Font size: +
37 minutes reading time (7423 words)

የእንደራሴነት ሕግ (Agency Law) ዋና ዋና ነጥቦች

ሰዎች ኑሮአቸውን ስኬታማ ለማድረግ በሚፈጽሙት የእለት ተእለት ተግባራቸው ከሌሎች የማህበረሰቡ ክፍሎች ጋር ዘርፈ ብዙ መስተጋብሮችን የሚፈጽሙ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ይሁንና እነኚህን መስተጋብሮች  በተለያዩ ምክኒያቶች በራሳቸው ለመፈጸም የማይችሉ በሆነ ጊዜ ሥራዎችን ሌላ ሰው እንዲያከናውንላቸው ፍላጎት ሊያድርባቸው እንደሚችል የሚያሻማ አይደለም፡፡ በዚሁ መሠረት ይህንኑ ሥራቸውን ማን፣ መቼ፣ በምን ሁኔታ እና በድካም ዋጋ ክፍያ ወይም ያለ ክፍያ  ሊሠራላቸው እንደሚገባ የመወሰን ነጻነት ሊኖራቸው የተገባ ነው፡፡  

ሁሉም የማህበረሰብ ክፍል ለማለት ባይቻልም አብዛኛው ስለ እንደራሴነት ወይም ውክልና ግንኙነት ጠቅለል ያለ መጠነኛ ግንዛቤ ይኑረው እንጂ በኢትዮጵያ ፍትሕ ሥርዓት ትግበራ መሣሪያ ከሆኑት ሕጎች አንዱ ስለሆነው የፍትሐብሔር ሕግ በልዩ ትኩረትም ስለ እንደራሴነት በቂ እና ጥልቅ ግንዛቤ ይኖረዋል ተብሎ ግምት አይወሰድም፡፡ በዚህም ምክንያት በሥራውም ሆነ በንብረቱ ላይ ሌሎችን ለመወከል የሚወስዳቸውን ጥንቃቄ  ለማወቅ፣ ያሉትን መብቶች እና ስለሚወክለው ሰውም ሆነ የተወከለው ሰው ከሦስተኛ ወገን ጋር ስለሚገባው ግዴታ ያሉበት ኃላፊነቶች ለይቶ ለማወቅ የሚቸገር በመሆኑ በጥቅሙ  እና በመብቱ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት ሲደርስበት እንታዘባለን፡፡

ከሕግ (ፍትሕ) አገልግሎት ጋር በተያያዘ  የሙያ ሥራ ላይ የተሠማሩ ባለሙያዎችም ይህንን የሕግ ጽንሰ ሀሳብ በሚገባ ማወቅ እና ሥራ ላይ ማዋል መቻል ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም በግንኙነት በደል የደረሰባቸውን ሰዎች መብት ከማስጠበቅ አንጻር የሚጫወቱት ሚና ጉልህ ነውና፡፡

የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ዋና ዋና በሆኑ የውክልና ሕግ ድንጋጌዎች ወይም ነጥቦች  ዙርያ ህብረተሰቡ የተሻለ ግንዛቤ ኖሮት  በውክልና ግንኙነት ውስጥ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ትስስር እንዲፈጥር እና መብቶቹ ተጥሰው ሲገኙም  የፍትሕ ተቁዋማትን በመገልገል መብቱን እንዲያሰከብር ለማስቻል ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ስለ እንደራሴነት ምንነት እና አስፈላጊነት፣ ስለ ውክልና ግንኙነት አመሠራረት እና የውል አግባብነትን፣ የወካይ እና የእንደራሴ ግዴታዎች፣ የወካይ እና የእንደራሴ ግንኙነት ስለሚቋረጥበት ወይም ቀሪ ስለሚሆንበት ምክንያት እና ሕጋዊ ውጤቱ የሚዳሰሱ ይሆናል፡፡

ስለ እንደራሴነት ምንነት እና አስፈላጊነት    

ስለውሎች በጠቅላላው ሁሉንም በአንድ ሊያስማማ የሚችል እና በወጥነት ለመጠቀስ የሚችል የጋራ የሆነ ትርጉም የሌለ እንደሆነ ሁሉ የእንደራሴነት ግንኙነትን በተመለከተም ወጥ የሆነ ትርጉም የለም፡፡ ሀገራት እንደየ ህዝቡ ማህበራዊ እና ምጣኔ ሀብታዊ መስተጋብር ባሕርይ እና ከሚከተሉት የፍትሕ ሥርዓት (justice system) አንጻር የተለያየ ትርጉም ሊሰጡት ይችላሉ፡፡

ለምሳሌ በሀገረ አሜሪካ በሥራ ላይ ያለው የእንደራሴነት ሕግ ለግንኙነቱ የሰጠው ትርጉም “it is a consensual relationship created by contract or by law where one party, the principal  grants authority for another party, the agent to act on behalf of & under the control of  principal to deal with a third party bind the principal” ሲል ነው፡፡

ወካዩ  እና ተወካዩ ወይም እንደራሴ በሆኑት ሁለት ሰዎች መካከል  በጋራ መግባባት ላይ በተመሠረተ የውል ግንኙነት  ወይም በሕግ ወካይ ለተወካይ በሚሰጠው ሥልጣን  ተወካዩ  በወካዩ  ቁጥጥር ስር በመሆን ስለእሱ ወይም በሱ ቦታ ሆኖ ወካዩን ሊያስገድድ የሚችል ስነምምነትን  ከሦስተኛ ወገን ጋር  እንዲዋዋል መፍቀድ በሚል ወደ አማርኛ ሊተረጎም ይችላል፡፡ በዚህ ትርጉም ውስጥ  አንኳር  የሆኑትን ነጥቦች ለመመልከት ያህል  የውክልና ግንኙነት በሁለት ሰዎች(በተፈጥሮም ሆነ ሕግ በወለዳቸው )  መካከል  የሚፈጠር ሲሆን ይህ ግንኙነት ተዋዋዮች  በሚገቡት ውል ወይም ሕጉ ባስቀመጠው አግባብ ሊመሠረት እንደሚችል፣ ተወካይ ሥራውን በሚሠራበት ጊዜም  ወካዩ ሊቆጣጠረው እና መመርያ ሊሰጠው እንደሚችል፣ ሥራውንም ስለ ወካዩ ሲል የሚሠራ እና ከሦስተኛወገን ጋር በሚገባው የውል ግንኙነትም ወካዩ የሚገደድ መሆኑን የሚያካትት ነው፡፡

በሌላ በኩል በዘርፉ ጥናት ያደረጉ የሕግ ጸሀፍት  ስለ እንደራሴነት ከሰጧቻው ትርጉሞች መካከል አንዱ እና ሌላኛው ’It is አ fiduciአry relአtion which results from the mአnifestአtion  of consent by the person (the principal) to another (the agent) that the other( the agent) shall act on his (the principal’s) behalf & subjected  to his principal’s control, a consent by the other(agent)so to act’ በሚል ያስቀምጣሉ፡፡ ይህ ትርጉም ከላይ ከተዳሰሰው የአሜሪካኖች ትርጉም  ጋር ተቀራራቢ ሲሆን መሠረቱም ሆነ ግቡ በመተማመን ላይ በሚመረኮዝ ግንኙነት አንዱ ለሌላው በሚገልጸው ፍቃድ መሠረት አንዱ የሌላውን ሥራ በዛ ሰው ቁጥጥር ስር ሆኖ  የሚሠራበት ስለመሆኑ የሚገልጽ ነው፡፡  

የ1952ቱም የንጉሰ ነገስቱ የፍትሐብሔር ሕግም ውክልና ማለት ተወካይ  የተባለ አንድ ሰው ወካይ ለተባለ ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ሕጋዊ ሥራዎችን በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ነው ሲል ትርጉም ሰጠቶታል፡፡ ከዚህ ትርጉም የምንረዳው በሁለት ሰዎች መካከል በሚፈጸም የውል ግንኙነት  እንደራሴው  የወካዩን የሥራ ተግባር  በወካዩ ስም ለማከናወን ግዴታ የሚወስድበት ሲሆን የሚሠራውን ሥራ በተመለከተ ምንም ዓይነት  የይዘት እና የጊዜ ገደብ ሳይደረግበት በአንድ ነጠላ ጉዳይ ወይም ተመሳሳይም ሆነ  ልዩነት ባላቸው ሁለት እና ከዛ በላይ ለሆኑ ጉዳዮች የውክልና ሥልጣንን መውሰድ የሚቻልበት መሆኑን ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ተዋዋዮች የውክልና ግንኙነቱን በሚመሰርቱበት ጊዜ የውሉ ፍሬ ነገር ሕጋዊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ በመሆኑም  እንደራሴው ስለ ወካዩ ሆኖ የሚያከናውነው ሥራ በሕግ የተከለከለን ድርጊት ለማድረግ እንዲደረግ የታዘዘውን ደግሞ ላለማድርግ መሆን አይገባውም ፡፡ ስለ ውል በጠቅላላው ርዕስ ስር ውልን ቀሪ ከሚያደርጉ ምክንያቶች አንዱ የውል ጉዳይ ሕጋዊ መሆን ነው፡፡

የእንደራሴነት ግንኙነት እና የሕጉ አስፈላጊነት

ሰዎች (የተፈጥሮ ወይም በሕግ ሰውነት የተሰጣቸው) የሚያከናውኗቸውን የንግድ፣ የአስተዳደር እና  የአገልግሎት ተግባራትን በራሳቸው ለመፈጸም የማይጣስ መብት አላቸው፡፡ ይሁንና በተለያዩ ምክኒያቶች ሥራውን በራሳቸው ለመፈጸም  የማይችሉበት አጋጣሚ ሊፈጠር እንደሚችል አያጠያይቅም፡፡ ከነኚ ምክኒያቶች የተወሰኑት ሰዎች በጤናቸው ላይ  በሚገጥማቸው እክል ወይም ሥራው ከሚከናወንበት ስፍራ መራቅ፣ ስለ ሥራው በቂ የሆነ ዕውቀት እና ልምድ ማጣት፣ በአንድ ጊዜ በተለያዩ ቦታዎች ያሉ ሥራዎችን ለመሥራት መቸገር፣ ውልን ለመዋዋል ችሎታ ማጣት እና የመሳሰሉት ናቸው፡፡

በነዚህ ምከንያትቶች ሊያጡ ከሚችሉት መብት እና ጥቅም አንጻር  ሥራው በሌላ ሰው እንዲፈጸምላቸው የማደርግ አማራጭ  መጠቀም  ይኖርባቸዋል፡፡

በመሆኑም  ሥርዓት ባለው፣ በሕግ በሚመራ  እና መብት እና ግዴታን በግልጽ በሚያቅፍ የእንደራሴነት  ግንኙነት ውስጥ መግባት ያስፈልጋል፡፡ ለምሳሌ  በሥራ ምክንያት ላልተወሰነ ጊዜ ወደ ዱባይ ሀገር  የተጓዘው አቶ ሀ ሀገር ውስጥ ቢኖር ኖሮ እንዲፈጽም ግዴታ የሆኑበትን እነደ የገቢ ግብር ክፍያ፣ የንግድ ሥራ ማሳደስ፣ ውልን የመፈጸም  እና ከሌሎች ከሱ ጋር በውል ተሳስረው ከሚገኙ ሰዎች የሚሰበሰቡ ገንዘቦች፣ የሚተላለፉ ሰነዶችን እንደየ ጉዳዮቹ  ባሕርይ እና ሁኔታ ሊፈጽማቸው ወይም ሊቀበላቸው  ባለመቻሉ  ተጠያቂነት የሚዳርግ ወይም  ሊያገኝ የሚገባውን  መብት ወይም ጥቅም  የሚያጣ በመሆኑ ሥራውን ለሚያከናውንለት አቶ ከ የውክልና ሥልጣን በመስጠት ከሄደበት ሀገር እስኪመለስ ሥራውን እንዲያከናውንለት ለማድረግ ይችላል፡፡

በዚህ ረገድ  የመኪና ባለቤት ለአሽከርካሪው  መኪናውን  በማሽከርከር ከሰጠው የትራንስፖርት  አገልግሎት  የሚገኘውን  ገንዘቦ እንዲያስረክበው በማድረግ  ወይም ቤቱ ወይም መኪናው ወይም ማንኛውም የሚነቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረትን በተመለከተ ግዢ ወይም ሽያጭ እንዲፈጸምለት  የሚፈልግ ገዢ ወይም ሻጭ፣ የሚከራይ ህንጻው ለሦስተኛ ወገን በኪራይ እነዲተላለፍለት  የሚፈልግ የህንጻ ባለቤት፣ ተቀጣሪው ሙሉ የማስተዳደር ሥራ  እነዲሠራለት የሚፈልግ ነጋዴ ከተወካ ይ ጋር በውል ወይም ከሕግ በሚመነጭ  አግባብ በሚፈጥሩት  ግንኙነት በሌሉበት ሊሠራላቸው ይችላል፡፡

