መግቢያ
ይህ አጭር ጽሁፍ በቅርብ ጊዜ በፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት የሰበር መዝገብ ቁጥር 76248 ላይ፤ በኦሮሚያ ጠቅላይና በአዳማ ልዮ ዞን ከፍተኛ ፍርድ ቤቶች መሰረታዊ የሕግ ስህተት ተሰርቷል ማለት አይቻልም በሚል፤ በሶስት ዳኞች ጥቅምት 6 2005 የተዘጋን ጉዳይ መሰረት አደርጎ የቀረበ ነዉ፡፡ የምንዳስሰዉ ጥያቄ በጽሁፉ ርእስ ላይ የተመለከተዉን ነዉ፤ ያለዉክልና የሌላን ሰዉ እዳ መክፈል ይርጋን ያቋርጣል? ለጽሁፉ አላማ የተከራካሪ ወገኖችን ስም መጥቀስ አስፈላጊ ስላልሆነ አበዳሪ፤ ከሳሽ፤ ተበዳሪ፤ እና የተበዳሪ ልጅ የሚሉትን እንጠቀማለን፡፡ በአጭሩ ፍርድ ቤቶቹ የወሰኑት ባለእዳዉ ሳይሆን ሌላ ሰዉ (የጽሁፍ ዉክልና ሳይሰጠዉ በፊት) በባለእዳዉ ስም ያደረገዉ የእዳ አከፋፈል እንዳልተደረገ ስለሚቆጠር ይርጋን አያቋርጥም በማለት ወስነዋል፡፡
የጉዳዩ መነሻ
ተበዳሪዋ ከኢትዮጲያ ንግድ ባንክ አዳማ ቅርንጫፍ ለንግድ ማስፋፊያ በሚልና ንብረት በማስያዝ በየወሩ ተከፍሎ በአንድ አመት ዉስጥ የሚያልቅ ብድር ወስደዋል፡፡ ነገር ግን አንድም ወር የተስማሙትን ወርሀዊ ክፍያ ሳይፈጽሙ በብድር ዉሉ ላይ የተጠቀሰዉ የእዳ መክፈያ ጊዜ ያልፋል፡፡ የብድር ዉሉ የተፈረመዉ በ25/11/1987 ሲሆን በ24/11/1988 ተከፍሎ ማለቅ ነበረበት፡፡ የተበዳሪዋ ልጅ የመጀመሪያዉን የ28000 ብር ክፍያ በተበዳሪዋ ስም የፈጸሙት በ24/11/1989 ነበር፡፡ ከዛ በመቀጠል በ15/8/1994 በዚሁ ልጅ በተዳሪዋ ስም የ2000 ብር ክፍያ ተፈጽሟል፡፡ ክሱ በቀረበበት ወቅት ከመጀመያዉ ክፍያ ጀምሮ ሲሰላ ከአስር አመት በላይ አልፎታል፡፡ ነገር ግን ከሁለተኛዉ ክፍያ ጀምሮ ከተሰላ አስር አመት አልሞላም፡፡
ተበዳሪዋ ለቀረበባቸዉ ክስ የይርጋ መቃወሚያ አንስተዋል፤ ክሱ በአስር አመት የይርጋ ጊዜ ዉስጥ ስላልቀረበ ይታገዳል በሚል፡፡ ሁለተኛዉን ክፍያ በተመለከተ፤ አልከፈልኩም በክፍያ ሰነዱም ላይ ያለዉ ፊርማ የኔ ፊርማ አይደለም ብለዋል፡፡ ይህንን እኔ ያልከፈልኩትን የሁለተኛ ክፍያ ሰነድ ያቀረበዉ ከሳሽ በይርጋ ቀሪ የሆነዉን የብድር ገንዘብ በፍርድ ቤት ክስ መስርቶ ለማስመለስ እንዲያመቸዉ ነዉ የሚል ነዉ፡፡