Font size: +
25 minutes reading time (4935 words)
Featured

ስለ እንደራሴ (ውክልና) ሕግ አንዳንድ ነጥቦች

ውክልናን የተመለከተው ሕግ በአገራችን በብዛት ስራ ላይ ከሚውሉ የሕግ ክፍሎች አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የፍትህብሄር ሕግ ቁጥር 2199 ውክልናን እንደተረጐመው “ውክልና ማለት ተወካይ የተባለ አንድ ሰው ወካይ ለተባለው ሰው እንደራሴ ሆኖ አንድ ወይም ብዙ ህጋዊ ሥራዎች በወካዩ ሥም ለማከናወን ግዴታ የሚገባበት ውል ማለት ነው” ይላል፡፡ ከትርጉሙ ለመረዳት እንደምንችለው ውክልና የሚደረገው በወካይና በተወካይ መካከል ሲሆን በውክልናው የሚከናወኑት ስራዎች ህጋዊ መሆን አንዳለባቸው ነው፡፡ ይህ ማለት ደግሞ ህጋዊ ባልሆኑ ነገሮች ላይ የሚደረግ ውክልና ተቀባይነት የለውም  ማለት ነው፡፡ በሰፊው ስንመለከት ሁለት አይነት ውክልናዎችን እናገኛለን፡፡ እነሱም በፍተሃብሄር ሕግ ቁጥር 2189 ላይ የተቀመጠው ፍፁም የሆነ እንደራሴነት /disclosed or complete  agency/ እና በዚሁ ሕግ ቁጥር 2197 ላይ የተቀመጠው እንደራሴው በራሱ ስም ተግባሮችን የሚፈፅምባቸው የውክልና አይነት/undisclosed agency/ ናቸው:: ለዚህ ፅሁፍ አላማ ግን  የመጀመሪያው አይነት ውክልና ማለትም ፍፁም የሆነውን የእንደራሴነት አይነት እንመለከታለን፡፡ ይህም በፍትሃብሄር ህጉ ቁጥር 2199-2233 ድረስ ያሉትን የህጉን አንቀጾች የተመለከተ ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ በዚህ ፅሁፍ ውስጥየውክልና አስፈላጊነት፣ የውክልና ምንጮች ፣ የውክልና አመሰራረት፣ የውክልና አይነቶች፣ የውክልና ግብ ፣ የተወካይና የወካይ ግዴታዎች፣ ውክልና የሚቋረጥበት ሁኔታ፣ ከውክልና መመሰረት ጀምሮ በውክልና አማካኝነት የሚከናወኑ ተግባሮችና ውጤቶቻቸው ድረስ ወካይ፣ ተወካይና የውክልና ማስረጃውን የሚሰጡ አካሎች ሊያደርጓቸው የሚገባቸው ጥንቃቄዎች የሚዳሰሱ ይሆናል፡፡

1.  ውክልና ለምን ያስፈልጋል?

አንድ ሰው አንዳንድ ተግባሮችን በራሱ ከማድረግ ይልቅ ሌላን ሰው በመወከል ተግባሮቹ እንዲከናወኑለት ይፈልጋል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ የጊዜ ጥበት፣ የቦታ ርቀት ወይም የሁኔታዎች አለመመቻቸት፣ የእውቀት ወይም የክህሎት አለመኖርና የችሎታ ማነስ ዋናዋናዎቹ ሲሆኑ ሌሎችም በምክንያትነት ሊጠቀሱ ይችላሉ፡፡ 

2.  የውክልና ምንጮች ምንድን ናቸው?

በኢትዮጵያ ፍትሃብሄር ሕግ አንቀፅ ቁ. 2179  ውክልና ወይም እንደራሴነት አንድም ከሕግ በሌላ መልኩ ደግሞ ከውል ሊመነጭ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡ ከሕግ የሚመነጨው ውክልና ከላይ እንደተገለፀው የውክልና ትርጉም አይነት ወካይና ተወካይ በመስማማት ስምምነት ላይ የሚደርሱበት የውክልና አይነት ሳይሆን ተወካይ የወካይን ተግባሮች ወካይ ባልፈቀደበት ሁኔታ ሊተገብረው የሚያስችለው አይነት ውክልና ነው፡፡ ይህም የውክልና ተግባር በህጉ ከተፈቀዱት የውክልና ሁኔታዎች ውጭ ሊመሠረት አይችልም፡፡ ለዚህ አይነቱ የውክልና አይነት እንደምሣሌነት የሚጠቀሱት ፤ ለአካለ መጠን ያልደረሰን ልጅ ንብረት ለማስተዳደር ሕግ የፈቀደላቸው ጠባቂዎች ውክልና አይነት እና በፍትሃብሄር ህጉ አንቀፅ ቁ. 2257 ላይ በተቀመጠው መልኩ ተግባሮችን የሚተገበሩ ሰዎች ውክልና አይነት ናቸው፡፡

ከውል የሚመነጨው ውክልና አይነት ደግሞ በፅሁፋ መጀመሪያ ውክልናን ለመተርጐም በተመለከተው መልኩ የተቀመጠው ወካይና ተወካይ የውክልና ስምምነት ውል የሚገቡበት አይነት ነው፡፡ በዚህም ፅሁፍ ውስጥ በሰፊው የሚዳሰሰው ይህ ከውል የሚመነጨው የውክልና አይነት ነው፡፡ ስለሆነም ከዚህ በመቀጠል የዚህን የውክልና አይነት አመሠራረትና የተለዩ ክፍሎቹን በፍትሃብሄር ሕግ ከቁጥር 2200-2207 በተቀመጠው መሠረት ለማየት አንሞክራለን፡፡

ውክልና እንዴት ይቋቋማል?  ምን ምን አይነት ውክልናዎችስ አሉ? ግባቸውስ ምንድን ነው?

ውክልና በግልፅ (ማለትም ወካይ የውክልና ስልጣኑን ለተወካይ እንደሰጠው በግልፅ በማሳወቅ) ወይም በዝምታ ሊሰጥ ይችላል፡፡ ተወካዩም ሊፈፅመው የሚገባው የሥራ ተግባር ስለአፈፃፀሙ በአንደንድ ህጋዊ ፎርም ውስጥ እንዲገባ የሚያስፈልገው ሲሆን ውክልናው ለተወካዩ ሊሰጠው የሚገባው ይኸው ሕግ በሚያዘው ፎርም መሠረት ነው (ፍ/ብ/ህ/ቁ.2200)፡፡ ማለትም ለምሣሌ ተወካዩ ከተወከለ በኋላ ሊያከናውናቸው የሚችሉት ጉዳዬች ወይም የሚዋዋላቸው ውሎች በፅሁፍ መሆን ግድ የሚላቸው አይነት ከሆኑ ከወዲሁ የሚደረገው የውክልና ውልም በፅሁፍ መሆን አለበት ማለት ነው፡፡

በሌላ መልኩ ውክልናውን የሚቀበለው ተወካይ መቀበሉን በግልፅ ወይም በዝምታ ሊፈጽም ይችላል፡፡ ውክልናውን መቀበል የማይፈልግ ከሆነ ደግሞ በግልፅ እንደማይቀበል በመግለፅ ከኃላፊነት እራሱን ማግለል ይችላል፡፡ ስለሆነም ተወካይ ውክልናውን የማይቀበል መሆኑን ከወዲሁ በግልፅ ካላስታወቀ በስተቀር የተወከለበት ነገር ከሚያካሂደው ሥራ ጋር ግንኙነት ያለው ጉዳይ መሆኑ በግለፅ የታወቀ ከሆነ፣ ወይም ከሙያ ሥራው አመራር ጋር የሚመሣሠል ጉዳይ ከሆነ፣ ወይም ይህንን የመሠለውን ጉዳይ ለመሥራት ፍቃደኛ ለመሆኑ በአደባባይ ገልጾ ሀሳብ በማቅረብ አስታውቆ እንደሆነ ውክልናውን እንደተቀበለ ይቆጠራል(ፍ/ብ/ህ/ቁ. 2201)።

በመሠረቱ አንድ ሰው ለቀረበለት ውል ምላሸ ሳይሰጥ ዝም ቢል የቀረበለትን የውል ሀሳብ እንደተቀበለ እንደማያስቆጥርበት የፍትሀብሄር ሕግ.ቁ 1682 ይደነግጋል፡፡ ነገርግን የውክልና ጉዳይ እንደ ልዩ ሁኔታ የሚወሠድ ስለሆነ እንድ ሰው በቀረበለት የውክልና ውል ላይ ግልፅ የሆነ ያለመቀበል ሃሣብ እስካላቀረበ ድረስ ዝምታው የውክልናውን ውል እንደተቀበለ የሚያስቆጥርበት መሆኑን የፍ/ብ/ህ//ቁ 2201 (2) ደንግጓል፡፡ ስለዚህ የውክልናው ውል ውክልናውን ባቀረበውና በተቀበለው ሰው መካከል ይመሠረታል ማለት ነው፡፡ ውክልናው የሚሰጠው ለብዙ ሰዎች ከሆነ ግን የውክልና ስልጣኑን ሁሉም ባንድነት መቀበላቸው ካልተረጋገጠ በቀር ውክልናው እንደጸና አይቆጠርም/የፍ/ብ/ህ/ቁ.2218/1/።