የእንደራሴነት ሕግ አስፈላጊነት

ውክልና በሁለት ስዎች መካከል  የሚፈጠር ግንኙነት ሲሆን ተዋዋዮች በሚገቡት ውል ወይም ከሕግ በሚመነጭ  ሥልጣን ሊመሠረት እንደሚችል  ሕጉ ይደነግጋል፡፡  በመሆኑም  ተዋዋዮች ወይም በሕግ በመነጨው  የውክልና ግንኙነት ወስጥ የገቡት  ሰዎች በግንኙነት ውስጥ የጥቅም ግጭት (conflict of interest)እንዳይፈጠር  ተወካይ ለወካዩ  የሚያከናውነውን  ተግባር በምን መልኩ መፈጸም  እንዳለበት፣ የሚኖርበት ግዴታ፣ በግንኙነት ውስጥ  የሚጠበቁለት መብቶች፣ ተወካይ ወካይን ወክሎ በሚገባው ግዴታ  በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው ጉዳተ የወካዩ የተጠያቂነት ድንበር እና ሀላፊ የሚሆንበት ሁኔታ፣ ግንኙነቱ በተናጠልም ሆነ በጋራ ቀሪ ሊሆን  እና በሕግ ፊት ዋጋ  ስለሚያጣበት ሁኔታ ገዢ የሆኑ ድንጋጌዎች እንዲኖሩ ማስቻል በዘፈቀደ ከሚደረጉ እና አነዱ የሌላውን ጥቅም የሚጎዳ  ድርጊቶችን  ከመፈጸም እነዲቆጠብ ለማድረግ  እና ጉዳት የደረሰበትም  ወገን ኪሳራን  ለመጠየቅ  እንዲችል መብት የሚሰጥ የሕግ ማዕቀፍ  አስፈላጊ በመሆኑ በፍትሐብሔር ሕጉ ከአንቀጽ 2179 ጀምሮ  ስለ እንደራሴነት  የተደነገጉት ድንጋጌዎች  የውክልና ግንኙነትን በሥርዓት ለመምራት የሚጫወቱት ሚና የማይተካ ነው፡፡ 

የውክልና ሥልጣን ምንጭ

የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2179 ‹የሌላ ሰው እንደራሴ በመሆን ሥራዎችን የመፈጸም ሥልጣን የሚገኘው ከሕግ ወይም ከውል ነው፡፡ በማለት ይደነግጋል፡፡

ከውል የመነጨ የውክልና ሥልጣን

የእንደራሴነት ግንኙነት ከሚመሠረትባቸው ምክንያቶች አንዱ ውል  ስለመሆኑ ከላይ ተመልክተናል፡፡ በመሆኑም  ወካይ ከሚወክለው  ሌላ ሰው ጋር በሚፈጥረው ስምምነት እሱን ወክሎ ከ ሦስተኛ ወገን ጋር ማንኛውንም  ዓይነት  ግዴታ እንዲገባ ሥልጣን ሊሰጠው ይችላል፡፡ ይህ ስምምነት ከወካዩ ውልን ማቅረብ (offer ) ጋር ብቻ ሳይሆን  ከእነደራሴው ውልን መቀበል(አcceptአnce )ጋር ተጣምሮ የሚታይ ጉዳይ ነው፡፡ ከዚህ ሀሳብ ጋር ተያይዞ መታወቅ ያለበት ጉዳይ የእንደራሴው ውልን መቀበል በግልጽ ወይም በዝምታ መሆኑን ነው፡፡ በተጨባጭ በሰነዶች ማረጋገጥ እና ምዝገባ ጽ/ቤት ግለሰቦች እንደራሴው በአካል ባልቀረበበት እና ፍቃዱን በግልጽ ባላሳወቀበት ሁኔታ ወካዩ የውክልና ሥልጣን ሊሰጥ ይችላል፡፡ ወካዩ ይህን እንደራሴው በሌለበት የሰጠውን ሥልጣን ተቀብሎ በውሉ ወይም በውክልና ጽሁፉ ላይ የተጠቀሰውን ሥራ ከሠራ ውሉን የተቀበለ ስለመሆኑ መረዳት እንችላለን፡፡ 

ሳልመንድ ውሎችን (contract);-are agreements creating and defining obligations between the parties. ወደ አማርኛ ሲመለስ ውል ማለት በተዋዋዮች መካከል ያለን ግዴታ የሚያቋቁም እና የሚገልጽ ስምምነት ነው ፡፡ በዚህ ስምምነት መሠረት የሚፈጠረው ግንኙነት በተዋዋዮቹ መካከል ሕግ ሆኖ የሚያገለግል ሲሆን ተዋዋዮች በገቡት ውል መሠረት የሚጠበቅባቸውን ግዴታ በአግባቡ እና በውላቸው መሠረት መፈጸም እና መገዛት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም የውል ስምምነት መርሁ ሰው በቃሉ ይታሠራል (pacta sunt servanda) የሚል በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ሷሚው ከእንደራሴው ጋር በሚገቡት ውል ማሰረት በሚገልጹት ግዴታዎቻቸው መሠረት መመራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተዋዋዮች  የውክልና ሥልጣንን ስለ መስጠትም ሆነ ስለ መቀበል በግልጽ ወይም በዝምታ ሊሰጡ ወይም ሊቀበሉ የሚችሉ ስለመሆኑ የፍትሐብሔር ሕጉ  አንቀጽ 2200 እና 2201 በግልጽ ይደነግጋል:: በመሆኑም እንደራሴው ከተሰጠው ግልጽ ሥልጣን በተጨማሪ ከወካዩ ጋር ባላቸው የሥራ ግንኙነት ወካዩ ሥልጣኑን የሰጠው መሆኑን ገልጾለት  ነገር ግን ተወካዩ ውሉን የተቀበለም ሆነ ያልተቀበለ መሆንን ወድያውኑ ሳይገልጽ ሥራውን ከጀመረ ውሉን በዝምታ የተቀበለ  ተደርጎ ይቆጠራል (the silence of the agent on offer is amounted to acceptance)፡፡

በግልጽ የሚደረጉ የውክልና ውል ግንኙነቶችንም ተዋዋይ ወገኖች በፈቀዱት መንገድ ማከናወን ይችላሉ፡፡ ውልን በልዩ አጻጻፍ እንዲከውኑ በመርህ ደረጃ አይገደዱም፡፡ ይሁንና ሕጉ ውሉ ልዩ የውል  አጻጻፍን ያዘዘ እንደሆነ ተዋዋዮቹ ውላቸውን በጽሁም የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ ሕጉ ባዘዘው መሠረት ካልተፈጸመ ውሉ በሕግ ፊት ዋጋ ያጣል እንዲሁም ውሉ በታዘዘው መሠረት እስኪዘጋጅ ድረስ ረቂቅ ሆኖ ይቆያል፡፡

በፍ/ህጋችን ተዋዋዮች የተለየ የውል አጻጻፍን እንዲከተሉ እና በልዩ መዝገብ እንዲመዘገቡ ግዴታ ያደረገባቸው ፡-

የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የተመለከቱ ውሎች

ከአስተዳደር መሥሪያ ቤቶች ጋር የሚደረጉ ውሎች

ለብዙ ዘመን የሚቆዩ ውሎች

የዋስትና እና የኢንሹራንስ ውሎች እና ሌሎች ሕጉ በልዩ ፎርም ወይም አጻጻፍ እንዲደረጉ ያዘዛቸው ውሎች ናቸው፡፡ ለምሳሌ በሥራ ምክንየት ሀገር ውስጥ የሌለው አቶ ሰ አዲስ አበባ ቦሌ ክ/ከ የሚገኝን አንድ ቪላ ቤት እነዲገዛለት ሌላውን ሰው መሾም ቢፈልግ የውክልና ውሉን በጽሑፍ ማድረግ አለበት፡፡ ምክንያቱም የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን በተመለከተ የሚደረጉ ውሎች በንግግር ሊደረጉ እንደማይችሉ ተደንግጓል፡፡

ከነዚ ከላይ በተጠቀሱት የውለታ ጉዳዮች ሳይወሰኑ ተዋዋዮች የትኛውንም ውል በጽሑፍ ማድረግ ቢፈልጉ የሚከለከሉበት የሕግ መሠረት የለም፡፡ ይህንን በተጨባጭ ለማየት የሚቸግር አይደለም፡፡ ማህበረሰቡ እራሱን ሌሎች በሚያጎለው እምነት ምክንያት ከሚፈጠሩበት ጥቅም ማጣቶች ለመጠበቅ ሲል የውል ጉዳዮችን ባለመናቅ በጽሑፍ እየደገፋቸው እናያለን፡፡

ውልን በጽሑፍ ማድረግ የህዝብን አና የመንግስትን ጥቅም ከማስጠበቅ፣ አይነስውራንንና መሀይማንን ከጉዳት ከመጠበቅ፣ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችንና የንግድ ማህበራትን በተመለከተ የህ/ሰቡን መብት ከጉዳት ለመጠበቅ ማለትም ንብረቱ ከዕዳ እና ከእገዳ የጸዳ እንዲሁም ከዚ ቀደም ለሌላ ሰው የተሸጠ መሆን አለመሆኑን ለመለየት እና የተሸጡ እቃዎችን ድጋሚ በመግዛት ለጉዳት የሚጋለጡ ሰዎችን ለመጠበቅ፣ በፍ/ቤት እምነት የሚጣልበት ማስረጃ ለማግኘት፣ በሰነዶች መጥፋት፣ መቃጠል፣ መለያየት ምክንያት ሰነዶችን መልሶ ለማግኘት የሚጫወተው ሚና እጅግ ጉልህ ነው፡፡ ከዚ ተቃራኒ በሆነ መንገድ በሚደረግ የቃል ውል ምክንያት በማስረጃ እጦት መብታቸውን ከሚተዉ ብሎም በክርክር ከሚረቱ ተዋዋዮች በተሻለ መልኩ ከጉዳት የመጠበቅ እድላቸው ሰፊ ነው፡፡

 

የውል አቋሞች

በፍትሐብሔር ህጋችን ላይ ከሚገኙ ልዩ የውል ግንኙነቶች አንዱ ውክልና ነው፡፡ በመሆኑም የውክልና ውል ውል  እንደመሆኑ መጠን ውሎች በሕግ ፊት የሚጸኑ ይሆኑ ዘንድ ስለ ውሎች በጠቅላላው ርዕስ ስር የተዘረዘሩትን አቋሞች አሟልቶ መገኘት አለበት፡፡ የነዚ አቋሞች ተሟልቶ ያለመገኘት ውልን ፈራሽ ያደርገዋል፡፡ እነኚ በሕግ ፊት የሚጸና ውል አቋሞች የመዋዋል ችሎታ፣ ፍቃድ፣ የቅጣት ውሳኔ ናቸው 

ሀ. የመዋዋል ችሎታ (capacity)

ሰዎች ንብረት ቢያፈሩም ወይም ከማህበራዊ ግንኙነቱ የሚፈልጉት መብት ወይም ጥቅም ቢኖርም ከሌላ ሰውጋር የውል ግዴታ ለመግባት የሚያበቃ ሕጋዊ  ችሎታ ከሌላቸው በራሳቸው ውል ሊገቡ አይችሉም፡፡   ሰዎች(የተፈጥሮ)ውልን የመዋዋል ወይም ማንኛውንም የማህበራዊ ኑሮን ተግባር ለመፈጸም የማይችሉ የሚሆኑባቸው ምክንያቶች ዕድሜ፣ የአእምሮ ሁኔታ ወይም ፍርድ ቅጣት ናቸው፡፡ በሕግ እድሜያቸው 18 እና ከዛ በላይ ከሆኑት በስተቀር እድሜው ውል ለመግባት ከደረሰም ሆነ ካልደረሰ ሰው ጋር በውል ግዴታ ለመግባት እንደማይችሉ ይደነግጋል፡፡ ይሁንና በእድሜው ከላይ ከተገለጸው በታች ሆኖ ውል የገባ እንደሆነ ውሉ ፈራሽ ይሆናል፡፡ በዐእምሯቸው ጤነኛ ያልሆኑ ሰዎችም የውክልና ውልን በራሳቸው መመስረት አይችሉም፡እነኚ በዐእምሯቸው እና በእድሜያቸው ምክኒያት ከማህበራዊ መብታቸው በቀጥታ መሳተፍ እንዳይችሉ የተከለከሉበት ዋነኛ ምክኒያት የነዚህኑ ሰዎች መብት እና ጥቅም ከጉዳት ለመጠበቅ በሚል ነው፡፡ ምክንያቱም እነኚ የማሕበረሰቡ ክፍሎች የሚበጃቸውን ለመወሰን  እና በግንኙንቱ ማግስት ምን ዓይነት ተጽዐኖ ሊደርስባቸው እንደሚችል አስቀድመው ለማሰብ እና ለመገመት የሚችሉ ባለመሆናቸው ነው፡፡ በፈጸሙት ወንጀል ምክንያት ቅጣት የተፈረደባቸው ሰዎችም ወይም ፍርድ ቤቶች ከማንኛውመ ማህበራዊ መብታቸው ያገዳቸው  ሰዎችም በተመሳሳይ የክልከላው አካል ናቸው፡፡

ለ. ውልን ፈቅዶ ስለመዋዋል (consent)

ወካይ ከእንደራሴው ጋር የሚያደርገው የውክልና ውል ስምምነት ሁለቱም ተዋዋዮች በውሉ ለመገዛት እና የሕግነት ሚዛን እንዲኖረው በሕግ ፊትም እንዲጸና ውሉን በሙሉ ፍቃዳቸው መመስረት አለባቸው፡፡ በተጓደለ የተዋዋዮች ፍቃድ የሚመሰረቱ ውሎች በሕግ ፊት ፈራሾች ናቸው፡የተዋዋዮች ፍቃድ ጎሏል የሚባለው ተዋዋዩ ውሉን የተቀበለው ከራሱ በሚመነጭ ስህተት፣ በሌላው ሰው በሚደርስበት መገደድ፣ በተንኮል ከሆነ ነው፡፡ ለምሳሌ አቶ ወ የቆዳ ውጤት ማምረቻ ድርጅቱን እንዲያስተዳድርለት እናደራሴው ለሆነው  አቶ ሸ የውክልና ሥልጣን የሰጠው በቢዝነስ ማኔጅመንት የመጀመሪያ ድግሪ እና በተመሳሳይ ሥራ መስክ የ10 ዐመት የሥራ ልምድ ያለው መሆኑን ስለ ገለጸለት ከሆነ እና ነገር ግን ውሉ ተመስርቶ ሥራው ከተጀመረ በኋላ ወካዩ ተወካዩ የሰጠው ማስረጃ  ትክክልኛ እንዳልሆነ ቢደርስበት እና ይህ መሆኑነ ቢያውቅ ኖሮ ውሉን የማይገባ የነበረ መሆኑን ያሰረዳ እንደሆነ ውሉ ፈራሽ ይሆናል፡፡ በኑሮው ሁኔታ ወይም በሀይል ተገድዶ  ውል የገባም ሰው በተመሳሳይ ሥልጣኑን  የመሻር መብት አለው፡፡ አንድ ሰው የውል ግዴታውን ለመፈረም ወይም ግዴታ ለመግባት የቻለው ውሉን እምቢ የሚል ከሆነ በራሱ፣ በቤተሰቡ፣ በሚስቱ ወይም በንብረቱ ላይ ጉዳት የሚደርስበት መሆኑ ተነግሮት በዚሁ ዛቻ ምክንያትም ፍርሃት አድሮበት ከሆነ ነው፡፡ ሆኖም መገደዱ አስገዳጅ ከሆነው ሰው እድሜ እና አጠቃላይ ሁኔታ አንጻር የሚመዘን መሆን አለበት፡፡

