Font size: +
6 minutes reading time (1117 words)

የኤቲኤም ካርድ በጠፋ ጊዜ የባንክ ኃላፊነት

በዘመናዊ የባንክ አገልግሎት ክፍያን ከሚያሳልጡ አሠራሮች መካከል አንዱ የኤቲኤም ካርድ አገልግሎት ነው፡፡ አንድ የባንክ ደንበኛ በባንኩ ውስጥ በከፈተው ሒሳብ ያጠራቀመውን ገንዘብ ለማውጣት የቁጠባ ሒሳብ ደብተሩን መያዝ፣ የባንክ ባለሙያን ማነጋገር፣ ገንዘብ ወጪ ለማድረግ የሚያስችል ፎርም መሙላት፣ ወረፋ መጠበቅ ወዘተ. አይጠበቅበትም፡፡ በደንበኛውና በባንኩ መካከል በሚፈጸም የኤቲኤም ካርድ አገልግሎት ውል ከባንኩ ካርዱንና የሚስጥር ቁጥሩን በመቀበል ባንኩ በተለያዩ ቦታዎች ካስቀመጣቸው የኤቲኤም ማሽኖች አገልግሎት ማግኘት ይችላል፡፡ በአገራችን ይህ አሠራር በተግባር ላይ ከዋለ የተወሰኑ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን፣ በጣም ውሱን ከሆኑ ጀማሪ ባንኮች በስተቀር በሁሉም የግልና የመንግሥት ባንኮች ተፈጻሚ ሆኗል፡፡ የኤቲኤም ካርድን መጠቀም የራሱ የሆኑ ጥቅሞች እንዳሉት የታመነ ቢሆንም፣ የተወሰኑ በአጠቃቀም ወቅት የሚስተዋሉ ችግሮች እንዳሉ ብዙ ሰው የሚያውቀው ነው፡፡ የኤቲኤም ካርድ በአንዳንድ ማሽኖች ተቀባይነት አለማግኘቱ፣ አንዳንዶቹ ፈጽሞ የማይሠሩ (Active ያልሆኑ) መሆናቸው፣ በአንድ ቀን ማውጣት የሚቻለው የገንዘብ መጠን መወሰኑ፣ የኔትወርክ አለመኖርና ተደጋጋሚ የማሽን ብልሽት፣ በቂ የክፍያ ማሽኖች በየቦታው አለመኖራቸው፣ በኤቲኤም አሠራር የሚታዩ ግድፈቶች ወዲያው ሊታረሙ አለመቻላቸው ተጠቃሽ ችግሮች ናቸው፡፡ በዚህ ጽሑፍ የምንመለከተው ግን ከባንኩ ውጭ በሆኑ ምክንያቶች በኤቲኤም ካርድ አገልግሎት ላይ ከተጋረጡ ችግሮች ዐቢይ የሆነውን የካርድ መጥፋት ጉዳይ ነው፡፡

በባንኮችና በደንበኞቻቸው መካከል የሚፈረም የኤቲኤም ካርድ አገልግሎት ውል ደንበኞች ካርዳቸውን ወይም የሚስጥር ቁጥራቸውን ለሦስተኛ ወገን አሳልፈው እንዳይሰጡ፣ ካርዳቸውን እንዳይጥሉ፤ ይህ ካልሆነ ግን ካርድ በመጥፋቱ፣ ወደ ሦስተኛ ወገን በመተላለፉ ወይም የሚስጥር ቁጥሩ በመገለጡ ምክንያት ለሚመጣው ጉዳት ደንበኞቹ ኃላፊ ሊሆኑ እንደሚገባ ነው፡፡ የኤቲኤም ካርድ በጠፋ ጊዜም ግን ባንኮች ኃላፊነት ሊኖርባቸው የሚችልበት ሁኔታ ዝግ አይደለም፡፡ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ሰበር ሰሚ ችሎት በ17ኛ ቮልዩም አስገዳጅ የሕግ ትርጓሜ ከሰጠባቸው ጉዳዮች ውስጥ የሰበር መዝገብ ቁጥር 96309 አንዱ ሲሆን፣ በዚህ ጽሑፍ ይህን አስተማሪ ፍርድ መነሻ በማድረግ አጠር ያለ ዳሰሳ ለማቅረብ እንሞክራለን፡፡