እንግዲህ በዚህ መልኩ ውክልናው ተቋቋመ። ውክልናው ሲቋቋም የውክልናው ወሰን እስከምን ድረስ ነው የሚለው ደግሞ በፍትሃ ብሄር ህጉ አንቀፅ ቁ 2202 ላይ ተቀምጧል። በዚህም መሠረት የውክልናው ወሰን በውሉ ላይ በግልፅ ተጠቅሶ ካልተቀመጠ በስተቀር ለውክልናው የሚሰጠው ወሰን እንደ ጉዳዩ አይነት ነው የሚሆነው (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2202 (1))። ወካዩ የውክልናውን ወሰን በውክልናው ውል ላይ በግልፅ ካስቀመጠ ወሰኑ በግልጽ በተቀመጠው መሠረት ይሆናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ውክልናው ለአንድ ልዩ ጉዳይ ወይም ለእያንዳንዱ ጉዳዬች ወይም ለወካዩ ጉዳዮች ሁሉ ጠቅላላ ውክልና ሊሆን ይችላል (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2202 (2))። ይህ ማለት አንድ ሰው ለአንድ ለተወሠነ ጉዳይ ብቻ ወይንም ለተለያዩ ከአንድ በላይ ለሆኑ ጉዳዬች ወይንም ለሁሉም ጉዳዬቹ ውክልና ሊሰጥ ይችላል ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ከላይ በተጠቀሰው የውክልና ወሰን መሠረት ውክልናን ጠቅላላ ውክልናና ልዩ ውክልና ብለን ልንከፍላቸው እንችላላን፡፡

ጠቅላላ ውክልና

ጠቅላላ ውክልና ማለት በጠቅላላ አነጋገር የተደረገ ውክልና ሲሆን ለተወካዩ በፍትሃብሄር ሕግ ቁ 2204 ላይ የተቀመጡትን የአስተዳደር ሥራዎች ከመፈፀም ውጭ ሌላ ሥልጣን  አይሰጠውም (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 2203)። ይህ ማለት ወካይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በዝርዝር ሳይገለፅ አንዲሁ ጠቅላላ አነጋገር ወክየዋለሁ በሚልበት ሁኔታ ተወካዩ ከአስተዳደር ሥራዎች ውጭ የመሥራት ሥልጣን አይኖረውም ማለት ነው። ይህም የሚሆነው ተወካዩ የተወከለበት ነገር ከሚያካሂደው ሥራ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው መረዳት ባልተቻለበት ጊዜ ነው። ይህ ማለት ለተወካዩ በውክልና እንዲያከናውን የተሰጠው ተግባር በእለት ተእለት  ከሚያከናውነው የግል ተግባሩ ጋር ግንኙነት ይኑረው አይኑረው መረዳት ካልተቻለ ማለት ነው፡፡ ተወካዩ የተወከለበት ነገር ከማያካሂደው ነገር ግንኙነት ካለው ግን ተወካዩ ከአስተዳደር ሥራዎች ይልቅ ከራሱ የዕለት ስራዎች ጋር የሚገናኘውን ሥራ ነው መስራት ያለበት።  ስለዚህ ተወካዩ የሚተገብረው ሥራ ወካዩ ከወከለው ጉዳይ ጋር ያለውን ግንኙነት መረዳት ካልተቻለ ተወካዩ በተሠጠው ሥልጣን መሥራት የሚችለው የአሰተዳደር ስራዎችን ብቻ ነው የሚሆነው፡፡

እነዚህ የአሰተዳደር ሥራ ተብለው የተቀመጡት ሥራዎች ደግሞ በሚከተለው መልክ ተዘርዝረዋል (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 2204)

·         የወካዩን ሀብት የማሰቀመጥ ፣ የመጠበቅ ሥራ

·         ከሶስት አመት ለማያልፍ ዘመን የማከራየት

·         በብድር የተሰጠውን ሀብት የመሰብሰብ

·         ከሀብቱ የሚመጣውን ገቢ ተቀብሎ የማስቀመጥና

·         ለተከፈሉ ዕዳዎች ደረሰኝ የመሥጠት ሥራዎች ናቸው።

በመሆኑም በጠቅላላ ውክልና የውክልና ሥልጣን የተሰጠው ተወካይ ከላይ ከተዘረዘሩት ሥራዎች ውጭ የመሥራት ወይንም የመከወን ሥልጣን የለውም። ይህ ጉዳይ ብዙ ጊዜ በብዙ ሰዎች  ዘንድ በአግባቡ ያለመረዳት ይስተዋላል፡፡ ስሙ ጠቅላላ ውክልና ስለሚል ብቻ ለተወካይ አጠቃላይ የወካዩን ተግባሮች የመከወን ሥልጣን የሰጠው አድርጐ የመረዳት ሁኔታ አለ፡፡ ያላግባብ መረዳት ብቻም ሳይሆን ወካዬች አጠቃላይ ሥራዎችን መወከል ሲፈልጉ ጠቅላላ ወክልና ወይም ሙሉ ውክልና ብለው የውክልና ስልጣን የመስጠት ሁኔታዎች ያጋጥማሉ።ጠቅላላ ውክልና ግን እነሱ ባሰቡት መልኩ ሳይሆን ህጉ ባስቀመጠው መሠረት የአስተዳደር ስራዎችን ብቻ የሚያካትት ነው። ስለሆነም በፍ.ብ.ህ.ቁ.2204 ከተቀመጡት የአስተዳደር ሥራዎች ውጭ ያሉ ሥራዎችን ማሠራት የፈለገ ወካይ ስራዎቹን በልዩ ውክልና መሠረት ለተወካይ ማስተላለፍ አለበት ማለት ነው፡፡

ልዩ ውክልና

ልዩ ውክልና ማለት አንድ ሰው ከአስተዳደር ሥራ ውጭ ያሉ ሥራዎችን በወኪሉ ለማሠራት የሚያስችለው የውክልና አይነት ነው (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2205(1)፡፡ ስለሆነም በልዩ ውክልና የውክልና ስልጣን የተሰጠው ተወካይ ተለይተው በዝርዝር የተመለከቱ ጉዳዬችንና እንደ ጉዳዩ አይነትና እንደ ልማድ አሰራር ከጉዳዩ ጋር ተከታታይነትና ተመሣሣይነት ያላቸው ነገሮችን ማከናወን ይችላል ማለት ነው (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2206/1/)፡፡ ከዚህ ባሻገር አንድ ተወካይ ልዩ የውክልና ሥልጣን ከሌለው በስተቀር ሊፈጽማቸው የማይችላቸው ተግባራቶች በፍ/ብ/ህ/ቁ 2205(2) ስር ተዘርዝረዋል። እነሱም፡-

·         የማይንቀሳቀሱ ንብረቶችን መሸጥ ወይም አሲዞ መበደር

·         ካፒታሎችን በአንድ ማህበር ውስጥ ማስገባት

·         የሀዋላ ሰነዶችን መፈረም (sign bill of exchange)

·         መታረቅ

·         ለመታረቅ ውል መግባት

·         ስጦታ ማድረግ ወይም

·         በአንድ ጉዳይ በፍርድ ቤት ቀርቦ መከራከር ናቸው።

ስለዚህ ተወካይ ያለ ልዩ ውክልና ሥልጣን ከላይ የተዘረዘሩ ተግባራትን መፈጸም የለበትም። ነገርግን ከተሠጠው የውክልና ሥልጣን ውጭ አልፎ ተግባሮቹን ቢፈጽም የፈፀመውን ተግባር ወካዩ ካላፀደቀው ወይም በሥራ አመራር መሠረታዊ ደንብ መሰረት ካልሆነ በቀር ወካዩን አያስገድደውም ( ፍ/ብ/ህ/ቁ 2203(2)። ይህ ማለት ወካዩ ተወካዩ ከተሰጠው ስልጣን ውጭ በሰራቸው ተግባራቶች ተጠያቂ አይሆንም ማለት ነው፡፡ ከላይ በሥራ አመራር መሠረታዊ ደንብ ተብሎ የተገለፀው በፍትሃብሄር ህጉ ስለ ሥራ አመራር(unauthorized agency) ተብሎ በምዕራፍ አምስት ስር ከአንቀፅ 2257-2265 ድረስ የተጠቀሱትን አንቀፃች የሚመለከት ነው፡፡ ይህ ፅሁፍ ሰለ ስራ አመራር መሠረታዊ ደንቦች ዘርዘር ያለ ማብራሪያ ባያቀርብም እንዲሁ ግን ባጭሩ አንድ ሰው የነገሩን ሁኔታ እየተገነዘበ ይህን አንዲፈፅም ሳይገደድ፤ የወኪልነትም ሥልጣን ሣይሠጠው የሌላውን ሠው ጉዳይ በመምራት ሥራ ውሥጥ ገብቶ ጉዳዩን ያካሄደ እንደሆነ የሥራ ጉዳይ አመራር እንዳለ ይቆጠራል በማለት የፍ/ብ/ህ/ቁ 2257 ይደነግጋል፡፡  ለምሳሌ አየለ እና ሀይሉ ጎረቤቶች ናቸው እንበል፤ አየለ በሌለበት ሀይለኛ ዝናብ እየጣለ ነው፤ ወደ አየለ ቤት ጎርፍ እንዳይገባ በማሰብ ሀይሉ ለውሃ መውረጃ ከአየለ ግቢ ውስጥ ቦይ ቢያስቆፍር ሀይሉ ስራውን የሰራው አየለ ሳይወክለው ቢሆንም አንኳ የስራ ጉዳይ አመራር  እንዳለ ይቆጠራል፡፡ ነገርግን የዚህን ሁኔታ አፈፃፀም በደንብ ለመረዳትና ለመለየት ከዚሁ ሕግ አንቀጽ ቁጥር 2257-2265 ያሉትን የሕግ ድንጋጌዎች መመልከት አስፈላጊ ነው፡፡ ስለዚህ እነዚያ በተወካዩ ከስልጣን ውጭ የተደረጉ ተግባራቶች ተቀባይነት እንዲኖራቸው አንድም ከላይ በተገለጸው መልኩ በሥራ አመራር መሠረታዊ ደንብ ሥር መሆን አለባቸው ወይንም ድርጊቶቹ በወካዩ መጽደቅ ግድ ይላቸዋል ማለት ነው፡፡ ሆኖም ግን ከውክልና ስልጣን ውጭ የተደረጉ ተግባሮችን በወካይ የማፅደቅ ሁኔታ እንዳንዴ በግዴታ የሚሆንበትም ሁኔታዎች አሉ። ይህም የሚሆነው በፍ/ብ/ህ/ቁ 2207(1) እና (2)ላይ በተቀመጠው መሠረት ነው። ተወካዩ በውክልና ከተሰጠው ሥልጣንና ወካዩ ከሠጠው ትዕዛዝ ውጭ በማለፍ ሠርቶ የተገኘ ቢሆንም ስራውን የሠራው በቅንልቦና ሆኖ ሲገኝ ወካዩ ሥራውን የማጽደቅ ግዴታ አለበት(ፍ/ብ/ህ/ቁ.2207(1)። በሌላ በኩል ደግሞ ወካዩ የሥራውን አረማመድና መልካም አካሄድ ሁኔታ ቢረዳው ኖሮ ለተወካዩ የሥራውን የሥልጣን ወሰን ማስፋት የሚያስፈልግ መሆኑን መገመት ይችል ነበር ተብሎ በአዕምሮ ግምት የሚታመን ሆኖ ሲገኝም ወካዩ ከስልጣን ውጭ የተደረገውን ተግባር የማፅደቅ ግዴታ ይኖርበታል(ፍ/ብ/ህ/ቁ2207(2)። ነገርግን ተወካዩ ያለተፈቀደለትን ሥራ በገዛ አሳቡ ከመፈፀሙ አስቀድሞ የሥልጣኑን ወሠን እንዲያሰፋለት ወካዩን ለመጠየቅ የሚያስችለው ምቹ መንገድ እያለው ፈቃድ ሳይጠይቅ ቸል ብሎ በራሱ አሳብ ስራውን ሠርቶ እንደሆነ ወይም አስፈላጊ ተግባሩን ከፈፀመ በኋላ ለወካዩ ሳያስታውቀው ቀርቶ እንደሆነ ያለፈቃድ የፈፀምኩትን አጽናልኝ ወይም አጽድቅልኝ ብሎ ወካዩን የመጠየቅ መብት አይኖረውም( ፍ/ብ/ህ/ቁ 2207(3)።