ሐ. የውለታው ጉዳይ

ወካይ ለወኪሉ የሚሰጠው የውክልና ሥልጣን የሚቻሉ እና ሕጋዊ የሆኑ ሥራዎችን ብቻ እንዲያከናውንለት መሆን አለበት፡፡ በሥራዎቹ ባሕርይ በሰው ልጅ ሊከናወኑ በፍጹም የማይቻሉ እንዲሁም በወንጀል፣ በፍትሐብሔር ወይም በሌላ በየትኛው ሕግ ክልከላ የተደረገባቸው አድራጎቶችን እንዲከናውንለት በሚል በሰጠው ውክልና የተመሰረተው ውል በሕግ ፊት  የሚጸና አይሆንም፡፡ ለምሳሌ አቶ ቀ የግብርና ባለሙያ ለሆነው አቶ ከ ማርስ ከተባለ ፕላኔት ግራናይት የተባለማዕድን እንዲያመጣለት ወይም ይህንኑ ሰው በኬንያ ድንበር በኩል የኮኬይን ምርት እንዲስገባለት ቢሾመው ሁለቱም ውሎች ፈራሽ ናቸው፡፡ ምክንያቱም መመጀመርያው ምሳሌ ኢትዮጵያ መንኮራኩሮችን ወደ ጠፈር ከሚልኩ የበለጸጉ ሀገራት ተርታ ሳትሰለፍ እና አንድ ተራ የግብርና ባለሙያ ወደ ሌላ ፕላኔት ለመጓዝ የማይችል በሆነበት ሁኔታ ይህንኑ ተግባር እንዲፈጽምለት ሊሾመው አይችልም፡፡  በሌላም በኩል በኢፌዲሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 525 ስር የናርኮቲክ፣ የሳይኮትሮፒክ መድሀኒቶችን ወይም የተከለከሉ እጾችን ወደ ሀገር ማስገባት፣ ለሽያጭ ማቅረብ፣ በግሉ ወይም ሌላው እንዲጠቀምበት በማሰብ ይዞ መገኘት በወንጀል የሚያስቀጣ ድርጊት በመሆኑ  የውል ጉዳይ ሊሆን አይችልም፡፡ እንደራሴውም ሥራውን የሠራሁት ለወካዩ ስል በመሆኑ ልጠየቅ አይገባም በሚል ሊከራከር አይችልም፡፡

የውክልና ሥልጣን

ሀ. በግልጽ የሚሰጥ የውክልና ሥልጣን (actual authority)

ይህ ሥልጣን ወካዩ እንደራሴው በሱ ቦታ ሆኖ እንዲሠራለት የሚፈልገውን ጉዳይ በመለየት እና በግልጽ በማሳወቅ የውክልና ሥልጣን ሰጥቶት ከዚሁ ሥልጣን ጣራ ሳይልፍ  በግልጽ የተለዩ ሥራዎችን የሚሠራበት ማለት ነው፡፡ በዚህ መሠረት እንደራሴው ወካዩ ከሰጠው ሥልጣን ወጥቶ ሊሠራ የማይችል በመሆኑ ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ በመውጣት ከሦስተኛ ወገን ጋር ለሚገባው የውል ግዴታ ወካዩ ተጠያቂ ወይም ሀላፊ ሊሆን አይችልም፡፡ ይሁንና ይህንን ተግባሩን ያወቀው ወካይ ሥራው የተሠራው ከሰጠውት ሥልጣን ውጪ  በመውጣት በመሆኑ ልጠየቅ አይገባም ከማለት ይልቅ ሥራውን ያጸደቀለት እንደሆነ ወካዩ ሀላፊ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ በጠቅላላ ውክልና ውል በፈጠሩት ግንኙነት መሠረት የሆቴል ሥራውን እንዲያስተዳድርለት ሌላውን ወክሎ የሚያሠራው ወካይ በግልጽ ሳይፈቅድ ያገለገሉ ወይም ያረጁ የእንጨት ሥራ ውጤቶችን ለሌላ ሰው ቢሸጥ ወካዩ በዚህ ውል ሊገደድ አይችልም፡፡ ምክንያቱም ለእንደራሴው የሰጠው ሥልጣን የማስተዳደር ሥራ እንዲሠራለት በመሆኑ እና አገልግሎት የሰጡም ሆነ አዳዲስ መገልገያ ቋሚ ዕቃዎችን የመሸጥ ተግባር የአስተዳደር ሥራ ባሕርይ ወይም አካል ባለመሆኑ ነው፡፡ የአስተዳደር ሥራዎች ምን ምን ተግባራትን እንደሚያካትቱ ጠቅላላ የውክልና ሥልጣን በሚል ርዕስ ስር የምንመለከተው ይሆናል፡፡ ይሁንና ገንዘቡን ተቀብሎ ዕቃዎቹም ለገዢው ካስረከበ ገዢው ሽያጩን በተመለከተ ለሚያነሳው ሕጋዊ ጥያቄ ወኪሉ መልስ ይሰጣል፡፡

በተመሳሳይ ከባድ የጭነት መኪናውን እያሽከረከረ ከሚሰጠው የዕቃ ማጓጓዝ አገልግሎት የሚገኘውን ገንዘብ ሰብስቦ እነዲያስረክበው ሹፌሩን ወክሎት ይህንኑ የተሰጠውን ሥራ ብቻ መሥራት ሲገባው ለመኪናው የሚጠቅም ነው በማለት 10(አስር) የመኪና ጎማዎችን መኪናውን አስይዞ ገነዘብ ተበድሮ ቢገዛ ወካዩ(የመኪናው ባለቤት)ድርጊቱን የራሱ ካላደረገለት በስተቀር ከሥልጣኑ ወጥቶ ለሠራው ሥራ በግሉ ሀላፊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ባለው የውክልና ሥልጣን መሠረት መኪናውን በመንገድ ላይ ሲያሽከረክር በሌላ ሰው አካል ወይም ንብረት ላይ ጉዳትን አድርሶ ከሆነ ወካዩም ሐላፊ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ሥራው የተሠራው ለወካዩ ሲባል በመሆኑ እና ከውል ውጪ በሚመነጭ ሀላፊነት  ወካዩም ተጠያቂ ከመሆን ስለማይድን ነው፡፡ ነገር ግን ታስቦም ሆነ በቸልተኛነት የሚፈጸሙ በአካል ላይ ጉዳት ማደረስ ወንጀል የሚያስቀጣ በመሆኑ ተወካይ መኪናውን ለሌላ ሰው ስል የማሽከረክር በመሆኑ ልጠየቅ አይገባም ሊል አይችልም፡፡

ጠቅላላ እና ልዩ ውክልና

ሀ. ጠቅላላ ውክልና

በኢትዮጵያ የእንደራሴነት ሕግ ወካይ ከተወካይ ጋር በውል ከሚመሰርተው የውክልና ግንኙነት ጋር ተያይዞ የሰጠው ሥልጣን የአስተዳደር ሥራዎችን ብቻ እንዲፈጽምለት ከሆነ ሥልጣኑ ጠቅላላ የውክልና ሥልጣን በመባል ይታወቃል፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉም በጠቅላላ አነጋገር የተደረገ ውክልና ለተወካዩ የአስተዳደርን ሥራ እንዲፈጽም ከሚያደርገው በቀር ሌላ ሥልጣን አይሰጠውም ሲል በአንቀጽ 2203 ስር ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ተወካይ (እንደፈራሴው) ከተሰጠው ጠቅላላ ሥልጣን ወጥቶ ሌሎች ተግባራትን ማከናወን አይፈቀድለትም፡፡ እንደራሴው ከዚህ ሥልጣን ወጥቷል ወይም አልወጣም ለማለት የአስተዳደር ሥራ በስሩ ምን ምን ተግባራትን የሚያቅፍ እንደሆነ መረዳት ተገቢ እና መሰረታዊ ነው፡፡ በዚህ ከላይ በተጠቀሰው ሕግ አንቀጽ 2204(1) እና (2) ስር የአስተዳደር ሥራዎችን ዝርዝር እንደሚከተለው አስፍሯል፡-

የወካዩን ሀብት የማስቀመጥ እና የመጠበቅ

ከ3 ዐመት ለማያልፍ ዘመን የማከራየት

በብድር የተሰጠውን ሀብት የመሰብሰብ

ከሀብቱ የሚመጣውን ገቢ ተቀብሎ የማስቀጥ እና ለተከፈሉ እዳዎች ደረሰኝ የመስጠት ሥራዎች

ሰብሎችን፣ ለሽያጭ የተመደቡ ዕቃዎችን ወይም ይበላሻሉ ተብለው የሚገመቱ ነገሮችን የመሸጥ ሥራዎች ናቸው፡

በተጨማሪም በንግድ ሕጉ አንቀጽ 35(1) “ከሦስተኛ ወገኖች ጋራ በሚያገናኙት ጉዳዮች ሁሉ ሥልጣን ያለው ሥራ አስኪያጅ ከነጋዴው ሥራ ጋር ነክነት ያላቸውን ማናቸውንም ግዴታዎች ለመፈጸም እና የሚተላለፉ የንግድ ሰነዶችን ጭምር ለመፈረም ሙሉ ሥልጣን እንዳለው ሆኖ  ይቆጠራል” በሚል ተደንግጎ እናገኘዋለን፡፡ ተላላፊ ሰነዶች ከምንላቸው አንዱ ቼክ ነው፡፡ ከላይ የዘረዘርናቸውን ተግባራት በተለይም ከመሸጥ እና ከመግዛት ጋር በተገናኘ ክፍያው የሚፈጸመው በሚወጣ ቼክ ከሆነ ይህንኑ ሰነድ እንደራሴው ስለ ወካዩ ሆኖ ሊቀበል ወይም ሊያወጣ ይችላል፡፡ ከነዚ ከላይ ከጠቀስናቸው ሥራዎች ውጪ የሆኑ ተግባራትን ተወካይ ይፈጽም ዘንድ ወካይ ከሆነው ሰው ልዩ የውክልና ሥልጣንን ማግኘት ይኖርበታል ፡፡ ይህንን ሥልጣን ሳያገኝ እንደራሴው ልዩ የውክልና ሥልጣን የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ሥራ ሰርቶ ከሆነ በዚሁ የእንደራሴው ተግባር ምክንያት በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ወካዩ ሊጠየቅ አይችልም፡፡

ለ. ልዩ ውክልና

የዚህ የውክልና ሥልጣን ወሰን በአብዛኛው ለአጭር እና ነጠላ ለሆኑ ጉዳዮች የሚሰጥ ነው፡፡ እንደራሴው የወካዩን ንብረት ወይም ሥራ የሚያስተዳድር ከሆነ በተሰጠው ጠቅላላ ሥልጣን  ሳይገደብ እንዲሁም ቀድሞ ምንም የሥራ ግንኙነት ከወካይ ጋር ያልነበረው ሌላ ሰው አንድን ሥራ እንዲሠራ በወካዩ ሊሾም ይችላል፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2205(2)ልዩ የውክልና ሥልጣን ካልተሰጠ በስተቀር እንደራሴው ስለ ወካዩ ሲል የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ ወይም አስይዞ መበደር፣ ካፒታሎችን በአንድ ማህበር ዘንድ ማስገባት፣ የለውጥ ግዴታን ውል መፈረም፣ መታረቅ፣ ለመታረቅ ውል መግባት፣ ስጦታ ማድረግ የማይችል ስለመሆኑ በግልጽ ይደነግጋል፡፡ የዚህ የውክልና ሥልጣን በሕግ መታቀፍ አስፈላጊነት የወካዩን ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር ወካዩ በማያሻማ መልኩ ንብረቱን መሸጥ ወይም መግዛቱን  እንደፈቀደ ባልተረጋገጠበት ሁኔታ በጠቅላላ  ውክልና የወካዩን ሥራ የሚያስተዳድረው ሰው አልያ ሥልጣኑ ያልተፈቀደለት  ሌላ ማንኛውም ሰው የወካዩ የሆነውን ሥራ በተመለከተ በሚያከናውኑት ተግባር ወይም በሚገቡት ውል በሌላ ሰው ላይ ጉዳት  ቢያደርሱ ጉዳት የደረሰበት አካል ከወካዩ  ኪሳራ ሊጠይቅ የማይችሉ በማድረግ የሚጫወተው ሚና ጉልህ ነው፡፡ አዎት ሀይለዝጊ እና አዲሱ ዳምጤ ‘’Ethiopiአn lአw of agency’’ በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የመማሪያ ጽሑፍ ’it requires a special authorization for an agent to mortgage a real state (immovable ). Because mortgege may ultimatliy results in desposition of the propertiy.’ ሲሉ የልዩ ውክልናን አስፈላጊነት ያሰምሩበታል፡፡ ማንኛውም ሰው ከፍቃዱ ውጪ ንብረቱን ማጣት አይገባውም፡፡ ለምሳሌ የመኖሪያ ቤቱን ወይም መኪናውን ለባንክ አስይዞ ብር የተበደረ ሰው እዳውን ከፍሎ ካልጨረሰ እና የመክፈያ ጊዜ ገደቡ ካለፈ ባንኩ በመያዣነት የያዘውን ንብረት በሀራጅ ሽጦ ገንዘቡን የማስመለስ ሕጋዊ መብት አለው፡፡ በመሆኑም ተበዳሪው ንብረቱን የሚያጣ ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህንን ዓይነቱን የንብረት ባለቤትነት ማጣት ወኪሉ በሆነው ሰው ሥራ ሲደርስበት እና ውክልናው ወካዩ የሠራውን ሥራ እንዲሠራ የማይፈቅድ ሲሆን ንብረቱን ልያጣ እንደሚችል ቢያውቅም ግዴታውን እንዲገባለት ፈቅዶለት ወይም ሥልጣን ሰጥቶት ካልሆነ በቀር ተወካዩ በራሱ ፍቃድ ለሠራው ሥራ ንብረቱን የሚያጣበት ሕጋዊም ሆነ ሞራላዊ ምክንያት አይኖርም፡፡ ከላይ ባየነው ምሳሌ ወካዩ እንደራሴው ቤቱን አስይዞ ብር እነዲበደርለት ሥልጣን ሰጥቶት ከሆነ እና እንደራሴው ብሩን ተበድሮ መክፈል ባይቻል ባለ ገንዘቡ ክፍያውን በተመለከተ የሚጠይቀው ሸዋሚውን ነው፡፡ ምከንያቱም ተወካዩ ውሉን ይፈርም እንጂ ተጠቃሚው ወካዩ ነውና፡፡ ውሉም በወካዩ እና በሦስተኛ ወገን መካከል እነደተደረገ የሚቆጠር ይሆናል፡፡ 

