሎቶች የሚታዩ መዛግብትም ቢሆኑ ከተከፈቱበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሠጣቸው ድረስ የታሰረ ሰው ያለባቸው መዛግብት ከሦስት እስከ ስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ እንዲሁም የታሠረ ሰው በሌለባቸው መዛግብት ላይ ከአምስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ይደርሳል፡፡ በአንዳንድ የይግባኝ ወንጀል ችሎቶች ላይ የይግባኝ ቅሬታው ተቃራኒ ወገን ያስቀርባል ወይም አያስቀርብም ለማለት በቅድሚያ ቅሬታውን ይግባኝ ባዩ ለብቻው እንዲሠማ ሲደርግ የቀጠሮው ብዛትና የሚወስደው ጊዜ በተጨማሪነት የቀጠሮውን ቁጥርና ጊዜውን ከፍ ያደርገዋል፡፡

ሦስት ዳኞች በሚያስችሉባቸው ችሎቶች የሚታዩ ጉዳዮች በአፈፃፀማቸው፣ የሚጣለው ቅጣትና ውስብስብነት አንፃር በአብዛኛው ከባድ የሚባሉ ሲሆኑ በእነዚህ ችሎቶች ተከሳሽ የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት መፈፀሙን ካመነ ከአንድ ሳምንት እስከ ሁለት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን ተከሳሽ የተከሰሰበትን የወንጀል ድርጊት ክዶ የሚከራከር ከሆነ በአብዛኛው ከስምንት ወራት እስከ ሁለት ዓመት ከሁለት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን በተከታታይ የሚሠጥ የቀጠሮ ብዛትም ከስምንት እስከ ሀያ ሁለት ይደርሳል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በአብዛኛው የሚታየው የወንጀል ይግባኝ ጉዳይ መዝገቡ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ግራ ቀኙ ወገኖች ተከራክረው የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሠጥ ድረስ በብዛት ከአራት እስከ ስምንት ወራት የሚወስድ ሲሆን የይግባኝ ባይን ቅሬታ ብቻ ሠምቶ ተቃራኒ ወገንን አስቀርቦ ለማከራከር ያስችላል ወይም አያስችልም ለማለት ደግሞ ከሁለት ወራት እስከ አምስት ወራት ጊዜ ይወስዳል፡፡

የፍትሐብሔር ጉዳዮችን በተመለከተ

በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት

በተከራካሪ ወገኖች በኩል ወሰብሰብ ያለ የፍሬ ነገርና የሕግ ክርክር ባለባቸው ጉዳዮች ላይ በአብዛኛው ከአንድ ዓመት እስከ ሁለት ዓመት ከስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን በተከራካሪ ወገኖች መካከል ግልፅ የሆኑና በቀላሉ ውሳኔ ሊሠጥባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ላይ ከአምስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ሲሰጥ ይታያል፡፡ የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳዮች ላይም በአንፃራዊነት ከሌላው የፍትሐብሔር ጉዳይ በተሻለ ቀጠሮ ለማሳጠር ጥረት የሚደረግ ቢሆንም ከአራት ወራት እስከ አስር ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥ ይስተዋላል፡፡

በፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 284 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሠረት በአጭር ሁኔታ ታይተው ውሳኔ እንዲሠጥባቸው የሚፈለጉ ጉዳዮችም ቢሆኑ በአብዛኛው ከሦስት ወራት እስከ አስራ አንድ ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥባቸው መሆኑ ይታያል፡፡

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

መደበኛ ክስ በሚቀርብባቸውና ሠነዶች በብዛት ባሉባቸው የፍሬ ነገርና የሕግ ክርክሮችም በሚኖርባቸው ጉዳዮች ላይ በአብዛኛው ከስምንት ወራት እስከ ሁለት ዓመት ከአምስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ የሚሰጥ ሲሆን ከውስብስብነት አንፃር ቀላል ሊባሉ በሚችሉ መዛግብት ላይ ከሰባት ወራት እስከ አንድ ዓመት በስድስት ወራት ባለው ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥባቸው ይታያል፡፡

የፍትሐብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 284 እና ተከታይ ድንጋጌዎች መሠረት በአጭር ሁኔታ ታይተው ውሳኔ እንዲሠጥባቸው የሚፈልጉ ጉዳዮች ላይም ቢሆን ከመደበኛ ክሶች ባልተናነሰ በአብዛኛው ከአምስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ከስምንት ወራት ጊዜ ውስጥ የመጨረሻ ውሳኔ ሲሰጥ ይታያል፡፡

የፍትሐብሔር ይግባኝ ችሎቶች ላይም በአብዛኛው ከአምስት ወራት እስከ አንድ ዓመት ከስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የግራቀኙ ክርክር ተሰምቶ የሚወሰን ሲሆን ይግባኝ ባዩን ብቻ ቅሬታውን በመስማት ተቃራኒ ወገን አስቀርቦ ለመከራከር የሚያስችል በቂ ምክንያት አለ ወይም የለም ብሎ ለመወሰን ከሦስት ወራት እስከ ሰባት ወራት ጊዜ ሲወስድ ይታያል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

የይግባኝ ባይን ቅሬታ ሠምቶ ተቃራኒ ወገን በማስቀረብ ለመከራከር የሚያስችል ምክንያት አለ ወይም የለም ለማለት መዝገቡ ከተከፈለበት ጊዜ ጀምሮ ከሦስት እስከ ሰባት ወራት ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ግራ ቀኙ የቀረቡበትንና ክርክር የተደረገበትን መዝገብ መርምሮ የመጨረሻ ውሳኔ ለመስጠት ከሰባት ወራት እስከ አንድ ዓመት ከሦስት ወራት ድረስ ጊዜ ይወስዳል፡፡

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት

የሰበር አቤቱታው ግራ ቀኙን ለማከራከርና ከአምስት ዳኞች ለሚታየው ችሎት ሊቀርብ ይገባል ወይስ አይገባም የሚለውን መርምሮ ተገቢውን ትዕዛዝ የሚሠጠው በሦስት ዳኞች በሚታየው ችሎት ላይ የሰበር አቤቱታ ለፍ/ቤቱ ቀርቦ መዝገብ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ ተገቢው ትዕዛዝ እስከሚሠጥ ድረስ በአብዛኛው ከሁለት ወራት እስከ አምስት ወራት ጊዜ የሚወስድ ሲሆን ግራ ቀኙ በሚከራከሩበት በአምስት ዳኞች በሚታየው የሰበር ችሎት መዝገቡ ከተከፈተበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሠጥበት ጊዜ ድረስ ከሰባት ወራት እስከ አንድ ዓመት ከሁለት ወራት ጊዜ ሲወስድ ይታያል፡፡

በጉዳዮች ላይ ውሳኔ ለመስጠት የተቀመጠው ጊዜ በተጨባጭ በችሎት ታይተው ውሳኔ ያገኙ መዛግብትን፣ የባለጉዳዮችንና የጠበቆችን አስተያየት እንዲሁም በቀጠሮ ላይ ያሉ መዛግብትን መሠረት በማድረግ የተቀመጠ ሲሆን እንደ ጉዳዩ ልዩ ባህሪና ሁኔታ እንዲሁም እንደ የችሎቶቹ ቅልጥፍናና ፍጥነት ማጣት ከፍ ብለው ከተቀመጡበት ጊዜያት ፈጥነው ያለቁና የሚያልቁ እንዲሁም ከተጠቀሰው ጊዜ በጣም ዘግይተው የተወሰኑና የሚወሰኑ መዛግብቶች አሉ፡፡ የተቀመጠው ጊዜም አንድ መዝገብ በፍርድ ቤት ተከፍቶ የመጀመሪያ ቀጠሮ እስከሚሰጥበት ድረስ ያለውን ጊዜ የማይጨምር ሲሆን በአብዛኛው መዝገብ ከተከፈተበት የመጀመሪያ ቀጠሮ እስከሚሰጥ ድረስ ከሦስት ሳምንት እስከ ሁለት ወራት ጊዜ ስለሚኖር በተጨማሪነት ይኼንኑ ጊዜ ማሰብ ይቻላል፡፡