የተወካይ ግዴታዎች

  1.ጥብቅ የሆነ ቅንልቦና መኖር /ቅን የመሆን ግዴታ/

ተወካዩ  ውክልናውን በመጠቀም ለወካዩ በሚሠራቸው በማንኛውም እንቅስቃሴዎች ውስጥ ለወካዩ የተሻለ ጥቅም ሲል በቅንነት ሊሠራ ይገባዋል፡፡ ተወካዩ የሚሠራቸው ድርጊቶች ሁሉ ወካዩን ተጠያቂ የሚያደርጉ ስለሆነ ተወካዩ ‘እኔ ምን ቸገረኝ እኔ አልጠየቅ፣አኔ አልጐዳ’ በሚል ስሜት ሥራውን በፍጹም መሥራት የለበትም፡፡ የራሱን ጉዳይ ሲሰራ ሊወስደው የሚችለውን ጥንቃቄና ጭንቀት ለወካዩም በሚሠራበት ጊዜ ማድረግ አለበት። የፍ/ብ/ህ/ቁ 2208(1) እንዳስቀመጠውም ተወካዩ ከወካዩ ጋር በሚያስተሳስረው ግንኙነት ውሥጥ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና ሊኖረው ይገባል፡፡ በስነ ሕግ ቅን ልቦና ማለት  በአስተያየት ወይም ግላዊ አመለካከት እውነታነት ወይም ውሸትነት ላይ ፣ወይም  በአንድ ተግባር ትክክለኛነት ወይም ህገወጥነት ላይ ያለ እዕምሯዊ ወይም ግብረ ገባዊ ቅንነት ወይም ፅኑ እምነት ነው፡፡[i]

በተጨማሪም የውክልናውን ሥልጣን የሚያስቀሩትን ምክንያቶች ወይም በውክልና ውስጥ ካሉ ነገሮች የተወሰነውን ማሻሻል አስፈላጊ የሚሆንበትን ምክንያት ለወካዩ ማሳወቅ አለበት (ፍ/ብ/ህ/ቁ.2208 (2). አንድን ሥራ ለመሥራት በውክልናው ውስጥ ያልተካተተ ነገር እያለ እንዲሁም ነገሩን ለመሥራት ያልተካተተው መካተት ያለበት እንደሆነ እያወቀ ለወካዩ ሣያሣውቀው ቀርቶ ሥራው ሳይሰራ  ቢቀር ተወካዩ ቅን ልቦና ይጐለዋል ማለት ነው። ነገር ግን ተወካይ ሊቆጣጠረው ባልቻለው ምክንያት ግዴታውን መፈፀም ሳይችል ቢቀር ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፡፡

ቅንልቦና ተወካይ እንደሚሠራቸው ሥራዎች የተለያየ ሊሆን ስለሚችል የቅንልቦና መኖሩንና አለመኖሩን ለማወቅ ተወካዩ የሚሠራቸውን ሥራዎች ባህሪ መረዳት መቻል አለብን፡፡

2.   ታማኝነት/ታማኝ የመሆን ግዴታ/

ታማኝ የመሆን ግዴታ የተወካዩን ከፍተኛ የሥነ-ምግባር ደረጃ የሚጠይቅ ነው። ተወካዩ ሥራውን በሚፈፅምበት ወቅት ሙሉ በሙሉ ለወካዩ ጥቅም ሊሠጥ በሚችልበት መንገድ ብቻ መሆን አለበት፡፡ ስለሆነም ተወካዩ ወካዩ ሣያውቅ በውክልናው በሚሠራው ሥራ አንድም ጥቅም ለግሉ ማዋል ወይም መውሰድ የለበትም/ፍ.ብ.ህ.ቁ.2209/1/። ስለዚህ ተወካዩ የወካዩን ጥቅም ሊጎዳ ወይም ሊቀንስ የሚችል ተግባር ከፈጸመና ጥቅሞችን ለግሉ ከወሰደ የታማኝነት ግዴታውን አልተወጣም ወይም ታማኝ አይደለም ማለት ነው፡፡

3.   ሚስጥር ጠባቂነት /ሚስጥር የመጠበቅ ግዴታ/

ተወካዩ ሥራውን በሚያከናውንበት ወቅት ከተለያየ አቅጣጫ የተለያየ መረጃ ሊያገኝ ይችላል፡፡ ታዲያ እነዚህን መረጃዎች መጠቀም ቢፈልግ መጠቀም ያለበት ወካዩን በማይጐዳ መልኩ ነው፡፡ መጠቀም የሌለበትም ከሆነ መጠቀም የለበትም። ይህም በፍ/ብ/ህ/ቁ 2219(2) ላይ ተወካዩ በውክልና ምክንያት ያገኛቸውን መረጃዎች የወካዩን ጥቅም በሚጐዳ ሁኔታ ሊሰራባቸው አይችልም ተብሎ ተደንግጓል፡፡ መረጃዎቹን ለሌላ ማሰተላለፍም የለበትም። ይህ የሚያሳየን ተወካዩ የሚያከናውናቸው ተግባራት ሁሉ የወካዩን ጥቅም ግምት ውስጥ ያስገቡ መሆን እንዳለባቸው ነው፡፡

 

4.   የሂሳብ አያያዝና ሂሣብ የማቅረብ ግዴታ

ይህ ግዴታ ከተወካዩ ግልፅነት ጋር የሚያያዝ ነው። ተወካይ ስራውን በሚሰራበት ወቅት ከስራው ጋር የተያያዘ ገንዘብ ነክ ጉዳዮች ሊኖሩ ይችላሉ፤ በተወካዩ የሚሰበሰብም ገንዘብ ሊኖር ይችላል። በመሆኑም ተወካይ የሚሰበስባቸው ገንዘቦች ለወካይ የማይገቡት እንኳ ቢሆኑ ተወካይ ሥራውን በሚሠራበት ወቅት ገቢ ያደረገውን ገንዘብና ትርፍ ሂሣብ መያዝ አለበት፡። የተሰበሰበውን ገንዘብም ለራሱ ጥቅም ማዋል የለበትም። ይህን ማድረግ ሲገባው ታዲያ ተወካዩ ገንዘቡን ለራሱ ጥቅም ያዋለ እንደሆነ ገንዘቡን ከወሠደበት ቀን አንሥቶ እስከነወለዱ ለወካይ እንዲከፍል ይገደዳል (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2210)። ከዚህም ባሻገር ደግሞ ተወካዩ ወካዩ በጠየቀው ጊዜ የስራውን አካሄድ መግለጫና ሂሳብ በየጊዜው የማቅረብ ግዴታ እንዳለበት የፍ/ብ/ህ/ቁ.2213/1/ ይደነግጋል።

 