ለ.መሰል የውክልና ሥልጣን (apparent authority)

ማንኛውም እንደራሴ በግልጽም ሆነ በዝምታ ከተሰጠው የውክልና ሥልጣን ውጪ ወጥቶ የሠራ እንደሆነ ሊከተሉ የሚችሉ ውጤቶችን ከላይ ባሉት ማብራሪያዎች ተመልክተናል፡፡ ይሁንና እንደራሴው ባደረበት ቅን የሆነ ልቦና ወይም መሳሳት ከተሰጠው ሥልጣን ውጪ ወጥቶ ሥራዎችን ሊሠራ ይችላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እንደራሴው ለሦስተኛ ወገኖች ሷሚውን ወክሎ መሥራት ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ በመግለጹ እና እነሱም ግለሰቡ ይኀው ሥልጣን ያለው ስለመሆኑ ግምት ወስደው ከዚሁ ሰው ጋር ግዴታ የገቡ እንደሆነ እንደራሴው መሰል የውክልና ሥልጣን እንዳለው ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ ይሁንና ሦስተኛው ወገን ከእንደራሴው ጋር የገባሁት ውል ወካዩን ሊያስገድድ ይገባል በሚል መብቱን ለመጠየቅ የሚችለው ይህንኑ የእንደራሴውን ተግባር ሊያጸድቅለት ሲችል ነው፡፡

በአብዛኛው የዚህ ዓይነቱ ግንኙነት የሚፈጠረው እንደራሴው ከወካዩ ጋር ቀድሞ ባለው ግንኙነት ወይም ከራሱ ከሷሚው አንደበት ከሚወጣ ንግግርም ነው፡፡ ለምሳሌ ሥራን በማስተዳደር የውክልና ሥልጣኑን እየተወጣ ያለው ሰው የሷሚውን የሚንቀሳቀሱም ሆነ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን የመሸጥ ሥልጣን ሳይኖረው ነገር ግን የሥራው ባለቤት ገዢ ለሆነው ሰው የመኪናውን ሽያጭ በተመለከተ እንደራሴውን እንዲያናግር እና ከተስማሙ ሽያጭ እንዲፈጽለት ቢነግረው እና ገዢም ከእንደራሴው ጋር ውል ቢገባ እንደራሴው መኪናውን ለሦስተኛ ወገን የሸጠበት ሥልጣን መሰል የውክልና ሥልጣን (apparent authority) የሚባል ነው፡፡

ከላይ በምሳሌነት ካነሳነው በተለየ መልኩ በሚወሰድ ግምት እንደራሴው ስለ ወካዩ ግዴታ በመግባት ለሠራው ሥራ ሷሚው ካላጸደቀ በቀር ውሉ ፈራሽ ይሆናል፡፡ ሦስተኛ ወገንም ከውሉ ጋር በተገናኘ ለሚያነሳቸው ጥያቄዎች እንደራሴው በግሉ የሚጠየቅ ይሆናል፡፡ ይሁንና ያጸደቀው ከሆነ ውሉ እንደራሴው በተሰጠው ሥልጣን መሠረት የሠራው ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ በዚህ ምክንያትም ሷሚው ስለ እንደራሴው ሥራ ሀላፊ ይሆናል፡፡

በሌላ በኩል ወካዩ እንደራሴው ከሥልጣኑ ወጥቶ ለሠራው ሥራ የማያጸድቅ ከሆነ እና ነገር ግን ሥራው የተሠራው ሙሉ በሆነ ቅን ልቦና ከሆነ ውሉ ፈራሽ በመሆኑ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚደርስ ኪሳራ እንደራሴው ሳይሆን ሽዋሚው ኪሳራ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል፡፡ የማጽደቅን ጽንሰ ሀሳብ በቀጣዩ ርዕስ ስር እንመለከተዋለን፡፡     

ሐ. ማጽደቅ (ratification)

እንደራሴው ከተሰጠው የውክልን ሥልጣን ውጪ በመውጣት የሠራው ሥራ የወካዩን መብት ወይም ጥቅም ለማስጠበቅ ወይም ትርፋማ ያደርገዋል ብሎ በማሰብ ቅን በሆነ ልቦና የፈጸመው እንደሆነ   እንዲሁም ከሥራው አጠቃላይ ባሕርይ አንጻር የተቀበለው ሥልጣን በበለጠ መስፋት ወይም ቀድሞውኑ ሥልጣኑ ሲሰጠው ግዴታውን በሚገባ ይወጣ ዘንድ ሥልጣኑ ሳይኖረው የሠራው ሥራም ሊካተት እና በሥልጣኑ ስር ሊወድቅ የሚገባ የነበረ መሆኑ የህሊና ግምት ሊወሰድበት የሚችል ከሆነ ወካዩ ዕንደራሴው ከሥልጣኑ ወጥቶ የሠራውን ሥራ ያጸድቅለታል፡፡ ማጽደቅ ማለት አንድን ቀድሞ የተሠራን ሥራ፣ የተጻፈን ጽሑፍ፣ የረቀቀን ሕግ ወይም ዕቅድ እና ሪፖርትን ገምግሞ እውቅና መስጠት ማለት ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ትኩረት በሆነው ጉዳይም ወካዩ ከሥልጣን ውጪ ለተሠራው ሥራ እውቅና መስጠት እና ግንኙነቱ የሚፈጥረውን  ውጤት የሚቀበለው እና የሚገዛበት መሆኑን  በማያሻማ ሁኔታ ከገለጸ አጽድቋል ለማለት እንችላለን፡፡ በሀገረ አሜሪካ ስለ ማጽደቅ የተሰጠው ትርጉም ‘ratifiction is the affirmance by a person of a prior act which didn’t bind him but which was done or professedly done on his account where by the act, as to some or all persons,is given effect as if originally authorized by him’

ወደ አማርኛ ስንተረጉመው ማጽደቅ ማለት አንድ ሰው በራሱ ስም የተደረጉ ወይም ሊደረጉ ቃል የተገቡ ነገር ግን ይህን ሰው ሊያሰገድዱ የማይችሉ የነበሩ ድርጊቶች በዚህ ሰው ተቀባይነት ካገኙ በኋላ ድርጊቶች ከስረ መሰረታቸው በዚሁ ሰው እንደተደረጉ የቆጠራሉ የሚል ትርጉም ይሰጣል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ ሊታወቅ የሚገባው ነገር የወካይን ማጽደቅ ተከትሎ የሚከተለውን ውጤት ነው፡፡  ከላይ በቀረበው ጽሑፍ እንደሚያመለክተው ወካይ ተወካዩ ለሚሠራው ማንኛውም ሥራ ሊጠየቅ የሚችለው በስልጠን ውስጥ የተከለለን ሥራ በተመለከተ ነው፡፡ ይህ መርህ ነው፡፡ ነገር ግን ወካዩ ማጽደቅ ካደረገ በተወካዩ እና ሦስተኛ ወገን መካከል የተደረገው የውል ስምምነት በወካይ እና ሦስተኛ ወገን መካከል እንደተደረገ ይቆጠራል፡፡ ውሉን በተመለከተ እንደራሴው የገባቸው ግዴታዎች በሙሉ የወካዩ ይሆናል፡፡ 

በሌላ በኩል እንደራሴው ወካዩ የሰጠውን ሥልጣን እንዲያሰፋለት ወካዩን የመጠየቅ ምቹ ሁኔታ ውስጥ እያለ በቸልተኛነት ሳይጠይቅ ሥልጣኑ ሳይሰፋለት በራሱ ፍቃድ ማንኛውንም ሥራ ከሠራ ወይም ግዴታ ከገባ ወይም በዚሁ አግባብ ሥራውን አከናውኖ ለወካዩ ሳያሳውቀው የቀረ እንደሆነ ወካዩ ውሉን እንዲያጸድቅለት የመጠየቅ መብት የሌለው መሆኑን የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2207(3) ይደነግጋል፡፡    

ከሕግ የመነጨ እንደራሴነት

ሌላኛው የውክልና ሥልጣን  ምንጭ ሕግ ነው፡፡ በሕግ በግልጽ በተደነገገ አግባብ የንብረት ወይም የአንድ ሥራ ባለቤት ንበረቱንም ሆነ ሥራውን በተመለከተ ሌላው ሰው እንዲያከናውንለት ምንም ዓይነት የውክልና ሥልጣን ሳይሰጠው ወይም ሕግ በውል ግዴታ ሳይገቡ አንዱ የሌላውን ሥራ ለዚሁ ሰው ጥቅም ሲል ሊፈጽም ይችላል፡፡ ይህ ሥልጣን በሁኔታ ወይም በዳኞች ውሳኔ ሊፈጠር የሚችል ስለመሆኑ በፍትሐብሔር ሕጉ በምዕራፍ 4 እና 5 ላይ ከሰፈሩት ድንጋጌዎች መገንዘብ እንችላለን፡፡

ሥራው የሚሠራለት ሰው ሥራውን በራሱ ለመሥራትም ሆነ ሌላው ሰው ሥራውን እንዲሠራለት ለመሾም በማያስችለው ሁኔታ ውስጥ ሲገኝ ዳኞች ሌላውን ሰው ሥራውን ስለ ንብረቱ ባለቤት ሆኖ እንዲያከናውን ሥልጣን ሊሰጥ ይችላል፡፡ በዚህ ሁኔታ በዳኞች የሚወከለው ጠባቂ ባለአደራ (curአtor) የሚያከናውናቸው ተግባራት አስቸኳይ እና ጊዜ የማይሰጡ ጉዳዮችን ብቻ መሆን እንዳለበት ሕጉ ይደነግጋለል፡፡ ምክንያቱም ጠባቂ ባለአደራው የሚሾመው ሥራው የሚሠራለትን ሰው ጥቅም ከማስጠበቅ አንጻር በመሆኑ ወካዩ ላይ ሊደርስ የሚችለውን ጉዳት ለማስወገድ ነው፡፡

በዳኞች ውሳኔ አማካኝነት ተሹሞ የሌላውን ሥራ የሚሠራው ሰው ከሥራው ባለቤት ጋር ስለሚኖረው ግንኙነት የሚመራው ከውል ከመነጨው የውክልና ግንኙነት ጋር በተመሳሳይ ነው፡፡

በሌላ በኩል በዳኞች ከሚሾሙ ባላደራ ጠባቂ እንደራሴዎች በተጨማሪ ሰዎች በሚኖራቸው ቀረቤታ፣ የዝምድና ቁርኝት፣ ያልተገመተ ክስተት ምክንያት ያለንብረቱ ወይም ሥራው ባለቤት ፍቃድ በባለቤቱ ቦታ ሆነው ሥራ ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ እነኝህም ሰዎች በዳኞ እችንደተሾሙት ሁሉ ሥራው ከሚሠራለት ሰው ዘንድ ፍቃድ ያላገኙ ናቸው፡፡ በዚህ መልክ ወደ ግንኙነቱ የገቡ ሰዎች የሥራው ባለቤትን ጥቅም የማስጠበቅ ሀላፊነት ያለባቸው ሲሆን ሥራቸውን ቅን በሆነ ልቦና የመምራት እና ስለ ሰሩት ሥራም ለወካዩ ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ባልታወቀ ምክንያት ከቀዬው ርቆ የነበረው አቶ መ ማሳ ላይ የተዘራው እና ለአጨዳ የደረሰው ሰብል ድንገት በተነሳ መነሻው ያልታወቀ እሳት እየተቃጠለ በስፍራው የደረሰው የ አቶ መ ጎረቤት አቶ ሠ በስፍራው ደርሰው ከአቶ ሸ ዛፍ ላይ ቅጠል በመቀንጠስ እሳቱ የጎላ ጉዳት ሳያስከትል አጥፍቶታል፡፡  በዚ ተግባሩ ከማሳው ባለቤት ጋር በሁኔታ የውክልና ግንኙነት የመሰረተ ተደርጎ ይቆጠራል፡፡ በመሆኑም በዛፉ ላይ ጉዳት የደረሰበት አቶ ሸ በንብረቴ ላይ ለደረሰብኝ ጉዳት ኪሳራ ሊከፈለኝ ይገባል በሚል ለሚያቀርበው ጥያቄ መልስ ሊሰት የሚገባው ንብረቱ ከውድመት የተጠበቀለት ከአቶ መ ነው፡፡ ለዚህ ደሞ ምክንያቱ አቶ ሠ እሳቱን ለማጥፋት የሌላውን ዛፍ ሊቆርጥ የቻለው የማሳውን ባለቤት ንብረት ከጥፋት ለመጠበቅ ለሌው ሰው ሲል በሠራው ሥራ ምክንያት ያደረሰው ጉዳት በመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም የማሳው ባለቤት ግለሰቡ እሳቱን እነዲያጠፋልኝ አልሾምኩትም እና ልጠየቅ አይገባም ሲል ሊከራከር አይችልም፡፡