በመዛግብት ላይ ውሳኔ ለመስጠት እንደየፍርድ ቤቶቹና ጉዳዮቹ ከፍ ብሎ የተጠቀሡትን ጊዜያት ከግምት በማስገባት ከመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጀምሮ ከፍተኛ ፍርድ ቤትንና ጠቅላይ ፍርድ ቤትን እንዲሁም የሰበር ችሎት የደረሱና የሚደርሱ ጉዳዮችን የሚከታተሉ ባለጉዳዮችና ጠበቆች ምን ያህል እጅግ ረጅም ጊዜና እልህ አስጨራሽ ሂደቶችን እንደሚያልፉ መገመት አያዳግትም፡፡

በሁለት ቀጠሮዎች መካከል የሚኖረው ጊዜ ምን ያህል ነው?

ፍርድ ቤቶች በተለያዩ ውስጣዊ እና ውጫዊ ምክንያቶች የሚሠጡት ተደጋጋሚ ቀጠሮ እንደተጠበቀ ሆኖ በሁለት ቀጠሮዎች መካከል ያለው የጊዜ ርቀት የተፋጠነ ፍትሕ ላላመስጠት ዋነኛው ምክንያት ነው፡፡

አንድ መዝገብ ተከፍቶ የመጀመሪያ ቀጠሮ እስከሚይዝበት እንዲሁም ተከራካሪ ወገኖች በችሎት በመቅረብ ተስተናግደው ቀጣዩን ተግባር ለማከናወን እስከሚቀጠርበት ቀጠሮ ድረስ ያለው የጊዜ ርዝማኔ በተለያዩ ምክንያቶች ረጃጅም ነው፡፡ በምሳሌነት ለማሳየትም

በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት

በወንጀል ጉዳዮች፡- በአብዛኛው በሁለት ቀጠሮች መካከል ያለው የቀጠሮ ርዝመት ከአንድ ወር እስከ ሁለት ወራት ከአስራ አምስት ቀናት ይደርሳል፡፡

በፍትሐብሔር ጉዳዮች፡- እንደሚቀጠርበት ምክንያት ቢለያይም ክስ ለመሰማትና ምስክር ለመሰማት እንዲሁም ለምርመራ የሚቀጠሩ መዛግብት በብዛት ከአንድ ወር እስከ ሁለት ወራት ይደርሳል፡፡ ለሌሎች ጉዳዮች የሚቀጠሩ መዛግብት በተመሳሳይ የጊዜ ርዝማኔ ቢቀጠርም አልፎ አልፎ አጠር ያለ ጊዜ ሲሰጥ ይታያል፡፡

በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት

በወንጀል ጉዳዮች - በሁለት ቀጠሮዎች መካከል ያለው የጊዜ ርዝማኔ ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወራት ይደርሳል፡፡

በፍትሐብሔር ጉዳዮች - በሁለት ቀጠሮዎች መካካል ያለ ቀጠሮ ርዝመት በአብዛኛው ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወራት ይደርሳል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት

በወንጀል ጉዳይ - በሁለት ቀጠሮዎች መካከል ያለው የጊዜ ርዝማኔ ከአንድ ወር እሰከ ሁለት ወራት ይደርሳል፡፡

በፍትሐብሔር ጉዳይ - በሁለት ቀጠሮዎች መካከል ያለው የጊዜ ርዝማኔ ከአንድ ወር እስከ ሦስት ወራት ከ15 ቀናት ይደርሳል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት

በሦስት ዳኞች የሚታየው ተጠሪን አስቀርቦ የሰበር አቤቱታውን መመርመር ያስፈልጋል ወይስ አያስፈልግም ለማለት የሚሠጠው ቀጠሮ መዝገቡ ከተከፈተበት የመጀመሪያ ቀጠሮ እስከሚይዝበት ያለውን ጊዜ ሳይጨምር አቤቱታ አቅራቢው አቤቱታውን አሰምቶ ከጨረሰ በኋላ ብዙውን ጊዜ ከአንድ ሳምንት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለሰበር ችሎት አያስቀርብም ወይም ያስቀርባል የሚል ትዕዛዝ ይሰጣል፡፡

በአምስት ዳኞች የሚያስችለው የሰበር ችሎት ላይ በሁለት ቀጠሮዎች መካከል ያለው የጊዜ ርዝማኔ ከአንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት እስከ አምስት ወራት ይደርሳል፡፡

በተለምዶ በየዓመቱ ከነሀሴ ወር መጀመሪያ እስከ መስከረም ወር መጨረሻ ድረስ ለሁለት ወራት ፍርድ ቤቶች መደበኛውን ስራ የማይሠሩበት ዝግ ጊዜ በመሆኑ ከፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት እስከ ፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት ድረስ በሰኔና ሐምሌ ወራት ላይ የሚሠጠው ቀጠሮ እስከቀጣዩ ቀጠሮ ድረስ ከሦስት እስከ አራት ወራት ድረስ የሚደርስባቸው ጊዜያት በርካታ ነው፡፡    

ፍርድ ቤቶች በሁለት ቀጠሮዎች መካከል ረጅም ጊዜ ቀጠሮ የሚሠጡባቸው የተለያዩ ምክንያቶች ያሉ ሲሆን ቀጠሮ ሲሰጥ ለተከራካሪ ወገኖች የሚነገሩት ምክንያቶች፡ - 

መዝገቡን መርምሮ ለመስራት በቂ ጊዜ ያስፈልገዋል፣

በስብሰባ ወይም ስልጠና ምክንያት ችሎቱ ስራ አይሰራም፣

በክረምቱ ጊዜ በተለይም ከነሐሴ መጀመሪያ እስከ መስከረም መጨረሻ ፍርድ ቤቶች አይሰሩም፣

ብዙ መዝገብ ስላለ መስራት አይቻልም፣

አጀንዳው የተጣበበ ነው፣ ወዘተ……. የሚሉ ይገኝበታል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፍርድ ቤቶች አሠራር የተፋጠነ ፍትሕ ከማግኘት መብት አንፃር ምን ይመስላል?

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጀመሪያ ደረጃ እና ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤቶች እንደ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በቁጥር እና በዓይነት በርካታ እና የተለያዩ መዛግብት ባይመለከቱም የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን በማክበር ረገድ ግን ውጤታማ አሰራር አላቸው ብሎ ለመናገር ይቻላል፡፡

ይኸውም፡ -

የከተማ አስተዳደሩ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ወራሽነትን እና ሚስትነትን በማረጋገጥ እንዲሁም የስም ለውጥ ወዘተ የመሳሰሉ ጉዳዮችን አቤቱታው ከቀረበበት ጊዜ ጀምሮ የመጨረሻ ውሳኔ እስከሚሰጥት ድረስ በግማሽ ቀን ውስጥ በጣም ከበዛ ደግሞ በአንድ ሙሉ ቀን ውስጥ ውሳኔ መስጠታቸው፤

የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤቶች ግራ ቀኙ በሚከራከሩባቸው እና ማስረጃ መስማትን በሚጠይቁ ጉዳዮች ላይም ቢሆን ውሳኔ የሚሠጡት ከአስራ አምስት ቀናት እስከ አንድ ወር ከአስራ አምስት ቀናት በሚደርስ ጊዜ ውስጥ መሆኑ፤