5.   ታታሪነት /ትጉህ የመሆን ግዴታ/

አንድ ተወካይ ስራውን የሚሰራው ሙያዊ ብቃቱን ተጠቅሞ እንደሆነ ግልጽ ነው። በመሆኑም የወካዩን ጉዳይ ለማሥፈፀም ተወካዩ ያለውን አስፈላጊ ሙያዊ ብቃት አሟጦ መጠቀም እንዳለበት የፍትሃብሄር ህጋችን ይደነግጋል፡፡ በሌላ አነጋገር ለጉዳዬች መሳካት ተወካዩ ትኩረት መሥጠት አለበት ማለት ነው። የፍ/ብ/ህ/ቁ 2211 (1) እንዳስቀመጠው ተወካዩ በውክልና ሥራው ላይ በሚገኝባቸው ጊዜዎች ሁሉ በውክልናው የተሠጠውን አደራ አንድ መልካም የቤተሠብ አባት ቤተሰቡን ለመጠበቅ አንደሚያደርገው ሁሉ በትጋትና በጥንቃቄ መጠበቅ አለበት፡፡ ብዙ ጊዜ የተወካዩ ታታሪ የመሆን ሁኔታ ተወካይ ከወካዩ ጋር ባለው ቅርበት፣ ዝምድና ወይም በሚከፈለው ክፍያ ይወሰናል፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን ተወካዩ አሰፈላጊ የሆነ ትጋትና ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበት ህጉ ደንግጓል፡፡ በመሆኑም ተወካዩ በማታለል በሠራው ሥራ ብቻ ሣይሆን ሥራውን በሚያከናውን ጊዜ በፈፀማቸው ጥፋቶችም ተጠያቂ እንደሚሆን በፍትሃ ብሄር ህጉ አንቀፅ 2211(2) ላይ በግልፅ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን የውክልናውን ሥልጣን በነፃ (ያለክፍያ) የተቀበለ ተወካይ የወካዩን ጉዳዬች እንደራሱ ጉዳይ አድርጐ ተጠንቅቆ እስከሰራ ድረስ በተፈጠሩት ጥፋቶች ተጠያቂ አይሆንም (ፍ/ብ/ህ/ቁ. 2211(3))። እዚህ ጋርም ቢሆን ተወካዩ ለሚሠራው ሥራ ተገቢውን ጥንቃቄ ባለማድረጉ ለሚፈጠሩ ጥፋቶች ተጠያቂ መሆኑ እንዳማይቀር ነው የምንረዳው፡፡

 

6.   ስራን በራስ የመፈፀም ግዴታ/obligation to act personally/

የተወካይን ኃላፊነቶችና ግዴታዎችን ስንመለከት ሌላው መታለፍ የሌለበት ጉዳይ ውክልናን ለ3ኛ ወገን የማስተላለፍ ጉዳይ ወይም በተለምዶ የውክልና ውክልና ተብሎ የሚጠራው ጉዳይ ነው፡፡ተወካይ የተሰጠውን የውክልና ስልጣን ለሌላ ወገን ማስተላለፍ ወይንም ሌላን መወከል የሚችለው በፍ/ብ/ህ/ቁ 2215 በተቀመጠው መሰረት ብቻ ነው፡፡ ማለትም ተወካይ ውክልናውን ለሌላ ሰው ማስተላለፍ የሚችለው ወካዩ ፈቅዶለት ከሆነ ብቻ ነው። ወካዩ ካልፈቀደለት ግን የተወከለበትን ሥራ እራሱ መፈፀም እንዳለበት በህጉ በግልጽ ተቀምጧል። ይህን ሳይከተል ሌላ ሠው ተክቶ ያሠራ እንደሆነ ግን ለተሠሩት ሥራዎች በሙሉ ተጠያቂ የሚሆነው ራሱ  ብቻ ነው /የፍ/ብ/ህ/ቁ. 2216(1)፡፡ ሆኖም ተወካዩ የተሠጠውን የሥራ ጉዳይ እንዳይፈፅም የሚያግድ ድንገተኛ መሰናክል ቢገጥመውና የወካዩንም ሥራ መስራት አስፈላጊ ሆኖ ካገኘው ብሎም ሁኔታውን ለወካዩ ለማሣወቅ የማያስችል ሁኔታ ላይ ከሆነ ሥራውን ሌላ ሠው ተክቶ ማሠራት ይኖርበታል፡፡ ይህን በማድረጉም ያለወካዩ ፍቃድ ሌላ ሰው ወክለሀል ተብሎም አይጠየቅም /የፍ/ብ/ህ/ቁ. 2215(3)፡፡

 

የወካይ ግዴታዎች

1 ለተወካዩ ደሞዝ /የድካም ዋጋ/የመክፈል ግዴታ

አንድ ወካይ ለተወካይ ደሞዝ የመክፈል ግዴታ የሚኖርበት ከተወካዩ ጋር ስለድካም ዋጋ/ ደሞዝ/ተዋውለው ከነበረ ነው፡፡ ማለትም ተወካዩ ስራውን ከማከናወኑ በፊት ደሞዝ እንደሚከፈለው ተነግሮት ከነበረ ወካዩ ያን እከፍልሃለሁ ያለውን ክፍያ መክፈል ግዴታ ይሆንበታል ማለት ነው፡፡ ይህም በፍትሀብሔር  ህጉ ቁጥር 2219 ላይ በግለፅ ተቀምጧል፡፡ ነገር ግን ተወካዩ በውክልናው እንዲያከናውን የተሠጠውን ተግባር ያከናወነው በግል ሙያው ውስጥ ከሆነ ወይንም የሰራው ሥራ በልማዳዊ አሠራር መሠረት ክፍያ የሚያስፈልገው ከሆነ በውሉ ላይ ለተወካዩ ክፍያ እንደሚከፈለው ባይገለፅም እንኳን ወካይ ለተወካይ ይህን የድካም ዋጋ /ደሞዝ/ መክፈል ግዴታ ይሆንበታል፡፡ በዚህ ጊዜም የክፍያው መጠን በታወቀው የሥራ ዋጋ ልክ ወይም በልማዳዊው አሠራር መሠረት ይሆናል (ፍትሐብሄር ሕግ ቁ.2220(1)እና (2)፡፡ ከዚህ ውጭ ግን ወካይ የሥራው ጉዳይ መልካም ወይም ጥሩ ውጤት አላመጣም በሚል ምክንያት ለተወካዩ ሊከፍለው የሚገባውን ገንዘብ አልከፍልም ለማለት አይችልም፡፡ ይሁን እንጅ በተወካዩ ግዴታ ላይ እንዳየነው ተወካይ በራሱ ጥፋት በወካይ ላይ ለደረሰ ጉዳት ለወካዩ የሚከፍለው ክፍያ አለ፡፡ ታዲያ በዚህ ጊዜ ወካዩ ከተወካዩ የሚቀበለውን ገንዘብ እና  እሱ ለተወካዩ ሊከፍለው ያሰበውን ገንዘብ (የተወካይ ደሞዝንና ተወካይ ላወጣቸው ወጭዎች የሚከፈሉትን ገንዘቦች ) ማቻቻል ይችላል፡፡ ለምሣሌ ተወካዩ ላጠፋው ጥፋትለወካዩ 500 ብር መክፈል ያለበት ቢሆንና ወካዩ ለተወካዩ የሚከፍለው ገንዘብ 800 ብር ቢሆን 500 ብሩን አቻችሎ ቀሪውን 300ብር ሊሠጠው ይችላል ማለት ነው(ፍ.ብ.ህ.ቁ 2223(1) እና (2)፡፡

2.  ወጭ የመሥጠትና የማወራረድ ግዴታ

ተወካይ በውክልና ስልጣን የተሠጠውን ኃላፊነት ለመወጣት ወይንም ተግባሮቹን ለማከናወን ወጭ ማውጣት ያስፈልገው ይሆናል፡፡ ስለዚህ ወካዩ ለሥራው ማስኬጃና ማከናወኛ የሚሆን ወጭ ተወካዩ ሥራውን ከመጀመሩ በፊት ወይንም አስቀድሞ ሊሠጠው ይገባል፡፡ ከዚህ ውጭም የተሠጠውን ሥራ በጥሩ ሁኔታ ለመሥራት ሲል ተወካይ ያወጣቸውን ሌሎች ወጭዎችም ወካይ ለተወካይ መክፈል ይኖርበታል (የፍትሐብሄር ሕግ.ቁ 2221(1) እና (2))

3.  ተወካይን ከግዴታ ነፃ ማውጣት

ተወካይ በወኪልነቱ ለወካዩ ጥቅምና ለውክልናው ሥራ መልካም አካሄድ ሲል ከገባው የውል ግዴታ ወካይ ነፃ ሊያወጣው ይገባል፡፡ ይህ ማለት ተወካይ በተሠጠው የውክልና ሥልጣን መሠረት ተግባሮችን በሚያከናውንበት ወቅት ለወካዩ ጥቅምና ለውክልናው ሥራ መልካም አካሄድ ሲል የውል ግዴታ ሊገባ ይችላል ወይንም ውል ሊዋዋል ይችላል፡፡ውሎቹን ደግሞ መፈፀም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ወካይ ውሎቹን በመፈፀምም ይሁን በሌላ መንገድ ተወካይን ከነዚህ አይነት የውል ግዴታዎች ነፃ ማውጣት አለበት (የፍትሐብሄር አንቀፅ ቁ 2222 (1))፡፡

4.   ለተወካይ ኪሣራ መክፈል (የካሣ ክፍያ ግዴታ)

አንድ ተወካይ በውክልና ስልጣን መሠረት የተሠጠውን ተግባር ሲያከናውን አደጋ ሊደርስበት ይችላል፡፡ በመሆኑም ይህ የደረሰበት አደጋ የተከሠተው በራሱ ጥፋት እስካልሆነ ድረስ ወካዩ በተወካዩ ላይ ለደረሠው አደጋ ካሣ ወይንም ኪሣራ የመክፈል ግዴታ ይኖርበታል፡፡ ነገር ግን ተወካዩ በራሱ ጥፋት ለደረሰበት አደጋ ወካዩን ኪሣራ ወይንም ካሣ የመጠየቅ መብት የለውም (የፍትሐበሄር ሕግ አንቀፅ ቁ 2222 (2))፡፡