በሌላ በኩል እናት እና አባት ለሚወልዷቸው ልጆች ወይም በተዋረድ ስለ አሳዳሪና ሞግዚትነት በፍትሐብሔር ሕጉ በተቀመጠው አግባብ በቤተ ዘመድ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ሞግዚት ሆነው የሚሾሙ ሰዎች ለአካለመጠን ላልደረሰው ልጅ ዕንደራሴዎች ናቸው፡፡ በመሆኑም የህጻኑን ጥቅም የማስጠበቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ ይህ መብት የልጁን (ለአካለ መጠን ያልደረሰው) የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን እስከመሸጥ ሊደርስ የሚችል መብት የሚሰጥ በመሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ የተገባ ነው የሚሆነው (ሞግዚቶቹ ከእናት እና አባት ውጪ ከሆኑ ይህን ሽያጭ በተመለከተ የቤተ ዘመድ ጉባኤው መፍቀድ አለበት)፡፡ የዚህን የእንደራሴነት ግንኙነት ከላይ ከተጠቀሱት የውክልና ስልጣኖች ጋር የሚያመሳስለው ሥራው የሚሠራለት ሰው ያልወከላቸው እና ስልጣናቸውን ያገኙት ከሕጉ መሆኑ ነው፡፡ 

ግዴታዎች

እንደራሴው ስለ ወካዩ ያሉበት ግዴታዎች

ቅን ልቦና (good fአith)፡-ተወካዩ ከወካዩ ባገኘው የውክልና ሥልጣን የሚያከናውነውን ተግባር ጥብቅ በሆነ ቅን ልቦና መፈጸም ይገባዋል፡፡ የራሱን ጥቅም ከማስቀደም ይልቅ  ወካዩን ከሚጎዱ አድራጎቶች በመቆጠብ መታመንን እና ቅንነትን መሠረት በሚያደርግ የአሠራር ሁኔታ መመራት አለበት፡፡ ቅንነት የሚመነጨው ሰዎች በሚያከናውኗቸው ተግባራት ስለ ሌሎች ጥቅም ሲሉ በምክንያታዊ አስተሳሰብ ሊመዘን ወይም ለመረዳት በማይቸግር ሁኔታ ከልብ ከመነጨ መታመን እና ደግ ደጉን በማሰብ ግለሰቡን የሚጠቅም ውጤት የሚያስከትል መልካም ሥራ እየሰሩ አድርገው ከማሰብ ነው፡፡ በመሆኑም የማይገባ ጥቅምን ለራስ ወይም ለሌላ ሰው ለማስማግኘት ወይም በሌላው ሰው ጥቅም ላይ ጉዳትን ለማድረስ በማሰብ ሥራው ግለሰቡን እነደማይጠቅም እያወቁ ሥራዎችን የሚያከናውኑ ከሆነ ከግን ልቦና ጽንሰ ሀሳብ የተቃረነ ይሆናል፡፡ በቅንነት መጓደል ምክንያት በወካዩ ላይ ለሚያደርሱት ጉዳትም ሀላፊ ይሆናሉ፡፡ በተጨማሪም የሰሩት ሥራ ከተሰጣቸው ሥልጣን ውጪ ከሆነ ወካዩን ሥራውን እንዲያጸድቅላቸው የመጠየቅ መብትንም የሚያጡ ይሆናል፡፡

የሥራ ተግባሩን ሲፈጽም ወካዩን በሚጠቅም መንገድ ብቻ መሆን ያለበት ስለመሆኑ፡፡ ወካዩ እስካልፈቀደለትም ድረስ በሥራው አጋጣሚ እጁ ከሚገባው ገንዘብ ላይ ጥቅም መውሰድ የለበትም፡፡ ግንኙነታቸው የተመሰረተው በክፍያም ሆነ ያለ ክፍያ (grአtuitously) ሥራው የሚሠራው ስለ ወካዩ በመሆኑ ክፍያን ወይም መጠቀምን በተመለከተ ከወካዩ ዘንድ ግልጽ ፍቃድ ማግኘት ወሳኝ ጉዳይ ነው፡፡  ሕጉ ይህን ካለ ዘንድ እንደራሴው የለ ሷሚው ፍቃድ ከሥራው ገቢ ወይም በማንኛውም ከሥራው ጋር በሚገናኝ ሁኔታ እጁ ከገባው ሀብት ውስጥ ጥቅም ከወሰደ የመክፈል(የመመለስ) ግዴታ አለበት፡፡

ምንም እንኳን ግዴታ ካደረጋቸው ጉዳዮች ተርታ ባይመደቡም በጠቅላላ ስለ እንደራሴነት ከተደነገጉት ድንጋጌዎች አንዱ የጥቅም ግጭት ነው፡፡ እንደራሴው ሥራውን የሚሠራው ለወካዩ ጥቅም ሲል በመሆኑ እራሱን ለማበልጸግ በማሰብ የሚያከናውናቸው ተግባራት በሕግ አይደገፉም፡፡ ይልቁንም ወካዩ በሁለት አመት ውስጥ ይፍረስልኝ ሲል ካመለከተ እንደራሴው በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሆኖ የገባቸው ግዴታዎች ሊቀሩ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ ወካይን ወክሎ ከሚስቱ ወይም ከልጁ ጋር የሚገባቸው ግዴታዎች የጥቅም ግጭትን ከሚፈጥሩ ምሳሌዎች አንዱ ነው፡፡ ምክንቱም ሚሰቱ ወይም ልጁ የሚያገኙት ጥቅም በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሱም ጥቅም ሊሆኑ የሚችሉ ስለመሆናቸው የሚገመት ጉዳይ በመሆኑ ነው፡፡ በተመሳሳይ ከእራሱ ጋር የሚገባቸው ግዴታዎች በወካዩ ዝም እስካልተባሉ ድረስ ፈራሾች ናቸው፡፡ ዕቃዎችን ለእራስ መሸጥ ማከራየት ወይም ከራስ መግዛት ወይም መከራየት የዚሁ ተግባር ምሳሌ ነው፡፡ እንደራሴው የውክልና ሥልጣኑ ባይኖረው ኖሮ ንብረቱን በእጁ ማስገባት የማይችል የነበረ ነገር ግን በዚሁ ሥልጣኑ በመጠቀም የንብረት ባለቤት ከሆነ በዚሁ ሰው ጥቅም እና በወካዩ ጥቅም መካከል ተቃርኖ የሚፈጠር በመሆኑ ይህንኑ ግጭት የማስወገድ ሃላፊነት ያለበት እንደራሴው ነው፡፡ የጥቅም ተቃርኖን በተመለከተ በሕግ ስህተት ላይ ተመርኩዞ የሚቀርቡ ይግባኞችን መርምሮ ውሳኔ የሚሰጠው ጠቅላይ ፍ/ቤትም በአመልካች ካሰች ተካልኝ እና በተጠሪዎች ሀ/ማርያም እና ትእግስት መካከል በተደረገ ክርክር በመ/ቁጥር 3224 መጋቢት 9/2000 ዓ/ም በሰበር ውሳኔው የሚከተለውን ጉዳይ መርምሮ አስገዳጅ ውሳኔ ሰጥቷል፡፡                                                                                    

ፍርድ፡- ይህ ጉዳይ የተጀመረው በፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ሲሆን የአሁን አመልካች ከሳሽ ተጠሪዎች ደግሞ በተከሳሽነት ተከራክረዋል፡፡ በዚህም መሠረት አመልካች በተጠሪዎች ላይ ባቀረቡት ክስ 1ኛ ተጠሪ የአመልካችን ንብረት እንዲያስተዳድር በአመልካች አማካኝነት ጥቅምት 20 ቀን 1998 ዓ.ም. የውክልና ሥልጣን ተሰጥቶት የነበረ ሲሆን ከዚያ በኋላም 1ኛ ተጠሪ አመልካችን አግባብቶ ቃለመሐላ ትፈጽሚያለሽ በማለት ወደ ንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ውልና ማስረጃ ምዝገባ ጽ/ቤት በመውሰድ አመልካች አንብቤ ምንነቱን ያልተረዳሁትን ሰነድ ሚያዝያ 19 ቀን 1998 ዓ.ም. እንድፈርም አድርጎኛል፡፡ ከዚያም አመልካች ያለአግባብ ለ1ኛ ተጠሪ ውክልና መስጠቴን ስገነዘብ በማግስቱ ሚያዝያ 2 ቀን 1998 ዓ.ም. ውክልናውን ሽሬያለሁ፡፡ ሆኖም ሰነዶቹ 1ኛ ተጠሪ እጅ ስለነበሩ በአራዳ ክ/ከተማ የሚገኘውን የአመልካችን ጅምር ቤትና ኒሳን የቤት መኪና ለባለቤቱ ለ2ኛ ተጠሪ እጅግ አነስተኛ በሆነ ዋጋ ሸጧል፡፡ ሰለሆነም 1ኛ ተጠሪ ከኑሮ አጋሩ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ያደረገው የቤትና የመኪና ሽያጭ ውል ከእራሱ ጋር እንደተደረገ ስለሚቆጠር በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2188 መሠረት ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ በሁለቱ ተጠሪዎች መካከል ሚያዝያ 19 ቀን 1998 ዓ.ም. የተደረገው የቤትና የመኪና ሽያጭ ውል ፈራሽ ነው ተብሎ ይወሰንልኝ በማለት ዳኝነት ጠይቀዋል፡፡ የአመልካች ክስና ማስረጃም ለተጠሪዎች ደርሶ የየበኩላቸውን ክርክር አቅርበዋል፡፡ በዚህም መሠረት 1ኛ ተጠሪ በሰጡት መልስ 1ኛ ተጠሪ የአመልካችን ንብረቶች ለ2ኛ ተጠሪ ያስተላለፉት ከአመልካች በተሰጣቸው የውክልና ሥልጠና መሠረትና ከሥልጣናቸውም ወሰን ሳያልፉ በመሆኑ የሽያጭ ውሉ በፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2189/1/ መሠረት ከሣሽ እራሳቸው እንዳደረጉት ስለሚቆጠር በዚህ ክስ ውስጥ 1ኛ ተጠሪ የተካተትኩት ያለአግባብ ስለሆነ ከክሱ ልሰናበት ይገባል በማለት የመጀመሪያ ደረጃ መቃወሚያ አቅርበዋል፡፡ ፍ/ቤቱም ይህንኑ መቃወሚያ መርምሮ የአመልካች የዳኝነት ጥያቄ ውል ይፍረስልኝ የሚል ሲሆን እንዲፈርስ በተጠየቀው ውል ተዋዋይ ወገኖች ደግሞ አመልካችና 2ኛ ተጠሪ ስለሆኑ 1ኛ ተጠሪ አመልካችን በመወከል ውሉን ያደረጉ በመሆኑ ውሉ በማናቸውም ምክንያት የሚፈርስም ሆነ የሚቀጥል ቢሆን ውጤት የሚኖረው በአመልካችና በ2ኛ ተጠሪ መካከል ስለሆነ 1ኛ ተጠሪ በክሱ ውስጥ የተካተቱት ያለ አግባብ ነው በማለት ከክሱ አስወጥቷል፡፡ 2ኛ ተጠሪም በበኩላቸው ባቀረቡት ክርክር አመልካች ለ1ኛ ተጠሪ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት ለመሸጥ የሚያስችል ውክልና መስጠታቸውን በማረጋገጥ ለክርክሩ ምክንያት የሆኑትን ቤትና መኪና ከ1ኛ ተጠሪ መግዛታቸውን ውሉ በተደረገበት ሚያዝያ 19 ቀን 1998 በ1ኛ እና በ2ኛ ተጠሪ መካከል የጋብቻ ግንኙነት እንዳልነበረና ጋብቻው የተፈጸመው ከዚያ በኋላ መሆኑን ገልጸው የሽያጩ ውል ሊፈርስ አይገባም በማለት ተከራክረዋል፡፡ የግራ ቀኙ ክርክር በዚህ መልኩ የቀረበለትም የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት ጉዳዩን መርምሮ አመልካች የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2188 ላይ የተመለከተውን በመጥቀስ 1ኛ ተጠሪ ከባለቤቱ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ያደረገው ውል ከእራሱ ጋር እንዳደረገው ይቆጠራል በማለት ያነሱትን ክርክር በተመለከተ በሕጉ ላይ የተደነገገው ተወካዩ