የከተማው ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤትም ሆነ የከተማው ሰበር ሰሚ ችሎት ግራ ቀኙን ወገኖች አከራክረው የይግባኝ መዝገብ ላይ ለመወሰን የሚወስድባቸው ጊዜ እጅግ ቢበዛ ከሁለት ወራት ያልበለጠ መሆኑ፤

በከተማው የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤትም ሆነ ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት በሁለት ቀጠሮዎች መካከል ያለው የጊዜ ርዝማኔም ከአንድ ሳምንት እስከ ሁለት ሳምንት የሚደርስ መሆኑ፤

የከተማ አስተዳደሩ ፍርድ ቤቶች እንደ ፌዴራል ፍርድ ቤቶች በየዓመቱ ከነሀሴ መጀመሪያ እስከ መስከረም መጨረሻ ድረስ መደበኛ ሥራቸው የማይቋረጥና የማይዘጉ መሆናቸው፣ የዳኞች ቁጥር ከመዝገብ ብዛት አንፃር ተመጣጣኝ መሆኑ እና ሌሎች ሁኔታዎች ለአሠራር ቅልጥፍናው አስተዋፅኦ ያበረከተ ሲሆን እንደአጠቃላይ ፍርድ ቤቶቹ የተፋጠነ ፍትሕ በመስጠት ሂደት ላይ ውጤታ አሠራር አላቸው ለማለት ያስደፍራል፡፡

የዳኞች ቁጥር እና የመዛግብት ቁጥር መመጣጠን ምን ይመስላል?

የመዛግብት ብዛት ምን ይመስላል?

ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. የወጣው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ እንደተገለፀው የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰባት ወራት ዕቅድ አፈፃፀም ሪፖርቱን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በምክትል ፕሬዚዳንቱ በኩል ሲያቀርብ፡ -  

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በበጀት ዓመቱ 9690 መዛግብት ለችሎት ይቀርባል ተብሎ ታቅዶ 9846 መዛግብት ለችሎት መቅረቡንና በ5896 መዛግብት ላይ ውሳኔ መሠጠቱን፤

በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በበጀት ዓመቱ 27260 መዛግብት ለችሎት ይቀርባል ተብሎ ታቅዶ 19808 መዛግብት ለችሎት መቅረቡንና በ8877 መዛግብት ላይ ውሳኔ መሠጠቱን፤

በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት በበጀት ዓመቱ 86100 መዛግብት ለችሎት ይቀርባል ተብሎ ታቅዶ 79307 መዛግብት ለችሎት መቅረቡንና በ53640 መዛግብት ላይ ውሳኔ መሠጠቱ ተገልጿል፡፡

የመዛግት ብዛትና የዳኞች ቁጥር ንፅፅር ምን ይመስላል?

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በየስድስት ወራቱ በሚያወጣውና “ችሎት” በተሠኘው ሚያዝያ 2007 ዓ.ም. በወጣው መፅሔት ላይ በአጠቃላይ በፌዴራል ፍርድ ቤቶች 224 ዳኞች በሥራ ላይ እንደሚገኙ በመፅሔቱ ገፅ 11 ላይ ተገልጿል፡፡

በፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሁሉም ችሎቶች እንዲሁም በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተወሰኑ ችሎቶች መዛግብት የሚታዩት በሦስት ዳኞች መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አንድ መዝገብ በአንድ ዳኛ ይታያል ተብሎ ቢታሰብ እንኳን በበጀት ዓመቱ በሰባት ወራት ውስጥ ለፌዴራል ፍርድ ቤቶች ከቀረቡና ከታዩ አጠቃላይ የመዛግብት ቁጥር አንፃር አንድ ዳኛ በሰባት ወራት ውስጥ በአማካይ 442 መዛግብት ላይ ክርክር እና ማስረጃ ሰምቶ መወሰን ይጠበቅበታል ብሎ መውሰድ ይቻላል፡፡ በሦስት ዳኞች የሚታዩ ጉዳዮች ላይም የመዛግብት ብዛቱ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችል መገመት ይቻላል፡፡