እንግዲህ ከላይ በተዘረዘረው መልኩ የወካይንና የተወካይን ግዴታዎች ለማየት ሞክረናል፡፡ ስለዚህ ውክልና ተመሥርቶ ፣ወካይና ተወካይ ግዴታቸውን አውቀው ተወካይ የተሠጠውን ኃላፊነት ይተገብራል ማለት ነው፡፡ ከዚህ በመቀጠል ደግሞ የጥቅም ግጭት (conflicting of interest) ፣ ከራስ ጋር መዋዋል (contract with oneself) ፣ የውክልና ስልጣንን አለግባብ መጠቀምንና ጊዜው ባለፈበት የውክልና ሥልጣን መገልገልን እንመለከታለን፡፡

የጥቅም ግጭት (conflicting of interest)

bወካይ ተወካይ ሂደት ውስጥ የጥቅም ግጭቶች ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ ማለት ተወካይ በተሠጠው የውክልና ሥልጣን መሠረት የወካይን መብት በማስጠበቅና የራሱን የጥቅም በማስጠበቅ መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል፡፡ የፍ/ብ/ህ/ቁ 2187(1)እንደሚያብራራው ተወካይ ከ3ኛ ወገን ጋር በፈፀመው ውል ምክንያት የወካዩና የተወካዩ ጥቀሞች የሚጋጩ የሆኑ እንደሆነና ይህን ውል የፈረመው 3ኛ ወገን ይህን ሁኔታ ያወቀና ሊያውቀውም የሚገባ የሆነ እንደሆነ በወካዩ ጥያቄ መሠረት ይህ በተወካይና በ3ኛ ወገን መካከል  የተፈፀመው ውል ሊፈርስ ይችላል፡፡ እዚህ ጋር ተወካይ ከ3ኛው ወገን ጋር የፈፀመው ውል ሲባል ተወካይ ከወካይ ባገኘው የውክልና ሥልጣን መሠረት ከ3ኛ ወገኖች ጋር የገባቸውን ውሎችን ለማመልከት ነው፡፡ ወካዩም ከላይ የተገለፀውን አይነት የጥቅም ግጭት መፈጠሩን ካወቀበት ጊዜ ጀምሮ እስከ ሁለት ዓመት ድረስ ውሉን ለማፍረስ አሳቡን ማስታወቅ እንዳለበት የፍ/ብ/ህ.ቁ 2187(2)ይደነግጋል፡፡ በዚህም መሠረት ወካዩ ውሉን የማፍረስ አሳቡን ቢያስውቅና ከተዋዋዩቹ መካከል አንዱ ማለትም ከተወካዩ ወይም ከ3ኛው ወገን አንዳቸው የወካዩን ማስታወቂያ ከተቀበለ ወዲህ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ውሉን የመቀጠል አሳቡን ቢያሳውቅና ከተዋዋዬቹ መካከል አንዱ ማለትም ከተወካዩ ወይም ከ3ኛው ወገን እንዳቸው የወካዩን ማስታወቂያ ከተቀበለ ወዲህ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ውሉን የመቀጠል አሳቡን ያልገለፁ እንደሆነ ውሉ ይፈርሳል (የፍ/ብ/ህ/ቁ 2187(3):: እዚህ ጋር ግን ሊነሣ የሚችል ነጥብ አለ፡፡ እሱም የጥቅም ግጭት መኖሩ ተረጋግጦ 3ኛው ወገንም ይህን የጥቅም ግጭት ያወቀው መሆኑ ሲረጋገጥና ወካዩ በፍ/ብ/ህ/ቁ.2187(2) መሠረት የውል መፍረስ ሃሳቡን ቢያሳውቅ  እንዲሁም በፍ/ህ/ቁ 2187(3) መሠረት 3ኛው ወገን የውሉን መቀጠል መፈለጉን ቢያሳውቅ የወካዩንና የ3ኛው ወገን ፍላጐት እንዴት እኩል ማስኬድ ይችላል የሚለው ጉዳይ ነው፡፡  በዚህ አይነት ሁኔታ ነገሩ ወደ ፍርድ ቤት ነው ማምራት ያለበት፡፡ ፍርድ ቤቱም በፍ/ብ/ህ/ቁ 2187(1) መሠረት የነገሮችን ሁኔታ አይቶ ውሉን ሊያፈርሰው ይችላል፡፡  ምክንያቱም ፍ/ህ/ቁ 2187ን ስንመለከተው የጥቅም ግጭት በሚፈጠርበት ጊዜ ውሉ መፍረስ አለበት ሳይሆን ሊፈርስ ይችላል ነው የሚለው ይህ ማለት ደግሞ ውሉ የመፍረስ ያለመፍረስም ዕድል እንዳለው ያመለክታል፡፡ ነገር ግን ተወካዩ የራሱን ጥቅም አስቀድሞ የወካዩን ጥቅም የሚጐዳ ሥራ ስለሰራ በፍ/ብ/ህ/ቁ 2209 የተጣለበትን ግዴታ አልተወጣም ማለት ነው፡፡ ስለሆነም ወካዩ ያጣቸውን ጥቅሞች በህጉ መሠረት የማግኘት መብት ይኖረዋል፡፡ ያም የሚሆነው አንድ ውል ሲፈርስ ተከትለው የሚመጡትን መብቶች መሠረት አድርጐ ነው፡፡

ከራስ ጋር መዋዋል (contract with oneself)

ከራስ ጋር መዋዋል ማለት ተወካይ ለራሱ ጉዳይ በመሥራትም ሆነ ወይም በሌላ ሰው ስም ለሌላ ሰው ጉዳይ ለመሠራት ውሉን ከራሱ ጋር ሲያደርግ ነው (ፍ/ብ/ቁ.2188 (1)፡፡ ይህ ማለት ከራስ ጋር መዋዋል በሁለት መልኩ ሊፈጠር ይችላል ማለት ነው፡፡ ይህን በምሣሌ ብናያው በቀላሉ መረዳት ይቻላል፡፡ የመጀመሪያው አንድ ወካይ ተወካዩን የሆነ ዕቃ እንዲሸጥለት ውክልና ቢሰጠውና ያን ዕቃ ተወካዩ ራሱ ቢገዛው ተወካዩ ከራሱ ጋር የሺያጭ ውል ተዋዋለ ማለት ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ አንድ ሰው ለሁለት ወካዬች ተወካይ ቢሆን ማለትም ከሁለቱም ወካዬች የውክልና ስልጣን ቢያገኝና አንድኛው ወካይ የሆነ ዕቃ እንዲሸጥለት ቢያዘው ያኛው ወካይ ደግሞ ተመሣሣይ ዕቃ እንዲገዛለት ቢያዘው ያኛው ሽጥልኝ ያለውን ለዚህኛው ወካይ ቢሸጥለት ለሁለቱም ተወካይ ራሱ ስለሆነ ውሉን ከራሱ ጋር እንደተዋለለ ይቆጠራል ማለት ነው፡፡ ስለዚህ በሁለቱም ሁኔታ ተወካይ ይህን ባደረገ ጊዜ ወካዩ ይህ ውል እንዲፈርስ ለመጠየቅ ይችላል (ፍ/ብ/ህ/ቁ 2188(1)፡፡ የወካይ ሀሳቡን የማፍረስ ጥያቄ ማሣወቅና የመፍረሱ ሁኔታ ከላይ በጥቅም ግጭት ላይ እንደተብራራው ነው የሚሆነው ወይንም በሌላ አነጋገር በፍ/ህ/ቁ.2187(2) ና (3) መሠረት ይሆናል ማለት ነው (በፍ/ህ/ቁ 2188(2))፡፡ እዚህ ጋር ለምን ተወካይ ከራሱ ጋር የተዋዋለውን ውል ፈራሽ ማድረግ አሰፈለገ የሚል ጥያቄ ይነሣ ይሆናል፡፡ ይህ ውል እንዲፈርስ የሚፈለገው ተወካይ ከራሱ ጋር ሲዋዋል የጥቅም ግጭቶች ይፈጠራሉ ተብሎ ሰለሚገመት ነው፡፡ ህጉም ይህን ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት ይመሥላል በፍትሃብሔር ሕግ ቁጥር 2188 ውስጥ ይህን ሁኔታ ያካተተው፡፡ በዚህም ሂደት ውስጥ ወካዩ ያጣቸው ጥቅሞች ወይንም የደረሠ ጉዳት ካለ በውል ሕግ መሠረት ውል መፍረስን ተከትለው የሚመጡት ወጤቶች ተፈፃሚ ይሆናሉ ማለት ነው፡፡ ይህም በህጉ መሠረት ተፈፃሚ ነው የሚሆነው፡፡  

የውክልና ስልጣንን አላግባብ መጠቀም

አንድ ተወካይ በተሰጠው የውክልና ስልጣን ሊሰራው ከሚገባው ተግባር ባሻጋር ሌላ ወካዩ እንዲሰራ የማይፈልገውን ተግባር ቢያከናውን ተወካዩ የተሰጠውን የውክልና ሥልጣን ያለአግባብ ተጠቅሟል ሊባል ይችላል፡፡ ይህ ደግሞ ተወካዩ የተጣለበትን አደራ በአግባቡ አለመወጣቱን ያሣያል፡፡ የተሰራውን ስራ በተመለከተ ደግሞ ወኪሉ ተወካዩ የፈፀመውን ተግባር ማፅደቅ ወይም ውድቅ ማድረግ ይችላል /ፍትህ ብሄር ሕግ ቁ. 2190/1/፡፡ በአጠቃላይ ግን የተሰጠውን የውክልና ስልጣን ያለአግባብ የተጠቀመ ተወካይ በፍትሃ ብሄር ሕግ ከአንቀፅ 2190-2196 በሠፈረው መልኩ የሚገዛ ይሆናል፡፡