የጉዳዩ አመጣጥ

ጉዳዩ የጀመረው በፌዴራል መጀመሪያ ፍርድ ቤት ሲሆን፣ ከሳሽ አቶ ዓለማየሁ ግርማ ተከሳሽ ደግሞ ዳሸን ባንክ ነው፡፡ ደንበኛው በባንኩ የቁጠባ ሒሳብ ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ የቁጠባ ሒሳባቸውን በኤቲኤም ካርድ ያንቀሳቅሳሉ፡፡ ጥር 23 ቀን 2003 ዓ.ም. የደንበኛው የኤቲኤም ካርድ ይጠፋል፤ ደንበኛውም መጥፋቱን ጥር 25 ቀን 2003 ዓ.ም. በጽሑፍ ለባንኩ ያሳውቃሉ፡፡ ይሁን እንጂ ባንኩ የኤቲኤም ሒሳባቸውን ባለመዝጋቱ ሪፖርት ከተደረገበት ቀን ጀምሮ እስከ የካቲት 9 ቀን 2003 ዓ.ም. ባንኩ ለማይታወቁ ሦስተኛ ወገኖች ብር 40,300 በኤቲኤም ክፍያ ይፈጽማል፡፡ በዚህ ጊዜ ነው ደንበኛው ባንኩ ሒሳቤን መዝጋት ሲገባው ባለመዝጋቱ ያለፈቃዳቸው ወጪ ለተደረገው ገንዘብ ወለድና ወጪ ባንኩ ኃላፊ እንዲሆን ክስ ያቀረቡት፡፡

ባንኩ በበኩሉ በሰጠው መልስ ካርዱ የጠፋ መሆኑንና ደንበኛውም በጽሑፍ ማሳወቃቸውን አልካደም፡፡ የባንኩ መከራከሪያ በባንኩ አሠራር መሠረት ደንበኛው ሒሳቡ እንዲዘጋ የመጠየቅ ግዴታ አለባቸው፡፡ እንደ ባንኩ አመለካከት በግራ ቀኙ ባለው ውል መሠረት ደንበኛው የሚስጥር ቁጥሩን ለሌላ ወገን እንዳያሳውቁ ግዴታ ያለባቸው ሲሆን፣ የሚስጥር ቁጥሩ ካልታወቀ ገንዘብ ወጪ ሊሆን አይችልም፤ በተጨማሪም የሒሳብ ይዘጋልኝ ጥያቄ ባልቀረበበት ሁኔታ ተከሳሽ የደንበኛውን ሒሳብ ሊዘጋ ስለማይችል ተጠያቂ ልሆን አይገባም ሲል ተከራክሯል፡፡