ከእራሱ ጋር ውሉን በሚያደርግ ጊዜ ሲሆን እመልካች ይፍረስልኝ በማለት የሚጠይቁት ውል ግን 1ኛ ተጠሪ አመልካችን ሻጭ እራሱን ገዢ በማድረግ ሳይሆን 2ኛ ተጠሪን ገዢ በማድረግ ስለሆነ ከእራስ ጋር የተደረገ ውል የሚያስብል ሁኔታ የለም ካለ በኋላ 1ኛ እና 2ኛ ተጠሪ በክብር መዝገብ ሹም ፊት ጋብቻ የፈጸሙት ሚያዝያ 30 ቀን 1998 ዓ.ም. ስለመሆኑ የክብር መዝገብ ኮፒ በማስረጃነት የቀረበ በመሆኑ ውሉ በተደረገበት በሚያዚያ 19 ቀን 1998 ዓ.ም. ሁለቱ ሰዎች ባልና ሚስት አልነበሩም፡፡  ባልና ሚስት ነበሩ ቢባል እንኳ የየራሳቸው ሰውነት /Personአlity/ በጋብቻው ምክንያት እንደሚጠፋና እንደ አንድ ሰው እንደሚቆጠሩ በሕግ ያልተመለከተ በመሆኑ 1ኛ ተጠሪ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ያደረጉት ውል ከገዛ እራሳቸው ጋር እንደተደረገ አይቆጠርም በማለት በውሣኔው ላይ አስፍሮ በመጨረሻም አመልካች በወኪላቸው አማካይነተ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ያደረጓቸው የቤትና የመኪና ሽያጭ ውሎች በአግባቡ በተሰጠ ሥልጣን የተደረጉ በመሆኑ ውሉ የሚፈርስበት ምክንያት የለም በማለት ክሱን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ አመልካች በዚህ ውሣኔ ቅሬታ አድሮባቸው የይግባኝ ቅሬታቸውን ለፌ/ከ/ፍ/ቤት ያቀረቡ ቢሆንም በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 337 መሠረት ፍ/ቤቱ ይግባኙን ሳይቀበለው ቀርቷል፡፡ የሰበር አቤቱታውም የቀረበው ይህንኑ በመቃወም ሲሆን ይህ ሰበር ችሎት አቤቱታውን መርምሮ የቤትና የመኪና ሽያጭ ውሉ አይፈርስም ተብሎ በበታች ፍ/ቤቶች መወሰኑ ተጠሪዎችን በመጥራት ሊወሰን የሚገባው መሆኑን በማመኑ በዚሁ መሠረት ተጠሪዎችን በመጥራት ግራ ቀኙን አከራክሯል፡፡    በአጠቃላይ የጉዳዩ ይዘት ከላይ የተመለከተው ነው፡፡  የዚህን ሰበር ችሎት ምላሽ ማግኘት የሚገባውም የጉዳዩ ጭብጥ 1ኛ ተጠሪ አመልካችን በመወከል ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ያደረጉት የቤትና የመኪና ሽያጭ ውል ሊፈርስ ይገባልን? ወይንስ አይገባም? የሚለው በመሆኑ ይህንኑ ጭብጥ በመያዝ አቤቱታው እንደሚከተለው ተመርምሯል፡፡   አመልካች ሚያዝያ 19 ቀን 1998 ዓ.ም. በተሰጠ የውክልና ሥልጣን በስማቸው ተመዝግቦ የሚገኝ የሚንቀሳቀስም ሆነ የማይንቀሳቀስ ንብረት መሸጥንም ጨምሮ ለ1ኛ ተጠሪ የውክልና ሥልጣን የሰጡ ስለመሆኑ በማስረጃ ተረጋግጧል፡፡   አወዛጋቢው ነጥብ ይህ የውክልና ሥልጣን ከተሰጠ በኋላ 1ኛው ተጠሪ ለክርክሩ ምክንያት የሆኑትን ቤቶችና መኪና በሽያጭ ለ2ኛ ተጠሪ ማስተላለፋቸው ከውክልና ሕግ አኳያ አግባብነቱን በተመለከተ ነው፡፡  ይህንንም የክርክር ነጥብ የግራ ቀኙ ግንኙነት በተለይ ከሚገዛው የውክልና ሕግ ጋር በማገናዘብ ተመልክተናል፡፡ 1ኛ ተጠሪ ከላይ በተመለከተው ሚያዝያ 19 ቀን 1998 ዓ.ም. የውክልና ሥልጣኑን ከአመልካች ከተቀበሉ በኋላ የዚያኑ እለት ለክርክሩ ምክንያት የሆኑትን ቤትና መኪና በወካዩ በአመልካች ስም ለ2ኛ ተጠሪ በሽያጭ ያስተላለፉ ሲሆን አመልካች ይህንን ሽያጭ የሚቃወሙት በ1ኛ እና 2ኛ ተጠሪ መካከል የባልና ሚስት ግንኙነት ስላለ ከፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2188/1/ አኳያ ከራስ ጋር እንደተደረገ ስለሚቆጠር ፈራሽ ነው በማለት ነው፡፡ የተጠቀሰውም የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2188/1/ ድንጋጌ እንደራሴው ከእራሱ ጋር ውሉን ተዋውሎ በተገኘ ጊዜ ሿሚው ይሄው ውል እንዲፈርስ መጠየቅ እንደሚችል ይደነግጋል፡፡ ነገር ግን 1 ኛ እና 2 ኛ ተጠሪ የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በውሣኔው ላይ እንደጠቀሰው የክብር መዝገብ ሹም ፊት በመቅረብ ጋብቻቸውን የፈጸሙት ሽያጩ ከተደረገ በኋላ ሚያዝያ 30 ቀን 1998 ዓ.ም. በመሆኑ በሕግ ዓይን የሽያጭ ውል በተደረገ ጊዜ በሁለቱ መካከል ጋብቻ አለ ለማለት ስለማይቻል አመልካች የጠቀሱት የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2188/1/ ለጉዳዩ አግባብነት ያለው ሆኖ አልተገኘም፡፡    በሌላ በኩልም እንደራሴው የውክልና ሥልጣኑን በሚያከናውንበት ጊዜ ተቃዋሚ ጥቅሞችን የማስወገድ ግዴታ እንዳለበት /Duty to አvoid conflict of interest/ ከእንደራሴውም ጋር ውሉን የፈጸመው ሦስተኛ ወገን የሚያውቅ

ወይንም ማወቅ የሚገባው ሆኖ በተገኘ ጊዜ በሿሚው ጥያቄ መሠረት ውሉ ሊፈርስ እንደሚችል በፍ/ብ/ሕ/ብ/ቁ. 2187/1/ ላይ ተመልክቶ ይገኛል፡፡ ክርክሩም ከዚሁ ድንጋጌ አኳያ ሲታይ የሽያጭ ውሉ በተደረገ ጊዜ ተጠሪዎች ባልና ሚስት እንዳልነበሩ የተረጋገጠ ቢሆንም ሚያዝያ 19 ቀን 1998 ዓ.ም. ሽያጩ ተደርጎ ሚያዝያ 30 ቀን 1998 ዓ.ም. ከ1 ቀን በኋላ ጋብቻቸውን መፈጸማቸው ሲታይ ሽያጩ በተደረገ ጊዜ በሽያጭ የሚተላለፈው ንብረት በቅርብ እርቀት የእራስ ንብረት ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ውሉ የተደረገ መሆኑን አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡  እንደራሴ ደግሞ ምንጊዜም ቢሆን የሿሚውን ፍላጎትና ጥቅም ብቻ መሠረት አድርጎ ግዴታውን ሳይወጣ ከቀረና የእራሱን ፍላጎትና ጥቅም መሠረት ካደረገ የጥቅም ግጭት መኖሩ የማይቀር ይሆናል፡፡  2ኛ ተጠሪም እንደራሴው 1ኛ ተጠሪ በሚያደረገው የሽያጭ ውል የጥቅም ግጭት መኖሩን እየተገነዘቡ ውሉን ማድረጋቸው የተረጋገጠ በመሆኑ በዚሁ ሁኔታ የተፈጸመው ውል ፈራሽ ነው እንዲባል አመልካች ያቀረቡት አቤቱታ ከተጠቀሰው የፍ/ብ/ሕ/ቁ. 2187/1/ አኳያ ተቀባይነት ያለው በመሆኑ የሥር ፍ/ቤቶች ውሉ ሊፈርስ አይችልም በማለት የሰጡት ውሣኔ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ሆኖ ተገኝቷል፡፡   ው ሣ ኔ 1. የፌ/መ/ደ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 69247 በሐምሌ 9 ቀን 1999 ዓ.ም. የሰጠው ፍርድ Eንዲሁም የፌ/ከ/ፍ/ቤት በመ/ቁ. 57884 በሐምሌ 19 ቀን 1999 ዓ.ም. የሰጠው ትEዛዝ መሠረታዊ የሕግ ስህተት የተፈጸመበት ስለሆነ በፍ/ብ/ሕ/ሥ/ሥ/ቁ. 348/1/ መሠረት ተሽሯል፡፡   2. 1ኛ ተጠሪ አመልካችን በመወከል በአራዳ ክ/ከተማ ቀበሌ 07/08 በካርታ ቁጥር 26651 ተመዝግቦ የሚገኘውን ጅምር ቤትና የሰ/ቁ. 2-52117 ኒሳን የቤት መኪና ላይ ከ2ኛ ተጠሪ ጋር ያደረጉት የሽያጭ ውል የጥቅም ግጭት /Conflict of interest/ ያለበት መሆኑ የተረጋገጠ ስለሆነ ውሉ ሊፈርስ ይገባል በማለት ተወስኗል፡፡  

ተወካይ ሊኖረው ስለሚገባ ትጋት፡-የፍትሃብሄፈር ህጋችን እንደራሴው ሥራውን በሚያከናውንበት ጊዜ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግ መትጋት እንዳለበት በአንቀጽ 2211 ስር ይደነግጋል፡፡ የትጋቱን ደረጃ ለማሳየትም አንድ መልካም አባት ቤተሰቡን ለመጠበቅ እንደሚያደርገው ሁሉ በሚል ሀረግ አስፍሮታል፡፡ ከዚህ አገላለጽ የምንረዳው ወካይ(እንደራሴው)ሥራውን ቸል ሳይል ልዩ ትኩረት ሰጥቶ የራሱን ሥራ በመልካም እንደሚሠራ ሰው መሥራት ያለበት ስለመሆኑ ነው፡፡ በመሆኑም ምክንያታዊ በሆነ የሰው ልጅ አስተሳሰብ ሊመዘን በሚችል ሁኔታ ሥራውም ሆነ በሥራው በተገቢ መሠራት የጥቅም ተጋሪ አለመሆንን ከግምት አስገብቶ ከሚፈጠር ስንፍና ወይም እራስ ወዳድነት በመራቅ ወካዩን ስኬትን ለማጎናጸፍ በሚያስችል የሥራ ትጋት መሥራት ይጠበቃል፡፡ 

ሥራን በራሱ ስለመፈጸም፡-በመርህ ደረጃ እንደራሴው ከወካዩ በተሰጠው የውክልና ሥልጣን የሚያከናውነውን ተግባር ወይም ሥራ በራሱ መፈጸም አለበት፡፡  ምክንያቱም ሌላ ምርመራ ሳያስፈልግ ወካዩ ለዚህ ሰው ውክልና መስጠቱ ሥራው በዚሁ ሰው እንዲሠራ በመፈለግ መሆኑን መገንዘቡ አቻ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው፡፡ ይሁንና እንደራሴው ሥራው በሌላ ሰው እንዲሠራ ከፈለገ በሱ ቦታ ሌላ ሰው ተተክቶ እንዲሠራ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ይህ የሚሆነው ወካዩ ሲፈቅድ እና ሥራው በእንደራሴው በራሱም ሆነ በተተኪው ቢሠራ ለወካዩ ለውጥ ከሌለው ወይም አንድ ከሆነ ነው፡፡  በመሆኑም የሚሠራውን ሥራ ባሕርይ በሚገባ መለየት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ በሌላም በኩል እንደራሴው ድንገት ባጋጠመው መሰናክል ሥራውን በራሱ መሥራት ባይችል እና  ይህንኑ ጉዳይ ወካይ ለሆነው ሰው ለማሳወቅ በማይችልበት የጊዜ ሁኔታ ውስጥ ከተገኘ ሌላውን የወካዩን ፍቃድ ሳየጠብቅ ሌላውን ሰው ተክቶ ማሠራት የሚገባው ስለመሆኑ በሕግ ታዟል፡፡

በዚህ አግባብ ወካዩ ሳይፈቅድለት ተተኪውን ተክቶ ያሠራ እንደሆነ ተተኪው በሠራው ሥራ በሦስተኛ ወገን ላይ ለሚያደርሰው ጉዳት እንደራሴው በቀጥታ ተጠያቂ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ሥራው እንዲሠራለት የውክልና ሥልጣኑን የሰጠው ለእንደራሴው በመሆኑ እና ከተተኪው ጋር ምንም ዓይነት ውል ስለሌላችው መጠየቅ የሚችልበት አግባብ ስለማይኖር ነው፡፡ ይሁንና እንደራሴው ተተኪውን የተካው ወካዩ ፈቅዶለት ከሆነ ተተኪው በሥራው በሌሎች ላይ ላደረሰው ጉዳት ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ባገኘው ፍቃድ መሠረትም ቢተካ ተተኪውን በተገቢው በመምረጥ ሂደት ስህተት ከፈጸመ(በጥንቃቄ ካልመረጠ) እና በሰጠው ተገቢ ያልሆነ መሪ የሥራ ትዕዛዝ መሰረጥ ጥፋት ከደረሰ ዕንደራሴው ስለ ተተኪው ሥራ ሀላፊ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አቶ ነ በጠቅላላ የውክልና ግንኙነት የ አቶ ፐ ወኪል ነው፡፡ ነገር ግን ባጋጠመው ህመም ምክንያት ከሥራዎቹ አንዱ የሆነውን የገቢ ግብር ክፍያ ለመፈጸም ፍጹም ባለመቻሉ የመክፈያው ጊዜ ካለፈ ሊከተል የሚችለውን ተጠያቂነት ለማስወገድ ወንድሙ የሆነውን አቶ ጀ ን በሱ እግር ተተክቶ ክፍያውን እንዲፈጽምለት አስቦ ወካዩን ለማሳወቅ ስልክ ቢደውልም ግለሰቡ ካለበት ቦታ አንጻር የስልክ አገልግሎት ባለመኖሩ ምክንያት ፍቃድ ያላገኘ ቢሆንም ጀ ን ተክቶ አሰርቷል፡፡ በዚህ ረገድ ወኪሉ ባልፈቀደበት ሁኔታ ተተኪው ለሠራው ሥራ ተወካይ ሀላፊ ይሆናል፡፡ ግብሩን በመክፈል ፋንታ ለግል ጥቅም አውሎት ቢገኝ ያልተከፈለውን ግብር ጨምሮ ባለመከፈሉ  ምክንያት በሥራው ላይ ለሚደርሰው ጉዳት ሁሉ እነደራሴው ሀላፊ ይሆናል፡፡