ጊዜው ባለፈበት የውክልና ሥልጣን መገልገል

አንድ ተወካይ የተሰጠው የውክልና ስልጣን ዘመን ካበቃ በኋላ ወይንም የውክልናው ሥልጣን ከተሻረ በኋላ በውክልናው ሥልጣን የሚገለገል ከሆነ ጊዜው ባለፈበት የውክልና ሥልጣን ተገልግሏል ለማለት ያስችላል፡፡  በተሻረ የውክልናው ስልጣን አማካኝነት የተሰራውን ስራ ደግሞ ወካይ ሊያፀድቀው ወይንም ሊሽረው ይችላል/ ፍትሃብሄር ሕግ ቀ. 2190/2/፡፡ የዚህን አይነት ስህተት የፈፀመ ተወካይም ከላይ በተጠቀሱት የህጉ አንቀፆች መሰረት /ማለትም በፍትሃብሄር ሕግ ከአንቀፅ 2190-2196 በሠፈረው መልኩ/ የሚገዛ ይሆናል፡፡

ስለውክልና ሥልጣን መቅረት ወይም መቋረጥ

የውክልና ሥልጣን ከዚህ በታች በተቀመጡት ሶስት ምክንያቶች መሠረት ሊቀር ወይንም ሊቋረጥ ይችላል፡፡ እነሱም ፡-

  • የውክልናን ሥልጣን በወካዩ መሻር
  • የተወካዩ  የውክልና ሥልጣኑን መተው
  • የወካዩ ወይም የተወካዩ መሞት፣ ከአካባቢ መጥፋት፣ ለመሥራት ችሎታ (አቅም ማጣት ወይም በንግድ መክሰር፡፡

 

  • የውክልናው ሥልጣን በወካዩ መሻር

አንድ ወካይ ለተወካይ የሠጠውን የውክልና ሥልጣን በፈለገው ጊዜ መሻር እንደሚችል እንዲሁም ተወካዩ የውክልና ሥልጣኑን የተቀበለበትን የውል ፅሁፍ እንዲመልስለት ሊያስገድደው እንደሚችል የፍ.ብ.ህ. አንቀፅ 2226(1) ደንግጓል፡፡ በሌላ መልኩ ደግሞ ይህን የውክልና ሥልጣንን በፈለገ ጊዜ የመሻር መብት ሊቃረን የሚችል ቃል በውላቸው ውስጥ ቢያካትቱ ቃሉ ፈራሸ እንደሚሆን በዚሁ የሕግ አንቀፅ ንዑስ አንቀፅ (2) ላይ በገልፅ ተደንግጓል፡፡ ወካዩ የውክልና ሥልጣኑን ለመሻር ለተወካዩ ምንም አይነት በቂ ምክንያትም ማቅረብ ሆነ ቅድመ ማሥጠንቀቂያ መስጠት አይጠበቅበትም፡፡ መሻር በፈለገ ጊዜ ብቻ መሻር ይችላል፡፡ ነገር ግን የውክልናው ሥልጣን የተሠጠው በብዙ ወካዮች ከሆነ የውክልናውን ስልጣን በአንዱ ወኪል ብቻ ለመሻር በቂ ምክንያት ከሌለ በስተቀር የውክልናውን ስልጣን ለመሻር ሁሉም ወካዮች መሥማማት አለባቸው፡፡ በቂ ምክኒያት በሌለበት ሁኔታ ግን አንዱ ወካይ ብቻውን ተወካዩን ሊሽረው አይችልም /ፍ.ብ.ህ.ቁ 2228/፡፡ እንግዲህ በዚህ መልኩ የውክልና ሥልጣን ከተሻረ በውክልናው ስልጣን መሻር ምክንያት የውክልናው ሥልጣን ይቀራል ወይም ይቋረጣል ማለት ነው፡፡ ነገር ግን የውክልናው መሻር በተወካይ ላይ ጉዳት ያደረሰ እንደሆነ በ.ፍ.ብ.ህ.ቁ 2227 መሠረት ወካዩ ለተወካዩ የጉዳት ኪሣራ መክፈል አለበት፡፡

የተወካዩ የውክልና ስልጣኑን መተው

ተወካዩ የውክልና ሥልጣኑን ካልፈለገ በማንኛውም ጊዜ የውክልና ሥራውን ትቻለሁ ሲል ለወካዩ ማሳወቅ ይችላል፡፡ ለወካዩ ሣያሣውቅ ግን የውክልና ሥራውን መተው የለበትም፡፡ የተወካዩ የውክልና ሥራውን መተው በወካዩ ላይ ጉዳት የሚያደርስበት ከሆነ ተወካዩ በወካዩ ላይ ለደረሠው ጉዳት ኪሣራ መክፈል አለበት፡፡ ነገር ግን ተወካዩ የውክልናውን ሥራ መቀጠሉ በራሱ ላይ ከፍ ያለ ግምት ያለው ጉዳት የሚያደርስበት መሆኑ ከታወቀና ሥራውንም ለመቀጠል በፍፁም የማያስችል ምክንያት መኖሩ ከተረጋገጠ ስራውን በመተዉ በወካዩ ላይ ለደረሠው ጉዳት ኪሣራ ለመክፈል አይገደድም (የፍትሃ ብሄር ሕግ ቁ. 2229)

 የወካዩ ወይም የተወካዩ መሞት ፣ከአካባቢመጥፋት ፣ለሥራት ችሎታማጣት ወይም በንግድ ኪሣራ ላይ መውደቅ

ተወካይ የሞተ እንደሆነ፣ በስፍራው ያለመኖሩ የተረጋገጠ እንደሆነ፣ ለመሥራት ችሎታ ያጣ እንደሆነ ወይም ኪሣራ ደርሶበት በንግድ ኪሣራ ላይ መውደቁ የተረጋገጠ እንደሆነ የውክልና ሥልጣኑ ወዲያውኑ ይቀራል፡፡ ተወካዩ በስፍራው አለመኖሩ ተረጋገጠ የሚባለው ሰውየው ከአካባቢው እንደተሰወረ ወይንም እንደጠፋ ህጉ ላይ በተቀመጠው መሠረት ከተረጋገጠ ነው፡፡ ተወካዩ ለመሥራት ችሎታ አጣ የሚባለው ደግሞ ተወካዩ የአካል ጉዳት ደርሶበት ሥራውን መሥራት እንዳይችል ቢሆን ወይንም በሕግ ጥላ ሥር ወድቆ (ታስሮ) ስራውን መሥራት የማይችል ሲሆን ነው፡፡

ይሁን እንጅ እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ቢከሰቱም የውክልና ሥልጣኑ ቀሪ እንዳይሆን የሚገልፅ ተቃራኒ ቃል በውክልና ውሉ ውስጥ ተቀምጦ ከነበረ ይህ በተወካዩ ላይ የደረሰው ክስተት የውክልና ሥልጣኑን ቀሪ ላያደርገው ይችላል፡፡ (የ.ፍ.ብ.ህ ቁ 2230(1)፡፡

በሌላ በኩል ወካይ የሞተ እነደሆነ፣ በሥፍራው አለመኖሩ የተረጋገጠ እንደሆነ፣ ለመሥራት ችሎታ ያጣ እንደሆነ፣ወይም በንግድ መውደቅ ኪሣራ የደረሰበት እንደሆነ የውክልና ሥልጣኑ ወዲያውኑ ይቀራል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ከላይ እንደተባለው እንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች ቢከሰቱም የውክልና ሥልጣኑ ቀሪ እንዳይሆን የሚገልፅ በውክልና ውሉ ውስጥ ተቃራኒ የውል ቃል ካለ ግን በወካዩ ላይ የደረሰው ክስተት የውክልና ሥልጣኑን ቀሪ አያደርገውም /የ.ፍ.ብ.ህቁ. 2232) (1)፡፡ በዚህ ጊዜ ግን ተወካዩ ይህ ክስተት እስኪነገረው ድረስ ስራውን መቀጠል አለበት(ፍ.ብ.ህ.ቁ.2232 (2)፡፡

 

ወካይ፣ ተወካይና የውክልና ማስረጃውን የሚሰጡ አካሎች

ሊያደርጓቸው የሚገባቸው ጥንቃቄዎች

ምንም እንኳ ብዙ ሰዎች  በአንድም ሆነ በተለያየ ምክንያት ስራቸውን በውክልና ቢያሰሩም ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ተገልጋዮች ግንዛቤያቸው እጅግ በጣም ውስን መሆኑንና ውክልና ከመስጠት ሂደት ጋር ተያይዞ ብዙ ክፍተቶች እንዳሉ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡[ii] በወካዮች በኩል ያሉትን ክፍተቶች ስንመለከት ሠነድ አሟልቶ አለመገኘት፣ ለተወካይ የሚሰጡ መብቶች የሚያስከትሉትን ውጤት ቀድሞ ያለ መረዳት፣ ለተወካይ ሊሰጡ ያሰቡትን መብቶች በውል ያለ መረዳት፣ ጉዳዩን ያለማወቅ ማለትም ስለሚሰጡት ውክልና የግንዛቤ እጥረት መኖር፣ የተወካይን ሥነ-ምግባር ያለማወቅ፣ ለተወካይ የሚሠጧቸውን መብቶች በይሉኝታ ለተወካይ ሙሉ በሙሉ አሣልፎ መስጠት፣ ለተወካይ ሊሰጥ የታሰበውን የውክልና ስልጣን ማሰረጃ ሠነድ ይዘት በቸልተኝነት መመልከት (በጥንቃቄ ያለመረዳት)፣ የውክልናን ክብደት ካለመረዳት በግዴለሸነት ውክልናን በመስጠት ለአደጋ መጋለጥ ዋነኞቹ ክፍተቶች ናቸው[iii]፡፡ በመሆኑም ወካይ የሚከተሉትን የጥንቃቄ እርምጃዎችን መከተል አለበት፡