ጉዳዩን በቅድሚያ የተመለከተው ፍርድ ቤት የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ ከሳሽና ተከሳሽ በገቡት የካርድ ክፍያ አገልግሎት ውል አንቀጽ 2(2) መሠረት ካርዱ መጥፋቱን በጽሑፍ ከማሳወቁ በፊት ለተደረገ ማንኛውም የክፍያ ትዕዛዝ ባለካርዱ ኃላፊነት እንዳለበት የሚያመለክት በመሆኑና የዚህ የውል ክፍል ተቃርኖ ትርጉም ባለካርዱ በጽሑፍ ካሳወቀ በኋላ በተደረገ የክፍያ ትዕዛዝ ባንኩ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን የሚያስገነዝብ በመሆኑ፣ የውሉ ድንጋጌዎች የመብትና ግዴታ ዝርዝር ውስጥ ኃላፊነት ለመውሰድ ባለካርዱ ሒሳብ እንዲዘጋለት ማመልከት እንዳለበት ያልተካተተ በመሆኑ ከሳሽ ካርዱ መጥፋቱን ለባንኩ ባሳወቁበት ዕለት ባንኩ ባዘጋጀው ፎርም ላይ የሚስጥር ቁጥሩን መጻፉ የታመነ በመሆኑ የካርዱን የሚስጥር ቁጥር የተከሳሽ ሠራተኞች በቀላሉ የማያውቁበት ምክንያት ባለመኖሩ የተከሳሽ ባንክ መከራከሪያ ተቀባይነት የለውም፡፡ በመሆኑም ፍርድ ቤቱ የክሱን ገንዘብ ከነወለዱ ባንኩ እንዲከፍል ሲል ፍርድ ሰጥቷል፡፡

የይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤትም ግራ ቀኙን ካከራከረና ተጨማሪ የሙያ ምስክሮችን ከሰማ በኋላ የሥር ፍርድ ቤቱን ውሳኔ አጽንቷል፡፡

ባንኩ ቅሬታውን ለሰበር ችሎት ቢያቀርብም ሰበር ከሥር ፍርድ ቤቶች ጋር ተመሳሳይ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ እንደ ሰበር ችሎቱ ትንታኔ ደንበኛው ካርዱ መጥፋቱን ካሳወቀ በኋላ የሒሳብ ይዘጋልኝ ጥያቄ አላቀረቡም በሚል ከኃላፊነት መዳን ስለመቻሉ በግራ ቀኙ ውል ካለመመልከቱም በላይ ደንበኛው በባንኩ ፎርም ላይ የሚስጥር ቁጥሩን ከሞላ በኋላ ሚስጥርነቱ ስለሚቀር ተገቢ ያልሆነ ተግባር እንዳይፈጸምበት በባንኩ በኩል ስለተደረገው ጥንቃቄ በባንኩ በኩል የቀረበ ክርክርም ሆነ ማስረጃ ባለመኖሩ ባንኩ ኃላፊ ነው ሲል ፍርድ ሰጥቷል፡፡

በፍርዱ ላይ የተደረገ ምልከታ

በዚህ ፍርድ የታየው የባንክ ጉዳይ የኤቲኤም ካርድ አጠቃቀምን የተመለከተ ሲሆን፣ በሕግ ዕይታ የግንኙነቱ ምንጭ የውል ግዴታ ነው፡፡ በባንኩና በደንበኛው መካከል የቀደመ የቁጠባ ሒሳብ የውል ግንኙነት ያለ ሲሆን፣ ይህ ግንኙነት በንግድ ሕጋችን በግልጽ እንደተደነገገው የአደራ ውል ግንኙነት ነው፡፡ ደንበኛው ባንኩን አምኖ ገንዘቡን በቁጠባ ሒሳብ መልክ ሲያጠራቅም ባንኩ ከሕጉ እንደተመለከተው እንደ መልካም አደራ ተቀባይ ደንበኛው ገንዘቡን በፈለገው ጊዜ የማውጣት መብትን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ በደንበኛውና በባንኩ መካከል የኤቲኤም ካርድ አጠቃቀምን በተመለከተ ያለው ውል የዚህ ውል ተቀጽላ ሲሆን፣ ደንበኛው በቁጠባ ሒሳብ ግንኙነት ያገኘውን መብት የተሻለ እንዲጠቀም ለማስቻል ያለመ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የኤቲኤም ግንኙነቱ በባንኩና በደንበኛው መካከል ከተገባው የኤቲኤም አገልግሎት ውል በተጨማሪ ባንኩ ለደንበኛው የአደራ ሰጪ ግዴታ አለበት፡፡