የጥቅም ግጭትን ማስወገድ (confict of interest) ማስወገድ እና ውሎችን ወካዩ በሆነው ስም የመፈረም እና ሦስተኛ ለሆኑ ወገኖች ሥራውን ለማን እንደሚሠራ የመግለጽ ግዴታዎች ይኖሩታል፡፡

ወካዩ ስለ እንደራሴው ያሉበት ግዴታዎች

የወካዩ ከሆኑት ግዴታዎች አንዱ እና የመጀመሪያው በእንደራሴነት ስለ እሱ ሆኖ ሥራውን ላከናወነለት ሰው ተገቢውን የድካም ዋጋ መፈል ግዴታ ያለበት ስለመሆኑ ነው፡፡ ይህ የሚሆነው በመካከላቸው ያለው ግንኙነት በክፍያ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ነው፡፡ የክፍያውን መጠን በተመለከተ በተዋዋዮች መካከል በተደረገው ውል ላይ በሠፈረ የክፍያ መጠን ወይም ያልተጠቀሰ ከሆነ ዳኞች ከሙያው ዓይነት ከልማዳዊ ሕግ አንጻር በሚወስኑት መሠረት የድካም ዋጋ የሚከፈል ይሆናል፡፡ የህንን ክፍያ ወካዩ የሚገባኝን ወይም ሥራው ሊያስገኝ የሚገባውን ያህል ውጤት አላገኘሁም ሲል ለተወካዩ ሊከፍል የሚገባውን ክፍያ መከልከል አይችልም፡፡ ነገር ግን ተወካዩ ጥፋትን ፈጽሞ ለወካዩ ሊከፍለው የሚገባ ክፍያ ካለ ወካዩ ለእንደራሴው ሊከፍለው ከሚገባው የድካም ዋጋ ክፍያ እና ባደረሰው ጉዳት ምክንያት እንደራሴው ለወካዩ ሊከፍለው ከሚገባው የክፍያ መጠን መሀል ያለውን የገንዘብ ልዩነት ይከፍለዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ ማቻቻል ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ከዚህ ከላይ ከጠቀስነውም ሆነ በሌላ በማንኛውም ምክንያት ወካዩ የድካም ዋጋ ክፍያውን ለመፈጸም እምቢተኛ ከሆነ ወካዩ ክፍያውን አጠናቅቆ እስኪከፍል ድረስ እንደራሴው በውክልና ግንኙነታቸው ምክንያት እጁ ከገቡት የወካዩ ንብረቶች መካከል ሊከፈለው ከሚገባው የገንዘብ መጠን ጋር እኩል የሆነውን በይዞታው ስር ሊያቆየው የሚችል ስለመሆኑ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2224 ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም በ1996 ዐ.ም የወጣው የኢፌዲሪ ወንጀል ሕግ አንቀጽ 436(ለ) ስር ሊከፈለው የሚገባውን ክፍያ ለማግኘት ሲል የባለዕዳው ንብረት የሆነውን ማንኛውንም ተንቀሳቃሽ ዕቃ የወሰደበት እነደሆነ በህገወጥ መንገድ መብትን ማስከበር ወንጀል ስር እንደሚቀጣ ለደነገገው ድንጋጌ በስተቀሩ(exception) ነው ወደሚል ድምዳሜ ይወስደናል፡፡ ምክንያቱም በሕግ እንዳይደረጉ በግልጽ ክልከላ የተደረገባቸው ተግባራትን የፈጸመ ካልሆነ በስተቀር በወንጀል ሊጠየቅ እንደማችል ግልጽ ነው፡፡ በተቃራኒው የተፈቀዱ ተግባራትን መፈጸም የወንጀል ተጠያቂነትን ሊያስከትል አይችልም፡፡   

እንደራሴው ሥራውን የሚሠራው ስለ ሷሚው ሲል በመሆኑ ሷሚው ሥራው የሚካሄድበትን ወይም የሚከናወንበትን ክፍያ ሊሰጠው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጪም ገንዘቡ ሳይሰጠው ወይም ሥራውን ባለመሸፈኑ ወይመ በሌላ ምክንያት ሥራውን በመልካም ለመምራት እና ውጤታማ ለማድረግ ከራሱ ያወጣውን ወጪ ሊተካለት ወይም ሊከፍለው የገባል፡፡

በዚሁ ሥራውም ከሦስተኛወገን ጋር ግዴታ ገብቶ ከሆነም ወካዩ ከዚህ ግዴታ ሊያወጣው ይገባል፡፡

እንደራሴው በወሰደው ሥልጣን መሠረት በሚያከናውነው ሥራ ምክንያት በጥቅሙ ወይም በአካሉ ላይ ጉዳት የደረሰበት እንደሆነ ሷሚው ኪሳራውን ሊከፍለው ይገባል፡፡ ይሁንና ወካዩ ይህ ግዴታ የሚኖርበት የደረሰው ጉዳት ከሥራው ከራሱ የመነጨ እንደሆነ ነው፡፡ ይህ ማለት በእንደራሴው ላይ የደረሰው ጉዳት በግለሰቡ በራሱ ጥፋት ምክንያት የደረሰ ጉዳት ከሆነ ሷሚው የኪሳራ ክፍያ እንዲከፍል አይገደድም፡፡

ስለ ውክልና መቅረት

የውክልና ግንኙነት በተዋዋዮች መካከል በሚኖር ውል ወይም በሕግ ሊመሠረት እንደሚችል ስለ ውል አመሠራረት በዳሰስንበት ርዕስ ስር ተመልክተናል፡፡ በተመሳሳይ ግንኙነቱ የሚያበቃው ወይም ቀሪ የሚሆነው በነዚሁ ሁለት መንገዶች መሆኑንም መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ውክልና ቀሪ የሚሆኑባቸው ምክንያቶች፡-

ሀ. የሷሚው ውክልናውን መሻር (revocation of agency)

በፍትሐብሔር ህጋችን ስለ ሷሚው ውክልናን መሻር በሰፈረው ድንጋጌ ሷሚው የጊዜ እና የሁኔታ ገደብ ሳይደረግበት በራሱ ግንዛቤ አስፈላጊ መስሎ በታየው ወይም ባሰበው ጊዜ ሁሉ ለእንደራሴው የሰጠውን የውክልና ሥልጣን ማንሳት እና በመካከላቸው የነበረውን ግንኙነት ማቋረጥ ይችላል፡፡ ይህን ለማድረግ በፍትሐብሔር ሕጉ ስለ ውሎች በጠቅላላው በሚል ርዕስ ስር ከተደነገገው በተለየ መልኩ ሷሚው ውክልናውን የሚሽር ስለመሆኑ የቅድሚያ ማስጠንቀቀያ (default notice) ለእንደራሴው እንዲሰጥ አይገደድም፡፡ እንደራሴውም ማስጠንቀቅያው ቀድሞ እንዲደርሰው የመጠየቅ መብት አይኖረውም፡፡

በብራዚል ሀገር በሥራ ላይ ያለው የእንደራሴነት ሕግ ከኢትዮጵያ ሕግ በተለየ መልኩ ወካዩ ሥልጣኑን መሻር ሲፈልግ ለእንደራሴው የ90 ቀናት ቅድሚያ ማስጠንቀቂ ሊሰጠው ግዴታ አለበት ሲል ይደነግጋል፡፡ በተነጻጻሪ የዚህ ጽሑፍ  አዘጋጅ የኢትዮጵያውን የደግፋል፡፡ በምክንያትም የውክልና ግንኙነት በባሕርይው የአንድ ሰው ጥቅም በሌላ በንብረቱ ላ መብት በሌለው ሰው አማካኝነት በሚሠራ ሥራ ላይ ሚመሠረት በመሆኑ ወካዩ የሰጠውን ሥልጣን በማንኛውም ጊዜ ማንሳት የማይችል ከሆነ የማስጠንቀቂያው ደብዳቤ የደረሰው እነደራሴ ሥራውን እነደማይቀጥል በማሰብ በሚቀሩት ቀናት ውስጥ ሷሚውን ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራትን ሊፈጽም እን የማይገባውን ብልጽግና ለማግኘት የሚችልበትን እድል የሚፈጥር በመሆኑ ነው፡፡ ተዋዋዮች በውላቸው ውስጥ ይህንን መርህ በሚቃረን መልኩ የወካዩን ሥልጣኑን በፈለገ ጊዜ የመሻር መብት የሚገድቡ ስምምነቶች በሕግ ፊት ተቀባይነት የላቸውም፡፡

ይሁንና ወካይ እንደራሴውን ከሥልጣኑ የሻረው የውል ጊዜው ከማለቁ በፊት ከሆነ እና በዚሁ መሻር ምክንያት ጉዳት ያደረሰበት ከሆነ ያደረሰበት ከሆነ ላደረሰው ጉዳት ኪሳራ የሚከፍል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ሥራውን ለማከናወን በሚል ከግል ኪሱ የቅድመ ክፍያ ለሦስተኛ ወገን ከፍሎ የነበረ እና ገንዘብ ተቀባዩ ውሉ ካልተፈጸመ በቀር ገንዘቡን የማይመልስለት ከሆነ ገንዘቡን ሊያጣ የሚችልበት ዕድል ሰፊ ነው፡፡ በመሆኑም በዚህ ምክንያት ለሚደርስበት ጉዳት ወካዩ ኪሳራውን ሊከፍል ግዴታ ይሆንበታል፡፡ ነገር ግን የእንደራሴነት ግንኙነታቸው ያለ ክፍያ(gratuitously) ከሆነ የውክልና ሥልጣኑን ለመሻር የሚያበቃ ምክንያት ሲኖረው ለምሳሌ ገንዘብ ወይም ሀብትን ሲመዘብር ወይም  ድርጅቱን ጥልቅ ለሆነ ኪሳራ እየዳረገው መሆኑን ሲረዳ የውል ጊዜው ባይጠናቀቅም የሰጠውን የውክልና ሥልጣን ሲሽር ዕንደራሴው ጉዳት ደርሶብኛል ሲል የካሳ ክፍያ መጠየቅ የማይችል ስለመሆኑ ሕጉ በግልጽ ይደነግጋል፡፡

ለ. የወኪሉ የውክልና ሥልጣኑን ስለመተው

ወካዩ የውክልና ግንኙነቱን ማቋረጥ በፈለገ በየትኛውም ጊዜ ሁሉ ሥልጣኑን የመሻር መብት እንዳለው ሁሉ እንደራሴውም  ሥልጣኑን ላለመጠቀም ወይም ለመተው በፈለገ ጊዜ ሁሉ ሥልጣኑን ሊተው እና ሊያቆም ይችላል፡፡ ይሁንና ከወካዩ ሥልጣን በተለየ መልኩ ሥራውን ለማቆም በወሰነ ጊዜ አስቀድሞ ወካዩን የማሳወቅ ግዴታ አለበት፡፡ ሕጉ ይህንን ግዴታ ያደረገበት ምክንያት እንደራሴው ሥራውን በሚያቆም ጊዜ ንብረቱ ወይም ሥራው ከጠባቂ ማጣት የተነሳ ለብልሽት፣ ለብክነት  ወይም ለጥፋት እነዳይዳረግ በማሰብ ነው፡፡

እንደራሴው ሥልጣኑን በሚያቆም ጊዜ በሷሚው ላይ ጉዳትን አስከትሎ ከሆነ ካሳ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል ፡፡ ነገር ግን ሥልጣኑን ለመተው የቻለው ሥራውን ባለበት ሁኔታ ቢቀጥል በገዛ  ራሱ ላይ ከፍ ያለ ጉዳት የሚያስከትልበት እና ሥራውን ለመቀጠል እንዳይችል የሚያደርገው በቂ ምክንያት መኖሩ ከታወቀ ወይም ከተረጋገጠ ጉዳትን አድርሶ እንኳን ቢሆን ኪሳራ የመክፈል ግዴታ የማይኖርበት 

ሐ. የተወካዩ መሞት ወይም ሥራ ያለመቻል

የውክልና ግንኙነት ከሚቋረጥባቸው ምክንያቶች አንዱ እና ሌላኛው የተወካዩ  መሞት፣ በስፍራው ያለመኖር፣ የመሥራት ችሎታ ማጣት ወይም በሥራው መክሰር ነው፡፡ የፍትሐብሔር ሕጉ አንቀጽ 2230(1)ወካይ እና እንደራሴው በውላቸው እነኚህ ምክንያቶች ሊከሰቱ እንደሚችሉ አስቀድመው በማሰብ በውላቸው ላይ ተቃራኒ የሚሆን ውል አካትተው ካለተስማሙ በቀር በመካከላቸው ያለው ግንኙነት ወድያውኑ ቀሪ ይሆናል፡፡ ተቃራኒ የሚሆን ስምምነት ስለሚለው ሃረግ ምሳሌ እናንሳ-አቶ ለ ከ አቶ ሀ ጋር በገባው የውክልና ግዴታ የወካዩን የአቶ ሀ ን የእርሻ ሥራ ሥራ በተመለከተ ሙሉ ሥራውን ሊያስተዳድርለት ፍቃዱን ሰጥቷል፡፡ ይሁንና ድንገት እየተነሳ ለሞት እንዳይዳርገው ሁሌም ስጋቱ የሆነው የልብ ህመሙ ቢነሳ እና የሚገለው ቢሆን እሱ ጀምሮት የነበረውን ሥራ ሕጋዊ ወራሾቹ የሆኑት ሰዎች በሱ ቦታ ተተክተው የሚቀጥሉት ይሆናል በሚል ከወካዩ ጋር ቢስማሙ የሱ መመትም ሆነ የመሥራት ችሎታ ማጣት ለውሉ መቋረጥ ምክንጣት መሆኑ ሊቀር ይችላል፡፡