የተወካይ ማንነት እና የሥነ-ምግባር ሁኔታ ጠንቅቆ ማወቅ፤

የተወካይ የግል ባህሪና የስራ እንቅስቃሴ ሁኔታን ወካይ በውል ማወቅ ይኖርበታል፡፡ ምናልባትም ተወካይ የግል ጥቅም አገኝበታለሁ ብቻ ብሎ፤ ከዚህም ባሻገር የተወካዩን ጥቅም ለመጉዳት በማሰብም ጭምር ሊሆን ይችላል  የውክልናውን ስልጣን የሚቀበለው፡፡ የወካዩን ጥቅም ለመጉዳት አስቦ የተነሳ ወይንም ለራሱ ጥቅም ሲል ብቻ የውክልና ስልጣኑን የሚቀበል አይነት ሰው እንኳን ባይሆን በውክልና የተቀመጡትን ተግባሮች በአግባቡ ሊያከናውን የማያስችል ስነ ምግባር ወይም ተግባሮቹን ባልተፈለገ ሁኔታ ሊያከናውናቸው የሚያስችል ስነ ምግባር የተላበሰ አይነት ሰው ሊሆን ስለሚችል ጥንቃቄ መውሰድ ተገቢ ነው፡፡ ስለዚህ በተለይ ተወካዩ  ከውክልና ስልጣኑ ጋር ተያይዞ ሊኖረው የሚችለውን የተለየ ግንኙነት ወካይ በአትኩሮት በመመልከት ቅድመ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡

ወካይ ለተወካይ የሚሠጣቸውን መብቶች እና የሚያስከትሉትን ውጤት ማለትም በሕግ መነሻ የሚያስከትሉን ውጤት በሚመለከት ግንዛቤ ማዳበር፤

ማንኛውም ተግባር በሕግ መሰረት አወንታዊም ይሁን አሉታዊ ውጤቶች ይኖሩታል፡፡ በመሆኑም አንድ ተወካይ እያንዳንዱ ለተወካይ ሊሰጣቸው ያሰባቸው መብቶች ከሕግ አንፃር ምን አይነት ውጤት ሊያስከትሉ እንደሚችሉ ብሎም በራሱ ላይ ምን አይነት ተፅዕኖ ሊኖራቸው እንደሚችል አስቀድሞ ማጤንና መገንዘብ ይኖርበታል፡፡ 

ወካይ ለተወካይ የሚሠጣቸውን መብቶች መጠን ቀድሞ መለየት፤

ብዙ ጊዜ የውክልና ውል ሊዋዋሉ ወደ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት የሚያመሩ ወካዮች የውክልናውን ፎርም የሚወስዱት በጽ/ቤቱ አካባቢ ከሚገኙ የጽህፈት ስራ ከሚሰሩ የንግድ ቤቶች አንዴ ተፅፎ የተቀመጠ የውክልና ፎርምን  ነው[iv]፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ የተቀመጠው ፎርም አንድ ወካይ ለተወካይ ሊሰጣቸው የሚችሉ የውክልና ስልጣን አጠቃላይ ዝርዝር የያዘ በመሆኑ ወካይ ለተወካይ በውክልና ስልጣን ሊሰጠው ካሰበው የስልጣን ወሰን በላይ ተጨማሪ ስልጣን ከመስጠቱም በላይ ተወካይ ወደ ተግባር ሲገባ ወካይ ከሚገምተው በላይ ጉዳት በወካይ ላይ ሊያስከትልበት እንደሚችል ግልፅ ነው፡፡ ስለዚህ ወካዮች ፎርሙን ቀጥታ ከመጠቀም ይልቅ በራሳቸው ፍላጎት ማሻሻያ እንዲደረግበት በማድረግ የፈለጉትን የስልጣን ወሰን ብቻ ለተወካይ እንዲተላለፍ ማድረግ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ስነምግባር የጎደላቸውና ለግል ጥቅማቸው ብቻ የቆሙ ተወካዮች ደግሞ ማንበብ በማይችሉ ወካዮች ላይ የወካዮቹን አለማንበብ እንደጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ በውክልና ስልጣኑ ላይ የሚፈልጉት ነገር እንዲፃፍ የሚያደርጉበት ሁኔታ አለ[v]፡፡ በመሆኑም ማንበብ የማይችሉ ወካዮች እንደዚህ አይነት ክፍተቶችን ለመሙላት አንድም የኔ የሚሉት ሰው በውሉ ጊዜ አብሯቸው እንዲሆን ማድረግ ወይንም የሚያዋውለውን ባለስልጣን የውክልና ውሉን ሰነድ እንዲያነብላቸው መጠየቅ ይኖርባቸዋል፡ በአጠቃላይ በተዘጋጀው የውክልና ስልጣን ሠነድ ላይ የተካተቱ ይዘቶችን በሚገባ መረዳት፣ ማወቅ ማለትም ማንበብ ወይም ማስነበብ ግልፅ ያልሆኑ ጉዳዮች ካሉ ጠይቆ ለመረዳት መቻል ተገቢ ነው፤

ወካይ በሠጣቸው የውክልና ስልጣን እና መብቶች መነሻ የተወካይን የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ለመከታተል የሚያመች ሥርዓት በተቻለ መጠን መዘርጋት ለምሣሌ የሚሠሩ ስራዎች ሪፖርት መቀበል እና በአግባቡ ለተፈፀሙ ተግባሮች ይሁንታ መስጠት እና ማስተካከያ ለሚሹ ተገቢ ማስተካከያ እንዲያደርጉ ማድረግ፤

 

-የእለት ተእለት እንቅስቃሴን መከታተል አንድም የተከሰቱ ችግሮች ካሉ ለማወቅና ተገቢውን እርምጃ ወይንም ማስተካከያ ለመውሰድ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ሌላ ተጨማሪ ችግሮችና ክፍተቶች እንዳይፈጠሩ ቅድመ ጥንቃቄ ለመውሰድ ይረዳል፡፡ ከዚህም ባለፈ ተወካይ በማወቅም ይሁን ባለማወቅ በወካይ ላይ ጉዳት አድርሶ ከሆነ ሌላ ተጨማሪ ጉዳት ሳያደርስ ወካይ የውክልናውን ስልጣን የመሻር እርምጃ እንዲወስድ ይረዳዋል፡፡ ስለሆነም የወካይ የተወካይን አንቅስቃሴ መከታተል ብሎም ሪፖርት መቀበል ተገቢና አስፈላጊ ነው፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የሰውን ንብረት ለመውሰድ ህጋዊ ያልሆኑ ሰነዶች ወይንም (forged documents) ይዞ የመምጣት ሁኔታም ይታያል[vi]፡፡ በብዛት የተጭበረበረ ሠነድ በተለይም የሶስተኛ ወገን ሙሉ መታወቂያ፣ ካርታ /ለዚሁም አስመስለው የሚሠሩት እንዳለ ሆኖ ማለት ነው /ይዞ ሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት የመሄድ ሁኔታዎች ይከሰታሉ[vii]፡፡ ለዚህም የመንግስታዊ ተቋማት ወጥ ያልሆነ አሠራር  የችግሩ ማባባሻ እንደሆነ ይታመናል[viii]፡፡ ለምሳሌ ከቀበሌ መስተዳድሮች ከሚሠጡ መታወቂያዎች ጋር በተያያዘ በሃሠተኛ የማንንት ማረጋገጫ መታወቂያዎች ለመገልገል የሚመጡ ባለጉዳዮች አሉ[ix]፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ በሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት  በሕግ አግባብ ተረጋግጠው ያልተመዘገቡ ሀሠተኛ የውክልና ስልጣን ማስረጃዎች በመያዝ እጅ ከፍንጅ የሚያዙ ባለጉዳዮች በፈፀሙት ወንጀል አሰተማሪ እና ተመጣጣኝ ቅጣት ለማሠጠት ጽ/ቤቱ ከፖሊስ፣ ከአቃቤ ሕግ እና ከፍ/ቤቶች ጋር በቅንጅት እንደሚሰራ ለመረዳት ተችሏል፡

በተወካይ በኩል ያለውን ክፍተት ስንመለከት ደግሞ የተሠጠውን መብት ወይም ስልጣን ወካይን በሚጐዳ መልኩ ያላግባብ መጠቀም፣ አልፎ አልፎ የወካይን ጥቅም ለማስጠበቅ ቸልተኛ መሆን፣ ስለሚፈጽማቸው (ስለሚያከናውናቸው) ጉዳዬች ለወካይ ሪፖርት ያለማድረግ፣ የጥቅም ግጭት የሚያስከትሉ ጉዳዮችን በውል ያለመረዳት፣ እንደ ወካይ ሆኖ በተሠጠው መብት ስልጣን መሠረት በቂ በሆኑ ምክኒያቶች ተግባሮችን ያለመፈፀም እና ተግባሮቹ የሚያስከትሉትን ውጤት ያለ መረዳት፣ ውክልናውን ቶሎ የማግኘት ጉጉት ማሳየት እና ሠነድ ባለመሟላት ሲመለሡ እንኳ ከወካዩ ይልቅ የተወካይ ቁጡ መሆን ዋና ዋናዎቹ ናቸው[xi]፡፡ ነገር ግን በተወካይ በኩል ሀላፊነቱን የሚወስደው ወካይ ስለሆነ የሚወክለው ነገር ምን እንደሆነ ፤ ለምን እንደሚወክል እና የሚወክለውን ተወካይ ለይቶ ማወቅ ያለበት ራሡ ወካይ ነው፡፡ ስለዚህ ወካዮች ተገቢውን ጥንቃቄና ክትትል ሊያደርጉ ይገባቸዋል፡፡