ደንበኛው ኤቲኤምን በተመለከተ ካርዱንና ሚስጥር ቁጥሩን የመጠበቅ ግዴታ አለበት፡፡ ይህን ግዴታውን ሳይወጣ ቀርቶ በኤቲኤሙ ከእሱ ውጭ ያሉ ሦስተኛ ወገኖች ገንዘብ ከሒሳቡ ካወጡበት ኃላፊነቱ የራሱ የደንበኛው ነው፡፡ ካርዱ ከጠፋና ለባንኩም በአንድም በሌላ መልኩ ካላሳወቀ ባንኩ ኃላፊነት አይኖርበትም፡፡ ባንኩ ኃላፊነት የማይኖርበት ደንበኛው የኤቲኤም ካርዱ ጠፍቶበት ካላሳወቀው ወይም ቢያሳውቀውም ከጠፋበት ጊዜ እስከ አሳወቀበት ጊዜ ለሦስተኛ ወገን ለወጣ ገንዘብ ነው፡፡ በተያዘው ጉዳይ ደንበኛው ካርዱ በጠፋበት በሁለተኛው ቀን ለባንኩ ያሳወቀ ሲሆን፣ ሦስተኛ ወገኖች ገንዘቡን አወጡ የተባለውም ደንበኛው ካሳወቀው በኋላ በመሆኑ ኃላፊነቱ የባንኩ ነው፡፡ ደንበኛው ለባንኩ ካርድ መጥፋቱን ያሳወቀበት ዓላማ ሌላ ምንም ሳይሆን ባንኩ ደንበኛው የካርዱ ባለቤት መሆኑ ማቆሙን ተረድቶ ጥበቃ እንዲያደርግለት ነው፡፡ ይህ ካልሆነ በማስታወቅና ባለማሳወቅ መካከል ያለው ልዩነት ትርጉም አይኖረውም፡፡ በቁጠባ ሒሳብ የአደራ ተቀባይ ግዴታ ላለበት ባንክማ ከዚህም የከበደ የጥንቃቄና የጥበቃ ግዴታን ሕጉ ይጥላል፡፡ ሪፖርት ከተደረገበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ የደንበኛቸውን ኤቲኤም እንዳይሠራ በማድረግ (Void በማድረግ)፣ ደንበኛው በቁጠባ ሒሳብ ደብተሩ ብቻ እንዲጠቀም፤ ከተቻለም አማራጭ ምትክ ሌላ ካርድ በመስጠት ከባለ አደራ አስቀማጭ የሚጠበቀውን ግዴታ መወጣት ነበረበት፡፡ ዳሽን ባንክ ይህን አለማድረጉ ደንበኛው በሦስተኛ ወገኖች ጉዳት እንዲደርስበት ምክንያት ሆኗል፡፡ ከሥር ፍርድ ቤቶች የፍሬ ነገር ክርክር ለመረዳት እንደቻልነውም የባንኩ ፎርም የደንበኛውን የሚስጥር ቁጥር የሚገልጥ በመሆኑ ሦስተኛ ወገኑ በባንኩ ክፍተት ለመጠቀሙ ከፍ ያለ ግምት መውሰድ ይቻላል፡፡ የሥር ፍርድ ቤቶችና የሰበር ችሎቱም በግራ ቀኙ መካከል ያለው የኤቲኤም አገልግሎት ውሉ ደንበኛው ካርዱ መጥፋቱን ማሳወቅ እንጂ የሒሳብ ይዘጋልኝ ጥያቄ እንዲያቀርብ ቅድመ ሁኔታ አለማስቀመጡ የባንኩን ክርክር ውኃ የማይቋጥር አድርጎታል፡፡ ከዚህ አንፃር የፍርድ ቤቶቹ አቋም ሕጉን የተከተለና ፍትኃዊ ነው፡፡ የሚደንቀው የባንኩ ክርክር እንዲያውም ደንበኛው ‹‹ሒሳብ ይዘጋልኝ›› ብሎ እንዲጠይቅ የመጠበቁ ጉዳይ ነው፡፡ የቁጠባ ድርቅ ለሚመታቸው የግል ባንኮቹ ደንኞች የኤቲኤም ካርድ በጠፋባቸው ቁጥር ሒሳብ እንዲዘጉ የመጠየቃቸው ነገር ገራሚ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ባንኩ የቀረበበትን ትንሽ ገንዘብ ቢከፍል ኖሮ የሕዝብ ሰነድ በሆነው ፍርድ ገመናው ባልተገለጠ ነበር፡፡ ባንኩ የደንበኛውን አቤቱታ በመቀበል ውስጡን ቢመለከት፣ ኢንስፔክሽን ቢያደርግ ደንበኛው ለባንኩ ካሳወቀበት ፎርም የተገኘውን የሚስጥር ቁልፍ በመጠቀም ክፍተቱን የራሱ ሠራተኞች ስለመጠቀማቸው መረጃ ማግኘት በቻለ ነበር፡፡ ውስጥን ሳይመለከቱ ወደውጭ የጥፋት ምንጭን መመልከት ባንኮች ደንበኞችን እንዲያጡ፤ ያሉትም ደንበኞች በባንኩ አሠራር መተማመናቸው እንዲቀንስ ያደርጋል፡፡ 