ከነዚ ምክንያቶች ለየት የሚለው የተወካዩ መክሰር ነው፡፡ ምክንያቱም መሞት፣ በስፍራ ያለመኖር እና ችሎታ ማጣት ግለሰቦች በማንኛውም ዐቋም ወይም የሙያ ሥራ ላይ ቢገኙ ሊከሰቱባቸው የሚችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የመክሰርን ጽንሰ ሀሳብ በተመለከተ ግን በንጉሰ ነገስቱ መንግስት የንግድ ሕግ(commertiአl code)አንጻር መመልከት ተገቢ ነው፡፡ ሕጉ መክሰርን በተመለከተ ከአንቀጽ 968 ጀምሮ ባሉት ድንጋጌዎቹ ሊከስሩ የሚችሉ ሰዎች ነጋዴዎች እንደሆኑ ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ስለ ተወካይ መክሰር ለማውራት በቅድሚያ ግለሰቡ ነጋዴ ሆኖ በዚሁ የነጋዴነት ሥራው ምክንያት ከወካዩ ጋር የተገናኘ መሆኑ መረጋገጥ አለበት፡፡

ነጋዴ የሚባለው የሚባለው የማህበረሰቡ ክፍል የትኛው እንደሆን በዚሁ ንግድ ሕግ አንቀጽ 5 እና 10 ስር ተዘርዝረው እናገኛቸዋለን፡፡ በመሆኑም እንደራሴው በመክሰሬ ምክንያት ውሉ ቀሪ ሊሆን ይገባል ሲል ለማመልከት በነዚ ዝርዝሮች አግባብ ነጋዴ ስለመሆኑ እና የውላቸውም ባሕርይ ከሱ ነጋዴነት ጋር በቀጥራ ተያያዥ መሆን ያለበት ጉዳይ ነው፡፡

እንደራሴው በነዚ ምክንያቶች ሥራውን መሥራት የማይችል ሲሆን ሕጋዊ ወራሾቹ ወድያውኑ ለሷሚው ማሳወቅ አለባቸው፡፡ ይህ የማሳወቅ ግዴታ በወራሾቹ ላይ የሚወድቀው የሚወርሱት ሰው ከዚህ ቀደም ከሷሚው ጋር ያለውን የውክልና ውል ግንኙነት ያውቁ የነበለ መሂኑ ከተረጋገጠ ብቻ ነው፡፡ የወራሾቹ አናውቅም ነበር የሚል መከራከሪያ ሀሳብ ከተጠያቂነት ሊያድናቸው የሚችለው የማየውቁ ስለመሆናቸው ማስረዳት ሲችሉ ነው፡፡

በተጨማሪም ሷሚው በእንደራሴው ላይ የደረሰውን እክል ሰምቶ እና አውቆ ሥራውን መስመር ለማስያዝ እና ለማደራጀት እስኪችል ድረስ ሥራውን በተመለከተ ሷሚውን በሚጠቅም መልኩ እየሰሩ እና እየጠበቁ መቆየት አለባቸው፡፡

መ. የወካዩ መሞት ወይም ሥራ ያለመቻል

የወካዩ መሞት በውክልና ግንኙነቱ እጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው ተጽዕኖ ከእንደራሴው መሞት ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ወካዩ የሞተው ወይም ችሎታውን ያጣው እንደራሴው ሥራውን ማከናወን ከጀመረ በኋላ ከሆነ ዕና ክስተቱን ተከትሎ ወድያውኑ ሥራውን የሚያቆም ከሆነ በሥራው ላይ ጉዳት ሊደርስ የሚችልበት ሁኔታ ካለ ሕጋዊ ወራሾች ሥራውን ተቀብለው ማስተዳደር ወይም አግባብነት ያለውን አካሄድ እስኪመርጡ እና እስኪያመቻቹ ድረስ እንደራሴው ሷሚው በሰጠው የውክልና ሥልጣን ላይ ይቆያል፡፡ ምክንያቱም የሷሚው መብቶች ወደ ወራሾች የሚተላለፉ በመሆናቸው ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ሥራውን ወይም ንብረቱን ለጥፋት የሚዳርገው ከሆነ የወራሾች ጥቅም ለጉዳት የሚዳረግ በመሆኑ ነው፡፡

ሠ. የውል ዘመን/ጉዳይ/ሲያበቃ ወይም ፍጻሜ ሲያገኝ

ስለ እንደራሴነት በተዘረዘሩት ድንጋጌዎች ስር ውሎች በራሳቸው ባበቁ ጊዜ ውለታው ሊቋረጥ የሚችልበት  አግባብ ያልተደነገገ ቢሆንም የውክልና ውል ከውል ከሚመሰረቱ የሰዎች ግንኙነት መሀል አንዱ እንደመሆኑ መጠን ስለውሎች በጠቅላላው የተደነገጉት የወል ድንጋጌዎች በውክልና ግንኙነት  ውስጥም ተፈጻሚነት  ያላቸው በመሆኑ በፍትሐብሔር ሕግ አንቀጽ 1807 ላይ የሰፈሩትን የግዴታ ማስቀሪያ ምክንያቶችን መመልከት ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ በዚሁ አንቀጽ ንዑስ ፊደል ሀ ስር ግዴታው የተፈጸመበት… የሚል ሀረግን ያቀፈ በመሆኑ በውክልና ግንኙነትም እንደራሴው ስለ ወካዩ ሆኖ ለማከናወን ግዴታ የገባበትን ጉዳይ በስምምነታቸው አግባብ ፈጽሞ ካጠናቀቀ ግዴታው ቀሪ ይሆናል፡፡ በዚሁ መሠረት የውክልና ግንኙነቱም ይቋረጣል፡፡ ለምሳሌ የቤት ግዢ ይፈጽም ዘንድ የተወከለው ሰው ቤቱን ገዝቶ እና የስም ማዛወር ሥራውን ካጠናቀቀ በኋላ በሱ እና ቤቱን በገዛለት ሰው መሀከል ያለው የውክልና ግንኘኑነት ፍጻሜ ያገኘ በመሆኑ ቀሪ ይሆናል፡፡

የ1960ው የኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት መንግስት የንግድ ሕግም የውክልና ግንኙነት ከሚቋረጥባቸው ምክንያቶች አንዱ ወካይ እና ተወካይ በውላቸው ውስጥ የገለጹት የጊዜ ገደብ ሲያለፍ ወይም የውላቸው እድሜ ሲጠናቀቅ እነደሆነ where the period of time for which it wአs entered into expires ሲል በአንቀጽ 52(1) ሀ ስር ይደነግጋል፡፡ በመሆኑም ምንም እንኳን ስለ እንደራሴነት ከተደነገጉት እና የእንደራሴነት ውል ወይም ግንኙነት ከሚቋረጥባቸው ምክንያቶች መሀል ያልሰፈለ ቢሆንም ከፍትሐብሔር ሕጉ እና ከንግድ ሕጉ ድንጋጌዎች አንጻር አጣምሮ በማየት እንደ ግንኙነቱ ባሕርይ የውክልና ግንኙነት የሥራውን መጠናቀቅ ከግምት ባላስገባ መልኩ ግንኙነቱ የሚያበቃበት ቀን ከደረሰ ከተጠቀሰው ከዚሁ ቀን አንስቶ በወካዩ እና በእንደራሴው መሃከል የነበረው ግንኙነት እነደሚቋረጥ ወይም ቀሪ እንደሚሆን መረዳት ተገቢ ነው፡፡             

ማጠቃለያ

እንደራሴነት ማለት ሁለት ስዎች(ወካይ እና ተወካይ)በጋራ መግባባት ላይ ተመርኩዘው ከሕግ ወይም  ከውል በሚመነጭ የውክልና  ሥልጣን  መሠረት  ተወካይ የተወካይን  ሥራ በሱ ቦታ ሆኖ ወካዩ እየተቆጣጠረው  እና ሊያስገድደው በሚችል ሁኔታ ክሦስተኛ ወገን ጋር ግዴታ እንዲገባ በፈቀደ ጊዜ የሚፈጠር ግንኙነት ነው፡፡

አንደራሴነት ከሕግ ወይም ከውል የሚመነጭ ሲሆን  ከውል የሚመነጨው የውክልና ግንኙነት ተዋዋዮች  በውል ግዴታ ለመግባት የሚያበቃ  አቅዋም (በእድሜ፣ በአእምሮ እና በቅጣት ፍርድ) ላይ ሲገኙ በግልጽ ወይም  በዝምታ የሚፈጥሩት  ግንኙነት ነው፡፡

በዚህ መሠረት ተወካይ የተሰጠውን  የሥልጣን  ገደብ ሳያልፍ የወካዩን ሥራ መሥራት ግዴታው ሲሆን ከተሰጠው ሥልጣን  ወቶ ለሚያከናውነው ተግባር ወካዩ ሀላፊ አይሆንም፡፡ ይሁንና እንደራሴው ይህን ሊያደርግ የቻልው ቅን በሆነ ልቦና  ከሆነ እና ከወካዩ ጋር ባለው የሥራ ግንኙነት ሦስተኛ ወገን ከዚ ስው ጋር ውል ሊገባ የቻለው ስለ ወካዩ ሲል ይህንን ድርጊት የመፈጸም ሥልጣን አለው ብሎ በማመን  እንዲሁም ከሥራው ባሕርይ አንጻር ሥልጣኑ መስፋት እና ይህንኑ ተግባር ሊያቅፍ ዪገባ ነበር የሚያሰኝ ከሆነ ወካዩ ተግባሩን ያጸድቅለታል፡፡ ይህ ማለት ወካዩ ሃላፊ ዪሆናል ማለት ነው፡፡

ባለ ንብረት በንብረቱ ወይም በሥራው ላይ ሌላውን ሰው መወከል በማያስችለው ሁኔታ ላይ ሲገኝ ዳኞች የንብረት ጠባቂ (curator) ይሾሙለታል፡፡ ነገር ግን ይሕ ሰው የሚያከናውነው ተግባር አስቸክዋይ እና ጊዜ የማይሰጡትን ሥራዎች ብቻ ነው፡፡

የውክልና ሥልጣን እንደ ሥራው ባሕርይ እና እንደ ግንኙነታቸው  ሁኔታ ጠቅላላ ወይም ልዩ ሊሆን ይችላል፡፡  የወካዩ ቅጥረኛ  ከወካዩ ልዩ ሥልጣን ካልተሰጠው በቀር ከአስተዳደር ሥራዎች ውጪ እንደ የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ፣ ስጦታ መፈጸም አና የመሳሰሉትን ተግባራት መፈጸም አይችሉም ፡፡

አስተዳደራዊ ሥራዎች (acts of management) የሚባሉት የወካዩን ሀብት ማስቀመጥ እና መጠበቅ፣ ከ3 ዐመት ለማያልፍ ዘመን ማከራየት፣ በብድር የተሰጡትን ሀብት መሰብሰብ፣ ከሀብቱ የሚመጣውን ገንዘብ ተቀብሎ የማስቀመጥ እና ለተከፈሉ እዳዎች ደረሰኝ የመስጠት ሥራዎች ናቸው፡፡ ሰብልን፣ ለሽያጭ የቀረቡ እቃዎችን እና የሚበላሹ እቃዎችን መሸጥ እንደ አስተዳደር ሥራዎች ይቆጠራሉ፡፡

እንደራሴው ስለ ወካዩ የሚሠራቸውን  ሥራዎች እና የሚገባቸውን ግዴታዎች በቅን ልቦና መፈጸም አለበት፡፡ ሥራውን ውጤታማ ለማድረግም  በትጋት እና በጥንቃቄ መከወን አለበት፡፡ በተጨማሪም በራሱ የመሥራት ግዴታ ያለበት ሲሆን ነገር ግን ሥራው በሌላ ሰው ቢሠራ ለወካዩ ልዩነት የሌለው ከሆነ ሌላውን ሰው ተክቶ ሊያሠራ ይችላል፡፡ ነገር ግን ተኪውን የተካው ወካዩ  ፈቅዶለት ካልሆነ በቀር ተተኪው ለሚፈጽመው ጥፋት እነደራሴው ሀላፊ ይሆናል፡፡

ወካይ ለእንደራሴው የድካም ዋጋ የመክፈል ግዴታ አለበት፡፡ የሚከፈለው የገንዘብ መጠን በውላቸው ላይ የተጠቀሰ ከሆነ ይህንኑ የክፍያ መጠን የሚከፈለው ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን ዳኞች ከሙያው እና ከልማዳዊ አሠራር አንጻር ተገቢ የሆነው ክፍያ እንዲከፈለው ያዛሉ፡፡

እንደራሴው በሚሠራው ሥራ ምክንያት ጉዳት የደረሰበት ከሆነ ወካዩ ኪሳራውን  ሊከፍለው ይገባል፡፡  ይህ የሚሆነው  የደረሰው ጉዳት ከእራሱ ከእንደራሴው የመነጨ ካልሆነ ነው፡፡

ወካዩ በማንኛውም ተገቢ ነው ብሎ ባመነበት ግዜ ሁሉ የውክልና ሥልጣኑን የመሻር መብት አለው፡፡ ቅድሚያ ማስጠንቀቅያ ሊሰጥ አይገደድም፡፡ በተመሳሳይ እንደራሴውም በማንኛውም ግዜ ሥልጣኑን የመተው መብት ያለው ሲሆን  ከወካዩ  የመሻር ተግባር የሚለየው ሥልጣኑን መተው ሲፈልግ ለወካዩ የማሳወቅ እና ወካዩ ሥራውን አደራጅቶ እስኪረከበው ድረስ ሥራውን እየሠራ መቆየት አለበት፡፡

የተወካይም ሆነ የወካይ መሞት እንዲሁም የውል ዘመን ማብቃት ለውክልና ግንኙነት መቅረት ምክኒያቶች ናቸው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

የተፋጠነ ፍትሕ የማግኘት መብት እና ተግባራዊ አፈፃፀሙ
በኢትዮጵያ የወንጀል ፍትሕ ሥርዓት ወንጀለኛን (ተጠርጣሪን) የመያዝ አጠቃላይ አ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 30 October 2024