የዳኞች ብዛትና የመዛግብት ብዛት ሲነፃፀርም አንድ ዳኛ ተመልክቶ እንዲወስን የሚጠበቅበት የመዛግብት ብዛት በጣም በርካታ ሲሆን እያንዳንዱ ጉዳይ ላይ በቂ ጊዜ በመውሰድ ክርክርና ማስረጃ ሠምቶ በአጭር ጊዜ ለሁሉም ተገልጋይ የተፋጠነና ውጤታማ ፍትሕ መስጠት አስቸጋሪ ይሆናል፡፡

በመሆኑም አንድ ዳኛ ምክንያታዊ በሚባል ጊዜ ውስጥ መዛግብት ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚመለከታቸው መዛግብት ብዛት ተመጣጣኝ እና በአግባቡ ሊሰራ በሚችል ልክ መሆን እንዳለበት ልብ ሊባል ይገባዋል፡፡

በየጊዜው እየጨመረ የመጣውን የመዛግብት ብዛት ወቅቱን በጠበቀና ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ለማስተናገድ ከመዛግብት ብዛት ጋር ተመጣጣኝ የሆነ የዳኞች ብዛት እንዲኖር ማድረግን ይጠይቃል፡፡

የመፍትሔ ሀሳቦች

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብትን በማክበርና ማስከበር ረገድ ውጤታማ ሥራዎች ለመስራት የሚከተሉት ነጥቦችን በመፍትሔነት ለመውሰድ ይቻላል፡፡ እነዚህም፡ -

ከመዛግብት ብዛት ጋር ተመጣጣኝ ቁጥር ያለው የሰው ኃይል ማዘጋጀት/ዳኞች እና ሌሎች ሠራተኞች/፣

ዕውቀት፣ ልምድ እና ሥነ ምግባር ያላቸው ዳኞችን ብቻ መሾም፣

ለዳኝነት ሥራው መቀላጠፍ የሚግዙ አቅርቦቶችን በአግባቡ ማሟላት፣

በችሎቶች ቁጥር ልክ ለሥራ የሚያገለግሉ አስፈላጊ አቅርቦቶች የተሟላላቸው ችሎቶች እንዲኖሩ ማድረግ፣

የፍርድ ቤቶችን አሠራር ሊያቀላጥፉ እና ፍጥነት ሊጨምሩ የሚችሉ የቴክኖሎጂ ውጤቶችን በሁሉም ችሎቶች ላይ መጠቀም፣

ጉዳዮችን እንደቅለታቸውና ክብደታቸው ታይተው ውሳኔ ሊያገኙ የሚገባበትን የጊዜ ርዝማኔ የሚመለከት ሕግ እንዲወጣ ማድረግ፣

በቀጠሮ ሠዓትና ቀናት ሥራቸውን ያለበቂ ምክንያት የማይሰሩ ዳኞች ላይ ተገቢውን እርምጃ መውሰድ፣

በስልጠና እና ስብሰባ ምክንያት የሚባክኑ የሥራ ጊዜያትን ማስወገድ ወይም የስልጠና እና ስብሰባ ቀናትን ከሥራ ሠዓት እና ቀናት ውጪ ማድረግ፣

 

ነሀሴ እና ሀምሌ ወራትን ለሁለት ወራት የሚዘጋውን ጊዜ ማሳጠር፣ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

አዲሱ የፀረ ሙስና ሕግ በግል ኩባንያወች ላይ ተፈፃሚነቱና የሕግ አንድምታው
የእንደራሴነት ሕግ (Agency Law) ዋና ዋና ነጥቦች
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Tuesday, 23 July 2024