ከዚህ ባሻገር ደግሞ አልፎ አልፎ በሚያዋውለው ባለስልጣን በኩል የሚታዩ ክፍተቶች ይኖራሉ፡፡ ለምሳሌ ወካይ ስለሚሠጣቸው መብቶች እና ውጤታቸው ጠንቅቆ ያውቃል በሚል እሣቤ ወካይ ስለሚሠጣቸው መብቶች እና ስለሚያስከትሉት ውጤት በበቂ ሁኔታ ያለማስረዳትና አንዳንዴ ከስራ ጫና የተነሣ ትዕግስት የማጣትና ሰነዶችን በጥንቃቄ ያለመመርመር ይታያል[xii]፡፡ ስለሆነም የሚያዋውለው ሰው ወይም ባለስልጣን በጥበብ፣ በዘዴና በትህትና መረጃዎችን፣ የባለጉዳዩን ማንነት ማጣራት ይኖርበታል፡፡ ይህን ካደረገ በኋላም በወካይና በተዋካይ መካከል የውክልና ውሉን ማዋዋል ይችላል፡፡ ከዚህ ሲያልፍ ደግሞ ጉዳዩ ትርጉም ቤቶችን( እውቅና ያለው)፣ ፍርድ ቤቶችንና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ይመለከታል፡፡ በውጭ ጉዳይ እና በፍርድ ቤት በኩል የሚጠበቀው የውክልና ማስረጃውን በትክክል አይቶ ማረጋገጥ ሲሆን በትርጉም ቤት በኩል ደግሞ ማስረጃውን በትክክል መተርጎምና ዋናውን ሠነድ ከኮፒው ጋር በአግባቡ በማናበብ የሠነዶቹን ኮፒ ማያያዝ ነው፡፡ በሌላ በኩል በአንዳንድ መስሪያ ቤቶች በኩል የሚገጥም ችግር አለ፡፡ እሱም በአንድ ውክልና ላይ ወካዩ ለተወካዩ በሰጠው የውክልና ስልጣን ማስረጃ ሰነድ ላይ “በማንኛውም መንግስታዊ መስሪያ ቤት በመቅረብ ጉዳየን ያስፈፅምልኝ ” ብሎ ገልፆ እያለ አንዳንድ መስሪያ ቤቶች የመስሪያ ቤታችን ስም በግልፁ መጠቀስ ነበረበት በሚል ተወካዩን አላስተናግድ ሲሉት ይታያሉ፡፡ ይህ ግን መሆን የሌለበት በመሆኑ መታረም አለበት፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰነዶች ማረጋገጫና ምዝገባ ጽ/ቤት ከላይ የተገለፁጽን ችግሮች ለመከላከል ብሎም ለመቆጣጠር የሚወስዳቸው እርምጃዎች አሉ፡-

§  በአዋጅ ቁ. 334/95 እና ይህን አዋጅ ለማሻሻል በወጣው አዋጅ ቁ. 467/97 መሠረት  በተሠጠው ስልጣንና ተግባሮች መሠረት የሠነዶችን ህጋዊነት አግባብ ባለው ሕግ መነሻ ማረጋገጥ፤

§  የሠነድ ፈራሚዎችን ችሎታ፣ስምምነት (ፍቃደኛነት)፣ የውሉን ይዘት እና የወካዩን የስልጣን ምንጭ ማጣራት በተለይም በውክልና ስልጣን ይዘቱ ላይ የተጠቀሠ ንብረት ካለ ስለንብረቱ እና ስለ ባለንብረቱ ሁኔታ በማረጋገጥ ለምሣሌ የባለቤትነት ማስረጃን መመርመር፤

§   የወካይን የማንነት ማረጋገጫ ህጋዊነት ብሎም ይዞ ከቀርበው ግለሰብ ጋር ማመሣከር ምስሉን ወይም መልኩን ማመሣከር;

§   በውክልና ስልጣን ማስረጃው ላይ የተጠቀሠውን የወካይ ሙሉ ስም፣አድራሻ እና ዜግነት ከግለሠቡ መታወቂያ ጋር በማመሣከር የውክልና ስልጣን ሠነድን ለወካይ በማንበብ እና ስምምነቱን ወይም ፈቃደኝነቱን በማጣራት ወዘተ የመሣሠሉት ተግባራት በቀናነት በመፈፀም የውክልናውን ውል ማዋዋል፤

§  ወካይ በነፃ ህሊናው ወዶና ፈቅዶ ውክልናውን ለመስጠት መቅረቡን በማረጋገጥ ውክልናውን ማስፈፀም፤

§  አንዳንዶች ከሀሳባቸው ውጭ የተፃፈ ይዘው ስለሚመጡ በደንብ በማስረዳት የማይፈልጉት ሀሳብ እንዲወጣ በማድረግ ውክልናውን ማስፈፀም፤

§  ሠነድን ከማስረጃዎች ጋር በጥንቃቄ ማየትና ባለጉዳዩ ምን እንደሚፈልገ በግልፅ መጠየቅ፤

§  በተቋሙም ሆነ በባለድርሻ አካላት ተከታተይ የሆነ የግንዛቤ ማስጨበጫ የሕግ ትምህርት ለህብረተሠቡ በተለያዩ ሚዲያዎች መስጠት፤

 

ማጠቃለያ

አንድ ሰው አንድ ወይንም ብዙ ህጋዊ ሥራዎችን ለማከናወን ካንድ ከሌላ ሠው ጋር የውክልና ወይንም የእንደራሴ ውል ሊገባ ይችላል፡፡ ሰዎች ከጊዜ ጥበት፣ ከቦታ ርቀት፣ ከሁኔታዎች አለመመቻቸት፣ ከእውቀት ወይንም ከክህሎት ወይንም ከችሎታ ማነስ የተነሣ ሥራዎችን በራሣቸው ከማከናወን ይልቅ ሌላን ሠው በመወከል ሊያሠሩ ይችላሉ፡፡

አንዳንዴ ውክልና ከውል  ባሻገርም ከሕግም ሊመነጭ ይችላል፡፡ የውክልና ውል በግልፅ ወይም በዝምታ ሊሠጥ ይችላል፡፡ የውክልናውም አይነት ጠቅላላ ወይንም ልዩ ውክልና ሊሆን ይችላል፡፡ በልዩም ሆነ በጠቅላላ ውክልና ውል ውስጥ ወካይና ተወካዩች የየራሳቸው ግዴታና ኃላፊነቶች አለባቸው፡፡ ጥብቅ የሆነ ቅን ልቦና፣ ታማኝነት፣ ሚስጥር ጠባቂነት፣ ሂሳብ መያዝና ሂሳብ ማቅረብ፣ ታታሪነት እንዲሁም ስራን በራስ መፈፀም የተወካይ ግዴታዎች ሲሆኑ ለተወካይ ደሞዝ መክፈል፣ ወጭ መስጠትና ማወራረድ፣ ተወካን ከግዴታ ነፃ ማውጣት፣ ለተወካይ ኪሳራ መክፈል ደግሞ የወካይ ግዴታዎች ናቸው፡፡  ወካይም ሆነ ተወካይ ግዴታዎቻቸውን መወጣት እንዳለባቸው፤ ግዴታቸውንም ካልተወጡ በህጉ አግባብ መሠረት እንደሚጠየቁ በፍ/ብ/ህ ውስጥ ያሉ የሕግ ድንጋጌዎች ያስረዳሉ፡፡ ወካይ ግዴታዎቹ ከመወጣቱ ባሻገር ለተወካይ የሠጠው የውክልና ስልጣን ውጤታማ እንዲሆን ዘንድ የሚሠጣቸውን መብቶች እና የሚያስከትሉትን ውጤቶች መገንዘብ፣ የውክልና ሥልጣኑን መጠን ቀድሞ መለየት፣ የተወካይን ማንነትና ሥነ-ምግባር ሁኔታ ጠንቅቆ ማወቅ፣ የተወካይን የዕለት ተዕለት ሁኔታ ለመከታተል የሚያስችለውን ሁኔታ መዘርጋት እንዲሁም ሌሎች ጥንቃቄዎች ማድረግ አለበት:: የውክልና ውል የሚያዋውለው ባለሥልጣን ደግሞ በተግባር በወካይና በተወካይ መካከል የውክልና ስልጣን ውል ከተመሠረተ በኃላ ሊፈጠሩ የሚችሉ ችግሮችን ከወዲሁ ለመከላከል የቅድመ ጥንቃቄ ርምጃዎችን መውሠድ አለበት፡፡ ከነዚህ ቅድመ ጥንቃቄዎች ውስጥ የሠነዶችን ህጋዊነት ማረጋገጥ፣ የተዋዋዬችን ችሎታ፣፣ስምምነት፣፣የውሉን ይዘት፣፣የወካዬች የሥልጣን ምንጭን ማጣራት እንዲሁም የወካይን ማንነት ህጋዊነት ማረጋገጥ ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

ይህ እንዳለ ሆኖ ተወካይ የተሰጠውን የውክልና ሥልጣን ያለአግባብ የሚጠቀምበት ከሆነ ወይንም በተሻረ ማለትም ጊዜው ባለፈበት የውክልና ሥልጣን የሚገለገል ከሆነ ወካዩ ተወካዩን በሕግ የሚጠይቅበት የሕግ አግባብ አለ:: በመጨረሻ ደግሞ በህጋዊ መንገድ የተመሠረተ የውክልና ውል በሶስት መንገዶች ይፈርሳል፡፡ እነሱም የውክልና ሥልጣን በወካዩ መሻር፣ የተወካዩ የውክልና ሥልጣኑን መተው፣ እንዲሁም የወካዩን ወይንም የተወካዩ መሞት ከአካባቢ መጥፋት ለመሥራት ችሎታ ማጣት ወይም በንግድ መክሰር ናቸው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

ሰበር በአዲስ አበባ ፍርድ ቤት ሥልጣን ላይ ያሰመረው ቀጭን መስመር
 አንድ አንድ ነጥቦች ስለ ቼክ እና በተግባር የሚያጋጥሙ የሕግና የአሰራር ችግሮ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Wednesday, 18 September 2024