ለማጠቃለል እንሞክር፡፡ የሰበር ፍርዱ አስተማሪና ፍትኃዊ ነው፡፡ አስተማሪነቱ ባንኮች የደንበኞቻቸውን ሕጋዊ ጥያቄ ባለማስተናገድ መልካም ስማቸውን እንዳያጡ መጠንቀቅ እንደሚገባቸው ያሳያል፡፡ የቀረበ ክስ ሁሉ መልስ ላይፈልግ ይችላል፡፡ አምኖ ኃላፊነትን መቀበል ብልህነት ነው፡፡ ፍትኃዊነቱ መብትን ለመጠየቅ የገንዘብ መጠን ትንሽነት ሳያዘናጋቸው እስከ ሰበር ለሄዱ ደንበኞች ፍትሕ በአደባባይ ለመገለጧ ምስክር ነው፡፡ ባንኮች የኤቲኤም አገልግሎትን ሲሰጡ ደንበኞቻቸው ሒሳባቸውን ለማንቀሳቀስ (ለማውጣት፣ ለማስተላለፍ፣ ሚዛን ለመጠየቅ) እንዲመቻቸው በመሆኑ ተቀጽላ ግዴታ መሆኑ ሊዘነጋ አይገባም፡፡ ዋናው ግዴታ የቁጠባ ሒሳብ ሲከፈት የተጀመረ በመሆኑ ባንኮቹ ባለአደራ መሆናቸውን መዘንጋት የለባቸውም፡፡ ባንኩ ደንበኞቻቸው ካርዱ እንደጠፋ ካሳወቁላቸው ገንዘባቸው በሦስተኛ ወገን እንዳይዘረፍ የተለመደውን የባንክ አሠራር በመጠቀም መብታቸውን ሊጠብቁላቸው ይገባል፡፡ የውልም ሆነ የሕግም መሠረት በሌለበት ሁኔታ የካርድ መጥፋት ሪፖርት ተደርጎላቸውም ሒሳብ እንዲዘጋ የሚጠይቁ ከሆነ ባንክ መሆናቸውን መዘንጋታቸው ለሁሉም የታወቀ ነው፡፡

×
Stay Informed

When you subscribe to the blog, we will send you an e-mail when there are new updates on the site so you wouldn't miss them.

በኮንስትራክሽን ውሎች አፈጻጸም ወቅት የመሀንዲሱ ሚና እና የጥቅም ግጭት
የቴምብር ቀረጥ የሚከፈልባቸውና የማይከፈልባቸው ግብይቶች

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Abebe
Saturday, 14 December 2024